አንድ ብልህ ንጉስ በከተማው ውስጥ ሦስት አዋቂዎች ነን እያሉ ህዝቡን ይመክራሉ፤ ያወናብዳሉ የሚባሉ ሰዎችን በተራ በተራ ጠርቶ ጥያቄዎችን ይጠይቃቸዋል፡፡
የመጀመሪያው አዋቂ እንደገባ እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፡-
“ህዝቡ ይውረድ ይውረድ እያለ እያስቸገረኝ ነው፡፡ እኔ ግን በስልጣን ላይ መቆየት እፈልጋለሁ፡፡ ምን ባደርግ ይሻላል?”
አንደኛው አዋቂም፤
“ንጉስ ሆይ፤ እርሶን የመሰለ ደግ ንጉስ ይውረድ ያለ ህዝብ ከእንግዲህ ሊታመን አይገባውም፡፡ ይልቁንም ሊቀጣ ይገባዋል፤ ስለዚህ ለመቀጣጫ ከህዝቡ መካከል ቀንደኛ የሚባሉትን አንድ ሦስቱን በአደባባይ ይቅጧቸው፡፡ ያኔ ሰጥ ለጥ ብሎ ይገዛል” ሲል መለሰ፡፡
ሁለተኛውን አዋቂ አስጠርቶ፤
“ህዝቡ ያላንተ መኖር አንችልም፤ ለዘላለም ቆይልን እያለ አስቸገረኝ፡፡ እኔ ግን ስልጣኔን ማስረከብ እፈልጋለሁ፡፡ ህዝቡ ኑርልን የሚለኝ እውነቱን ይሁን ውሸቱን ለማወቅ ተቸግሬያለሁ፤ ምን ትመክረኛለህ?”
ሁለተኛው አዋቂም፤
“ንጉስ ሆይ፤ ይህን ህዝብ አይመኑት፤ ይኑሩልን ሲል ይሙቱ ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማወቅ ቀንደኛ የሚባሉትን አንድ ሦስቱን አስጠርተው በአደባባይ ቢቀጡ ማታለሉን ትቶ ሰጥ ለጥ ብሎ ይገዛል” አለ፡፡
በመጨረሻም ሦስተኛውን አዋቂ አስጠርቶ፤
“ህዝቤ ይውረድም አይለኝም፡፡ ይኑርም አይለኝም፡፡ ዝም ብሎ እየተገዛ ነው፡፡ የልቡን ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ ምን ባደርግ ይሻለኛል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ሦስተኛው አዋቂም፤
“ይህን ህዝብ አይመኑት፡፡ ይኸኔ ሴራ እየጎነጎነ ነው፡፡ ስለዚህ የህዝቡ ተጠሪ ናቸው የሚባሉትን ሽማግሌዎች አስጠርተው ሸንጎ ፊት ቢያስገርፏቸው የተዶለተችው በሙሉ ትጋለጣለች፡፡”
ከዚህ በኋላ ንጉሱ ህዝቡ እንዲጠራ አዋጅ አስነገረና፤ ህዝብ ሲሰበሰብ እንዲህ አለ፤
“እነዚህን ሦስት አዋቂዎች አስጠርቼ ህዝቡ ይጠላኛል ወይ? ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ህዝቡ ይወደኛል ወይ? ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ህዝቡ መውደዱንም መጥላቱንም አልነግር አለኝ ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ምን ታስባላችሁ?” ሲል ጠየቀ፡፡
ህዝቡም መክሮ ሲያበቃ በተወካዩ በኩል መልስ ሰጠ፡፡ ተወካዩ የአገር ሽማግሌ፤
“ንጉስ ሆይ፤ ከህዝቡ ጋር ስንመክር አንድ እልባት ላይ ደረስን፡፡ እነዚህ ሦስት አዋቂዎች በተለያየ ጊዜ ስለ እርሶ ጠይቀናቸው የመለሱልን መልስ ’ንጉሱን አትመኗቸው’ የሚል ነበር፡፡ ስለዚህም በወዲህም ወገን በወዲያም ወገን፤ መተማመን እንዲጠፋ አድርገዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሊቀጡልን ይገባል” አሉ፡፡
ንጉሱም፤
“እናንተ ባላችሁት እስማማለሁ፤ ስለሆነም ቅጣታቸውን ይቀበላሉ፡፡ ያም ሆኖ ለእናንተ አንድ ምክር ልምከራችሁ፡፡ ሁልጊዜ ተነጋገሩ፡፡ ተመካከሩ፡፡ ግልፅ ሁኑ፡፡ ጥፋት ስታገኙ ጥፋተኛውን ቅጡ፤ ንጉስ ያልፋል መንግስት ይለወጣል፤ ሁሌም ነዋሪው ህዝብ ነው” ሲል ነገራቸው፡፡
***
ብልህ ንጉስ ማግኘት መታደል ነው፡፡ የአገር አዋቂዎች ማጣት መረገም ነው፡፡ የሚመካከር ህዝብ መላ ያገኛል፡፡ ችግሩን የማይፈታ ህዝብ በሽታውን እንደደበቀ ህመምተኛ ነው፡፡ ግልፅነት ሲኖር እውነት ወደ አደባባይ ትወጣለች፡፡ ግልፅነት ከመሪዎችም፣ ከምሁራንም፣ ከህዝብም የሚጠበቅ ፍቱን ወርቅ ነው፡፡ ግልፅነት ከአንድ ወገን ብቻ የሚጠበቅ ከሆነ ሌላውን ወገን መሸፈኛ፣ የተንኮል ጭምብል ይሆናል እና ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ግልፅነት አለቃ ምንዝሩ የሚተችበት መሳሪያ ብቻ ተደርጎ አንዱን ንፁህ፣ አንዱን አዳፋ፣ አንዱን ቀና፣ ሌላውን ጎልዳፋ ብሎ ለመፈረጅ፤ መጠቀሚያ መሆን የለበትም፡፡ ግልፅነት ሁሉም ላይ የሚሰራ፣ ለሁሉም የሚያገለግል መርህ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡
ግልፅነት ከብልጥነት መለየት አለበት፡፡ ግልፅ ነኝ ማለት ድብቅነትን መሸፋፈኛ እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ አዋቂ ሳይሆኑ የወቅቱን መፈክር በማንበብ ብቻ አዋቂ ለመምሰል መሞከር ግልፅነት አይደለም፡፡ ከስህተት ሳይማሩ ከስህተት የተማሩ ለመምሰል መሞከር ግልፅነት ከቶ አይደለም፡፡ በአፍ ቅቤ፣ በልብ ጩቤ ይዞ መቅረብ ግልፅነት አይደለም፡፡ “ብቅል ለመበደር የምትሄድ ብቅል ያላስቀመጠችውን ምን ሴት ትባላለች! ትላለች” እንዲሉ፤ አንዱ ካንዱ ላይሻል ነገር፣ ጥፋተኛ እራሱን እንከን-የለሽ አድርጎ ሌላውን ጥፋተኛ ሲወቅስ፤ ያኛውን አጋልጦ እራሱን ሸሽጓል እና ግልፅነት እሱ ዘንድ የለም፡፡ የግልፅነት ስርአት ሁሉን-አቀፍ ሊሆን ይገባል፡፡ ከእሙናዊው ተግባር የፈለቀ መሆን አለበት፡፡ ግልፅነት ከሁሉ አስቀድሞ እውነተኝነት መጠየቁ ለዚህ ነው፡፡
የአስተዳደግ ጉድለት፤ የአስተዳደር ጉድለትን ያስከትላል፡፡ እራሱ በወጉ ሀላፊነት ያልተረከበ፣ እራሱ እድገቱን ያላግባብ የወሰደ፤ እራሱ ሹመቱን በኢርትኡ መንገድ የነጠቀ ሰው ስርአት ያለው አስተዳደር ለማስፈን ይቸግረዋል፡፡ ይልቁንም “ብልጥ ሌባ የቆጮ መቁረጫ ትሰርቃለች” እንደሚባለው፤ ከቆጮውም ይልቅ መቁረጫውን ይዟልና ህግ አውጭውም፣ ፈራጅም፣ ገምጋሚም አስገምጋሚም፣ ሰብሳቢም፣ መራጭም፣ ሆኖ ሁሉን ከእፍታው ይጨልፋል፡፡ ጠያቂ የለበትምና ልቡም እጁም አያርፍም፡፡ ሙስናን ለማስፋፋት ቅርብ ሆነ ማለት ነው፡፡ የአገርና የግለሰብን ጥቅም ያደበላልቃል፡፡ የተማረረን ከተማረ በላይ ያደርጋል፤ ባለሙያነትንና ባለእውቀትነትን ከአፋዊ ችሎታ በታች ያያል፡፡ ይህን መሳይ ድርጊት ሁሉ የመልካም አስተዳደር አለመምጣት መርዶ ነው፡፡ ያ በፈንታው የዲሞክራሲን በር ይዘጋል፡፡ የሰላምን ውጋጋን ይጋርዳል፤ የፍትህን ሚዛን ይነጥቃል፡፡
በተለይ እጅግ ወቅታዊ የሆኑትን፤ የሀገርም ሆነ የአገርና አገር ጥያቄዎችና ችግሮች በዲሞክራሲያዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት፤ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ አፍጦ የመጣበት ሰአት ነው፡፡ የችግር ቅደም-ተከተልን ጥያቄ (prioritization) ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ሁኔታና ከተጎራባች አገሮቿ እንዲሁም ከሉላዊ እንቅስቃሴና መስተጋብር (global action and interaction) ጋር አጣጥሞ ለመጓዝ ይቻል ዘንድ ለአቻ ቦታ አቻ ሰው መድቦ መራመድ ከወደቁ ወዲያ ከመንፈራገጥ ማዳን ብቻ ሳይሆን እስከ ፍልሚያ ሜዳ ያለውን ጎርበጥባጣና ኩርንችታማ ጎዳና ለመጥረግ በቅጡ ያግዛል፡፡ ጦርነት የሰላማዊ መንገድ መሟጠጫ እንጂ መነሻ መሆን በጭራሽ የለበትም፡፡ አለመዘናጋት ግን ሁሌም ወሳኝ ነው፡፡
የጥንቱ የጠዋቱ ሼክስፒር በሀምሌት ውስጥ “ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም፣ አንዴ ከገባህበት ግን፣ እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም!” (ፀጋዬ ገብረመድህን እንደተረጎመው) ያለውን አለመርሳት ደግ ነው፡፡
ረጅም መንገድ አለብኝ ብሎ በርካታ ስንቅ የጫነ ሰው፤ ስንቁን ቅርብ ቦታ መጨረስ የለበትም፡፡ በትንሽ እንቅፋትም መውደቅ የለበትም፡፡ ነገ ሰፊ የምርጫ ትግል ያለበት የዛሬ አዘገጃጀቴ “የሚወጋ ጦር ከእጅ ሲወጣ ያስታውቃል” አይነት መሆን አለበት፡፡ የብዙዎችን ተሳትፎና ድጋፍ በጠዋት ለማግኘት መጣር አለበት፡፡ መፎካከር ለማሸነፍ ብቻ እንዳልነበረ ሁሉ፣ ነገም እንደዛው መሆኑን አውቆ መጓዝ ያሻል፡፡ መጋቢ ጅረቶች ሁሉ ወደ ወንዝ ለመቀላቀልና የአገር ሃይል ለመሆን እንደሚችሉ አጢኖ፤ ጊዜ መውሰድ አቅጣጫ ማግኘት ያሻዋል፡፡ ጊዜያዊ የሀገር ጉዳዮችን ከዘላቂ ፍሬ ነገሮች አነፃፅሮ አንዱ በሌላው እንዳይጋረድ ደህና አደርጎ ማስተዋል የሁሉም ድርጅቶች አጓጓዝ መሆን አለበት፡፡
ዳምኖም አጉረምርሞም ላይዘንብ እንደሚችል ሁሉ፣ ዘንቦም ሙሉ ጥጋብ ላይሆን እንደሚችል፣ ማስተዋል ይገባል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ከህዝብ ያልመከሩበት፣ ህዝብን ያላሳተፉበት አካሄድ መሰረት-የለሽ ፒራሚድ ነው፤ ብዙ እድሜ የለውም፡፡ በአጭር ጊዜ ፈተና ይዳከማል፡፡ አዋቂዎቹን እንደፈተሸው ብልህ ንጉስ፣ ጠያቂ የመጣ እለት በአደባባይ መጋለጥ ይከተላል፡፡ ብዙም ሳይቆይ በቅንጣት ጥያቄ ግዙፍ ሀጥያት ይታያል፡፡ የሚታዘቡትን ፈረስ ጉቶ ላይ ይጋልቡበታል የሚባለው እንግዲህ ያኔ ነው!
Published in
ርዕሰ አንቀፅ