Saturday, 08 June 2024 12:36

አስራ አምስተኛው ህግ

Written by  በደረጄ ጥጉ (የአለም አቀፍ ህግ መምሀር)
Rate this item
(3 votes)

   “ጠላትህን እስከ ወዲያኛው አስወግደው”
                         

         በቻይና የመንግስት አስተዳደር ታሪክ ውስጥ እንደ ሲያንግ ዩ እን ሊዩ ፓንግ በባላንጣነት ታሪካቸው በጉልህ የሚጠቀስ የለም፡፡ እነዚህ ሁለት ገናና የጦር መሪዎች ግንኙነታቸው የጀመረው በወንድማማችነት ስሜትና የልብ ወዳጅ በመሆን ነው፡፡ በብዙ የጦር አውዶች አብረው ጎን ለጎን ተሰልፈው ተዋግተዋል፤ አንዱ የአንዱ መከታና ጋሻ በመሆን ፈተናዎችን ተጋግዘው አልፈዋል፡፡ ሲያንግ ዩ ከነገስታት ቤተሰብ የተወለደ በባህሪውም ነውጠኛ ፤ደመ ሞቃትና የተወሰነ ደደብ ቢጤም ነው፡፡ ሊዩ ፓንግ በበኩሉ፤ ከገበሬ ቤተሰብ የተወለደ ነው፡፡ በታሪኩ እንደሰፈረው ፤ ሊዩ ፓንግ በወጣትነቱ ብዙም የጦረኝነት ስሜት ያልነበረው፣ ከመዋጋት ይልቅ ሴትና ወይንን አብዝቶ የሚወድ ነበር፡፡ ጠጪና ሴት አውል ቢሆንም አስተዋይና አርቆ አሳቢ  ነበር፡፡ በጎልማሳነቱ ምርጥ ምርጥ የሚባሉ የጦርነት ስልቶችን ጠንቅቆ የሚያውቅና እነዚህን የጦርነት ስልቶች እንደአንድ ጥሩ መካሪ አድርጎ የሚጠቀምባቸውና የሚመራባቸው ነበር፡፡ በኋላ ለደረሰበት ከፍተኛ  የስልጣን ደረጃ የደረሰው በነዚህ ምክሮች ታግዞ ነው፡፡ ልዩ ፓንግ ታላቅ የፖለቲካ ግንዛቤ የነበረው ሰው ነው፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ208 የቹ ንጉስ የቺህን ስርወ-መንግስት  ለመቆጣጠር ሁለት ሀያል ጦሮችን ወደ ንጉሱ መናገሻ ከተማ ላከ፡፡ አንደኛው ጦር በሱንግ ዩ መሪነትና በሲያንግ ዩ ረዳትነት ወደ ሰሜን አቅጣጫ ሲዘምት ፤ ሌላኛው ጦር በሊዩ ፓንግ መሪነት ጉዞውን ቀጥታ ወደ ቺን አደረገ፡፡ ኢላማቸውም የስርወ-መንግስቱ ዋና ከተማና ደማቋን ሐስየን ያንግ መቆጣጠር ነበር፡፡ የሊዩ ፓንግ ጦር ግስጋሴውን በማፋጠን ወደ ዋና ከተማዋ ተቃረበ፡፡ በሰሜን አቅጣጫ የዘመተው ነውጠኛው ሲያንግ ዩ ሊዩ ፓንግ፣ ዋና ከተማዋን ቀድሞ ሊቆጣጠራት ነው የሚለውን ይህን ዜና ሲሰማ ተረበሸ፤ሊያምነው የተዘጋጀበትም ጉዳይ አልነበረም፡፡ ሊዩ ፓንግ ይህንን ማድረግ ከቻለ የጦሩ ብቸኛ መሪ ሆነ ማለት ነው፡፡ የሲያንግ ዩ ህልምም ውሀ በላው ማለት ነው፡፡ ሲያንግ ዩ ለዋና ጦር መሪነት ራሱን ሲያዘጋጅ ነበር፡፡
በአንድ አጋጣሚ በሰሜኑ ግንባር ጦርነት ላይ የሲያንግ ዩ የበላይ የነበረው ሰንግ ይ ጦሩን ወደግንባር ለመላክ አቅማማ፡፡  ሲያንግ ዩ በንዴት ሰንግ ይ  ያረፈበት ጎጆ ገብቶ የበላዩን ከሀዲ ብሎ ዘልፎ አንገቱን ቀላው፡፡ በዛውም ሲያንግ  ዩ የጦሩ መሪ ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ ሲያንግ ዩ የማንንም ትእዛዝ መጠበቅ ሳያስፈልገው የሰሜኑ ግንባር ላይ ፊቱን በማዞር ግስጋሴውን ወደ ዋና ከተማዋ አደረገ፡፡ ሲያንግ ዩ ከጀብደኝነቱ በተጨማሪ ለእራሱ የነበረው ግምት የተጋነነ ነበር፡፡ እራሱን የተሻለና ጎበዝ የጦር መሪ አድርጎ የሚያምን ግብዝ ነበር፡፡ ለራሱ የተጋነነ ግምት ቢኖረውም ይግረምህ ሲለው ባላንጣው ሊዩ ፓንግ በአነስተኛ ግን በጣም ፈጣን በሆነው ጦሩ በመታገዝ ዋና ከተማዋን  በቁጥጥሩ ስር ቀድሞ አደረገ፡፡ ሲያንግ ዩ ፋን ሰንግ የሚባል አማካሪ ነበረው፡፡ ፋን ሰንግ ሲያንግ ዩን እንዲህ ብሎ አስጠንቅቆት ነበር፤ “የዚህች ከተማ ገዢ ሊዩ ፓንግ ሴትና ገንዘብ ብቻ የሚወድ አይነት ሰው ነው፡፡ ነገር ግን ከተማዋን በቁጥጥሩ ስር ካደረግ በኋላ ግን ሀብት ወይን ወይም ወሲብ አላዘናጉትም፡፡ ይህ ምን ይነግርሀል? አላማው ትልቅና ከፍ ያለ ነው፡፡ ሳትቀደም አስወግደው፡


ሲያንግ ዩ ምክሩን በመቀበል ከዋና ከተማዋ ወጣ ባለ ቦታ ትልቅ የእራት ግብዣ አሰናድቶ ለሻሞላ ዳንስ እንዲጋብዘውና በዛም መሀል አንገቱን እንዲቀነጥሰው አሳሰበው፡፡ ግብዣው ወደ ሊዩ ፓንግ ተላከ፡፡ ሊዩ ፓንግ ግብዣውን ተቀብሎ ወደ ግብዣው ቦታ ሄደ፡፡ በግብዣው ላይ ሲያንግ ዩ የሻሞላ ዳንስ ትርኢቱ እንዲጀመር ትእዛዝ ለመስጠት ሲያመነታ  ሲያንግ ዩ ፊት ላይ ደስ የማይል ነገር በመመልከቱ ሊዩ ፓንግ ወጥመድ ውስጥ እንደገባ ጠረጠረ፤ በአስቸኳይ ከግብዣው ሾልኮ አመለጠ፡፡ “ሁሁሀሀ” አለ አማካሪው በንዴትና በመደነቅ ውጥናቸው መክሸፉን ሲረዳ፡፡ ጥንቃቄ የሚያስፈልገውን እቅድ እንዴት እንዲህ ታዝረከርከዋለህ? እንዴትስ አቅልለህ ታየዋለህ? አትጠራጠር ከዚህ በኋላ ሊዩ ፓንግ ግዛትህን ነጥቆ ሁላችንንም ምርኮኛው ያደርገናል፡፡ ሲያንግ ዩ ከስህተቱ በመንቃት የሊዩ ፓንግን አንገት ቀንጥሶ እንደሚመለስ እየዛተ ጉዞውን ወደ ዋና ከተማዋ አደረገ፡፡ ገድ  ፊቷን አንዴ ካዞረችበት መዋጋት እንደሌለበት ጠንቅቆ የሚያውቀው ሊዩ ፓንግ ዋና ከተማዋን ለቆ ወጣ፡፡ ሲያንግ ዩ ከተማዋን በእጁ ካስገባ  በኋላ ወጣቱን የቸዪ ልዑል አንገቱን ቀላው፡፡ ለእልሁ መወጫ እንዲሆነውም ዋና ከተማዋን እንዳልነበረች አድርጎ አወደማት፡፡
ከዚህ በኋላ በሁለቱ መሀከል ያለው ታሪክ ሲያንግ ዩ አሳዳጅ ሊዩ ፓንግ ተሳዳጅ ሆነው በጠላትነት የተፈላለጉበት ነው፡፡ ለብዙ ወራት ሲያንግ ዩ ሊዩ ፓንግን በእግር በፈረስ ተከታተለው፡፡ ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሊዩ ፓንግ እንቅስቃሴው  በአንድ ጠባብ ከተማ ተገደበ፡፡ ሲያንግ ዩ የከተማዋን ዙሪያ በመክበብ ሊዩ ፓንግ ምግብም ሆነ ማንኛውም አስፈላጊ ነገር የማያገኝበትን ሁኔታ ፈጠረ፡፡ ሊዩ ፓንግ ለራሱ የሚበላው ለጦሩም የሚያስፈለገውን ስንቅ ሲያጣ ሰላምና እርቅ እንዲወርድ ለሲያንግ ዩ መልእክት ላከ፡፡
የሲያንግ ዩ አማካሪ ፋን ሰንግ ሲያንግን በድጋሚ አስጠነቀቀው፤ “ዩ ፓንግን አስወግደው፡፡ ዳግመኛ እድል እንዳትሰጠው”፡፡ ይህን ባታደርግ በኋላ ትፀፀታለህ፡፡ ሲያንግ ዩ ግን ምክሩን ገሸሽ በማድረግ ለሊዩ ፓንግ የእዝነት እጁን ዘረጋለት፡፡ ሊዩ ፓንግ ምንም እርምጃ ሳይወሰድበት ከነሕይወቱ ተይዞ ወደ ቺዩ እንዲመጣ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ሲያንግ ዩ ይህ እንዲሆን የፈለገበት ምክንያት ሊዩ ፓንግ ከዚህ በኋላ ሲያንግ  ዩ መሪው መሆኑን እንዲቀበልና ለመሪ የሚገባውን ክብር እንዲሰጠው በመፈለጉ ነበር፡፡ የሲያንግ አማካሪ ፋንግ ልክ ነበር፡፡ ሊዩ ፓንግ ሰላምና እርቅ እንዲወርድ ያቀረበው ተማፅኖ ማሳሳቻና የጊዜ መግዣ ስልት ነበር፡፡ ሊዩ ፓንግ የተረፈውን አነስተኛ ጦር ይዞ አመለጠ፡፡ ሲያንግ  ዩ በሊዩ ፓንግ ለሁለተኛ ግዜ በመቄሉና ሊዩ ፓንግ ዳግም ከእጁ በማምለጡ በከባዱ ተገረመ፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ሊያሳድደው ተነሳ፡፡ አእምሮውን የሳተ እብድ እስኪመስል ድርስ በጀብደኝነት እየዛተ ወደ ሊዩ ፓንግ ዘመተ፡፡ በዚህ ሶስተኛ ዘመቻው ሲያንግ ዩ ሊዩ ፓንግን ሳይሆን የ ሊዩ ፓንግን አባት ማረከ፡፡ ለሊዩ ፓንግ የሚከተለውን መልእክት ላከለት፡፡ “እጅህን ስጥ፡፡ እጅህን የማትሰጥ ከሆነ አባትህን ከእነ ህይወቱ በቁሙ እቀቅለዋለሁ”፡፡ ሊዩ ፓንግ ለሲያንግ ዩ መልእክት ረጋ ብሎ እንደሚከተለው መለሰ፡፡ “ቃልኪዳን ያለን ወንድማማቾች እኮ ነን፡፡ የእኔ አባት የአንተም አባት እኮ ነው፡፡ አባትህን እቀቅለዋለሁ ካልክ ምን ይደረጋል እንግዲያው አንድ ኩባያ መረቅ ላክልኝ” ብሎ አፌዘበት፡፡
ይህ ከሆነ ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ሲያንግ ዩ ሊዩ ፓንግን ለመያዝ በነበረው እቅድ ትልቅ ስህተት ሰራ፡፡ ጦሩን ያለበቂ እቅድ በዘፈቀደ አሰማራ፡፡ እንዲህ አይነት መዝረክረክ ለሊዩ ፓንግ እልል በቅምጤ ነው፡፡ በፈጣንና አስገራሚ ማጥቃት ሊዩ ፓንግ የሲያንግን ጦርና ስንቅ በቀላሉ መማረክ ቻለ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ነገሮች ተገለባበጡ፡፡ ሲያንግ ዩ ከአሳዳጅነት ወደ ተሳዳጅነት ወረደ፡፡ አሁን ሊዩ ፓንግ ሳይሆን ሲያንግ ዩ ሆነ፤ እርቅና ሰላምን ተመጽዋች፡፡ በዚህን ግዜ የሊዩ ፓንግ አማካሪ ያለምንም ርህራሄ ሲያንግ ዩን እንዲያስወግደው መከረው፤አያይዞም “ጦሩን ድባቅ እንዲመታው፤ ምንም አይነት እዝነትም ሆነ ርህራሄ እንዳያሳየው ጭምር:- የነብር ጅራቱን አይዙም ከያዙም አይለቁም” የሚለውን ልብ እንዲል መከረው፡፡ የሀሰት ውልን በመዋዋል ሲያንግ ዩን አዘናግቶ ጦሩን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ደመሰሰው፡፡ ሲያንግ ዩ ለማምለጥ ሞከረ፤ግን ረፈደበት፡፡ ሲያነግ ዩን ብቻውን አስቀረው፡፡ ሊዩ ፓንግ የገባለት የቃልኪዳን ውል ማሞኛ መሆኑን በመረዳት ሲያንግ ዩ እራሱን ገደለ፡፡
የመልእክቱ ፍቺ ምንድን ነው?
በታሪክ ሂደት ውስጥ ሲያንግ ዩ ጨካኝነቱን በብዙ አጋጣሚዎች አስመስክሯል፡፡ ይጠቅመኛል ብሎ ካለሰበ በስተቀር ማንኛውንም ነገር ለማድረግ አያመነታም ነበር፡፡ በሊዩ ፓንግ ጉዳይ ግን ሲያንግ ዩ ልዩ እና አዲስ ሰው ሆኖ ነበር፡፡ በማጭበርበር ሊያሸንፈው ስላልፈለገ ባላንጣው ሊዩ ፓንግ በክብር እጅ እንዲሰጥ ፈለገ፡፡ የበላይነቱን ሊያሳየው የፈለገው የበላዩ እሱ መሆኑን እንዲቀበልለት በማድረግ ነበር፡፡ ሲያንግ ዩ ቂል እንደነበር የምንረዳው ብልሁና የጦር ስልት ስትራቴጅስቱ ሊዩ ፓንግ እጁን በሰላም እንዲሰጥና አገልጋዪ እንዲሆን መፈለጉን ስናነብ ነው፡፡ ሲያንግ ዩ ለሊዩ ፓንግ ያሰየው ክብር ርህራሄና እዝነት ለሊዩ ፓንግ ጉልበት ሆኖት ለእሱም የፍፃሜ መጥሪያ ደውል ሆነ፡፡ ሊዩ ፓንግ ግን የሲያንግን ፈለግ አልተከተለም፡፡  ለድሮ ወዳጁ ርህራሄም እዝነትም አላደረገለትም፡፡
ሊዩ ፓንግ “ለጠላትህ እዝነትን የምታደርግ ከሆነ ጠላትህ አፈር ልሶ ያጠፋሀል” የሚለውን የጥንት የቻይናውያን ምክር ልብ ብሎ ተረድቶታል፡፡ እርቅና የሰላም ጥሪን መቀበል እራስ ላይ ነገር መጎንጎን መሆኑንም ያውቃል፡፡ ስልጣን ሲያንግ ዩ ባደረገው መልኩ ለድርድር አይቀርብም፡፡ ጠላት የተባለ በሙሉ ቅሪቱ እንዳይኖር ሆኖ ተመትቶ መወገድ አለበት፡፡ ይህ በዘመን የተፈተነ እውነት ነው፡፡ ወደ ስልጣን በሚደረግ ጉዞ አንድ ወቅት ወዳጅ የነበረ የነገ ጠላታችን ይሆናል፤ ጠላት ደግሞ ምንግዜም ጠላት ነው፡፡ ተቃርኖን የሚገዛው ትልቁ ህግ እርቅ ከጥያቄ ውጪ መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ አንዱ ወገን ብቻ ነው አሸናፊ የሚሆነው፡፡ ወደ ስልጣን በሚደረግ ጉዞ እርታ ልርታ( win win) የሚባል መርህ የለም፡፡ አንዱ ወገን ብቻ ያሸንፋል፤ ካሸነፈም ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ አለበት፡፡ ሊዩ ፓንግ ይህን ወርቃማ ህግ በደንብ ተረድቶታል፡፡ ወደ ስልጣን በሚያደርገው ጉዞ ላይ እንቅፋት ይሆኑብኛል ብሎ ያሰባቸውን በሙሉ አስወገደ፡፡ ሲያንግ ዩን ድል ካደረገው በኋላ ይህ የገበሬ ልጅ የቺዩ የጦር ኢታማጆር ሹም ለመሆን በቃ፡፡ አንድ የቀረውን ባላንጣ የቸሂን ንጉስ ማለትም የቀድሞውን መሪውን ድል ካደረገው በኋላ  ሊዩ ፓንግ ራሱን አነገሰ፡፡ የሀን ስርወ መንግስት መስራች ሊዩ ፓንግ በቻይና የነገስታት ታሪክ የቻይና የምንጊዜም ታላቅ ንጉስ በመባል ይታወቃል፡፡
ህጉን ማጤን
ዉቻዎ በ625 ተወለደች፡፡ አባቷ የአንድ የቻይና ግዛት መስፍን ነበር፡፡ እንደ ማንኛዋም ውብ ሴት የቤተመንግስትን የተድላ ህይወት  በማለም ማረፊያዋ በዛ እንዲሆን ታላቅ ምኞት ነበራት፡፡ ብዙ ሴቶች የንጉሱ እቁባትና ቅምጥ ለመሆን የሚራኮቱበት ቦታ ስለነበር የንጉሱ ቤተመንግስት አደጋኛ ስፍራ ነው፡፡ የውቻዎ ውበትና ያላት ጠንካራ ባህሪ ይህንን ቅምጥ ለመሆን የሚደረግ ትግል በድል እንድትወጣ አስቻላት፡፡
ንጉስም እንደማንኛም ወንድ በሴት ውበት በቀላሉ የሚረታበት ድክመት አለው፡፡ ይህ በሴት ውበት በቀላሉ መማረክ መውደቂያም ጭምር ነው፡፡ ውቻዎ ሴት ልጅ በተፈጥሮ የታደለችውን ይህ የንጉስን ልብ በቀላሉ መስረቅ የሚችል መሳሪያ ምን ያህል ሀያል እንደሆነም ጭምር ታውቃለች፡፡ ይህ በመሆኑም በሌላ ውብ ሴት በቀላሉ እንደምትተካ በማወቅ ከአላማዋ ላለመደናቀፍ እንደ ቼዝ ተጫዋች ነገሮችን በንቃት ትከታተል ነበር፡፡ ሁሌም ትኩረቷ የነገ ህልሟ ላይ ነበር፤ የቻይና ንግስት መሆን፡፡
በቤተመንግስት ውስጥ በነበራት ቆይታ ውቻዎ ወራዳውን የንጉሱን ልጅ በውበቷ አማለለችው፡፡ ብቻውን ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ በወሲብ ስሜት ፈተነችው፤ በኋላም አጠመደችው፡፡ እንዲህም ሆኖ ንጉሱ ሞቶ ልጁ ስልጣኑን ሲወርስ ሁሉም የሟች ንጉስ ሚስቶችና  ቅምጦች በባህልና በልማድ የሚደርስባቸውን እጣ ማሰቡ አሰቃያት፡፡ ውስጧ ተረበሸ፡፡ ፀጉራዋን ላጭታ ኑሮዋን በሴቶች ገዳም ውስጥ ለማሳለፍ በመወሰን ለ7 አመታት እራሷን በሴቶች ገዳም ውስጥ ሰወረች፡፡ በገዳም ውስጥ ከቤተመንግስት ህይወት ተድላ የተሰወረች አስመስላ ተደበቀች፡፡ ላይ ላዩን ሲያዩት ይህን ቢመስልም  ከቤተመንግስት ርቃ በነበረችባቸው ሰባት አመታት ውቻዎ በድብቅ ከአዲሱ ንጉስ ጋር መልእክት ትለዋወጥ ሚስቱንም ትወዳጅ ነበር፡፡ በኋላም በንጉሱ ግብዣ ወደ ቤተመንግስት እንድትመለስ ሆና ከፍ  ያለን ቦታ ያዘች፡፡ ወደ ቀድሞ ክብሯም ተመለሰች፡፡ ከንጉሱ ጋር ድብቅ ወሲባዊ  ግንኙነት ጀመረች፡፡ ንግስቲቱ ይህን ሁኔታ አይታ እንዳላየች አለፈች፡፡ ንግስቲቱ ይህን ብታውቅም ንጉሱን ተው ልትለው አልቻለችም፤ አደጋ ላይ ይጥላታል፡፡ የስልጣን ወራሽ ባለማዘጋጀቷ ይህን ነውር እንዳላየች አለፈችው፡፡


ከማን እንደፀነሰች ባይታወቅም  በ654 ውቻዎ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ በአንድ አጋጣሚ ንግስቲቱ ውቻዎን እንኳን ደስ አለሽ ለማለት  ሄዳ ጎብኝታት እንደተመለሰች ውቻዎ ህፃኑን በጨርቅ አፍና ገደለችው፡፡ የህፃኑ ሞት እንደተሰማ  ጥርጣሬዎች በሙሉ ወደ ንግስቲቱ አመሩ፡፡ ምክንያቱም ግድያው ከመፈፀሙ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በቦታው የታየችው ብቸኛዋ ሴት እሷ ስለነበረች ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ንግስቲቱ በሁሉም ዘንድ ቀናተኛ ሴት መሆኗ የታወቀ ነው፡፡ ጥርጣሬዎች በሙሉ እሷን ገዳይ ቢያደርጉም ንድፉ ግን የውቻዎ ነበር፡፡ ጥርጣሬውን መነሻ በማድረግ ንግስቲቱን ለድግያው ተጠያቂ በማድረግ በሞት እንድትቀጣ ሆነ፡፡ ውቻዎ በንግስቲቱ ቦታ በመተካት ንግስት ተብላ ዘውድ ደፋች፡፡ አዲሱ ባሏ የፈንጠዝያ ህይወት አቅሉን አስቶት በገዛ ፍቃዱ የመንግስቱን የአስተዳደር ስራ በሙሉ ለውቻዎ ሰጠ፡፡ ከዚያን ግዜ ጀምሮ ንግስት ውቻዎ በመባል ታወቀች፡፡ ትልቁን ስልጣን በእጇ ብታስገባም ምንም አይነት ደህንነት ግን አይሰማትም ነበር፡፡ ጠላቶች በየቦታው ነበሯት፡፡ በዚህም የተነሳ ለአፍታም አትዘናጋም ነበር፡፡ ውቻዎ እድሜዋ ገፍቶ 41 አመት ሲሆናት የወንድሟ ልጅ ውቧ ወጣት ሴት የንጉሱ ተቀዳሚ ምርጫ ሆነች፡፡ ንግስቲቱ ይህንን የምትቀበለው አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ወጣቷን ሴት መርዛ ገደለቻት፡፡ በ672 ዙፋኑን ለመውረስ የታጨው ልጅም ተመርዞ ተገደለ፡፡ የሱ ታላቅ የነበረው ሀጋዊ ወራሽ ባይሆንም ለመውረስ የታጨው ልኡል በሀሰት ክስ ግዞተኛ ሆኖ እንዲቀመጥ ሆነ፡፡ ንጉሱ በ683 ሲሞት ወራሴ ሆኖ ሲጠበቅ የነበረውን ልኡል ብቁ አይደለህም ብላ ሻረችው፡፡ ይህን ሁሉ ያደረገችው  ወጣት ልጇን ለማንገስ ነው፡፡ የተገመተውም አልቀረም፤ የእሷ ወጣት ልጅ ንጉስ ለመሆን በቃ፡፡ በዚህ መንገድ ውቻዎ ንግስናዋ ቀጠለ፡፡
በተከተሉት 5 አመታት ብዙ የቤተመንግስት መፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች ተደረጉ፡፡ ሁሉም ከሸፉ፤ ተሳታፊዎቹም በሙሉ አንድ በአንድ ተገደሉ፡፡ በ688 የእሷን ስልጣን የሚገዳደር በቤተመንግስቱ አካባቢ አንድም አልነበረም፡፡ ውቻዎ እራሷን ብቸኛ የቡድሃ ወራሴ ብላ ማእረግ ሰጠች፡፡ በ690 የእድሜ ዘመን መሻቷ ግቡን መታ፡- ውቻዎ እራሷን ቅዱስና መለኮታዊ የቻይና ንግስት ብላ ሾመች፡፡ ያለምንም ተቃናቃኝ  በአንፃራዊ ሰላም 10 አመት ለሚሆን ጊዜ ገዛች፡፡ በ80 አመቷ ስልጣን በፈቃዷ እንድትለቅ ተገደደች፡፡
 የመልእክቱ ፍቺ
ውቻዎን በቅርብ የሚያውቁ በሙሉ የእሷን ሀይልና ብስለቷን በደንብ ይረዳሉ፡፡ በዘመኑ እንደሷ አይነት ሴት በቤተመንግስት ውስጥ በተድላ ከመኖርና ዝናን ከማሳደድ ውጪ የተሻለ ፍላጎት የላትም፡፡ ዘገምተኛ በሚመስለው ግን አስደማሚ በሆነው የስልጣን እርምጃዋ ውቻዎ ሞኝ አልነበረችም፡፡ ማመንታትና ጊዜያዊ መዘናጋት ወድቀቷን እንደሚያፋጥኑላት  የተረዳች ሴት ነበረች፡፡ ሁሌም ጠላቶችዋን ባስወገደች ቁጥር አዲስ ጠላት እንደሚኖራት ታውቅ ነበር፡፡ ለዚህ መፍትሄው ቀላል ነው፡፡ ድል ማድረግ ወይም እስከ ወዲያኛው ማሰወገድ፡፡ ሁሉም ከእሷ በፊት የነበሩት ገናና ነገስታት ይህንን አድርገዋል፡፡ እሷ ግን ሴት እንደመሆኗ መጠን ስልጣን ለመያዝ ጨካኝ ከመሆን  ውጪ ምርጫ አልነበራትም፡፡ በቻይና የነገስታት ታሪክ የውቻዎ የ40 አመታት ንግስና ረዥሙ ነው፡፡ ወደ ስልጣን ያዳረሳት በደም የተበከለ መንገድ መሆኑ በደንብ ቢታወቅም፣ በቻይናዎች ስኬታማዋና ብቁዋ ሴት በመባል ትታወቃለች፡፡
ወደ ስልጣን መዳረሻው ቁልፍ
እንደ ሮበርት ግሪን እምነት፤ ከላይ የጠቀስነው ታሪክ ከቻይና መቀዳቱ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፡፡ ቻይናዎች ታሪካቸው በሙሉ በእንደዚህ አይነት እውነት የተሞላ ነው፡፡ የነገስታቱ ወርቃማ መርህ ሆኖ ያገለገለውም “ጠላትህን ድባቅ ምታ” የሚለው ነበር፡፡ ይህ ቁልፍ የስትራቴጂ መርህ ነው ይለናል ሰን ዙ የአራተኛው ክፍለ ዘመን The Art of war መፅሐፍ ደራሲ፡፡ እንደ ሰን ዙ እምነት፤  “ጠላቶችህ አንተን ከማስወገድ ውጪ ሌላ ምኞት የላቸውም፤ በጎ ያስቡልኛል ብለህ አትሞኝ”፤”ከጠላቶችህ ጋር በምታደርገው ትግል ግማሽ መንገድ ላይ ከቆምክ ለጠላትህ ወርቃማ እድል ሰጥተሀዋል ማለት ነው” ጠላትህ መራር ይሆናል፤ ቀን ጠብቆም ይበቀልሃል፡፡ ጠላቶችህ ለጊዜው ውዳጅ መስለው በመቅረብ ያሞኙሀል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ለምንም ሳይሆን ጊዜ ለመግዛት ብቻ ነው፡፡ በሲያንግ ዩ እና በሊዩ ፓንግ መሀከል የሆነው ይህ ነው፡፡
መፍትሄው፡- “እዝነት አይኑርህ፡፡ ጠላትህን ሙሉ በሙሉ አስወግደው” ከጠላትህ የምትጠብቀውን ሰላምና ደህንነት የምታገኘው በምኞት ሳይሆን ስታስወግዳቸው ብቻ ነው፡፡ የቻይናን ታሪክ በሙሉና ሰን ዙን በደንብ ያነበበው ማኦ ዜዱንግ ከላይ የተጠቀሰውን ህግ አስፈላጊነት በደንብ የተረዳ መሪ ነበር፡፡ ረዥሙ ዘመቻ በሚባለው ታሪክ ውስጥ በ1934 የኮሚኒስት መሪ የነበረው ማኦ እና 75ሺ ብዙም ያልታጠቀ ጦር የቻንግ ኪሻንን ጦር በመሸሸ ወደ ቻይና ምእራብ ተራሮች አፈገፈገ፡፡
ቻንግ ኪሻን እያንዳንዱን ኮሚኒስት ለመስወገድ ቁርጠኛ ነበር፡፡ ከአመታት በኋላ ማኦ ከ10000 ያነሰ ወታደር ነበረው፡፡ በ1937 ቻይና በጃፓን ስትውረር ቻንግ ኮሚኒስቶች ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ላይ ነበሩ ብሎ በማሰቡ እነሱን ማሳደዱን ትቶ ፊቱን ወደ ጃፓኖች አዞረ፡፡ ኮሚኒስቶች ከአስር አመት በኋላ እራሳቸውን መልሰው በማደራጀት፣ የቻንግን ጦር እንዳልነበር አድርገው ብትንትኑን አወጡት፡፡ ቻንግ የጥንቱን ወርቃማ ምክር “ጠላትህን ድል አድርገው” የሚለውን ረስቶት ነበር፡፡ ማኦ በበኩሉ፤ ይህንን በደንብ የተረዳ መሪ ነበር፡፡ ቻንግን እስከ ታይዋን ሩቅ ተራሮች ድረስ አሳደደው፡፡
በዘመናዊው አለም የጦርነት ግብ ጠላትን ሙሉ በሙሉ ድል ማድረግ ነው ይላል የጦርነት ፈላስፋው(philosopher of war) የሚባለው ካርል ቮን:: ካርል ቮን ከናፖሊዮን የጦር ግስጋሴ የተረዳውን ሲያብራራ፤ “ቀጥታ የጠላትን ሀይል ማዋረድ ዋናው ትኩረታችን መሆን ይገባዋል፡፡ ድል ካደረጉ በኋላ መዘናጋትና መዝናናት አይገባም፡፡ ጠላትን ማሳደድ፤ እግር በእግር መከተል፤ የጠላትን መናገሻ መቆጣጠር፤ ቀሪውን ጦር በሙሉ ማጥቃት፤ የእርዳታ መተላለፊያ መንገዶችን በሙሉ መዝጋት፡፡ በአጠቃላይ ጠላትን እረፍት መንሳት” ካርል ቮን እንደሚለው፤ ከእያንዳንዱ ጦርነት በኋላ ድርድር አለ፤ ድርድር ካለ ሰጥቶ መቀበል ይኖራል፤ ግዛት መካፈልና የመሳሰለውም ይከተላል፡፡ ከፊል ድል በድርድር ተሸናፊ እንድትሆን ያደርግሀል፡፡ በጦርነት ያገኘኸውን ድል በድርድር ትነጠቀዋለህ፡፡ ይህ ሀሳብ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በደንብ ተንፀባርቋል፡፡ ኢትዮጵያ በጦር ሜዳ ያገኘችውን ድል በአልጀርስ ጠረጴዛ ተነጥቃለች፡፡ ጠላትን ሙሉ ለሙሉ ሣይደመስሱ ግማሽ መንገድ ላይ መቆም ማለት እንዲህ ነው ውጤቱ፡፡
ለዚህ መፍትሄው ምንድን ነው፡- ለጠላትህ ምንም አይነት እድል አትስጠው፡፡ አዋርደው፤ ግዛቱንም የግዛትህ አካል አድርገው፡፡ የስልጣን የመጨረሻ ግብ ጠላትን ሙሉ በሙሉ ድል በማድረግ መቆጣጠር ነው፡፡ ጠላትህ እንዳይነሳ አድርገህ ቅበረው ፤ጨካኝ ሁን ጨካን መሆን ይጠቅምሀል እንጂ አይጎዳህም፤ ይለናል ሮበርት ግሪን፡፡ የሚከተለውን ልብ በል፡፡ ለስልጣን ብለህ በምታደርገው ትግል ጠላት ትቀሰቅሳለህ፡፡ ቀኑ ሳይረፍድብህ እርምጃ ውሰድበት፡፡ ከእንዲህ አይነት ጠላት ጋር አብሮ በመኖር ደህንነት ሊሰማህ አይችልም፡፡ የማኦ ዜዱንግን ጥበብ ተማር፡፡ ግማሽ መንገድ ብቻ አትሂድ ፤ሙሉ በሙሉ አስወግደው እንጂ፡፡ ጠላትህ ሥጋት የማይሆንበት ደረጃ አድርሰው፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ወዳጅህ ማንም ሳይሆን አደጋን የማሽተት አቅምህ ነው፡፡ በሱ በደንብ ተጠቀም፡፡ ሁሌም ቢሆን ጠላትህን ድል ማድረግ ብልህነት ነው ይለናል፤ ሮበርት ግሪን፡፡ በሀገራችን በቅርቡ የሆነውን በዚህ ፅሁፍ ውስጥ አስገብቶ ማንበብ ጠቃሚ ነው፡፡
ከላይ የሰፈረው ፅሁፍ ከሮበርት ግሪን The 48 laws of war መፅሐፍ ላይ ወደ አማርኛ የመለስኩት ነው፡፡ የኃይለስላሴን ታሪክ በቀጣይ ከዚሁ መፅሐፍ ወደ አማርኛ በመመለስ ለአንባቢ እንዲሆን አድርጌ አቀርባለሁ፡፡ ጤና ሰጥቶ ለሳምንት ያቆየን፡፡

Read 276 times