Monday, 10 June 2024 00:00

ከሰላምና ከምክክር በፊት ምን ይቀድማል? ከዶሮዋና ከዕንቁላሏስ?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(0 votes)

  ሰላም ካለ ነው፣ ሰዎች ሠርተው መግባት የሚችሉት። ከሁሉም በፊት ሰላም ይቀድማል ብንል መሬት ጠብ የሚል ስህተት የለውም። ክርክር ለመፍጠር ሰበብ የማይሰጥ፣ ቀዳዳ የሌለው አስተማማኝ ሐሳብ ይመስላል።
“ከምንም በላይ ሰላም ይበልጣል” ቢሉን ይከፋናል እንዴ? “ከምንም በፊት ሰላም ይቀድማል” ብንልስ ይከፋቸዋል እንዴ? እንዲያውም ሁሉም ሰው እየተሽቀዳደመ ምሎ ተገዝቶ ይቀበለዋል። መሽቀዳደም ይቅርና ከነጭራሹም የማይቀበል እንደሚኖር አይካድም። እንዲሁ “ተቃራኒ” የመሆን አመል ያጋጥማል። የክፋት ባህርይም ይኖራል። ግን ደግሞ በቅንነት ቢሆንስ?
በእርግጥ፣ አንዳንድ ሐሳቦች በደፈናው ሲታዩ በጣም ቀላል መስለው፣ ገለጥ-ገለጥ ፈታ-ፈታ ሲደረጉ ስለሚወሳሰቡም ሊሆን ይችላል። በተለይ ደግሞ “መሠረታዊ ሐሳቦች” በባህርያቸው አሻሚና አሳሳች ገጽታ አላቸው። በዚህም ምክንያት፣ “ሰላም” የሚለው ቃል ለሁሉም ሰው ሁልጊዜ ጣፋጭና ተናፋቂ ጣዕም ላይኖረው ቢችልስ?
ኧረ አይደረግም!
አብዛኛው ሰው ባይሽቀዳደም እንኳ፣ “አሜን፣ ሰላም ይቀድማል” እያለ በጋራ የሚጸልይ አይመስላችሁም? ሰላምን ይወዳል፤ “እንከን የማይወጣለት ትልቅ ምኞትና እጅግ የተቀደሰ ሕልም” እንደሆነ በማመን፣ በኅብር ለሰላም ይዘምራል… ብለን ብንገምት አይገርምም።
ደግሞስ ምን ጥያቄ አለው? “በሰላም ማደር”… ብለን የምንናገረው ያለምክንያት አይደለም። በሰላምታ ተቀብሎ በሰላምታ ሲሰናበትም፣ “በሰላም ያገናኘን” ይባባላል።
ሰላም ሲኖር ነው ሕይወት የሚሰነብተው።
የአእምሮ፣ የአካልና የመንፈስ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች በሙሉ፣ ከቀን ቀን ከዘመን ዘመን እያበቡ የሚያፈሩት፣ እየበለጸጉ የሚያምሩት፣ የክብር አክሊልና ግርማ ሞገስን የሚቀዳጁት ሰላም ካለ ነው።
በጦርነት ጊዜ ከእውነትና ከዕውቀት ይልቅ፣ ፕሮፓጋንዳና አፈና፣ አሉቧልታና ጭፍን እምነት እየገነኑ ይነግሣሉ።
በትርምስ ወቅት ከሙያ ትጋትና ከሥራ ፍሬ ይልቅ፣ በስግብግብነት የመዝረፍና በምቀኝነት የማቃጠል ዘመቻዎች ከዳር ዳር ይዛመታሉ።
በጦርነት ጊዜ፣ ከመከባበር መርሕ ይልቅ የመጠፋፋት ሰበቦች ይራገባሉ፤ ይበራከታሉ። መልካምነትን ከመውደድ፣ ሰዎችን እንደየ ሥራቸው ከመዳኘትና እንደየ ብቃታቸው ከማድነቅ ይልቅ፣ የጅምላ ፍረጃና የጭፍን ጥላቻ በሽታዎች ይስፋፋሉ። ወደ ከፍታ የሚያማትሩ ዐይኖችን የመዝጋት፣ የብቃት አርአያዎችን ከወገብ እየጎረዱ የማዋረድ፣ አዳዲስ ቡቃያዎችን በእንጭጭ የመቅጨትና ከሥር እየነቀሉ ድራሻቸውን የማጥፋት ክፉ መንፈስ አገር ምድሩን ያጥለቀልቀዋል - በጦርነት ጊዜ።
ለሰው ያላቸው ግምት ይሟሽሻል፤ ለራሳቸው ያላቸው ክብርም ይወርዳል። ከዚያ በኋላማ፣ የትኛውንም ክፋትና ወንጀል በይሁንታ ተቀብሎ ማስተናገድ እየተለመደ፣ በተሳታፊነትም ክፋትን መፈጸም እየተዘወተረ፣ የሰው ኑሮ እጅግ ስቃይ የበዛበት አስቀያሚ ገሀነም ይሆናል - ሰላም ከሌለ።
አሳማኝ ሐተታ ይመስላል። እውነትም፣ “ከሁሉም በላይ ሰላም ይቀድማል” ያሠኛል።
በእርግጥ፣ ሌሎች መሠረታዊ ፍሬ ሐሳቦችና “እሴቶች” ላይም ተመሳሳይ ሐተታ ማቅረብ ይቻል ይሆናል።
እንዲያው ስታስቡት ጤንነትን የመሠለ ነገር አለ እንዴ?
“ሕይወት እና መብት”፣ “እውቀትና የማሰብ ነጻነት”፣ “መሥራትና የኑሮ መተዳደሪያ ማግኘት”… ከእነዚህ በፊት የሚቀድም ነገር አለ?
“ፍቅርና መከባበር” የምንላቸው ነገሮችም መረሳት የለባቸውም። ሌላውን ሁሉ ብንተወው እንኳ፣  ፍቅር ከሌለ ሕጻናትን ማሳደግ ይቻላል? ሌሎች እንስሳት’ኮ ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ ብለን “የወላጅ የአሳዳጊ ፍቅርን” ጣል ጣል ብናደርገው አያዋጣንም። አዎ… ዶሮ ጫጩቶቿን፣ ላም ጥጆቿን ያሳድጋሉ። ሰው ግን እንደ ሌሎች እንስሳት መሆን አይችልም። ውሎና አዳሩ፣ ምግቡና መኝታው እንደ ሌሎች እንስሳት አይደለም። የልጅ አስተዳደጉም እንደዚያው። ኧረ… የፍቅር ትልቅነት ላይ ይሄ ሁሉ ክርክር አያስፈልግም። ፍቅር የሌለው ሕይወት ምን ጣዕም አለው?
ቢሆንም ግን፣… ሕግና ፍትሕ ከሌለ፣ ሌላው ሁሉ ብን ብሎ ይጠፋል? አይጠፋም? እልም ይላል እንጂ። ሕግና ሥርዓት ከሌለ እንደ ዱር አውሬ እንጂ እንደ ሰው መኖር አይቻልም። በዚህ ዐይን ስንመለከታቸው፣ “ፍትሕና ሕግ” ከሌላው ሁሉ የሚቀድሙ ይመስላሉ።
የሥነ ምግባር ትምህርት (ፍልስፍ) እንዲሁም መልካምነትን የማክበር መንፈስ (ሃይማኖትና ኪነ ጥበብ) ከሌለስ፣ ሕይወት ምን ትርጉም ይኖረዋል? ጥሩና መጥፎ፣ መልካምና ክፉ፣ የተቀደሰና የረከሰ፣ የከበረና የወረደ… እነዚህን መለየት ካልቻልን፣ ወይም ደግሞ በውስጣችን ቅንጣት ደንታ የማይፈጥሩ ከሆነ… እንዴት እንኑር? በዘፈቀደ መቅበዝበዝና “በደመ ነፍስ” መደናበር? በመንጋ መነዳትና መንጋጋት? ሥነ ምግባርና የክብር መንፈስማ፣ “ሰው የመሆን ጉዳይ ናቸው” ብንል፣ በጭራሽ አልተሳሳትንም።
ጥሩን ከመጥፎ፣ ክብርን ከውርደት መለየት ካልቻልን ወይም ከቁብ ካልቆጠርናቸው፣ ፍትሕና ሕግ ጥሩ መሆናቸውን የማወቅ ዐቅም አይኖረንም። የነጻነት አስፈላጊነትና የሰላም ውድነት ላይስ እንዴት መናገር እንችላለን? ደንታ አይኖረንም እንጂ። “መልካም ሥነ ምግባርና ለክብር መንፈስ… “የቅድሚያ ቅድሚያ” ብንሰጣቸው አይበዛባቸውም።
ቢሆንም ግን… መቼም የክብርና የውርደት ትርጉም የሚገባን… የሕይወትና የኑሮ ነገር ቢያሳስበን፣ በሰላም ወጥቶ የመመለስ ነገር ቢያስጨንቀን አይደል? ስለ ሥነ ምግባር የምንነጋገረውስ ለዚሁ አይደል?
እውነትም፣ “ሰላም ውድ ነው፤ ሰላም ይቀድማል” ብንል ሳይሻል አይቀርም። ሰላም ካለ፣ ቤተሰብ ልጆቹን በፍቅር ማሳደግና ሥነ ምግባር ማስተማር ይችላል። ሰዎች አርሰውና ዘርተው አዝመራ መሰብሰብ የሚችሉት ሰላም ካለ ነው። በዓመታት ጥረት እንደምንም ተቸግረው ያጠራቀሟት ጥሪት ላይ ጨክነው ፋብሪካ ለመትከል የሚደፍሩት፣ በአምስት በዐሥር ዓመት ልፋት ትርፋማ እንደሚሆኑ በመተማመን ነው - ሰላም ካለ።
እንደየ ዐቅማቸውም የሥራ ዕድሎችን ይከፍታሉ። ወጣቶች ተምረው በሥራ አጥነት ከመባከንና በስደት ከመንከራተት ይድናሉ። የጦርነት ማቀጣጠያ ማገዶ ከመሆን ይተርፋሉ። በሙያቸው የመሥራት ዕድል ያገኛሉ - ሰላም ካለ። የአገር ኢኮኖሚ የሚያድገው፣ የሰዎች ኑሮም የሚሻሻለው ሰላም ካለ ነው።
ሰላም ከሁሉም ይበልጣልም፤ ይቀድማልም ብለን ብንደመድም ይቀልላል።
በተገላቢጦሹም ግን፣ “ሰዎች በብርታት ከሠሩና ካመረቱ፣ ወጣቶች የሥራ ዕድል ካገኙ፣ ኢኮኖሚ ካደገና የዜጎች ኑሮ ከተሻሻለ ነው ሰላም የሚኖረው” ብንልስ አያስኬድም?
ደግሞስ፣ የሰዎች የግል ነጻነት ካልተከበረ፣ ያመረቱት ነገር ከተወረሰ፣ ፍትሕ እየጠፋ ግፍና በደል ከነገሠ፣ ሕግና ሥርዓት ከተረገጠ፣ ሰላም ሊኖር አይችልም። ወይም አይሰነብትም።
በኢኮኖሚ ዕድገት የሰዎች ኑሮ ካልተሻሻለ፣ ሕግና ሥርዓት ካልሰፈነ፣ የሰዎች ነጻነት ካልተከበረና ፍትሕ ካልተፈጸመ፣… ሰላም አይኖርም የሚሉም አሉ። ጥፋተኞችና ወንጀለኞች በሕግ የማይጠየቁና የዳኝነት ቅጣት የማይፈጸምባቸው ከሆነ፣ ተጨማሪ ጉልበት ያገኛሉ። በብዙ ተከታይ ይታጀባሉ። እናም፣ የሰላም ችግር እየተባባሰ ይሄዳል።
የኢኮኖሚ ዕድገት ከሌለ፣ የሥራ ዕድል ከጠፋና ተስፋ ከጨለመ፣ ለነውጥና ለትርምስ በማገዶነት የሚቀርቡና ተቀጣጣይ ነዳጅ ሊሆኑ የሚችሉ ወጣቶች ቁጥራቸው ይበረክታል።
“ሕግና ፍትሕ ከሌለ ሰላም አይኖርም”፤ “የተራበ ሰው፣ ሕግ አይገዛውም” የሚሉ መፈክሮችን አታስታውሱም?
ከሰላም በፊት የሚቀድሙ ነገሮች በዙሳ! “ለሰላም የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች” ብለን ብንሰይማቸውስ?
ግን፣ “የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጆችን” አትዘንጉ። ሰላም ሲደፈርስ፣ በርካታ ነገሮች እየተሸራረፉ እየተሸረሸሩ በፍጥነት ከእግራችን ሥር ይጠፋሉ። ሰላም ሲቃወስ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ይመጣል። እገዳና ክልከላ፣ እስርና ግርፊያ… ሰዓት እላፊና ግድያ ይበረክታሉ።
ምናለፋችሁ፣ ሰላም ሲኖር ነው፣ የሰዎች ሕይወትና ነጻነት የሚከበረው። ፍትሕ የሚፈጸመው። ሰላም ከሌለ፣ በትርምስ የሰዎች ሕይወት ይቀጠፋል። ኑሯቸው ስቃይና ረሀብ ይሆናል። ወንጀለኞች ይፈለፈላሉ። ጥቃትና በቀል፣ ወንጀልና ዐጸፋ… በአዙሪት እየተደጋገመ ሲጦዝ፣ ነውጠኞችን ከሰላማዊ ሰዎች መለየት ያስቸግራል። ማጣራትና ዳኝነት መስጠት ያቅተናል። ጉልበተኞችና ጨካኞች ለሥልጣን ሲራኮቱ፣ ሌላው ሰው ሰለባ ይሆናል።
አገር ሲበጠበጥ መያዣ መጨበጫ ይጠፋል።  የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ተጭኖብንም ቢሆን፣ በርካታ የነጻነትና የመብት እገዳዎችን ለጊዜው ተሸክመንም ቢሆን፣ “እንደገና ወደ ሰላም በተመለስን!” ብለን እስከ መመኘት እንደርሳለን። ሌላ አማራጭ አይኖርም?
“በአገራዊ ምክክር አማካኝነት ሰላምን መፍጠር ይቻላል” ብሎ የሚናገር አይጠፋም። በእርግጥ በተለያዩ አገራት የተሞከሩ “ምክክሮች” ብዙም ውጤት አላስገኙም። “ችግርን ያባባሱ” ምክክሮችም አሉ።
የኢትዮጵያ ምክክር፣ በአመዛኙ ብዙም ለውጥ ከማያስከትሉት ተርታ ከሆነ፣ የተወሰነ ጥቅም ካስገኘ በቂ ሊሆን ይችላል። በእርግጥ፣ “ምክክር” ትልቅ በጎ ውጤት ሊያመጣ አይችልም ማለት አይደለም። የአሜሪካ ሕገ መንግሥትን ጨምሮ፣ ለስልጡን ፖለቲካ በጎ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰነዶችና ክስተቶች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከምክክር ጋር የተያያዙ መሆናቸው አይካድም።
ቢሆንም ግን፣ “ሰላም የሚመጣው ከምክክር በኋላ ነው” ለማለት መቸኮል የለብንም። የአገራችን የምክክር ኮሚሽንም በዚህ የሚስማማ ይመስላል። በእርግጥ “በምክክር ሰላም ይመጣል” ማለቱ አይቀርም። ቢሆንም ግን፣ “አገራዊ ምክክር” ለማካሄድ፣ “የተወሰነ ያህል ሰላም ያስፈልጋል” በማለት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ሲናገሩም ሰምተናል።
ምክክር ይቀድማል ወይስ ሰላም? በቅድሚያ ዶሮ ወይስ ዕንቁላል?
ዕንቁላል ለማግኘት፣ ዕንቁላል የምትጥል ዶሮ ታስፈልጋለች። ከዶሮዋ በፊት ግን ዕንቁላል መኖር አለበት። ከዕንቁላል ነው ዶሮ የሚፈለፈለው። “ሰላም የሚፈጥር ምክክር” ለማካሄድ፣ “በቅድሚያ ሰላም ያስፈልጋል” እንደማለት ነው?
በእርግጥ እንዲህ ዐይነት አጣብቂኝ የሚፈጠረው፣ የኮሚሽነሩን አባባል ትንሽ ካዛባነው ብቻ ነው። “የተወሰነ ያህል ሰላም ያስፈልጋል” ነው ያሉት። “ከምክክር በፊት ሰላም ያስፈልጋል” አላሉም። “ትንሽ ሰላም” እና “ሰላም” ምን ዐይነት የትርጉም ልዩነት ያመጣሉ?
ሌሎቹ አጣብቂኝ ወጥመዶችንም በዚህ ዐይን ብንመለከታቸው ሳይሻል አይቀርም።
እንግዲህ፣ በሥነ ፍጥረት ታሪክ ውስጥ፣ ከዶሮ እና ከዕንቁላል ማን እንደሚቀድም መመርመር ወይም መከራከር ይቻላል። እነ ዳርዊን እንዳደረጉት፣ በኢቮሊሽን መሠረተ ሀሳብ ላይ በመመርኮዝና ሳይንሳዊ ጥናቶችን በማካሄድ፣ አስተማማኝ ምላሽ ወይም ማብራሪያ እናገኛለን ብለን ብናስብ አስተዋይነት ነው።
ጥያቄው ግን፣ ተጨማሪ ቁምነገሮችን ያዘለ ነው። አሁን ዛሬ፣ የዶሮ እርባታ ላይ መሰማራት የሚፈልግ ሰው፣ በቂ ዕንቁላሎችን ቢገዛ ይሻለዋል? ወይስ ዕንቁላል የሚጥሉ በቂ ዶሮዎችን ቢያሟላ ይሻለው ይሆን?
በእጃችን የጨበጥነውን ወይም በአጠገባችን ያገኘነውን ይዘን ብንጀምር አይሻልም? አንድ ሁለት ዶሮ ቢኖረው፣ ዐሥር ወይም ሀያ ዕንቁላል ቢኖረው፣ በነባሮቹ ዶሮዎች ተጨማሪ ዕንቁላል ለማከማቸው፣ በነባሮቹ ዕንቁላሎች ደግሞ አዳዲስ ዶሮዎችን ለማርባት ቢጥር ነው ብልህነት።
በሌላ አነጋገር፣ ዕንቁላልና ዶሮ፣ እንደ ተቀናቃኝ እርስ በርስ ማጣላት፣ አንድም የአላዋቂ ስህተት፣ አልያም ተላላነት፣ ወይም ደግሞ አታላይነት ከመሆን አይድንም። አንዱን ነገር ቀዳሚ ለማድረግ ሌላኛውን አፍርሶ ወደ ዜሮ የመመለስ ሙከራ ይሆናልና።
ሰላም ሙሉ ለሙሉ ካልሰፈነ፣ ሕጎቼን በሙሉ ካላከበራችሁ… “ስለ ኢኮኖሚና ስለ ነጻነት ማሰብ ከንቱ ነው” የሚል መንግሥትና ገዢ ፓርቲ… ወይም ደግሞ
ዛሬውኑ እንከን አልባ ምርጫ ካልተካሄደ፣ ፍትሕና ነጻነት ሙሉ ለሙሉ ካልነገሠ፣… “ሰላም አልሰጣችሁም” የሚል ተቃዋሚ ፓርቲ ወይም ዓማጺ ቡድን…
የመጀመሪያዋን ዕንቁላል ወይም የመጀመሪያዋን ዶሮ ለማግኘት በሚል ስሌት ይሳሳታሉ፤ ወይም ራሳቸውን እያታለሉ። አልያም ሌሎችን ያምታታሉ።
በነገራችን ላይ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ ውስጥም፣ የመጀመሪያ ዕንቁላልና የመጀመሪያ ዶሮ የሚለው ጥያቄ፣ ትክክለኛ መልስ የሌለው አሳሳች ጥያቄ እንደሆነ ነው የሚነገረው። ከዶሮዎች በፊት “የዶሮ የሚመስል ዕንቁላል የሚመስል ዕንቁላል ነበረ” ይላሉ ሳይንቲስቶቹ። “ከዶሮ ዕንቁላል በፊት ደግሞ፣ ዶሮ የሚመስል ዕንቁላል ጣይ እንስሳ ነበረ” ሲሉም ይናገራሉ።
በሌላ አነጋገር፣ ትንሽ የኢኮኖሚ ዕድገት ለተጨማሪ ሰላም፤ ትንሽ ሰላም ደግሞ ለተጨማሪ ዕድገት… ሁሉም መሠረታዊ እሴቶችና መልካም ነገሮች እርስ በርስ እየተደጋገፉ ነው የሚበለጽጉት፣ የሚዳብሩት። በቅደም ተከተል አይደለም።

Read 242 times