Saturday, 08 June 2024 12:44

እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት በኢትዮጵያ . . .

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)


       በዚህ እትም እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎትን አስመልክቶ ልናስነብባችሁ ያሰናዳነውን ከማቅረባችን አስቀድሞ የ1 እናት ልምድ እናካፍላችሁ።
“ሰብለ ምንያህል እባላለው። በስራ አጋጣሚዎች ወደ ተለያዩ ሀገራት የመሄድ እድል አለኝ። ሰዎች በቤታቸው ውስጥ ምርመራ እና ህክምናዎችን ሲያደርጉ አያለው። የሚወጉ መድሃኒቶችን እራሳቸው ወይም ቤተሰብ እንዲወጋ ይደረጋል። እኛ ሀገር ሰዎች ቤት ውስጥ ምርመራ እና ህክምና ሲያደርጉ አልመለከትም። የዛሬ ዓመት አከባቢ ውጪ የምትኖር ጓደኛዬ የማህፀን ካንሰር የሚያመጣውን ቫይረስ መመርመሪያ [የ HPV መመርመሪያ ኪት] አመጣችልኝ።  እኔ በትንሹም በትልቁም ሆስፒታል መሄድ አልወድም። በዛ ላይ ቤት ውስጥ ምርመራ ማድረጌ ነፃነት ይሰጠኛል። ግን ማንም ይሄን ሀሳቤን አይረዳውም። እንደውም ስለ በሽታ እያሰብኩ እራሴ ላይ እርግማን እንደማመጣ ነው የሚያስቡት። እና ጓደኛዬ ባመጣችልኝ መመርመሪያ እራሴን መረመርኩ እግዚአብሔር ሲረዳኝ በሽታው የለም። ቤተሰቦቼ ግን “ባልጠፋ ነገር ከውጭ ይሄን ታመጫለሽ? አንቺ በሽታ እራስሽ ላይ ትጠሪያለሽ” ብለው ተቆጡ። ተባብሶ መዳን በማይቻልበት ደረጃ ላይ ሀኪም ቤት ከመሄድ ወይም ለጥቃቅን ችግር ሆስፒታል ከመመላለስ ሀኪም እያማከሩ እራስን ቤት ውስጥ መንከባከብ የተሻለ ይመስለኛል።”                                                      
          ወ/ሮ ሰብለ ምንያህል ከአዲስ አበባ    
በዓለም የጤና ድርጅት ትርጉም መሰረት እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ማለት በህክምና ባለሙያ ድጋፍ ወይም በእራስ በሚደረግ ህክምና (የህክምና ስርአቱን በመከተል) የግለሰብ፣ ቤተሰብ እና ማህበረሰብ ጤናን ማሳደግ፣ በሽታን አስቀድሞ መከላከል እና ጤናን አስጠብቆ መቀጠል የሚያስችል አቅም(አሰራር) መፍጠር ማለት ነው።
የኢትዮጵያ ጤና ሚንስቴር እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት መመሪያ (National selfcare guideline) ይፋ አድርጓል። ይህንን አስመልክቶ ግንቦት 13 እና 14 2016 ዓ.ም የጤና ሚንስቴር፣ የኢትዮጵያ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ማህበር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቢሾፍቱ ከተማ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በጤና ሚንስቴር የእናቶች፣ ህፃናት እና አፍላ ወጣቶች ጤና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ዓለማየሁ ሁንዱማ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ለእራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት መስፋፋት ምክንያት የሆነው የኮቪድ ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ነው። ይህም ችግርን ወደ መፍትሄ የቀየረ ሲሆን ሰዎች በእርሳቸው ጤና ላይ እንዲወስኑ እድል ሰጥቷል። “ህብረተሰቡ ጤናው ላይ እንዲሰራ ለማድረግ እራስ አገዝ ህክምና (selfcare) አስተዋፅኦ ያበረክታል” ብለዋል ዶ/ር ዓለማየሁ ሁንዱማ።
“እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ማለት ታካሚዎች ወደ ህክምና ተቋም ሳይመላለሱ እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያክሙ ማድረግ ነው” በማለት የተናገሩት በጎንደር ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አቸንፍ አስማማው ናቸው። ነገር ግን ሙሉበሙሉ የህክምና ባለሙያ አያስፈልግም ማለት አለመሆኑን ባለሙያው አክለው ተናግረዋል። ከባለሙያው ጋር የሚደረገውን ግንኙነት ወይም ወደ ህክምና ተቋም የሚደረገውን ምልልስ በመቀነስ ሰዎች ባሉበት ሆነው ራሳቸውን እንዲያክሙ የሚደረግበት አሰራር ነው። እራስአገዝ የህክምና አገልግሎት በ2 መንገድ ይሰጣል። ይህም ከህክምና ባለሙያ እገዛ ጋር(በጋራ) እና ከህክምና ባለሙያ ውጪ(ለብቻ) ለእራስ የሚሰጥ ህክምና ነው። ከህክምና ባለሙያ ውጪ ለሚሰጠው አገልግሎት በግንዛቤ፣ በቁሳቁስ እና በእራስ መተማመንን በማዳበር ድጋፍ ይደረጋል። እንዲሁም በእራስ የሚሰጥ ህክምና ላይ ያጋጠመው ችግር(ህመም) ከፍ ሲል (ከፍተኛ ከሆነ) የህክምና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል።
እንደ ዶ/ር አቸንፍ አስማማው ንግግር እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ሁሉንም አይነት የህክምና አይነቶች የያዘ ነው። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ሁሉንም የህክምና አይነቶች ማዳረስ ስለማይቻል ቅድሚያ የሚሰጣቸው የህክምና አይነቶች ይኖራሉ። ከዚህም ውስጥ የስነተዋልዶ ጤና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የህክምና አገልግሎቶች ውስጥ እንደሚሆን ነው ባለሙያው የተናገሩት። “የተለያዩ ችግሮች ውስጥ ነው ያለነው። ስለዚህ በጣም ሊያንገበግብ እና ቅድሚያ ሊሰጠው ይችላል ብዬ የማስበው የስነተዋልዶ ጤናን ነው። ከዛ በመቀጠል ዘላቂ በሽታዎችን (chronic disease) ነው” ብለዋል ዶ/ር አቸንፍ አስማማው። ለዚህም እንደ ምክንያት ያስቀመጡት የሚሰጠው ህክምና በቀላሉ ለተጠቃሚዎች መድረስ መቻሉን ነው።
መመሪያው ላይ እንደተቀመጠው በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ የሚሰጥ የእራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ትኩረት የሚያደርገው እናቶች፣ ህጻናት፣ አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ላይ ነው። ይህ አሰራር መሰረታዊ የሆኑ የሰው ልጅ መብቶችን (ሰብአዊ መብት) ማዕከል አድርጎ የሚሰራ ሲሆን የግለሰቦችን ፍላጎት፣ አኗኗር እና የመኖሪያ አከባቢ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደርጋል።
(Selfcare) እራስአገዝ የህክምና አገልግሎት ላይ ከሚሰጡ የስነተዋልዶ ጤና የህክምና አገልግሎቶች መካከል;
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት
ቅድመ እና ድህረ ወሊድ ህክምና
የእርግዝና ምርመራ
ጡት ማጥባት
በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ማነስ፣ የስኳር እና የደም ግፊት ምርመራ
የወለዱ እናቶች ከህክምና ተቋም ውጪ (በቤት ውስጥ) ለእራሳቸው ማድረግ ስለሚገባቸው እንክብካቤ
የህፃናት አያያዝ(እንክብካቤ)
የእናቶች እና ህፃናት የአመጋገብ ስርአት
የኤች አይ ቪ ምርመራ
በግብረ ስጋ ግንኙነት ስለሚተላለፉ በሽታዎች ግንዛቤ መፍጠር
የእራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ነው ተደራሽ የሚሆነው። ተንቀሳቃሽ ስልኮች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ ሁሉም የመገናኛ ብዙሀን መረጃውን ያሰራጫሉ። አገልግሎቱ በዋናነት ወደ ህክምና ተቋምት ለመሄድ አመቺ ባልሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ ታካሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው። እንዲሁም በኢትዮጵያ የህክምና ተቋማት እና የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ እንደመሆኑ ታካሚዎች ለእራሳቸው ጤና ተሳታፊ መሆናቸው እጥረቱ የሚፈጥረውን ችግር ለማስተካከል ይረዳል።
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አቸንፍ አስማማው እንደተናገሩት ሰዎች በማንኛውም ቦታ ሆነው በቴክኖሎጂዎች አማካኝነት አገልግሎቱን ማግኘታቸው ከአላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት ይታደጋል። ነገር ግን ቴክኖሎጂ ላይ ያለው አጠቃቀም እንደ ሀገር ወደ ኋላ የቀረ መሆኑን ነው ባለሙያው የተናገሩት። በገጠር እና ከተማ የሚኖሩ ሰዎች (እናቶች) ተመሳሳይ የሆነ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም (እውቀት) የላቸውም። ከዶ/ር አቸንፍ ጋር በተመሳሳይ መልኩ የተማሩ እና ያልተማሩ ሴቶች ያላቸው አተገባበር እንደሚለያይ የገለፁት በጤና ሚንስቴር እናቶች፣ ህፃናት እና አፍላ ወጣቶች የጤና አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ የእናቶች ጤና ፕሮግራም ዴስክ ሀላፊ የሆኑት ሲስተር ዘምዘም መሀመድ ናቸው። ስለሆነም አስፈላጊውን መረጃ መስጠት ለችግሩ መፍትሄ እንደሚሆን ሲስተር ዘምዘም መሀመድ ተናግረዋል።
ለእራስ ስለሚደረግ ህክምና መረጃ የሚገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ተገቢውን እውቀት መስጠት እና ማህበረሰባዊ ድጋፍ እንዲኖር ማድረግ ለህክምናው አስፈላጊ ናቸው። ስለሆነም ሴቶች ለእራሳቸው ስለሚሰጡት ህክምና እውቀት እና ክህሎት እንዲኖራቸው በማድረግ የሴቶችን ተሳትፎ እና ብቃት ማሳደግ ይቻላል። በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እንደ ስኳር እና ደም ግፊት ያሉ ሥር የሰደደ በሽታዎች ባለባቸው ሴቶች ላይ ለእራስ የሚሰጥ ህክምና የጤና መሻሻሎች አሳይቷል። ብሄራዊ እራስአገዝ የህክምና አገልግሎት መመሪያ (national selfcare guideline) ላይ እንደተገለጸው መመሪያው ሴቶች የእራሳቸውን ጤና እንዲጠብቁ የሚያደርግ ሲሆን በጤናቸው ላይ ሃላፊነት እንዲወስዱ እድል ይሰጣል። ይህም ሴቶች በጤናቸው ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ጠንካራ የጤና ስርዓቶችን ለመገንባት ያግዛል። እንዲሁም የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን የሚያበረታታ እና ሴቶች በጤና ጥበቃ ስርአት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። በጤና ሚንስቴር እናቶች፣ ህፃናት እና አፍላ ወጣቶች የጤና አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ የእናቶች ጤና ፕሮግራም ዴስክ ሀላፊ የሆኑት ሲስተር ዘምዘም መሀመድ እንደተናገሩት አንዲት እናት በእራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ብቁ ከሆነች እንደ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና ሀገር ተጠቃሚ መሆን ይቻላል።
የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት የህክምና ባለሙያ እጥረት፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የቁሳቁስ እና የገንዘብ እጥረት አለበት። በተጨማሪ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በተለይም የእናቶች፣ የጨቅላ ሕጻናት እና የወጣቶች የስነተዋልዶ ጤና ላይ ክፍተቶች አሉ። ስለሆነም እነዚህን እጥረቶች (ውስንነት) በመቅረፍ ሂደት ላይ እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎቶች ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው መመሪያው ገልጿል። በተለይም በስነ ተዋልዶ ጤና ላይ እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት የግለሰቦችን ምርጫ የሚያሳድግ እና አላስፈላጊ ወጪን የሚቀንስ ነው። እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ተግባራዊ ለማድረግ አመቺ፣ ተስማሚ እና ከመመሪያው ጋር አብሮ የሚሄድ መሆን አለበት። በዚህም በጤና አገልግሎቶች እጦት ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉት ጉዳቶች እና የህይወት ማጣት ሁኔታዎችን መቀነስ ይቻላል። ነገር ግን በጎንደር ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አቸንፍ አስማማው እንደተናገሩት እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት የሚያስፈልገው ለማን፣ በምን አይነት ሁኔታዎች ላይ እና እስከ ምን ድረስ ነው የሚለውን በማስተዋል(በመለየት) ተጠቃሚ መሆን ያስፈልጋል።


Read 356 times