Saturday, 08 June 2024 12:55

እኔና ባለአደራው

Written by  ከውድነህ ክፍሌ
Rate this item
(6 votes)

 (ምናባዊ ልቦለድ)
                                     ከውድነህ ክፍሌ



          ጮርናቄ እየበላሁ ያለሁበት ነው ፤ ደክሞኝ የለ? ቤቴን ቀለም ሳስቀባ፣ስቀባ ውዬ።
የዛሬ አለባበሴ ደግሞ ምስኪንና አሳዛኝ አስመስሎኛል። ምናለበት መኪናዬ ውስጥ ያስቀመጥኩትን ቱታ ቀይሬ ብወጣ!? ለነገሩ ትኩስ ጮርናቄው እንዳያልቅ ብዬ ነው ዝርክርክ እንዳልኩኝ የወጣሁት። ያውም እኮ መንገድ ዳር፣ድስስ ያለች የሳጠራ ቤት ውስጥ ሆኜ ነው ለትኩሌ የተሰየምኩት። ተሰይሜም ነው ጮርናቄውን እያጣጣምኩት ያለሁት።
ቆይ እስቲ የሆነ መኪና ውስጥ እጁን እያውለበለበ የሚጠራኝ ሰው አለ። “ማነው?”
ኧረ እኔን ነው። እንዴ አውቀዋለሁ፤ አውቀዋለሁ እናንተ! የሆነ ቲቪ ላይ አይቼዋለሁ። ‘ባለአደራው’ የሚባለው ነው።
ያልሰማሁ መስሎት “አባባ የኔ አባት፣ኑ እስቲ” ሲል ጮሆ ተጣራ። አሁን እኔ አባባ የምባል ነኝ? ይሁንለት። ዙሪያዬን ‘ሰው አየኝ፣ አላየኝ’ እያልኩኝ፣ እየቃኘሁ ተጠጋሁት። ከነደያን አንዱ  መስዬው ከሆነ ምን ሊለኝ እንደሆነ ገብቶኛል።
‘ምን እያደረጉ ነው?...ትክዝ ብለው አየሁዎት። ምን ሆነው ነው?’ ይለኛል።
አላልኳችሁም?...እንደገመትኩት አለኝ። ለነገሩ ጮርናቄ እወዳለሁ። ልጅነቴን ስለሚያስታውሰኝ በትካዜ እነጉዳለሁ።
“አዎ ተክዣለሁ!” አልኩት።
“ምን ሆነው የእኔ አባት?”
ምን ልበለው?
ብሯን ማግኘት አለብኝ። ‘ገና አሁን ምግብ መቅመሴ ነው!’ ልበለው እንዴ? አዎ። ሀዘኑን ማባባስ ይሻላል።
“እርቦኝ ነው!” አቤት ባለቤቴ ይህንን ስል ብትሰማ ዘመኗን ሁሉ ስትረግመኝ ነው የምትኖረው። ኧረ ትፈታኛለች። በርሜል ሙሉ ኩንታል ጤፍ አስፈጭታ የእኛን ሆድ ነው የምትሞላው፣ከእነልጆቼ። መሶቧ መች ጎድሎ ያውቅና።
ትክዝ ብሎ እያየኝ “እኔን ይራበኝ!...እስቲ ወደ መኪናው ይግቡ አባቴ!” አባቴ የሚለውን ደጋገመው። ለብሩ ብዬ እንጂ ልጅህ ነው የምሆነው ብዬ ፍርጥ አደርግለት ነበር። ግን በመሓላችን ብሩ አለ።
ወደ መኪናው ገባሁ። ውስጧ ከእኔ መኪና ጋር ይመሳሰላል። ቅስስ ብዬ ነው የገባሁት፤ችዬበታለሁ። ለካንስ ብዙ በማየት መተወን ይቻላል?...በቃ ቻልኩበት።
“የት ነው የሚኖሩት አባቴ?” የት ልበለው? ቪላ ቤት አለኝ ልበለው? የማከራያቸው ሰርቪስ ቤቶች እንዳሉኝ ልጠቁመው? እንዲሁ በደፈናው፥
“እዚሁ ነኝ። ...በቃ መንገድ ዳር!” ወይ ጉዴ መንገድ ዳር አልኩት? ጉድ ነው መቼም።
ብዙ ሰው በብር ትሰክራለህ ይለኝ ነበር። እንዴት ያለሁት ሰው ወጣኝ። ከተቸገሩት ጋር ችግረኛ መስሎ ሽሚያ!? ለብር ያለኝን ፍቅር የበለጠ የተረዳሁት ዛሬ ነው። ትወናውን ትቼ ምናለበት ለእውነተኞቹ ምስኪኖች ብተውላቸው? ግን ለአፌ እለዋለሁ እንጂ በተግባር አልገለጥም፤ ይኸው ነኝ።
“አይዞት የእኔ አባት! ለመሆኑ ልጆች፣ቤተሰብ አሎት?” አለኝ።
“ነበሩኝ!” ከነበሩኝ በኋላ ምን ልበል?
“የት ናቸው?”
“እንጃ አላውቅም!” አሁን አላውቃቸውም ያልኳቸውን ልጆች ፈጣሪ ቢወስድብኝስ? ስል አሰብኩ። ደግሞ ይህን እያሰብኩ ቦርሳ ያነገበውን የዩኒቨርስቲ ተማሪ ልጄን በመኪናው አጠገብ ሲያልፍ አየሁት። እንዳያየኝ ሸሸግ ብዬ አሳለፍኩት። እንዴት ደግሞ አምሮበታል። ልጅስ አሳድጌአለሁ።
“አሁን ምን እየሰሩ ነው የሚኖሩት አባቴ?” ሲለኝ ከሄድኩበት ሀሳብ ባነንኩኝ። ምን ልበለው? ቤት አከራያለሁ። ፎቅ ቤት አለኝ። ድለላ ላይም አልቦዝንም። ምን ልበለው!?
“ምን እንግዲህ የሚሰራ የለም! ሳገኝ እሸከማለሁ። ወፍጮ ቤትም...ያገኘሁትን እሰራለሁ!” አልኩት። ወይ እኔ! ደግሞ ተቅለሰለስኩኝ። ውይ ሰው።
“ብርቱ ኖት የኔ አባት! ጀግና!”
ቶሎ ፈጥኖ ወደ ብሩ እንዲገባ እየጸለይኩኝ ነው። ‘ፍጠን፣ፍጠን!’ አልኩት በሀሳቤ።
“እኔ አባቴ ስሜ ባለአደራው ይባላል!” ሀዘን እየተናነቀው። ‘አውቅሀለሁ!’ ልለው ነበር። እንዳይባንን ብዬ ነው ዝም ያልኩት። እንደማያውቅ ሆኜም “ባለአደራው?”
“አዎ። እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉና ውጭ አገር ያሉ ሰዎች እንደእርሶ ያሉ ብርቱ አባቶችን እንድረዳ ይልኩኛል! አደራቸውን አደርሳለሁ።” አለኝ በየዋህነት።
ግራ የተጋባ መስዬ አየሁት።
‘የመጀመሪያ ዙር ስንት ይሆን የሚሰጠኝ?’ የእጁ እንቅስቃሴ ላይ አይኔ አረፈ። የመኪናውን ኮሜዲኖ ከፈተና የታሰረ ብር አወጣ።
“አባቴ ይህቺን ያዟት!”
እዚህ ጋ ማስመሰል አለብኝ። ግራ የተጋባ ሰው መስዬ ተግደረደርኩኝ።
“ይቀበሉኝ አባቴ!...እኔ አይደለሁም የሰጠሆት! አንዲት እህቴ ወለተ ሰንበት ትባላለች። ይህን እሷ ነች የላከችው። “
በግድ ተቀበልኩኝ።
“እስቲ ቁጠሩት” አለኝ። እንደሌባ ሰው አየኝ አላየኝ እያልኩ ቆጠርኩት።
“አስር ሺህ ብር ናት!” አለኝ የፊቴን የደስታ ሀዘን እያጤነ።
አሁን ብሩን በላይ በላዩ እንዲጨምርልኝ ማልቀስ አለብኝ። እንባ ባጣ በድርጊቴ አፍሬ ማልቀስ አያቅተኝም። አላልኳችሁም አለቀስኩ።
“አይዞት አባቴ!” አለና ጨመረልኝ።
“ይህን ደግሞ ዱባይ ያለች ፋጤ የምትባል እህት ነች የላከችሎት!”
ቀጠለ።...እንባዬም ዘነበ...ቀጠለ...ቀጠለ...
በእንባዬ ልክ የተቋጠሩ ብሮች እጄ ላይ ገቡ። የእንባዬ ዋጋ ነው።
“አያልቅሱ አባቴ። እርሶ ብርቱ ሰው ኖት። በሉ ብሩን የላኩትን ሰዎች ይመርቁ!” አለኝ፣ ከልቡ አዝኖልኝ ሀዘኑን ዋጥ አድርጎ።
ምን እንዳልኩ ሳይገባኝ ምርቃቴን ጨረስኩት።
“ምናልባት እርሶን መርዳት የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ ስልክ ቁጥር ካሎት ይስጡኝ!” ከችኮላዬ ብዛት ውድ ስልኬን አውጥቼ የእሱን ቁጥር ልመዘግብ ትንሽ ነበር የቀረኝ። ተዋርጄ ነበር።
“ስልክ የለኝም!” አልኩና የእሱን ቁጥር እንዲሰጠኝ ጠበኩት። አላልኳችሁም ጽፎ ሰጠኝ። “በእዚህ ደውለው ስልክ ቁጥሮትንም፣የባንክ አካውንቶትንም ይነግሩኛል አባባ!”
“እሺ” አልኩት።
ሌቦች እንዳይወስዱብኝም በየጃኬቴ የሚስጥር ኪስ ብሩን እንድሸጉጥ ካስደረገኝ በኋላ “እጆትን ልሳመው!” አለኝ።
ጮርናቄ የበላሁበትን እጄን ደጋግሞ ሳመው፣ከልቡ። እኔም ምላሽ ሰጠሁትና ከመኪናው ወጣሁ።
ቆሜ እጄን እያውለበለብኩለት እያለ አንድ አስደንጋጭ ስሜት ወረረኝ። ከባለአደራው ጋር ያወራሁት ሁሉ በመገናኛ ብዙኃን በኩል እንደሚቀርብ። ግን እኮ የቀረጸኝ ሰው የለም? ነው መኪናው ውስጥ የተጠመደ ካሜራ አለ!? ውስጤ ተረበሸ።
“እንዴት?” አልኩኝ።
ሰፈሬም፣የሰፈሬም ማህበረሰብ ድርጊቴን ካዩ እንደሚተፉኝ፣ ባለቤቴ፣ልጆቼም እንደሚሸማቀቁብኝ ተረዳሁ። ቀድሜ አለመረዳቴ ጭምር አናደደኝ። ለነገሩ ‘የገንዘብ ነገር የልብህን ብርሃን ይነጥቀዋል!’ የሚሉኝ ወዳጆቼ ወደው አይደለም።
ብቻ ከመዋረዴ በፊት በፍጥነት አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ወሰንኩ። በብጫቂ ወረቀት በሰጠኝ ስልክ ቁጥር ደወልኩኝ። ልቤ የእፍረት ምቱን እየደለቀ ነው። ስልኩን አነሳው። ብርክ እየያዘኝ
“ሀሎ...ባለአደራው ነህ?”      


Read 536 times