Saturday, 15 June 2024 00:00

“ብልጥ ዋሾ፤ አምላኬ ሆይ! ውሸቴን አታስረሳኝ ብሎ ይፀልያል!”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 አንድ ሰው አንዲት በጣም የሚወዳት ሴት ዘንድ ሄዶ “ዛሬ የት ውዬ እንደመጣሁ ታውቂያለሽ?” ሲል ይጠይቃታል፡፡
ሴትዮይቱም፤ “የት ዋልክ የኔ ጌታ?” ትለዋለች፤ በፍቅር ቃና፡፡
ሰውዬው፤
“አንድ ጫካ ሄጄ፣ በእኔ ላይ ሸፍተው ከነበሩት ደመኞቼ ጋራ ተዋግቼ፣ ድባቅ መትቻቸው መጣሁ፤ በሙሉ ጨረስኳቸው” ይላታል፡፡
ሴትዮይቱ፤ “እንዲህ ነው እንጂ የኔ ጀግና! እኔ አንተን የወደድኩህ ለዚህ ለዚህ ታላላቅ ገድልህ ስል አይደል!” ትለዋለች፡፡
ሌላ ቀን ወደ ወዳጁ ዘንድ ሲመጣ፤ “ዛሬስ የት ሄጄ እንደመጣሁ ታውቂያለሽ?” ይላታል፡፡
“የት ዋልክልኝ የኔ ጀግና?”
“አንድ ጫካ ሄጄ፤ በእኔ ላይ ያደሙ ሽፍቶች አግኝቼ ጉድ አደረግኳቸው፡፡ አንድም ሳይቀረኝ ድምጥማጣቸውን አጥፍቻቸው መጣሁ!” ሲል ይፎክርላታል፡፡
ሴትዮይቱም፤ “እንዴ! የዛሬ ወር እዚያ ጫካ ሄደህ ድባቅ እንደመታሃቸው ነግረኸኝ አልነበር? ደግሞ ዛሬ ከየት መጡ?”
ሰውየውም ደንግጦ፤ “አይ ያኛው ሌላ ጫካ ነው!” ይላታል፡፡ ሴትየዋ ታዝባው ዝም ትላለች፡፡ ተጨዋውተው ይለያያሉ፡፡
ደሞ በሌላ ጊዜ ሲያገኛት፤ “ምነው ጠፋህ?” ትለዋለች፡፡
“ምን እባክሽ ወደ ጫካ ሄጄ ጠላቶቼን አንድ በአንድ ስለቅማቸው ውዬ፣ ድል በድል ተጎናጽፌልሽ መጣሁ፡፡ የመንደራችን ሰው ሁሉ “ጉሮ ወሸባዬ! እንዲያ እንዲያ ሲል ነው ግዳዬ!” እያሉ ነው ወዳንቺ የሸኙኝ፡፡”
ሴትየዋም ግራ በመጋባት፤ “እንዴ ባለፈው ጊዜ እዚያ ጫካ ሄጄ አሸንፌ መጣሁ አላልከኝም?” አለች ጥርጣሬዋ በግልጽ እየተነበበባት፡፡
“አ…ጫካው…ልክ ነሽ ያው ነው፡፡ ግን ጠላቶቼ፣ ….ሽፍቶቹ… ሌሎች ናቸው…”
ልቧ አልተቀበለውም፤ ግን ዝም ትለዋለች፡፡
አንድ ስድስት ወር አልፎ ሌላ ጊዜ መጣና፤
“እንደምን ከረምሽ? እኔ ጫካ ሄጄ ስንት ሽፍታ ዘርፌ ስመጣ፣ አንቺ የት ጠፋ ብለሽ እንኳ አልፈለግሽኝም?” ይላታል፡፡
ወዳጁም፤ “እንዴ ያንተ ጠላቶች አያልቁም  እንዴ? ይኸው በመጣህ ቁጥር ዘረፍኳቸው፤ ድባቅ መታኋቸው፣ ለቀምኳቸው ትለኛለህ?” ስትል የምሯን ተቆጥታ ትጠይቀዋለች፡፡
እሱም፤ “አይ እነዚህ የኔ ጠላቶች ሳይሆኑ የህዝቡ ጠላቶች ናቸው!” ይላታል፡፡
ሴትየዋ ጉራውና ውሸቱ በቅቷታልና፤ “በል ከዛሬ ጀምሮ እኔ ዘንድ ድርሽ እንዳትል፡፡ በየቦታው እየሄድክ እየቀበጣጠርክ ስላስቸገርክ፣ ቆርጦ-ቀጥል የሚል ስም እንዳወጡልህ ያልሰማሁ እንዳይመስልህ” ብላ በሯን ዘግታበት ወደ መኝታዋ ትሄዳለች፡፡ እሱም ተስፋ ቆርጦ ይወጣል፡፡
ሰነባብቶ አስታርቁኝ ብሎ የነፍስ አባትዋን አማላጅ ይልክባታል፡፡ ሴትየዋም ለነፍስ አባትዋ “ከእንግዲህ ወዲያ ከእሱ የምታረቀው፤ ይህን መዋሸቱን እንዲተው፤ ጠበል የሚረጩት ከሆነ ብቻ ነው!” ትላለች፡፡ የነፍስ አባትዋ በሃሳቧ ተስማምተው ሰውየው ዘንድ ሄደው፣ የውሸት ሰይጣኑንን እንዲያርቅለት ዳዊት ደግመው፣ ፀበል ከረጩ በኋላ፤ “በል ልጄ፤ አንድ ነገር ልንገርህ “ብልጥ ዋሾ፤ አምላኬ ሆይ! ውሸቴን አታስረሳኝ” ብሎ ይፀልያል!” አሉት፡፡
***
ከውሸትና ከዋሾ ይሰውረን ማለት የፀሎቶች ቁንጮ ነው፡፡ ከእርግማኑ አድነን እንደማለት ነውና፡፡  ስለ ዲሞክራሲ ውሸት፣ ስለ ሹም-ሽር  ውሸት፣ ስለ ሰላም ውሸት፣ ስለ ፍትህ ውሸት፣ ስለ ውስጠ-ፓርቲ ትግል ውሸት፣ ስለ ድል ውሸት፣ ስለ ታሪክ ውሸት፣ ስለ ዲፕሎማሲ ውሸት… ከመናገር ይሰውረን፡፡
የአንድ ሀገር የፖለቲካ ሂደት፤ ከተራ ቅጥፈት እስከ መረጃ ክህደት፤ ድረስ ከሄደ፤ እየዋለ እያደር “ሦስት የውሸት አይነቶች፡- ውሸት፣ የተረገመ ውሸትና ስታቲስቲክስ ናቸው” እንደሚባለው ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡
ልብ ብለን ካየነው ደግሞ፤ ማናቸውም የሀገራችን ፖለቲካ፤ አንዴ ውሸት፤ አንዴ እውነት እየተቀየጠ የሚመረትበት ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ በርካታ ነው፡፡ አልፍሬድ ፔንሰን እንዳለው፤ “አይኑን በጨው ታጥቦ፤ ሽምጥጥ የሚያደርግን ቀጣፊ  ፊት ለፊት ሙሉ በሙሉ በመጋፈጥ ይፋለሙታል፡፡ ከፊል እውነት ያለበትን ውሸት ግን መዋጋት አስቸጋሪ ነው፡፡”
እርግጥ ነው፤ ውሸትን ለማጋለጥ መቻል ሌላው መታደል ነው፡፡ ለአገርና ለህዝብ ትልቅ አስተዋጽኦ አለውና፡፡ በ1950ዎቹ በአንጎላና ኬፕ ቬርዲ ዋና የፖለቲካ ተዋናይና የነጻነት ታጋይ የነበረውና እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ከቅኝ ገዢዎች ጋር ሲፋለም የወደቀው አሚልካር ካብራል ስለ ታማኝነት ሲናገር፤ “ከህዝባችን ምንም ነገር አንደብቅ፡፡ ምንም አይነት ውሸት አንዋሽ፡፡ የተዋሹ ውሸቶችን እናጋልጥ፡፡ ችግሮችን አንሸፋፍን፡፡ ስህተቶችን ቀባብተን ትክክል አናስመስል፡፡ ለህዝቡ የስራችንን መልካም መልካሙን ብቻ አናውራለት፤ ውድቀታችንን አንደብቀው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ድል በቀላሉ ይገኛል ብለን አናስብ” ይለናል፡፡
የአሜሪካ ልብ ወለድ ደራሲና ጋዜጠኛ ኖርማን ሜይለርም፤ “በየቀኑ ጥቂት ጥቂት ውሸቶች የትውልድ ሀረጋችንን እንደምስጥ እየበሉ ያመነምኑታል፡፡ በጋዜጣ ህትመት ውጤት ትናንሽ ተቋማዊ ውሸቶች ይቀርባሉ፡፡ በዚያ ላይ የቴሌቪዥን አስደንጋጭ ሞገድ ይጨመርባቸዋል፡፡ ከዚያ ደግሞ የስሜትን ስስ-ብልት የሚያማስሉና የሚያታልሉ የፊልም ሰሌዳዎች ይደመሩበትና ሙሉ ውሸት ይሆናል” ይለናል፡፡
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ “እኔ በእነሱ ቦታ ብሆን እዋሽ ነበር ብሎ የሚያስብ ሰው፤ የባላንጣዎቹን እውነት መቀበል አዳጋች ይሆንበታል” እንዳለው፤ ሀያሲው የጋዜጣ አዘጋጅ ሜንከል፤ ብዙ እውነቶች ከውሸት ጎራ ተደምረው ሲወገዙ ማየትም ያዘወተርነው ፍርጃ ነው፡፡
በተጨማሪም፤ እንደሚታወቀው በየአገሩ ያሉ የፖለቲካ መሪዎች የመዋሸት ፍቃድ የተሰጣቸው ብቸኛ ፍጡራን የሚመስሉበት ጊዜም አለ፡፡ “አገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ የሀገር መሪዎች ለሀገሪቱ ደህንነት ሲሉ ይዋሹ ዘንድ ይፈቀድላቸው ይሆናል” እንዲል ፕላቶ፤ የጆሯችን ግዱ ያንን ማዳመጥ የሆነበት ወቅት አንድና ሁለት የሚባል አይደለም፡፡
ይህ የሆነው በአገራችን የፖለቲካ አየር ውስጥ እስከዛሬም ጠፍቶ ያለ አንድ ዋና ነገር አሁንም የጠፋ በመሆኑ ነው፡፡ ትናንት የተናገሩትን አሊያም የዋሹትን፣ ዛሬ አለማስታወስ እናም በተደጋጋሚ መዋሸት፡፡ መቅጠፍ፡፡ ማንም አይጠይቀኝም፣ ወይም ልብ- አይልም ብሎ መኩራራት፡፡ ይሄ ደግሞ ለዋሺም ለተዋሺም ጎጂ ባህል ነው፡፡ ውሎ አድሮም ህዝብ  ያልኩትን አያስታውስም አሊያም ለሱ ስል ነው የዋሸሁት ወደሚል ንቀትና ተአብዮ፣ ብሎም ወደ አምባገነንነት ሊመራ ችላል፡፡ “የረባ የማስታወስ ችሎታ የሌለው ሰው ከመዋሸት ቢታቀብ ይሻላል” የሚለው ገና በ15ኛው ክ/ዘመን ፈረንሳይ አገር የተነገረ ማስጠንቀቂያ ቢኖርም፣ እስከዛሬም ኢትዮጵያ የደረሰ አይመስልም፡፡
ያልሆንነውን ነን፣ ያላደረግነውን አደረግን ብለን መዋሸትና ራስን መገበዝ ፍፃሜው አያምርም፡፡
አንድ ልዑል መቃብር ላይ እንደተፃፈው ጥቅስ ማለት ነው፤
“ጀግና ነው ይሉታል ሣንጃ ሳይሞሸልቅ  
ጨዋ ነው ይሉታል ማላውን ሳይጠብቅ
ይህ ያገሩ ልዑል፣ ያገር ሙሉው ግዛት
በህይወቱ እያለ፣ አገር ምድሩ ጠልቶት፣
እዚያም እሰማይ ቤት-
ገነት ፍትህ ነሳው፣ ፊቱን አዞረበት፡፡”
እንዳንባል መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ቢያንስ “ብልጥ ዋሾ፣ አምላኬ ሆይ! ውሸቴን አታስረሳኝ ብሎ ይፀልያል የሚለውን አባባል አትርሳ” የሚለውን አለመዘንጋት ደግ ነው፡፡
ማርክ ትዌይንም በምፀት፣ “ውሸት መፀለይ አይቻልም፤ ያንን ደርሼበታለሁ” የሚለው ውሸት ከልብ የማይመነጭ መሆኑን ሲያስረዳን ነው፡፡ የማይዋሽ የፖሊቲካ ሰው ይስጠን!Read 278 times