Saturday, 15 June 2024 00:00

አጼ ኃይለስላሴ በ48ቱ የሥልጣን ህግጋት መነጽር

Written by  በደረጄ ጥጉ (የአለም አቀፍ ህግ መምህር)
Rate this item
(0 votes)

 “ራስ ተፈሪን አድንቋት እንጂ አትናቋት”
                                

          የሮበርት ግሪን “The 48 laws of power” መፅሐፍ በፖለቲካው አለም ልክ እንደእነ ሰንዙ The Art of War እና ማኬቬሊ The Prince ሁላ እንደ አንድ ቅዱስ መፅሐፍ የሚነበብ ነው፡፡ የሀሳብ አወራረዱና ደራሲው ሮበርት ግሪን 48ቱን ለስልጣን መሰረታዊ የሆኑትን ህግጋት ያጠናከረባቸው ምሳሌዎች፣ በተግባር ተፈትነው ያለፉ መሆናቸው መፅሐፉን ተመራጭና የቅድሚያ ተነባቢ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ሮበርት ግሪን በዚህ መፅሐፉ የፖለቲካ ስልጣንን በእጁ ማስገባት የፈለገና በዛውም የስልጣን ወንበር ላይ መፅናት የፈለገ ሊከተላቸው የሚገቡ ገንቢ ህግጋትንና መርሆዎችን ያብራራበትና የቀመረበት ነው፡፡ ለዛሬ በመረጥነው ርእሰ ጉዳይ ላይ ማለትም “ልታደርግ ያሰብከውን ነገር ለራስህ ሰውረህ ያዘው” በሚለው ህግ ላይ እናተኩራለን፡፡
እንደ ሮበርት ግሪን እምነት ከሆነ፤ ስልጣንን በእጅህ ማስገባት ከፈለክ ታማኝነትና ቅንነት የሚባሉትን ሰው የመሆን ፀጋዎች ወደዚያ ብሎ ማስወገድ ይገባል፡፡ ወይም እነዚህን ፀጋዎች ለአንተ ጥቅም በሚውሉበት መንገድ ተጠቀምባቸው እንጂ እነሱን የአንተ ፀጋዎች አታድርጋቸው፡፡ ቅን ምሰል ግን ቅን አትሁን፡፡ ልታደርግ የፈለከውን ሀሳብ ከሌሎች ሰዎች የመሰውርን ጥበብ ተማር፡፡ የራስን ሀሳብ ለራስ ሰውሮ የመያዝ ጥበቡን ተካነው፤ ይህን ካደረክ ምንግዜም የበላይነቱን የምትወስደው አንተ ነህ፡፡ ሰው በተፈጥሮው ተላላ ፍጡር እስከሆነ ድረስ ትክክለኛውን ማንነትህን ለማንም አታሳይ፡፡ ለሰዎች መስለህ እንጂ ሆነህ አትቅረባቸው፡፡ መምሰልን ለእውነት አሳስተው የሚረዱ ናቸውና ሰዎችን መጠቀሚያህ አድርጋቸው፡፡ እውነተኛ ውስጣዊ ባህሪህን ሳይሆን ውጫዊ መልክህን (ማለትም መስሎ የሚታየውን ባህሪን) ማመን የሰው ተፈጥሮ ነው፡፡ የምናየውንና የምንሰማውን ብዙ ጊዜ አንጠራጠርም፤ እውነት ነው ብለን እናምናለን፡፡ ከዚህ ጀርባ የተደበቀ አላማ አለ የሚለው ሀሳብ ላይ ማሰላሰልና ማውጠንጠን አድካሚ ስለሆነ ማንም ጊዜውን በዛ ላይ ማጥፋት አይፈልግም፡፡ ስለዚህ የማስመሰልንና ሀሳብን ደብቆ የመያዝን ጥበብ ተካንበት፡፡ ልታደርግ የፈለከውን ነገር መሰወሩ በጣም ያስፈልግሃል፤ ስለዚህም ጥበቡን ተማር፡፡ ወደምትፈልገው የስልጣን ደረጃ እስክትደርስ ወይም የምትፈልገውን ለማግኘት የማትፈለገው መስለህ ዥዋዥዌ ተጫወት፡፡ አስመስል፡፡ ስኬታማ የሚባለው ወጥመድ የማታምንበትን ሀሳብ የምትደግፍ መስለህ መቅረብ ነው፡፡ ወረድ ብለን የቢስማርክን እንዲህ ያለውን ጥበብ እናያለን፡፡ በዚህ ወጥመድ ሰዎችን ወደራስህ ሳብና ተጠቀምባቸው፡፡ የያዝከው አቋም ከአንተ እምነት ሙሉ በሙሉ ተቃራኒ ቢሆንም እንኳን እንደ ቢስማርክ በዘዴና በብልሀት ተጠቀምበት፡፡ ብዙሃኑ ሃሳብህ ተቀየረ ብለው ያምናሉ፡፡ እንዲህ ሆነ ማለት ደግሞ ጠላቶችህን በቀላሉ አሳሳትክ ማለት ነው፡፡ ሰዎች መንገድህ ላይ ደንቃራ እንዳይሆኑ እያደረካቸው ነው፡፡ እራስህን አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ ፍላጎትህን ደብቅ-ስለእውነተኛው እምነትህና ግብህ ሳይሆን ሰዎችን ሊማርክና ወደ አንተ ሊስብ ስለሚችል ጉዳይ በመናገር ሰዎችን አሳስታቸው፡፡ ይህንን ማድረግ ከቻልክ እንደ ሮበርት ግሪን እምነት፣ በአንድ ድንጋይ ሦስት ወፍ ገደልክ ማለት ነው፡፡ አንደኛ ለሰዎች ወዳጅ መስለህ ትታያለህ፤ ሁለተኛ ግልፅና የሚታመን ፍላጎትህን ትደብቃለህ፤ ሦስተኛ ባላንጣህን ጊዜን በሚበላ ፍላጎት አሞኘኸው ማለት ነው፡፡ በቀላሉ ድል አደረክ ማለት ነው፡፡ ነገር ሳታበዛ የምትናገረው ነገር ለመልእክትህ ክብደት ይሰጠዋል፡፡ ንቁ ሰዎች ከሌላ ሰው የሚገኝን እመነት በሚገባ በመጠቀም ወዳጆቻቸውን በቀላሉ ማስወገድ ችለዋል፡፡ ጠንቃቃ ነን ብለው የሚያስቡ በሙሉ በቀላሉ የሚታለሉ ግብዞች ናቸው፡፡ ተፈሪ በባልቻ ላይ ያደረገውን ከዚህ ወረድ ብሎ በሰፈረው ፅሁፍ ውስጥ እናነባለን፡፡ ሰዎች ለአንተ ያላቸውን ታማኝነት በአንድ ቦታ ማግኘትህን እርግጠኛ ስትሆን በሌላው ቦታ እይታቸውን የሚጋርድ ጭጋግ ፍጠር፡፡ እንዲህ ማድረግ በተስተካከለ ቦታ ላይ ቆመህ ተቀናቃኞችህን በካልቾ እንድትመታቸው ያስችልሀል፡፡ ከዚህ
በላይም በታችም የሰፈረው ፅሁፍ ሮበርት ግሪን “The 48 laws of power” መፅሐፍ ላይ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠውን የስልጣን ህግ (conceal your intenetions) አስረጅ ሆነው የቀረቡትን፣ የሀገራችንን የቀድሞ ንጉሰ ነገስት ኃይለስላሴንና የጀርመኑን ሀያል ሰው ቢስማርክ፣ ሀሳብን ለራስ ሰውሮ የመደበቅ ጥበብን እንመለከታለን፡፡
ልታደርግ ያሰብከውን ነገር ለራስህ ሸሽገህ ያዘው
(conceal your intentions)
በ1927 (እ.ኤ.አ) ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ ታላላቅ የኢትዮጵያ የጦር አበጋዞችና መኳንንት ወደ ስልጣን ኮርቻው የተቃረበውን ተፈሪን እውቅና ሲሰጡና ታማኝነታቸውን ሲያስመሰክሩ የሲዳሞ አገረ ገዢ የነበረው ባልቻ አባ ነፍሶ ግን በእንቢታው ፀና፡፡ ባልቻ አባ ነፍሶ ተፈሪን ደካማና ሰነፍ ነው ብሎ ስለናቀው እውቅና ሊሰጠው አልፈለገም፡፡ ተፈሪ ቁጡውንና እልኸኛውን ባልቻን ፊት ለፊት በጦር ድል ለማድረግ የሚጠይቀውን አላስፈላጊ መስዋዕትነት ሊተገብረው ስላልፈለገ፣ ባልቻን በሌላ ረቂቅ ዘዴ እውቅና እንዲሰጠው ፈለገ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደተስተዋለው ባልቻ ኃይለስላሴን የማይረባና ደካማ ብሎ የሚንቅ ሰው ነበር፤ ግንኙነታቸውም በአብዛኛው ሻካራ ነበር፡፡ ስክነቱን፤ ዝግ ያለውን አካሄዱን ፤በአካላዊ ቅርፁ ኮስማና መሆን ምክንያት ነበር ባልቻ ተፈሪን የሚንቀው፡፡ የአብዛኛዎቹን የጦር አበጋዞች ይሁንታና ድጋፍ ካገኘ በኋላ፣ ተፈሪ በቤተመንግስት ድግስ አሰናድቶ ባልቻን የግብዣው ታዳሚ እንዲሆን መልእክት ላከበት፡፡ ባልቻ የተፈሪን ግብዣ በአዎንታ ተቀበለው፡፡ ለማንኛውም ግን ጦርነት ወይም ችግር ቢነሳ ብሎ ስለጠረጠረ ባልቻ 10000 የሚጠጋ ጦሩን አስከትሎ ወደ ግብዣው ቦታ እንደሚመጣ ለተፈሪ አስቀድሞ አስታወቀ፡፡ ከብዛቱና ከታጠቀው መሳሪያ አንፃር ይህ ጦር ብቻውን የእርስ በእርስ ጦርነት መቀስቀስ የሚችል ነበር፡፡ ከተፈሪ የይሁንታን ቃል ስላገኘ ባልቻም ይህን ቁጥሩ የበዛውን ጦሩን ይዞ ወደ ዋና ከተማዋ ጉዞውን አደረገ፡፡ ጦሩንም ከዋና ከተማዋ 3 ማይል ርቀት ላይ እንዲሰፍር አድርጎ በካምፕ ተቀመጡ፡፡ ወጥመድ ሊኖር ይችላል የሚለውን አርቆ ተመልካችነታቸው እንዲታወቅላቸው በሚመስል መልኩ ባልቻ ወደ ግብዣው የሚመጣው ብቻውን ሳይሆን ከ10000 ጦሩ ውስጥ 600 ጠንካራ የሚባለውን የግል ጠባቂዎቹን ይዞ እንደሆነ ለኃይለስላሴ በድጋሜ አሳወቀ፡፡ ኃይለስላሴም ሀሳብ አይግባህ “የባልቻን አጃቢ ተቀብሎ ማስተናገድ ክብሬ ነው” ሲል መልእክት ላከ፡፡ ተፈሪ በቤተ መንግስቱ በክብር እንደሚያስተናግዷቸው በማሳወቅ ባልቻ ከነአጃቢ ጦሩ ወደ ግብዣው እንዲመጣ ለመኑት፡፡ ባልቻም 600 የሚሆኑትን አጃቢዎቹን አስከትሎ ወደ ግብዣው አቀና፡፡ ባልቻ ለቤተመንግስቱ ልማድ ቅርብ እንደመሆኑ መጠን የቤተመንግስትን የተንኮልና ጠልፎ የመጣል ዘዴን ጠንቅቆ የሚያውቅ ነበረና ወጥመድ እንኳን ቢኖር ቶሎ ወጥመድ ውስጥ መውደቅ አልፈለገም፡፡ የጥንት ነገስታት የሚገዳደራቸውን ወይም ስጋት ነው ብለው ያሰቡትን የሚያስወግዱበት አንዱ መንገድ የቤተመንግስት እራት ግብዣን በማሰናዳት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ባልቻም በወጥመድ ላለመጠለፍ ሲል ግብዣውን መቀበሉን ማሳወቁ፡፡ ሆኖም ወደ ግብዣው የሚሄደው 600 የግል ጠባቂውን ጦር ይዞ እንደሆነ ማሳወቁ፡፡ እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ እንደሚባለው፣ ኃይለስላሴም የባልቻን ጥርጣሬ ተረድቶ ይህን ጦር ተቀብሎ ማስተናገድ ክብሩ እንደሆነ ለባልቻ መልእክት መላኩ፡፡ ባልቻ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ደርሶ ወደ ግብዣው ከመሄዱ በፊት ከከተማው በ3 ማይልስ ርቀት ላይ ለሰፈረው ቀሪ ጦሩ “ምንም አይነት አልኮል እንዳይቀምሱና ነቅተው እንዲጠብቁ አስጠንቅቆ” ነበር፡፡ ባልቻ በግብዣው ቦታ ሲደርስ ኃይለስላሴ በክብር ደጅ ድረስ ወጥቶ ተቀበለው፡፡ ይህ ቢሆንም ባልቻ የሚከተለውን መልእክት ለተፈሪ አሳሰበ፡፡ “ከግብዣው በኋላ ወደመጣበት በሰላም የማይመለስ ከሆነ በከተማዋ ዙሪያ የሰፈረው ጦሩ ከተማዋን እንዲያጠቃ ትእዛዝ መስጠቱን” ባልቻ ተናገረ፡፡ ተፈሪ፤ ባልቻ በእሱ ላይ የያዘው ጫፍ የወጣ ጥርጣሬው እንዳሳዘነው በሀዘኔታ ተናገረ፡፡ ተፈሪም እስከዚህም ድረስ ሃሳብ አይግባህ ብሎ ወደ ግብዣው ቦታ ተያይዘው ገቡ፡፡ በግብዣው መሀል ኃይለስላሴ ወደ ባልቻ ጠጋ ብሎ ይህን የመሰለ ግብዣና ድግስ ያሰናዳው የባልቻን እርዳታውንና ድጋፉን ፈልጎ እንደሆነ ነገረው፡፡ ባልቻ ለኃይለስላሴ የነበረው ግምት እስከዚህም ስለነበር ይህንን እንደማያደርግ በድጋሚ አሳወቀ፡፡ በባልቻ እምነት ኃይለስላሴ ለኢትዮጵያ አይመጥንም፡፡ ኃይለስላሴ በሚታወቅበት ትሁት ሳቁና በሚያባብል ትህትና፣ ባልቻን በሚገባ በክብር አስተናገደው፤አያይዞም የግብዣው አድማቂዎች ለነበሩት አዝማሪዎች ይህን የሲዳሞ ገዢ ብቻ በታላቅ ክብር እንዲያወድሱ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ የአዝማሪው ጨዋታና ፉከራው ሁሉ ባልቻን ሲያወድስና ሲያሞግስ ዋለ፡፡ እንዲህ በማድረግ የባልቻን ልብ መስረቅ እንደሚቻል እሙን ነበር፡፡ ቢሆንም ይህ አይነት መተናነስ በተቃራኒው ለባልቻ የልብ ልብ ሰጠው፡፡ ኃይለስላሴ እስከዚህ ድረስ እንደፈራውና በባልቻም የጦር ጥንካሬ እንደተርበደበደ አመነ፡፡ ቀጣዩን የሀገር መሪ የሚሾመው እሱ እንጂ ሌላ ማንም እንዳልሆነ እያሰበ ፈገግ አለ፡፡
የቤተ መንግስቱ ግብዣ በሰላም ተጠናቆ ባልቻም 600 ጦሩን አስከትሎ አደራ ወዳላቸው  ቀሪ የጦሩ አባላት፣ በሆታ፤ ፈንጠዝያና በተኩስ ደምቆ በመመለስ ላይ ሳለ፣ አንድ ጊዜ ከተማዋን ዞር ብሎ ቃኝቶ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ እንዴት እንደሚያጠቃትና እንደሚወራት፤ ኃይለስላሴንም ወይ ወደ ግዞት ወይ እስከ ወዲያኛው እንዴት  እንደሚያስወግደው ማሰላሰል ያዘ፡፡  ሆኖም ባልቻ ጦሩ የሰፈረበት ካምፕ ሲደርስ ክው ብሎ ቀረ፡፡ በከባድ ድንጋጤም ተመታ፡፡ እንኳን በእውኑ በህልሙ እንኳን ይሆናል ብሎ ያልገመተው ደርሶ ተመለከተ፡፡ እንዲህ አይነት ውርደትን ከመመልከት ምድር ተሰንጥቃ ብትውጠው ሳይወድ አይቀርም፡፡ የተበላሸ ነገር እንዳለ ጠረጠረ፡፡ ጦሩ በሰፈረበት ቦታ ከተዳፈነ እሳት የሚነሳ ጭስ እንጂ ሌላ ምንም አይታይም ነበር፡፡ በምን አስማት እንዲህ አይነት ውርደት ሊደርስ እንደቻለ ሊገባው አልቻለም፡፡ በቦታው ሆኖ የደረሰውን መአት የተመለከተ የአይን እማኝ የሆነውን ሁሉ ለባልቻ በሚከተለው መልክ አስረዳ፡፡ ባልቻ የንጉሱን ግብዣ በሚታደምበት ሰአት የሀይለስላሴ ጦር በሌላ አቅጣጫ ተጉዞ የባልቻ ጦር ያረፈበት ካምፕ ደረሰ፡፡ የጦሩ አመጣጥ ለውጊያ ሳይሆን የባልቻን ጦር ትጥቅ ለማስፈታት ነበር፡፡ ውጊያ ቢነሳ የባልቻ ጦር የተኩስ ድምፅ በመስማት ወደ ውጊያ እንደሚገባ የጠረጠረው ኃይለስላሴ፤ ሌላ ማንም የማይገምተውን ረቂቅ ስልት ተከተለ፡፡ የኃይለስላሴ ጦር በቦታው የደረሰው ጠመንጃን ታጥቆ ሳይሆን ወርቅና ብር የተሞላ ጆንያ ተሸክሞ ነበር፡፡ የኃይለስላሴ ጦር በያዘው ብርና ወርቅ የባልቻን ጦር መሣሪያ ይገዛው ጀመር፡፡ አንዳንዶች ቢያንገራግሩም በወርቅ የሚጨከን ልብ አልነበራቸውም፡፡ በወርቅና በገንዘብ ተረቱ፡፡ በጥቂት ሰአታት ውስጥ የባልቻ ጦር ሙሉ በሙሉ ትጥቁን ፈትቶ ባዶውን በተለያየ አቅጣጫ ተበታተነ፡፡ በከፍተኛ ድንጋጤና ሀዘን ስሜት ውስጥ ሆኖ ከአይን እማኙ የሰማውን አሳዛኝ መርዶ ተከዘበት፡፡ ከዚህ በኋላ ባልቻ ወደ ምእራብ አቅጣጫ 600 ወታደሩን ይዞ ዳግም ለመደራጀት ተንቀሳቀሰ፡፡ ጦሩን ትጥቅ ያስፈታበት ያው የኃይለስላሴ ሰራዊት መንገዱን ዘጋበት፡፡ የቀረው ብቸኛ መንገድ ወደ ዋና ከተማዋ መመለስ ነበር፡፡ አሁንም ኃይለስላሴ የተደራጀ ጦር አዘጋጅቶ መንገድ ዘጋበት፡፡ እንደ ቼዝ ተጫዋች እያንዳንዱን የባልቻ አካሄድ ኃይለስላሴ ቀድሞ ገምቶት ነበር፡፡ በቃህ አለው፡፡ ጨዋታው አበቃ ነው መልእክቱ፡፡ ከዚህ በኋላ አጉል መንፈራገጥ ለመላላጥ መሆኑን የተረዳው ባልቻ፤ በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይታኮስ እጁን ሰጠ፡፡ አያይዞም የእድሜ ዘመኑን ሀጥያት ስርየት ሊሰጠው ቀሪ ዘመኑን በገዳም ለማሳለፍ ገዳምን ምርጫው አደረገ፡፡
ኃይለስላሴ ትሁት አቀራረቡን፤ አሳሳችና አዘናጊ ሳቁን ጋሻ አድርጎ፣ ባልቻን ያለምንም የጥይት ተኩስ በወጥመዱ ውስጥ ጣለው፡፡ እያሱን፤ ዘውዲቱንና ታላላቆቹን የጦር አበጋዞች ድል ያደረገውና ከጨዋታ ውጪ ያደረገው በዚህ ጥበቡ ታግዞ ነው፡፡ ተፈሪ እድሜ ዘመኑን በሙሉ ውስጡ የማይታወቅ ሰው ነበር፡፡ አባ መላ (ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ)፤ “ ተፈሪ የዋዛ ሰው አይደለችም፡፡ በአንዳንድ ነገሩ የአባቱ የራስ መኮንን ጠባይ አለው፡፡ በአንዳንድ ነገሩ ደግሞ ተንኮለኛ ነው፡፡ እኔም ሴረኛነቱን ደህና አድርጌ ተረድቻለሁ፡፡ ፊት ለፊት ባለው በር ይመጣል ብለው ሲጠብቁት በጀርባ ቀድሞ ቦታ ይዞ ይገኛል፡፡ ተፈሪ ደካማ ካጋጠመው በቀጥታ ማጥቃቱ፤ ከጠነከረበት ደግሞ በተንኮል መውጋቱ የማይቀር ነው” ብለው ነበር፡፡ ለዛም ነው በተፈሪ መበለጣቸውን ባመኑበት ወቅት፤ “ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ቆመን ማውረድ አቃተን” ያሉት፡፡ የኃይለስላሴ ጥንካሬ ያለው በእንደዚህ አይነት ጥበቡ ላይ ነው፡፡ ባልቻ ገዳም ከመግባቱ በፊት የተናገረው የመጨረሻ ቃሉ፤ “የተፈሪን ጡንቻ አትናቋት፡፡ እንደ አይጥ ፈሪ መስላ ብታደባም፤ ጥርሷ ግን የአንበሳ ነው” (don’t underestimate the power of Tafari. He creeps like a mouse but he has jaws like a lion.)
ኃይለስላሴ ኮራ ያለ፣ ሰላም ወዳድና ርህሩህ ፊቱን በማሳየት ረዘም ላሉ አመታት ለመግዛት ቻለ፡፡ ንዴቱን ሁሉ ዋጥ አድርጎ ትዕግስቱን በሚገባ ተቆጣጥሮ፣ ሀሳቡን ከተቀናቃኞቹ ደብቆ ጠላቶቹን በሙሉ በሳቅ እየተቀበለ አስወገዳቸው፡፡ መንግስቱ ሀይለማሪያም፤ “ለምሳ ሲያስቡን ቁርስ አደረግናቸው” ያለው እንዲህ ያለውን ጥበብ ተጠቅሞ ነው፡፡ በ1850ዎቹ በከባድ የህልውና አደጋ ፈተናዎች የተከበበች ሀገር ብትኖር አውሮፓዊቷ ጀርመን ነበረች፡፡ የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ብዙ ሀገራት ፕራሽያን ጨምሮ በሰአቱ ተከፋፍላ የነበረችው ጀርመን ጋር መዋሃድ አለብን ሲሉ፤ የጀርመንን መከፋፈልና መዳከም አብዝታ የምትፈለገው ኦስትሪያ፣ ጀርመን ላይ የደቀነችው የጦርነት ስጋት ነበር፡፡ ውህደት የሚኖር ከሆነ ጦርነት መጀመሩም እንደማይቀር ኦስትሪያ አስጠነቀቀች፡፡ በዚህም ምክንያት የጀርመን ህልውና አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ነው ውልደቱ ከፕራሽያ፣ እድሜውም 25 አመት የሆነው ወጣት ቢስማርክ ወደ ፖለቲካው መድረክ ብቅ ያለው፡፡ በጊዜው ቢስማርክ የፕራሽያ ፓርላማ ምክትል ፕሬዚዳንት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ከፕራሽያ ንጉስ ቀጥሎ የሀገሪቱ ሁለተኛ ሰው የሆነው ልኡል ዊልያም ፕራሽያ፣ ከኦስትሪያ ጋር በአስቸኳይ ጦርነት ማካሄድ አለባት ብሎ አጥብቆ ተከራከረ፡፡ ፓርላማውም አበጀህ አለው፡፡ ፓርላማው የእሱን ድምፅ ደግፎ በጭብጨባ አስተጋባ፡፡ የዚህ ጦርነት ብቸኛ ተቃዋሚዎች ሆነው የቀረቡት ፈሬደሪክ ዊሊያም አራተኛና የእሱ ሚኒስትሮች ነበሩ፡፡ ሀያሏን ኦስትሪያ በጦርነት ሳይሆን በማባበል መያዝ ይበጃል በሚል መነሻ ምክንያት፡፡ ፈሬደሪክ ዊሊያም አራተኛ በተፈጥሮው ሰላም ወዳድ እንደሆነ በሀገሩ ሰዎች የታወቀ ነበር፡፡ ነገሮችን በስክነትና በጥሞና የሚመለከት ሰው ነው፡፡ ቢስማርክ በወጣትነቱ ሀገሩን በታማኝነትና በታታሪነት ያገለገለ ቁርጠኛ ወታደር ነበር፡፡ ሀገሩ ፕራሽያ ሃያልና ጠንካራ ሆና እንድትወጣ በከባድ ወኔ ያገለገለም ሰው ነው፡፡ በመጨረሻ ስልጣኑን ከመያዙ በፊት ሀገሩን በወታደርነት በፈለገችው ግዳጅ ሁሉ በቁርጠኝነትና ታማኝነት አገልግሏል፡፡
 ቢስማርክ የጀርመን ውህደትና አንድነት ደጋፊ የነበረ ሲሆን፤ ኦስትሪያ ከጀርመን መከፋፈልና ደካማ መሆን ጀርባ በመሆኗ መዋረድ አለባት ብሎ ያምን ነበር፡፡ ከኦስትሪያ ጋር ጦርነት መግጠም አለብን ብሎም ያምን ነበር፡፡ ለሀገር ክብርና ልእልና ሲባል የሚደረግ መስዋእትነትን ከሁሉ በላይ የተቀደሰ ተግባር ነው ባይ ነበር፡፡ የሀገሩን አንድነት ከማትፈልገው ኦስትሪያ ጋር በመዋጋት የሀገሩን አንድነት ማስጠበቅን ከልቡ ቢያመንበትም፣ ይህንን እምነቱን በጊዜው ለገበያ አላቀረበውም፡፡ ለማንም አላሳወቀም፡፡ እምነቱን ከሁሉም ሰውሮ ለራሱ ብቻ ያዘ፡፡ ልኡል ዊልያምና ብዙኃኑ የፓርላማ አባለት ጦርነት እንጀምር የሚለውን ሃሳብ በሚያራምዱበት ጊዜ ነበር ቢስማርክ ንግግር እንዲያደርግ የተጋበዘው፡፡
ከላይ እንዳልነው ከኦስትሪያ ጋር ጦርነት መደረግ አለበት ሲል የነበረው ያው ቢስማርክ ነው የሚከተለውን ያለው፡፡ አስደናቂ ንግግሩ እንዲህ ይላል፡- “አሁን ያለንበት ወሳኝ ጥያቄ መልስ የሚያገኘው በንግግርና በድምፅ ብልጫ ውሳኔ ሳይሆን በደምና በጦር መሳሪያ ነው፡፡” ፓርላማው በጭብጨባ ድጋፉን ሰጠው፡፡ ሁሉም እንደሚያውቁት ቢስማርክ ከዚህ የተለየ ሃሳብ ሊያራምድ አይችልም፡፡ ከዚህ በማስከተል ያደረገው ንግግር ግን ማንም ያልጠበቀው ነበር፡፡ “ወየውለት ያለበቂ ዝግጅትና አሳማኝ ምክንያት ጦርነትን ለሚቀሰቅስ መሪ፡፡ እንዲህ አይነት መሪ በጦርነቱ ፍፃሜ ሽንፈቱን ለመሸፈን የጦርነቱን ፍትሃዊ ምክንያት ለማስረዳት አጉል ሲደክም አየዋለሁ፡፡ ዛሬ እዚህ የተሰበሰባችሁት ለሚከተሉት ጥያቄዎቼ ምላሻችሁ ምን እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ ተስፋ ጥሎበት ሲያርስው የነበረው የእርሻ መሬት በጦርነት እሳት ተለብልቦ ወደ አመድነት የተቀየረበት ገበሬ መንደር፤ በጦርነቱ እግሩ ተቆርጦ አካለ ጎዶሎ የሆነው ጎበዝ ወታደር፤ ልጆቹን በጦርነት ተነጥቆ ባዶውን ወደቀረው አባት ቤት ሄዳችሁ የምትቆሙበት ሞራል ይኖራችኋልን?“ ሁሉም ዝም አሉ፡፡ ይህ ከቢስማርክ አንደበት  ይወጣል ብሎ የጠበቀ ይቅርና የጠረጠረም አልነበረም፡፡ ከሀገር በላይ ምን አለ? በዝምታቸው ላይ የጦርነትን አውዳሚነት ብቻ ሳይሆን ጦርነት እብደት ጭምር እንደሆነም አስገነዘባቸው፡፡ ንግግሩን አያይዞ በመቀጠል በብዙኃኑ ፕሩሻውያንና ሹማምንት፣ የፕራሽያ የህልውና አደጋና ጠላት ተብላ የተፈረጀችውን ኦስትርያን በብዙ አደነቃት፤ አቋሟንም ፍትሃዊ ነው ሲል አደነቀ፤ እርምጃዋም ትክክል ነው ሲል አከለበት፡፡ ይህ የቢስማርክ ንግግር ማንም ያልጠበቀው ከመሆኑ የተነሳ ሁሉን ግራ መጋባት ላይ ጣለው፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው ቢስማርክ ታላቅ አርበኛና ለሀገሩም ታላቅ ፍቅር የነበረው ሰው መሆኑን ነው፡፡ በእሱ አፍ እንዴት ጠላት ሊወድስ ይችላል? ሌላዋን ሀገር ጀርመን በክፉ ኮነናት፤ ጀርመን ፕራሽያን የግዛቴ አካል አድርጋለሁ ብላ ማሰቧን የማይሆን ቅዠት ነው ሲል ተሳለቀበት፡፡ ይህ ሁሉ በኋላ እንደምናየው የቢስማርክ እውነተኛ እምነቱና አቋሙ አልነበረም፡፡ እሱ እምነቱ ሌላ ነው፡፡ ፓርላማው ላይ ባደረገው ንግግር ተቃውሞና ውግዘት ቢደርስበትም፣ ቀስ በቀስ የንጉሱንም ፓርላማ አባላት ልብን መግዛት ቻለ፡፡ ቀስ አድርጎም ወጥመዱ ውስጥ አስገባቸው፡፡ ቢስማርክ ፓርላማው ያስተጋባውን የጦርነት ፉጨት አበረደው፡፡

Read 150 times