Saturday, 15 June 2024 00:00

እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት በኢትዮጵያ . . .

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ከዚህ ቀደም በነበረው እትም ስለ ራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ምንነት እና በውስጡ ስለሚገኙ የህክምና አይነቶች ለንባብ ማቅረባችን ይታወሳል። የዚህን ቀጣይ ክፍል ከማስነበባችን አስቀድሞ የ1 ሰው ልምድ እናካፍላችሁ።
“ነብዩ ዳዊት እባላለው። ሃይማኖቴ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት እንድንጠቀም ስለማይፈቅድ እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ ተጠቃሚ አይደለንም። አንድ ጊዜ ግን ከባድ ነገር አጋጠመን። እናቴ ባለባት ህመም ምክንያት እንዳታረግዝ ተነግሯት ነበር። ነገር ግን እርግዝና ተፈጠረ። እናም ፅንሱ ወረደ። ወደ ህክምና ተቋም መሄድ አልፈለገችም። ሲመስለኝ እንዳታረግዝ ተነግሯት ስለነበር ሀፍረት ተሰምቷት ነው መሄድ ያልፈለገችው። በዛ ላይ እናቴ ሀኪም ቤት መሄድ የምትወድ ሰው አይደለችም። እናቴን የመንከባከብ ሀላፊነት እኔ ላይ ወደቀ። ኢንተርኔት ላይ መረጃዎችን አየሁ። እና የማውቀውን ሀኪም አማከርኩ። በዚህም እናቴ እንድታገግም ማድረግ ቻልኩ። ከተሻላት በኋላ የህክምና ተቋም ይዣት ሄድኩ እና ሙሉበሙሉ ደህና ሆነች። እኔ በቻልኩት አቅም ባልንከባከባት ኖሮ እናቴ የከፋ በሽታ ውስጥ መግባቷ አይቀርም ነበር። ብቻ እራስን ማሳመን ነው እንጂ ምንም ነገር ማድረግ ይቻላል። ለእራሳችን እና በዙሪያችን ላሉ ሰዎች ጤና በቅድሚያ ተጠያቂዎቹ እኛው ነን።”
 ነብዩ ዳዊት ከአጠና ተራ
የኢትዮጵያ ጤና ሚንስቴር ብሄራዊ እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት መመሪያ (National selfcare guideline) ይፋ አድርጓል። ይህንን አስመልክቶ ግንቦት 13 እና 14 ቀን 2016 ዓ.ም የጤና ሚንስቴር፣ የኢትዮጵያ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ማህበር እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቢሾፍቱ ከተማ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በጤና ሚንስቴር እናቶች፣ ህፃናት እና አፍላወጣቶች የጤና አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ የእናቶች ጤና ፕሮግራም ዴስክ ሀላፊ የሆኑት ሲስተር ዘምዘም መሀመድ በመድረክ ላይ እንደተናገሩት እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት በኦሮሚያ፣ አማራ እና ሶማሊ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ተግባራዊ[ሙከራ] እየተደረገ ይገኛል።
እ.ኤአ በ2016 በተደረገ ጥናት መሰረት 49.8 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በገጠር አከባቢ የሚኖሩ እና ያልተማሩ ናቸው። ሲስተር ዘምዘም እንደተናገሩት የህክምና አገልግሎቱን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ላይ በተማሩ እና ባልተማሩ ሰዎች መካከል ልዩነት አለ። ስለሆነም አገልግሎቱን ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ማህበረሰቡን ማስተማር እና ብቁ ማድረግ ከቀዳሚ ስራዎች ውስጥ ነው።
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አቸንፍ አስማማው እንደተናገሩት ለእራስ የሚሰጥ ህክምና በኢትዮጵያዊያን ዘንድ በባህላዊ መንገድ ሲተገበር የቆየ ነው። አዲስ ጉዳይ [የህክምና አገልግሎት] አይደለም። “ሰው ጉንፋን ሲታመም አጥሚት መውሰድ የተለመደ ነው። ይህም ህክምና ነው” ብለዋል ዶ/ር አቸንፍ አስማማው። ስለሆነም በልማድ[ባህላዊ] ይሰጥ የነበረው ህክምና ዘመናዊ በሆነ መንገድ እና ከህክምና ባለሙያ ድጋፍ ጋር [የህክምና ስርአትን በመከተል] ይሰጣል።
ብሄራዊ የእራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት መመሪያ እንዳስቀመጠው አገልግሎቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ነው ተደራሽ የሚሆነው። ተንቀሳቃሽ ስልኮች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። “ስለ ራስ አገዝ ህክምና ትምህርት ለማግኘት ቴክኖሎጂን መጠቀም ያስፈልጋል” ብለዋል ዶ/ር አቸንፍ አስማማው። እንዲሁም ከህክምና ባለሙያ ጋር መልዕክት በመፃፃፍ እና በመደዋወል አገልግሎቱን መጠቀም እንደሚቻል ዶ/ር አቸንፍ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተጠቃሚዎች እርስበርስ በመማማር (በመረዳዳት) አገልግሎቱ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ። ይህ መረዳዳት (መማማር) ቴክኖሎጂ መጠቀም ለማይችሉ ሰዎች ድጋፍ ይሆናል።
ብሄራዊ ራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት መመሪያ ላይ አገልግሎቶቱን ለማጠናከር የተቀመጡ መንገዶች
ስለ እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ግንዛቤ መፍጠር
መረጃ እና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶች የሚገኙበት ሁኔታዎችን ማመቻቸት (ማሳደግ)
አገልግሎቱ የሚሰጥበትን መንገድ ማጠናከር
በሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ላይ ያለውን ክትትል እና ቁጥጥር ማጠናከር
የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው ማድረግ (ማጎልበት)
አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው እኤአ በ2030 18 ሚሊዮን የሚሆን የህክምና ባለሙያ እጥረት እንደሚያጋጥም እንዲሁም ወደ 130 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ይገመታል። ስለሆነም የሰዎች የእራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ችግሩን ለመቀነስ ይረዳል። “ለምሳሌ ፓራሲታሞል መድሃኒት ለመጠቀም ሰዎች ሆስፒታል ሄደን እንመርምር አይሉም። የመድሃኒት መሸጫ ሱቅ ሄደው ይገዛሉ። ራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ላይም ይህ እንዲፈጠር ነው የሚፈለገው። ተጠቃሚው ስለ ጤናው እና ስለሚወስደው ህክምና በቂ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል” በማለት ዶ/ር አቸንፍ አስማማው ተናግረዋል። ይህም ተጠቃሚዎች ለእራሳቸው ህክምና በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ የሚተገበር ሲሆን የህክምና ተቋም በመሄድ የሚያባክነው ጊዜ እና ገንዘብ እንዲቆጠብ ያደርጋል። እንዲሁም ያለውን የህክምና ተቋም እና ባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ ይረዳል።
ራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ላይ ያሉ መሰናክሎች
የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ በቂ እውቀት አለመኖር
አጠቃቀም ላይ ችግር ይኖራል (ስህተት ይፈጠራል) የሚል ፍራቻ
ገንዘብ ለሌላቸው ሰዎች አይሆንም የሚል እሳቤ
ያለ ህክምና ባለሙያ እገዛ ሙሉበሙሉ ለእራስ ህክምና ለማድረግ ማሰብ እና መሞከር (ባለሙያ እንደሚያስፈልግ ማሰብ)
ሀሳባቸውን ካከፈሉን ሰዎች መካከል ወ/ት ሀረግ ማሞ አንዷ ናት። እንደ ሀረግ ትዝብት ስለ ስነተዋልዶ ጉዳዮች መነጋገር የተለመደ አይደለም። በዚህ ዙሪያ ሰዎች በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ለእራስ የሚሰጥ የህክምና አገልግሎት [ስርአት] ተግባራዊ ከተደረገ ችግሩን እንደሚፈታ ወ/ት ሀረግ እምነት አላት። ወ/ት ሀረግ ማሞ ተስፋ ያደረገችው አገልግሎቱ በቂ እውቀት ከመስጠቱ በተጨማሪ ወደ ህክምና ተቋም ለመሄድ እና አገልግሎቱን ለማግኘት የሚኖረውን ፍራቻ ያስቀራል በሚል ነው።
“የስነ ተዋልዶ የህክምና አገልግሎቶችን እጠቀማለው። እርግዝና የተከታተልኩት፣ የወለድኩት እና ልጄ ህክምና የሚከታተለው ጤና ጣቢያ ነው” ያሉት ወ/ሮ መቅደስ ስንታየሁ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ወ/ሮ መቅደስ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሆኑ እና የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ እንዳደረጉ ተናግረዋል። ወ/ሮ መቅደስ እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ጠቃሚ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ይህም ወደ ህክምና ተቋም የሚደረግ አላስፈላጊ ምልልስን ይቀንሳል ብለዋል። እንዲሁም በተለይ የማህፀን ጫፍ ካንሰር፣ ኤች አይቪ ኤድስ እና መሰል ምርመራዎችን በቤት ውስጥ ማድረጋቸው ምቾት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ሌላኛው ሀሳባቸውን ያካፈሉን አቶ ካሳሁን ማሙሽ የ50 ዓመት ጎልማሳ ናቸው። አቶ ካሳሁን እንደተናገሩት ቀለል ያሉ ህመሞች በቤት ውስጥ ህክምና ቢደረግላቸው የተሻለ ነው። ከበድ ያለ ከሆነ ግን የህክምና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል። “ቀለል ያለ ከሆነ በሀኪም ምክር ቤት ውስጥ እራስን መንከባከብ ጥሩ ነው። ከበድ ካለ ግን ስለጤናው የሚያውቁ ሀኪሞችን ማማከር ተገቢ ይመስለኛል” ብለዋል አቶ ካሳሁን ማሙሽ።
ብሄራዊ ራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት መመሪያ ሲወጣ ከሌሎች ሀገራት ጋር ልምድ ልውውጥ ተደርጓል። በተለይም ከናይጄሪያ ጋር የልምድ ልውውጥ መደረጉን ዶ/ር አቸንፍ አስማማው ተናግረዋል። ናይጄሪያ ያላት የህዝብ ቁጥር ብዛት እና የህዝቦቿ አኗኗር ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ነው ቅድሚያ ሊሰጠው የቻለው። “እንደ አጋጣሚ ሆኖ ናይጄሪያን አውቀዋለው። ከ5 በላይ በናይጄሪያ ኖሬያለው። በባህል እና በተለያዩ ነገሮች ተመሳሳይነት አለን” ብለዋል ዶ/ር አቸንፍ አስማማው። ናይጄሪያውያን በስነተዋልዶ ጤና ላይ ከራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት ውስጥ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን (የወሊድ መቆጣጠሪያ) ቅድሚያ በመስጠት እየሰሩበት ይገኛሉ። በኢትዮጵያም ቅድሚያ የሚሰጣቸው የእራስ አገዝ የህክምና አገልግሎቶች ቢኖሩ የተሻለ እንደሚሆን የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል።
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አቸንፍ አስማማው ተጠቃሚዎች ስለ እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት በቂ እውቀት አግኝተው ከህክምና ባለሙያ አስፈላጊውን ድጋፍ እየወሰዱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

Read 80 times