Saturday, 15 June 2024 00:00

ሚስቴ አረጀችብኝ…

Written by  በኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(1 Vote)

ጊዜው እንዴት ነው የሚሄደው፡፡ … ጊዜ …፡፡  ምን የሚሉት ነገር ነው፡፡ ውስጡ ውጭው የማይታወቅ ንፋስ ወለድ የሁለንታ እስትንፋስ፡፡ በቀኖች ላይ ሰልጥኖ ሀሳብን በደርዙ ልክ የሚያሰፋ፡፡ ሚስጥራዊ መስሎ በህልማችን ውስጥ የሚሰለጥን ነገር፡፡ የህይወትን ጡት እየጠባ ሞትን የሚያፋፋ ግሩም ክስተት፡፡ ጊዜ ራሱ ፈጣሪ ይሆን እንዴ? የማይታይ የማይዳሰስ፣ የተተረጎመ የሚመስል ግን የማይተረጎም፣ ቅኔውን ለመፍታት እስትንፋስ የሚሻ፣ ወልዶ የሚገድል፣ በስጋችን ውስጥ እንደነፍሳችን የምናደምጠው የሚመስለን ግን ምንም የሆነ ነገር…ብዙ፡፡ ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ጊዜን መግደል አይቻልም፡፡ ጊዜ ገዳይ ነው፡፡ በአንድ ግለሰብ ህይወት ውስጥ መጀመሪያውም መጨረሻውም የማይታወቅ ነገር፡፡ ልክ እንደ ፈጣሪ….ልክ እንደ ፈጣሪው፡፡
አሁን የመጣሁት ስለ ጊዜ ሚስጥር ለመዘብዘብ አይደለም፡፡ ሲጀመር ምንም የማውቀው ነገር የለም፤ ራሱ ጊዜ፣ ጊዜውን ጠብቆ እስኪሰብከኝ ድረስ፡፡
ሚስቴ አረጀችብኝ፡፡ የፊቷ ቆዳ የፀሀይ ብርሀን እንዳላገኘ ቅጠል መድረቅ ጀምሯል፡፡ ፈገግታዋ ለዛው ጠፍቶ የጥርስ ጋጋታ ብቻ ሆናለች፡፡ ጀርባዋ ጎብጦ እንደው ድንገት ዞር ብላ ስታየኝ የሆነ አደጋ ልታደርስብኝ ነው የምትመስለው፡፡ ንቃቷ ጠፍቶ የምትተክዝበት ጉዳይ ራሱ ትርጉም የሌለው ሀሳብ ላይ ነው የሚመስለው፡፡ በሆነው ባልሆነው ነገር ልትፈልገኝ ትሞክራለች፡፡ ሞክራ ግን ብዙም አትቆይ…ይደክማታል፡፡ ልጆች አልወለድንም፡፡ አንዳችን አንዳችንን እያሳደግን ነው፣ የትዳር ዘመናችንን ስንለጥጠው የከረምነው፡፡ አሁን ግን መጋባታችን ራሱ ከትውስታዬ እየጠፋብኝ ነው፡
ድንገት ሌሊት ላይ ከተኛሁበት ተነስቼ ስመለከታት፣ ከሌላ ሴት ጋር ያደርኩ እስኪመስለኝ ድረስ ገፅታዋ ሞቶ፣ የሚተነፍስ የሴት ስጋ ብቻ ሆና ታየችኝ፡፡ ድንገት በአንድ ሌሊት ውስጥ አርጅታ የጠበቀችኝ ነው የምትመስለው፡፡ ጠዋት ላይ ነቅቼ ወደ ስራ ገበታዬ ልሰማራ ስል ቁርሴን ልታቀርብ ተደፍታ ስትንቀሳቀስ ሳያት አለ አይደል…ድንገት የሆነ የማይገባኝ ጥላቻ በውስጤ ይመላለሳል፡፡ የምፈልገው ስሜት ሆኖ አይደለም፡፡ ስሜቱ የሚመጣው ድንገት ነው …የማልቆጣጠረው አይነት ጥላቻ፡፡ ይሄ የጊዜ ቀመር መሆኑን ለመረዳት ብዙ የጥላቻ ቀናትን  ከህይወቴ ላይ ቸክችኬ ተቀምጬ ነበር፡፡
ሚስቴ አረጀችብኝ፡፡
መጀመሪያ ጊዜ…(ቃሉ የሚያከራክር ቃል ቢሆንም ልጠቀመው፡፡)
መጀመሪያ….
ሳያት የተሰማኝ ስሜት ልዩ ነበር፡፡ ልጅ ሆና፡፡ ደስታን ብቻ የሚጓተት የወጣትነት ግለት ውስጥ ሳለች፣ ትዳር የሚባል ነገር አፈታሪክ እንደሆነ መስበክ ለሷ እጅግ ጥልቅ ፍልስፍናዋ የሚመስላት ወቅት ላይ፣ ዝምታ የሚያስፈራት፣ በሰው ካልተከበበች እንባ የሚቀድማት፣ ወንዶች ተሰብስበው ሲመለከቷት በጉራዋ የምታሸሻቸው እድሜዋ ላይ እኔን አገኘችኝ፤ የዚያን ጊዜው እኔን…፡፡
ጉልበቴን እስክጨርስ ድረስ በፍቅሯ አነዘረችኝ፡፡ አማራጭ ያለኝ እንዳይመስለኝ አድርጋ አንጠልጥላ፣ ማንም የማይደርስበት የስሜት ጋራ ላይ አመነነችኝ፡፡ ያኔ እንደዛ ነበረች…ማንም የማይተረጉማት የሴትነት ተምሳሌት፡፡ ጉልበታም ….ውበታም፡፡
የሌላ መንፈስ ስራ እስኪመስል ድረስ…በጊዜ ርዝመት ውስጥ ፍቅረኛዬ ሆነች፡፡ ሁሉም ነገር በፍጥነት ነው የሆነው፡፡ ስለ ታሪኳ በራሷ አንደበት አጠናሁ፡፡ እናቷም አባቷም በምድር ላይ የሉም …ጊዜ ቀርጥፎ በልቷቸዋል፡፡ አሁን ከቤተሰቦቿ የዘር ግንድ እሷ ብቻ ነች ያለችው፡፡ የዚያን ጊዜ ላይ መውለድ ባትፈልግም፣ ሃላፊነቷ እንደሆነም ግን ታውቃለች፡፡
ይመስል ነበር መጀመሪያ ጊዜ ላይ አብረን ስንኖር፣ ዘላለምን የሚያስንቅ ፍቅር ከመሀላችን አድርገን፣ በከንፈሮቻችን ቃላት ስንፈበርክ፡፡ ይመስል ነበር…ጠዋት ማታም ባያት እንደማልሰለቻት አዕምሮዬ ሲናገረኝ እና አምኜው ፈጣሪዬን ሳመሰግን…ይመስል ነበር ቃላቶቼን አምና፣ ተስፋዎቼን ተከትላ አብራኝ ዘመኗን ለኔ ልትሰጥ፣ ፍቅሯን ከአለት በላይ በውስጧ ስታጠነክረው፡፡ ሁሉም ነገር የሚሆን ይመስል ነበር…
አሁን ግን ይሄ ሁሉ ነገር የለም፡፡ ልጅም መውለድ እንደማትችል ካወቀች በኋላ…እድሜዋ በላይዋ ላይ ሰልጥኖባት ውበቷን መጦ ሲጨርሰው፣ ሞት የትም ሩቅ የሆነ ነገር እንዳልሆነ ጊዜ አልምዶ ካስተማራት በኋላ፣ ሁሉም ነገር መልኩን ቀየረ፡፡ ፈገግታዋ ጠፍቶ መልኳ ታይቶ እንደሚረሳ ህልም መሰለ፡፡ ጉልበት ያጠረው የውስጥ ግለቷ ቀዝቅዞ፣ ጊዜ ቃላቶቿን ከአንደበቷ ላይ አድርቆባት፣ የዝምታ ድምፅ ብቻ ነው የምታስተጋባው፡፡ አታዋራኝም፡፡ እንዲሁ ሞት የሚጠብቅ የሴት ገላ ብቻ ሆና ቀረችብኝ፡፡
ይሄ ባህሪዋ ሊጀማምራት ሲል አንድ ቀን ላይ ያወራነው መቼም አይረሳኝም…
ከስራ ደክሞኝ ገብቼ እራት እንድታቀርብልኝ እየጠበኳት ባለሁበት፣ በትካዜ ከአልጋዋ ላይ ሆና የተዘጋው ቴሌቪዥን ላይ አፍጥጣ ቀርታ አየኋት…፡፡ የምር አሳዘነችኝ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ፡፡
“ምን ገጠመሽ አስቴር?” አልኳት፡፡
አይኖቿን ከቴሌቪዥኑ ላይ ሳትነቅል ይህን አለችኝ፡፡
“የሰው ልጅ ግን ሞትን ለምን የሚፈራው ይመስልሀል? ወይስ በድሮ ጊዜ የሚወደድና በጉጉት የሚጠበቅ ነገር ሆኖ፣ በጊዜና በሰው ብዛት ልክ ትርጉሙን እያጣ የመጣ ነገር ነው?”
የዚያን ጊዜ እሷን እያሰብኩ ለሷ ደንግጬላት ነበር…ለመጨረሻ ጊዜ፡፡
“ምኑን አውቄው፡፡ ምን አይነት ጥያቄ ነው እየጠየቅሺኝ ያለሽው?”
አስቴር ብዙ ስታስብበት ነበርና ሀሳቧን ቀጠለች….
“እኔ ግን የሚመስለኝ የሰው ልጅ ገና አድጎ አልጨረሰም፡፡ የሚሸከመውን እውነት፣ የሚኖርበትን ሀቅ፣ የተፈጥሮውን ውስጠ ሚስጥር ተረድቶ ገና አልተግባባውም፡፡ ዝም ብለን ነው እየኖርን ያለነው፡፡ እያሰብን አይደለም፡፡ እየኖርን አይደለም፡፡ እየሞትን ብቻ ነው፡፡ እንመጣለን ብዙም ሳንቆይ እንሞታለን፡፡ ምንድን ነው ታዲያ ትርጉሙ…?”
“አስቴር ዛሬ ምን ገጥሞሽ ነው…? ከመች ጀምሮ ነው ደግሞ እንዲህ ያለ የፈላስፋ ባህሪህ ያመጣሽው…?”
አስቴር ብዙ ስታስብ ነበርና መልስ አላጣችም፡፡
“ምን ያህል ጊዜ እዚህ ቤት ውስጥ ተቀመጥኩ…? ምን ያህል ጊዜ ብቻዬን ሆኜ ጠበኩህ…? ምን ያህል ጊዜ አስተከዝከኝ…? ረሳኸኝ መሰለኝ፡፡ ስታስብ ብዙ ነገር ይገባሀል፡፡ ስትተክዝ ብዙ ጉድ ከጭንቅላትህ ውስጥ እየተሯሯጠ መውጣት ይጀምራል፡፡”
በስተመጨረሻ ዞራ ተመለከተቺኝ፡፡ አይኖችዋ ውስጥ ጉም ይታያል፡፡ እንዳረጀች የዚያን ቀን ነው የገባኝ፡፡ አልመሰለኝም ነበር የምታረጅ፡፡ ሚስቴ ግን ካረጀች ቆይታ ነበር፡፡ ብቸኝነትና ልጅ የማጣት ቁጭት አስረጃት፡፡ ሳላስተውላት ከራሷ ጊዜ ጋር በሚስጥር ተጋብታ፣ እኔን ያልገቡኝን ጉልበታም ሀሳቦችን ስትወልድና ስትፈለፍል ከርማለች፡፡ አጠገቤ ስትሆን የምናፍቃት ሴት፣ አጠገቤ ሆና በዛችብኝ፡፡ ብዙ ሆነችብኝ፡፡ ሁሉም ነገር ወደ መሞቱ እየሄደ እንደሆነ ገባኝ፡፡ እሷ ናት እንዲገባኝ ያደረገችኝ፡፡
አንድ ቀን ላይ…
ያን  ቀን…
ከእንቅልፌ ተፋትቼ ከንጋቱ ጋር ልጋባ አይኖቼን ስገልጥ፣ ፊት ለፊቴ ተቀምጣ እያየችኝ አየኋት፡፡ በድንጋጤ ነበር የነቃሁት፡፡
“ምን እያደረግሽ ነው አስቴር?” ብዬ ጠየኳት፡
“አሁንም ትወደኛለህ…?”
በምን አይነት ዘዴ ውስጤ ሳልፈልገው እያደገ የመጣውን ጥላቻ እንዳወቀችው ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ በጣም ለመጠንቀቅ ሞክሬ ነበር፡፡ በጣም፡፡
“አዎን እወድሻለሁ…አስቴር ምን ሆንሽብኝ የኔ ውድ?”
ከአልጋዬ ወጥቼ አቀፍኳት፡፡ ትከሻዬ ላይ ጤዛ የምታክል እንባ አስቀመጠች፡፡ ያ የእንባ ዘለላ ውስጡ የተሸከመው የትዝታና የተስፋ ዶሴውን እንደያዘ፣ አሁን ድረስ ትከሻዬ ላይ ተከምሮ ጉልበቴን እየበላው ነው፡፡
“ዛሬ ከስራ እንደመጣሁ ወጣ ብለን ራታችንን አንዱ ሬስቶራንት እንበላለን፡፡ እ…የኔ ውድ…?”
ሚስቴ አርጅታለች…የዚያን ቀን ፈገግ ትበል ትናደድ፣ በፊቷ ላይ የተተበተበው የቆዳ አጎዛ ስሜቷን ሸፍኖት ስለነበር ምንም ሳልረዳ ወጣሁ፡፡ የዚያን ቀን ሚስቴን ምን ያህል እንደምወዳት ገባኝ፡፡ መጀመሪያም እወዳት ነበር…አሁንም እወዳታለሁ…ብትሞትም ሞቴ ድረስ አርዝሜ እወዳታለሁ፡፡
የዚያን ቀን በፍፁም ልለያት እንደማልችል ገባኝ፡፡ መስሪያ ቦታዬ ጋር ያለው መስታወት ፊት ቆሜ ራሴን ተመለከትኩት፡፡ ለካ እኔ ነኝ የባሰ ያረጀሁት፡፡ ለካ እኔ ነኝ ያስረጀኋት፡፡ ራሴን እስክዘነጋ ነበር በሷ እርጅና ውስጥ ወጣትነቴን ያቆየሁት፡፡ የዚያን ቀን ከስራ ገበታዬ ላይ ቀደም አድርጌ ወጣሁ፡፡ እጅጉን ናፈቀችኝ፡፡ የዚያን ጊዜ ‘ብትፈቅድልኝ ስራዬን አቁሜ ያለችንን ጊዜ አብረን ሀገራትን እየዞርን እናሳልፍ’ ልላት ነበር…
ቤቴ ተንደርድሬ ሄድኩኝ፡፡
ቤቴን ከፍቼ ገባሁ…አስቴርን ፍለጋ…ሚስቴን ፍለጋ፡፡ የመጀመሪያውን ቀን ፍቅር ተሸክሜ…
በቤታችን ውስጥ አስቴር የለችም፡፡ ሁሉም ነገር በቦታው ሳለ አስቴር ግን የለችም፡፡ የትም ርቃ የምትሄድበት ቦታ ስለሌለ አካባቢውን በሙላ አሰስኩት፡፡ አስቴር የትም አልተገኘችም፡
የዚያን ቀን፣ አስቴር ቤታችንን ጥላ የጠፋችበት ቀን ነው፡፡ ሸሽታኝ የተሰወረችበት ቀን፡፡
***
ቀናት በቀናት ላይ ተደራርበው አንድ አመት አለፈኝ፡፡ እኔም ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ አብረውኝ አንዱንም አመት ሲያፈላልጉኝ የነበሩት ወዳጆቼም ተስፋ ቆረጡ፡፡ ከዛም ባለፈ ለአንድ ሰፊ የስራ ፕሮጀክት ወደ ክፍለሀገር እንድሄድ ተወሰነ፡፡ የሆነ ጊዜ ላይ እቃዎቼን ወደ ሻንጣዬ በማስገባበት ቅጽበት፣ አንዲት አይቻት የማላውቃት ወረቀት ከመሬት ላይ ወደቀች፡፡ አንስቼ ተመለከትኩት፡፡ ስብርብር ባለ የእጅ ፅሁፍ የተፃፈ የአስቴር ደብዳቤ ነበር፡፡ አነበብኩት፡፡
“ጊዜ ጨካኝ ነው… አንተን አስረጀብኝ፡፡ ጊዜ እርጉም ነው…ምንም ልረዳው በማልችለው ጥበብ አንተን ከውስጤ እንድጠላህ አደረገኝ፡፡ ጊዜ ቂመኛ ነው … ለብቻህ እየወደድከኝ እንደሆነ አውቆ ካንተ እሰወር ዘንድ የመለያየትን ጉልበት እጅጉን አብዝቶ ሰጠኝ፡፡ እወድህ ነበር፡፡ አሁን ግን…”
እዚህ ድረስ ሀሳቧ ተስቦ ሄዶ በነዚህ ቃላት ውስጥ ሞተ፡፡
የጊዜ ጥበብ ይህን አስተማረኝ፡፡ ቀድማኝ ነበር ለካ፡፡ ለመሸሽ ጎልብታ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ አልወቅሳትም፡፡ ተመሳሳይ የጊዜ ምጣድ ላይ ነው እኩል ተገላብጠን የበሰልነው፡፡
አሁን ሚስቴ የሆነ ቦታ ወይ ሞታለች ወይ አርጅታለች፡፡
ጊዜ ሆይ … እኔ እሆን የፈጠርኩህ? አስቴርን አይተሀታል??  


Read 616 times