Saturday, 22 June 2024 00:00

“ላምህ ባትታለብ እንኳ እምቧ ትበልልህ” “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ!”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንድ የአይሁዶች አፈ-ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡
አይሁዶች በአንድ ክፉ-አጋጣሚ የሆነ እርኩስ (እኩይ) መንፈስ ሲገጥማቸው፣ ያን መንፈስ ለማባረር ሦስት ነገሮች ያደርጋሉ ይባላል፡፡
አንደኛ- ወደ አንድ ጫካ ይሸሹና አንድ ልዩ ቦታ ይመርጣሉ፡፡
ሁለተኛ -እሳት ያነዳሉ፡፡
ሦስተኛ -ፀሎት ይደግማሉ፡፡
ይህንን ሲያደርጉ ያ እርኩስ መንፈስ ይሸሻል፡፡ ይጠፋል፡፡
አንድ አይሁዳዊ የዕምነት ሰው ከዕለታት አንድ ቀን እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡ ይህ ሰው ሦስቱን ህግጋት ያውቅ ስለነበር፣ ቶሎ ብሎ  ወደ ጫካ ይሄድና ቦታ ይመርጣል፡፡
እሳት ያነዳል፡፡
ቀጥሎም ይፀልያል፡፡ ይደግማል፡፡
እርኩስ መንፈሱ በንኖ ሄደ፡፡ ድራሹ ጠፋ፡፡
ሌላ ጊዜ አንድ ሌላ የዕምነት ሰው እንደዚሁ እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡ ይህ ሰው ሦስቱን ህግጋት ለመፈፀም ወደ ጫካ ይሄዳል፡፡
ምቹ ቦታ ይመርጣል፡፡
መፀለይና መድገም ያለበትን ያሰላስላል፡፡
እሳት ማንደድ ግን አልቻለበትም፡፡
ያም ሆኖ እሳቱን ሳያነደድ ፀለየ፡፡ እርኩስ መንፈሱ ድራሹ ጠፋ፡፡
ሦስተኛው የዕምነት ሰው እንደዚሁ ከዕለታት አንድ ቀን እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡
ይሄኛው፤ ቦታውን ያውቃል፡፡
እሳት ማንደድ አይችልም፡፡
የሚደገመውን ፀሎትም አይችልም፡፡ ሊያስታውሰው አልቻለም፡፡ ያም ሆኖ ቦታውን በመምረጡና ወደዚያ በመሄዱ እርኩስ መንፈሱ ተሰወረ፡፡
የመጨረሻው የዕምነት ሰው እንደሌሎቹ ሁሉ እርኩስ መንፈስ ያጋጥመዋል፡፡
ይሄ ሰው ግን፤ ቦታውን አያውቀውም፡፡
እሳት ማንደድም አያውቅም፡፡
የሚደገመውን ፀሎትም አያውቀውም፡፡
ምን እንደሚያደርግ ሲያሰላስል ቆይቶ እንዲህ አለ፡-
“በቃ፡፡ ከዚህ ቀደም እርኩስ መንፈስ ያጋጠማቸው ሦስት የዕምነት ሰዎች ታሪክ ልናገር” አለ፡፡
የሦስቱን ሰዎች ታሪክ ተናገረ፡፡
የነሱ ታሪክ መነገሩ በቂ ሆነ! እርኩስ መንፈሱ ድራሹ ጠፋ፡፡
***
 ታሪኩ መነገሩ በቂ መሆኑን የሚያምኑና ታሪክ ለመናገር የሚችሉ ሰዎች ማግኘት መታደል ነው፡፡ እርኩስ መንፈስን ለማጥፋት ቦታ መምረጥ የሚችሉ ሰዎች መኖራቸው እሰየው ነው! እርኩስ መንፈስን ለማግለል ፀሎት መድገም የሚችል ሰው ማግኘት ትልቅ ዕድል ነው፡፡ እርኩስ መንፈስ ለማጥፋት እሳት ማጥፋት የሚቻለው ሰው ማግኘት የሚችል ብልህ ሰው መኖሩን ማወቅ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ ሦስቱንም ማግኘት በማይቻልበት ቦታ የሦስቱን ታሪክ የሚናገር ሰው ማግኘት አገር ማዳን ነው፡፡ እነማን ምን ሰሩ?  እነማን ምን አደረጉ? እነማን የት ዋሉ? ታሪክ የሚናገር ሰው መኖር አለበት፡፡ እርኩስ መንፈስን ያስወግዳል፡፡ “ፃዕ እርኩስ መንፈስ!” የሚል ሰይጣንን ከየውስጣችንም ሆነ ከየአካባቢያችን የሚያወጣ ደጋሚ ያስፈልገናል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውና በጣም ድንቅ የሚባሉ የዘመናችንን መጻሕፍት (ለምሳሌ እንደ Clashes of Civilizations /የሥልጣኔዎች ግጭት እንደ ማለት፣) ያሉ፤ የፃፈውና በፖለቲካ ትንተና ባለሙያነቱ የሚታወቀው ሳሙኤል ሀንቲንግተን፣ የመደብ ፖለቲካ እያበቃ ሲሄድ ሀይማኖት እናም ባህል የግጭት ማትኮሪያ ነጥብ ይሆናል ይለናል፡፡ ቀጥሎ፤ “የአንድ አገር ህዝብ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያለው እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ድርጅቶችና አስተማማኝ የፍትህ አካላት (ፍርድ ቤቶች) ሊኖሩ ይገባል፡፡ አለበለዚያ ውጤቱ የባሰ ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መግባት ነው” ይላል፡፡ ሀገራችን የተረጋጋ ህልውና ይኖራት ዘንድ ዲሞክራሲ ያሻታል ሲባል፣ ያንን የሚተገብሩ ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ ያላቸው ተቋማት ያሻታል  የማለት እኩሌታ ነው፡፡ ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ ሲባልም ሀሳዊ-ዲሞክራሲያዊ (Pseudo-democracy) አለና ነው፡፡ አንድም በምሪት የሚሄድ ዲሞክራሲ (guided democracy) አለና ነው፡፡ የሚያማምሩ ዕቃዎች ስናይ በዐይናችን እንደምንማረክ፣ ውሎ አድሮ ግን በአገልግሎት ላይ ውለው ስናይ ከቶም ዕድሜ የሌላቸው ሆነው ስናገኛቸው እንደሚቆጨን ሁሉ፤ በመልካም ሀረጋትና ስሞች የሚጠሩ እንደ ዲሞክራሲ፣ ነፃነት፣ የፕሬስ ነፃነት፣ ኮሙኒኬሽን፣ ኮሚሽን፣ ሚኒስቴር፣ ባለስልጣን፣ ኤጀንሲ፣ ፍትህ፣ ዲሞክራሲያዊ ግንባር፣ ዲሞክራሲያዊ መንግስት፣ ኮከብ አምራች፣ ሀቀኛ ካድሬ፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ራእይ፣… ያሉ አያሌ መጠሪያዎች ተግባሪዎቻቸው በሌሉበት እንዲያው መጠሪያዎች ናቸው፡፡ የአራዳ ልጆች “የቻይና ሶኬት ስትገዛ፣ የሚይዝልህ ጩሎ አብረህ ግዛ” የሚሉት አባባል መንፈሱ ይሄው ነው፡፡ ተግባራዊነት ምኔም ወሳኝነት አለው፡፡ አፈፃፀምም አልነው ተግባራዊነት፤ “አንተ ዘፈን አልከው፣ እኔ ስልት ያለው ጩኸት አልኩት” ሁሌም ትርጉሙ ያው ነው እንዳሉት መምህር ያለ ነው፡፡
ምንም አይነት ጉዳይ ይሁን ምን፣ ምንም ዓይነት ለውጥ ይሁን ምን፣ ምንም ዓይነት ስያሜ ይሰጠው ምን፣ መለኪያው ለሀገርና ለህዝብ ጠቀሜታው ምንድን ነው የሚለው ነው፡፡ ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ-አገር የሆነ አገዛዝ ሁሉ እርኩስ መንፈስ ነው፡፡ ይህንን የሚናገሩ ታሪክ ተራኪዎች፣ አይጥፉ፡፡ የሚናገሩ አፎች አንጣ፡፡ የሚፅፉ ብዕሮች አይንጠፉ፡፡ “ላምህ ባትታለብ እንኳ፤ እምቧ ትበልልህ” ማለት ይሄው ነው፡፡ በፖለቲካዊ- ኢኮኖሚኛ “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ” ማለትም ነው፡፡

Read 350 times