Saturday, 22 June 2024 00:00

የመጨረሻ ጉዞ ወደ ንጉሰ ነገስትነት---

Written by  በደረጄ ጥጉ (የአለም አቀፍ ህግ መምህር)
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት በቀረበው ጽሁፍ፣ ራስ ተፈሪ የግብ መዳረሻው (የመጨረሻው የፖለቲካ ስልጣን መቆናጠጥ) ላይ እንቅፋት ይሆኑብኛል ብሎ ያሰባቸውን በረቀቀ መንገድ እንዴት ገለል ሲያደርግ እንደነበር ተመልክተናል፡፡ በዚህ ሳምንት ፅሁፍ ደግሞ የስልጣኑ የመጨረሻ ተቀናቃኞቹ ሆነው የቆሙትን ባልና ሚስቱን ዘውዲቱ ምኒልክና ራስ ጉግሳ ወሌን እንዴት ከጨዋታ ውጪ እንዳደረጋቸው እንመለከታለን፡
በ1920ዎቹ  መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ የንጉሰ ነገስትነትን ስልጣን በእጁ ለማስገባት የተቃረበ የመጨረሻ ሰው ቢኖር ራስ ተፈሪ ነበር፡፡ ራስ ተፈሪ ሀገሪቱን አዘምናለሁ በጠንካራ አመራርም አንድ አደርጋታለሁ ብሎ ያምን ነበር፡፡ ከንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ጎን ሆኖ ፤ ከመጋረጃው ጀርባ  መሀል ሰፋሪን የድብቅ አላማው ማስፈፀሚያ መሳሪያ አድርጎ የአፄ ምኒልክ መሳፍንትን፤ የጦር አበጋዞችንና ሚኒስትሮችን ጉልበት ሲያዳክምና ከስልጣን ወንበር ላይም ገለል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በሹም ሽሩ ሂደት የመጨረሻ ውሳኔው የንግስቲቱ ቢሆንም ጉዳዩን አቅራቢውና አስፈፃሚው ግን ተፈሪ ነበር፡፡ እንደ ውጥኑ ሁሉን መልክ ካስያዘ በኋላ የመጨረሻ የስልጣን ደንቃራ ሆነው የቆሙበት ንግስቲቱና የንግስቲቱ ባል የነበሩት ራስ ጉግሳ ወሌ ነበሩ፡፡ በራስ ተፈሪ እምነት፣ ጉግሳ እንደማይተኛለት ቀድሞ ገምቷል፡፡ ራስ ጉግሳ በሂደት የሚስቱን የንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ስልጣንን ጋሻ አድርጎ ከጨዋታ ውጪ እንደሚያደርገው ጥርጥር አልነበረውም፡፡ ሚስት ንግስት ከሆነች  ባልም ንጉስ መሆኑ እሙን ነው፡፡ እሩቁን ለሚመለከተው ተፈሪ፣ ከዚህ በላይ እንቅፋት ሊኖር አይችልም፡፡ ኃይለስላሴ ሁሌም ከፊት የሚመጡ ነገሮችን ቀድሞ ማየት የሚችል ሰው ነበር፡፡
በ1902 ዓ.ም ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው የመንግሥት እንደራሴ በነበሩበት ዘመን እቴጌ ጣይቱ ከመንግሥት ስልጣን ሲገለሉ፣ ጉግሳም በደም ይዛመዳልና ተንኮል ሊጎነጉን ይችላል ተብሎ ስለተሰጋ ለእስር ተዳረገ፡፡ ቀጥሎም አፍቀራ ወደ ተባለ ቦታ በግዞት ተጋዘ፡፡ አፄ ምኒልክ በ1906 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ከተለዩ በኋላ ልጅ እያሱ እቴጌ ጣይቱን ከቤተመንግስት አስወጥተው በእንጦጦ ማርያም እንዲቀመጡ ሲያደርጉ፣ ዘውዲቱም ፋሌ በተባለው እርስታቸው በግዞት እንዲኖሩ ወደዛው ተላኩ ሲሉ ታሪኩን የዘገቡት መርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ፅፈዋል፡፡ በዚህን ጊዜ የዘውዲቱ ባል ራስ ጉግሳ ወሌ ቀድሞ በግዞት ካረፉበት ቦታ ተዛውረው ባለቤታቸውን በፋሌ ተቀላቀሉ፡፡ በፋሌም ለሁለት አመት አብረው ኖሩ፡፡
ከሁለት አመት አስከፊ የግዞት ህይወት በኋላ የሚከተለው የምስራች መልእክት ወደ ዘውዲቱ ተላከ፡፡ የሁለት አመቱን አስከፊ የግዞት ህይወት በቃህ ሊላቸው “መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም መሳፍንቱ፤ መኳንንቱና ሰራዊቱ የምኒልክን ልጅ ዘውዲቱን ንግሰተ ነገስታት ወለቱ ለዳግማዊ ምኒልክ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ተብለው እንዲነግሱ መወሰኑን” መልእክቱን እንዲያደርሱ የተላኩት የግቢ ሚኒስትር የነበሩት መታፈሪያ መልከፀዴቅ ነገሯቸው፡፡ ዘውዲቱ ግን ግራ በመጋባትና ባለማመን ስሜት ውስጥ ሆነው “እያሱ ምን ሆኖ ነው እኔ የምነግሰው?” ብለው ሲጠይቁ፤ “እያሱማ ሰልሟል፤ ውሎውም በመስጂድና ከእስላሞች ጋር ነው” ተባሉ፡፡ ከዚህም አልፎ “ኢትዮጵያንም አሰልማለሁ” ብሏል የሚለው ንግግሩ ስለተደረሰበት ተሽሯል፡፡ ጳጳሱም ገዝተውታል፡፡ ይህን የምስራች ዜና ጉግሳም አብረው ታድመዋል፡፡ አንድም የመንግስት አስተዳደር ስራውን ጠቅልሎ የሚይዘው ተፈሪ መሆኑን  ባለመገመት፣ ሁለትም በራሱ በጉግሳና በሚስቱ ዘውዲቱ የወደፊት ህይወት ዕጣፈንታ ላይ የተወሰነውን ባለመጠርጠር ወደፊት የሚጠብቀውን ስልጣን እያሰበ ጉግሳ በተድላ ተሞላ፡፡ የንግስት ባል ንጉስ ነው መቼም፡፡ ጉግሳም ወደፊት ንጉስ ሆኖ ኢትዮጵያን ሲመራ ሳይታየው አይቀርም፡፡
ካህናት፤ የተፈሪና የቤተመንግስት ባለሟሎች ግን በንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ የወደፊት የግልና የፖለቲካ ህይወት ላይ የሚከተለውን ውሳኔ ወስነው ጠበቋቸው፡፡ “ንግስተ ነገስታት ሆነው የአባታቸውን ዘውድ የሚወርሱት ወይዘሮ ዘውዲቱ ምኒልክ ከእንግዲህ ወዲህ ህይወታቸውን ለኢትዮጵያ አገራቸውና ለህዝባቸው ደህንነት ሰውተው ከምድራዊ አለም በመራቅ  በጾም፣ በፀሎትና በንፅህና  መኖር ስላለባቸው ከባለቤታቸው እንዲለያዩ” ይሆናል ተብሎ በታላላቆቹና በሃይማኖት አባቶች ተወሰነባቸው ሲሉ፣ ውሳኔውን በቅርብ የሰሙት መርስኤ ኀዘን ወልደቂርቆስና እምሩ ኃይለስላሴ በመፅሐፋቸው ጠቅሰውታል፡፡ ራስ ጉግሳ እንኳንስ ሙሉ ንግስና ሊቀዳጁ  ከባለቤታቸው ጋር የነበራቸው ህጋዊ የትዳር ገመድም ተበጠሰ፡፡
ሸዋ በጠነሰሰው ሴራ ዝምተኛዋና ሀይማኖተኛዋ ዘውዲቱ በ40 ዓመታቸው ምድራዊ ተድላ ይብቃዎ ተባሉ፡፡ ዘውዲቱ በትዳር ህይወትሽ ተረገሚ ሲላት ከአንድም ሁለት ጊዜ ያልሰመረ ትዳር ቢኖራትም፣ ይኸኛው ግን በቁስል ላይ እንጨት የመስደድ ያህል ነበር፡፡ ዘውዲቱ የተፈለጉት የዙፋኑ ምልክት እንዲሆኑ እንጂ ለሌላ እንዳልሆነ ተነገራቸው፡፡ ከዚህ ውሳኔ ጀርባ ያለው ታላቅ አላማ ግን ራስ ጉግሳን ከቤተመንግስትና ከስልጣን ክልል ማራቅ ነበር፡፡ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ በኖረው ልማድም ሆነ በፍትሀ ነገስቱም የኢትዮጵያ ንግስተ ነገስታት  እንድትሆን የተመረጠች ሴት ከህጋዊ ባሏ መለያየት አለባት የሚል ህግ የለም፡፡ ደርሶም የታየ በታሪክ አንድ እንኳን አልተመዘገበም፡፡ በነገስታት ታሪክ አግብታ ፍቺ የተባለች የመጀመሪያዋ ሴት ንግስት ዘውዲቱ ናት፡፡ ታላቁን ተንኮል ባለመረዳት ዘውዲቱ ውሳኔውን በፀጋ ተቀበለችው፡፡ በታላላቆቹ ሹማምንትና በሀይማኖት አባቶች ተንኮል ከባሏ እንድትፋታ ብትደረግም፣ የተፈሪ ተንኮል ግን ከዚህም በላይ የረቀቀ ስለነበር ለህዝብ የተነገረው በሚከተለው መልኩ ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ፣ አምባሳደር ዘውዴ ረታ በመፅሐፋቸው፡፡ ውሳኔው የማንም ሳይሆን ዘውዲቱ በፈቃዷ የወሰነችው በማስመሰል፤ “ከእንግዲህ ወዲህ ህይወቴ የኢትዮጵያ ህዝብ ደህንነት ስለሆነ ከዚህ ህይወት የተለየ የለኝም” አሉ ተባለ፡፡ በታሪክ እንደሰፈረው ዘውዲቱ ሃይማኖቱ ላይ እንጂ የአስተዳዳር ስራው ላይ እስከዚህም ስለነበሩ የቤተመንግስቱን ጠልፎ የመጣል ተንኮል ገና አልተለማመዱትም ነበር፡፡
የመጀመሪያ ውጥኑን መልክ ካስያዘ በኋላ ራስ ተፈሪ ቀጥሎ ያለውን ሁለተኛ ወጥመድ ዘረጋ፡፡ ”የኢትዮጵያ ስልጣኔ እድገት ሊገሰግስ የሚችለው ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ በመንግስቱ አስተዳደር ውስጥ እንዳይገቡ የተደረገ እንደሆነ ብቻ ነው” ሲሉ የተፈሪ ደጋፊዎች ወሬ እንዲነዙ አስደረገ፡፡ የዚህ አቋማቸው ማጠናከሪያ አድርገው ያቀረቡትም ዘውዲቱ ከፋሌ የግዞት ህይወታቸው እንዲመጡና ዘውድ እንዲጭኑ የተደረጉት ለምንም ሳይሆን የሀገሩን ወግ በጨዋነት እንዲጠብቁ እንደሆነ፣ ተፈሪም ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ የተባለው የመንግስቱን ስራ በሙሉ ስልጣን እንዲከውን ነው ሲሉ ተናገሩ፡፡ በዚህን ጊዜ ሿሚና  ሻሪ የነበረ መሃል ሰፋሪ እየተባለ የሚጠራው የአድማ ስብስብ በ1921 ዓ.ም “ራስ ተፈሪ ንጉስ” ተብሎ ይሾምልን ሲል ጥያቄውን ለንግስቲቱ አቀረበ፡፡ ይህ መሀል ሰፋሪ እየተባለ የሚጠራው ስብስብ ከየትም የተገኘ ሳይሆን “አልጋወራሽ ራስ ተፈሪ ቀስቀስውት የነበረው የህዝብ ወገን እነ ራስ ናደውና ሌሎችም መኳንንቶች ባሉበት ጃንሜዳ ላይ ስብሰባ ተደርጎ ሚኒስትሮችን መቃወም የጀመረ ቡድን ነው” ሲሉ ”ካየሁት ከማስታውሰው“ በተባለው መፅሐፋቸው ላይ እምሩ ኃይለስላሴ አስፍረዋል፡፡ ከዚህ የአድማ ቡድን ጀርባ ያለው ዋነኛው ሰው ራስ ተፈሪ ነበር፡፡ ተፈሪ ይንገስልን የሚለውን ጥያቄ እንዲያነሱ ያደረጋቸውን ምክንያት ሲያብራሩ፤ ልጅ እያሱ አባቱን ንጉስ ብሎ በወሎና ትግሬ ላይ ሹሟል፤ እርሶም ንግስት ዘውዲቱ ዘውድ እንደጫኑ ራስ ወልደጊዮርጊስን የጎንደር ንጉስ ብለው ሾመዋል፡፡ እኛም የምንጠይቀው ረዳትዎ ራስ ተፈሪ ንጉስ ተብሎ እንዲሾምልን ነው ሲሉ አሳወቁ፡፡ ዘውዲቱ ይህ የመሀል ሰፋሪ ግማሽ ልመናና ግማሽ ትእዛዝ መሰል ጥያቄ ቢያሳዝናቸውም፣ የማስብበት ጥቂት ጊዜ ስጡኝ አሉ፡፡ ጊዜ መስጠት ንፋስ ያስገባልና መሀል ሰፋሪው፣ አሁኑኑ ካልሆነ ብሎ አሻፈረኝ አለ፡፡ ተፈሪ በሚታወቅበት ብልጠቱ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ እጁ እንደሌለበት ሆኖ ድምፁን አጥፍቶ ዝም አለ፡፡ እንደ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ትዝብት፤ “ተፈሪ የመሀል ሰፋሪ ጥያቄ ከምን ደረሰ ብሎ አልጠየቀም፤ንግስቲቱንም በምክር  አላገዘም”፡፡ መሀል ሰፋሪ በጊዜው ሀያል ስለነበር ንግስናው በሦስት ቀናት ውስጥ እንዲፈፀም ብለው ንግስቲቱን ቀን እንዲቆረጥ አስደረጉ፡፡ ንግስናው እውን እንደሚሆን ሲያውቅ ተፈሪ መጋረጃውን ገልጦ ብቅ አለ፡፡
ተፈሪ የሚከተለውን ምክረ ሃሳቡን አካፈለ፤ “ንጉስነትን የሚያህል ሹመት በሦስት ቀናት ውስጥ ማዘጋጀት አይቻልም፡፡ የንጉሱ በአል በሚገባ እንዲሆን ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ የውጪ ሀገር መንግስታት እንደራሴዎች የንጉሱ በአል ተካፋይ ቢሆኑ ለሀገራችን ትልቅ ክብር ነው፡፡ መሳፍንቱም ሁሉም  አዲስ አበባ እንዲመጡ ቀን ይሰጣቸው ሲል አከለበት”፡፡ የንግስናውም በአል እሁድ መስከረም 27 ቀን 1921 ዓ.ም ከሦስት ሳምንት በኋላ ቢሆን ይሻላል ብለው ዋና ተዋናዩ ተፈሪ ሲያስረዷቸው፣ መሀል ሰፋሪ አድማቸውን በትነው በደስታ ወደየ ቤታቸው ተመለሱ ይሉናል፤ አምባሳደር ዘውዴ ረታና መርስኤ ኀዘን ወልደቂርቆስ በመፅሐፋቸው፡፡
በዚህን ጊዜ ተፈሪና የተፈሪ ደጋፊዎች ንግስናው መፈፀም ያለበት በቤተክርስቲያን ነው  የሚል ወሬ ያናፍሱ ጀመር፡፡ እዚህ ጋ የቤተመንግስቱን የተንኮል ስራ ለምደውታልና ዘውዲቱ  የተፈሪን ሴራ ያሸተቱ መሰሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በሁለቱ መሃል ግልፅ አለመግባባት ተፈጠረ ሲሉ ያትታሉ፤ አምባሳደር ዘውዴ ረታ በመፅሐፋቸው፡፡ አለመማግባባቱም  ተፈሪ “የምሾመው በቤተ ክርስቲያን” ነው ሲሉ፣ ዘውዲቱ ደግም “ልክ እንደ ወልደጊዮርጊስ  የምትሾመው እዚሁ በቤተመንግስት ውስጥ” ነው ሲሉ አቋማቸውን አሳወቁ፡፡ ዘውዲቱ የሚከተለውን በምሬት ተናገሩ፤ “ለኢትዮጵያ ህዝብ ንግስተ ነገስታት ሆኜ በቤተ እግዚአብሄር የተቀባሁት እኔ ነኝ ፤ አንተ ለእኔ ረዳት እንድትሆን ንጉስ ብዬ የሾምኩህን፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ እንደተሰጠህ ቆጥረህ ስርአቱ በቤተ ክርስቲያን እንዲፈፀምልህ የጠየቅከውን አልቀበልም”፡፡ የዚህ የዘውዲቱ ከረር ያለ ንግግር አዝማሚያ ክፉ ውጤት እንደሚኖረውና አደገኛ መሆኑን የተረዱት ተፈሪ፣ ለእርቅ ሽማግሌ ላኩ፡፡ መልእክተኞቹም ወልደፃድቅና ራስ ሙሉጌታ ነበሩ፡፡ የተፈሪም የዘውዲቱም ሀሳብ ተቀይሮ የንግስ በአሉ በቤተመንግስትም በቤተክርስቲያንም መሆኑ ቀርቶ ጎተራ ሜዳ በሚባለው ቦታ እንዲሆን ተወሰነ ሲሉ አምባሳደር ዘውዴ ረታ በመፅሐፋቸው ጠቅሰዋል፡፡ ለጊዜውም ቢሆን በሁለቱ መሃል እርቅ የወረደ መሰለ፡፡
በራስ ተፈሪ የንግስ ስነስርአት ላይ ዘውዲቱ የሚከተለውን ተናገሩ፡- “ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሄር እኔን መርጦ በአባቴ አልጋ ላይ ለመንገስ ሲያበቃኝ አንተ ደግሞ ለእኔ ረዳት እንድትሆን አምላክ መርጦሀልና  እነሆ ለክብርህ ዘውድ ሰጠሁህ፡፡ ወደፊትም ለንጉሰ ነገስቱ ዘውድ ወራሽ ለመሆን ያብቃህ” ብለው መልካም ምኞታቸውን ገለፁላቸው፡፡ ስነስርአቱን የታዘቡት መርስኤ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ እንዳሉት፤ የንግስ ስነስርአቱ ራስ ተፈሪን የኢትዮጵያ  ንጉስ ያደረገ እንደሆነ እንጂ፣ በንግስቲቱ ዙፋን ስር የንጉስነት መአረግ እንደተሰጣቸው አይመስልም ነበር፡፡ መስከረም 27 እሁድ ራስ ተፈሪ ንጉስ መሆናቸው ከታወጀ በኋላ እንደ ቀድሞው ከንግስቲቱ ጋር በአንድነት ሆነው ለቅዳሴ ቤተክርስቲያን አልሄዱም፡፡ ቅራኔያቸው ግልፅ ወጣ፡፡ ዘውዲቱ ወደ ኪዳነምህረት፤ ተፈሪ ወደ ቅድስት ስላሴ ሄዱ፡፡ የታረቁ ቢመስሉም ልባቸው ግን ለየቅል ነበር፤ አልተናበበም፡፡ ስለተፈራሩም በግል ዘቦቻቸው ይታጀቡና ይጠበቁ ጀመር፡፡ ከበደ ተሰማ ”የታሪክ ማስታወሻ“ በተባለው መፅሐፋቸው  ላይ እንዳሰፈሩት፤ አልጋወራሽ ዘውድ ከጫኑ በኋላ የንግስቲቱና የንጉሱ ግንኙነት ከአንገት በላይ ሆነ፡፡ ልጄ- ወንድሜ- እናቴ- እመቤቴ የሚለውም ቀረ፡፡
በዚህ ሁሉ ጊዜ ራስ ጉግሳ የት እና ምን ሲሰሩ ነበር?
ታሪካቸውን በደንብ ፈር ለማስያዝ ያህል ጉግሳ ወሌ ዘውዲቱን በ1893 ዓ.ም ካገቡ በኋላ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ገዢ ሆነው ተሾሙ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በ1902 ዓ.ም ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው የመንግሥቱ ጠባቂ ሆነው በተሰየሙበት ወቅት፣ እቴጌ ጣይቱን ከመንግሥቱ ስልጣን በማሰናበት ከቤተመንግስት አስወጥቶ ነበርና ጉግሳም ጣይቱን በደም ይዛመድ ነበርና እጁን ተይዞ ታሰረ፡፡ እያሱ ጣይቱን ሽረው ከቤተመንግስትም በማስወጣታቸው ጉግሳ ለአክስታቸው በመቆርቆር ነገር ይፈጥራሉ ብለው ስለሰጉ በግዞት እንዲኖሩ ወሰኑባቸው፡፡ የመጀመሪያ የግዞት ማረፊያቸው የነበረችው አፍቀራ ነበረች፡፡ ከዛም ባለቤታቸው ዘውዲቱ በግዞት ወዳረፉበት ፋሌ ተዛወሩ፡፡
ከሁለት አመት አስከፊ የግዞት ህይወት በኋላ ባለቤታቸው “ንግስተ ነገስታት” ተብለው መሾማቸውን እሳቸውም የናፈቁት የንግስና ህይወት  በቀሳውስቱና በታላላቆቹ እንደራሴዎች ተንኮል እንዳይሆን ሆኖ ተበላሸባቸው፡፡ ዘውዲቱ ምንም እንኳን ማረፊያቸው ቤተመንግስት ቢሆንም ሸዋ ግን ንግስቲቱ በብህትውና እንዲኖሩ ወሰነባቸው፡፡ ራስ ጉግሳ እንዲህ አይነት ውሳኔ ዘውዲቱ በራሷ እንደማትወስን ስላወቁ ከጀርባው የሸዋ ተንኮል እንዳለበት ጠረጠሩ፡፡ ቢሆንም በጊዜው ራስ ጉግሳ አቅም ስላልነበራቸው አንገታቸውን ደፍተው  ተቀመጡ፡፡ ጎንደርን እሾማለሁ ብለው ተስፋ ቢያደርጉም፣ ተፈሪ ከዘውዲቱ ተማክሮ  ራስ ወልደጊዮርጊስ ጎንደርን ተሾመ፡፡ በጉዳት ላይ ስድብ ማለት እንግዲህ ይህ ነው፡፡ ከሚስቱ መፋታቱ በቃህ ሳይለው ራስ ተፈሪ የተመኘውን ስልጣንም ነሳው፡፡ ራስ ጉግሳ ቅሬታ አደረበት፡፡ በዛው ሰሞን ተፈሪ ከዘውዲቱ ተማክረው ራስ ጉግሳን የአማራ ሳይንት ገዢ አድርገው ሾሟቸው፡፡ ይህ ለጉግሳ መቼም ስድብ ነው፡፡ ህልሙ ጎንደርን መሾም እንጂ ሌላ አልነበረም፡፡ በ1909 ዓ.ም  የአማራ ሳይንት ግዛት ተሰጣቸውና ወደ ግዛታቸው እንዲሄዱ ታዘዙ፡፡ በታህሳስ በተሾሙበት ግዛታቸው አማራ ሳይንት ደረሱ፡፡ የሚስታቸውን የንግስና በአል እንኳን መታደም አልቻሉም፡፡ ፈጣሪ ልመናውንና የጎንደር ሹመት ምኞቱን የሰማለት ይመስል ራስ ወልደጊዮርጊስ በተሾሙ ብዙም ሳይቆዩ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡ በየካቲት 1910 ዓ.ም ራስ ወልደጊዮርጊስ ሲሞቱ ጉግሳ ጎንደርን  ተሹመው መቀመጫቸውን  ደብረታቦር አደረጉ፡፡  ጉግሳ ጎንደርን ቢሾሙም፣ ዘውድ ጭኜ እነግሳለሁ ብለው ሲያስቡ፣ ሸዋ አሁንም በተንኮሉ ቀደማቸው፡፡ ግዛትህን በሹመት ትቀበላለህ እንጂ ዘውድ አትደፋም ተባሉ፡፡ እንዲህ በመባላቸው ራስ ጉግሳ በድጋሚ አዘኑ፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ መስከረም 27 ቀን 1921 ዓ.ም አልጋወራሽ ተፈሪ ንጉስ ተብለው ዘውድ ጫኑ፡፡ ለጉግሳ ወሌ ይህ አዲስ ዜና እንቆቅልሽ ሆነባቸው፡፡ ተንኮለኛው ተፈሪ ይህን ያደረገው ያቺን የዋህና ቅድስት ሴት አስገድዶ ስልጣኗን ለመቀማት መሆኑ የማይጠረጠር ነው ብለው እንዳዘኑ ዘውዴ ረታ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ራስ ጉግሳ የነበረው ምርጫ የተፈሪ አሻንጉሊት መሆን ወይም ሞት ነበር፡፡ ውስጥ ለውስጥ ግንኙነቱን ከተለያዩ ገዢዎችና የውጪ መልእክተኞች ጋር  አርዝሞ ሳይቀደም ለመቅደም ሴራውን በደንብ መንደፍ ጀመረ፡፡ ሴራውም፡-“ተፈሪ አውሮፓ በነበረ ጊዜ የካቶሊክ ሀይማኖትን ተቀብሏል፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያን ካቶሊክ አደርጋለሁ ብሏል” ብሎ ወሬው እንዲነዛ አደረገ፡፡ ህዝቡ ለሃይማኖቱ ቀናተኛ ስለሆነ ይከተለኛል ብሎ ግምት ወስዶ ነበር፡፡ ልጅ እያሱስ ስልጣኑን ያጣው፤ እስራትና ሞት እጣው የሆነው በዚሁ የሀይማኖት ነገር መሆኑ መች ይታጣል፡፡ ተፈሪ ግን እያሱን አልነበረም፡፡ እያሱ እንደልቡ የአደባባይ ሰው የነበረ፣ እራሱን ለአደባባይ እውነት ያጋለጠ ሲሆን፤ ተፈሪ ግን የዚህ ተቃራኒ ነበር፡፡ ጭምት፤ ዝምተኛ በአደባባይ መታየት የማይፈልግ ነበር፡፡ ተፈሪ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቁርባን ሲቀበልም ሆነ ሲያስቀድስ አልታየም፤ ስለ ሀይማኖት ጉዳይ በህዝብ ፊት ይህ ነው ትክክለኛ፣ ያኛው ነው ሀሰት ሲል አስተያየት ስጥቶ አያውቅም፡፡ ራስ ጉግሳ ከህዝብ ያገኘው ተቀባይነት የልብ ልብ ሰጥቶት ጦርነት ለመጀመር ሁሉ ዳዳው፡፡ ራስ ጉግሳ ምን አልባት የተሞኘው እዚህ ጋ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ይህን ሴራውን እንዲተው በዘውዲቱ በኩል ተደጋጋሚ መልእክት ቢላክበትም በሚያዘናጉ መልእክቶቹ እራሱን ለተፈሪ አሳልፎ መስጠት አልፈቀደም፡፡ “በአባትህ በወዳጅህ በአፄ ምኒልክና በእናትህ በእቴጌ ጣይቱ አፅም ብዬ የምለምንህ፤ ይህ መልእክቴ እንደደረሰህ ገስግሰህ ደሴ ድረስ እንድትመጣና ንጉስ ተፈሪም እዚያው ድረስ መጥቶ የልብህን ሁሉ አውጥተህ ተነጋገር” ብለው መልእክት ቢልኩም ጉግሳ ግን አድፍጦ ዝም አለ፡፡
“እኔና ተፈሪ ተስማምተናል፡፡ ምንም የሚደርስብህ ነገር የለም፡፡ እንዲያውም የተቸገርክበትና የተከፋህበትን ነገር ለንጉስ ብትነግር የምታስበውን ሁሉ በደስታ ይፈፅምልሀል፡፡ ለዚህ ዋስህም ጠበቃህም እኔ ነኝ፤ በምትወደው በመድሀኒአለም በተሰቀለው ጌታ ብለህ ወደ ወሎ እንድትመጣና ከንጉሱ ጋር እንድትነጋገር ይሁን” ብለው  ዳግመኛ ላኩበት፡፡ ጉግሳ ግን በልባቸው እንዴት ነው ከተንኮለኛ ጋር የምነጋገረው ብለው በእምቢታቸው ፀኑ፡፡
ራስ ተፈሪ ንግስናውን ከጫነ በኋላ የሰሜኑን ክፍል ለመጎብኘት ተነሳ፡፡ በዚህን ጊዜ ራስ ጉግሳ የየጁ ግዛት እንዲጨመርላቸው ቀድመው ለተፈሪና ለንግስቲቱ ልመና አቅርበው ነበር፡፡ ተፈሪም ልመናውን ለመፈፀም እስከ ወረኢሉ ድረስ መጥተው እንዲገናኟቸው ቀን ወስነው ንጉስ ተፈሪ ላኩባቸው ይላሉ፤ መርስኤ ኀዘን ወልደቂርቆስ፡፡ ራስ ጉግሳ እሺታቸውን ቢያሳውቁም በተባሉበት ቀን ከመናገሻ ከተማቸው ደብረታቦር ሳይነሱ ቀሩ፡፡ ድጋሚም ቢላክባቸው “ንጉስን እስከ ወረኢሉ ምን የሚያስመጣ ነገር አለ” ብለው ስለጠረጠሩ ለመሄድ አመነቱ፡፡ አሁንም እንድትመጣ ከተባልኩ ይኸው ልነሳ ነው ብለው አስታወቁ፡፡ ግን ሳይነሱ ቀሩ፡፡ ጉግሳ ተፈሪን እያቄለው ነበር፡፡ ተፈሪም ይህ አይጠፋውም መቼም፡፡
ራስ ተፈሪም ትእግስቱ አልቆ የመጨረሻ ሙከራውን  በሚቀጥለው ትእዛዝ ሊፈትነው ፈለገ፡፡ “የጁ ሄደው  በራያ እና አዘቦ ላይ ዘምተው የሚዘራረፈውን የባላገር ከብት እንዲያመላልሱ፤ ለሞተውም እንደ አገሩ ልማድ የነፍስ ዋጋ በማከፋፈል እንዲያስተራርቁ፤ እምቢ ብሎ ያመፀውን እንዲወጉ” የሚል  የንጉስ ተፈሪ ትእዛዝ ተላለፈላቸው፡፡ ተፈሪ ይህን ትእዛዝ የሰጠው ራስ ጉግሳ ወሌ በዚያ እንዲወገድለትና እስከ ወዲያኛውም ሊገላገለው ስለፈለገ እንጂ በኋላ እንደታየው ሰው አጥቶ አልነበረም፡፡ ራስ ጉግሳ ግን ዝመት በተባሉበት ሳይሆን ባልታዘዙበት አገር ዋድላ ላይ ሰፍረው ከረሙ ይላሉ፤ መርስኤ ኀዘን ወልደቂርቆስ፡፡ አያይዘውም፤ የምዋጋበት ጥይት የለኝም ይላክልኝ ብለው ለተፈሪ መልእክት ላኩ፡፡ ራስ ጉግሳ ወሌ ያመፀኛውን አገር ብርታቱንና ሀይሉንም በደንብ ስለተረዱ የሚዋጉበት ምክንያት አልነበራቸውም፡፡ ከነሱ ጋር በመዋጋት ክብርን ከማስደፈር ውጪ ጥቅሙ አልታይህ አላቸው፡፡ ወግተህ ስርአት አስይዝ የተባሉትን ትእዛዝ ወደ ጎን ትተው ከራያና አዘቦ ከዋጅራት ከየጁና ከራሳቸው ህዝብ ከበጌምድር ጋር ተማምለው፣ ንጉሱ የሰጡትን ትእዛዝ ትተው ወደ መናገሻ ከተማቸው ደብረታቦር ተመለሱ፡፡ ከንጉሱ የተላከላቸውን የጥይት ስንቅ  ለአመፀኛውና ለባላገሩ አከፋፍለው በሽልማት መልክ ሰጡ፡፡
“የሚዋጋው የራያና አዘቦና የየጁ ህዝብ እርቅ ገብቶልኛል” ብለው ለንጉስ በስልክ ቢያስታውቁም፣ ተፈሪ ግን እኔ ወደ ደሴ መምጣቴ ነውና  በእርቅ የገባውን የኦሮሞውን ባላባት ይዘው ደሴ ድረስ ይምጡ ብለው ትእዛዝ አስተላለፉ፡፡ ራስ ጉግሳ ግን ወደ ደብረታቦር ተመልሰው ሳንቃ በሚባል ስፍራ አሞኛል ብለው ተቀመጡ ይሉናል፤ መርስኤ ኀዘን ወልደቂርቆስ፡፡ ካሉበት እንዳይንቀሳቀሱ ተብለው ቢታዘዙም ራስ ጉግሳ ግን በራሳቸው ፍቃድ ዋድላ ገብተው ተፈሪን  የሚያስወግዱበትን ንድፍ በደንብ ያደራጁ ጀመር፡፡ መልክ ካስያዙ በኋለ ተመልሰው ደብረታቦር ገቡ፡፡
የጉግሳ ፍፃሜና የተፈሪ የዙፋን መንበር ላይ መቀመጥ
ተፈሪን በብዙ ያገዙትና የጉግሳንም የመንቀሳቀስ ገመድ ካሳጠሩት የዘመኑ ዋነኛ ሰዎች  አንዱ የነበሩት እምሩ ኃይስላሰሴ በመፅሐፋቸው የሚከተለውን ይሉናል፤ “እኔም ያን ጊዜ በያለበት እሳቸውን (ማለትም ራስ ጉግሳን) የሚቃወም አሳባቸውንና ስራቸውን የሚያፈርስ ትልልቅ (ፕሮፓጋንዳ) ነገር ዙሪያቸውን ባለው አገር ላይና  በበጌምድርም አደረግሁ፡፡ ደህና ደህና ብርቱ ሰዎች መርጬ የሚስጥር ሰዎች አቆምሁ፤ በጌምድር ደብረታቦር ድረስ እየሄዱ የራስ ጉግሳን ሁናቴ የጧት የማታውን የሚያስታውቁኝ ነበሩ”፡፡ ሰላይ አሰማርቶ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በመከታተል የአንዳንድ ወዳጆቹን ልብ ማሸፈት ቻለ፤ እነዚህ ወዶ ገቦች መረጃ በማቀበል በብዙ አግዘዋል፡፡
ከሸዋ የዘመተው የንጉሱ ጦር ወረኢሉ መድረስን ሲሰሙ ራስ ጉግሳ ወሌ፤ “በዘመቻ የደከመውን ሰው አሳርፌ ያልዘመተውን አስከትዬ ንጉሱ ወረኢሉ ሲመጡ እመጣለሁ” ብለው ለንግስቲቱ አሳወቁ፡፡ ንግስቲቱ በምላሹ፤ “የንጉስ ጓዙ ተነስቷል፤እርሱም እኩሌታውን መንገድ የሚሄደው በአውቶሞቢል ስለሆነ በቅርብ ቀን ወረኢሉ ይደርሳልና አንተም ገስግሰህ ለየካቲት ኪዳነምሀረት ወረኢሉ እንድትገባ ይሁን” ብለው አሳሰቧቸው፡፡ ጉግሳ ግን  በጣም አዝነው፤ “በኮርቻ ስዞር የከረምሁት ምነው አያስዝኖትም ወይ” ብለው በማሳወቃቸው ከንጉሱ መገናኘት አለመፍቀዳቸው በሹማምንቱና በጦር አለቆቹ ታወቀ፡፡ ራስ ጉግሳ ተፈሪን መጣያ ገመዴ ነው ብለው ያመኑበትን ተፈሪ ኮትልኳል (ካቶሊክ ሆኗል) የሚለውን ዜና አሰራጩት፡፡ ተፈሪ ሀገሪቱንም በካቶሊክ ሀይማኖት ያጠምቃል፤ በዛውም ኢትዮጵያን ለጣልያን አሳልፎ ሊሰጥብህ ነውና ተከተለኝ ብለው ህዝባቸውን ቀሰቀሱ፡፡ ይህ ወሬ ከንጉስ ዘንድ በመድረሱ ይህን የሚያስተባብል በራሪ ወረቀት በአውሮፕላን ተበተነ፡፡ ራስ ጉግሳ በዚህ ውጥኑ ተቀድሞ ነበር፡፡ ራስ ተፈሪ የቤተክርስቲያኒቱን ሙሉ ድጋፍ ማግኘቱን አስቀድሞ አረጋግጦ ነበር፡፡ ጳጳሱም ራስ ጉግሳንና ተከታዮቹን አወገዙ፡፡
የሆነውን ሁሉ በአንክሮ ሲከታተሉ የነበሩት ንግስት ዘውዲቱ፤ “የተከፋህበትስ ነገር ቢኖር እንደዚህ ያለ ተቀይሜያለሁ፣ይህን አድርጉልኝ ብለህ ሳትልክብን ሌላ አሳብ ታስባለህ አልልም፡፡ በአንተ ላይ የሚሰማው ሁሉ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ቀድሞ ባልከው ንጉስ ተፈሪ ሲመጣ ያልዘመተውን ጦሬን ይዤ እገኛለሁ ባልከው መሰረት ተፈሪ ወደ ደሴ ሊመጣ ነውና በእዛው ተገኝ” ብለው አሳሰቡ፡፡ ራስ ጉግሳ ይህን የንግስት ዘውዲቱ ደብዳቤ በዝምታ አለፈው፡፡ ዘውዲቱ የከፋ አደጋ ይደርሳል ብለው ስላሰቡ  ሌላ ደብዳቤ ፃፉ፡፡
“ይህን  ሁሉ የሚያደርገው ንግስት አዘውት ነው እየተባለ ይወራልና አንተስ በዚህ የተነሳ ከሞት ስፍራ ብትደርስና ተዋርደህ ብትወድቅ ምንድን ነው ጥቅምህ? አሁንም በአባትህ በወዳጅህ በአፄ ምኒልክ፣ በእናትህ በእቴጌ ጣይቱ፣ በአባትህም በራስ ወሌ አፅም ብለህ፣ እንደዚሁ እንደላኩብህ ቃል ወረኢሉ ድረስ ቀደም ብለህ ገስግሰህ እንድትመጣ ይሁን”፡፡
ራስ ጉግሳ የሚከተለውን መልስ ፃፉ፤ “የላኩልኝ የስልክ ቃል ደረሰኝ፤ ባየሁትም ጊዜ እጅግ አዘንኩ፡፡ አሁንም ቢሆን ከመገዛቴ በቀር የጃንሆይን አልጋ ንግስትን የጠላሁበት ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ንጉስ ተፈሪን ስለፈራሁ እስር መሮኛልና  ከንጉስ ጋራ የሚያስታርቀኝን ሽማግሌ አላገኝም ብዬ ነው” አሉ፡፡
ራስ ጉግሳ የእርቁን መንገድና ቁርጡን ቀን ስላላሳወቁ የደብዳቤ ምልልሱን ጊዜ መግዣ አድርገው እየተጠቀሙበት እንደሆነ በተፈሪና በተፈሪ ደጋፊዎች ታወቀ፡፡ አከታትለውም ዘውዲቱ የሚከተለውን ላኩ፤ “ያጠፋና የተጣላስ ሰው ጥየቃ ቃል ሲመጣበት ጊዜ  እጄ እንዳይያዝ አስታርቁኝ ይላል እንጂ  በቀድሞ አገሬ ላይ አገር ጨምራችሁልኝ ልታረቅ ብሎ መላክ የሚገባና የሚያዋጣ መስሎ ታየህን? እኔማ እንዲያው ለነገሩ የኋላውን ሀዘን እንዲያስቀርልኝ ከሆዴ ያለውን አሁን ላውጣው ብዬ ነው  እንጂ በምኒልክ አፅም ብዬ ብልክብህ የማይረባ ቃል ከመለስክልኝ ወዲያ እንዲያው ልቤ አልችል ብሎ እናገራለሁ እንጂ ነገሩ በቅቶኛል፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ ግን እወቅ፤ እኔም መጨረሻ ቃሌ ነው፡፡ አሁን ለእጅህ የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ከንጉስ ጋራ ቆርጠን ተነጋግረናልና ብትመጣ ነው መልካሙ”፡፡ ራስ ጉግሳ ወደ አንገታቸው ልትገባ የተዘጋጀችው ገመድ እየጠበቀችባቸው ነበር፤ ምን አልባት ተመሳሳይ ገመድ  በዘውዲቱ የስልጣን አንገት ላይም እየገባ ይሆናል፡፡
ጉግሳ ግን “እርቁን እሺ እታረቃለሁ፤ ነገር ግን የእርቅ ነገር በሽማግሌ ነው እንጂ በስልክ አይደለም፡፡ ሰው ሰድጄ በመሀላ ነገሩ ቢጨረስ መልካም ነው፤ ንጉስ ግን የእርቁ ነገር ሳይጨረስ ጦር እየያዙ ይሰዳሉ” ሲሉ የቅሬታ መልስ ላኩ:: ዘውዲቱ “የተቆረጠ ቃል ስልክብህ ያልተቆረጠ ምላሽ እየላክህ ምነው እኔንስ ታስቸግረኛለህ፡፡ ጦሩስ እኔ ሳልሰማው ንጉስ ብቻ የሰደደው ይመስልሃልን፤ እኔንስ ለምን ከእሱ አሳብ የተለየሁ ታስመስለኛለህ፤ ጦሩንም የላከው ለራያ ኦሮሞ ነበር፡፡ ነገር ግን በገዛ እጅህ ወዳንተው ልታደርገው ነው” ብለው መለሱ፡፡ አሁንም “ከፈቃድ አልወጣም እርቅንም አልጠላም፣ የምትለው እውነትህን እንደሆነ ለአንተ የሚሻልህ  ለእጅህ አምላክ በቃልሀ መዋቀስ ነው”፡፡ ጉግሳ ግን በዘመኑ ቋንቋ መስሚያ አልነበራቸውም፡፡
ተፈሪ ለጉግሳ በፃፉት ደብዳቤ፤ “በግርማዊት ንግስት በኩል ለእኔ የመጣውን የወቀሳ ወረቀት አየሁት፡፡ ከወደ እርሶ የሚሰማው ምላሽ ግን የልብ ያልሆነ ቁርጥ የማያስታውቅ ቃል ሆነ፡፡ መወቃቀስ ቢሆን ምን የሚያስተፋፍር ጠብ ኖሮን ነው ለእጅዎ እስከ መስጋት ያደረሰዎ፡፡ አባታችንስ ያቆዩን ፍቅር ነው እንጂ  ምን ጠብ አለን፡፡ አሁንም ከዚህ ቀደም ያለውን ጠብ እርሶ ካበረዱት ለእጆ ክፉ ሀሳብ የለምና ይመኑኝ” የሚል አንጀትን እሚያላውስ ደብዳቤ ላኩ፡፡ ጉግሳም ”ቃልዎ ደርሶኛል፤ እሺ እታረቃለሁ” አሉ፡፡ ተፈሪ ግን “ለምንድን ነው እሺ እሺ እያልክ ጊዜያችንን የምትበላው” ብለው በድጋሚ ቁርጡን ብቻ ያሳውቁን አሉ::
ይህ ሁሉ የደብዳቤ ምልልስ ቢኖርም ራስ ጉግሳ ወሌ በመጨረሻ ጦራቸውን ክትት ብለው የተፈሪ ጦር አዛዥ ደጃዝማች ሙሉጌታ ወደ ሰፈሩበት ደላንታ ጉዞ ጀመሩ፡፡ በአውሮፕላን እንቅስቃሴያቸውን ሲከታተል የነበረው አብራሪው፣ የጉግሳ ጦር ለጦርነት ዝግጅቱን ጨርሶ ወደ እርሶ እየመጣ ነው ሲል ለደጃዝማች ሙሉጌታ አሳወቀ፡፡ መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም አንቺም በሚባል ቦታ ጦርነት ገጠሙ፡፡ ራስ ጉግሳ እጄን አልሰጥም ብሎ በጀግንነት ቢዋጋም፣ በጦርነቱ መሀል ቆስሎ ከጥቂት አፍታ በኋላ በ53 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡ ዘውዲቱም በዚያው ሰሞን አረፉ፡፡ ተፈሪም ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ለመሆን በቃ፡፡ መንበሩ ላይ ለ44 አመታትም ለመቀመጥ ቻለ፡፡
መደምደሚያ
ራስ ተፈሪ የአፄ ምኒልክ ባለሟሎችና ሚኒስትሮችን አንድ በአንድ ከስልጣን መሻርና ማስወገድ የቻለው መሀል ሰፋሪ በሚባለው የአድማ ስብስብ ታግዞ ነበር፡፡ በ1966 ዓ.ም የመሀል ሰፋሪ አምሳያ የሆነ ደርግ የሚባል ስብስብ ተመሳሳይ ነገር አደረገ፡፡ የንጉሰ ነገስቱን  ባለስልጣናት አንድ በአንድ ሲያስርና ሲገድል ቆይቶ በመጨረሻም ንጉሱን ገደለ፡፡ “በአንተ እንዲደርስ የማትፈልገውን በሌላው አታድርስ” የሚለውን አምላካዊ ትዕዛዝ ራስ ተፈሪ ዘንግቶት፣ በሌሎች ላይ ሲያደርስ የነበረው በእሱም ላይ ደረሰ፡፡ ይህ ህግ ለፖለቲከኞች  አይሰራ ይሆን?
ከአዘጋጁ፡-
ደረጄ ጥጉ፤ የመጀመሪያ ዲግሪውን በፍልስፍና ከአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ በ1998 ዓ.ም የወሰደ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከቻይና ዉሃን ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ ኢንተርናሽናል ሎው በ2009  ዓ.ም አግኝቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ፍልስፍና እና አለም አቀፍ ህግ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡


Read 381 times