Friday, 28 June 2024 17:31

ታሪክና አገርን በጭፍን ከማጠልሸት በጭፍን ማስጌጥ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

“ያለፉት ሥርዓቶች”… ብሎ የሚጀምር ንግግር ምን አስከትሎ እንደሚመጣና አጨራረሱ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት አያቅታችሁም። ለውንጀላ ጣት ይቀስራል። ከባሰም፣ በዛቻ ስሜት ጣቱን ይነቀንቃል። ከለየለትማ “ጦር እንደመስበቅ” ይቆጠራል።
“የቀድሞ ሥርዓቶች፣ ያለፉት መንግሥታት፣ ገዢዎች”… ብሎ ከተንደረደረ፣ በጎ ታሪክ ለማውራት አይሆንም። ክፉና በጎውን እንደየ ልካቸው ለመጥቀስም አይደለም። ለማውገዝ ነው። የአገሪቱ ታሪክ ሁሉ “ገሀነም” መስሎ ይታያችኋል። የድሮ ዘመን በአካል መጥቶ የሚዘምትባችሁ “ደመኛ ጠላት” ይሆንባችኋል (በእውን ሳይሆን በምናብ)። “ለውጥ” የሚል መፈክር ያምራችኋል።
“ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን”… ብሎ ንግግሩን ከጀመረ ደግሞ በቃ… አገራችን ድሮ ጥንት “ቅድስቲቱ ገነት” እንደነበረች የሚያበሥራችሁ ይመስላል። ጥንታዊ ታሪክ ማለት የወርቃማ ዘመን ታሪክ ማለት ነው ያስብላችኋል። ቅንጣት አያጠራጥርም፣ ማስረጃም አያስፈልገውም - “ምድረ ቀደምት” እንደሆነች ይነግራችኋል። ግን ምን ዋጋ አለው! ያ ሁሉ ዛሬ የለም። ድሮ ቀረ! በቁጭት ያብሰለስላችኋል።
እንዲህ ለውድቀት የዳረጓት ዘመን አመጣሽ ምክንያቶችን ነቅለን ለመጣል፣ ለቅመን ለማስወገድ ያነሣሣናል። ታሪካዊ ጠላቶችና የውጭ ኃይሎች፣ ለመጤ ባህል የተገዙ ከንቱ ትውልዶችና የውስጥ ከሀዲዎች… ያው፣ ይሄኛው ንግግርም እንዲሁ፣ ለውንጀላና ለዛቻ ጣቶቹን ማንሣቱ አልቀረም ማለት ነው። ከዚያም “በጦር በጎራዴ”… ብሎ ይፎክራል።
በነገራችን ላይ፣ እንዲህ ስል ሁለቱም ላይ ጣቴን ለመቀሰር አይደለም። በእርግጥ የቀሰርኩ ይመስላል። ግን… ማለቴ…
ሁለቱም ንግግሮች ሙሉ ለሙሉ ስህተት ናቸው እያልኩ አይደለም። የየራሳቸው “እውነት” አላቸው። …ቢሆንም ግን በጣም የተሳሳቱ አስተሳሰቦች መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በእነሱ ጫማ ውስጥ ሆነን ስናስበው ግን…
(ይበቃል፤ ይበቃል። “ጣት አልቀሰርኩም” ለማለት ይሄ ሁሉ መጠማዘዝ ምንድነው? አቅጣጫ እየለዋወጡና እየተጠማዘዙ ሐሳቦችን ከማደፍረስ ይልቅ፣ አንደኛውን ጣት መቀሰር ይሻላል ልትሉ ትችላላችሁ። መልካም ብላችኋል)።
ወደ መነሻ ሐሳባችን እንመለስ።
“ያለፉት የቀድሞ ሥርዓቶች” ብሎ የሚጀምር ንግግር ከሰማችሁ፣ ነባሩ አገር እንደ ገሀነም ጠቁሮ ይታያችኋል። ታሪክም የወንጀል ምርመራ መስሎ ይታያችኋል። በተበዳይነት ስሜት መቆዘም ያሠኛችኋል። ወይም ደግሞ የማፍረስና የበቀል ስሜት ይፈጥርባችኋል። በጊዜ ወደ ኅሊና ካልተመለስንም፣ በየፊናችን የተለያዩ የለውጥ መፈክሮችን ይዘን እርስ በርስ መጠፋፋት እንጀምራለን።
“የቀድሞ አባቶቻችን፣ የጥንት እናቶቻችን” ብሎ ከጀመረ ደግሞ፣ ለካ አገራችን ጥንታዊቷ ገነት ነበረች ያስብለናል። ታሪክ ማለት “ድሮ ቀረ!” ብለን እንተክዛለን። ወይም ደግሞ “ገነቲቱን ያረከሱብንና የነጠቁን ጠላቶች” ላይ ክንዳችንን እንድናነሣ ይገፋፋናል። አእምሮ ካልገዛን፣ ያው በየፊናችን የአገርና የታሪክ ጠበቃ እንደሆንን እያወጅን እርስ በርስ ለመጠፋፋት እንዘምታለን።
ትልቁ ጥያቄ እዚህ ላይ ነው። ሁለቱም አስተሳሰቦች ጭፍን ስህተቶች ከሆኑ፣ ለምንድነው ገናና አስተሳሰቦች ሲሆኑ የምናየው?
እንደማንኛውም ስህተት፣ እንደማንኛውም ውሸት፣ “ግማሽ እውነት” ወይም “ግማሽ ትክክል” የሆነ ሐሳብ የያዙ ናቸው። (ይህን እንደ መጠማዘዝ አትቁጠሩት! “ቅንጣት እውነት ያልያዘ ንጹሕ ውሸት” ብሎ ነገር የለም። የተሳሳተ ሐሳብም እንዲሁ፣ ግማሽ ትክክል የሆኑ ሐሳቦችን መያዙ አይቀርም)።
እዩና ፍረዱ።
“የቀድሞ ሥርዓቶች” ብለው ታሪክን የሚያጠቁሩ ሰዎች፣ እንዲሁ ያለ አንዳች ሰበብና ማመካኛ አይደለም የሚናገሩት። መቼም ዛሬ አገራችን ውስጥ የምናያቸው ችግሮች በሙሉ፣ ዛሬ ወይም ዘንድሮ ብቻ የተፈጠሩ ትኩስ ችግሮች አይደሉም። ጦርነቱም፣ ድህነቱም፣ ኋላቀርነቱም… ብዙ ዘመናትን ያስቆጠሩ ባለረዥም ዕድሜ ችግሮች ናቸው።
መከራችን የበዛው ያለ ምክንያት ሊሆን አይችልም። “ያለፉት ሥርዓቶች”… ብለን ማማረርና ማውገዝ የምንጀምረው ይኼኔ ነው። ለማፍረስም እንሽቀዳደማለን እንጂ። ግን ምን ዋጋ አለው? የተሻለ ነገር ለመሥራትና ለመጨመር እንደምንችል ሳናረጋግጥ ነው ነባሩን ለማፍረስ የምንቸኩለው። ከነባሩ ሐሳብ የተሻለ ትክክለኛ ሐሳብ ለመያዝ ሳንጥር ነው፣ የቀድሞውን ለማጣጣልና ለማውገዝ የምንሮጠው።
ይህም ብቻ አይደለም ስህተታችን። እንዲያው በሆነ መንገድ የተሻለ ሐሳብና ብቃት፣ የተሻለ ጥበብና ትጋት ቢኖረን እንኳ፣ ከሌላ ፕላኔት አልመጣንም - ከዚሁ አገር እንጂ። እንደ “ቢግ-ባንግ” ድንገት አልተፈጠርንም - ከነባር ወላጆችና አስተማሪዎች፣ ከነባር ባህልና ሥርዓት ውስጥ እንጂ። በሌላ አነጋገር፣ በጭፍንና በደፈናው “የቀድሞ ሥርዓትን” ወይም “ነባሩን አገር” መተቸት፣ ራስንም ጭምር ዋጋ የሚያሳጣ፣ እርስ በርሱ የሚምምታታ ንግግር ውስጥ እንደመስከር ይሆናል።
ደግሞስ፣ በሆነ ጊዜ በሆነ ቦታ፣ በዕውቀትና በጥበብ መልካም ነገር ለመሥራት የበቁ ብልኅና ትጉህ ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ፣ እንዴት ለሺ አመታት የሚሻገር የአገር ታሪክ ተፈጠረ? በየጊዜው የሚከሰት ጥፋትና ክፋት ይኖራል። ነገር ግን በጊዜው በሥልጣኔ ለመገሥገሥ የቻሉ ታሪክ ሠሪዎች ባይኖሩ ኖሮ፣ የጨዋነት ባሕልና አስደናቂ ቅርሶች ከወዴት መጡ?
እንግዲህ፣ ግራ ቀኙን አገናዝበን ስናየው፣ ወደድንም ጠላንም፣ “የቀድሞ ታሪኮች ያለፉት ዘመናት”… በደፈናው “ሲኦል” ወይም በደፈናው “ገነት” ተብለው የሚወገዙና የሚወደሱ አይደሉም የሚል ድምዳሜ ላይ ነው የምንደርሰው። በጭፍን ማውገዝ ወይም በጭፍን ማወደስ… ለንግግር ማራኪ፣ ለሐሳብም ቀላል መስሎ ሊታየን ይችላል። ነገር ግን፣ በቀላሉ ከሐሳብ ለመገላገልና በከንቱ ንግግርን ለማስጮህ ብለን፣ ከእውነታና ከዕውቀት ጋር ብንጣላ ምን ዋጋ አለው? ቀሽም አስቀያሚ ታሪክ ከመሥራት ያለፈ ሌላ ቅንጣት ዐቅም አይኖረንም።
ይልቅስ፣ እውነታን የማክበርና ዕውቀትን የመውደድ ቀና መንገድ ውስጥ ብንገባ፣ ከታሪክ መማር እንችላለን። ይህም ብቻ አይደለም። ለበጎ የሚያነሣሡ መልካም አርአያ አብነቶችን እናገኝበታለን።
የመጀመሪያው ነጥብ፣ ከታሪክ መማር ነው - (ጠቃሚና ጎጂውን፣ ክፉና ደጉን ማወቅ ያስፈልጋል። አስጊጦ ማቆንጀት ወይም ጥላሸት መቀባት አይኖርብንም)።
ሁለተኛው ነጥብ፣ መልካም አርአያ ማግኘት ነው - (ለዚህም… ጎጂውን ትተን ጠቃሚው ላይ ማተኮር፣ ከክፉ ርቀን መልካም መልካሞቹን መውደድና ማክበር ይጠበቅብናል)፡፡
እነዚህን ሁለት ነጥቦች ይዘን፣ እንደገና ወደ መነሻ ሐሳቦቻችን እንመለስና እንመርምራቸው።
አንደኛው… “ያለፉት ሥርዓቶች” በማለት በደፈናው ታሪክንና ባህልን ያማርራል፤ ያወግዛል።
ሌላኛው ደግሞ… “ቀደምት አያቶቻችን” በማለት በደፈናው የቀድሞ ታሪክንና ባህልን ያወድሳል። ይኸኛው የአስተሳሰብ ቅኝት እንደተቀናቃኙ የተሳሳተ አስተሳሰብ ቢሆንም፣ ቢያንስ ቢያንስ በጎ በጎ ላይ በማተኮር መልካም አርአያዎችን አጉልቶ የማውጣት ዕድል ስለሚኖረው፣ “ትንሽ ይሻላል” ማለት እንችላለን። በደፈናው ከማጠልሸት በደፈናው ማስጌጥ አይሻልም?
በዚያ ላይ፣ ከጭፍን ጥላቻ መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ መልካምን ነገር የማመስገን የማድነቅና የማክበር በጎ መንፈስና መላበስ ነው ስልጡን ባህል ማለት።
ደግሞም፣ ቸል እያልነው ነው እንጂ እንደመታደል ሆኖ ለስልጡን ባህል ባዳ አይደለንም። ብናምንበትም ባናምንበትም፣ “መልካምነትን በማክበር ላይ የተመሠረቱ ሃይማኖቶችን” የማክበር ባህልና እርስ በርስ የመከባበር ዝንባሌ ለአገራችን እንግዳ አይደለም።
በየጊዜው በርካታ ስህተቶች በርካታ ጥፋቶች ስላልተፈጸሙ አይደለም። በየቦታውና በየዘመኑ እልፍ ጥፋቶችና አሳዛኝ መከራዎች ታይተዋል። ድሮስ ላይታይ ነው?
ጥፋት ያተፈጸመበትና መከራ ያገጠመው አገር የለም። በውጭ ወረራና በእርስ በርስ ጦርነት ያልተተራመሰ አገር የለም። አንድም የለም።
“አብዛኛው አገር” ሳይሆን፣… “ሁሉም አገር”… ከውጭና ከውስጥ በብዙ ጦርነት ታምሷል። አንዴ በዘረኝነት በሽታ፣ ሌላ ጊዜ በሃይማኖት ሰበብ፣ ብዙውን ጊዜ በስልጣን ፉክክር፣… ምናለፋችሁ በጭፍን ጥላቻ አለያም በማይረባ ማመካኛና በተራ ስህተት ሳቢያ ለንግግር የሚከብዱ ጥፋቶች ደርሰዋል።
ልዩነቱ ምኑ ላይ ነው? በእነዚሁ ስህተቶችና ጥፋቶች መሀል፣ ይብዛም ይነስ የአገር ህልውናን ከጥፋት የሚያድንና ለዘመናት ጠብቆ የሚያቆይ ታሪክ ተሠርቷል ወይ? ከዘርና ከሃይማኖት ልዩነት ባሻገር ተከባብሮ የመኖር ሙከራና እንደ ስንቅ የሚያገለግል ዝንባሌስ ተፈጥሯል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ላይ ነው ልዩነቱ።
እዚህ ላይም ነው የኢትዮጵያ ልዩነት።
ኢትዮጵያ እንደሌሎች አገራት ከስህተትና ከጥፋት ባታመልጥም ለእልፍና ለእልፍ ዓመታት በህልውና ለመቀጠል ከቻሉ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ናት። ጃፓን፣ ራሺያ፣ ኢትዮጵያ… ሌላ ማን አለ? ሌላ እንደሌለ ነው ታሪክ ተመራማሪዎች የሚነግሩን።
በአንድ በኩል መታደል ነው። የወራሪዎች መጫወቻ ከመሆን መዳን ቀላል ነገር አይደለም። ከቅኝ ግዛት ጋር አብሮ የሚፈጠር የውርደትና የተጎጂነት፣ የጥላቻና የዝቅተኝነት ስሜት ለብዙ ዘመን የሚዘልቅ የመንፈስ ጠባሳ ነው። ከዚህ መዳን መታደል ነው።
የጥበባቸውና የብቃታቸው ያህል በብርቱ ጥረትና በጽናት የአገርን ህልውና ጠብቀው ማቆየት የቻሉ ሰዎች ምስጋና ይግባቸው። “የቀድሞ አያቶቻችን” ምስጋና ይገባቸዋል ብንልም ያስኬዳል። “ሁሉም አያቶች” ለማለት አይደለም። የጅምላ ዳኝነትና የጅምላ አድናቆት ከንቱ ነው። እናም “የቀድሞ አያቶች…” ሲባል የቀድሞ ሰዎች መሆናቸውን ለመግለጽ ያህል እንጂ፣ እያንዳንዱ ሰው እንደየ ሥራውና እንደየ ባሕርይው ነው መመስገንም መወቀስም የሚኖርበት። ይህን እስከተገነዘብን ድረስ፣ የቀድሞ አያቶቻችን ምንስጋና ይግባቸው ብንል ስህተት የለውም። ለአገር ሕልውናና ለነጻነት ባበረከቱት ድርሻ መጠን ነው ምስጋናው።
ድርሻ ማበርከታቸው፣ ለነሱ ኩራት ነው። (“ለቀድሞ አያቶቻችን” ኩራት ነው)።
ከነሱ ቀጥሎ ለሚመጣው ትውልድ ደግሞ ዕድል ነው። የአገር ባለቤት ሆነዋልና። በእርግጥ፣ “ዕድለኛ” መሆን በቂ አይደለም። በየዘመኑ ብዙ አዳዲስ አደጋ ይፈጠራል። በየዘመኑም አገርን ከአደጋ የማዳን ጥራት ያስፈልጋል።
የቀድሞ ጥበበኞችንና ደግኖችን እያመሰገኑ እያሞገሱ፣ በተራቸው ተጨማሪ መልካም ታሪክ የሚሰሩ ሰዎች ባለመጥፋታቸው ነው የአገር ህልውና ለእልፍ ዓመታት ከዚያም ለእልፍ ዓመታት ሳይቋረጥ የሚቀጥለው።
በዝርዝር ብናውቀውም ባናውቀውም፣ አገራችን እንዲህ ዐይነት ታሪኮች አሏት።
እዚህ ላይ፣ “መጥፎ የጥላቻና የመጠፋፋት ታሪኮችምኮ ተፈጽመዋል” የሚሉ የወቀሳ ሐሳቦች መነሣታቸው አይቀርም። የወቀሳ ሐሳቦች የሚመጡት፣ በደፈናው ወይም በዝርዝር፣ በቅንነት ወይም በክፋት ስሜት ሊሆን ይችላል። መምጣታቸው ግን አይቀርም።
“የጥፋትና የጥላቻ ታሪክ ከአገራችን አጠገብ ደርሶ አያውቅም” ብሎ የሚከራከር አላዋቂ ገጥሟቸው ነው?
“ገና ጥንት፣ ገና ከመነሻው፣ ኢትዮጵያ የሥልጣኔና የፍጽምና አምባ ሆና መፈጠር ነበረባት። ግን ከስህተትና ከጥፋት ስላላመለጠች እናውግዛት” ለማለት ነው?
“የቀድሞ ዘመን ሰዎች በእውቀትና በጥበብ በሙያና በስነምግባር ቅንጣት እንከን የማይወጣላቸው የስልጣኔ ተምሳሌት መሆን ነበረባቸው” ለማለት ነው? እንዲህ ዐይነት “መላእክት” የመሳሰሉ ሰዎችን ብቻ የያዘ አገር በየትኛው ዘመን ኖሮ አያውቅም። ወደፊትም አይኖርም።
እንዲህ በጭፍን ስሜት ካልተነዳን በቀር፣ “እንከን የለሽ የቀድሞ አያቶቻችን” ብለን በደፈናው ለማወደስ፣ አለያም “ጎጂና መጥፎ ታሪኮችም ተሰርተዋል” ብለን አገርንና ታሪክን ለማውገዝ እየተሽቀዳደምን ከንቱ አተካራ እንፈጥራለን? ለምን ብለን?
አንዳንዴ ግን፣ ነገረ ሥራችን እንደዚያ ይመስላል። ማለትም የአንዳንዶቻችን ነገረ ሥራ። ማለቴ የአንዳንዶቹ ሰዎች ነገረ ሥራ።

Read 272 times