Saturday, 22 June 2024 00:00

የድህነትና ፖለቲካ ኤኮኖሚክስ

Written by  ስንታየሁ ገ/ጊዮርጊስ
Rate this item
(0 votes)

1.  እንደ መግቢያ
ባለፈው ሳምንት የድህነትንና ብልጽግናን ታሪካዊ ዳራ አንስቼ ዳር ዳሩን ሳጫውታችሁ፣ ዓለም [የዓለም ባንክ፣ አይኤም ኤፍና ዕዳ የተጫናቸው ድሀ አገሮች (Higly Indepted Poor Countries (HIPIC)] እና ኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስ ስለ አከናወኗቸው ተግባራት፣ በተለይ በኢትዮጵያ ተካሂዶ የነበረውን የድህነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነድን (Poverty Reduction Strategy Paper (PRSP)) አስመልክቶ በሚቀጥለው ጽሁፍ አንደምመለስበት በመግለጥ ጨዋታዬን በእልባት[1] አኑሬው ነበር፡፡ ለጊዜው ቃሌን አልጠበቅሁም፡፡  
በኢትዮጵያ ውስጥ ተካሂዶ ወደ ነበረው የድሕነት ቀነሳ ስትራተጂ ሰነድ ጉዳይ በዝርዝር ከመግባቴ በፊት በቅድሚያ አንዳንድ ነገሮችን አንስቼ ላወጋችሁ ፈለግሁ፡፡ አሁን ላጫውታችሁ የተነሳሁበት ጉዳይ በርዕሱ የምትመለከቱት “የድህነትና ፖለቲካ ኤኮኖሚክስ” የሚል አጫዋች ሀሳብ ነው፡፡ ድህነት በፖለቲካ፣ ፖለቲካ ደግሞ በድህነት ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አንድነትና ልዩነት ቀለል አድርገን በማየት ለወደፊት ለማነሳቸው ጉዳዮች፣ የቱ በማንኛው ላይ ተጽዕኖ እንዳደረገ በመቃኘት፣ በጋራ ለመፍረድ እንድንችል በማለት ያደረግሁት ነው፡፡ ድሕነት የተወሳሰበ በመሆኑ ቀለል አድርገን ልናየው በምንችልበት መንገድ መመልከቱ አግባብ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በየመንገዱ የምናየውን “ድሐ” (የእኔ ቢጤ) በመመልከት ብቻ ድሕነት ማለት እሱ ነው፣ ያ ነው ለማለት አንችልምና ፍቺውንና (አካዳሚያዊ ቢመስልብንም) መፍትሔውን መወያየት መልካም ነው፡፡  
ድህነት ምን ማለት ነው? ብሎ በመጀመር ለውይይት መነሳት፣ በድህነት ላይ ትኩረት ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ በሌላ በኩል፣ ድህነት ምንም ገለጻ አያስፈልገውም፤ ራሱን በራሱ የሚገልጽ፣ ሁሉም ሰው ከራሱና ከሌሎች የኑሮ ማጀት የሚያውቀው ጉዳይ ነው በማለት፤ ከመወያየት ይልቅ በመፍትሄዎች ላይ ማትኮር ይቀድማል የሚሉ በርካቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የውይይት አቅጣጫዎቹ በርካታ ናቸው፡፡
በድህነት ላይ ውይይትን ማድረግ እንደ አንድ የመፍትሄ አካል አደርጎ በመውሰድ፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ችግሩን ተመልክቶ ለተግባራዊነቱ የጋራ አቋም (የፖሊሲ አቅጣጫ) መያዝ አስፈላጊ መሆኑን በግሌ አምናለሁ፡፡ ስለ ድሕነት ዘወትር ማውራት በሕዝብና በመንግሥት ትኩረት ውስጥ እንዲውልና እንዲያድር ይረዳል በማለት ማሰብም ቅንነት ነው፡፡ አብረውት የዋሉትና ያደሩት ነገር ሁሉ በቀላል አይረሳም፡፡ እንግዲያማ ድሕነት ምኑ መልካም ገጽታ አለውና ይወራለታል?
ድህነትን መግለጥ ወይም መተንተን ለምን ያስፈልጋል? ለሚለው፣ አጭር የሆኑ መንደርደሪያዎችን ለማሳየት ልሞክር፡፡
1ኛ/    ድህነት በየት ሥፍራ፣ በምን መጠንና ጥልቀት ላይ እንደሚገኝ መረጃ ለማግኘት ውይይቱ እንደ መነሻ ያገለግላል፤
2ኛ/    መረጃን በመተንተን፣ ማን በምን ያህል መጠን መደገፍ እንደሚገባው ለማወቅ ዕቅድን ያዘጋጃል/ይተልማል፣
3ኛ/    የአገሪቱን የድህነት ደረጃ ለማሳየት መነሻ ከመሆኑም በላይ፣ በውይይት መድረክ ላይ ጎልቶ እንዲወጣና በእያንዳንዱ ዜጋ አእምሮ ውስጥ እንዲቆይ ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ ይህም ጉዳይ ድህነትን ለመቀነስ ምን እየተደረገ ነው? የሚለው ጥያቄ ፊት ለፊት እንዲቀመጥ (እንዲታይ) ዕድልንና የተነሳሽነት እልህን ይፈጥራል፡፡ በአንድ ወቅት ብቻ ብልጭ ብሎ የሚጠፋ ሂደት አይሆንም፣  
4ኛ/    አንድ አገር የሕዝቦቿን የድህነት መጠንና ጥልቀት ሳታቋርጥ እንድትከታተልና፣ ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችል ፖሊሲዎችን በመቅረጽ እርምጃዎችን ሳታሰልስ እንድትወስድ ለማድረግ ይረዳል፣
5ኛ/    ድህነት በአይነቱ ከአንድ በላይ (በርካታና የተወሳሰበ) በመሆኑ፣ እያንዳንዱን የድህነት ዓይነት በዝርዝር በማየትና እርምጃዎቹንም በማስተባበር፣ አጠቃላዩን አገር አቀፍ የድህነት መጠንን በቅደም ተከተል ለመቀነስ የሚያስችል መተማመንን ያሰፍናል፣ ያሰርፃል፡፡
2.  ከድሕነት የመላቀቅ ጥያቄዎች ኤኮኖሚ ተኮርና ፖለቲካዊም ሆነው ሊታዩ ይችላሉ
በሁሉም አገራት የሚገኝ ሕዝብ መንግሥትን የሚጠይቃቸው የኤኮኖሚና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች አሉት፡፡ እኔ የማተኩረው በኤኮኖሚ ጥያቄዎቹ ላይ ነው፡፡ ጥያቄ ስለምወድ በምጠይቃቸው ጥያቄዎች አትሰልቹ፡፡  
ሕዝብ መርጦ እንዲያስተዳድረው የሰየመውን መንግሥት መልካም አገልግሎት እንዲሰጠው ሊጠይቀው ይችላል፡፡ እንድከፍል ከምገደዳቸው ግብሮች፣ ታክሶችና ቀረጦች የምትሰበስበው ሀብት (ገንዘብ) በቀጥታ ለእኔ አገልግሎትና ለልማት ለምን አልዋሉም? መሠረታዊ የሆነውን የምግብ ፍላጎቴን እንዳላሟላ እንኳን የዳቦ ዋጋ በመጠን እያነሰ በዋጋ ሲያሻቅብ ለምን ዝም ትላለህ? በማለት ሊጠይቅ ይችላል፡፡ እነኚህ እንደ ምሳሌ የቀረቡ ቀላል የኤኮኖሚ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹ ፖለቲካዊ አንደምታ ሊኖራቸው ቢችል ባህሪያቸው በመሆኑ ነው፡፡
ፖለቲከኞች ጥያቄዎችን በሙሉ ከፖለቲካ ጋር ያያይዟቸዋል እንጂ፣ በተገልጋዩ ሕዝብ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ሁሉ የፖለቲካ ጥያቄዎች አይደሉም፡፡ መሠረታዊ የኤኮኖሚ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ፖለቲካ የሚያደርጓቸው ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ቀላል በማይባል ሁኔታ ፖለቲካና ኤኮኖሚ አንዱ በሌላው ላይ ተጽዕኖን የሚያደርጉ በመሆኑ፣ መንግሥት (ፖለቲካው) ጥያቄዎቹን በዋዛ ላይመለከታቸው ይችላል፡፡ ተገልጋይ ሕዝብ መንግሥትን ተገቢ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥትም ተገቢ የሆነ መልስን ሊመልስለት ይገባል፡፡
3. የመንግሥት (የፖለቲካው) እና የግል ሀብት ለድሕነት ቅነሳው ነፃነት
መሠረታዊ ከሆነው የዳቦ ጥያቄ ውጪ የሚገኙ ሌሎች መሠረታዊ የኤኮኖሚ ልማት ፍላጎቶችና ሀብትን ማፍራት እንዲቻል የሚቀርቡ ጥያቄዎችም አሉ፡፡
ሁሉም ነገር የግል በሆነበትና የግል ሀብትና የፈጠራ ውጤቶች በሙሉ ባለመብትነት በሕግ በሚጠበቁበት ዓለም ውስጥ ጥያቄዎች ሁሉ ለመንግሥት አይቀርቡም፡፡ መንግሥት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ የሁሉም ሀብት ባለቤት አይደለም፡፡ ያደጉ አገራት በየዘርፉ ያደጉትና የበለጸጉት፣ የግሉ ዘርፍ መንግሥት ላይ የተለጠፈ ባለመሆኑ ነው፡፡ መሬት የመንግሥት በሆነበት ታዳጊ አገር ግን ፈቃጁም ሆነ ሻጩ መንግሥት ብቻ ነውና ጉዳዩ ይወሳሰባል፡፡ መሬቱ የእኔ፣ የአንተ ንብረት ከመሬቱ ላይ የተቀመጠው ቤት ብቻ ነው በማለት ሕዝብን ያሳሳባል - መንግሥት፡፡ ለልማት የሚውሉ ሀብቶች በአብዛኛው በመንግሥት እጅ በሚወድቁበት ወቅት ልማትና የድሕነት ቅነሳ ነፃ አይሆኑም፡፡ ልማትና ብሎም የኤኮኖሚ ዕድገት የድሕነት ቅነሳ አንድ አካል ነው፡፡ ይህንን ለምሳሌ ብቻ ያቀረብኩት መሆኑን ያዙልኝና ጨዋታዬን ልቀጥል፡፡
ሥራን በመሥራት ራሳቸውን ጠቅመው አገርን ለማልማት የሚነሳሱ የአደጉ አገራት ዜጎች፣ ለሠሩት ልማት ባለቤቶች ናቸው፡፡ ያንን ለማድረግ መሬትን ከመንግሥት አይለምኑም፡፡ መሬት የሚሸጥና የሚለወጥ የግል ሀብት ነው፡፡ ያፈሩት ሀብት (መብታቸው) በሕግ የተጠበቀላቸው በመሆኑ ፖለቲከኞችን ሲያዩ አይሸማቀቁም፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ፖለቲከኞችን አይለማመጡም፡፡ የሚጠይቁት በዜግነት ያላቸውን መብት ብቻ ነው፡፡ ፖለቲከኞቹም የዜጎችን መብቶች ያከብራሉ፡፡
የግል ባለሀብቶች ያከማቹት ሀብት በእጃቸው ካለ በራሳቸው ሀብት፣ ገንዘብ/ሀብት ያጠራቸው ከሆኑ ደግሞ በባንክ ብድር የግል ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ ብድር የሚሰጣቸው (ሰ ይጠብቃል) በሚያቀርቡት ፕሮጄክት ጠቃሚነትና ትርፋማነት እንጂ በማንነታቸው አይደለም፡፡ ከሶሻሊስታዊ መርህ ጋር ተበራርዞ በሚመራ የመንግሥት ፖሊሲና መዋቅር ላይ የማንነት ፖለቲካ ቃጭል ሲጨመርበት፣ የዜጎች የንብረት ዋስትና በማንነታቸው ጭምር ሊቃኝ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ የግሉን ሴክተር በኤኮኖሚ ለማልማት እንቅፋቱ በርካታ ነው፡፡ የጠቃቀስኳቸው ጉዳዮች ጥቂቶቹን ብቻ ነው፡፡
ያደጉ አገራት ከላይ የጠቀስኳቸውን በማድረጋቸው በአገራቸው ድሕነትን አጥፈተዋል? ወይንስ የግልና የአገር ሀብት እንዲከማች አድርገዋል? ብሎ መጠየቅ ግን አግባብነት አለው፡፡ መልሱ፣ ድሕነትን አላጠፉም የግል ሀብት እንዲያድግና እንዲከማች ግን አድርገዋል፡፡ የግልንና የአገርን የሀብት ክምችት፣ በአጠቃላይም የአገር ውስጥን ምርትና የአገልግሎትን መጠን አሳድገዋል፡፡
የአደጉ አገራት የልማት ፖሊሲያቸው (ለምሳሌ፣ ዩናይትድ ስቴትስ)፣ የአገርን የግል ሀብት ክምችት ማሳደግ ለድህነት ቅነሳ (ድሆችን) ይጠቅማል የሚል ነው፡፡ ፖሊሲያቸው የተቀረጸው ድሕነትን በመቀነስ ስልት ላይ አይደለም፡፡ በእርግጥ ድህነትን የመቀነሻ ስልቶች ሊያወያዩ የሚችሉ ናቸው፡፡
አንዳንዶቹ ድሕነትን መቀነስ የኤኮኖሚ ዕድገትና የሀብቶች ልማት (ብልጽግና) የሚፈጥረው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ የግል ሀብት ሲያድግና አገር ሲለማ ቀስ በቀስ ድሆች ሥራ እያገኙና አምራችና ባለሀብት እየሆኑ ይሄዳሉ ይላሉ፡፡ ሌሎች ይህንን አባባል/አካሄድ የጠብታ ውጤት/ተጽዕኖ (trickling effect) ብቻ የሚኖረው በማለት ያፌዙባቸዋል፡፡ እናንተ ሀብት እያከማቻችሁ፣ ሌሎቹ/ድሆቹ ርሀባቸውን በጠብታ ውኃ ቀስ በቀስ እንዲያርሱ ትፈልጋላችሁ በማለት ይተቿቸዋል፡፡ ጠብ ጠብ እያለ በሚቀርብ ድጎማ (ለምሳሌ፣ በዌልፌር ሥርዓት) ድህነት ሊወገድ እንደማይችል ይከራከራሉ፡፡ እይታ ከቆሙበት ቦታ አንጻር ነው፡፡
በዩናይትድ ስቴትስ ባሉት ሁለት ግዙፍ ፓርቲዎች መካከል ከሚሰሙት የፖለቲካ ክርክሮች አንዱ ይህን ዓይነት ነው፡፡ ሁለቱም ፓርቲዎች ግን ድሕነትን የሚያጠፋ እርምጃ ለመውሰድ ዘገምተኛና ልግመኛም ጭምር ናቸው፡፡ ሁለቱም በጋራ የሚስማሙባቸው አንድ ጉዳይ ቢኖር፣ የግል ሀብት እንዲያድግ በሚያወጧቸው ሕግጋትና ፖሊሲዎች ላይ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ፖሊሲ ያውጡ፣ የግል ሀብት የሚበለጽግበትና የግለሰብ ነጻነት በሕግ የተጠበቀ መሆኑ ላይ ልዩነት የላቸውም፡፡
በውይይቶቻቸው ስለ ድሕነት ቅነሳ በተደጋጋሚ ያነሳሉ፡፡ ድሕነትን ለመቀነስ በሚሄዱባቸው መንገዶቻቸው ላይ (ፖሊሲ) ግን ይለያያሉ፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ድሕነት አሁንም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አለ፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን ከመወዳደሪያ ነጥቦቻቸው ውስጥ አንዱ ድሆችን/አነስተኛ ገቢ ያላውን ዜጎች የሚጠቅም ፖሊሲን መንደፍ ነው፡፡ ፖለቲካና ድሕነት በልጽገዋል በሚባሉ አገሮች ውስጥም የፖለቲከኞች መጫወቻ ሩሮች/ኳሶች ናቸው፡፡ ታዲያ ፖለቲካ ድሕነት ላይ ሚና የለውም ማለት ይቻል ይሆን? በማለት መጠየቄ ለዚህ ነው፡፡
4.  የሕዝብ (የጠያቂዎች) ጥያቄዎችና የተጠያቂዎች ችግሮች
መንግሥት ይህንን አላደረገም፣ መንግሥት ያንን አልፈጸመም በማለት ለሁሉም ጉዳይ ባለማቋረጥ ጥያቄ የሚያቀርበውን የአገራችንን ዜጋ ስመለከትና የድሕነታችንን ስፋትና ጥልቀት ሳጤን ለምን? በማለት መጠየቄ አልቀረም፡፡
ድህነትን ለመቀነስ ብቸኛው ተዋናይ መንግሥት (ፖለቲካው) ብቻ እንደሆነ በመደምደም፣ ሕዝብ መንግሥትን (ፖለቲካውን) መጠየቁ በምክንያት ነው፡፡ መንግሥትም በበኩሉ፣ የርሱ ረዳቶች የሆኑትን (የውጭ መንግሥታትንና ባንኮቻቸውን) ለዕርዳታና ለብድር አንጋጦ መጠበቁ በምክንያት ነው፡፡
ለልማት የማውለው በቂ ሀብት (የውጪ ምንዛሪን ጨምሮ) የለኝም የሚለው የፖለቲከኞች ሰበብ/ሪፖርት ተደጋግሞ የሚደመጥ ጉዳይ ነው፡፡ በአገር ውስጥ እየተመረተ ወደ ውጪ ከሚላከው ምርት የሚገኘው የውጪ ምንዛሪ መጠን አገሪቱን በስፋት ለማልማት አይበቃም፤ ስለዚህም ለውጪ ገበያ የሚውል ምርት በብዛት መመረት አለበት ይላል መንግሥት፡፡ ለማምረትም ገንዘብ/ሀብት ያስፈልጋልና ችግሩ እውነትን የለውም አይባልም፡፡
ወደ ውጭ የምልከው ምርትና ወደ አገር ውስጥ የማስገባው የፍጆታና የካፒታል የልማት ዕቃዎች ሚዛን እኩል አይደሉም፡፡ የምልከው ምርት ጥቂት፣ የማስገባው የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጥ ደግሞ ከፍ ያለ ነው፤ ይህም የዕዳ ጫና ፈጥሮብኝ ለልማት ላውለው የምችለውን ገንዘብ ለውጭ ዕዳ መክፈያ እንዳውል እየተገደድኩኝ ነው ይላል፡፡ እውነትነት የለውም በማለት መሟገት ይከብዳል፡፡
የዚህን ዓይነት ሪፖርት መስማት በኢትዮጵያና በብዙ የአፍሪካና በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮችም ጭምር የተለመደ ነው፡፡ በኢትዮጵያና ቁጥራቸው ቀላል በማይባል የአፍሪካ አገራት የዚህ ዓይነት ሪፖርት ተደጋግሞ የሚደመጠው፣ ሁሉንም የልማት ግብዓቶችን (መሬትን፣ ፋይናንስን፣ ማዕድናትን፣ …) አንቀው በመያዝ የሕዝቡን ሃብት በፖለቲካ መነጽር እየተመለከቱ እንደፈለጋቸው የሚያዝዙበት የሦስተኛው ዓለም መንግሥታት የተበራከቱ በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ድህነትና ፖለቲካ ከተቆራኙበት ምክንያቶች አንዱ ለዚህ ይሆን? በማለት መጠየቅ ይቻላል፡፡
ሁሉም አገሮች ግን በየወቅቱ የሚያወጧቸውንና ተግባር ላይ የሚያውሏቸውን የፖሊሲዎቻቸውን ድክመቶች አይተቹም፡፡ የእርሻና የኢንዱስትሪ ምርት፣ የገንዘብ፣ የፋይናንስ፣ የውጪ ግንኙነት፣ … ፖሊሲዎችን በፍጥነት እየገመገሙ፣ በአገር ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተንተርሰው የተሻለ ለመቅረጽ አይጥሩም፡፡ በፖለቲካ መነጽር ተቃኝቶ አንድ ቦታ በተቸነከረ ፖሊሲ፤ ልማት፣ ዕድገትና የድሕነት ቅነሳን ለማምጣት ይከብዳል፡፡ ሁሉንም አንድ ላይ ጨፍልቆ በማየት ችግሮችን መፍታት አይቻልም፡፡
መልካም አስተዳደር የሌለው ፖለቲካና ድህነት ተወራራሽ ናቸው በማለት ማሰብ ከጀመርኩኝ ቆይቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያና በብዙ ታዳጊ አገሮች ውስጥ ፖለቲካው ድህነትን የሚፈጥርና የሚያባብስ መሆኑ ተደጋግሞ ታይቷል፡፡ በአንጻራዊነት፣ የታዳጊ አገሮች ፖለቲካ ሁከት ፈጣሪና አባባሽ እንጂ ያልተቋረጠ (sustainable) ልማት አምጪ በመሆን አይታወቅም፡፡ የችግሮች መፍቻ፣ ማርገቢያና ማቻቻያው አለመረጋጋት/ጦርነት እንዲሆን ፖለቲካው አይወስንም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ሲያቅት ተቃራኒ ርምጃዎችን ወስዶ ጊዜ በመግዛት፣ በፖለቲካ ሥልጣን ላይ መቆየት ቀላል የማይባሉ የታዳጊ አገሮች የሚከተሉት የአስተዳደር ዘይቤ በመሆን ተመዝግቧል፡፡
ከዚህ አንጻር፣ ፖለቲካና ድህነት የተቆራኙበትን የአሠራር ሂደቶች በቅርበት መመርመርና ለድህነት ምክንያት የሆኑና ሊሆኑም የሚችሉ ፖለቲካዊ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን አሳይቶ በመተንተን የመፍትሔ ሀሳብን መጠቆም ወሳኝ ይሆናል፡፡ በመፍትሄ ሀሳብ ዙሪያ በጋራ ተወያይቶ አቋም መያዝም ይገባል፡፡ ከፖሊቲካ የጸዳ የድህነት ቅነሳ ስትራጂዎች ላይ ሀሳብ አንድታዋጡ እጠይቃለሁ፡፡ ማንኛውንም ሀሳብ የምሰነዝረው ለውይይት መነሻ ሆኖ ሌሎች የተሻሉ አስተሳሰቦች ወደ ፊት እንዲመጡ ካለኝ ምኞች መሆኑን አስምራችሁ ያዙልኝ፡፡
5. የውይይት ሀሳቦች
ለውይይት መንደርደሪያ እንዲሆን በገቢ መጠን ላይ ከሚያተኩረው የድህነት ትንታኔ ላይ ልነሳ፡፡ በገቢ መጠን ላይ ያተኮረውን የድህነት መረጃ/መለኪያ/ትንታኔ ለመመልከት የምሞክረው የዩናይትድ ስቴትስን የሴንሰስ ቢሮን አካሄድ በማሳየት ነው፡፡ ወደፊት የሌሎችን ለማየት እጥራለሁ፡፡  
የዩናይትድ ስቴትስ የሴንሰስ ቢሮ የድህነት ደረጃን የሚወስነው ከታክስ በፊት ያለውን የገንዘብ ገቢ መጠን የድህነት ወለል ተደርጎ ከተመደበው የገንዘብ መጠን ጋር በማነጻጸር ነው፡፡
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አራት ሰዎች ላለው የቤተሰብ ቁጥር የድህነት ወለል ተደርጎ  የተመደበው የገንዘብ መጠን 24257 ዶላር ነው (ይህንን በኢትዮጵያ የገንዘብ ምንዛሪ ባታበዙት እመርጣለሁ)፡፡ ከዚህ አንጻር፣ አጠቃላይ ብሔራዊ የድሕነት ምጣኔው 13.5 ፐርሰንት የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ስሌት 43.1 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ድህነት ውስጥ እንደነበረ የሚጠቁም ነው፡፡
የሴንሰስ ቢሮው የድህነት ጥልቀትንም ይለካል፡፡ በድህነት ጥልቀት መለኪያው ምን ያህሉ ሕዝብ በድህነት መስመር ላይ፣ ከድሕነት መስመሩ በታችና ከመስመሩ በላይ እንዳለ ያሳያል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የአጠቃላዩን ድህነት መለካት ከጀመረበት ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጋር ሲነጻጻር በወቅቱ የድህነት ምጣኔ መቀነሱንም መረጃው ይገልጣል፡፡ ሴንሰሱ፣ ድህነትን ለመቀነስ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ሥራን በየወቅቱ መሥራት አንድ ጥቅም እንዳለው ያመለክታል፡፡ የድህነት ደረጃን በውል አውቆ ለተግባር መዘጋጀትን ያፋጥናል፡፡ ይህ አንድ ሃሳብ ነው፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ በድህነት ላይ ዘመቻ የጀመረችው ካዛሬ ስልሳ ዓመታት በፊት ነው፡፡ ዛሬም ድህነት ከ30-45 በመቶ በሚሆነው ሕዝቧ ላይ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ ለድሕነት አለመወገድ ከምክንያቶቹ አንዱ የሚሆነው በፓርቲዎቹ መካከልና በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ ስለ ድሕነት ያለው አቋም መለያየቱ ይመስለኛል፡፡ የሐብት ችግር አይደለም፡፡ ስለ ሁለቱ ግዙፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከላይ በአጭሩ ለማሳየት የሞከርኩት ያንን ነው፡፡ አንደኛው ቀስ በቀስ በሚወሰድ እርምጃ (trickling effect) ድሕነት ይቀንሳል ሲል፤ ሌላው ድሕነትን የሚቀንስ ራሱን የቻለ ፕሮግራም መኖር አለበት ይላል፡፡
ድህነት እንደየአገሩ ሁኔታ የሚለያይ ነው፡፡ ድህነት በጣም ውስብስብ ችግር ነው፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም ላይ በሃብት መጠን ቀዳሚ ሥፍራን ከሚይዙ አገሮች የመጀመሪያዋ የበለጸገች አገር መሆኗም እሙን ነው፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በልጽገዋል ከሚባሉ አገሮች ቀዳሚዋ አገር ናት፡፡ እንደ ሃብት ብዛት/ክምችት መጠን ቢሆን ኖሮ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ድህነትን ለማጥፋት ከስልሳ ዓመታት በላይ ፈጅቶ ዛሬም ከሠላሳ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ከድህነት ወለል በታች አይገኝም ነበር፡፡ የአገሪቱ ብልፅግና ድሕነትን ለማጥፋት ዋስትና አልሆነም፡፡ ለምን ብሎ መጠየቅ ያጓጓል፡፡ በዝቅተኛ ዋጋ ተቀጥሮ ለባለጸጋዎች መሥራት የሚችል ድሐ ሠራተኛ ያስፈልግ ይሆን? ከታዳጊ አገራት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚፈልሰው ሕዝብ የሚፈለገውስ ለዚህ ይሆን? በማለት ጠይቆ መብሰልሰል ይቻላል፡፡   
ድህነትን መቀነስ/ማጥፋት ከማንም አገር አቅምና ፍላጎት በላይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አንድ አገር ያላት የሃብት መጠን ብቻ ሳይሆን የምትከተለው የፖለቲካ ፍልስፍና፣ የልማት ፖሊሲ፣ የፖለቲካውና የሕዝቡ ቁርጠኝነት ወሳኝ ሥፍራ አላቸው በማለት መውሰድ ግን ይቻላል፡፡ እንደ ዩናይትት ስቴትስ ከበለጸጉ በኋላ ድህነትን ማጥፋት ከባድ እንደሚሆን መረዳት ቀላል ነው፡፡ ሊኖር የሚችለው ዌልፌር ሲስተም ሆኖ ያርፈዋል፡፡ ያም ቢሆን የሕዝብን ጥያቄ ማስታገሻ እርምጃ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ የድሕነት ቅነሳ ፖሊሲ መጀመር ያለበት ገና ከጠዋቱ ልማትን ከዕድገትና ከግል ሀብት ማከማቸት ጋር አያይዞ (የብልጽግናን መንገድ ሲያስቡ) ለድሕነት ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ይመስለኛል፡፡ የሚቀረጹ የልማት ፖሊሲዎች ድሕነትን መቀነስና ማጥፋት ላይ ያተኮሩ ሆነው ለተግባራዊነታቸው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ይህም ሌላ ሀሳብ ነው፡፡
ድህነትን ለመቀነስ/ለማጥፋት የኢትዮጵያ ፖለቲካና ዜጎቿ ቁርጠኝነታቸው እስከ ምን ድረስ ነው? የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ግን አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ጥያቄ መነሳት፣ የድህነት ቅነሳ ሰትራተጂዎችን ለመተለምና ወደ ተግባር ለመሰማራት ይጠቅማል፡፡ ይህኛው ደግሞ ሌላ የመንደርደሪያ መስመር ነው፡፡
ድህነት ዘርፈ ብዙ /multidimentional/ ነው፡፡ መገለጫዎቹም እንዲሁ በርካታ ናቸው፡፡ በገቢ መጠን ማነስ፣ በአገልግሎት አናሳነት (ምግብ፣ የውኃ እጦት/እጥረት፣ የጤና አገልግሎት አናሳነት፣ የትምህርት ኋላ ቀርነት)፣ በአስተሳሰብ ደካማነት (attitude)፣ … ሊገለጥ ይችላል፡፡  
አንድ አገር በቂ ሃብት ኖሮት ለእያንዳንዱ ዜጋ ለኑሮ የሚበቃውን የገቢ ድጎማ ሊያቀርብ ቢችል እንኳን ድሕነት በአንጻራዊነት ሊኖር ይችላል (ለዚህ ዩናይትድ ስቴትስን በምሳሌነት መውሰድ የሚቻል ነው)፡፡ ጥያቄው፣ የሚኖረው ድሕነት ምን ዓይነት ድሕነት ነው? የሚለው ነው፡፡ ጥያቄው፣ መንግሥትና የአገሪቱ ዜጎች ድህነትን ለማጥፋት እልህ አላቸው ወይ? በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ፣ የግል ሀብትን አከማችቶ ራስንና አገርን ማበልጸግ እንጂ ድሕነትን በማጥፋት ረገድ የጎላ እልህ አልተፈጠረም፡፡ ድሕነትን ለማጥፋት እልህ የሌለው ሕዝብና መንግሥት በድሕነት ውስጥ ለመቆየት ያለው ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ድሕነቱ አንጻራዊ (relative) ወይንም ፍጹማዊ (absolute) ሊሆን ይችላል:: ይህም ሌላ ሃሳብ ነው፡፡
ድህነትን ለመቀነስ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ የተወሰዱ እርምጃዎች ምን ምን ናቸው? እርምጃዎቹ አሳታፊና ውጤታማ ነበሩ? አሁን አገሪቱ በምን ያህል የድህነት ደረጃ ላይ ትገኛለች? አበይት ችግሮቹ የትኞቹ ናቸው? በችግሮቹ ላይ እነማን፣ እንዴት ያሉ እርምጃዎችን ቢወስዱ ይጠቅማል? ብሎ መጠየቅና ድሕነትን ለመቀነስ (ቢቻል ለማጥፋት) ከአሁኑ ሳያሰልሱ መሥራትን መለማመድ የግድ ይሆናል፡፡ በእውቀትና በቅንነት የታገዘ ከድሕነት የመላቀቅ እልህን መሰነቅ የግድ ነው፡፡
ከጠየቅኳቸው ጥያቄዎች እንጀምርና፣ በርካታ ጉዳዮችን በደረጃ እያነሳን በመመርመር የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ለመድረስ የምንጥር ይሆናል፡፡ ውይይቱም ሆነ ከሃሳብ አንድነት ላይ መድረሱ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል አትዘንጉ፡፡ መደማመጥን፣ ለሌላው ሰው ሃሳብ አክብሮት መስጠትንና (ተሳስቶ ቢገኝ እንኳን) በመፍትሄ ሃሳብ ላይ ብቻ በማትኮር አስተያየት መቀባበልን አንዘንጋ፡፡ ጨዋነት የኢትዮጵያውያን ታላቅ ዕሴት መሆኑንም እናስታውስ፡፡ የቲዎሪና የፍልስፍና ጨዋታዎችን ለለመደበት ለፖለቲካው ተወት አድርጉት፡፡ ፖለቲካው ለዘመናት ወደፊት መራመድ ያቃተው፣ በተውሶ ቲዎሪና የፍልስፍና ሰንሰለት (chain) ሲፋተግ ወዝ የሚሰጠውን ዘይቱን/ቅባት ጨርሶ በመዛጉ መሆኑን ካለፉ የፖለቲካ ታሪኮቻችን የተማርን ይመስለኛል፡፡ ብንችል፣ ፖለቲካን ወደ ጎን ትተን በኤኮኖሚ ልማትና ድሕነት ቅነሳ ስትራተጂዎች ላይ እናትኩር፡፡ ያ ወደ ምናልመው ሁለንተናዊ ልማት፣ ዕድገት፣ ብልጽግና’ና ድሕነት ቅነሳ ሊያቃርበን የሚችል ይመስለኛል፡፡
በኢትዮጵያ ተካሂዶ የነበረውን የድህነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነድን (Poverty Reduction Strategy Paper (PRSP)) አስመልክቶ ስለተከናወኑ ጉዳዮች፣ በወቅቱ በነበረው መንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ስለተወሰዱ/ስለተሰጡ ተግባራዊ ምላሾችና ስለነበሩባቸው ችግሮች ዝርዝር በሚቀጥለው ጽሁፌ ለማቅረብ ጥረት የማደርግ ይሆናል፡፡ ሰላም፡፡
[1] (ማስታወሻ፡- እኔ እልባት የምለው፣ መጽሐፍን ስታነቡ ያቆማችሁበት ሥፍራ እንዳይዘነጋችሁ በገጾች መካከል የምታኖሩትን ምልክት ነው፡፡ ያ ምልክት የክር፣ የሳር፣ የወረቀት፣ የቅጠል ሊሆን ይችላል፡፡ ማንበብ ስትቀጥሉ ከእልባቱ ትጀምራላችሁ ለማለት ነው፡፡)
ከአዘጋጁ፡-
ጸሃፊው ስንታየሁ ገብረጊዮርጊስ ወልደሐዋርያት፤ BSc በእርሻ ኤኮኖሚክስ፣ MSc  በኤኮኖሚ ፖሊሲና ፕላኒንግ ያገኙ ሲሆን፤የዶክትሬት ድግሪያቸውን በባሕሪያዊ ኤኮኖሚክስ (Behavioral Economics) ማጥናት ጀምረው አላጠናቀቁም፡፡ በተማሩት ዘርፍም፣ በሲአርዲኤ በድኽነት ቅነሳ ስትራቴጂ ኦፊሰርነት፣ በኢትዮጵያ ግራጁዌት ስኩል ኦፍ ቴዎሎጂ በዲቨሎፕመንት ኦፊሰርነት፣ በዓለም ባንክ ፕሮጄክት የዘር ሥርዓት ልማት ፕሮጄክት (SSDP)የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ስፔሻሊስት ሆነው አገልግለዋል።  ጸሃፊው በአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው ያልታተሙ በርካታ መጻሕፍት ያላቸው ሲሆን፤ ”በቀልና ፍትህ“ የተሰኘ የትርጉም ሥራቸው በያዝነው ሳምንት በገበያ ላይ ውሏል፡፡  ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 282 times