Saturday, 22 June 2024 00:00

ሕዝቤ ሆይ፤ እባክህ ተመከር!

Written by  የአብሥራ አድነው
Rate this item
(1 Vote)

ውሃ ስትጠየቅ ወተት፤ ኩርማን ስትለመን ድፎ የምትሰጠው ሕዝብ ሆይ፤ እንደምን ከርመሃል? ልግስናህ የተለፈፈልህ እጀ ሰፊ ሆይ እንደምን ይዞሃል? እስቲ ዛሬ ደግሞ እንደ ቤተልሔም ማለትም- እንደ እንጀራ ቤት ስለምንቆጥረው ኢ-መንግስታዊ የተራድኦ ድርጅቶች እናውጋ!
የኖርኩበትና የማውቀው ሕዝብ አንተ ስለኾንክ ብበረታብኽ አይክፋኽ. . . ተረቱስ ራሱ ሰው ባለው ነው አይደል የሚለው? የራስን ነገር አገላብጦ ማየት ደንብ ነው፥ አይዞህ ለፍቅር ነው አልጎዳህም! እኔ የምልህ ልጆችህ የሕግ ባለሙያና መምሕር ሲኾኑልህ ዝም ብለህ፣ የተራድኦ ጥበቃ ሲኾኑ “እልልልልልል!” የምትለው ምን ነክቶኽ ነው? የጥበቃ ስራን አክብረህ ነው እንዳልል፣ በደህናው ቀን የመንግስት መስሪያ ቤት ጥበቃን ጥንብ ርኩስ ስታወጣና የአብራክህን ክፋዮች፤ “ካልተማራችሁ እንደነሱ ትሆናላችሁ!” ብለኽ ስታስፈራራ ነው የማውቅኽ። እንደው በጤናህ ነው ልጅህ ኢ-መንግስታዊ ድርጅት እግሩን ሲያስገባ፣ በተለይ የሀገር ውጭ ሲኾን አኮቴትህ ኦዞንን ሸንቁሮ ጸባኦት ካልከተምኹ የሚለው?
የጉድ ሀገር ገንፎ እያደር ይፋጃል አሉ! እንደ ደንቡማ የተራድኦ ድርጅት ለመስራት ልቡ ያለው ሰው፤ ርህራሄ ቋንቋው፥ ሀዘኔታ መታወቂያው፤ መስጠት የኑሮ ዘይቤው፤ ያገኘውን መበተን መክሊቱ፤ ጥሪቱ በሰማይ፤ መዝገቡ አምላኩ ጋር፤ መኖሪያውና ልቡ በድንኳን ነበር . . . .ነበር። ፈሊጡ እስከ አሁን ያልገባኝ እኔ ብቻ እኾን? ወይስ የምናውቃቸው የተራድኦ ሰራተኞች  አብዛኞቹ የዚህ ተቃራኒ ናቸው? እንዳልኩኽ ግድ የለም ዛሬ ልበርታብኽ. . . . ቢያመንም እውነቱን እየተጋገርን እንፈወስ፤ ምን ኾነህ ነው ማብላትና መብላት የተምታታብኽ? እንዴት ኾነኽ ብታድግ ነው ዳቦ የሌለው ውጫቅላ ልታገለግል እየሄድኽ የዳቦ ቅርጫት የሚታይኽ? ችጋር ሩቅህ ነው እንዳልል እየፎከተች የኖረች ሀገር ያበቀለችህ ነህ፤ ቢርቅህ እንኳን ከአንድ አጥር ወይም ስልኩን ከማታነሳለት ገጠር ካለው አጎትህ በላይ አይርቅህም።
እርግጥ ስሙን ውስጥ ከምትሰራው ከአንተ በላይ አላውቀውም፤ ግን ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅትም ትባሉ አይደል? ነው ወይስ ትርፉ በነፍስ ወከፍ ከኾነ ነውር የለውም? ዳስ ውስጥ ከትሞ ለአንተ ደም-ወዝ ግብዓት ከመኾኑ በፊት የተከበረ አባወራ የነበረ ስንት አለ መሰለህ፤ ጉንጩን ሲነኩት የሚፈርጥ ይመስል የነበረውን ልጅ ጥጋበኛ መሪዎች በጦርነት አሳቅቀው አጥንቱ የሚቆጠር ጣረ-ሞት አስመስለውታል . . . ከዚህ ሁሉ ሸሽቶ የተራበውን አንጀቱን የሚያስታግስበትን ፕላምፕሌት ነጥቀህ የምትሸጠው አውሬ እጅ ላይ ገብቷል። ለመኾኑ ከአንተና በጦርነት አፈናቅሎ ከቤቱ ካስሰደደው ስርዓት ማነኛችሁ ናችሁ ክፉ? ስደተኛ መጠለያ ያለች ረዳት አልባ እናት፣ ከዚህ በኋላ ወዬት ትሰደድ? አንዳንዱን በሪፖርት እንጂ ቦታው ላይ ሔደህ አይተኽው ስለማታውቅ አልፈርድብኽም።
አንተ ወንድም ወንድሙን ገደለ ስትባል ለእግዚኦታህ ምድር የምትጠብህ ሆይ፦ለርዳታ የመጣ ወተት በጅጅጋ አስጭነህ መርካቶ ስታስገባ ወንድምህን ቂቤ እየቀባኽው ኖሯል እንዴ? ለውሎ አበል ትምህርት ቤት የሚከፍት ገንዘብ ስታወራርድ ካራህ በወንድምህ አንገት ላይ መዋሉ አይደለምን? ከሚለግስ መስረቅ አግባብ ባይኾንም ተርፎት ይባል፤ ከሚቀበል መስረቅ ግን ምን የሚሉት ጭካኔ ነው በል?    
ታውቃለህ USAID የሚል ጽሑፍ ያለበት የወተት ቆርቆሮና የስንዴ ከረጢት አያትህ ቤት ሳይ ምን እንደሚሰማኝ? እኔ ልሙት ከቤተ-መቅደስ እንደተሰረቀ ሙዳይ፣ ያለ ስፍራው እንደ ተቀመጠ ንዋየ ቅዱሳት ዝግንን የሚያደርግ ስሜት ይነዝረኛል። ልክ የባቢሎኑ ንጉስ ናቡከደነጾር ሕዝበ እስራኤል ማርኮ የቤተ-መቅደሱን ዕቃ ዘርፎ ቤተ-ጣኦት ውስጥ ሲያኖር አይሁድ እንደተሰማቸው ጠገን አልባ ስብራት የኔም ልብ ተንሸራቶ እግሬ ስር ሊገባ ያምረዋል። ጻሕል፥ ጽናጽል፥ መሶበ ወርቅ አልያም ሌሎች የመቅደስ ዕቃዎች ግልጋሎታቸው ልዑል አምላክን ለማምለክ አይደለምን? ቢጫ ጀሪካን፥ ዩኤስኤድ የሚል ጣሳ፥ ፕላምፕሌትና ተጨማሪ የዕርዳታ ግብዓቶች ስደተኛ መሃል እግዜሩ አብሮ ከትሞ ባለበት መገልገያ ንዋያተ ቅዱሳቱ ለመኾን ያንሳሉን? ለድሃው ቸርነት ማድረግ፣ ለምጻተኛው ከለላ መስጠት፣ አዱኛ ፊቷን ላዞረችበት የሚደገፍበት ትክሻ መስጠት እውነተኛ አምልኮ አልነበረምን?
ያዝማ! አንድ በቅርቡ የኾነ ታሪክ ላጫውትህ፡፡ ልክ እንዳንተው በተራድኦ ድርጅት ውስጥ ትሰራ የነበረች ላልዛውሚ ፍራንኮም ስለምትባል ሴት። ወርልድ ሴንትራል ኪችን በሚባል በተለያየ ሰው ሰራሽ ወይም ተፈጥሮአዊ ቀውሶች ምክኒያት የምግብ ዕጥረት የገጠማቸው ሰዎች መጋቢ ድርጅት ውስጥ ከቀደምት ሰራተኞች መካከል የምትመደብ አውስትራሊያዊት ነበረች። ጓደኞቿ ዞሚ ብለው ይጠሯታል፤ በጓቲማላ፥ ባንግላዲሽ፥ ሞሮኮ፥ ሄይቲ፥ ፓኪስታን፥ ሮማኒያ፥ ቱርክ፥ ዪክሬን፥ ግብጽ፥ ጆርዳንና ሌሎች መሰል ሀገሮች በጣም ከፍተኛ ችግር በነበረባቸው ጊዜያት የስደተኛ ጣቢያዎች እንዲሁም ሕዝብ የሰፈረባቸው መንደሮች ውስጥ በመጓጓዝ ምግብ ማብሰል ከዚያም መመገብን ስትሰራ ቆይታለች። በጋዛ ለሚገኙ ሰዎች እርዳታ ለመስጠት ወደ ስፍራው ለመጓዝ ማሰቧን ለጓደኛዋ ቴሬሳ በስልክ ታወራታለች፤ እሷም ቦታው አደገኛ ሊኾን እንደሚችል ትነግራታለች፤ ራሷ ዞሚም ነገሩን አልካደችም። ጓደኛዋ ይህንን መለስ ብላ ስትተርክ፤ “አደገኛነቱን ብንተማመንም እንደማትቀር ግን ሁለታችንም እናውቅ ነበር” ትላለች። ዞሚ በስፍራው ደርሳ የተለመደውን ስራዋን መከወን ቀጠለች፤ ነገር ግን በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 1 ቀን 2024 ዓ.ም ከስራ ባልደረቦቿ ጋር በመኪና እየተጓዙ፣ ባለቤትነቱ የእስራኤል በኾነ የድሮን ጥቃት እሷና ሰባት የተራድኦ ሰራተኛ የነበሩ ጓደኞቿ ሕይወታቸውን አጡ። ከሕልፈቷ በኋላ የጓደኛዋ ቴሬሳ ቃላት እንዲህ ይነበባሉ፦
I am sure people are wondering, “why were they even in Gaza?” I will tell you why- because people needed to be helped. That’s always why we are wherever we are-to help people.
ወገኔ ምን እያልኩኽ መሰለህ፤ ሙያ መለኪያው “ያበላል?” ብሎ ድፍን ጥያቄ ብቻ አይደለም፤ የሕይወትን ትርጉም ታኝኮ ሆድ ከሚገባ ነገር ትንሽ ከፍ አድርገን ብናስበው አይጎዳም። የዞሚ ዓይነቶቹ በተራድኦ ቤት ንብረት አላደረጁም፥ ዕንብርታቸው እስከሚፈታ እህል አላሻመዱም፥ ቅንጡ መኪና አላሽከረከሩም፤ በአንጻሩ እንደ መልካም ዕጣን በስደተኛ ነፍሶች መካከል ጊዜያቸውን አጤሱ፤ ምቾታቸውን ለጎስቋሎች ሲሉ እንደ ቁርባን አፈሰሱት። የተራድኦ ድርጅት ብትችል ያለኽን ኹሉ የምታፈስስበትና የምትበትንበት እንጂ የምትሰበስብበት ለመኾን የመጨረሻው ቦታ ነው።
ሕዝቤ! እባክህ ተው! ለሀገሪቱ የሚኾን በቂ እርግማን አለን፤ የአንተ ተጨማሪ ግፍ አያስፈልገንም፤ ተው ተመከር! ጠኔ ካጠወለገው አይነጠቅም፤ የእግዜሩን ተወው ሰይጣን ራሱ በዚህ ነገር ጥይፋት በቀላቀለው ድንጋጤ ፊቱ አሻቦ ይመስላል። ተው አትዳፈር! ምን አልባት ሰማይ ቤት የሚታወቀው ብቸኛ ባንዲራ የስደተኛ መጠለያዎች ዳስ ይኾናል፤ ባይኾን እንኳ የእነርሱ በጊዜያዊነት በድንኳን መኖር የአንተን መዋቲነት ያስታውስህ። እባክህ የመሰብሰብን ብቻ ሳይኾን የመበተንንም ጥበብ ተማር።
  ወላድ ሆይ፤ የማይታይ ሐብት ለሚያከማቹ ከራሳቸው ይልቅ ለሌላው እየተጉ ላሉ አመድ አፋሽ ልጆችህ፣ አንዴ ዕልል ብትል ክብርህ አይዋረድም።  Read 256 times