Saturday, 22 June 2024 00:00

ቦብ - አፄ ኃይለስላሴ - እና ራስ-ተፈሪያውያን

Written by  ሣሙኤል ልጅዓለም ሃሰን
Rate this item
(0 votes)

ቦብ ማርሌይና ጃማይካውያኑ በስማቸው መጨረሻ ላይ ያሉትን የእንግሊዝኛ ፊደሎች “ሪ” ማለት ሲገባቸው “ራይ” ብለው በማንበብ ንጉሥ ኃይለሥላሴ፣ ከንግሥና በፊት ይጠሩበት  የነበረውን “ራስ ተፈሪ መኮንን” የሚለውን ሥማቸውን፣ “ራስ ተፈ ራይ” እያሉ ነው የሚጠሯቸው፡፡ በራስ ተፈሪያውያን እምነት ተከታዮች ዘንድ እንደ ፈጣሪ ወይም አምላክ ወደ ምድር እንደላከው ነቢይ የሚቆጠሩት የኛው አፄ ኃይለስላሴ፤ ከጃማይካውያን ጋር ታላቅ ታሪካዊ ቁርኝት አላቸው፡፡ በነገራችን ላይ፣ እንግሊዛውያንም ጋንዲን እንዲሁ ነው የሚጠሩት… “ሚስተር ጋንዳይ” በማለት፡፡
እ.ኤ.አ በፌብሩዋሪ ወር 1945 ዓ.ም፣ ሴንት ኦን ፓሪሽ በተባለች ጃማይካ ውስጥ በምትገኝ መንደር የተወለደውና ሜይ 11 ቀን 1981 ዓ.ም ላይ ሚያሚ ፍሎሪዳ ውስጥ ያረፈው ድምፃዊ፣ የዘፈን ግጥም ደራሲ፣ ሃይማኖተኛና የሰብአዊ መብት ተከራካሪው ቦብ ማርሌይ፤ ከ20 ሚሊዮን በላይ አልበሞችን መሸጥ የቻለ፣ የሬጌ ሙዚቃ ንጉሥና የሦስተኛው ዓለም አምባሳደር ነበር፡፡
ማርሌይና ጓደኞቹ በ1963 ዓ.ም The wailing wailers የተባለውን የሙዚቃ ቡድን የመሠረቱ ሲሆን፣ ቡድኑ በ1972 ዓ.ም ግድም  ከፍተኛ ታዋቂነትና ተወዳጅነትን አትርፎ ነበር፡፡ የሬጌ ሙዚቃ በዓለም ላይ እንዲናኝና እንዲወደድ ያደረገው ማርሌይ፤ ከወጣትና ጥቁር ጃማይካዊት እናትና ማንነቱ በግልፅ ካልታወቀ ሽማግሌ ፈረንጅ አባት የተወለደ ሲሆን፣ የልጅነት ጊዜውን  ያሣለፈው Nine Miles በተባለች የገጠር ከተማ ውስጥ ነው፡፡


ማርሌይ ጊታር መጫወት እንዲለምድ የገፋፋው አብሮት የሚማር፣ በቅፅል ስሙ Bunny ተብሎ የሚጠራ የልጅነት ጓደኛው  ነበረ፡፡ በወጣቶቹ ትውውቅና ቅርርብ ምክንያት የማርሌይ እናትና የቡኒ አባት በኪንግሥተን ከተማ  በአንድ ጎጆ ውስጥ በፍቅር ኖረዋል… ከእነ ልጆቻቸው፡፡
ቦብ ማርሌይ ኪንግሥተን ውስጥ መኖር የጀመረው በ1950ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ሲሆን፤ አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው Trench Town በተባለችውና በዘፈኑ ውስጥ በሚያነሳት የሞላጫ ድሆች መኖሪያ መንደር ውስጥ ነበር፡፡ ማርሌይ፣ በድህነት ያደገባት ይህች መንደር በወቅቱ በበርካታ ለሙዚቃ ፍቅር ባደሩ ግለሰቦች፣ ዘፋኞችና “ከተፋ ቤቶች” የተሞላች ነበረች፡፡ የማርሌይም የወደፊት ሕይወት ከሙዚቃ ጋር እንዲቆራኝ ካደረጉት ነገሮች አንዱ፣ የዚህ አካባቢ ተጽዕኖ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
ማርሌይ በድህነት ያደገባት Trench Town፣ “Motown of Jamaica” የሚል ተጨማሪ መጠሪያ እንዲኖራት ያደረገውም የእነዚህ ሙዚቀኞችና ሙዚቃ ቤቶች መናኸሪያ መሆኗ ነበር፡፡  ከዚህም በላይ ማርሌይ ወደ ሙዚቃ እንዲገባ ያደረጉት ዘፈኖቻቸው በአሜሪካን አገር Jukeboxes አማካኝነት ይተላለፉ የነበሩት ሬይ ቻርልስ፣ ኤልቪስ ፕሬስሊ፣ ፋትስ ዶሚኖ እና ዘ ድሪፍተርስ የተሰኙት የወቅቱ ዝነኛ ሙዚቀኞች ነበሩ፡፡
በ1962 ዓ.ም ላይ የተወሰኑ የማርሌይ ነጠላ ዜማዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ ጆሮ እንዲደርሡ ያደረገው የአገር ውስጥ ሙዚቃ አታሚና የማርሌይ ድምፅ ከፍተኛ አድናቂ የነበረው Leslie Kong የተባለ ግለሰብ ነው፡፡ ለህዝብ ጆሮ በአግባቡ የደረሰው የቦብ ማርሌይ የመጀመሪያ ነጠላ ዜማም “Judge Not” የሚል ርዕስ ነበረው፡፡
ኤክሶደስ የተባለውና ትንሽ ቆየት ብሎ የወጣው የማርሌይ ዘፈን፣ አይሁዶቹን ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያንንም ለባርነት ከተሰደዱበት ጃማይካን የመሰሉ አገራት ወደ በቀሉበት ምድር የመመለስን ምኞት ያመላክታል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ኤክሶደስ የተባለው ዘፈን በእንግሊዝ አገር የምርጥ ዘፈኖች ዝርዝር ውስጥ ለብዙ ጊዜ የአንደኛነት ደረጃ ይዞ  ቆይቷል፡፡ ከኤክሶደስ ሌላ “Waiting in Vain” እና “Jamming” የተባሉ ዘፈኖቹም እንዲሁም በሙዚቃ ቻርቱ ላይ ከዓመት በላይ የቆዩ ናቸው፡፡
ቦብ በ1981 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ የሞቱ ምክንያት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው እንደሚወራው ከመጠን ባለፈ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት አይደለም፡፡ ማርሌይ የሞተው በ1977 ዓ.ም በአውራ ጣቱ ላይ የወጣበትን ቁስል ለመታከምም ሆነ ሃኪም የሠጠውን የተመረዘ ጣት ቆረጣ ጥያቄ “ሃይማኖቴ አይፈቅድልኝም” በሚል አሻፈረኝ በማለቱና፣ በሣቢያውም በጣቱ ላይ የነበረው ቀስል ወደ ካንሠርነት ተቀይሮ መላ አካላቱን በመመረዙ ነው፡፡
ማርሌይ ቅድስት ምድር ብሎ ወደሚጠራትና የራስ-ተፈሪያን ዕምነት መፍለቂያ አገር ናት ብሎ ወደሚያምናት ኢትዮጵያ በ1978 ዓ.ም መጥቶ ነበር፡፡ “Could You BeLoved” እና “Redemption Song” የሚል ርዕስ ያላቸውንም ዘፈኖቹን  ያወጣው በ1980 ዓ.ም ኢትዮጵያን ጎብኝቶና ክርስትና ተነስቶ ከተመለሠ በኋላ ነው፡፡ ቦብና የሙዚቃ ቡድኑ The Wailers እነዚህን ሙዚቃዎች በአውሮፓ ተዟዙረው አቀንቅነዋል፡፡
ቦብ ማርሌይ-ራስ ተፈሪ እና ራስ ተፈሪያውያን
ራስ ተፈሪ መኮንን (አባባ ጃንሆይ) በራስ ተፈሪያውያን እንቅስቃሴ ውስጥ በጣም ትልቁን ቦታ እንዲይዙ ወይም እንደ አምላክ (መሢህ) እንዲታዩ ካበቃቸው ነገር ውስጥ አንዱ፣ ከመፅሐፍ ቅዱሶቹ ንጉስ ሰለሞንና ንግስት ሳባ ጋር ቀጥተኛ የሆነ የዘር ግንድ ወይም የደም ትስስር አላቸው ተብሎ በመታመኑና፣ ይህንንም ራሳቸው “ሞ አንበሣ ዘ እምነገደ ይሁዳ” በሚል በማረጋገጣቸው ነው፡፡
ራስ ተፈሪ - ሐሙስ ኤፕሪል 21 ቀን 1966 ዓ.ም ጃማይካን  (ከቅኝ ግዛትነት በተላቀቀች ማግስት) በጎበኟት ወቅት፣ አምላክ ብለው የሚያስቧቸውን ንጉስ በአካል ለማየት የጓጉ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ጃማይካውያንና ሌሎች የካሪቢያ ደሴቶች ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው በዕልልታና በሆታ፣ ከበሮ እየደለቁ፣ ችቦና ጧፍ ለኩሰው ጥሩንባና መለከት እየነፉ ነበር የተቀበሏቸው፡፡
አፕሪል 21 ቀን 1966 ዓ.ም ከቀኑ 7፡30 ላይ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ኪንግሥተን ከተማ ሲያርፍ፣ ቀኑ ያለወትሮው፣ ከዛ በፊት ባልነበረ ሁኔታ በሃይለኛ ዝናብና ወጀበኛ ነፋስ የታጀበ ነበር፡፡ ንጉሱ ከአውሮፕላን እንደወረዱ፣ ከዚያ ቀደም ለማንም መሪ ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ፣ በደስታ ብዛት አቅላቸውን የሳቱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሆነው፣ ጆሮ የሚያደነቁር የደስታ ጩኸት እያሰሙ፣ ከጥበቃ ሰራተኞች ቁጥጥር ውጭ በሆነ የህዝብ ጎርፍ አውሮፕላን ማረፊያውንና ንጉሱ ይራመዱበት ዘንድ የተዘረጋውን ቀይ ምንጣፍ አጥለቀለቁት - ንጉሡ ወደ አውሮፕላኑ ውስጥ ተመልሰው እስኪገቡ ድረስ፡፡ ንጉሱ ከአውሮፕላን ወርደው ወደተዘጋጀላቸው ሊሙዚን መኪና የሄዱት ህዝቡ እንዲረጋጋና መንገድ እንዲከፍትላቸው በአንድ ታዋቂ የራስታ ሰው ከተለመነ በኋላ ነበር፡፡
ራስ ተፈሪ፣ ቆየት ብሎ በጃማይካውያኑ ዘንድ “ተፈጥሮ ያደለችውንና እግዚአብሄር የፈጠራትን ንፁህ ምድር በእግራቸው መርገጥ ስለፈለጉ ነው” በሚል እና በአንዳንዶችም ዘንድ አምላካዊ ተግባር ተደርጎ በተቆጠረ ሁኔታ፣ አውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ የተዘረጋላቸውን ቀይ ምንጣፍ አልረግጥም ብለው በልሙጡ አስፋልት ላይ ነበር የተጓዙት፡፡
ራስ ተፈሪ፣ በራስ ተፈሪያውያን ዘንድ እንደ አምላክ (መሢህ) እንዲታዩ ካደረጓቸው ክስተቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ፡-
ከመፅሐፍ ቅዱሱ ንጉስ ሰለሞን ጋር የደም ትስስር እንዳላቸው  በመታመኑ፤
በርካታ አድናቂና ተከታይ ያላትና አሁንም ድረስ በህይወት ያለችው ተፅእኖ ፈጣሪዋ የቦብ ማርሌይ ሚስት (ሪታ ማርሌይ)፣ “ኃይለሥላሴ ጃማይካን በጎበኙበት ወቅት መኪና ውስጥ ሆነው እጃቸውን በሚያውለበልቡበት ጊዜ ፈረንጆቹ STIGMATA የሚሉትንና “ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን በመስቀል ላይ በተቸነከረ ጊዜ በምስማር የተመታበትን አይነት ቀዳዳ (ሽንቁር) በመዳፋቸው መሃል ላይ አይቻለሁ” በማለት ወዲያውኑ ዕምነቷን ወደ ራስ ተፈሪያን ዕምነት መቀየሯን ለህዝብ በመግለፅ፣ አምላክነታቸውን በመመስከሯ - ይህንንም ምስክርነቷን No Woman No Cry በተባለው መፅሐፏና ባደረገቻቸው የተለያዩ ቃለ ምልልሶች ላይ ሁሉ ግጥም አድርጋ በማረጋገጧ፤
የትንሿ (ድንክዬ) ውሻቸው ድምፅ አምላካዊ ስጦታ ወይም ቡራኬ ስላለው፣ ከአንበሳ ድምፅ የበለጠ እንደሚያስተጋባ በጉብኝታቸው ወቅት ባካባቢው ነበርን ያሉ ሰዎች በመመስከራቸው፣
የኃይለስላሴ የኑሮ ዘይቤ - ከአለባበስ ጀምሮ ከጃማይካው የነፃነት መሪ ማርከስ ጋርቬይ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ በመገኘቱ፤
የጫናቸው አውሮፕላን ኪንግሥተን ሲያርፍ፣ ቀኑ ያለወትሮው በሃይለኛ ዝናብና ወጀበኛ ነፋስ በመታጀቡ፤
የክብር ቀይ ምንጣፍ ትተው እግዚአብሄር በፈጠራት ንፁህ ምድር ላይ በእግራቸው በመራመዳቸው፤
በህዝቡ ዘንድ እንደ መሢህ መታየታቸውን እያወቁ፣ እሳቸው ግን “ኧረ እኔ መሢህ አይደለሁም” ብለው አንድም ቀን እንኳን ባለመናገራቸውና፣ ከዚያ ይልቅ የራስ ተፈሪያንን ዕምነት ለሚያራምዱ መሪዎች የኢትዮጵያ ማህተም ያለበት የወርቅ ሜዳልያ በመሸለማቸው፤
ከጃማይካ ጉብኝታቸው በኋላ በወቅቱ የራስ ተፈሪያውያን መሪና የቦብ ማርሌይ መንፈሳዊ መምህር (Guru) የነበረው ፕላኖ የተባለ ግለሰብ፣ የራሱንና የራስ ተፈሪ መኮንንን ፎቶ አንድ ላይ በማድረግ በትልቁ አሰርቶ በጃማይካ ምድር በማሰራጨቱ ናቸው፡፡
ሌሎች እውነታዎች
ኃይለስላሤ ጃማይካ የገቡበት ዕለት፣ አፕሪል 21፣ በራስ ተፈሪያን አማኞች ዘንድ በየዓመቱ ይከበራል፡፡
ኃይለስላሴ ለራስ ተፈሪያውያንና ለሌሎችም አፍሪካዊ ስደተኞች መጠለያ ይሆን ዘንድ በሻሸመኔ ከተማ የሚገኘውን የግል መሬታቸውን በመኖሪያነት ሰጥተዋል - ለዚህም ነው ብዙ ጃማይካውያን ሻሸመኔ ውስጥ የሚኖሩት፡፡
በየሄደበት የሚወልደው ማርሌይ፤ ከተለያዩ ዜጎች የተወለዱ ብዙ ልጆች እንዳሉት ይነገራል- እንዴት እንዳፈጠነው ባይታወቅም፣ ኢትዮጵያ መጥቶ በነበረ ጊዜ የተፀነሰ አንድ ቁርጥ እሱን የሆነ ኢትዮጵያዊ ልጅም አለው … አንድ ሰሞን ኢቲቪ ላይ በተደጋጋሚ ቀርቧል፡፡
ቦብ ከህጋዊ ሚስቱ የወለዳቸው ስድስት  ልጆችም አሉት፡፡
ከአዘጋጁ፡-
ፀሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 552 times