Saturday, 22 June 2024 00:00

“ከተስፋ ስካር ሥር - ቀይ አበባ”

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(3 votes)

 -1 -
ከሞት ጡቶች ሥር የንቃትን  ወተት ልጠባ እንደተዘጋጀ (ጓጓቶ አፉን እንደከፈተ) ህፃን ሆንኩ። ከህይወት ይልቅ ሞት መቃብር ውስጥ ነቃሁ። የመቃብሩ ድርብርብ እውነት  የዓለምን ደማቅ ቀለም አደበዘዘብኝ። የህይወትን ትርታ አደከመብኝ። የታይታዉን ዓለም ባንዲራ በሞት እጆች አወረድኩ።  በመጀመሪያ ህይወቴ ሞት ነበር። በእርግጥ አሁን ሞቱ ህይወት ሆኗል።
መቃብሬ ላይ ወደ ‘ሚያለቅሱ ሰዎች ገባሁ። ወደ ልባቸው ገባሁ። ነፍሳቸውን መረመርኩ።  ያለቅሳሉ ሃዘን ግን ልባችው ላይ የለም። መከፋታቸውን በእንባቸው እየገለፁ መከፋትን ግን  አያውቁትም። ደማቅ ውሸት ነፍሳቸው ላይ ነግሷል። ባለ ጭንብል ናቸው። ይሄ ጭንብል የህይወታቸው አንዱ አካል ነው።  ውስጣዊ ዓለማቸውና ውጫዊ ዓለማቸው ፍፁም የተለያየ ነው። መልካቸው ፈክቶ ልባቸው ግን ፀልሟል።  አካላቸው ከብሮ ሳለ መንፈሳቸው ተዋርዷል። ሃይማኖት አላቸው ፣ እምነት አላቸው ግን ከሃዲዎች ናቸው።  በአንደበታቸው ፍቅርን ይሰብካሉ፤ ውስጣቸው ግን በጥላቻ ተበክሏል። ህይወታቸውን በንቃት ለመኖር ጎድለዋል። ለሰውና ለእግዜር ታምነው ለእራሳቸው ግን አልታመኑም። ለሰው ሞልተው ለእራሳቸው ጎድለዋል።
መንፈሴም የሰዎችን ልብ ሁሉ መረመረ። ነገር አንድም የሚረባ ነገር አጣሁ። ሰዎች አውሬዎች ሆነዋል። መበላላትን ተፈጥሯቸው አድርገዋል። መወጋጋትን እጣፈንታ አድርገዋል። ክፋትን የተፈጥሮ ስጦታ አድርገዋል።
2
አስክሬኑ ወደተዘጋጀለት ጉድጓድ ገባ። ሰዎች ያለቅሳሉ።  ሰዎች ስለ ሟች እሷ ፀጉራቸውን ይነጫሉ። ደረት ይደቃሉ። የወጣቷን ሟች  ፎቶ ሰዎች ይዘዋል። አበባ የያዙ፣ ጥቁር ባርኔጣ ያደረጎ ጎልማሶች ፣ ጥቁር ጥለት ነጠላ ያዘቀዘቁ ወይዛዝርት ፣ መቀበሪያውን ሞልተውታል። ከሁሉም ተለይቶ የቆመ አንድ ወጣት አለ። ፈገግታው ሰማይ ላይ እንደወጣችው ፀሃይ ሆኗል። ነጭ ሸሚዝ አድርጓል።  ሰዓቱን ደጋግሞ ያያል።  ሰዎች ይገላምጡታል። ድምፁ የጎላ ሳቅ አሰማ። በዙሪያው የነበሩ ሰዎች ሰሙት። በሰሙት ነገር የተደናገጡ መሰሉ። በድጋሚ ያ ደማቅ ሳቅ ተሰማ።
“የጀንበሯ መጥለቅ የዓለም ምፅኣት ምሳሌ ናት። የቆምነው በወደቁ ሰዎች ብርታት ነው። ጨለማው የወጣው በብርሐን ሽንቁር በኩል ነው። የአንዲት አበባ መፍካት የእልፍ አበቦች መጠውለግ ምሳሌ ነው። የኮረዳዋ ፅጌነት …  የባልቴቷ ቆዳ መሸብሸብና አቅም መድከም ትዕምርት ነው። የዚህችም እንስት ሞት የእልፍ እንስቶች መወለጃ ማህፀን ነው።”
በሁሉም ሰዎች የተመላለሰው ይህ ንግግር ከማን እንደወጣ አልታወቀም። ቀብሩ ላይ ግራ መጋባት አጠላ። ነፋሱ ያስነሳው አቧራ ጭንቀቱን ሰው ፊት ላይ በትኖ ጠፋ።
ያ ንግግር ጀመረ።
“አቧሮች ሁሉ ተጠርጎ የመጣል ገቢሮች ናችው። በነፋስ ቅኝ የመገዛትን ትዕንቢት ተናጋሪዎች ናቸው። “
የቀብሩ ፕሮግራም ተጠናቆ - ሁሉም ሰዎች ሄዱ። የተነጠለው ወጣት ወደ መቃብሩ ተጠጋ።  ፈገግታው አሁንም እንዳለ ነው። የሸሚዙ ንጣት መቃብር መሐል መቆሙን የሚክድ የፈንጠዝያ መለከት ይመስላል።  ቀይ ፅጌረዳ አበባ አወጣ። አስቀመጠው።  የፃፋቸውን ደብዳቤዎች አወጣና ማንበብ ጀመረ።
“ሰዎች ጅል ሆነዋል - መውደዴ።  ማፍቀርን እውርነት ይሉታል። መውደድ ልቤ ላይ ሲያርፍ፣ ፍቅር ሲጎበኘኝ ጨለማዬ እንደነጋ፣ ብርሐን እንዳገኘሁ አያውቁም። በእርግጥ አንቺም ጅል ሆነሻል ወድደዴ።  በሰው ስሜት ተስፋ ታደርጊያለሽ። ወደ አንቺ የተዘረጉ እጆች ሁሉ መርዳት የፈለጉ ይመስልሻል። ክፉዎችን የመመልከት ትኩረትሽ ጨምሯል። ጉድለት ላይ ልብሽ ማነጣጠር ጀምሯል። ቆሻሻን ለይቶ የሚመለከት ዓይን ጉድፍ ያለበት ነው። ሰው ንፁህ ነፍስን  በልቦናው መመልከት እስካልጀመረ ልቦናው ሙሉ አይሆንም። መውደዴ ነሽ። ላንቺ ያለኝን ፍቅር ስናገረው ግን በዚያ ቅፅበት ፍቅሬ ትርጉም ያጣል። ማፍቀር ከልብ ወርዶ ምላስ ላይ ሲቀመጥ ማፍቀር ስህተት ይሆናል።
ንገሪኝ እስኪ ፍቅር ምላስ ላይ ምን ይሰራል?
መውደዴ እንዴት ነሽ ግን?”
ሁለተኛውን ወረቀት አወጣ፡-
“መውደዴ፤ ሰዎች ሁሉ አብደሃል ይሉኛል። እስኪ ንገሪኝ የምር አብጃለሁ? እብደትስ የሚባለው ነገር ምንድነው? ተነጥሎ ማሰብ እብደት ነው? ተለይቶ መቆም ማበድ ነው? ማበድ ምንድነው? እስኪ ልጠይቅሽ … ሰዎች ሁሉ እየራቁኝ ብቻሽን እንዴት ልትቀርቢኝ ቻልሽ? ሁሉም ሲርቁኝ እንዴት ብቻሽን ካጠገቤ ቆምሽ? እንዴት በጠሉኝ ሰዎች ተከበሽ ልትወጂኝ ቻልሽ? እንዴት ተረስቼ ሳለሁ አስታወስሽኝ? እንደ ሙት ስታይ ኗሪነቴን እንዴት ልታስታውሽኝ ቻልሽ? እንደ መለኮት ሞቼ ሳለሁ ፈጥረሺኝ ነው? መለኮትስ ቢሆን እንዳንቺ ሊወደኝ ይችላል? ታስታውሻለሽ። እብድ ብለው አንድ ክፍል ቤት ውስጥ ትተውኝ በጠፉ ጊዜ መጣሽ።  በጨለማዬ ውስጥ ብርሐን ሆንሽ።  ቆሻሻ ነኝ ባልኩበት ሰዓት ንፁህ ነህ አልሽኝ። ምን ተሰማህ አትይኝም? በክርስቶስ ቃል መግነዙን ፈትቶ እንደወጣው አላዛር ተዓምራትሽ ልቤ ላይ መደነቅን ዘራ።
ትዝ ይልሻል? ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀፍሽኝ ቀን?  ያኔ ቆሽሾ እንደጠራ ፣ ጎድሎ እንደሞላ ወንዝ ሆንኩ። ያቺ ቀን ፈወሰችኝ። እና አሁን ለእንደኔ አይነት እብዶች መታቀፍ መድሃኒት ነው እላለሁ። ቡና ልጋብዝህ ብለሺኝ ወጣን። ፈርቼ ነበር። አምስት አመት ሙሉ ከአንድ ክፍል ያልወጣ ሰው ፀሃይዋን ለመመልከት ፣ ንፁውን አየር ለመተንፈስ የበቃው ባንቺ ታቅፎ መሆኑ አይገርምም? አንቺ ሴት ሆይ፣ ትንግርትሽ የሚፈልቀው ከወዴት ነው? የልብሽ ንፅህና ምንጩ ምንድነው? የነፍስሽ ታላቅ ልዕልና የታነፀው ከምንድነው? አንቺ ፍቅርን የማመልክበት መቅደስ ሆንሽኝ።  ሰው አይደለሁም ባልኩበት ሰዓት መጥተሽ ሰው ያደረግሽኝ፣  ብቻዬን ነኝ ባልኩበት ጊዜ መጥተሽ ከጎኔ የቆምሽ አንቺ ሴት ሆይ ማን ነሽ?
የጠላሁትን ዓለም ባንቺ ውስጥ ሳየው ተዋበ።  በቃ ልብሽ ውስጥ ጠፋሁ። ከነፍስሽ ገዳም ገብቼ የፍቅርሽን ቆብ ደፋሁ። ከተዓምራትሽ ፀበል ጠጣሁ። ከትንግርትሽ ቡራኬ ተካፈልኩ። “
ሦስተኛውን ደብዳቤ አወጣ።
“መልከ ጥፉነቴን ተቀብዬው ነበር።  የእድሌን ጨለምተኝነት ፣ የእጣፈንታዬን ሰንካላነት ፣ የህይወቴን ጎዶሎነት አምኜ ተቀብዬ ነበር። ማንም ሊወደኝ ፣ ማንም ሊፈልገኝ እንደማይችል አምኜ ነበር። ወደድኩህ ያለችኝ ሴት አልነበረችም።  ቆንጆ ነህ ስትዪኝ ምን ተሰማኝ?  ምንም አልተሰማኝም። ግን ድጋሚ ተወለድኩ። ፍቅርሽ የህልውናዬ ማረጋገጫ  ሆነ።  ወንድ ልጅ መኖር የሚጀምረው በሴት ከተፈቀረ በኋላ ነው። ሴቶች ወደ እኔ ተስበው መጥተው አያውቁም ነበር። ቆንጆ ነህ ካልሺኝ በኋላ መልኬን ሳየው ተለውጧል። መልከ ጥፉነቴ ወደ ውበት ፣ ወደ  ቁንጅና ተለውጧል።
ማን ነሽ አንቺ እኔን ከአፈር የፈጠርሽ? ማን ነሽ ሟችን ከመቃብር ያወጣሽ? ማን ነሽ አንቺ ጨለማዬን በብርሐን የለወጥሽ? መውደዴ ሴት መሆንሽን ስጠራጠር ሰው አለመሆንሽን አወቅኩኝ። አንቺ ጠይም መልዓክ ነሽ። “
አራተኛው
ፈገግታው ወደ ሳቅ አደገ። ደብዳቤውን ማንበብ ተወውና ተነሳ። ወረቀቶቹን መቃብሯ ላይ በትኗቸው መጓዝ ጀመረ። የመንገዶቹ ጠርዞች ህልም የሚመስል ፍካት አሊያም የሆነ የውድቀት ለምለም ሳር የበቀለባቸው ይመስላሉ። ከሃሳቡ መኪኖቹ አናጠቡት።  ወደ ቤት ገባ። ነጭ ሸሚዙን አወለቀ። አልጋው ላይ ተንጋለለ። ጥልቅ እንቅልፍ ወሰደው።
3
በእርግጥ ቀብረውኝ ሄደዋል። ነገር ግን አልሞትኩም። አበባና ደብዳቤ ወዳጄ አስቀምጦልኝ ሄደ። በነጭ ሸሚዝ ቀበረኝ። በፈገግታ ሸኘኝ። ፍቅር የወለደው ሃዘን ከደስታዎች ሁሉ የላቀ ደስታ ነው። በእርግጥ ከስጋ ነፃ ሆኖ መኖር ደስ ይላል።  ወደ እዚህ ወዳጄ ቤት ሄድኩ። ቤቱ አልተቀየረም። አልጋው ላይ ተኝቷል።  የአፈቀሩትን ከቀበሩ በኋላ የሚተኙት እንቅልፍ ንፁህ እንቅልፍ ነው። ይሄም እንቅልፍ ውስጥ ንቃት አለ። ፍቅር ውስጥ እንቅልፍ አልነበረም። ፍቅር ውስጥ እንቅልፍ እንኳን ታላቅ ንቃት ነው። መድከም የለም።  መንፈስ አያረጅም። ደብዳቤዎቹን አጠገቡ አስቀምጬለት ወጣሁ።
ወደ ቤተሰቦቼ ጋ  ሄድኩ። የሀዘንን ከንቱ ሙሾ አየሁ። ለሀዘናችን እንጉርጉሮ ካለ ሃዘናችን በእርግጥ ሃዘን አይደለም።  ሃዘን ቃላትን አያውቅም።  ሃዘን እንቅስቃሴ የለውም። ሃዘን ከስሜት ቀንበር ወጥቶ ባዶ መሆን ነው። በምንምነት መጠመቅ ፣ ለሁሉም ነገር ስሜት ማጣት ነው።  ሃዘን ደረት አይደቃም። ሃዘን ድንኳን አያውቅም።  ሃዘን ጥቁር ሊለብስ ቀርቶ ጥቁር ቀለምን እንኳን አያውቅም።  ቃላትና ቁስ የገለፁት ሃዘን በእርግጥ ሃዘን አይደለም።
ሃዘናቸውን በለቅሶ ፣ሃዘናቸውን በደረታቸው መድቃት ፣ በፀጉራቸው መንጨት ፣አመድ ነስንሶ በመቀመጣቸው ፣ በሙሾ እንጉርጉሯቸው ውስጥ ሳየው በእርግጥ እንዳላዘኑ አወቅሁ። ሃዘን ከስሜት የተሻገረ ባዶነት ነው። ባዶነቱ ስሜት አልባነትን ያቀነቅናል።
4
ሲነቃ መቃብር ላይ በትኗቸው የመጣው ደብዳቤዎች አጠገቡ ናቸው።  ግን ያረጁ የተጎሳቆሉ ይመስላል።  ደርቀዋል ግን ፅሁፋቸው ጥርት ብሎ ይነበባል። ቀና ሲል ቤቱ በሸረሪት ድር ተሞልቷል። ከመተኛቱ በፊት የከፈተው ሙዚቃ እየተጫወተ ነው።
“በመላ በሰበብ ፣ በዘዴ አመኻኝተሽ”
ሁሉም ነገር አርጅቷል። ቤቱ በአቧራ ተሞልቷል። መስታወቱን ጠራረገው። መልኩን ሲያይ አርጅቷል።  ቆዳው የተሸበሸበ ፣ ፀጉሩ ፣ ፂሙ የሸበተ ፣ ዓይኑ የሞጨሞጨ ሰው አየ። እራሱን ተጠራጠረ። ጊዜን ተጠራጠረ። ዘመኑን ተጠራጠረ።
ወደ ደጅ ወጣ።  ሁሉንም ሰዎች አያውቃቸውም።  ልጆች ይጫወታሉ። አበቦች ፈክተዋል። ፀደይ የመጣ ይመስላል።  ነፋስ ይነፍሳል።  ፀሐይ ደምቃ ወጥታለች። ሰማዩ እንደ ኩል ጠርቷል። አሮጊቶች እንጨት ይለቅማሉ። ጠጅ ቤት ፊት የተቀመጠ አግድም ወንበር አለ። ጠጅ በብርሌ ተደርድሮበታል -  ሰዎች ግን የሉም። ብርሌው ይጎድላል። ጠጅ አሳላፊው መጥቶ ይሞላዋል።
ተመልሶ ወደ ቤት ገባ።  በድጋሚ ተኛ።  ነገር ግን በድጋሚ አልነቃም።
5
ብዙ ሰዎች ቤቱን ሞሉት። ከሞተ ክሰላሳ አመት በኋላ ተገኘ። ሙዚቃው ብቻ እየዘፈነ ነበር። እነዚያ ሰላሳ አመት ካንዲት ቅፅበት ያነሱ ነበሩ።
በእነዚህ ሰላሳ አመታት ውስጥ የፍቅር ምንጮች አልደረቁም። የተስፋ ቅጠሎች  አልረገፉም። አበቦች አልጠወለጉም። ሞት እንኳን ሞት ሆኖ  ህይወት ውስጥ ለመገኘት አልተቻለውም። ዓለም በሰው ትንፋሽ አልሞቀችም። በዚህች ፀሃይ አልደመቀችም። ምድር በሰዎች አስክሬን አልቀዘቀዘችም። ያዘኑ አንቀላፍተዋል።  እድሜ አንድ ዘመን ላይ ቆሟል።  ሰላሳ አመት ሙት ሆነው አልጋቸው ላይ የተገኙት ስጋቸው አልበሰበሰም።
በእርግጥ የሞቱ ሰዎች ህያው ናቸው።
6
ምድር ለነፍሴ ፍፁም ባይተዋር ስትሆን ...ምድር ከመቃብሬ ጨለማ እንኳን እንደከፋች ሳውቅ ወደ ተቀበርኩበት ጉድጓድ ተመለስኩ።
ህይወቴን ሞቼ ፣ ሞቴን ኖሬ አሳልፌያለሁ።  ዛሬ ግን መቃብሬን ወደድኩት።  ምክንያቱም ያልጠወለገ ቀይ አበባ ውስጡ አለ።  ክፍቅር የተሰጡ ስጦታዎች ፍፁም አያረጁም።  መውደድ ያመጣቸው ገፀ በረከቶች አይደበዝዙም። ከንፁህ ስሜት የተቸሩ አበቦች በዘመን ብዛት አይጠወልጉም።


Read 858 times