Saturday, 22 June 2024 00:00

ሙያና ጥበብ ሲመጋገብ - ከታወቁ ደራስያን ሥራዎች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሁለተኛ ክፍል

      ሐ. በዓሉ ግርማ
በዓሉ ግርማ በዐማርኛ ልቦለድ ታሪክ የታወቀ ብቻ ሳይሆን፣ ለጥበቡ ሰማዕትነትን የከፈለም ነው። በዓሉ፣ በኢላባቡር ክፍለ ሀገር ሱጴ ውስጥ በ1928 ዓ.ም. ተወለደ። የ፩ኛ ደረጃ ትምህርቱን በልዕልት ዘነበወርቅ ትምሕርት ቤት ተከታትሏል፤ ፪ኛ ደረጃን የተማረው ደግሞ በጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ነው። በትምህርቱ ትጉሕ ስለነበረ፣ በሁለተኛ መልቀቂያ ፈተና ባስመዘገበው ከፍተኛ ነጥብ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለመሆን በቅቷል። በዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪው ያጠናው ሥነፖሊቲካልና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መስክ ነበር። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ፣ በተመሳሳይ የሙያ መስክ በውጪ ሀገር ተምሮ ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል።
ከደረሳቸው በርካታ ልቦለዶች መካከል ከአድማስ ባሻገር የተሰኘው ሥራው በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ታሪክ እንደ ቀዳሚ ዘመናዊ ልቦለድ ይታያል። ይህ መጽሐፍ ታትሞ ሲወጣ ነው ሊቃውንቱ «አሁን ስለኢትዮጵያ ልቦለድ መነጋገር እንችላለን» አሉ እየተባለ የሚነገረው። ከአድማስ ባሻገር  ዓለማቀፋዊ አድናቆት አትርፎ፣ በሩስኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለመስኮባውያን አንባብያንም ቀርቧል። ከዚህ መጽሐፍ በተጨማሪ፣ የሕሊና ደወል (በኋላ ተሻሽሎ ሐዲስ የተባለው)፣ የቀይ ኮኮብ ጥሪ፣ ደራሲው እና ኦሮማይ የተሰኙ ረጃጅም ልቦለዶችን ደርሷል።  ይህ ዕውቅ ደራሲ፣ አጫጭር ልቦለዶችም እንዳሉት ይታወቃል። ለምሳሌ፣ ጭጋግና ጠል በተባለው መድበል ውስጥ «የፍጻሜው መጀመሪያ» በሚል ርእስ አንድ አጭር ልቦለድ አስነብቦናል።  
በበዓሉ ልቦለዶች ውስጥ ዓለማት የስሜት ብርሃን ለብሰው የሚከሰቱ ናቸው። ትረታውን የሆነ ተራኪ የሚነግረን ሳይሆን፣ ራሳችን በዐውደ ዓለሙ ላይ በአካለ ሥጋ ተገኝተን የምንከታተል እስኪመስለን ድረስ ዓለማት ግልጽና ክሱት ናቸው። የሚከተለውን መቀንጭብ እንመልከት፤  
ከባድ ዝናብ ያረገዘው የሀምሌ ሰማይ አጣዳፊ ምጥ ይዞት በጣር ያጉረመርማል። አዲስ አበባ ጥቁር የጉም ብርድ ልብስ ለብሳለች። በጥፊ የሚማታ፤ ቀዝቃዛ ስለታም ንፋስ እያፏጨ የሽምጥ ክንፍ አውጥቶ ይበራል። ዛፎችና ቅጠሎች የዛር ዳንኪራ እየረገጡ ይወዛወዛሉ።
ጠብ ያለሽ በዳቦ እያለ ሲፎክር ከመጣው አህያ ከማይችለው ዝናብ ለማምለጥ እግረኞች ወደየቤታቸው ወይም መጠለያ ካለው ሱቅ ለመጠጋት ይሮጣሉ፤ ወፎች ጫጫታቸውንና እልልታቸውን ትተው ወደየጎጆአቸው ይበራሉ። ሁሉም ወደሰማይ እያዬ ሲሮጥ፤ ሽብር የመጣ ይመስል ነበር።  
ያለርህራሄ በጥፊ የሚማታው ንፋስ አቧራ አንስቶ እሰዉ አይን ውስጥ እየሞጀረ፤ የሴቶችን ቀሚስ ወደላይ እየገለበና ጃንጥላቸውን ለመንጠቅ እየታገለ መንገደኞችን ይተናኮላል። ንፋሱ ከራሱ ላይ የነጠቀውን ባርኔጣ የሚያባርር አንድ መላጣ ሰው አይቶ አበራ ፈገግ አለ። ከታች የሚመጣ አንድ ሰው ባርኔጣውን ባይዝለት ኖሮ ሰውዬው መቆሚያ አልነበረውም።
የበዓሉ ልቦለዶች ስሜት የሚያናውጡት በሐሳባዊ አቀራረብ አይደለም፤ ይልቅስ ተጨባጭ በመሆናቸው የእውነታ መልክና ገጽታ ተላብሰው ነው። ለዚህም ነው፣ በዓሉ የእውነታዊነት ልቦለድ ፈር ቀዳጅ ነው የሚባለው።

ጋዜጠኝነትና ሥነጽሑፍ በበዓሉ ግርማ ድርሰት
በዓሉ ግርማ፣ በጋዜጠኝነት ሙያም ስሙ የተጠራ ነበር። «የዛሬይቱ ኢትዮጵያ» ጋዜጣ አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል፤ የ«መነን መጽሔት» አዘጋጅም ነበር። «አዲስ ረፖርተር» መጽሔትን በአዘጋጅነት በመምራትም ስሙን ተክሎ ያለፈ ሰው ነው። «አዲስ ሪፖርተር» የዓለም አቀፍ መስፈርትን የሚያሟላ ብቃት ያገኘው በበዓሉ አዘጋጅነት ዘመን ነበር። በጋዜጠኝነት ሙያ በኢትዮጵያ ራዲዮ መሥራቱም ይታወቃል።
በኋላ ግን ጋዜጠኛ አልነበረም። በሙያው ላይ ያልቀጠለው፣ ምናልባት፣ ከነበረበት የኃላፊነት ደረጃ እንዲሁም በወቅቱ ከነበረው የትምህርት ደረጃው ከፍተኛነት የተነሳ ሊሆን ይችላል። በሚንስቴር ደረጃ የነበረ ሰው በጋዜጠኝነት ደረጃ ተመልሶ ለመሥራት የኃላፊነት ደረጃው አይፈቅድም። ይሁን እንጂ፣ ከሙያው ጋር የነበረው ፍቅር እስከ ኦሮማይ ድረስ ጅራቱን አንቆ ይከተለው እንደነበር እንመለከታለን። ኦሮማይ ልቦለድ ብቻ አይደለም፤ ዘጋቢ ፊልም ዓይነት ጠባይ ያለውም ነው። ምክንያቱም፤
ትኩረቱ በአንድ ወሳኝ ታሪካዊ ፕሮግራም ላይ ያነጣጠረ ነው። በቀይ ኮከብ ዘመቻ ነባራዊ ተግባራት ላይ ካሜራውን ደግኖ፣ የፈጣሪ ፍጡራን ያከናወኗቸውን ተግባራት ከሥር … ከሥር … እየተከታተለ በመቅረጽ ነው የሚተርከው።
በውሱን ነባራዊ መልክዓ ምድር ዳራ ላይ አተኩሮ፣ በገሐድ የነበሩ ምስላዊ ትረካዎችን ያቀርባል።
ታሪኩ እውነት ከመሆኑም በላይ፣ በታሪክ የሚታወቁ ሰዎች ናቸው ስማቸው እየተቀየረ፣ በገጸባሕርይነት የተሣሉት። በዘመኑ የነበሩ ሰዎችን አግኝተን የማነጋገር ዕድል ብናገኝ፣ «ፊያሜታ እገሊት ናት፤… ሥዕልም እግሌ ነው፤ … እያሉ፣ የፈጣሪ ፍጡራን የሆኑ ሰዎች ይነግሩን ነበር።
ተራኪው ጋዜጠኛ ነው።
እነዚህ ጉዳዮች የጋዜጠኝነት ሙያ በበዓሉ ውስጥ ካሳደረው የክሂሎት ተፅዕኖ የመነጩ ናቸው።
ለነገሩ፣ የበዓሉ ልቦለዶች ወደ ኣማናዊ ዓለም ተጠግተው የዘጋቢ ፊልም ጠባይ የተላበሱ ናቸው። ኦሮማይ ደግሞ፣ ከታሪካዊ እውነታው ጋር ሲገናዘብ የበለጠ ዘጋቢ ፊልም የመሆን ጠባዩ ጎላ። ይህ ብቃት የበለጠ እውን የሚሆነው ደግሞ በሙያው ሠልጥኖ፣ ልምድና ክሂሎት ካዳበረ ጠንቃቃ ጋዜጠኛ ነው። ለዚህ ነው፣ በዓሉ በአካሉ ከጋዜጠኛ ቢሮ ቢርቅም፣ ሙያው ግን ጥበቡን እያበለጸገለት ቀጥሏል ማለት ያለብን፤ ሙያና ጥበብ አንገትና ክታብ ሆነዋል፤ ሙያው አንገት አካሉን ገንብቷል፤ ክታቡ አካሉን አስጊጦታል።  
መ. ደምሴ ጽጌ
ደምሴ ጽጌ ታኅሳስ 21 ቀን 1943 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ነው የተወለደው። የ፩ኛ ደረጃ ትምህርቱን በስብስቴ ነጋሢ ተከታትሎ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በሽመልስ ሀብቴ ፪ኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀቀ። ከዚያ በመምህርነት ሙያ ሠልጥኖ፣ ለተወሰኑ ዓመታት ከሠራ በኋላ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ  ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ደምሴ፣ ከመምህርነት ሙያ በኋላ ያመራው ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ነው። ጋዜጠኝነት የጀመረው፣ በቱሪዝም ኮሚሽን ይታትም በነበረው «ዜና ቱሪዝም» ጋዜጣ ላይ ምክትል አዘጋጅ ሆኖ በመሥራት ነው። ከዚያ በኋላ፣ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን ተቀላቀለ። በማስታወቂያ ሚኒስቴር «የዛሬይቱ» ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል። ከዚያ፣ በዚያው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ወደ «አዲስ ዘመን» ጋዜጣ ተሸጋግሮ፣ የዚህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን ለረጅም ጊዜ ሠርቷል።
ከዚህ ሙያው ጎን-ለጎን፣ የተለያዩ ግለፈጠራ ልቦለዶችን አበርክቷል። መጀመሪያ የልቦለድ እጁን ያሟሸው ፍለጋ በተባለው ኖቬላ ነው። ሌላው ግለፈጠራው ምትሐት የተሰኘው ልቦለዱ ነው። አጫጭር ልቦለዶችንም ይጽፍ ነበር። ለምሳሌ፣ ጭጋግና ጠል በተሰኘው መድበል ውስጥ «ማን ያውቃል» በሚል ርእስ አንድ አጭር ልቦለድ ድርሰት አስነብቦናል። ከግለፈጠራ ሥራዎች በተጨማሪ፣ ከባሴ ሀብቴ ጋር ሆኖ በጣም ተነባቢ የነበረውን የካርንጌን ሥራ ጠብታ ማር በሚል ርእስ ተርጉሞ ለአንባብያን አቅርቧል።
ደምሴ ጽጌ በአርትኦት ሥራውም  ይጠቀሳል። በጋዜጣ አዘጋጅነት ሙያው ከዐበይት ተግባራቱ  አንዱ አርትኦት መሆኑን ማንም አይዘነጋውም። ከዚያ ውጪ የአርታኢነት ብቃቱን የሚያረጋግጥለት በስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ሥራዎች ያተመው የአርትኦት አሻራ ነው። በዚህ ተግባሩ፣ የስብሐት የተፈጥሯዊነት አጻጻፍ ይትበሃል ከአንባቢው ማኅበረሰብ ባህልጋር እንዲቀራረብ በማድረግ ረገድ ጉልሕ ሚና መጫወቱን ስብሐት ራሱ መስክሯል። ከስብሐት ምስክርነት ባሻገር፣ በደምሴ አርትኦት የተቃናውን ቅጽና የደምሴ አርታኢነትን አሻፈረኝ ብሎ የታተመውን ቅጽ ልዩነት ተመልክቶ፣ የዚህን ደራሲ የአርታኢነት አሻራ ማጠየቅ ቀላል ነው።  
ሠ. ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር
ትግራይ ውስጥ አድዋ አካባቢ በምትገኝ በእርባ ገረድ መንደር ሚያዚያ 27 ቀን 1928 ተወለደ። አባቱ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ዮሐንስ ይባላሉ፤ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ መዓዛ ተወልደ መድኅን። በልጅነት ዕድሜው አዲስ አበባ ከዘመድ ዘንድ መጥቶ መጀመሪያ ስዊድን ት/ቤት ተማረ። በኋላ ደግሞ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተምሯል። በትምህርቱ ውጤታማ ሆኖ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትምህርት አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ዲግሪውን እንደተቀበለ፣ በአስፋ ወሰን ት/ቤት ለሁለት ዓመታት ያህል እንግሊዝኛ አስተምሯል። ቀጥሎም በትምህርት ሚኒስቴር የውጪ ትምህርት ዕድል ጽ/ቤት ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ባልደረባ በመሆን አገልግሏል። በኋላም፣ የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በሰጠው የትምህርት ዕድል በፈረንሳይ ሀገር ተምሯል። ይህን የትምህርት ዕድል ለዘለቄታው ባይገፋበትም፣ ከአውሮፓ የሥነጽሑፍ ባህል ጋር እንዲተዋወቅ ግን ሰፊ በር ከፍቶለታል። ይህንን የምናረጋግጠው በቀጣይ ዘመኑ በድርሰት ቆሌ በመለከፉ ብቻ ሳይሆን፣ ፈረንሳይ ሌቱም አይነጋልኝ ለተባለው ድርሰቱ መጻፍ ዐበይ ማዕከል በመሆኗ ነው። የልቦለዷንም መዋጣት ከሚያሳዩን ጉዳዮች አንዱ Les Nuits d’Addis-Abeba በሚል ስያሜ ወደ ፈረንሳይኛ በመተርጎሟ ነው።
ስብሐት፣ ከምንም በላይ፣ የሚታወቀው በልቦለድ ደራሲነቱ ነው።  ካበረከተልን ልቦለዶች መካከል የሚከተሉትን እንጥቀስ፤
አምስት ስድስት ሰባት እና ሌሎችም ታሪኰች
(1981)
እግረ-መንገድ  (በተለያዩ ቅጾች፤ 1985-
1990)
ትኩሳት (1990)
ሰባተኛው መልአክ (1992)
ሌቱም አይነጋልኝ (1992)
እነሆ ጀግና (1997)
የጋዜጠኛነት ሙያ ተመክሮ ካላቸው የሥነጽሑፍ ደራስያን መካከል ስብሐት አንዱ ነው። ስብሐትን መጀመሪያ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ የሳበው የልብ ወዳጁ የነበረው በዓሉ ግርማ ነው። አንድ ቀን በዓሉ፣ «እዚህ ዝም ብለህ ከቢሮክራሲ ጋር ጊዜህን አታባክን፡፡ … ላንተ ተፈጥሮ የእኛ ሙያ ነው የሚስማማህ” እንዳለው ይናገራል። ከዚያም፣ “እሺ እውነትህን ነው …» ብሎ ከበዓሉ ጋር በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥራ ጀመረ። ስብሐት ከ1946-1947 “የተፈሪ መኮንን አላማ” የተባለ መጽሔት አዘጋጅ ሆኖ እንደሠራም ታሪኩ ይናገራል። ከ1960-1962 ባሉት ዘመናትም የኢትዮጵያ ጀግኖች ማኅበር የእንግሊዝኛው መጽሔት አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል። ለረጅም ዘመናት ታዋቂ በነበረው «የካቲት መፅሔት» ውስጥም ተቀጥሮ መስራቱ ይታወቃል፡፡ በዘመነ ደርግ  ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሲቋቋም በአርታኢነት አገልግሏል።

ጋዜጠኝነትና ሥነጽሑፍ በስብሐት የድርሰት ሕይወት
ስብሐት የድርሰት ዓለምን የተቀላቀለው በጋዜጠኛነት ነው። ሒደቱን ብንገምት፣ በስኮላርሽፕ ቢሮ በሚሠራበት ዘመን፣ በዓሉ «ላንተ ተፈጥሮ የእኛ ሙያ ነው የሚስማማህ” ብሎ ከወሰደው ጊዜ ጀምሮ ጋዜጠኛ ሆነ፤ የሙያውን ብዕር አነሳ። ሙያው እያደር የመጻፍ ተነሳሽነትን እያሳደገበት ሔዶ፣ የድርሰት ክሂሎት መበልጸግ ቀጠለ። የድርሰቱ ክሂሎት መበልጸግ ተፈጥሮ ያስታጠቀችውን የሥነጽሑፍ ተሰጥኦ አነቃውና፣ ወደ ጥበቡ መድረክ ተሳበ።
ስብሐት በኋላም መነቃቃትና ክሂሎት የፈጠረለትን የጋዜጠኝነት ሙያ አልተወም፤ ሁለቱን እያዋሐደ ቀጥሏል። ለዚህ አስረጂ የሚሆነን፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ይጽፍ የነበረው «እግረ መንገድ» ነው። በጥናት ቢፈተሽ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተፈልጎ የተነበበበት ዘመን ቢኖር፣ «እግረ መንገድ» ይጻፍ የነበረበት ሳይሆን አይቀርም። ይህ የሙያውንና የጥበቡን በተዋህዶ መክበር ያጠይቃል። አምዱ ዋዘኛ ወጎች የሚተረክበት ነበር። በኢ-መደበኛ፣ በንግግር አከል፣እንደዋዛ፣ … ይተረክ የነበረው «እግረ መንገድ» የጋዜጣውን ጣዕም የማር-እና-ወተት ባሕርይ ሰጠው። ሥነጽሑፋዊነት ለጋዜጠኝነት ኃይል ሰጠው ማለት ነው። ይህ ኃይል መመንጫው የጋዜጠኝነት ክሂሎት መሆኑ ደግሞ እርግጥ ነው። በአጭር አባባል፣ ጋዜጠኝነት ሥነጽሑፍን ወለደ፤ ሥነጽሑፍ ጋዜጠኝነትን አጣፈጠ፤ ለጋዜጣው መነበብ ዐቢይ ምክንያት ሆነ። ከዚህ ማጠየቂያ ተነስተን፣ በስብሐት የድርሰት ዓለም ሙያና ጥበብ ተገጣጠሙ፤ ጋዜጠኛና ደራሲ በሁለት አምዶች ቆሙ እንበል።  

ረ. ነቢይ መኮንን
ነቢይ መኮንን ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ አርታኢ እንዲሁም ጋዜጠኛ ነው። ነቢይ ዕውቅና ያተረፈው በብዙ ዘርፍ ነው፤ ግሩም ችሎታ ያለው ተርጓሚ ነው። ይህም በተለይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያለውን ድንቅ ሥነጽሑፍን የመረዳት ችሎታ ያረጋግጣል። ከዚያ በላይ ግን፣ ሥራዎችን ከእናት ቋንቋ ወደ መጥለፊያ ቋንቋ (ዐማርኛ) በመመለስ ሒደት የሚያጋጥሙ በርካታ ተግዳሮቶች የመጋፈጥ ጥንካሬውንም ጭምር የሚመሰክር ነው። ነቢይ አንቱ የተባለ ገጣሚም ነው። ግጥሞቹ ልብን ይመስጣሉ። በተለይ በግጥሞቹ የሚያነሳቸው ርእሰ ጉዳዮች ከአዲስ እይታ የሚፈልቁና፣ ሀገራዊ አንድምታ ያላቸው ናቸው። በዚያ ላይ የተነገረለት አርታኢም ነው። በ«አዲስ አድማስ» ጋዜጣ ለረጅም ዓመታት በአዘጋጅነት ሲሠራ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ያስተዋለ ሰው፣ ጠንካራ አርታኢነቱን ለመመስከር ግንባሩን አያጥፍም።  
በርካታ የነቢይ ተደራስያን ነቢይን የሚያውቁት በተለይ በ«አዲስ አድማስ» ጋዜጣ ላይ በሚጽፋቸው ተረቶቹ ነው። ከዶ/ር እንዳለጌታ ከበደ ጋር ባደረገው አንድ ውይይት ላይ እንዳስተዋልነው፣ በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ ተረቶችን በተጠቀሰው ጋዜጣ ላይ በርእሰ አንቀጽነት ጽፏል። ይህ ለየት ያለ የርእሰ አንቀጽ ይትበሃል ለጋዜጣ የተለየ የተነባቢነት ሞገስ እንዳጎናጸፈው መናገር ይቻላል።
ነቢይ መኮንን በደርግ ዘመን እሥር ቤት ሆኖ፣ Gone with the Wind የተሰኘውን መጽሐፍ ነገም ሌላ ቀን ነው በሚል ርእስ ተርጉሟል። ይህ የትርጉም ሥራ ለየት ያለ ታሪክ ያለው ነው። መጽሐፉን የተረጎመው በቁርጥራጭ የሲጋራ ወረቀቶች መሆኑ አንዱ የሚያስገርም ጉዳይ ነው። Gone with the Wind የማርጋሬት ሚሼል ረጅም ልቦለድ ነው። የመጀመሪያ እትሙ ዋል-አደር ያለ ነው፤ 1936። ዋል-አደር ይበል እንጂ፣ በጣም ተወዳጅ መጽሐፍ ነበር። በጥቂት ወራት ውስጥ በሚሊየን ቅጂዎች የተሸጠ ልቦለድ ነው። በኋላም ወደ ፊልም ተቀይሮ ለተመልካች ቀርቧል። ይህን የመጽሐፉን ተደናቂነት ያነሳነው፣ ነቢይ መኮንን ጠንካራ ሥራዎችን የማጣጣም ሥነጽሑፋዊ ብቃቱን ለማስታወስ ያህል ነው። Gone with the Wind በነቢይ ወደ ዐማርኛ ተተርጉሞ ለሕትመት ቢቀርብም፣ የሳንሱር መቀስ እየተለተለ ጉዳተኛ አድርጎት ነው የታተመው። ከታተመ በኋላም፣ ምንም እንኳን በገበያ ላይ ተፈላጊነት ቢኖረውም፣ ዳግም እንዳይታተም ተፈርዶበት፣ በመጀመሪያ እትም ብቻ እንዲቀር የተደረገ ሥራ ነው።
ነቢይ መኮንን በወርኃ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት አጋርነት፣ በፍሬንድሺፕ ሆቴል ሦስት የትርጉም መጻሕፍት ተመርቀውለታል። ከሦስቱ አንዱ ራሱ ነገም ሌላ ቀን ነው ሲሆን፣ ሁለቱ ደግሞ የመጨረሻው ንግግር እና የእኛ ሰው በአሜሪካ ናቸው።
ነቢይ ሌላው በጣም የሚደነቅበት የሥነጽሑፍ ጥበብ ሥነግጥም ነው። የተለዩ የሥነግጥም መድበሎች አሉት፤ ስውር ስፌት (በሁለት ቅጾች) እና ጥቁር፣ ነጭ፣ ግራጫ ግጥሞች የተሰኙት ሥራዎቹ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የሚያውቃቸው ናቸው። «ጁሊየስ ቄሳር»፣ «ናትናኤል ጠቢቡ» እንዲሁም “ማደጎ” የተሰኙ በመድረክና በቴሌቪዥን የቀረቡ የተውኔት ሥራዎችም እንዳሉት ይታወቃል። ባለካባና ባለዳባን  በመሳሰሉ ተውኔቶች ውስጥ በተዋናይነትም መሳተፉን መረጃዎች ያሳያሉ። “ማለባበስ ይቅር” የተባለውንና በኤች-አይቪ ላይ ያተኮረውን የዘፈን ግጥምም የገጠመው እሱ ነው።
ጋዜጠኝነትና ሥነጽሑፍ በነቢይ የድርሰት ዓለም
«አዲስ አድማስ»ን ተወዳጅና ተነባቢ ካደረጉት ዐበይት ጉዳዮች አንዱ ርእሰ አንቀጹ ነው። ርእሰ አንቀጹ በትውፊታዊ ትረታዎች እየተቀመመ ሲቀርብ ኖሯል። ትረታዎቹ ልቦለዶች መሆናቸው ነው፤ ሥነጽሑፍ። ነቢይ መኮንን በጋዜጠኝነት ሙያው የሚታወቀው፣ ከልቦለድ ዓለም ለሙያው ማበልጸጊያ የሚሆኑትን እነዚህን ትረታዎች እያመጣ፣ ሙያንና ጥበብን በማስተቃቀፍ ነው። ጋዜጠኝነቱን ለልቦለዱ ድልድይ ወይም መድረክ እንዲሆን ሲያበቃው፣ ልቦለዱን ደግሞ የጋዜጣውን የተነባቢነት ጸጋ ማጎናጸፊያ አደረገው። በሌላ አባባል፣ ልቦለድ ለጋዜጠኝነት ማጣፈጫ ቅመም ሆነ ማለት ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ጋዜጣው ትረታዎቹን አትሞ ሲያቀርብ ልቦለዶቹ የሚነበቡበት መድረክ አገኙ፤ ሙያው ለጥበቡ መናኘት አብነት ሆነ። የነቢይም ስም የናኘው ሁለቱ በሚያመነጩት መልካም መዓዛ እየታወደ ነው።
ሰ. ዓለማየሁ ገላጋይ
ዓለማየሁ ገላጋይ በ1960 ዓ.ም. አራት ኪሎ አካባቢ እንደተወለደና፣ በዚያው አካባቢ እንዳደገ ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በየምክንያቱ አውግቶታል፡፡ ፩ኛ ደረጃን የተማረው በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ነው። ወደ ፯ኛ ሲያልፍ ግን ፈተና ገጠመው፣ አሳዳጊው የነበሩት አያቱ በእኛ ዘር ከዚህ በላይ የተማረ የለምና፣ ይበቃሃል ብለው፣የትምህርት ማዕቀብ ጣሉበት። እናቱ ግን አልተስማሙም፤ ካልተማርክ የማላይህ ሀገር ሔደህ ዱርዬ ሁን ብለው ስለተቆጡት፣ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒልክ ፪ኛ ደረጃ ት/ቤት ቀጥሎ ማጠናቀቅ ነበረበት፡፡ በኋላም፣ በአዲስ አበባ ስኩል ኦፍ ጆርናሊዝም ጋዜጠኝነት አጥንቶ ተመርቋል፡፡ የሥነተግባቦት ባለሙያ ነው እንበል።
የዓለማየሁ መጀመሪያ ቀለም የቀመሱት ሥራዎቹ ዜማ በተሰኘው መድበል ውስጥ የታተሙ ሁለት አጫጭር ልቦለዶች ናቸው፤ «ሙትና ሐውልት» እንዲሁም «ሚዛኑ-ሰብእ ወ እንስሳት» የተሰኙት። በዚያው ቀጥሎ፣ ዛሬ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሆኗል። በዚህ ዘመን በሰፊው ከሚነበቡ ልቦለድ ደራስያን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ዓለማየሁ ነው። በርካታ ልቦለዶችን ደርሷል፤ አጥቢያ፣ ወሪሳ፣ የብርሃን ፈለጎች፣ ታለ በእውነት ስም፣ ኩርቢት፣ የመሳሰሉትን። ከልቦለዶቹ በተጨማሪ፣ የስብኃት ገብረ እግዚአብሔር ሕይወትና ክህሎት፣ ኢህአዴግን እከሳለሁ፣ የፍልስፍና አፅናፎት እንዲሁም መልክአ ስብሐት የተሰኙ ኢ-ልቦለዳዊ መጻሕፍትን አሳትሟል::
ከጋዜጠኝነት ት/ቤት ተመርቆ ከወጣ በኋላ፣ በቀጥታ የተሰማራው በተመረቀበት ሙያ ነው። የሠራባቸው ጋዜጦች በርካታ ናቸው። “ኔሽን”፣ “አዲስ አድማስ”፣ “ፍትሕ”፣ “አዲስ ታይምስ”፣ እና “ፋክት” ሊጠቀሱ ይችላሉ። በነዚህ የንባብ ሚዲያዎች ላይ ኂሳዊ መጣጥፎችን የሚጽፈው በግንባር ሥጋነት ነበር፡፡ በድርሰቶች፣ በሰዎች አመለካከትና በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሙያዊ ዕውቀቱንና የብዕር ክሂሎቱን ተጠቅሞ ትንታኔ ይሰጣል፤ ይተቻልም። ያልታየውን የሚያይ መረር ያለ ኃያሲ ነው። ባጭሩ፣ ዓለማየሁ ጋዜጠኝነትን፣ ደራሲነትንና ኃያሲነትን አስተባብሮ በስፋት የሠራ፣ ወደፊትም ብዙ እንደሚሠራ የምንጠብቅበት ለሚዲያ ባልደረባው፣ ለሥነጽሑፍ ባለካባው ነው።
በዓለማየሁ ሥራዎች ሙያና ጥበብ ምንና ምን ናቸው?
ዓለማየሁ ገላጋይ ራሱን ከጋዜጠኛነት ሙያ አፋቶ ከልቦለድ ጋር የቃልኪዳን ቀለበት ማጥለቁን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያምናል፤ አልፎ-አልፎ፣ በሚዲያዎች የሚለቃቸው መጣጥፎች ሳይዘነጉ። ሆኖም፣ አንድ ባል ከሚስቱ ሲፋታ፣ የሚጋራው ባሕርይም ሀብትም እንዳለ ሁሉ፣ ጋዜጠኝነትም ለዓለማየሁ ያጋራው ነገር ይኖራል። ምን?
ዛሬ አያምስልበትና፣ ዓለማየሁ በሙያው ለተለያዩ ጋዜጦች ሲሠራ ነበር። ያ አጋጣሚ ለልቦለድ ጥበቡ ብዙ ትሩፋቶች መቸሩ ግልጽ ነው። አስቀድሞ ነገር፣ ሙያው የድርሰት ክሂሎቱን አበልጽጎለታል፤ ብዕሩን ስሎለታል፤ የድርሰት ክሂሎት አስታጥቆታል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሙያው በተደራስያን ዘንድ ዓይን ውስጥ የሚገባ ብዕረኛ አድርጎታል። ዓለማየሁ (እንደጋዜጠኛ)፣ ከሌሎች ጋዜጠኞች (ለምሳሌ ከስብሐትም ከነቢይም) ተለይቶ እንዲነበብ የሚያደርግ ባሕርይ አለው። ስብሐትና ነቢይ መኮንን በማዝናናት ላይ ያተኩራሉ። ዓለማየሁ ግን ተደራሲን በመተንኮስ የሚታወቅ አምደኛ ነበር (ዛሬም ነው)። ተንኳሽ ርእሰ ጉዳዮችን ያነሳል። እይታው ምን ጊዜም ብርቅዬ ነው፡ በዚያ ላይ፣ ትንኮሳው ልብ በሚያርድ-ትጥቅ የሚያስፈታ የቋንቋ አረር የሚተኮስ ነው። ይህ የአጻጻፍ ባህሉ የተወሰነውን አንባቢ በተቃውሞ፣ የተቀረውን ደግሞ በተደሞ ለንባብ የሚያቁነጠንጥ ነው። ዓለማየሁ ጻፈ ሲባል፣ አንባብያን ጽሑፉን በማደን ሥራ ይጠመዳሉ። ይህ ሁኔታ ለዓለማየሁ የልቦለድ ጥበብ ምንድግና አንዱ ቁልፍ ጉዳይ ነበር።
ጋዜጠኝነት ያተረፈለት ሌላም ትሩፋት አለ፤ የተመክሮ ክምችት ባለጸጋ አድርጎታል። ጋዜጠኛ በነበረባቸው ዘመናት፣ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የገበየው ሰብአዊ፣ መልክዓ ምድራዊ፣ ባህላዊ፣ ወዘተ፣ ቁምነገር ለቁጥር ያታክታል። ይህ ግብይት በየዘመኑ ለሚጽፋቸው ልቦለዶች የስሜት፣ የምናብ፣ የጭብጥ፣ … ጥሪትና እርሾ ማስገኘቱን ማን ይክዳል? ባጭሩ፣ ከዓይነተ ብዙ ዐውደ ዓለም የተገበየ የተመክሮ ክምችት፣ በጋዜጣ የታሸ የድርሰት ክሂሎት፣ ከእይታ ብርቅዬነት የተገበየ ተነባቢነት፣ … ዓለማየሁ ከጋዜጠኝነት ሙያው ገብይቶ ለልቦለድ ድርሰቱ በግብአትነት የተጠቀመባቸው ጥሪቶች ናቸው። በዚህ የተነሳ፣ የጋዜጠኝነት ሙያ ለዓለማየሁ ልቦለዶች ፋና ወጊና መንገድ ጠራጊ ነበር ብለን እንፈጠማለን።
፬. ማጠቃለያ   
የደራሲነት ጸጋ ከተሰጥኦ ነው የሚገኘው ብለን እንፈጠም። ሆኖም፣ የሚያዳብረው ክሂሎት ይሻል። ጥበቡን የማመንጨት ጸጋ ተሰጥቶ በወጉ ካላቀረብነው ጥበቡ ግቡን አይመታም። ጥበቡን የማመንጨት ጸጋውን በክሂሎት ስናግዘው ግን የታለመው ጥበብ ይሳካል። በብዙዎቹ ደራሲዎቻችን ተመክሮ እንደምናስተውለው፣ ጋዜጠኝነት የድርሰትን ቴክኒካዊ ክሂሎት ማዳበሩ ግልጽ ነው። ይህን የሚያረጋግጥልን ተተኳሪዎቹ ደራስያን ወደ ድርሰት ዓለም የገቡት በጋዜጠኝነት ሙያ ሐዲድ ላይ ተጉዘው ነው።
በልቦለድ ድርሰት የሚያመረቃ ሥራ ደርሶ ለአንባብያን በማድረስ ረገድ ውጤታማ ለመሆን ሦስት ጉዳዮች የግድ ናቸው።      
የሥራው ጥበባዊ ጥራት (ብቃት)፡- ይህ የመጀመሪያው ጉዳይ ነው። የጥበቡ ብቃት እንዲረጋገጥ፣ አስቀድሞ ደራሲው የጥበቡ ተሰጥኦ ያለው መሆን አለበት። የጋዜጠኝነት ሙያ በእርግጥ ሰውዬው ተሰጥኦው እንዳለው ወይም እንደሌለው ለማረጋገጥ የመፈተሻ ሜዳ ነው። በሙያው ውስጥ እየሠራ የተሰጥኦውን ልክና መልክ ማጤን ይችላል።      
የመነበብ ጥያቄ፡- አንድ ተሰጥኦው ያለው ደራሲ ቀጥሎ የሚያሳስበው ጉዳይ፣ ብጽፍ  ማን ያነበኛል የሚለው ነው። የጋዜጠኝነት ሙያ የተሰጥኦ ጸጋ ለተለገሰው ደራሲ የመነበብ መድረክ ያመቻቻል። ጋዜጠኝነትን እንደሙያ በሚሠራበት ዘመን የጥበብ ተሰጥኦው በአንባብያን ዓይን ውስጥ እንዲገባ ያደርገውና፣ በጋዜጣ መጣጥፎች ከሰው ቀልብ የመግባት ዕድል ያገኛል። ለተተኳሪ ደራሲዎቻችን ጋዜጣ ይህን የዕድል ማዕድ እንደዘረጋላቸው እንገነዘባለን።
የማሳተም አቅም፡- ይህ ኪስን የሚመለከት ጉዳይ ነው። ተሰጥኦንና ተነባቢነትን በጋዜጠኝነት ሙያ ያዳበረ አንድ ደራሲ፣ የሚያወጣው የጥበብ ሥራ የመሸጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ይህን የሚፈጥረው የመነበብ ዕድሉ ስፋት ነው። የሥራው የመነበብ ዕድሉ ከፍተኛ ሆኖ ከተገኘ፣ ደራሲው በኪሱ መሳሳት ምክናት ሥራውን ከማሳተም የሚታቀብበት ሁኔታ አነስተኛ ነው፤ አቅሙ ያላቸው የገበያ ሰዎች ተሻምተው ያሳትሙለታል።
በእነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ የጋዜጠኝነት ሙያ ለልቦለድ ጥበብ የሚኖረውን ውለታ ማስተዋል ይቻላል። ተተኳሪ ደራሲዎቻችንም በዚህ የሙያው ውለታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል።  
ማስታወሻ፡- (ጽሁፉ በኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን፤ የኤፍ.ኤም. 97.1 ሬዲዮ ጣቢያ  24ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ለውይይት መነሻ የቀረበ (ግርድፍ ሐሳብ) ነው፡፡ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም.)

Read 172 times