Saturday, 22 June 2024 00:00

ባሻ አሸብር በጀርመን

Written by  ዘላለም ከበደ (ጋዜጠኛ)
Rate this item
(1 Vote)

 እንደ ቀድሞው ባይሆንም አልፎ አልፎ መጽሐፍ እገዛለሁ፤ አነባለሁ፡፡ ከምርጫዎቼ አንዱ ደሞ ጋሽ ግጥም ናቸው፡፡ ከላይ ርዕስ ያደረኩት  የአዲስ መጽሐፍ መጠሪያ ነው፡፡ ድንቅ ድንቅ ግጥሞችን የያዘ አዲስ የግጥም መድብል፡፡ ጸሃፊው ሰሎሞን ሞገስ /ፋሲል/ ይባላል፡፡ ከዚህ ቀደም አራት  ስራዎች አንብቤለታለሁ፡፡ በተለይ ከአንባቢ ጋር ያስተዋወቀው “ እውነትን ስቀሏት!” የተሰኘው ቀዳሚ ስራው ነው፡፡ ባልሳሳት ይህ ስራ የታተመው በ2001 ዓ .ም አካባቢ ነው፡፡ በቃሌ የማስታውሰው አንድ ስራም ተካቶበታል፡፡ “አክሱምን አቃጥሉት” የሚል ደንግጬና ተናድጄ ያነበብኩት፡፡ ደግሞም አንዳች እውነት ያለው ግጥም።
በስውር በስውር ሳታወጡ ይፋ፣
አክሱምን አቃጥሉት ላሊበላም ይጥፋ፤
ሁሉም ቢተባበር የሚያቅት አይደለም፣
ጢያና ጀጎልን ባንድ ላይ ለማውደም፤
መስጅድ ፣ ቅርሳቅርሱ ፣ ፍልፍል ቤተ
መቅደስ፣
በዘዴ በዘዴ በየተራ ይፍረስ፤
የጥበብ መጻህፍት ጥንታዊ ብራና፣
በእሳት ይቀጣጠል ጋዝ ይርከፍከፍና።
የአያቶቹ ጥበብ ደብዛው የጠፋበት
ለምን ይሄ ትውልድ ወቀሳ ይብዛበት?
አክሱም ፋሲል ግንብን ማቃጠል ነው ጥሩ፣
በዘመናችን ላይ እንዳይመሰክሩ።
ስንፍናዬን ያየሁበት ሞጋች ስራው ነበረ፤ እውነትን ስቀሏት፡፡ ከዚያ በኋላ ያቀበለን ስራዎች በ2004 ዓ.ም ከፀሃይ በታች፣ በ2006 ዓ.ም ጽሞናና ጩኸት እንዲሁም በ2009 ዓ.ም  የተገለጡ ዓይኖችን አሳትሞ አንብበቤለታለሁ፡፡ አሁን ደግሞ በስደት ከሚኖርበት አገር ባሻ አሸብር በጀርመን ብሎ መጥቷል፡፡
በነገራችን ላይ ሰሎሞንን አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄ አስተዋውቆኝ የመጨዋወት እድልም ነበረኝ፡፡ እናም የማልረሳው ደርዝ ያለው ጉዳይ እንዳወራኝ አስታውሳለሁ፡፡ ይህንንም በዚህ አዲስ ስራው ውስጥም አግኝቼዋለሁ፡፡ ጂጂ /እጅጋየሁ ሺባባው/ ነፍሱ ነች፤ አቤት ሲወዳት፡፡ ሃሳቧን ይጋራታል፡፡ በሷ ቀልድ አያውቅም፡፡ እንደ ማሳያ ከዚህ ስራው ላይ እንጥቀስ፡፡  ቃል በቃል ባይሆንም የጂጂን የሃገራዊ አብሮነትና የአድዋ ሙዚቃዋን ሃሳብ ይጋራል፡፡ እንዲህ እያለ:-
የመለያየትን ግንብ ከፈረካከስነው፣
የጥላቻ ግንብን በፍቅር ካከምነው፣
ስንዴህ ውስጥ ያለውን አረም ከነቀልከው፣
የጎጠኛን አጥር ከደረማመስከው፣
ሌላ አድዋ የለም አድዋ ይሄ ነው።
እዚህ ጋ የጂጂን “እኔን የራበኝ ፍቅር”ን ማስታወስ የግድ ይላል አይደል?
የሰሎሞን ሞገስ አዲስ ስራ “ባሻ አሸብር በጀርመን” 48 ግጥሞችን የያዘ የ76 ገጾች መጽሐፍ ሲሆን፤ ለገበያ የዋለውም በ150 ብር ነው፡፡  አያሌ እይታዎች በውስጡ ተካተዋል፡፡ ገጣሚው አንድ ሆኖ ብዙ መሆኑን ያሳየናል፡፡ በተለይ እኔ እንደታዘብኩት  ሰሎሞን መሰደዱ ለመጻፍ ጠቅሞታል ወይስ ጎድቶታል የሚል ጥያቄ ፈጥሮብኛል። የህትመት ስራውን ካደረሰን ከ6 አመታት በላይ ቢሆንም፣ አሁንም የብዙ ስራዎቹ ጭብጥ ከአድማስ ባሻገር መሆናቸውን ያሳብቃሉ፡፡ ለአብነት ያህል እኔና ፈረንጆች የተሰኘ ስራውን ጀባ ልበላችሁ:-
እዚህ ነጮች አገር በየጎዳናው ላይ ደሞም በየሞሉ፣
ውሻውን ይዞ ነው የሚዞር ሰው ሁሉ፤
ግና ከፈረንጆች እኔስ መች አንሳለሁ?
ይኸው ክፉ አመሌን ይዤው እዞራለሁ።
እንቀጥል ደሞ፡፡ የመጽሐፉ መጠሪያ ስራም የተጠነሰሰው እዚያው ስደት ማሳ ላይ ነው፡፡ ግጥምን ስናነሳ ፈጽሞ የማንረሳቸው ተወዳጅ ባለቅኔ መንግስቱ ለማ  /አብዬ መንግስቱ/  ከባህር ማዶ ሆነው የጻፉት ባሻ አሸብር በአሜሪካ ከዓመታት በኋላ በጀርመን ተከሰተ፤ በሚጣፍጥ መልኩ፡፡ ለቆንስላ ተግባር በታላቅ ሹመት ወደተሄደባት ሃገር፡፡ አንዴ እኛን ሊተቸን ቀጥሎም እነርሱን /በርሊኖችን/፡፡
የታክሲ የባቡር የአውቶቡስ ብዛት፣
ሰማይ ጠቀስ ህንጻ የመንገዱ ጽዳት፤
ግሩም መናፈሻ የከተማው ውበት፣
ለማለት ያሰኛል የፈረንጆች ገነት። ……
              ……….
ይልህ ይልህና
ቁጭት እያኘኩኝ ስዋብ በጎዳናው፣
ቀልቤን አንዳች ነገር በስተግራ ጠራው፤
በአይኔ ጥልቅ ያለው አንዳፍታ በስሱ፣
ሴትና ሴት ሆነው ከንፈር ሲዋዋሱ ፤
‹እንዳማረ አይገድል’ አለ ያገሬ ሰው!!
የሞጃው ተወላጅ የጠራሁት መንዜ
እኔ አሸብር ከልካይ፤
ምናለ በሞትኩት ይሄን ነውር ከማይ!?
እንዲህም አለ ወይ ቅጡ ያልተያዘ፣
ላዩን እጅግ አምሮ ውስጡ የነቀዘ……
ደሞ ያመጣህና ናፈቀኝ ሃገሬ ይልሃል፡፡ በምጸት ያደባይሃል፡፡ ከተለመደው የአገሬ ናፈቅሽ አፃፃፍ ወጣ ብሎ :-
ናፈቀኝ ሃገሬ ስንቱ ጉድ የቻልነው፣
በርበሬ ተብሎ ሸክላ የሸመትነው፣
ጤፍ እንጀራ ብለን ጀሶ የጎረስነው፤
        …………
ቀበሌ እገባና ወይ አንዱ መስሪያ ቤት፣
ፋይሌ ሲጠፋ ጉዳዬ ሲጓተት፤
ቢሯቸው ገብቼ አንጀቴ ካረረ፣
እንደልቤ እሳደብ እጯጯህ ነበረ፤
እዚህ በሰው አገር መብቴ አልተከበረም፣
እንኳንስ መሳደብ መገላመጥ የለም፤
አገሬ ናፈቀኝ !.....
ሰሎሞንና አዲሱ መጽሐፉ በጥቂቱ ይህንን ይመስላል። ገዝታችሁ ብታነቡት ታተርፋላችሁ። በነገራችን ላይ የኮሜዲያን ማርቆስ ተወዳጅ ስራዎች እሮሮ ፣ እጅጋየሁ እና ቁራሌው የዚሁ ገጣሚ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው፡፡ ሌላም ላክል፡፡ በ2014 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደውና የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዳኝነት በተሳተፉበት የዳሽን አርት አዋርድስ ላይ ገጣሚ ሰሎሞን ሞገስ በግጥም ዘርፍ አሸናፊና የ100 ሺህ ብር ተሸላሚ ነበር፤ ህልሞቻችሁን ፈልጉ በሚለው ግጥሙ። ሰሎሞን ቀጣይ የግጥም ስራዎቹን ቶሎ ቶሎ እንደሚያደርሰን በመመኘት፣ በባሻ አሸብር በጀርመን ላይ ያደረግሁትን ዳሰሳ በዚሁ እቋጫለሁ።

Read 132 times