Friday, 28 June 2024 21:14

60 ሚሊዮን. ዶላር የሚያሸልመው የኢ-ስፖርት ዓለም ዋንጫ በሪያድ ሊጀመር ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  አሸናፊዎች በሚሊዮን ዶላሮች ይንበሸበሻሉ
 
በነዳጅ ሀብቷ የበለጸገችው ሳውዲ አረቢያ፣ ከአንድ ዓመት በፊት ኢ-ስፖርት የዓለም ዋንጫ የሚል አዲስ የስፖርት ውድድር እንደምታዘጋጅ አስታውቃ ነበር፡፡  በየዓመቱ ክረምት ወር ላይ እንደሚካሄድ የተነገረለት አዲሱ ውድድር፤ ቴክኖሎጂዎችን መሰረት ያደረጉ የዓለም ዋንጫ ውድድሮችን ያካትታል፡፡  

ሀገሪቱ ለዋንጫ አሸናፊዎች በአጠቃላይ 60 ሚሊዮን ዶላር የምትሸልም ሲሆን፤ ውድድሩ ከሰኔ 26 ቀን እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በሪያድ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡  የሳውዲ አረቢያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው፤ በዚህ የዓለም ዋንጫ ላይ በ21 የውድድር አይነቶች 30 ክለቦችን የወከሉ 1ሺህ 500 ተጫዋቾች ይሳተፋሉ፡፡

ለጨዋታው አሸናፊዎች 33 ሚሊዮን ዶላር፣ በየውድድሩ ኮከብ ለሆኑ ተጫዋቾች 1 ሚሊዮን ዶላር፣ ወደ ቀጣይ ዙር ለሚያልፉ 7 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለሌሎች የማጣሪያ ጨዋታ አሸናፊዎች 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሸለሙ ተነግሯል፡፡  

 በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ መካከል በስፖርት ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት፣ የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጆችና ፈጣሪዎች ይገኙበታል፡፡ አዲዳስ፣ ሶኒ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የንግድ ኩባንያዎች የውድድሩ ስፖንሰሮች እንደሆኑም ተገልጿል፡፡

ሳውዲ አረቢያ ይህን ውድድር ይፋ ያደረገችው ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ ጎብኚዎችን ለመሳብ፣ የ2029 የእስያ ዓመታዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት፣ እንዲሁም  የ2034 ፊፋ ዓለም ዋንጫና ኦሎምፒክ ውድድሮችን ለማስተናገድ በማለም  ነው፡፡

Read 1125 times