Saturday, 22 June 2024 00:00

የኮሪደር ልማቱ - በልማት ተነሺዎች አንደበት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

* ሌሎች አካባቢዎችም እንደዚሁ ለምተው ለማየት እጓጓለሁ
* እኛ ለቅቀን ስንሄድ አካባቢው ጭልምልም ያለ ነበር
* አዲስ አበባ የእውነትም ”አዲስ አበባ“ ሆናለች



የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የተጀመረ ሰሞን ብዙ ቅሬታዎችና ተቃውሞዎች መስተጋባታቸው አይዘነጋም፡፡  ”ታሪካዊ ቅርሶች እየፈረሱ  ነው“ ከሚለው ጀምሮ፣ ”የልማት ተነሺዎች ከመኖሪያቸው እየተፈናቀሉ ነው“ እስከሚለው ድረስ፣ የተለያዩ እውነታ ላይ ያልተመሰረቱና በሃቀኛ የመቆርቆር ስሜት የተንጸባረቁ ድምጾች  ተደምጠዋል፡፡
ይሄ ብቻም አይደለም፡፡  የኮሪደር ልማቱ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የሚለውን የከተማዋን አስተዳደር መግለጫ  በጥርጣሬ የተመለከቱም ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም፡፡ አንዳንዶች እንደውም  የኮሪደር ልማቱ ከመጠናቀቁ በፊት ክረምት እንደሚገባና የልማት ሥራው እንደሚስተጓጎል ገምተው  ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ነው  የኮሪደር ልማቱ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መገባደዱን ሲመለከቱ በእጅጉ የተገረሙት፡፡     

ለነገሩ ቢገረሙም  አይፈረ

ድባቸውም፡፡ ለምን? ቢሉ፣ ለረዥም ዘመን  መንግሥት የገባውን ቃል ባለማክበር ነበር  የሚታወቀው፡፡ አያሌ የልማት ሥራዎችና ፕሮጀክቶች ተጀምረው መሃል ከደረሱ በኋላ ሲቋረጡ ታይተዋል፡፡

በፕሮጀክቶች መጓተት ሳቢያ ህዝብና አገር ለኪሳራ ተዳርገዋል፡፡ በርካታ የመሰረት ድንጋዮች አንቱ በተባሉ የመንግሥት ሃላፊዎች ተጥለው የተረሱበት አጋጣሚም ብዙ ነው፡፡  በአጠቃላይ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው ዕቅድና በተገባላቸው ቃል መሰረት አከናውኖ ማጠናቀቅ ለአገራችን እንግዳ ነበር ማለት ይቻላል፡፡  
በእርግጥ የፕሮጀክቶች ክንውን ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በእጅጉ ተለውጧል፡፡ በለውጡ ማግስት በአዲስ አበባ ብቻ በርካታ ፕሮጀክቶች በአስደናቂ ፍጥነትና የጥራት ደረጃ ተጠናቅቀው ብዙዎችን  አጀብ አሰኝተዋል፡፡ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትም ከእነዚህ መሰል ክንውኖች አንዱ ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡ የፕሮጀክቶች ክንውን እየተለወጠ መምጣቱን ከሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተርታ የሚጠቀስም ነው፡፡
የኮሪደር ልማት ተነሺዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ከመነሳታቸው በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የሚሰራውን የልማት ሥራ በፈለጉ  ጊዜ መጎብኘት እንደሚችሉ ቃል ተገብቶላቸው ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ነው ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ሃላፊዎችና ሌሎች የወረዳ ሃላፊዎች የልማት ተነሺዎችን በቡድን ተከፋፍለው፣ የለሙ የከተማዋን  አካባቢዎች ያስጎበኙት፡፡
በዚህ ጉብኝት ወቅት ነዋሪዎች በሞባይላቸው የለሙ አካባቢዎችን ፎቶ ሲያነሱና እርስ በርስ ሲነሱ፤ እንዲሁም በደስታ ሲያዜሙና  ሲጨፍሩ ተስተውለዋል፡፡ በአጠቃላይ ነዋሪዎቹ ባዩት የልማት ሥራ መደሰታቸውንና መደነቃቸውን ሁለመናቸው ይናገር ነበር፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡን ጎብኚዎች የነገሩንም ይሄንኑ መንፈስና ድባብ የሚያረጋግጥ ነው - ደስታንና መደነቅን፡፡  
በዕለተ ቅዳሜው የጉብኝት መርሃግብር፣ የልማት ተነሺ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ከአራት ኪሎ አንስተው እስከ ፒያሳና ቴዎድሮስ አደባባይ ድረስ የለሙ አካባቢዎችን በእግራቸው ተዘዋውረው  ጎብኝተዋል፡፡
እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ ተወልደው ለ50 ዓመታት ያህል መኖራቸውን የገለጹልን  ወ/ሮ ትዕግስት አዘዘ፤ እነዚህን  የልማት ሥራዎች በመመልከታቸው  በእጅጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ ጠላ በመሸጥ ሥራ እንደሚተዳደሩ ያወጉን  እኚህ እናት፤ ”አካባቢውን በፊት አውቀው ነበር፤ እንደዚህ ግን አልነበረም“  ይላሉ፡፡ “አሁን በጣም ተለውጧል፤ እንዲህ በመልማቱም ደስተኛ ነኝ፡፡” ሲሉም ወይዘሮ ትዕግስት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡    
ከየካ ክፍለከተማ፣ ወረዳ 7 የመጡት ወ/ሮ የወይንሸት አለባቸውም እንዲሁ በጉብኝቱ  በተመለከቱት ልማት  መደነቃቸውን  ነው የተናገሩት፡፡
“እኔ ይህን ቦታ ሳውቀው ዝም ብሎ መንደር ነበር፤ መንገዱ ወጣ ገባ የሆነ፣ በሸራ የተከለለ፣ ለዕይታ ደስ የማይሉ ቤቶች የነበሩበት ሥፍራ ነው” ያሉት ወ/ሮ የወይንሸት፤ “አሁን ሳየው አዲስ አበባ ውስጥ ያለሁ ሁሉ አልመስል ነው ያለኝ፤ አዲስ አበባ የእውነትም አዲስ አበባ ሆናለች” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመዲናዋ ሲኖሩ  ብዙ ልጆች ወልደው ማሳደጋቸውንና የዕድሜያቸውን አጋማሽ ማሳለፋቸውን  የጠቆሙት ወ/ሮ የወይንሸት፤ ያዩት ልማት በተለይ ለልጆቻቸው ብሩህ ተስፋን የሚፈጥር አለኝታ እንደሚሆናቸው  ተናግረዋል፡፡
ለኮሪደር ልማቱ ከመነሳቸው በፊት  ፒያሳ  ዳርማር ተብሎ በሚታወቀው  ፎቅ ላይ ለብዙ ዓመታት መኖራቸውን የነገሩን አቶ ግርማ ገዜ፤ አካባቢው የቆሻሻ መጣያ እንደነበር ያስታውሳሉ፡
“እንደዚያ ቆሻሻ የነበረ አካባቢ እንዲህ ተለውጦ፣ ህይወት ዘርቶ እናየዋለን ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ በዓይናችን የተመለከትነው ልማት ለትውልድ የሚተላለፍ ነው“ ሲሉ አስተያየታቸውን  ገልጸዋል፡፡
አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ሲናገሩም፤ ”በአቃቂ ክፍለከተማ አዲስ መኖሪያ  ቤት ተሰጥቶኝ  በደስታ እየኖርኩ ነው“ ብለዋል፤ አቶ ግርማ፡፡   
ለመልሶ ማልማቱ ከፒያሳ ተነስተው  ቃሊቲ አካባቢ መኖሪያ ቤት የተሰጣቸው አቶ ሸቢር አብደላ ደግሞ  በፒያሳ አካባቢ ያዩትን ለውጥ ከቀድሞው ጋር እያነጻጸሩ  በዝርዝር ገልጸውልናል፡፡  
”እኛ ከዚህ ለቅቀን ስንሄድ እንደዚህ አልነበረም፡፡ ያኔ አካባቢው ያስፈራ ነበር--ጨለማ ነው---በነጻነት የምትሄድበት ቦታ አልነበረም ---ቤቶች አሰራራቸው ወጥ አይደለም---ሁሉነገሩ ጭልምልም ያለ ነበር፡፡“ ይላሉ፤ የቀድሞ የፒያሳ አካባቢ ገጽታን ሲያስታውሱ፡፡
አሁንስ? አቶ ሸቢር አሁን ያስተዋሉትን ለውጥ እንዲህ ይገልጹታል፡-
“አሁን ቤቶችና ህንጻዎች እየታደሱ  ነው---ዛፎቹ በጣም ያምራሉ---ጽዶችና አበቦች ተተክለዋል---የእግረኛው መንገድ ሰፍቷል---ብስክሌቶች የሚሄዱበት መንገድ ለብቻው ተሰርቷል---ለሞተር ብስክሌቶች እንዲሁ መንገድ ተሰርቶላቸዋል---አሁን ሁሉ ነገር ጽድት ብሏል---መብራቱ ራሱ ኩልል ብሎ መርፌ ቢወድቅ እንኳን የሚታይበት ሆኗል፡፡”
በጉብኝታችን ያየነው የልማት ሥራ  በእጅጉ የሚያስደንቅና የሚያስደስት ነው ያሉት አቶ ሸቢር አብደላ፤ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎችም እንደዚሁ ለምተው ለማየት ጉጉት እንዳላቸው  ተናግረዋል፡፡
 ይሄ ጉጉት የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች  ጉጉት ነው፡፡ ሁሉም አካባቢው እንዲጸዳና እንዲዋብ ይፈልጋል፡፡ሁሉም ኑሮው እንዲሻሻልና እንዲዘምን ይመኛል፡፡ ሁሉም አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ አበባ እንድትሆን ይሻል፡፡ ደሞም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እንኳን አዲስ አበባ መላዋ ኢትዮጵያ መልማቷ አይቀሬ ነው፡፡


Read 1191 times