ጊዜያዊ አስተዳደሩ እርምጃ ባለውሰድ ተወቅሷል
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ አራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በትግራይ ሴቶች ላይ የሚደርሱ የፆታ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲገቱና የመፍትሔ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል። ፓርቲዎቹ ባለፈው ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. መቐለ ከተማ በሚገኘው የሳልሳይ ወያነ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በሰጡት የጋራ መግለጫ፤ በክልሉ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች መነሻቸው ሥርዓተ አልበኝነት ነው ብለዋል።
ጋዜጣዊ መግለጫውን በጋራ የሰጡት አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ ሳልሳይ ወያነ፣ ባይቶና እና የትግራይ ነጻነት ፓርቲ (ውናት) ናቸው።
“ትግራይ በአሁኑ ሰዓት የመንግስት አልባነት ሁኔታ ገጥሟታል ያሉት የአረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አምዶም ገብረስላሴ፤ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ እገታዎች፣ ግድያዎችና ጾታዊ ጥቃቶች የተበራከቱበትን ምክንያት ዘርዝረዋል።
እገታ እንደ አንድ የገቢ ማግኛ ዘዴ ማገልገሉ አንደኛው ምክንያት መሆኑን ያነሱት አቶ አምዶም፤ በዚህም የተነሳ የወንጀል ድርጊቱን ለመፈጸም የተደራጁ ቡድኖች፣ ታዳጊና ወጣት ሴቶችን በማገት ረብጣ ብር እንደሚጠይቁ ተናግረዋል። “እነዚህ ቡድኖች በክልሉ የፖሊስ ኮሚሽነሮችና ሌሎች ባለስልጣናት ከለላ እየተሰጣቸው ወንጀሉን ይፈጽማሉ፤ ፍትሕ ስለማይሰጥ ተጎጂዎች ስጋት ውስጥ ይገባሉ” ሲሉም ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡
የባይቶና ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ክብሮም በርሄ በበኩላቸው፤ “በጠቅላላ ከሕግና ስርዓት ውጪ የሆኑ አሰቃቂ ድርጊቶችን በሴቶች ላይ የሚፈጽሙ ሃይሎች ተፈጥረዋል። እነዚህ ሃይሎች ደግሞ ህወሓት ያደራጃቸው ቡድኖች ናቸው። ስለዚህም እኒህን ቡድኖች ለማውገዝ ነው ጋዜጣዊ መግለጫው የተጠራው” ብለዋል።
አክለውም ሲያስረዱ፤ “የወንጀል ድርጊቶቹ ከፖሊስ ምክትል ኮሚሽነሩ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ፖሊስ ክስ አቅርቦ፣ እንዳይመረምር ተደርጓል። ምክንያቱም ከእነዚህ የወንጀል ድርጊቶች መካከል አንደኛውን የፈጸመው የምክትል ኮሚሽነሩ ልጅ ነው። በአጠቃላይ በህወሓት ተመርጠው፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሾሙ ሃላፊዎችም በጉዳዩ ተሳታፊ ናቸው።” በማለት ከስሰዋል፡፡ ፡
የሴቶች ተገድዶ መደፈርና መገደል የአራቱም ፓርቲዎች “ቀይ መስመር” መሆኑን የገለጹት አቶ ክብሮም፤ የፓርቲዎቹ ዓላማ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ለመብታቸው እንዲቆሙ መቀስቀስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ከወንጀል ድርጊቶቹ ጋር በተያያዘ የታሰሩት ዋናዎቹ ሳይሆኑ ሌሎች ሰዎች ናቸው። ነገሩ የይስሙላ ነው። ባደረግነው ጥናት መሰረት፤ ይሄ ተራ ሰዎች የሚፈጽሙት ወንጀል አይደለም። ታጋቾቹን ሆቴል ውስጥ በማስቀመጥ፣ ከታጋች ቤተሰቦች ጋር የዋጋ ድርድር ይደረጋል። ከዛም ብሩ ወደ አጋቾቹ አካውንት ይገባል። ካልሆነ ደግሞ ትኬትና መታወቂያ ለታጋቾቹ ተዘጋጅቶ ወደ አዲስ አበባ ይላካሉ” ሲሉ የወንጀል ድርጊቱ ሂደት ምን እንደሚመስል በጥቂቱ አብራርተዋል፤ አቶ ክብሮም።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ “የስርዓተ አልበኞች አስተዳደር ሆኗል” ሲሉ የወቀሱት አቶ ክብሮም፤ “ህወሓት ፖለቲካው አልሆንለት ሲለው ክልሉን ወደ ማመስ፣ ወደ መዝረፍና የወንጀል ቡድኖችን ወደ ማደራጀት ገብቷል፡፡” ብለዋል።
የፓርቲዎቹ የወደፊት ዕቅድ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት፣ ጉዳዩ የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ መስራት መሆኑን የባይቶና ሊቀ መንበር ጠቁመዋል፤ በፆታዊ ጥቃት ዙሪያ ሌሎች እንቅስቃሴዎችንም እንደሚያደርጉ በማከል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች፤ “መንግስት ጸጥታን ያስከብር”፣ “ፍትህ ለትግራይ ሴቶች”፣ “ፆታ ተኮር ጥቃት ይቁም” በማለት የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡ በቅርቡ ታፍነው የተወሰዱና የተገደሉ ሁለት እንስት የጥቃት ሰለባዎችን ስም በመጥራትም፣ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ከችግሩ ጋር በተያያዘ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እርምጃ ለመውሰድ ቸልተኝነት አሳይቷል ሲሉም ወቅሰዋል።
ለሴት ሰልፈኞቹ ምላሽ የሰጡት፣ የትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሓዱሽ ተስፋ፤ በክልሉ በተለይ በሴቶች ላይ አሰቃቂና በጭካኔ የተሞሉ ያልተለመዱ ጥቃቶች መበራከታቸውን ገልፀው መንግስት ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
Published in
ዜና