ከእለታት አንድ ቀን፣ አንዲት ወፍ፣ አንድ ባህር አጠገብ፣ ጎጆዋን መስራት ትፈልጋለች፡፡ ጥሩ ቦታ ስትፈልግ ቆይታ በገደል አፋፍ ላይ አንድ ጥላ ያለው ጎድጎድ ያለ ቦታ ታገኛለች፡፡ እዚህ ቦታ ጎጆዬን ብሰራ በደንብ የተከለለና ከአደጋ የተሰወረ ይሆናል ብሎ ወሰነች፡፡ ሳርም፣ ቄጤማም አምጥታ ጎጆዋን አሳምራ ሰራች፡፡ እሷ ጎጆዋን ስታሳምር ባህሩ በፀጥታ፣ ቀስ በቀስ ዳርቻውን አልፎ ወደ ገደሉ አፋፍ እየመጣ ነበር፡፡ ወደ ገደሉ ደርሶ ከጠርዙ ጋር እየተላተመ መመለስ ጀመረ፡፡ ውሎ አድሮም ወፏ ጎጆ ጋ ደረሰና፣ ጥርግርግ አድርጎ ወሰደባት፡፡ ወፊቱ እየጮኸች ክንፏን እያራገበችና በንዴት እያጨበጨበች ወደ ሰማይ በረረች፡፡ ከላይ ሆናም ጎጆዋ ባህር ውስጥ ገብቶ ሲፈራርስ ተመለከተች፡፡
“እንዴት እንዲህ ትደፍረኛለህ? እንዴት ዋናውን መቀመጫ ቤቴን ታፈርሳለህ? ስገነባው አላየህም? ምን ያህል ጊዜና ጉልበት እንደወሰደብኝስ ሳታውቅ ቀርተህ ነው?” እያለች ጮኸች፡፡
ሆኖም ባህሩ ምንም መልስ አልሰጣትም፡፡ እንደተለመደው ገደሉ አፋፍ ድረስ እየመጣ ተመልሶ ወደ ቦታው ይመለሳል፡፡ ወፊቱም “ቆይ ሳልሰራልህ ብቀር!” ብላ ከበረረችበት ወደ መሬት ወርዳ፣ በኩምቢዋ ጥቂት ውሃ ጨልፋ ወስዳ፣ ሜዳው ሳር ላይ ትተፋለች፡፡ እንደገናም ትመጣና ሌላ ውሃ ጨልፋ ትወስዳለች፣ እሳሩ ላይም ትደፋለች፡፡ “በዚህ ሁኔታ ቀኑን ሙሉ እየተመላለስኩ ውሃውን ብወስድበት ባዶ አደርገዋለሁ” ብላ አስባ ነው፡፡ ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደከማት፡፡ ውሃውን መጨለፏን ግን አላቋረጠችም፡፡ ምክንያቱም እበቀለዋለሁ ብላ ቆርጣ ተነስታለችና ነው፡፡ ያልተገነዘበችው ነገር ቢኖር ምንም ያህል ውሃ እየቀዳች ብትወስድ፣ ባህሩን ልታጎድለው አለመቻሏን ነው፡፡ ውሃ እንደቀድሞው እየመጣ ማዕበሉም ከዳርቻው ጋር በሃይል እየተላተመ ይመለሳል፡፡ ወፏ ወደ ሞት እስከምትቃረብ ድረስ ለፍታ ለፍታ ደከማትና፣ አንድ ቋጥኝ ላይ ተቀምጣ አረፍ እንዳለች፣ አንድ ሌላ ትልቅ ወፍ ወደ እሷ ይመጣል፡፡ መጤው ወፍም፤ “ወፊት ሆይ! እስካሁን ስትሰሪ የነበረውን ነገር ሁሉ ራቅ ብዬ ስመለከት ነበር፡፡ ምን ለማድረግ እየሞከርሽ እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ ግን አንድ ምክር እንድሰጥሽ ትፈቅጂልኛሽ?” አላት፡፡ የደከማት ወፍ መልስ ለመስጠት እንኳን አቅም አልነበራትም፡፡ ስለዚህም እንግዳው ወፍ ቀጠለ፡፡ “በቀል የደካማ በትር ነው፡፡ አቅምሽን ሁሉ በበቀል ላይ መጨረስ አያዋጣሽም፡፡ ራስሽን ተመልከቺ፡፡ ከጊዜ ጊዜ እየደቀቅሽ፣ እየተመናመንሽ እየሄድሽ ነው፡፡ ምን ተጠቀምሽ? ባህሩ እንደሆን ምንጊዜም ባህር ነው፡፡ ምንጊዜም ውሃ አለው፡፡ ምንጊዜም እንደሞላ ነው፡፡ ምን ጊዜም ጠንካራ ነው፡፡ ስለሆነም ልበቀለው ብለሽ የፈለግሽውን ያህል ብትፍጨረጨሪ ከንቱ ድካም ነው፡፡ ይልቅ አቅምና ጉልበትሽን በሚጠቅም ነገር ላይ አውይው፡፡ አስቢበት፡፡” ብሏት በረረ፡፡ ወፊቱ ቋጥኙ ላይ ተቀምጣ ድካሟን እያስታመመች ብዙ ካሰበች በኋላ፣ ቀጥሎ የምትሰራውን ወሰነች፡፡ ከዚያ ተነስታ ከባህሩ ዳርቻ ራቅ ብሎ፣ ለጎጆ መስሪያ አመቺ ቦታ መረጠች፡፡ ሳርና ቅጠል እየሰበሰበች እንደገና አዋቅራ አዲስ ጎጆ ሰራች፡፡ ቀጥላም፤ “እንግዳው ወፍ የነገረኝ እውነት ነው፡፡ አቅምና ጉልበቴን ጠቃሚ ነገር ላይ ባውለው ይሻላል፡፡ በቀል የደካማ በትር ነው፡፡ ትላንት የሰራሁትን ስህተት እንዳይ ያደርገኛል” አለች፡፡
***
በቀል በማንኛውም መልኩ ቢሆን የጥፋት ዝርያ ነው፡፡ ከማይቋቋሙት ባላጋራ ጋር መቀያየም፣ አልፎም ለበቀል መነሳት ትርፉ ፀፀት ነው፡፡ ጨልፈው የማይጨርሱትን ባህር ቀድቼ ባዶ አደርገዋለሁ ብሎ ማሰብ ከንቱ ቅዥት ነው፡፡ በቀል ለትውልድ ቂም ማኖር እንጂ የሀገርን አብራክ አያለመልምም፡፡ የህዝቧንም ተቀራርቦ ተስማምቶና ተቻችሎ የመኖር ተስፋ አይጠቁምም፡፡ ይልቁንም አድሮ ይቆጠቁጣል፡፡ የእንግሊዙ ገጣሚና ደራሲ ጆን ሚልተን ይህንኑ በግጥም ሲገልጽ፣ “ምን መጀመሪያ ቢጣፍጥ፣ በቀልም እንደማር ቢጥምም፣ ብዙ ሳይቆይ መምረሩ አይቀር፣ ዞሮ በራስ ሲጠመጠም፡፡” እንዳለው ሁሉ፣ ዛሬ በሌላው የምንወስደው እርምጃ፣ ነገ በእኛው ላይ የሚያነጣጥር በቀል-መላሽ ትውልድ እንደ መፈልፈል ነው፡፡ የሀገራችን እውቅ ገጣሚ መንግሥቱ ለማ፤ “… ማን ያውቃል እንዳለው ለድንጋይስ ቋንቋ፣ ዛፍ ለሚቆረጥ ዛፍ፣ እንዳለው ጠበቃ…” ያሉትም የዚሁ የበቀል መንፈስ ሌላው ገፅታ ምን እንደሆነ ሲጠቁሙ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲ፣ በድርጅት፣ በማህበር፣ በመስሪያ ቤት፣ በግለሰብ ወዘተ ላይ ወይም መካከል የሚደረግ የበቀል እንቅስቃሴ፣ “በቀልን የመረጠ የራሱን ቁስል እንዳስመረቀዘ ይኖራል” እንዳለው ፍራንሲስ ቤከን፣ ነገ የሚያቆጠቁጥና የሚቆጠቁጥ የትውልድ ህመም፤ ታሪካዊ ተውሳክ መትከል ነው፡፡ መቼም ይፈፀም መቼ፣ ማንም ይፈፅመው ማን ህዝብ ባህር ነው፡፡ የበቀል እርምጃ ሲወሰድ ዞሮ ዞሮ ህዝቡ የሀገሩ ባለቤት ነውና፣ በትዝብት ዐይን አስተውሎ በታሪክ ማህደር ጽፎ፣ አጥፊውን መጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡ ኢፍትሐዊም ነውና በህግ መሟገቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ነፃነቴ ተነካ ሲል ሰብዓዊ መብቱ፣ መብቴ ተደፈረ ሲል ለዲሞክራሲያዊ መብቱ መቆሙ አይቀርም፡፡ ከቶውንም በየጊዜው የሚነገሩም ሆነ የሚተገበሩ የህግ የበላይነት አከባበር፣ አፈርሳታ፣ አውጫጪኝ፣ አዲስ አወቃቀር፣ ተሐድሶ፣ አዲስ አደረጃጀት ምልመላ፣ አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን፣ አሮጌ ሰው በአዲስ ጠበል ወዘተ… እያልን ላይ ታች የምንልባቸው ጉዳዮች፣ ልባችን ውስጥ የበቀል ቋጠሮ ቋጥረን፣ “ቆይ ሳልሰራልህ ብቀር” “ረዥም እረፍት ሳላስወስድህ ብቀር” እያልን ከሆነ፣ ተጫውቶ ተጫውቶ ቁር ሲሉ፤ “ፉርሽ ትሉኝ” ብሎ ከመጀመሪያው የገበጣ ቤት እንደ መጀመር ይሆናል፡፡ የፈሰሰ ንዋይ፣ የባከነ የስው አዕምሮ፣ የባከነ ጊዜ… የሀገር ሀብት መሆኑን መዘንጋት በታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ያ ሳያንስ ጥፋተኛ ለመፈለግ በወገናዊ መንገድ መሄድና እሱንም በበቀል ቀመር ለማከናወን መጣር፣ ለሀገርና ለህዝብ ጥፋት መደገስ ይሆናል፡፡ ከቶውንም ፓርቲና ፓርቲ፣ የፖለቲካ ድርጅትና የፖለቲካ ድርጀት፣ አለቃና አለቃ፣ አለቃና ምንዝር ለመበቃቀል እቅድ ይዘው ስለመድብለ ፓርቲ፣ ድህነትን ስለመቀነስ ቢያወሩ፣ የትም ፈቀቅ ማለት አይቻልም፡፡
ወደ መተሳሰብ፣ ወደ መወያየት፣ ችግርን ከሀገር አንፃር ወደ መፍታት ሳይጓዙ ክፉ ክፉውን ወደ ማየት መጓዝ፣ ወደ ትንኮሳና አምባጓሮ ማምራት ለእድገት አያበቃም፡፡ ይልቁንም “ለመራመድ ያቃተው እግር፣ ለመርገጥ ሲሉት ይነሳል” እንደሚባለው ይሆናል፡፡