Saturday, 29 June 2024 19:58

በሰው ላብ የመክበር ጥበብ!

Written by  በደረጄ ጥጉ (የአለም አቀፍ ህግ መምህር)
Rate this item
(2 votes)

 ስልጣን እንዴት ይያዛል? እንዴትስ ይታጣል?
                                 

        የሮበርት ግሪን መፅሐፍ(The 48 laws of power)) ሀሳብ ቀስቃሽና ጠንካራ ህግጋትን የያዘ ድንቅ ሰነድ ነው፡፡ ደራሲው በመፅሐፉ ህግጋቱን ለማስረዳት  ያሰፈራቸው አስረጅ ምሳሌዎች ከታሪክ፤ ከፖለቲካ፤ ከጦርነት ገጠመኞችና የንግድ አለም እውነቶች የተቀዱ ናቸው፡፡ ህግጋቱን ተጨባጭና እውነታዊ ናቸው የሚያስብላቸውም አንዱ መነሻ ይህ ነው፡፡ በታሪክ ሂደት በበቂ ተፈትነው ያለፉ ናቸው፡፡ ሮበርት ግሪን ህግጋቱን ያብራራበት እያንዳንዱ ምሳሌ፣ በታላላቅ ሰዎች ስኬት ወይም ውድቀት ላይ መነሻውን በማድረግ አንባቢ መውሰድ የሚገባውን ትምህርት እንካችሁ ይለናል፡፡ በጥልቀት ላነበበ አንባቢም ተለዋዋጩን የአለም ፖለቲካ እንዲቀዝፍበትና በተጨባጭ እንዲገነዘበው ያስችለዋል፡፡ አንዳንዶች አፃፃፉና ስልጣንን ለመቆናጠጥ ያስፈልጋሉ ብሎ ያሰፈራቸው ስልቶች “ማኪቬላዊ” ናቸው እያሉ ትችት ቢያወርዱበትም፣ መፅሐፉ ግን የህይወትን ጨዋታዎች በቅርበት እንድንረዳ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ መፅሐፉ ውስጥ ስብከት ሳይሆን ተጨባጭ ትምህርትን ነው የምናገኘው፤ በዚህም ምክንያት ከማወቅም በላይ የመረዳታ አቅማችንንም ከፍ ያደርግልናል፡፡
እርግጠኛ አመክኖአዊ ተዋረድን የተከተሉ እስከሆነ ድረስ ህግጋቱ በህይወት ላይ እንድናውጠነጥን፣ አልፎም ከውስጣችን ጋር እንድናዋህዳቸው ያደርጉናል፡፡ በመፅሐፉ ውስጥ ያሉት ህግጋት ተጨባጭና ተግባራዊ ናቸው የሚያስብላቸው ሌላው ምክንያት፣ መፅሐፉ የሞራል ፍርድን ሳይሆን፣ ተለዋዋጭ የሆነውን የስልጣንና የፖለቲካ  ባህሪ በማሳየቱ ነው፡፡ የፖለቲካው አለም ህግ ከቢሆን ህግ ውጪ አንዳንዴም ተቃራኒ ሆኖ ይገኛል፡፡ ስልጣን እንዴት ይያዛል? እንዴትስ ይታጣል? የሚለውን በደንብ ያሳየናል፡፡ መንገዴ በፖለቲካው ጎዳና ነው ያለ ሊያነበው የሚገባ መፅሐፍ ነው፡፡
ሮበርት ግሪን በታላላቅ ሰዎች ተሞክሮ ላይ ጥናት አድርጎ የደረሰበትን ድምዳሜ ድንቅ በሆነ መልኩ አስፍሮታል፡፡ ህግጋቱ በእውኑ አለም ትላንትና ዛሬ ላይ እውን ሆነው ያለፉና ነገም ላይ እውነት ሆነው የሚቀጥሉ ናቸው፡፡ ዘመንና ጊዜን ተሻጋሪ ናቸው፡፡ መፅሐፉ በፖለቲካ አጥር ውስጥ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ በተለያዩ የህይወት ፈርጆች ላይ ሊተገበሩ የሚችሉ መርሆዎችን አቅፎ ይዟል፡፡ ድንበር ዘለል ነው፡፡ መፅሐፉን በደንብ ላነበበው ሁኔታዎችን መገንዘብና ተለዋዋጭ ባህሪን መላበስ ተገቢ እንደሆነ ይረዳል፡፡ እያንዳንዱ ህግ ግልጥና እጥር ባለ መልኩ ቀርቧል፡፡ የመፅሐፉ አንድ ጠንካራ ጎንም ይህ ነው፡፡ ባልተንዛዛና ውብ በሆነ መልኩ ቀርቧል፡፡ አንዳንዱ ህግ አሻሚና አወዛጋቢ ቢመስልም  በገሃዱ አለም  ግን እውነት ነው፡፡
በመጨረሻም መፅሐፉ አውዳሽም ነቃፊም አለው፡፡ ስልጣንን በእጃቸው ማስገባት ለሚሹ መፅሐፉ ጠቃሚ ሰነድ ሲሆን፤ ነቃፊዎቹ ደግም ብዝበዛንና ኢ-ስነምግባራዊ ባህሪን ያበረታታል ሲሉ ይነቅፉታል፡፡ ህግጋቱን በጥልቀት ለመረመራቸውና ለተረዳቸው ግን  ስልጣንን ለመያዝና ለመተግበር የሚጠቅሙ ናቸው፡፡


በሌሎች ሰዎች ጥበብ፤ እውቀትና የላብ ወዝ (ድካም) የመጠቀም ጥበብን ተማር ይለናል፤ ሮበርት ግሪን በ7ኛው የስልጣን ህጉ፡፡ እንዲህ ማድረግ ከቻልክ ከአላስፈላጊ ድካም እራስህን ትጠብቃለህ፡፡ ውድና መተኪያ የሌለውን ጊዜና አቅምህን በአግባቡ ትጠቀምበታለህ፡፡ በእውኑ አለም እንደሚታየው በሰዎች ድካም ተጠቅመው ላስመዘገቡት ውጤት፣ የውጤቱ ባለቤት እነሱ የሆኑ እስኪመስሉ ድረስ ዝንተአለም በታሪክ ሲታወሱ፣ የጉዳዩ ባለቤቶች (ስራውን የሰሩት) ግን እስከመፈጠራቸው የሚያስታውሳቸው የለም፡፡ አለም እንደዚህ ናት፡፡ ሌሊሳ  ግርማ “አፍሮጋዳ” በተሰኘው መፅሐፉ እንዳለው፤ አንዲ ዎርሆል ምትክ የሌላትን ሞናሊዛ ሊሰራ ስላልቻለ ከአንድ ሞናሊዛ መቶ ይሻላል ብሎ ሞናሊዛን እንደ ፋብሪካ ምርት ብዙ አድርጎ ኮፒ አድርጎ ስራውን ጥበብ ብሎ ጠራው፡፡ ታዋቂም ሆነበት፡፡ በዳቪንቺ ድካም አንዲ ዎርሆል ከበረበት፤ ዝነኛም ሆነበት፡፡ የትልልቆችን ሀሳብ መንጠቅ፤ በሱም መበልፀግና ዝናን መቀዳጀት የዚህ የ7ኛው ህግ መሰረታዊ አስኳል ነው፡፡ ዝናን መላበስ ዝናውን ካስገኘው ውጤት በላይ ነው ብሎ ማሰብ፡፡ ከአንድ ትልቅ ግኝት ጀርባ ብዙ ላብ ፤ ጊዜ ፤ እውቀት የፈሰሰ መሆኑ እሙን ቢሆንም፣ ዝናውንና ክብሩን ጠቅልሉ የሚይዘው ግን ውጤቱን የሚያስተዋውቀው (ዘራፊው) ነው፤ አልያም ለህዝብ እንዲስማማ አድርጎ አለዝቦ የሚያቀርበው ነው፡፡ ደማቁን ማቅጠንና ለሁለም ማዳረስ ይለዋል፤ ሌሊሳ ግርማ፡፡ ትላንት እንደዚያ ነበር፤ ዛሬም እንደዚህ ነው፤ ነገም እንደዚያ ይሆናል፡፡ የካፒታሊዚም አንዱ መልክ ይህ ነው፡፡ የምርት ባለቤቱ ለምርቱ እውን መሆን የሚያስፈልግ እውቀት ፤ ጉልበት ይገዛል ወይም ይቀጥራል፡፡ ጉልበትና እውቀትን በገንዘብ ይገዛል፡፡ የእውቀቱንና የጉልበቱን ውጤት እሱ ያተርፍበታል፡፡ ከምርቱ የሚገኘውን ትርፉን አምራቾቹ (የአውቀቱና የጉልበቱ ባለቤቶች) ሳይሆኑ የምርቱ ባለቤት (ቀጣሪው) ይወስደዋል፡፡ ውጤቱን ያመጡት ተቀጣሪዎቹ (የጉልበት ወይም የአእምሮ) ቢሆኑም፤ የምርቱ ትርፍ ብቸኛ ተጠቃሚ ግን ባለሃብቱ ነው፡፡ በሰው ላብ መክበር ማለት በአጭሩ ይህ ነው፡፡ ካፒታሊስቱ ሌሎች ሊሰሩልህ የሚችሉትን አንት ምን በወጣህ ትሞክረዋለህ እያለ ያፌዛል፡፡


በ1883 ለ European continental division ድርጅት ተቀጥሮ የሚሰራ ኒኮላስ ቴስላ የሚባል ወጣት ሰርቢያዊ ነበር፡፡ ቴስላ ጎበዝ የፈጠራ ሰው ነው፡፡ ቴስላ ጎበዝና ምጡቅ አእምሮን የታደለና አሁን ያለንበትን የዘመናዊ አለም የኤሌክትሪክ ሀይልና የግንኙነት መንገዶች የፈጠረ ሰው ነው፡፡ አለም አሁን የደረሰበት የስልክም ሆነ ሌሎች የገመድ አልባ ግንኙነት መንገዶች አብዛኛዎቹ የቴስላ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው፡፡ ምናበ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ስራዎቹን በወረቀት ንድፍ ሳይሆን የሚያስቀምጣቸው፣ በአእምሮው በስእል መልክ ይቀርፃቸዋል፡፡ ገመድ አልባ  የግንኙነት መንገድንና የድምፅ ማስተላለፊያ  ሞገዶችን ለመስራት አመታትን ደክሟል፡፡ ደክሞም  አልቀረም፤በመጨረሻ እውን አደረጋቸው፡፡ ስልክ፤ ቴሌቪዝንና የተንቀሳቃሽ ምስል የእሱ የአእምሮ ውጤቶች ናቸው፡፡ መጪውን ዘመን ቀድሞ ተመልካች የነበረው ቴስላ፤ የ20ኛ ክፍለ ዘመን ታላላቅ ውጤቶች የሆኑትን ስልክ ፤ቴሌቪዥንና ሬድዮንን ለአለም አስተዋውቋል፡፡ የፈጠራ ስራውን ሀ ብሎ የጀመረበት  ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የነበረው ቻርለስ ባችለር(Charles Batchelor) ነው፡፡ ባችለር  የቶማስ ኤድሰን የግል ወዳጅ ነበር፡፡ ኤዲሰን የዘመኑ ሌላኛው ገናና የፈጠራ ሰው ተብሎ የሚታመን ነበር፡፡ ባችለር አብሮ በመዋል እንደተረዳው፣ ቴስላ ታላቅ የፈጠራ ሰው መሆኑን ነው፡፡ ባችለር ቴስላ ታላቅ የፈጠራ ሰው መሆኑን ስለተረዳ የወደፊት ህይወቱን እጣፋንታ  ወደ አሜሪካ ሄዶ ከኤዲሰን ጋር እንዲሞክር አሳሳበው፡፡ ጉብዝናውንና የፈጠራ አቅሙን የሚገልፅ  ደብዳቤን አስይዞ ወደ ኤዲሰን ላከው፡፡ የቴስላ ፈተናዎች የበዙበትና በሃዘን የተሞላው ህይወቱ ከዚህ ይጀምራል፡፡


ቴስላ አሜሪካን ሄዶ ኤዲሰንን በሚኖርበት ከተማ ተገናኘው፡፡ ወዲያውም በኤዲሰን ድርጅት ተቀጠረ፡፡ የወጣቱ ቴስላ ህልም የነበረው ዘገምተኛና ኋላቀር የነበረውን  የኤዲሰን power dynamos ማሻሻል ነበር፡፡ ይህን መስራት እንደሚፈልግና እውን እንደሚያደርገውም ለኤዲሰን አወያዋየው፡፡ ኤዲሰን እሺ  በርታ አለው፡፡ ይህን መስራት ማለት አንድ ታላቅ የፈጠራ ሀውልት የማቆም ያህል ነው፡፡ ይህንን መስራት ከቻለ 50000 ዶላር ጭምር እንደሚሰጠው ኤዲሰን ለቴስላ ነገረው፡፡ ቴስላ ቀን ከሌት በመስራት አዲሱን ግኝት በዛው አመት መጨረሻ አካባቢ ጥንቅቅ አድርጎ ጨረሰው፡፡ DC( Direct current) ወደ AC(Altenating current) ቀየረው፡፡ ቴክኖሎጂውን ብቻ ሳይሆን አለምንም ጭምር ነበር የቀየረው፡፡ አለምን ከኋላ ቀሩ ወደ ዘመነው የኤሌክትሪክ ሲስተም ነበር ቴስላ  ያሸጋገረው፡፡
ቴስላ ግኝቱን እውን ካደረገ በኋላ ዜናውን ለማብሰርና በዛውም ቃል የተገባለትን 50000 ዶላር ለመቀበል ወደ ኤዲሰን አመራ፡፡ ኤዲሰን ተገረመ፡፡ እሱም ድርጅቱም የፈጠራው ተቋዳሽ ይሆናሉ፡፡ 50000 ዶላሩን በተመለከት ግን የአሜሪካኖችን የዋዛ ጨዋታ ገና አለመድከውም ሲል አፌዘበት፡፡ አሜሪካዊ ስትሆን እንዲህ አይነቱን የዋዛ ጨዋታ ትላመደዋለህ አለው፡፡ ለድካሙ የተወሰነ ገንዘብ ብቻ ሰጠው፡፡ ኤዲሰን ከግኝቱ ጀርባ ያለውን ገንዘብ ሲያስብ፣ የቴስላ ብቸኛ ህልም የነበረው የኤዲሰንን ዘገምተኛ DC ወደ AC ማዘመን  ነበር፡፡ ምርምሩን ሲያከናውን ኤዲሰን አይደለም በገንዘብ ሊያግዘው  ከጀርባ ሆኖ እቅዱን ለማክሸፍ ሲያሴር ነበር፡፡ በቴክኖሎጂው አለም “war of currents” የተባለው ግብግብ የጀመረው በዚህን ግዜ ነው፡፡ ያ ዘመን የሁለቱ የፈጠራ ሰዎች የፍልሚያ ሜዳ ነበር፡፡የተሻለው የማነው በሚለው ጉዳይ የጋለ ውይይት ከተደረገባቸው የሳይንስ አለም ወቅትች አንዱ የነዚህ ሁለት ሰዎች ነበር፡፡ ኤዲሰን አዲሱ ግኝት እክል የሞላበትና ለአደጋም የተጋለጠ ነው በማለት አጣጣለው፡፡ ለጊዜው እውነት ቢመስልም በሂደት ግን አለም የቴስላን ግኝት ምርጡ ብሎ ተቀበለው፡፡ ቴስላ ከእሱ ጋር አብሮ በነበረበት ጊዜ፣ ኤዲሰን ጉልበቱን ከመጠቀሙም በላይ ፈጠራዎቹንና  የፈጠራ ሀሳቦቹን ጭምርም እንደዘረፈው  ተፅፏል፡፡
ቴስላ ወደ ቀጣይ መዳረሻው ፊቱን አዞረ፡፡ pitsburgh magnate companyን ተቀላቀለ፡፡ የዚህ ድርጅቱ ባለቤት Westinghouse በፈቃደኝነት  ለቴስላ ጥናትና ምርምሩ የሚያስፈልገውን  ገንዘብ  አቀረበለት፡፡ አያይዞም ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚያስገኝለትን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ቴስላ ለአለም ያበረከተው የ AC ግኝት የዘመናችን የመጨረሻው ግኝት ነው፡፡ ይህን ታላቅ ግኝት ለዚህ ድርጅት ሸጠው፡፡ የፈጠራ ግኝቱን በስሙ ካስመዘገበ በኋላ ለእኔ ነው የሚገባኝ የሚሉ ድምፆች ተበራከቱ፡፡ ግኝቱ የእሱ መሆኑን ባይክዱም  ለእሱ የፈጠራ ግኝት መሰረት የጣሉት ግን እነሱ እንደሆኑ ሽንጣቸውን ገትረው ተከራከሩ፡፡ በዚህ ለእኛ ነው የሚገባን ጫጫታ መሀል የቴስላ ስም ጭራሹን ጠፋ፡፡ የAC ፈጠራንም ተቀጥሮ ከሚሰራበት ድርጅት ጋር እንጂ ከእሱ ጋር የሚያነሳው አልነበረም፡፡ ስራን ሳይሆን ስምን የመሸጥ አባዜ ይሉሃል ይህ ነው፡፡ የአፍሮጋዳዊ እንቅስቃሴ በአብዛኛው ከትልልቆቹ መንደርደሪያነት ተነስቶ የሚሰራ ነው የሚለው ሌሊሳ ግርማ፤ እንዲህ አይነቱን ቁጭ በሉ ነው፡፡
ከአንድ አመት በኋለ ይሰራበት የነበረው ድርጅት ባለቤት በብድር እዳ ተይዞ፣ የፋብሪካው ህልውና አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ በእዳ በመያዙም ከቴስላ ጋር ገብቶት የነበረው ውል እንዲሰረዝ ሆነ፡፡ የማጭበርበር ዘመን ስለነበር Westinghouse ድርጅቱን ለማትረፍ ውሉን ሰረዘ፡፡ ለቴስላም ሙሉ ክፍያውን የሚከፍለው ከሆነ ድርጅቱ ህልውና እንደማይኖረው ነገረውም፡፡ በትህትና 216000 ዶላር ብቻ እንዲቀበለው አደረገ፡፡ በዘመኑ ይህን ያል መጠን ያለው ገንዘብ ትልቅ  ቢመስልም፣ የቴስላ ፈጠራ ግን በጊዜው 12 ሚሊዮን ዶላር ሊያወጣ የሚችል ነበር፡፡ ጬሉሌ ሀብታሞች ቴስላን ከሚገባው ሀብት፤ የፈጠራ ባለቤትነትና ከድካሙ ዋጋ እንዳይጠቀም አደረጉት፡፡ ቴስላ ሀሳቡን ሸጠ፤ ነጋዴው የድርጅቱ ባለቤት ከበረበት፡፡ ጠቀም ያለ ገንዘብ አገኘበት፡፡ የሌሊሳ ግርማ የአፍሮጋዳዊ የማገንተር ዘመን በዛም ጊዜ ነበር ማለት ነው፡፡
ማርኮኒ የሚለውን ስም ሲነሳ ወደ ውስጣችን ቀድሞ የሚመጣው ራድዮ ነው፡፡ ለብዙሃኑ የራድዮ ፈጣሪ በመባል የሚታወቀው ማርኮኒ ነው፡፡ ማርኮኒ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1899 በእንግሊዝ የስርጭት ሞገዶች ሙከራውን እውን አደረገ፡፡  የፈጠራ ባለቤትነቱም በራሱ ስም አስመዘገበ፡፡ ይህ ቢሆንም  ቴስላ በ1897 በስሙ ያስመዘገበውን ፈጠራ ነበር፣ ማርኮኒ ለአዲሱ ግኝት የተጠቀመው፡፡ የማርኮኒ ፈጠራ በቴስላ ግኝት ላይ የተመረኮዘ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ቴስላ ለሶስተኛ ጊዜ ገንዘብም እውቅናም ሳያገኝ ቀረ፡፡ ሃሳቡን ቢዘረፍም በእውነተኛው የሳይንሱ አለም ግን እውነተኛው የሬድዮ አባት በመባል የሚታወቀው ቴስላ ነው፡፡ የሚገርመውና የሚያሳዝነው ግን ሁሉም ፈጠራዎች የቴስላን ስም አልያዙም፡፡ ረዳት እንደሌለው ሽማግሌ ብቻውን በድህነት ኖረ፡፡ እዳውን እንኳን ሳይከፍል ነበር የሞተው፡፡
በጉዳት ላይ ስድብ እንዲሉ ቴስላ ለሳይንሱ አለም ላበረከተው የላቀ አሰተዋፅኦ የEdison medal of American institute for the genius ሽልማትን ሊሰጡት እንደሚፈልጉ የሳይንሱ አለም ሰዎች አስታወቁት፡፡ ቴስላ ሽልማቱን እንደማይቀበል ቀድሞ አሳወቀ፡፡ አያይዞም እንዲህ አለ፤ “ለአእምሮዬና የእእምሮዩ ውጤቶች ለሆኑት ፈጠራዎች እውቅናን በመንፈጋችሁ ለከፋ ችግር መዳረጋችሁ ሳያንስ ሜዳልያችሁን  በደረቴ  አንጠልጥዬ፣ ለማይረቡ ባዶ ሰአታት በእናንተ  ፊት መቆም አልፈልግም፡፡ ብታውቁት የስራ ፈጠራዎቼ ለእናንተ ተቋማት መሰረትን የጣሉ ነበሩ፡፡ ያለ እኔ ፈጠራዎች ተቋማቶቻችሁ ባልነበሩም ነበር”፡፡
ለብዙሃኑ የሳይንስ ትኩረቱ ተጨባጭ ነገር ላይ እስከሆነ ድረስ ከንትርክና ጭቅጭቅ ውጭ ይመስላቸዋል ይለናል፤ ሮበርት ግሪን፡፡ ንትርኩ ሌላውን ያውክ እንጂ የሳይንሱን አለም ሲያልፍም አይነካካው፡፡ ዋና ንጥቂያ ግን ያለው በሳይንሱንና በጥበቡ አለም ውስጥ ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ ሰለባ ከሆኑት መሃል አንዱ ቴስላ ነው፡፡ ለቴስላ ልክ እንደ ብዙሃኑ ሁሉ ሳይንስና ፖለቲካ ለየቅል ናቸው፡፡ ዝምድናም የላቸው፡፡ የፖለቲካውን ስልት የሚያውቁት እንደቀደሙት አላወቀም ነበርና፣ በፈጠራዎቹ ተጠቀሙበት፡፡ ዝና፤ ስም ገናና ሆኖ መታየት ለቴስላ ቁብም አልነበራቸው፡፡ ታላላቅ ውጥኖቹን ለኣለም ሲያስተዋውቅ ግን አጃቢውና ፈላጊው በዛ፡፡ ቴስላ የተንኮሉን አለም አውነት ስላልተረዳና ሁሉን ብቻውን እንደሚከውን በማመኑ፣ ለድህንትና ጉስቁልና ተዳረገ፡፡ የሰው ጅብና ጆፌ ከቦት ነበር፡፡
በዘመኑ የቴስላ ፍፁም ተቃራኒ የነበረው ኤዲሰን ነው፡፡ ስለእሱ በተፃፉ ፅሁፎች ውስጥ እንደምንረዳው ኤዲሰን ያን ያህል አሳቢና የፈጠራ ሰው አልነበረም፡፡ እራሱ ኤዲሰን በአንድ ወቅት እንደተናገረው፤ “ሰው ቀጥሮ ማሰራት  እስከቻለ ድረስ የሂሳብ ሰው መሆን እንደማይጠበቅበት”  ተናግሮ ነበር፡፡ ባህሪው የነጋዴ ተፈጥሮው ዝናን ናፋቂ ነበር፡፡ ከፊቱ ተሰልፈው የሚጠብቁትን እድሎችና ገፀ በረከቶች በመለየት እነሱን እውን ሊያደርጉለት የሚችሉትን ሰዎች ይቀጥራል፡፡ ይገባኛል ብሎ ካሰበ፣ የተቀናቃኞቹን ፈጠራ ከመስረቅ የማይመለስ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ድክመት ቢኖርበትም ከቴስላ በተሻለ ዝነኛና እውቁ ሰው እሱ ነበር፡፡ ከብዙ የፈጠራ ግኝቶች ጋር ስሙ በብዙ የሚነሳው ኤዲሰን እንጂ ቴስላ አይደለም፡፡ ኤዲሰን ሲሞት በስሙ 1091 ፈጠራዎች ተመዝግበዋል፡፡ የቴስላ ከ300 ያነሱ ነበር፡፡


ከላይ የሰፈረውን ሀሳብ ተከትለን ስንወርድ፣ ለፈጠራ የሚሰጠው ዋጋ ከፈጠራው በላይ ነው፤ ወይም የእሱን ያህል አስፈላጊ ነው ይለናል፤ሮበርት ግሪን፡፡ ከፈጠራው የሚገኘውን  ዳጎስ ያለ ዋጋ የራስህ አድርግ፡፡ ግሪን እንደሚለው፤ ፈጠራህንና የፈጠራ ሀሳብህን ሌሎች እንዳይነጥቁህ ነቅተህ ጠብቅ፡፡ ተቀናቃኖችህን ልትሰራ ካሰብከው መንገድህ አርቃቸው፡፡ የዋህና ገራገር አትሁን፡፡ ከሌሎች ሰዎች ውድቀት ተማር፡፡ ፈጠራህንና የፈጠራ ሃሳብህን ለራስህ ሰውረህ ያዝ፡፡ አለም በጆፌ አሞራዎች የተሞላች ነችና ጆፌ አሞራዎች በአቅራቢያህ አለመኖራቸውን እስክታረጋግጥ ድረስ ፈጠራህን ለራስህ ደብቀህ ያዝ፡፡ የሌሎችን ሰዎች ድካም በአግባቡ መጠቀምን ተረዳ፡፡ ህይወት አጭር ስትሆን ጊዜ ደግሞ እንደ እንቁ ውድ ናት፡፡ ይህን እውነት በደንብ ተረዳ ይለናል፤ ግሪን፡፡ ሁሉንም በራሴ እሰራለሁ ብለህ ካሰብክ፣ ጊዜ ህይወትህን እየገበርክ ነው፡፡ ስለዚህ አቅምህን አታባክን፡፡ በሌሎች ላብ ላይ ፊጥ ማለትን ተለማማድ፡፡ እንዲህ ካደረግክ የሌላው ድካም ውጤት  የአንተ ይሆናል፡፡ “በንግድ አለም ሁሉም ይሰርቃል፤ አዎ እኔም ብዙ ሰርቄያለሁ፡፡ ግን እንዴት እንደሚሰረቅ አሳምሬ አውቃለሁ” ብሎ ነበር፤ በአንድ ወቅት ኤዲሰን፡፡
በጫካው የእንስሳት አለም ህይወታቸውን በአደንና በመግደል የሚገፉ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በእነሱ ድካም የሚኖሩም አሉ፡፡ በሌላው ድካም ከሚኖሩት ውስጥ ጅብና ጆፌ አሞራ ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ እነዚህ እንስሳት ጊዜና ሀይላቸውን በማደን አያባክኑም፡፡ ሌሎች ለአደን እስኪወጡ ይጠብቃሉ፡፡ አደኑን ለሌሎች ይተዋሉ፡፡ ከአደኑ ግዳይ ራሳቸውን በሚገባ ይመግባሉ፡፡ በአንተ ድካም ምንም ሳይለፉ እንደ ጆፌና ጅብ ሊነጥቁህ ያቆበቆቡ እንዳሉ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ልክ እንደ ቴስላ የድካምህን ውጤት ከተነጠቅክ በኋላ ማዘን አይገባም፤ ምሬት መልበስም እንዲሁ፡፡ ተናጥቆ መኖር የሚባለውን የጨዋታ ህግ ተቀላቀል፡፡ ግሪን እንደሚለው፤ በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ መሆንህን ስታረጋግጥ፣ የጆፌ ሰለባ ከመሆን እራስህን ጆፌ አድርገህ ጠብቅ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን፤ ጅብ መጥራት የሚሉትን ሀሳብ  በመፅሐፋቸው አስፍረዋል፡፡ ይህን ሀሳብ ያስተዋወቃቸው የይፋት ገበሬ ነው፡፡ ይህ ገበሬ ከሚያርሰው መሬት ሌላ እንዳለው ስጠይቀው ሌላ ማሳም እንዳለው ነገረኝ፤ ይላሉ ፕሮፌሰር መስፍን፡፡  ለምን ያንንም እንደማያርሰው ስጠይቀው፣ እሱን ጨምሬ ባርሰው ጅብ ይጠራብኛል አለኝ ይላሉ፡፡ ምን ለማለት ነው፣ አለም በሙሉ የሰው ጅብ የበዛበት፣ ንጥቂያ የነገሰበት መንደር መሆኑን ለመግለጽ  ነው፡፡ ሀሳቡ ጅብ መኖሩን ከማወቅ ጋር ጅብን መፍራትን እንድንቀበል ያደርጋል፡፡ ጆፌ መኖሩን ማወቅ ትልቅ ነገር ነው፤ ይለናል ግሪን ፡፡ ጅብ እንዳለ ማወቅ አንድ ሰው ያለበትን አደገና ሁኔታ ማወቅ ማለት ነው ፡፡ ከጅብ ዝርፊያ ለማምለጥ የሀሳብ ደሃ መስሎ መታየት ይገባል ነው፤ መልእክቱ፡፡ ካልሆን እንደ ቴስላ በጆፌ መዘረፍ ይመጣል፡፡ ከጅብ መትረፍ የሚቻለው ምንም ከሌለን ብቻ ነው፡፡
መደምደሚያ
ከትላንት የምትማረው ብዙ ስላለ ወደ ትላንት ተመልሰህ ትላንትህን ፈትሽ፡፡ ትላንት ውስጥ ብዙ እውቀትና ጥበብ አለ፡፡ ከትላንት መማርን “በታላላቅ ሰዎች ትከሻ ላይ መቆም” ይለዋል፤ ኒውተን፡፡ የኒውተን ፈጠራዎች መሰረታቸውን ያደረጉት በሌሎች ሰዎች ፈጠራ ላይ ነው፡፡ ሁሉም በሌላው ድካም ነው የከበረው፡፡ ብዙሃኑ በሌላው ትከሻ ላይ ቆሞ ነው ዝነኛ የሆነው፡፡ ሼክስፒር እራሱ የሴራን ንድፍና አጫጭር ገለፃዎችን ኮርጆ ነው ያገኘው፡፡ በጊዜው በእንደዚህ አይነት አፃፃፍ፣ ከPlutarch በላይ ዝነኛና ታዋቂ አልነበረም፡፡ ሌሎች ፀሀፊዎች ከሼክስፒር ኮርጀዋል፡፡ ማይክል ጃክሰን፣ ስቲቭ ጆብስ፣ ቢል ጌትስ ወዘተ ኮራጅ አይነት ሰዎች ናቸው፡፡
ቢስማርክ እንዳለው፤ ቂሎች በተሞክሮ እንማራለን ይላሉ፤ እኔ ግን በሌሎች ተሞክሮ መጠቀምን እመርጣለሁ ብሎ ነበር፡፡ ከህይወት መድረክ ሊታወቅ የሚችለው ብዙ ነው፡፡ ግሪን የሚነግረን እንደዚህ አይነት ትምህርት አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ደረጄ ጥጉ፤ የመጀመሪያ ዲግሪውን በፍልስፍና ከአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ በ1998 ዓ.ም የወሰደ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከቻይና ዉሃን ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ ኢንተርናሽናል ሎው በ2009  ዓ.ም አግኝቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ፍልስፍና እና አለም አቀፍ ህግ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡





Read 827 times