Monday, 01 July 2024 00:00

ተወካዮቻችን “እየተመካከሩ” ነው? በኋላ “የለሁበትም” እንዳትሉ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

• የኛ ተወካዮች? የወጣቶች ተወካይ፣የሴቶች ተወካይ፣ የብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች፣ የከተማና የወረዳ ተወካዮች… ያልተወከለ
“ቡድን” የለም ተብሏል። ተወካዮችየየቡድናቸውን “ሐሳብ” እና “አቋም” ያቀርባሉ። ለየቡድናቸው “መብት” ይከራከራሉ? የየቡድናቸውን ቅሬታና እሮሮ ያሰማሉ?
      • ከዚያም ሁላችንም የተሳተፍንበት፣ ወይም የተወከልንበትና የተስማማንበት ሐሳብ ይጸድቃል፤ አገር ይለወጣል፤ ሕገ መንግሥት ይሻሻላል?
      • ነገሩ ሁሉ በዚህ መንገድ ከተጓዘ፣ አገራችን አማን ይሆናል? ችግርም ይጠፋል ማለት ነው?
      • ችግርማ ይኖራል። አገርስ እንዴት አማን ይሆናል! ለምን?
      • ሐሳብ “በቡድን” አይደለም። “ትክክለኛ ሐሳብና ትክክለኛ ሕግ” የብዙኃን ስምምነት ጉዳይ አይደለም።
               ዮሃንስ ሰ

      በቅድሚያ፣ የብሔር ብሔረሰብ ተወካይ፣ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካይ፣ የወጣቶች፣ የሴቶች ምናምን የሚለውን  አገላለጽ እንመልከት።
ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የተለያዩ ሰዎች በምክክር ላይ እንዲሳተፉ ወይም በጉባኤ ላይ እንዲታደሙ ማድረግ ጠቃሚ ነው ወይ? አዎ ጠቃሚ ነው።
ነገር ግን “ውክልና” አይደለም። እንደ “ውክልና” ከተቆጠረ፣ “ለመፍትሔ ይጠቅማል” የተባለ ምክክር፣ ነባር ችግሮችን አባብሶ አዳዲስ ችግሮችን የሚፈጥርብን ሊሆን ይችላል። ለዚህም ነው ጥንቃቄ ማድረግ የሚኖርባቸው።
ደግሞም ነገርዬው ያን ያህልም የተወሳሰበ ጉዳይ አይደለም። “የወጣቶች ተወካይ፣ የእገሌ ብሔር ተወካይ” የሚሉ ሐረጎች ምን ትርጉም እንዳላቸው አስቡት። ቁምነገር የሌላቸው አባባሎች ናቸው። ለምን?  
የወጣቶች “ሐሳብ”፣ የሴቶች “ውሳኔ”፣ የእገሌ ብሔር “አቋም”፣ የእከሊት ብሔረሰብ “ቅሬታ” የሚባል ነገር የለም። ኖሮ አያውቅም። ወደፊትም አይኖርም። በተለያዩ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ውስጥ በተቃራኒ ጎራ የተፋጠጡ ብዙ ወጣቶችን የምናየው ለምን ሆነና? ገዢው ፓርቲም ውስጥ በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ውስጥ የተለያየ ሐሳብ ይዘው የሚጨቃጨቁ ሴቶችም ሞልተዋል።
በተቃራኒ ፓርቲዎች ይቅርና፣ በአንድ ፓርቲ ውስጥም ብዙ የሐሳብ ንትርክና ሽኩቻ ሁሌም ውስጥ ለውስጥ ይብላላል፤ ይንተከተካል። ማምለጫና መተንፈሻ የተገኘ ሲመስል፣ ያኔ ግልብጥ ብሎ ይወጣል፤ በይፋ ይታያል። ሲብላላ የቆየው ይፈነዳል፤ ሲንተከተክ የነበረው ይገነፍላል።
በብሔር ብሔረሰብ የተቧደኑ ፓርቲዎችም ከዚህ ውጭ ሊሆኑ አይችሉም። ሐሳብ በቡድን አይደለምና። የሆኑ ሰዎች በብሔረሰብ ተወላጅነት ተጠራርተው ስለተቧደኑ፣ የብሔረሰቡ ተወላጆች በሙሉ ተመሳሳይ ሐሳብ ይኖራቸዋል ማለት አይደለም። እንዲያውም፣ በፖርቲ መሥራቾቹም ውስጥ ሽኩቻና ንትርክ ይፈጠራል።
ለጊዜው አፍነው ከድነው ለመያዝ ቢሞክሩም፣ ብዙም ሳይቆይ ንትርካቸው እየገነፈለ ወደ አደባባይ ተዘርግፎ ይወጣል። ሽኩቻቸውም ሲፈነዳም እርስበርስ “ለጥሎ ማለፍ? ሲሽቀዳደሙ ይታያሉ። አንዱ ሌላኛውን ያግዳል። ወይም ሌላኛው ቀድሞ ያባርረዋል። ከቻሉ ደግሞ የማሳደድና የማሰር ዘመቻ ያካሂዳሉ። መገዳደልም ጭምር። ይሄ አዲስ ነገር ነው? ምሥጢር ነው? አይደለም።
እንዲያውም ጸብ ክፉኛ የሚብሰውና የሚጦዘው በብሔር ብሔረሰብ የተቧደኑ ድርጅቶች ውስጥ ነው። በሃይማኖት ሰበብ ለፖለቲካ ሲቧደኑም እንደዚያው ነው።
ለምን? በብሔረሰብ፣ በሃይማኖት፣ በዕድሜ፣ በጾታ፣ በትውልድ ቦታ ስለተቧደኑ፣ የብሔረሰብ ሐሳብ፣ የወጣቶች አቋም፣ የደቡብ ጥያቄ፣ የሰሜን ውሳኔ… የሚባል ነገር ይፈጠራል ማለት አይደለም። “የቡድን አእምሮ የለም”፣ “የቡድን ሐሳብም የለም”። የቡድን ጸብ መፍጠር ለሚፈልጉ ሰዎች አመቺ ሰበብ ከመስጠት በስተቀር፣ “የቡድን ተወካይ” የሚል አገላለጽ ጥቅምም ቁምነገርም የለውም።
ከዚያ ይልቅ፣ “ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የተለያዩ ሰዎች በሰፊው የሚሳተፉበትና የሚታደሙበት ነው” የሚል አገላለጽ መጠቀም ይሻላል። “የወጣቶች ተወካይ” ተብሎ ስለመጣ፣ የሁሉም ወጣቶች ሐሳብ ሊናገር አይችልም። ጠቃሚ የሚመስለውን ሐሳብ በግሉ ይናገራል። ቁምነገሩም ይሄው ነው።
ወደ ሁለተኛው ነጥብ እንሸጋገር። የሕገ መንግሥት ጉዳይ።
“ሕዝብ ያልተሳተፈበት ሕገ መንግሥት”…
“የኅብረተሰብ ክፍሎች ያልተወከሉበት ሕገ መንግሥት”…
“ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ ሕገ መንግሥት”…
“ዘመኑን የማይዋጅ ሕገ መንግሥት”…
በሕገ መንግሥት ላይ የያዝነው ቂም፣ የተሳትፎና የውክልና ጉዳይ ከሆነ፣ ወይም የወቅታዊነት ጉዳይና የዓመተ ምሕረት ቆጠራ ከሆነ… አገራችንም ኑሯችንም ብዙ ተስፋ አይኖራቸውም።
“አልተሳተፍኩበትም፤ አልተወከልኩበትም፤ አልተስማማሁበትም” የሚል ምክንያት ሕግ ላይ አይሰራም። ሕግ የውል ስምምነት አይደለም። ሕጎች ሁሉ እንደ ውል ስምምነት ከሆኑ ግን፣ እስከ ዛሬ ብዙ በደል ደርሶብናል ማለት ነው።
ሰው ላይ ጥቃት አለመፈጸምና አለመግደል የሚል ሕግ ሲዘጋጅና ሲጸድቅ ተወካዮቻችን በቦታው ነበሩ? አልነበሩም። ታዲያ ይሄ ትልቅ ግፍ አይደለምን?
አትስረቅ፣ አትዝረፍ የሚሉ ሕጎች ላይስ ተሳትፈንበታል? ተስማምተን ፈርመንበታል? አልተሳተፍንም፤ አልፈረምንም። ይሄስ ከባድ በደል አይደለምን?
ደግነቱ እነዚህን እሮሮዎች ለማስወገድ “አገራዊ ምክክር” ማድረግ እንችላለን። ለመመካከርስ ተስማምተናል?
እ… “ለምክክር ተስማምተናል ወይ? ምን ዐይነት ጥያቄ ነው? ነገሩን ቧልትና ጨዋታ አናድርገው እንጂ” ብትሉ አልተሳሳታችሁም። ያልተሳተፍንበትን፣ ያልተወከልንበትንና ያልተስማማንበትን ሕግ በምክክር የማስተካከል ዕድል አግኝተን ባናበላሸው ይሻላል። መልካም። እሺ ይሁን። መመካከር ጀመርን። ቁምነገር ነው። ከዚያስ? ተመካክረንም በሆነ ሐሳብ ተስማማን።
በምን መንገድ እንደተሳካ እንጃ። ብቻ ተስማማን እንበል። ሁላችንም የተስማማንበት ሕገ መንግሥት አጸደቅን። በእርግጥ፣ ሁላችንም የምንስማማበት ሕገ መንግሥት ሊኖር አይችልም።
ከሰዎች ዘንድ ሁሌም የዕውቀት ወይም የሐሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ። ታይቶ በማይታወቅ አጋጣሚ ወይም በአንዳች አስገራሚ ተአምር፣ የሐሳብ ልዩነቶች በምክክር ድንገት ቢጠፉ እንኳ፣ እንዲሁ በጭፍን ለማፈንገጥና ለመቃረን የሚፈልግ ሰው አይጠፋም።
ለነገሩ፣ “ሁላችንንም የሚያስማማ አንዳች ተአምር”፣ “የሐሳብና የስሜት ልዩነቶችን የሚያጠፋ አስገራሚ ምትሃት”… ላይ ላዩን ሲያደምጡት መልካም ዕድል ይመስላል እንጂ መጥፎ ዕዳ ነው። ሰልፍን ይዞ እንደሚያዘግም ጉንዳን፣ በመንጋ እንደሚግተለተል የዱር እንስሳት፣ ሁላችንም አእምሮ ቢስ ሆነን ብንቀር ምን እናተርፋለን? እንዲህ ዐይነት ተአምርም ይሁን ምትሃት፣ በሩቁ የሚሸሹት ርግማን እንጂ የሚናፍቁት ቡራኬ አይደለም። “ሁላችንም የምንስማማበት ሕግ” የሚለውን ቅዠት እንተወው!
እሺ፣… ሁላችንም ባንስማማበት እንኳ፣ ሕጉን ለማዘጋጀት ወይም ለማጽደቅ ሁላችንም በምክክር ተሳትፈንበታል እንበል። በእርግጥ ብዙ ሚሊዮን ሰዎች በቀጥታ “ተሳታፊ” ሊሆኑ አይችሉም። እንኳን ተሳታፊ፣ ተጋባዥ ታዳሚ መሆንም አይችሉም። ሕግ ለማጽደቅ ወይም ለአገራዊ ምክክር ይቅርና፣ …”ፌስቡክ”፣ “ቴሌግራም”፣ “ትዊተር” በመሳሰሉት መነኻሪያዎችም ሁላችንም ተሳታፊ አንሆንም።
እና ምን ተሻለ? ሁላችንም ተስማምተን የምንወልደው ሕገ መንግሥት ሊኖረን አይችልም ብለናል።
ሁላችንም ተሳትፈን ወይም ታድመን “ሕገ መንግሥትን ማዋለድ” እንደማንችልም አይተናል።
ሁላችንም የተወከልንበት የሕገ መንግሥት ጉባኤ ወይም ምክክር ማካሄድ ግን እንችላለን። ተወካያችን “የሕግ ልደት” ላይ እንዲገኝ መላክ አንችልም? ይሄ ከባድ አይመስልም። ይቻላል። አይደለም እንዴ? በከፊል… ይቻላል! እንዴት?
“ተወካይ” ተብሎ የሚሄደው ማን ነው? ብለን እንጠይቅ።
ከስንት ሰዎችስ ነው ውክልና የተቀበለው?
አንዳንዴ፣ “ቀደም-ቀደም” የሚል ሰው ነው “የሕዝብ ተወካይ” ተብሎ የሚሄደው። ራሱን መርጦ መሾሙ አይደለም ጥፋቱ። ራሱን እንደ ሕዝብ ቆጥሮ ሹመት ሰጪ መሆኑ ላይ ነው - ነውሩ። ሕዝብ ነኝ ብሎ ማንን ይሾማል? ራሱን።
ገዢው ፓርቲ ወይም የየአካባቢው ጉልበተኛ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ራሱን እንደ ሕዝብ ቆጥሮ፣ ከየወረዳውና ከየመንደሩ የራሱን አባላት በተወካይነት የሚመርጥበት ጊዜም አለ። “የተለመደ ነው” ብንል ይሻላል - እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት።
ግን፣ ዜጎችና ፓርቲዎች ሁሉ፣ በአንዳች ተአምር የሥነ ምግባር መንፈስ ድንገት ቢሰርጽባቸውና የቅንነት ባሕርይ ተላብሰው በእውነት መንገድ ላይ መጓዝ ስለጀመሩ፣ “የሕዝብ ተወካዮች” በትክክል ተመርጠዋል እንበል።
ማለትም፣ በድምጽ ብልጫ!
በሌላ አነጋገር፣ ገሚሶቹ የመረጡት ተወካይ ወደ ሕገ መንግሥት ጉባኤ፣ ወደ ምክክር ድግስ ይሄዳል። ገሚሶቹ የመረጡት ተወካይ ግን ለጥቂት ተበልጦ ወደ ቤቱ ይመለሳል። አንገቱን ደፍቶ ሰዎች ያጽናኑታል - “ተስፋ አትቁረጥ፤ ዘንድሮ ባይሆንልህ በሚቀጥለው ዓመት ይሳካልሃል” ይሉታል። በሚቀጥለው ዓመትም ሌላ የሕገ መንግስት ጉባኤ፣ ሌላ አገራዊ ምክክር፣ አዲስ “የሕግ ልደት” ይኖራል?
ጥሩ ጥያቄ ነው። በቅድሚያ ግን፣ የጀመርነውን የቅንነት መንገድ እንጨርስ።
ያለ እንከን በቅንነት በተካሄደው ምርጫ አማካኝነት፣ ገሚሱ ሕዝብ የሚፈልጋቸው ተወካዮች በሕገ መንግሥት ጉባኤ ላይ ለመገኘት ሄደዋል። ገሚሱ ሕዝብ የፈለጋቸው ተወካዮች ግን “በድምጽ ተበልጠው” ወይም “በመመዘኛና በመስፈርት ተቀድመው” በአገራዊው ላይ ሳይታደሙ ቀርተዋል። ጉባኤው ሲያልቅ፣ ሕገ መንግሥት ሲጸድቅ፣ “አልተወከልንበትም” ይሉ ይሆን እንዴ?
የሚሉ ይኖራሉ። ግን ብዙ አያሳስብም። በምርጫ፣ በመመዘኛ… በሆነ መስፈት ተበልጠዋል፤ ወይም ተቀድመዋል። ተወካያቸው ሳያልፍ ቀርቷል። ቁጥራቸውም ከ50 በመቶ በታች ነው። ከ50 በመቶ የሚበልጠው ሕዝብ ግን በተወካይ አማካኝነት በአገራዊ ምክክር ላይ ወይም በሕገ መንግሥት ጉባኤ ላይ ታድሟል ማለት ይቻላል። አማን ነው። ወይም አማን ይመስላል።
ለጊዜው ሰላም ነው።
ችግሩ ግን፣ “አብዛኛው ዜጋ” በቀጥታ መሳተፍም ሆነ በተወካይ አማካኝነት መታደም አይችልም። አብዛኛው ዜጋ፣ ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች ነው።
እና ምን ችግር አለው? ዕድሜያቸው ለዓቅመ አዳምና ለዓቅመ ሔዋን አልደረሰም። እስከዚያው ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ አለባቸው። ልጆች በወላጆችና በአሳዳጊዎች ኀላፊነት ሥር ናቸው። አይደለም እንዴ?
እሺ። መልካም። ግን ለጊዜው ብቻ ነው። ከጊዜ በኋላስ? ከዐሥር ዓመት በኋላስ? ያኔ ብዙ ሚሊዮን “ልጆች”፣ ብዙ ሚሊዮን “ዐዋቂዎች” ይሆናሉ። ዕሠዬው ነዋ። መቼም “ዐዋቂ” ከሆኑ በኋላ፣ ያልሆነ “የሕጻን ነገር” አይጠይቁም።
“ያልተስማማንበት ሕግ፣ ያልተሳተፍንበት ምክክር፣ ያልተወከልንበት የሕገ መንግሥት ጉባኤ”… የሚል ክርክር ያመጣሉ እንዴ?
“ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ፣ ከዘመኑ ጋር አብሮ የማይራመድ፣ ያረጀ ያፈጀ ሕገ መንግሥት!” የሚል መፈክር ይፈጥሩ ይሆኑ እንዴ?    
እንደገና አዲስ ሕገ መንግሥት፣ እንደገና ሌላ አገራዊ ምክክር ማዘጋጀት አለብን ማለት ነው? በአምስት በዐሥር ዓመት ውስጥ፣ ሕጎችን ሁሉ መቀየር ሊኖርብን ነው?
ይሄ ሁሉ ምን ለማለት ነው? “ሕግ እንደውል ስምምነት አይደለም” ለማለት ነው።
አልተስማማሁበትም…
አልተሳተፍኩበትም…
አልተወከልኩበትም…
ወቅታዊ ሁኔታዎችን አላገናዘበም…
ዘመኑን የሚዋጅ አይደለም… በሚሉ ሰበቦች ሕጎችን ለመሻር ወይም ሕጎችን ለመውለድ የምንሞክር ከሆነ፣ የሕጎችን መሠረታዊ ባህርይ አለመረዳታችንን ነው የሚመሰክርብን።
ስምምነትና ተሳትፎ፣ ውክልናና ወቅታዊነት መጥፎ ነው ለማለት አይደለም።
ሕግ፣ አብዛኛው ሰው የሚስማማበት ቢሆን መልካም ነው። ነገር ግን፣ ብዙ ሰው ስለተስማማበት አይደለም የሕጉ ትክክለኛነት የሚረጋገጠው።
በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ወጣቶች፣ “የሰዎችን ንብረት ለመውረስ የሚዘጋጅ ዐዋጅ ጥሩ ሕግ ነው” ብለው የተስማሙበት ዘመን በታሪክ ተመዝግቧል። ለዚያውም በበርካታ አገራት ነው። በኢትዮጵያም ጭምር። በተግባርም ዐዋጅ ጸድቆ የሰዎች ንብረት በመንግሥት ተወርሷል። እና እንዲህ ዐይነት ሕግ፣ ብዙዎች ስለተስማሙበት ብቻ “ትክክለኛ ሕግ ነው” እንላለን?
“እውነትና ውሸት”… የስምምነት ጉዳይ አይደለም። ከእውኑ ዓለምና ከእውን ክስተት ጋር ተመሳክሮ ነው እውነትነቱና ውሸትነቱ የሚረጋገጠው።
ትክክለኛ ሕግ እና ሰንካላ ሕግም፣… የስምምነት ጉዳይ አይደለም። የእያንዳንዱን ሰው መብት… የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት፣ ንብረትና ነጻነት ከጥቃት የሚከላከል፣ አጥፊዎችን በአግባቡና በልኩ የሚቀጣ መሆኑ ላይ ነው - የሕግ ትክክለኛነት ማረጋገጫ። በብዙኃን ስምምነት አይደለም።
ብዙኃን ቢስማሙበት ግን ጥሩ ነው። ሥልጣኔም ነው እንጂ።
ብዙ ሰዎች እውነትን ቢያከብሩ መልካም አይደለም? ነው እንጂ። ብዙ ሰዎች በትክክለኛ ሕግ ቢስማሙም መልካም ነው።
አልተስማማሁበትም ቢሉም ግን፣ ትክክለኛነቱን አያጎድሉበትም። ቸል ሊሉት ይችላሉ። ተግባራዊ እንዳይሆን ማገድና ማሰናከልም አያቅታቸውም። ከናካቴው፣  ከሕግ መጽሐፍ ውስጥ ሊሰርዙትም ይችላሉ።
ቢሆንም ግን፣ ትክክለኛ ሕግ ሁሌም ትክክለኛ ነው - በቦታና በዘመን አይታጠርም።
መጥፎ ሕግ በስምምነት ብዛት ጥሩ ሕግ አይሆንም። ትክክለኛ ሕግ በቅሬታ ብዛት ክፉ ሕግ አይሆንም። ስምምነትና ቅሬታ… እዚህ ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም።
ብዙ ሰዎች በክፉ ሕግ ላይ ቢስማሙ፣ አገሬው በጥፋት ጎዳና ቁልቁል ይወርዳል። በትክክለኛ ሕግ ላይ ብዙ ሰዎች ሲስማሙ ደግሞ፣ አገሬው በትክክለኛ መንገድ ወደ ሥልጣኔ የመጓዝ ዕድሉ ይቃናል። የስምምነት ጥቅሙ እዚህ ላይ ነው። ተሳትፎና ውክልናም እንዲሁ።
አትስረቅ፣ አትግደል፣ በሐሰት አትመስከር የሚሉ ሕጎች… በተሳትፎና በውክልና የመጡ ቢሆኑ… አልያም ባይሆኑ፣ ትናንት የታወጁ አልያም ከሺ ዓመታት በፊት የተጻፉ ሕጎች ቢሆኑ… በሕጎቹ ትክክለኛነት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም።
“ሕጎች ሲጸድቁ አልተሳተፍንም፣ በሕይወት አልነበርንም” የሚል ቅሬታ ስላቀረብን፣ ትክክለኛ ሕጎች መጥፎ አይሆኑም። አልያም…
“ሕጎቹ የጸደቁት በተሳትፎና በውክልና ነው። ሕጎቹ የታወጁት በኛ ዘመን ነው” ብለን ስለተናገርን ብቻ መጥፎ ሕጎች በአስማት መንገድ ጥሩ ሕጎች አይሆኑም።
መጥፎ ሕጎችን በቅጡ ተገንዝበን በጥሩ ሕጎች ለመተካት ወይም ጉድለቶችን ለማሻሻል ከፈለግን፣ ከሁሉም በፊት መፍትሔው የዕውቀትና የቅንነት መንገድ እንጂ፣ የስምምነትና የውክልና ጉዳይ አይደለም። ዕውቀትንና ቅንነትን ማስፋፋት ግን ያስፈልጋል። ብዙዎች የተወከሉበት፣ የተሳተፉበትና የተስማሙበት እንዲሆን መጣርም የግድ ነው።
አለበለዚያ ጥሩ ሕግ፣ ያለ ብዙኃኑ ስምምነት፣ ብዙም አይዘልቅም። ቢዘልቅም በአግባቡ ተግባራዊ አይሆንም።Read 484 times