Saturday, 29 June 2024 20:08

በጎ ፈቃደኝነት - ነባሩ ቱባ እሴታችን

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “በጎ ፈቃደኝነት ድንበር፣ ወሰንና ዘር አያውቅም”



        ነገርን ከሥሩ ውሃን ከምንጩ እንዲሉ፣ በጎ ፈቃደኝነት ምንድን ነው? እንዴትስ ይገለጻል? በሚለው መሰረታዊ  ጥያቄ  የዛሬ ርዕሰ ጉዳያችንን  እንጀምር፡፡ እርግጥ ነው በጎ ፈቃደኝነት ለኢትዮጵያውያን አዲስ ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ብቻ ሳይሆን ባህር ማዶ ጭምር ተሻግረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡ ኮንጎና ኮሪያ ድረስ ዘምተው ዓለማቀፍ የበጎ ፈቃድ ተግባር  ተወጥተዋል፡፡
 በሌላ በኩል፣ በጎ ፈቃደኝነት ወይም በጎ አድራጎት የሚል መደበኛ ስም አይሰጠው እንጂ፣ በዕለት ተዕለት ህይወታችንም  ቢሆን  አንዱ ለሌላው በጎ እያደረገ ነው እዚህ የደረስነው፡፡ ሆኖም ዘመናዊነትና ግላዊነት ባሳደሩብን አሉታዊ ተጽዕኖ ሳቢያ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ  ይህ ቱባ  እሴታችን እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ ለዚህም ነው ባለፉት ጥቂት ዓመታት፣ በመንግስት ደረጃ ጭምር፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሥራ  የተጀመረው፡፡ በእኒህ ዓመታት በተለይ በመዲናዋ የተከናወኑ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን መቃኘት የዚህ ጽሁፍ ዓቢይ ዓላማ ነው፡፡   
ከዚያ በፊት ግን መነሻችን ላይ ያነሳነውን መሰረታዊ  ጥያቄ አስቀድመን እንመልስ፡፡ በጎ ፈቃደኝነት ምንድን ነው? እንዴትስ ይገለጻል? በጎ ፈቃደኝነት የራስን ጊዜ፣ አቅምና ችሎታ ወይም ሃብትና ክህሎት ሌላውን  ለማገዝ ወይም ሸክሙን ለማቅለል  የማዋል ተግባር ነው - በምላሹ ምንም ዓይነት ክፍያና ጥቅም ሳይፈልጉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ለማህበረሰብ ወይም ለአገር በፈቃደኝነት ነጻ አገልግሎት መስጠት ብንለውም ያስኬዳል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን፣ ዋና ኮሚሽነር አቶ አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው፤ “በጎ ፈቃደኝነት ማለት ሁሉም ሰው በራሱ ተነሳሽነትና ፍላጎት፣ ያለማንም አስገዳጅነት፣ በነጻ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ፣ ያለምንም ክፍያ የሚሰጠው አገልግሎት ነው፡፡” ይላሉ፡፡ አክለውም፤ “በጎ ፈቃደኝነት ለሰዎች ጊዜህን፣ ገንዘብህንና ጉልበትህን በመስጠት ዘላቂ የሆነ የመንፈስ እርካታ የምታገኝበትና አብሮነትና ትብብርን ለማዳበር የሚያግዝ ተግባር ነው፡፡” በማለት ይገልጹታል፡፡
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ መሃመድ ፊት አውራሪነት እየተለመደና እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን የሚያሳትፍ ዘርፍ ሆኗል፡፡ በተለይ በመዲናዋ  ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተቋማዊ በሆነ አሰራር እየተተገበረ ነው፡፡ በቅርቡ ይህንኑ ዘርፍ የሚመራ ተቋም በኮሚሽን ደረጃ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ዋና ተግባሩ ይሄው ነው፡፡
በነገራችን ላይ በዓለም  ላይ ለረዥም ዘመናት የዘለቀ ጠንካራ የበጎ ፈቃደኝነት ባህል ያላቸው በርካታ አገራት ይገኛሉ፡፡ እነ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድና ስዊድን ይጠቀሳሉ፡፡ በወጉ የዳበረና የበለጸገ የበጎ ፈቃደኝነት ባህል እንዳላት በሚነገርላት አሜሪካ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች  በተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶች ውስጥ  በንቃት እንደሚሳተፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እኒህ  አገራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎታቸውን ከራሳቸው አልፈው  ለሌሎችም ማድረስና ማዳረስ  ማዳረስ ችለዋል፤ ድንበር እየተሻገሩ፡፡  
በጎ ፈቃደኝነት ሌላው  ባህርይው - ወሰን፣ ድንበርና ዘር የማይገድበው መሆኑ ነው፡፡ የሰው ልጅ በመሆናችን ብቻ የተቸረን ጸጋ ነው፡፡ ስለዚህም የሰው ልጆች ባሉበት ሁሉ ይተገበራል፡፡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያለ ልዩነት የሚሳተፍበት ዘርፍም ነው፡፡ ከሕጻናት እስከ አረጋውያን፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ---ሁሉንም ያሳትፋል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት እርዳታ አይደለም፤ ይልቁንም የፍቅርና አጋርነት መገለጫ ነው፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት፣ በመዲናዋ፣ በሰብአዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች መርሃ ግብሮች አማካኝነት 22.7 ቢሊዮን ብር የሚገመት  የመንግስት ወጪ መሸፈን ተችሏል፡፡ በእኒህ ፕሮግራሞች በየዓመቱ በአማካይ ከ2 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞች የተሳተፉ ሲሆን፤ 900ሺህ ገደማ ነዋሪዎችም  ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚከናወኑ  የበጎ ፈቃድ ተግባራት ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ በክረምት ወራት  የአቅመ ደካሞችና  አዛውንቶች  ቤትን  የማደስና የመገንባት ተግባር እየተስፋፋና እየተለመደ  መምጣቱን አለመመስከር ንፉግነት ነው፡፡ የዛሬ አምስት አመት ገደማ ጠ/ሚኒስትሩ የአንዲት አረጋዊት ቤት በማደስ ሀ ብለው ያስጀመሩት የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ፣ ዛሬ ተስፋፍቶና ተጠናክሮ  በአቧሬና አካባቢዋ  አጀብ የሚያሰኝ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ የበርካታ ነዋሪዎችን ህይወት በተጨባጭ  ለውጧል፡፡ በአካባቢው ባለ አስራ ሁለት ወለል የመኖሪያ  ሕንጻዎች ተገንብተዋል፡፡ የበጎ ፈቃደኝነት ትሩፋቱ ታዲያ በአቧሬ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡  ልደታ አካባቢ “የበጎነት መንደር” ተመስርቷል - በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፡፡ በተመሳሳይ .በአራዳ፣ በቂርቆስ፣ በቦሌ፣ በየካ፣ በለሚ ኩራ፣ በንፋስ ስልክ፣ በኮልፌ፣ በአዲስ ከተማና በሌሎችም ...የአቅመ ደካማዎችና አረጋውያንን ቤቶች  የማደስና የመገንባት ተግባራት በስፋት ተከናውነዋል፡፡
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ማዕድ ማጋራትም፣ ሌላው በስፋት እየተለመደ የመጣ የበጎ አድራጎት ተግባር  ነው፡፡  በዚህ ዓመት ብቻ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች  ማዕድ የማጋራት ተግባር ተከናውኗል፡፡ በገንዘብ ሲሰላ ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነው፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ሰው” እና “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ህፃን” በሚል በጀመራቸው መርሃ ግብሮች ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አረጋውያንና ህጻናትን መደገፍ ተችሏል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን፣ ዋና ኮሚሽነር አቶ አብርሃም ታደሰ እንደሚናገሩት፤ ”ባለፈው ዓመት ከ24 ሺህ 500 በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ በዚህ ትስስር ተቆራኝተው፣ ትናንት ለአገር ውለታ የከፈሉ አዛውንቶችን  እያገዙና  እየደገፉ ነው፡፡ ለአብነት ያህል፡- ”ታፍ ኢትዮጵያ“ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አርባ እናቶችን፣ ለሁለት ዓመት፣ በየወሩ አራት ሺህ ብር እየሰጠ በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡” ብለዋል፡፡
 “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ሕጻን” በሚል መርሃ ግብርም፣ አንድ ባለሃብት 100 ሕጻናትን ከጨቅላነት እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ ለማስተማር መረከቡን የኮሚሽኑ ሃላፊ ገልጸዋል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ባለሃብቱ መቶ ሕጻናትን ከእናቶቻቸው ሳይለዩ በየወሩ 3 ሺህ 500 ብር በመስጠት በእንክብካቤ ያድጋሉ፡፡ በባለሃብቱ ድጋፉ እስከ ዩኒቨርስቲ ትምህርት ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ በተመሳሳይም 430 የሚሆኑ ሕጻናት በየክፍለ ከተማው እንዲሁ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው - ባለሃብቶች  ህጻናትን እየወሰዱ እያሳደጉ ነው፤ አረጋውያንን እየጦሩ እየደገፉ ነው፡፡
 እኒህ ሁሉ በመዲናዋ እየተካሄዱ ያሉ  የበጎ ፈቃደኝነት ትሩፋቶች ናቸው፡፡ ነዋሪዎች በሌላ በኩል በአረንጓዷ አሻራ መርሃ ግብር፣ ችግኝ በመትከል በንቃት ይሳተፋሉ፡፡ በጤናው ዘርፍ ደግሞ ነዋሪዎች ደም በመለገስ ለወገናቸው ይደርሳሉ፡፡ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት፣ እስከ ቀዶ ጥገና የሚደርስ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ  ነጻ የህክምና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ አንጻር በመዲናዋ የሚከናወኑ የበጎ ፈቃደኝነት ተግባራት ድርብርብ የሆነ ትርፍ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ አብርሃም፤  የበጎ ፈቃደኝነት ተግባር የሃብት  ክፍፍልን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይገልጻሉ፡፡  ከዚህ ሌላ “ትልቁ ሃብት” የሚባለው የወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ላይ ያመጣው ለውጥ ነው ባይ ናቸው። ”ወጣቶች ለአካባቢያቸው፤ ለማሕበረሰባቸውና ለአገራቸው በነጻ መስራትና ማገልገል ሲለምዱ፣ አገር ወዳድ ትውልድ ይፈጠራል።” ብለዋል፡፡
የበጎ ፈቃደኝነት ትሩፋቶች ተቆጥረው አያልቁም፡፡  በነዋሪዎች መሃል የአንድነትና የትብብር ስሜት በመፍጠር የማህበረሰብ ግንኙነትን ያጠናክራል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት ሙያዊ ዕድገትን ያዳብራል፡፡ በጎ ፈቃደኞች  በበጎ አድራጎት ተግባራት ሲሳተፉ፣ እግረ መንገዳቸውን አዳዲስ ክህሎቶችና ልምዶችን ይቀስማሉ፡፡ ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ በጎ ፈቃደኝነት ማህበራዊ ግንኙነትንም ያሰፋል፡፡ አዳዲስ ሰዎችን ለመተዋወቅ፣ ወዳጅነትን ለመመስረትና ማህበራዊ ትስስርን ለማስፋት ዕድሎችን ይፈጥራል፡፡ አስገራሚ ቢመስልም በጎ ፈቃደኝነት የጤና ትሩፋቶችም አሉት፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፣ በጎ ፈቃደኝነት ውጥረትን በመቀነስ፣ ድባቴን በማስወገድና በአጠቃላይ የመንፈስ እርካታና  የደስታ ስሜትን በመጨመር የአዕምሮ ጤንነትን ያሻሽላል፡፡
መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚለው፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በአገራችን እንደ ባህል እንዲዳብርና ጥቂቶች ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ሚሊዮኖች የሚሳተፉበት ተግባር  ይሆን ዘንድ፣ በጽንሰ ሃሳቡ ዙሪያ ትርጉም ያለው  የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ማከናወን ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ በየጊዜው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጥና ማስረጽ ተግባራትን እያከናወነ  ይገኛል፡፡  
በጎ ፈቃደኝነት፤ የማህበረሰብ አንድነትንና ትብብርን እንዲሁም ማህበረሰባዊ ለውጥን ለማምጣት ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ ትሩፋቱ ለብዙሃን የሚዳረስ ነው፡፡ በድፍን አገር ላይ  አዎንታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡
ባለፉት ጥቂት  ዓመታት፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በተሻለ መጠንና ፍጥነት  በመዲናዋ  እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ሌሎች የክልል መንግስታትና የከተማ አስተዳደሮችም የመዲናዋን አርአያነት በመከተል የበጎ ፈቃድ  አገልግሎትን ለማስፋፋትና ለማዳበር እየተጉ ይገኛሉ፡፡  
በመዲናችንም ሆነ በመላው አገሪቱ  የበጎ ፈቃደኝነት ጥረቶችንና ጅምሮችን በማበረታታትና በመደገፍ፣ ጠንካራና አይበገሬ ማህበረሰቦችን መገንባት እንዲሁም ለሁሉም  የምትመች ኢትዮጵያን መፍጠር የሁላችንም ሃላፊነት ነው፡፡ ክረምቱ ስኬታማ የበጎ ፈቃደኝነት ተግባራት የሚከናወንበት ይሁን!!

Read 1179 times