Saturday, 29 June 2024 20:21

የከሸፈው የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነድ (PRSP)

Written by  ስንታየሁ ገ/ጊዮርጊስ
Rate this item
(0 votes)

 “---የድሕነት ቅነሳ ሰነዱና በሱም ላይ በየደረጃው የተደረጉ ውይይቶች ምን ውጤት አስገኙ? ዛሬና የዛሬ 24 ዓመትየነበረው ድሕነት አንድ ዓይነት ነውን? ብላችሁ መጠየቅ መብታችሁ ነው፡፡ ግዴታችሁም ይመስለኛል፡፡ መልሱ ያለው ግን እናንተ ዘንድ እንጂ ከእኔ ዘንድ አይደለም፡፡ ለእኔ ስታትስቲክሰ ቁጥር ነው፡፡--”
        

           መንደርደሪያ
በቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ፣ በ80ዎቹ መጨረሻ፣ ሁለቱ ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶች (የዓለም ባንክና አይኤምኤፍ) የዕዳ ጫና በነበረባቸው ታዳጊ አገራት ተግባራዊ የሚሆን የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም (Structural Adjustment Program (SAP)) ቀርጸው ነበር፡፡ የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራሙ (SAP)፤ በድርጅቶች የሚገኘው የሰው ኃይል ተቀንሶ እንዲስተካከል፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም እንዲዳከም፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በግል እንዲያዙ፣ … የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎች ነበሩት፡፡ የዕዳ ጫና የከበዳቸው አገሮች በዚያ መሠረት የልማት ድርጅቶቻቸውን መዋቅር ካሻሻሉ የእዳ ስረዛ ይደረግላችኋል ተብለዋል፡፡ ለወደፊቱ ኤኮኖሚያችሁ አድጎ ትርፋማ በመሆን የተበደራችሁትን ዕዳ ልትከፍሉ የምትችሉት የቀረበላችሁን ፕሮግራም ተግባራዊ ስታደርጉ ብቻ ነው ተብሎ ተነግሯቸዋል፡፡ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ አስገዳጅ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ይህንን ፈጽሙና የዕዳ ስረዛ ይደረግላችኋል የሚል የአበዳሪዎች ጫና የነበረበት ፕሮግራም ቀርቦላቸው ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ፕሮግራሙ ያተኮረው በዕዳ ጫና ወገባቸው የጎበጠው በማደግ ላይ የነበሩት እነኚያ አገሮች ኤኮኖሚያቸውን በማሳደግ ትርፋማ እንዲሆኑ፣ ድሕነትን እንዲቀንሱና ለወደፊት የሚበደሩትን ዕዳ ለመክፈል እንዲጠናከሩ ሳይሆን፣ የፋይናንስ ድርጅቶቹ ያቀረቡትን ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት የድርጅቶቻቸው መዋቅሮች ለዓለም ዓቀፍ አበዳሪዎች ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ ነበርና ውጤት አላመጣም፡፡ አንድ ፕሮግራም መልካም የሆኑና ያልሆኑም ውጤቶች አሉት፡፡
መቼም “ለማኝ መራጭ አይደለምና” የሚሉትን መፈጸም ግዴታው ነው፡፡ በተነደፈው ፕሮገራም ውስጥ የተካተቱት ድሐ አገሮች የተነገራቸውን ከመፈጸም ውጭ የራሳቸው የሆነ ድምጽ እንዲኖራቸው አልተደረገም፡፡ ተቋሞቻቸውን እንደገና በማዋቀራቸው ምክንያት ለማግኘት ተስፋ የተሰጣቸው የዕዳ ስረዛም፣ ተዘፍቀው ከነበሩበት ከፍተኛ የዕዳ ጫና ምንም ያህል አልታደጋቸውም፡፡ ቀድሞውንም የተበደሩትን ዕዳ መክፈል ያቃታቸው ሊከፍሉት የሚያስችላቸው የገንዘብ ክምችት (ጥሪት) ስላልነበራቸው ነው፡፡ ዕዳን መሰረዝ ብቻውን ልማታቸውን በማስቀጠል ድሕነትን እንዲቀንሱ አዲስ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ሊፈጥርላቸው አልቻለም፡፡ ያለፈው ዕዳቸው ተሰርዞላቸው አዲስ የልማት ርዳታና ብድር (አዲስ የካፒታል ፍሰት) ቢቀርብላቸው እንኳን የተሻለ ነበር፡፡ በእጃቸው የሌላቸውን እንዳላቸው አድርገው እንዲያስቡት ፕሮግራሙ ረድቷቸው ይሆን? ለፌዝ የጠየቅኩት ጥያቄ ነውና፣ ችላ በሉት፡፡
ፕሮግራሙ ብዙም ለውጥ ሳያመጣ ከጅምሩ የከሸፈ እንደነበረ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ እዳ በነበረባቸው አገሮችም ሆነ በሌሎች ዘንድ አልተወደደም፡፡ እስከዛሬም የሚታወቀው በከሸፈ ፕሮግራምነቱ ነው፡፡ በአንጻሩ የ90ዎቹና የሚሊኒየሙ ዓመታት ድሕነት (የድሕነት ቅነሳ) ትኩረት ሊቸረው እንደሚገባ ያመላከቱ ወቅቶች ነበሩ፡፡ ከዚህ አንጻር እ.ኤ.አ በ1990 ላይ የዓለም ባንክ እትም በሆነው የዓለም ልማት ሪፖርት (World Development Report (WDR)) ውስጥ ድሕነትን (Poverty) ነጥሎ ርዕስ ያደረገ ሪፖርት መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ያ በራሱ አንድ መልካም ጅምር ነበር የሚሉ አሉ፡፡
ከከሸፈው የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም ተመክሮ በመነሳት፣ በነዚህ ወቅቶች የተሻለ የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነድ (Poverty Reduction Strategy Paper (PRSP)) የተሰኘ በዓይነቱና በይዘቱ የተለየ ፕሮግራም እንዲዘጋጅ መንገድ መጥረግ የተቻለ ይመስላል፡፡ ለዚህም የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና (መያድ) የሲቪል ማኅበረሰብ ክፍሎች አዎንታዊ የሆነ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ የዓለም ዓቀፍ ፋይናንስ ድርጅቶቹ ከለመዱት ውጪ ብዙም መሄድ አይችሉበትም፡፡ ምዕራባውያን “መጭ” ሲሏቸው የሚጋለቡ ፈረሶች ናቸው፡፡ ጋላቢዎቻቸው ደግሞ ያቋቋሟቸው ትልልቆቹ አገራት ናቸው፡፡ ከድሐ አገራት ጋር አብሮ ለመቆም አፈጣጠራቸው አይፈቅድላቸውም፡፡
በድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነድ (Poverty Reduction Strategy Paper (PRSP)) እና በመዋቅራዊ ማሻሻያ ፕሮግራም (Structural Adjustment Program (SAP)) መካከል ግልጽ ልዩነቶች ነበሩ፡፡ ልዩነቶቹንና የተለያዩ ክፍሎች (ተሳታፊ አገራቱን ጨምሮ) ስለ መዋቅራዊ ማሻሻያ ፕሮግራሙ (SAP) ውድቀት ሲሰጡት የነበረውን ዝርዝር ምክንያቶችና ቅሬታዎች በዚህ አጭር ጽሑፍ ማቅረብ ይንዛዛልና ለጊዜው ትቼዋለሁ፡፡ ይሁን እንጂ፤ ከልዩነቶቹ መካከል አንዱና ዋናው በመዋቅራዊ ማሻሻያ ፕሮግራም ወቅት ያልነበረ፣ በድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነዱ (PRSP) ውስጥ ግን እንዲካተቱ የተደረጉ፣ መሠረታዊ መርሆዎች (አንኳር መለኪያዎቸ) እንዲኖሩት መደረጉ ነው፡፡ እኒህን ቀጥሎ እንያቸው፡፡
የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነድ [Poverty Reduction Strategy Paper (PRSP)]
የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነዱ ስድስት መሰረታዊ ዓላማዎች/መርሆዎች (principles) የነበሩትና አገራቱ ድምጽ እንዲኖራቸው ተደርጎ እንዲቀረጽ የቀረበ ነው፡-
ውጤት ተኮር (Result Oriented)፡ የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂዎቹ ተጨባጭና (tangible) የሚቆጠሩ/የሚመዘኑ (monitrable) መሆን፣
ሰፊ ሽፋን (Comprehensive): ስትራተጂዎቹ ማክሮ ኤኮኖሚውን፣ የተለያዩ ተቋማትንና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ሁሉ ያቀፉ እንዲሆኑ ማድረግ፣
አገር መር (Country-driven)፡ ፕሮግራሙ አገር በቀል እንዲሆንና ተግባራዊነቱም የተሳታፊ አገራቱን ሕዝብ አዎንታ/ስምምነት የያዘ መሆን፣
አሳታፊነት (Participatory): መንግሥት ለብቻው ከሚያወጣቸው የልማት ፖሊሲዎች በተለየ መልኩ፣ የሚያገባቸው (Stakeholders) ሁሉ በድሕነት ስትራተጂ ቀረጻውና በቁጥጥሩ በቀጥታ እንዲሳተፉና ድምጻቸውን እንዲያሰሙ መደረግ እንዳለበት፣
አጋርነት (Partnership): በመንግሥትና በሌሎች ተሳታፊዎች መካከል አጋርነትና የጋራ ቅንጅት መፈጠር እንደሚኖርበት፣
የረዥም ጊዜ ትልም (Long-term): የአጭር ጊዜ ግቦች የማይታለፉ ቢሆንም፣ ትኩረቱ በረዥም ጊዜ ግቦች ላይ እንዲያነጣጥር ማስቻል (ለምሳሌ፤ የድርጅቶችን መዋቅር ማሻሻልና የአቅም ግንባታን ሳያሰልሱ ማሳደግ)፡፡
የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነዱ ከላይ የተጠቀሱትን ስድስት ዓላማዎች/መርሆዎች (principles) በማስቀመጥ መከናወን እንደሚገባው ግዴታን የጣለ ፕሮግራም በመሆኑ፣ መንግሥት ለዘመናት እንደለመደው ብቻውን ስትራጂዎቹን እንዲቀርጽ አላመቸውም፡፡ ሌሎች የልማት ተሳታፊዎችን (Stakeholders) ሊያቅፍ የሚችል የተሳትፎ ፕሮግራም የመንደፍና የማሳተፍ ግዴታ ተጥሎበት ነበር፡፡
በሰነዱ የዝግጅት ሂደት የመንግሥት መዋቅራዊ ዝግጅት
ወደ ድሕነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነድ (PRSP) አጠቃላይ የውይይት/ምክክር ሂደት ውስጥ በቀጥታ ከመገባቱ በፊት፣ የፌዴራል መንግሥቱን ጥረት ለማስተባበርና ለመምራት እንዲያስችል በፋይናንስና የኤኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የሚመራ ኮሚቴ (steering committee) ተቋቁሞ ነበር፡፡ የፌዴራል ድሕነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነድ ጽሕፈት ቤት (Federal PRSP Secretariat) ይባል ነበር፡፡ የሰነዱን ዝግጅት በማንኛውም ደረጃ ያስተባብርና ይቆጣጠር የነበረው የመንግሥት አካል ይኸው ጽሕፈት ቤት ነበር፡፡
የፌዴራል መንግሥቱ በየደረጃው ያቋቋመውና ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን ያቀፈው ኮሚቴ ጊዜያዊ/የአጭር ጊዜ የድሕነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነዱን (Interim Poverty Reduction Strategy Paper (I-PRSP)) በ1993 ዓ.ም (Nov 2000 እኤአ) አዘጋጀ፡፡ በድሕነት ቅነሳው ሂደት መሳተፍ ይገባቸዋል የሚባሉ ሌሎች ተዋናዮችን (stakeholders) በመለየት፣ በሰነዱ ዝግጅት ሂደት በሚደረጉ ውይይቶች/ምክክር እንዲሳተፉ [አሳታፊነት በሚለው በዓላማ አራት ላይ እንደተመለከተው] አዘጋጀ፡፡ ከዚህ አንጻር፣ መንግሥት ያዘጋጀውን ጊዜያዊ የድሕነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነድ (I-PRSP) ለመያዶችና ሌሎች የሲቪል ማኅበረሰቡ (Civil Society) ክፍሎች በማሰራጨት ሂደቱን ጀመረ/አስጀመረ፡፡
 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፎ  
በወቅቱ 212 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በአንድ ጥላ ስር ይዞ ያስተባብር ለነበረው ሲርድኤ (CRDA) ይኸው መንግሥት ያዘጋጀው ጊዜያዊ የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነድ (I-PRSP) እንዲደርሰው ተደረገ፡፡
ሲርዲኤ በበኩሉ በደረሰው ሰነድ ላይ ግንዛቤን ከጨበጠ በኋላ፣ አባላቱን ለውይይቱ እንዲዘጋጁ አደረገ፡፡ ለዚህም ሲል በቅድሚያ ሰነዱን ያዘጋጁትን የመንግሥት አካላትንና የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ድርጅቶችን ስለ ሰነዱ ገለጻ እንዲያደርጉለት በመጋበዝ ስብሰባ ጠራ፡፡ ካገኘው ገለጻ በመነሳትም ሰነዱን አስመልክቶ በመያድ አባል ድርጅቶቹ ውስጥ ግንዛቤን ለማስጨበጥና መደረግ በሚኖርበት የተሳትፎ ርምጃ ላይ ለመወያየት ጉባኤ/ወርከክሾፕ አዘጋጅቶ አባላቱን በሙሉ አወያየ፡፡  
በውይይቱ መጨረሻ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ተሳትፎ በማስተባበርና ሀሳባቸውን በማቀነባበር የሚመራ 22 የመያድ አባላትን ያቀፈ አንድ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም በጉባኤው በመወሰኑ፣ የመያድ የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነድ ግብረ ኃይል (NGO PRSP Taskforce) ተሰኝቶ በሰኔ 1993 (2001 አእኤ) እንዲቋቋም አደረገ፡፡
የመያድ የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነድ ግብረ ኃይል
ግብረ ኃይሉ በድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነዱ ውይይት (consultation) ተሳትፎውን የጀመረው ሦስት ዐበይት ዓላማዎችን የያዘ የሥራ አቅጣጫ በመንደፍ ነበር ፡-
በኢትዮጵያ በሚካሄደው የውይይት (PRSP consultation) ተሳትፎ ውስጥ የመያድን አመለካከት/ርዕይ (perspective) ማቀናበር/መቅረጽ፣
ፕሮግራሙን አስመልክቶ በሲቪል ማኅበረሰቡና በመያድ የሚደረጉ ተሳትፎዎችን ማስተባበር፣
በፕሮግራሙ ውይይት/ምክክር (consultation)፣ ተግባራዊነት (Implementation)፣ ቁጥጥርና ምዘና (Monitoring and Evaluation) የመያድን ተሳትፎ የሚያረጋግጥ ሥርዓት (mechanism) ማዘጋጀት፡፡
በነዚህ ሦስት ዐበይት ዓላማዎች ላይ ተመስርቶ ሥራን የጀመረው ግብረ ኃይል (Taskforce) ለዓላማዎቹ ተፈጻሚነት መያድን ማስተባበር ጀመረ፡፡ በፌዴራል፣ በክልልና በወረዳ በሚካሄዱ የውይይት መድረኮች ውስጥ የመያድን ሀሳቦች/ፍላጎቶች (conserns) በመግለጥ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ጀመረ፡፡ በነዚሁ እርከኖች ውስጥ ለውይይቱ የሚመጥኑትን ተሳታፊ አባላትንም ሰየመ፡፡ የግብረ ኃይሉ ተሳትፎ የአጠቃላይ ውይይቱን ሂደት (consultation process) ዲሞክራሲያዊነት እንዲላበስ ያግዛል የሚል የጸና እምነትና ንቃት ላይ ያተኮረ እንደነበረ አውቃለሁ፡፡ ከዚህ አንጻር፣ ግብረ ኃይሉ የሲቪል ማኅበረሰቡ (Civil Society) ለፕሮግራሙ የሚደረገውን አዎንታዊ አስተዋጽዖ ለማሳደግ እንዲችል ሰፋ ያለ የተሳትፎ ድርሻ ከመንግሥት እንዲሰጠው ጥሯል፡፡ በዚህም የመያድ ግብረ ኃይሉ የፌዴራል የድሕነት ቅነሳ ጽሕፈት ቤቱ አባል እንዲሆን ተደርጓል፡፡  
ግብረ ኃይሉ ከተጣለበት ኃላፊነት አንጻር፣ መንግሥት የሚያካሂዳቸው ውይይቶች ዲሞክራሲያዊ እንዲሆኑ ከመከታተልና ከማገዝ በተጨማሪ፣ ሰነዱ ሲቀረጽ የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂዎቹ የይዘት ጥራት (quality) እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ተሳትፎዎችን ለማድረግ በሁሉም መስክ ተዘጋጀ፡፡ በውይይቱ ዲሞክራሲያዊነትና የይዘት ጥራት ላይ ትኩረት እንዲኖር የመጣሩ ዐቢይ ዓላማ፣ የረዥም ጊዜ ዓላማን ያነገበና ሁሉን ያካተተ (በመዋቅር፣ በተሳታፊነትና በስትራተጂዎች ጥራት) የድሕነት ቅነሳ ሰትራጂ እንዲቀረጽ ለማስቻል ያለመ ነበር (በመርሆ 6 ከላይ እንደተቀመጠው)፡፡
የድሕነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነድ (PRSP) መሠረታዊ የተሳትፎ ዓላማዎች/መርሆዎችን ቢያስቀምጥም፣ ያንን ዓይነት አሰራር የለመደው ስላልነበረ፣ መንግሥት ባመቸው መንገድ ቀጥሎበት ነበር፡፡ የድሕነት ቅነሳን አስመልክቶ፣ መያድ ከመንግሥት ጋር የረዥም ጊዜ መዋቅራዊ ግንኙነት/ትስስር ኖሮት ቀጣይ አስተዋጽኦ ሊያደርግ በሚያስችል መልኩ መንግሥት ያሰበ አልመሰለም፡፡ ያ ሁኔታ በራሱ ግብረ ኃይሉና የሲቪል ማኅበረሰቡ ድርጅቶች በመንግሥት አሠራር ላይ ቅሬታ እንዲኖራቸው ያደረገ ጉዳይ ነበረ፡፡ ቅሬታው ጊዜያዊ የድሕነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነድ (I-PRSP) ሲዘጋጅ ከመጀመሪያው ተሳትፎ በማድረግ የሰነዱን ጥራት ለመጠበቅና የተሳታፊነት ደረጃንም ከፍ በማድረግ አስተዋጽኦ ማድረግ ይቻል ነበር ከሚል መነሻነት የተጸነሰ ነው፡፡
መያድን ወክሎ የሚሰራው ግብረ ኃይል ቅሬታ ቢኖርበትም፣ በጊዜያዊ የድሕነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነዱ (I-PRSP) ላይ ከመወያየትና አቃፊና ገንቢ አስተያየቶችን ከመስጠት አልተቆጠበም፡፡ መያድና ሌሎች የሲቪል ማኅበረሰቡ (Civil Society) ክፍሎች ከዕቅዱ ጀምረው በባለቤትነት የሚሳተፉበት እንዲሆን መንግሥት ፈልጎ ቢሆን ኖሮ የበለጠ አቃፊ (inclusive) እና መዋቅራዊ (institutionalized) የሚሆንበትን መንገድ ያመቻች ነበር የሚለው ቅሬታ ግን እስከ መጨረሻው (ጊዜያዊው ሰነድ (I-PRSP) ሙሉ ሰነድ (PRSP/SDPRP) እስከሆነ ድረስ) የከረመ ጉዳይ በመሆን ዘልቋል፡፡
የውይይቱ ሂደትና ተሳትፎ
የድሕነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነድ (PRSP) የውይይት ሂደት (Consultation Process) በመንግሥትና መያድን ጨምሮ እንደ አዲስ አባባ ምክር ቤት የመሳሰሉትን የሲቪክ ድርጅቶች አካትቶ እስከ ወረዳ ደረጃ ተከናውኗል፡፡ ከኅዳር 1994 (2001 እኤአ) እስከ መጋቢት 1994 (2002 እኤአ) ውይይቱ ሳያቋርጥ በተለያዩ ደረጃዎች ሲካሄድ ነበር፡፡ መንግሥት ከዘረጋው ሂደት በአንጻሩ የመያድ ግብረ ኃይሉ አባል ድርጅቶች (የሲቪል ማኅበረሰብ) በራሳቸው እስከ ወረዳ ድረስ ውይይት እንዲካሄድ አድርገዋል፡፡ በሰነዱ ላይ የሕዝቡን አስተሳሰብና ጥያቄዎች አሰባስበዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በሲርዲኤና በመያድ ግብረ ኃይል በተዘጋጁ ወርክሾፖች የአባል ድርጅቶች ሀሳቦችና አቋሞች ተሰባስበው እንዲጠናቀሩ ተደርጓል፡፡ በዚህም የመያዶችን አቋም በዝርዝር እንዲያስረዳና ለድሕነት ቅነሳ ሰነዱ ግብዓት እንዲሆን (NGO Perspective on Poverty Reduction Strategy Paper for Ethiopia የተሰኘ) አንድ የጥናት ሰነድ ቀርቧል፡፡ በመያድ ግብረ ኃይል የተዘጋጀው የጥናት ሰነድ ዓላማ፣ እያንዳንዱን የልማት ሴክተር የሚዳስስ የፖሊሲ ስትራተጂ እንደሚያስፈልግና በዚያም ሰነዱ/ፖሊሲው ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት፣ የመያድን ያላሰለሰ እገዛና ተሳትፎን አስቀጥሎ ለድሕነት ቅነሳ ሰነዱ ግብዓት በመሆን ለቁጥጥርና ለምዘና እንዲያመች ለማስቻል    ነው፡፡
በጥቅሉ፤ በኅዳር 1993 (November 2000) በጊዜያዊ የድሕነት ቅነሳ ሰነድ (I-PRSP) የተጀመረው ሥራ፣ በሰኔ 1994 (June 2002) የሰነዱ (PRSP) ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለአጠቃላይ ውይይት ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ ተችሎ    ነበር፡፡
በመጨረሻም፤ የአገር ውስጥና የውጪ መያዶችን፣ ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶችን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ የማኅበረሰብ ድርጅቶችን (CBO)፣ የርዳታ ለጋሽ አገሮችንና የልማት አጋሮችን ያቀፈ ሰፊ ጉባኤ በኢሲኤ አዳራሽ ውስጥ ለሦስት ቀናት በማካሄድ፣ የድሕነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነዱ (PRSP) ረቂቅ ቀርቧል፡፡ በግብረ ኃይሉ አማካኝነት ተጠንቶ የተዘጋጀውና የመያድን አቋም (NGO Perspective) የሚዘረዝረው የጥናት ሰነድም በዚሁ ጉባኤ ላይ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
መንግሥት፣ የድሕነት ቅነሳ ስትራጂ ሰነድን (PRSP) ያቀረበው፣ ስትራተጂዎቹ በጥቅሉ ከልማት ዕቅዶቼ ጋር ተዛማጅ የሆኑና ቀድሞም ቢሆን ተግባራዊ ለማድረግ በዕቅድ የያዝኩት ትልም አካል/ደጋፊ ሰነድ እንጂ አዲስ ግኝት አይደለም በሚል አቋም ነው፡፡ ያዘጋጀውንም ሰነድ “ቀጣይ ልማት ለድሕነት ቅነሳ” (Sustainable Development for Poverty Reduction Program (SDPRP)) በማለት ሰይሞ ባቀናበረው ሰነድ አማካኝነት ሪፖርቱን በስፋት አቀረበ፡፡ በወቅቱ PRSP በመባል የተጀመረው የሰነድ ቅንብር፣ SDPRP ተብሎ በተደጎሰ የኢትዮጵያ የድሕነት ቅነሳ ሰነድነት እንዲታወቅ ተደረገ፡፡
በነሐሴ 94 (August 2002) በመጨረሻ መልኩ የተጠናቀቀው የስትራተጂው ሰነድ፣ በመስከረም 95 (September 2002) ላይ በሙሉ ሰነድነት (Full PRSP/SDPRP) በዓለም ባንክና በአይኤምኤፍ እንዲጸድቅ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ የበጀት ዓመት ከሐምሌ (94/95) ከመጀመሩ አኳያ፣ መንግሥት ሰነዱን ተግባር ላይ ያዋለው ከመጽደቁ 2 እና 3 ወራት ቀደም ብሎ ነበረ፡፡ ከዚያ በኋላ የድሕነት ቅነሳ ሰነድ ዝግጅትና የውይይት ሂደቱ አብቅቷል፡፡ የድሕነት ቅነሳው የመያድ ግብረ ኃይልም በዚያው እንዲከስም ተደርጓል፡፡ ውይይቱ ጤናማ ሂደትና ውጤትም ነበረው፡፡
ግብረ ኃይል ቋሚ መዋቅር አይደለም፡፡ አንድን ተግባር ለማከናወን ተቋቁሞ ሥራው ሲጠናቀቅ የሚከስም ውቅር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ግብረ ኃይሉ የተቋቋመበትን ዓላማ በማሳካቱ ከስሟል፡፡ ከመበተኑ አስቀድሞ ግን፤ የግብረ ኃይሉን አባላት እርሾ በመጠቀም የድሕነት ቅነሳ ተግባራዊ መረብ (Poverty Action Network of Ethiopia (PANE)) የተሰኘ የሲቪል ማኅበረሰብ (CSO) ድርጅት ሕጋዊ ሆኖ እንዲመሠረትና በድሕነት ቅነሳ ላይ የሲቪል ማሕበረሰቡ ያላሰለሰ ተሳትፎ በሚያደርግበት ሂደት ላይ የተመረኮዘ ዓላማና ግብ ሰንዶ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
የድሕነት ቅነሳው ሂደት በአንድ ጊዜ ውይይት በሚዘጋጅ ሰነድና በተሳታፊዎች ገደብ ሳይወሰን፣ ቋሚ እንዲሆንና ከቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልል መሠረታዊ የሕዝብ ተሳትፎን (grassroot participation) ያቀፈ የሲቪል ማኅበረሰብ (CSO) መረብ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ፣ ሀሳቡን ከማርቀቅ እስከ ሕጋዊነት ጉዞው መንደርደሪያ ድረስ የድሕነት ቅነሳ ተግባራዊ መረብ (Poverty Action Network of Ethiopia (PANE)) እንዲመሰረት ቀዳሚ በመሆን አውቀዋለሁ፡፡ በወቅቱ የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ኦፊሴር፣ በሲርዲኤ የሚሊኒየም ልማት ግብ (MDG) እና የአዲስ ትብብር ለአፍሪካ ልማት (NEPAD) ተጠሪ በመሆን ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ ድሕነት ቅነሳ ሂደት እንጂ፣ በአንድ ወቅት በዘመቻ መልክ ምሳር የሚያነሱበት ጠላት አይደለምና ለዘላቂ የድሕነት ቅነሳ ሥራ መዘጋጀት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በቅንነት ሲሰሩ ለነበሩት የመያድ የድሕነት ቅነሳ ስትራጂ ግብረ ኃይል አባላት ምስጋናዬ ይድረሳቸው፡፡  
ድሕነት ቅነሳ ሂደት ነው፡፡ ተሳትፎም እንደዚሁ ሂደት ነው፡፡ የውይይት ሂደት (ጥራቱ፣ ዲሞክራሲያዊነቱና አሳታፊነቱ) የሰነዱን ጥራት፣ የአተገባበሩንና የክትትልን ጤናማነት ይወስናል፡፡ የድሕነት ቅነሳ የበርካታ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅና ሳያቋርጥ መከናወን የሚገባው የልማት ጥያቄ ነው፡፡ በውይይት ተሳትፎ ውስጥ ልምዶችን መካፈል፣ ሀሳብን በመለዋወጥ ሌላውን ማሳመን፣ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት (consensus) መድረስ፣ የሀብትን ድልድል ፍትሀዊ ማድረግ፣ የተቋማትን ትስስርና ቅንጅት ማሳደግ የሚያስችሉ መንገዶችን ያመቻቻል/ይጠርጋል፡፡
በልምድ በመንግሥት ብቻ ይካሄድ ከነበረው እቅድና ቁጥጥር ወደ ተሳትፏዊ እቅድና ቁጥጥር (participatory Monitoring) በማደግ ብክነት የተቀነሰበት ልማትና የድሕነት ቅነሳ እንዲኖር ውይይት ይጠቅማል፡፡ ካለፈው የድሕነት ቅነሳ ስትራተጂ ሰነድ የውይይት ሂደትና የሰነድ ዝግጅት ጥንካሬም ሆነ ድክመት መማር ለወደፊቱ ጠቃሚ ነው፡፡ “ማየት ማመን ነው” ይባላል?
የድሕነት ቅነሳ ሰነዱና በሱም ላይ በየደረጃው የተደረጉ ውይይቶች ምን ውጤት አስገኙ? ዛሬና የዛሬ 24 ዓመት የነበረው ድሕነት አንድ ዓይነት ናቸውን? ብላችሁ መጠየቅ መብታችሁ ነው፡፡ ግዴታችሁም ይመስለኛል፡፡ መልሱ ያለው ግን እናንተ ዘንድ እንጂ ከእኔ ዘንድ አይደለም፡፡ ለእኔ ስታትስቲክሰ ቁጥር ነው፡፡ ካለፈው ምን ተማርክ? ምን ጥሩና መልካም ያልሆኑ ሂደቶችን (ችግሮችን) አየህ? ለወደፊት ድሕነትን ለመቀነስ ፕሮግራም ቢነደፍ መንግሥትና ሕዝብ ምን ማድረግ አለባቸው? ካላችሁኝ፣ መልስ እንዲሆናችሁ በሚቀጥለው ጊዜ በአጭሩ ላወጋችሁ እችላለሁ፡፡ ሰላም፡፡  Read 483 times