Monday, 01 July 2024 00:00

የኛ ልጅ ---- በርታ በርታ!

Written by  የአብሥራ አድነው
Rate this item
(1 Vote)

ጅንን……..ቁልል እስከ ጥጉ…..እስከ ወዲያኛው፤ ወንድነትን ከኩራት ቀላቅሎ፣ በወር ሰላሳውንም ቀን ክብር…ክብርብር!! ቁንን ለይቅርታ፤ ኩፍስ ራስን ለማየት…… የኛ ልጅ በርታ በርታ እንዳትረታ!
ግንባርህን ቋጠር…… ጥርስህን ደበቅ….. አካልህን ከዚህ…… ልብህን ከዚያ…… እጅህን ለማንተራስ ዘርጋ….. ዕቅድህን ከውስጠትህ እጠፍ! የኛ ልጅ በርታ በርታ እንዳትረታ!
ድር……ቅ ዐሳብ፤ ከመለወጥ….. “የሽንፈትን” ቡልኮ ከመከናነብ….ግንፍል ከቃልህ፣ ውልፊት ሲባል…… ሰው ከእግዜር እንኳን አፈንጋጭ መኾኑን እንደመርሳት……ስምር የሌላውን ሕይወት….. ክርክም ነጻነቱን…..የኛ ልጅ በርታ በርታ እንዳትረታ!
አንተ ትጠየቃለህ  ወይስ ያሳደጉህ? ወይስ ያሳደጉህን ያሳደጉት?
“ወንድ ልጅ አይፈራም!” ብለው አይደል ያሳደጉህ? ይኼን አምነህ ተመንድገህ፣ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ኮሽታ ሰማሁ ብለህ፣ በር በርግደህ ትወጣለህ…… ዐሳብ ለማንሸራሸርና ሒስ ለመዋጥ፤ መቀመጥን ታዲያ ምን ኾነኽ ነው የምትፈራው?……አይፈራም ጋሜ አይፈራም! ወንድ ልጅ……..
ሀዘንህን ሽክፍ…… ቁጣህን ዝርግት…… ርህራሄን ካድ….. ዕብሪትህን ግልጥ….. ዕንባህን እንደ ድካም…… ድካምህን እንደ ብስጭት…..በጣም ተኮፍሰሀል እኮ፣ መቼ ነው ወርደን የምንነጋገረው?
“ወንድ ልጅ ተወልዶ ካልሆነ እንዳባቱ
ስጡት አመልማሎ ይፍተል እንደናቱ!”
እንደ እናትህ ማልቀሱን ተወው፣ ስቀህ ታውቃለህ? ሰው ፊት አልቅሶ በማግስቱ ራስን ሰብስቦ መኖር፣ ወደ ውስጥ ከማንባት በላይ ወኔ ጠይቆስ ቢኾን ማን ያውቃል? አልደከመኽም፤ “ሴት” ላለመኾን ተጠርዞ መኖር? አይፈራም ጋሜ አይፈራም!!
ተወዳጅ እንዳይቀብጥ፣ መውደድህን ሽሽግ….. ተናፋቂ እንዳይኮራ ናፍቆትህን እፍን….. መውደድህን አውቀው፣ ቢቀብጡብህ ትፈራለህ እንዴ? ናፍቆትህ ተገልጦ ኩራትን ብትዘግን ወኔ ይከዳሃል? በቃ ሁሌ መከላከል? ተጋላጭ መኾን ጋር ሳትደርስ እንዴት ጀግንነትህ ላይ እንተማመን? ጀግንነትን ስታሳድድ፣ ከሰውነት እንዳትጎድል ብዬ’ኮ ነው! አንበሳው ጋሜ አይዞህ ወንድሜ!
እኔ እጠየቃለኹ? ወይስ ያሳደጉኝ ይጠየቃሉ? ወይስ ያሳደጉኝን ያሳደጉት?
ዓለሜ ራሴንም እኮ እጠይቃለኹ፤ ያቀረብኩብኽን ወቀሳ ኹሉ ውድቅ የምታደርግ ምሉዕ ብትኾን የእውነት በደስታ እቀበልሃለኹ ወይስ በተስኪያን እንደገባች ውሻ ክፍ! እልሃለሁ? ምላሼን  እንጃ፣ እርግጠኛ አይደለኹም። ሲከፋህ ጠርተኽኝ፣ ትክሻዬን አቅፈህ ብትንሰቀሰቅ ወንድነት የጎደለው አልቃሻ የመምሬ ውሻ! ብዬ በልቤ መታዘቤ ይቀራል? መውጣት መግባቴን የማታምን እንስፍስፍ ብትኾን፣ ስስነትህን የሚሸከም ትሁት ልብ ባለቤት ለመኾኔ፣ በራሴ ላይ አመኔታ የለኝም። የኛ ልጅ በርቺ በርቺ እንዳትረቺ!
ፊቱን ሲያዩት ሐምሌ 17 ነገር ይመስላል። ሐምሌ 17 ምን ይመስላል? እንጃ ምን አውቄ፤ የሆነ ብርሃን ያልፈነጠቀው፣ ደብዛዛ፣ መከፋት ያረገዘ፣ከዚያ ደግሞ ምንም የማይነበብበት ሌጣ ፊት ነገር። አብሮት መዋል ደስታና ፈንጠዝያን ለለመደ ግራዋ ግራዋ ይላል፣ ከልጅነቱም ከፌጭታ ጋር ጠበኛ ነው። በመንገድ ሲጓዝ አቅል እስክታስት ከተዋበች እንስት በላይ የነተበ ልብስ ለብሰው ቅርቃር ላይ የተወተፉ አዛውንት፣ እግሩን በፍጥነት ከማወናጨፍ ያዘገዩታል፤ ከቆነጃጅት ከሚናኝ ውድ ሽቱ ይልቅ፣ ከእናቶች የሚነሳ የቅቤ ክርፋት ለሕይወት ያቀርበዋል፤ እውነት ያለው እነርሱ ጋር ይመስለዋል።
የራሱ ዓለም ሰፍቶት የሚንከላወስ ባተሌ ነው፤ ጥቂት ሰው፣ ጥቂት ንግግር፣ ጥቂት ፈገግታ፣ ጥቂት ንክኪ….የተደቆሰ የሰው ምጥን።  የሆነ የእመጫት መኝታ ቤት ውስጥ የሚተከል ዜሮ ሻማ አምፖል!  ምንምነትና ደብዘዝ ማለትም ለካ፣ የራሱ የማይገለጥ ውበት አለው?
በጋራ ስቀን እናውቃለን እንዴ? አያይ እንጃ! በእኛ አንደበት ያልተዳወረ ሀዘን፣ ያልተፈተለ ግፍና  ያልተቋጨ መከራ መኖሩን እጠራጠራለሁ። ቁዘማ የስራ ቋንቋችን ነው፤ አብረን እንቆዝማለን፤ እንብሰለሰላለን።
ልቡን ሳየው ጳጉሜ 5 ነገር ይመስላል። እሺ ጳጉሜ አምስትስ ምን ይመስላል? እንጃ በሞቴ! ገና በጅምር ያለ ነገር፣ አብሰልሳይ አእምሮውን ያህል የማይሰፋ ነገር! ዳቦ የማይሆን ጢቢኛ፣ እንጀራ የማያህል እንጎቻ ነገር! የእርሱ ጳጉሜ ስድስት ራሱ አይደርስም፤ አምስትም ተንፏቅቆ በመከራ ነው የደረሰው። ልቡ ያጠረ ሰው ግን ምን ይጎድለዋል? ሐዘኔታ? ርህራሄ? ትዕግስት? ፍቅር ወይስ ትዝታ?
ትዝታ ግን ስንት ዲናር ነው የሚሸጠው? ገዢስ አለው ለመሆኑ? ዓለምን ለብቻችን የታዘብንበት ቦታ ክብደቱ ስንት ሰቅል ነው? ምን እርሱ ብቻ የተባባልናቸው፣ ለሰማይ ለምድር የከበዱ ቃላትና መኃላዎች ሒሳቡ በማን ነው? ያንቀላፋውን ልብ ጮኸን የቀሰቀስንበትን ማን ያወራርድ? እጅ መያያዝ ትክሻ መደጋገገፍ፣ የዕዳ ስረዛው ወዬት ነው? ምሽት ልክ ሦስት ሰዓት ሲል፣ የትዝታ አድባራት ሕዝባቸውን በደውል ድምፅ ለምኅላና ቅዳሴ ይጠራሉ። ተነስ…..ኦ ለትዝታ፤ ሰው ትዝታን ሲያስቀድስ እንደ መቋሚያ የሚደገፈው ምንድነው? ናፍቆት ነው ወይስ ፀፀት?
 ፍቅርና መንሰፍሰፍ፣ ቅንነትና ተጋላጭነት፣ ፍርሃትና እኔነት፣ ርህራሄና እርግጠኝነት፣ ጥርጣሬና ስጋት፣ ክህደትና እምነት አግድም እግራቸውን ዘርግተው ለጨዋታ ተቀመጡ:-
አሌ ሆይ አላሌ ሆይ
ገረዴን አያችሁ ወይ
ገረዴን ማርያም ስማ
በርኩማ አሸክማ
በርኩማ የዳገቴ
የሸማ ቅዳዶቴ
ቀድጄ ቀዳድጄ
ሰጠኋት ላበልጄ
አበልጅ ብትወደኝ
ጨረቃ ሳመችኝ
ጨረቃ ድንቡል ቦቃ
አጤ ቤት ገባች አውቃ
አጤ ቤት ያሉ ልጆች
ፈተጉ ፈታተጉ
በቁልቢት አስቀመጡ
ቁልቢቷ ስትሰበር በዋንጫ ገለበጡ
ከስንዴ ቆሎ
ከዳቦ ቆሎ
ይችን ትተሽ
ያቺን ቶሎ!
ክህደት ብቻ እግሩን አንከርፍፎ ቀረ፤ ሌላው ሁሉ ቁልቢት አረፈበት፤ ተሸንፎ ወጣ። ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል፤ ማሕበረሰቡ ለካ “ገረድ” ነበረው! ማሕበረሰቡ ትዝታው እንዳይጠፋ በንፁህ የልጆች አእምሮው ውስጥ በዘፈን መልክ እሾህ ይጠርቃል? ምን አውቄ! ተጫውቼ ያደግኹትን ዘፈን የምጠረጥረው፣ የነፍስህን ቅዝቃዜ አጋብተህብኝ ንው? እኔ የምለው---ትዝታን በቁልቢት ላይ ዘረር ቢያደርጉት የማይዘግን ይኖራል? ስለ መድኃኔአለም እያልን ብናስይዝ?Read 491 times