Tuesday, 02 July 2024 00:00

አሊ በርኪ ቱቾና ካራማራ

Written by  አብዲ መሃመድ
Rate this item
(0 votes)

ሙዚቃ ረቂቅ የሆነ ጥበብ ነው፡፡ ያዘነን ከማጽናናት፣ ስብራትን ከመፈወስ ባሻገር የተጎዳን ያበረታል፣ የደከመንም ያነቃቃል፡፡ ሙዚቃ ህዝብን ወደ አንድነት የማምጣት አቅም አለው፤ ወይም የማምጣት አቅሙ ከፍ ያለ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ እኩልነትን በማጽናት ማህበራዊ የጋራ ስሜትን በማስተጋባትና ፍቅርን በመስበክ፤ እንዲሁም የአስተሳሰብ አድማስን በማስፋት ረገድ ያለው ድርሻ የላቀ ነው፡፡ ከአያሌ ዘርፈ ብዙ ሚናዎቹ ባለፈ ደግሞ ታሪክን ይዘክራል፡፡ የሀገር ፍቅርን ከፍ ያደርጋል፣ ጀግኖችን ያወድሳል፣ የበለጠም ያጀግናል፡፡
በሀገራችን በሙዚቃው ዘርፍ ውስጥ ቀደም ባሉት ዘመናት እንዲህ ያሉ የጀግኖችን ታሪክ አጉልተውና ገድላቸውን አድምቀው እሚናገሩ፤ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መጠበቅ ቀዳሚ ምሽግ የሆኑና ዘብ የቆሙ ገድለኞችን እሚፈክሩ ብሎም የሚዘክሩ…ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ስራዎች በስፋት ይቀነቀኑ ነበር፡፡ ዛሬ-ዛሬ አልፎ አልፎም ቢሆን እኒህን መሰል ዜማዎች መደመጣቸው አልቀረም፡፡ በተለይ ወጣቱ ከያኒ ከፆታዊ ፍቅር በዘለለ የጀግኖችን መስዋዕትነት… በስንኞቹ ነቅሶ ሲገኝ ባልተለመደ ሁኔታ ቀልብን ይስባል፣ በእጅጉም ያኮራል፡፡ እነሆ ድምፃዊ ወንድወሰን መኮንን (ወንዲ ማክ) የአንድ ታላቅ ጀግናን (አሊ በርኪ ቱቾ) ስሙን የሚያነሳ፤ የካራማራ ድሉን የሚያወሳ ሙዚቃ ሰርቷል፡፡ በግሩም ሁኔታ አንጎራጉሮ ለአድማጮች አድርሷል፡፡… ኢሳያስ ሆርዶፋ የተባሉ ሰው ደግሞ (ደራሲና ጋዜጠኛ ናቸው) በአሊ የጦር ግንባርና አጠቃላይ የህይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ጽፈው ወደ አማርኛ እንዲተረጎም በማድረግ ለንባብ አብቅተውለታል፡፡ እኛም ከወንዲ ማክ አፍ፣ ከኢሳያስ መጽሐፍ… የጀግናውን አሊ ገድል እያወሳን፣ ስራዎቹን እያነሳሳን በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡
 ... በሰኔ 18 ሸገር ተማምሎ
ወቶ አደርሽ ወጣ ሰልፉን አስተካክሎ
የእናት የእህት ስንቁ፣ በአገልግል ሸክፎ
በምስራቅ ተገኘ ወኔውን ታቅፎ
ታጠቅ ከተመ ሚሊሺያው ገባ ለሀገር ተመመ
በታጠቅ የጦር ካምፕ 1961 ዓ.ም  ምሽት ላይ አንድ ጥሪ አስተጋባ፡፡ ሶስት መቶ ሺህ ሰልጣኝ ሚሊሺያዎች ትጥቃቸውን ማዘገጃጀት ጀመሩ፡፡ በየብርጌዳቸው ተሰልፈውም ወደ አብዮት አደባባይ ተመሙ፡፡ ምስራቅ የሀገራችን ክፍል የሆነው ሶማልያ ወደ ጦር ግንባር ለመዝመት አሸኛኘት ተደረገላቸው፡፡ በሽኝት ስነሥርዓቱ ላይ ከመንግስቱ ኃይለ ማርያም ጋር የዙምባቤ ነፃ አውጭ ግንባር ሊቀመንበር የሆኑት ሮበርት ሙጋቤም ተገኝተዋል፡፡ የወቅቱ ሹማምንት፣ ሙዚቀኞችም አሉ፡፡ እኚህ አንጋፋና እውቅ የሙዚቃ ባለሙያዎች ወኔ ቀስቃሽና ሀገራዊ ስሜትን የሚያንፀባርቁ ህብረ ዜማዎቻቸውን አቅርበው ሸኟቸው፡፡ ይሄን ህብረ ዝማሬ ወንዲ ማክ በሙዚቃው መግቢያ ላይ ለመንደርደሪያነት ተጠቅሞበታል፡፡
… “ይህ ነው ምኞቴ እኔ በህይወቴ
ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ … ይሰኛል፡፡ ሳህሌ ደጋጎ ነው የደረሰው፡፡ ብዙነሽ በቀለም አዚማዋለች -  በኦሮምኛም ጭምር፡፡ ከትግል በፊትም ሆነ ከድል በኋላ፤ እንደነ ጥላሁን ገሰሰና ብዙነሽ በቀለን የያዘ የሙዚቃ ቡድን ወደ ጦሩ ካምፕ ጎራ እያለ ለሰራዊቱ የሞራል ማነቃቂያና ማበረታቻ እሚሆኑ ሙዚቃዎችን በማቅረብ ያዝናና ነበር፡፡ ወንድወሰን ገድልሽ ተሰማ ሲል ሙዚቃውን ይጀምራል፡፡
… ብስራት ገድልሽ ተሰማ፣ የድልሽ ዜና
ፈጣሪ ትቶ ማይተውሽ፣ ሀገር ሆንሽና
እንደ አሊ በርኬ፣ ታንክ ማርኬ
ለሀገሬ መስዋዕት ነው ልኬ!
የቁርጥ ቀን ልጅ ነው፡፡ የእናት ሀገር ፍቅር አንገብግቦት ገና በአፍላነቱ የዘመተ፣ ለኢትዮጵያ ለድል አጥቢያዋ መንገድ የከፈተ፡፡ የጦር ትምህርት በወጉ ሳይማር፤ ለጦር ሜዳ ጀግንነት ብቻ የተወለደ ነው ይሉታል፡፡ ሲፈጥረው ጀግና አድርጎ ነው ያበጃጀው፡፡ አንድ ሙሉ ክፍለ ጦር ብርጌድን ማንበርከክ፣ ታንክ መማረክ…. አሊ በየአውደ ውጊያው እሚከውነው የአዘቦት ግብሩ ነው፡፡ የሶማሊያን መንግስት ታንኮች ያወደመ መለዮ ለባሽ ሚሊሺያ ነው፡፡ አዎን! የታንክ ቀበኛ ነው እሱ - ጠጅ ነፍሱ፡፡ የካራማራው ባለድል - በኦጋዴን ሜዳዎች ላይ የዚያድ ባሬን ታንኮች ያደባየ ባለገድል (ቀላል አይወድድም ጠጅ!) እንዲያውም አንድ እለት በጦርነት አፍታ መሀል (16 የሶማሌ ወታደሮችን የማረከ ቀን) ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም ባቢሌ የጦር ካምፕ መጥተው፡፡ በአሊ ልበ ሙሉነት፣ በጀግንነቱና በራስ መተማመኑ ተደምመው፤ ባዩት ነገር በእጅጉ ተደስተው ከተቀመጡበት ብድግ ብለው ወደ አሊ በርኪ እየተራመዱ፤ “አሊ…አሁን ምን ላድርግልህ?” አሉት…በሁለመናው ቀልባቸው ተማርኳል፡፡ ለጠየቁት ጥያቄ መልስ ሳይጠብቁ “ምን ትፈልጋለህ?…ምንስ ላድርግልህ?” ሲሉ መንግስቱ አክለው ጠየቁት፡፡…“እኔ ሁልጊዜ የሚናፍቀኝና የምወደው ጠጅ ስለሆነ ጠጅ ግዛልኝ!” አለ - አሊ፡፡ እየሳቁና የናፈቀውን ልጁን እንደሚቀበል አባት ‹አንድ መቶ ብር› ሰጡት፡፡ ወታደር ፖሊሶች ጠጅ ቤት እንዲወስዱትም ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ‹ለወደፊቱም ቢሆን ጠጅ ሲያምርህ ሄደህ እንደልብህ መጠጣት ትችላለህ፤ የሀገሩን ዳር ድንበር ለሚያስከብር ጀግና ይሄ ሲያንሰው ነው›! አሉ፡፡ አሊም ያማረውን ጠጅ በደስታ ተጎንጭቶ ከልቡ አጣጣመ፡፡
… አብሮ መኖር በፍቅር እንጂ፣ ጥቃት የ
ማይለምደው
ዳርሽን ሲነኩት መሀሉ ሚነደው
ሀገር ተወረረች ብሎ እንቅልፍ ባይወስደው
ጀግናው ልጅሽ ወጣ፣ ልክሽን ሊያስለካው፡፡
ያ ዚያድ ባሬ ምን አለ
ካርታ እስከ አዋሽ ላይ የሳለ
እሱማ ቆርጦ ከመጣ
ሀገር ጠርታለች ና ውጣ
ሀረር ተከበበች ድሬንም ጨነቃት
ለሁሉ ፈጥኖ ደራሽ ያ ድንበር ጠባቂ
ለነብሱ ሳይሳሳ ለሀገር ወዳቂ!
እማረካለሁ እና እመታለሁ፣ ለጠላት ጥይት ሲሳይ እሆናለሁ ብሎ አይሰጋም፡፡ ሞት እና ህይወት… ጉዳዩ አይደለም፡፡ የቱንም ያህል ፈታኝ የሆነ ወታደራዊ ተልዕኮና ትዕዛዙን በጀግንነት፣ በቆራጥነትና በድል አድራጊነት ፈጽሞ በኩራት ወደ ብርጌዱ ይመለሳል፡፡ ግዳይ ሊጥል፣ ለግዳጅ ሲወጣ… “በህይወት ከተመለስኩም ተመለስኩ፤ ከሞትኩም ደግሞ ለህይወቴ አልሳሳም!”…ይላል ወኔ በሚንጸባረቅበት መንፈስ፡፡ አለቆቹ የሆኑት የብርጌድ አዛዦች መቶ አለቆች፣ ኮሎኔሎች፤… እነ ገበየሁ አበበ የአሊን ደፋርነትና ለሀገሩ ያለውን ፍቅር እያሰላሰሉ ዘወትር ይደነቃሉ፡፡ ይህን ነው እንግዲህ አቀንቃኙ በስንኞቹ ለነብሱ ሳይሳሳ!…ሲል ለመግለጽ የሞከረው፡፡ በዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሊያ ጦር እቅዱ ሰፊ ነበር፡፡ ‹ታላቋን ሶማሊያ እንመሰርታለን›!…ብሎ ተነስቷል፡፡ ሙሉ ኃይሉን አደራጅቶና አጠናክሮ፣ የኛን የጦር ካምፕ ተቆጣጥሮ፣ ሀረርና ድሬዳዋንም ጨምሮ… ወርሮ ለመያዝ ሲል በቂ የጦር መሳሪያዎችን ከእግረኛ ሰራዊት ጋር አሰልፎና እየደመሰሰ፤ ከተሳካም አዋሽ ወንዝን አልፎ አዳማን ለመያዝ አልሟል፡፡ በዚህ አጣብቂኝ ሰዓት አሊ ከተፋፋመው ጦርነት መሀል የማንንም ትዕዛዝ ሳይጠብቅ ወደ ጠላት ታንኮች ተጠግቶ፤ ታንኮቹ ላይ በክላሽ ይተኩሳል፡፡ የተሰጡትን ቦንቦች ይዞ በእልህና ፍፁም ቆራጥነት በተሞላበት ቴክኒክ እሳት በሆነው ጦርነት ውስጥ እየተሹለከለከ ታንኮች አጠገብ እየደረሰ ይወረውራል፤ ጠላትን ድባቅ ይመታል፡፡ አያሌ ታንኮችን እየተሳበ ደርሶ የእሳት እራት አደረጋቸው፣ ወደ አመድነት ለወጣቸው፡፡ አሊ በርኪ በዚህ መልኩ ይሄንን መሰል ጀግንነት እየፈፀመ የሶማሊያን ወራሪ የጥፋት መረብ ባይበጣጥስ ኖሮ፣ የኛ ጦር ያለው ምርጫ እጅ መስጠት ብቻ ነበር፡፡ ምክንያቱም በቂ መሳሪያ የለም፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ተከቧልና ማምለጫ ቀዳዳ የለም፡፡ አዲስ አበባ ለመግባት ምንም የሚያግደውና የሚያቆመው ኃይል አልነበረም፡፡
... ያ ፊደል ካስትሮ የሀገር ባለውለታ
ወጥቶ አደሩን ልኮ ድሉም ድሉን መታ
በሰማይ ተናንቆ የአየር ኃይሉ ጀግና
ጀቱን አዘነበው በረዶ አረገና
በገስጥ መድፈኛው ፋፈሞና ቆሬ
መንግስቱ ኃ/ማርያም ዘመተ ለሀገሬ
ከቀዬ ቢርቅም የሰራውን ሰርቶ
ሀገር በማዳኑ አይረሳም ከቶ
እነሆ በካራማራ ድላችን ውስጥ አሻግረን የዛሬይቱ ኢትዮጵያን ስናጤን፤ እንዲህ ነፃነቷ ተጠብቆ፣ ዳር ድንበሯ ተከብሮ እዚህ የደረሰችው አሊና መሰል ጓዶቹ፣ አዛዥ መሪዎቹ ፍፁም በሆነ ቅንጅትና አንድነት በተሞላበት ስልት ሀገር በማዳን ቆራጥ ተግባራቸው ነው፡፡ ከያኒው እንዳብራራው፤ መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ የኩባው ፊደል ካስትሮ፣ የአየር ኃይሉ አብራሪ ብ/ጄኔራል ለገሰ ተፈራ…በኦጋዴን ግንባር ከጠላት ጋር ከፍተኛ ተጋድሎ በምናደርግበት ወቅት ሀገርንና ህዝብን ከጥፋትና ውርደት በመታደግ ረገድ ሰፊ ድርሻ አላቸው፡፡  ሚሊሻው አሊ በየብስ ታንከኛና እግረኛ ጦርን እያሳደደ ሲመታ፤ በአየር ለአየር ውጊያ ደግሞ ለገሰ የሶማሊያን ተዋጊ አውሮፕላኖችን፣ ሚግ ጀቶችን እርስ በርስ እያጋጨ፣ ከኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እንደ ቅጠል አርግፎ እንደ ጉም ይበትናቸው እንደነበር ታሪክ በደማቁ ዘግቦታል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ዛሬ መከላከያ ሰራዊቷን ሳታቋቁምና ሳታደራጅ በፊት፤ ሀገር በውጭ ወራሪ ስትወረር የሀገሩን ክብር ላለማስደፈር፣ ዳር ድንበር የሚያስጠብቀው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነበር፡፡ ታላቁ የአድዋ ድልም የተገኘው ህዝቡ በአንድነት ተሰባስቦ ባደረገው ተጋድሎ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ (በሀገር ጉዳይ ላይ በአንድነት የመሰባሰብ እሴት ትልቅ የሆነ ሀገራዊ ንቃት ይፈጥራል!...ያለው ምሁር ማን ነበር?”)  ከወራት በፊት የካቲት 23 የአድዋ ድልን በስፋት አክብረናል፡፡ እሱን ተከትሎ ደግሞ፣ የካቲት 26 በየአመቱ ጥቁር አንበሳ በሚገኘውና የነዚሁ ጀግኖች መታሰቢያ በሆነው ‹ድላችን ሀውልት› ባለበት ግቢ ውስጥ ካራማራ ይከበራል፡፡ በያዝነው በዚህ በሰኔ ወር ውስጥ፣ ከፊታችን ባለው በአስራ ስምንት መላው የኢትዮዽያ ህዝብ የዚያድ ባሬን ወራሪ ለመመከት ቀፎው እንደተነካ ንብ ተምሞ በነቂስ የወጣበት ነውና፣ ከወዲሁ እሱን እያሰቡ ማዝገሙ የተለየ ድባብ ይኖረዋል፡፡
የጀግናው አሊ በርኪ እውነተኛ ታሪክን የያዘው የኢሳያስ ሆርዶፋ ስራ የታሪክ አወቃቀሩና የመረጃ አያያዙ እሚደነቅ ነው፡፡ (ፀሃፊው ሬዲዮ ጣቢያ በጋዜጠኝነት ተመድቦ በሚሰራበት ወቅት በተደጋጋሚ አሊ ወደሚኖርበት በማምራት በግሉ ቃለ-መጠይቅም አድርጎለታል፡፡ ለጀግናው ያለው ቀረቤታ ከፍ ያለ ነው፡፡) በእውነቱ እንደ ታሪክም ሊጠና የሚገባው አንድ ራሱን የቻለ ሰነድ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በደምና በላባቸው ያስገኙትና ያኖሩት፣ ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉበት፣ ታላቅ ድል የተቀዳጁበት ገድል ነውና ታሪክም እራሱ በወጉ አስታውሶ ሊዘክራቸው የሚገባው ጀግኖች ናቸው፡፡ ሻለቃ አሊ በርኪ ቱቾ ከወገኖቹ ጋር በመሆን የፈፀመው አኩሪ ተግባር ከቶም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ዘመን ተሻጋሪ የጀግንነት መሰረትንም ጥሏል፡፡ ለታላቅ ጀግንነቱም የያኔዋ የመንግስቱ ኃ/ማርያም ህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የላቀ የጦር ሜዳ ጀግና ሜዳልያ ተሸላሚም ነበር፡፡


Read 455 times