Wednesday, 03 July 2024 00:00

አባቱን ገድሎ እናቱን ያገባው

Written by  ወንዲፍራው መኩሪያ
Rate this item
(3 votes)

ይሄንን ታሪክ፣ የግሪክ ሰዎች ይቅሩ፣ ግዑዛኑ የግሪክ ግድግዳዎችና ትሁቶቹ የግሪክ ዛፎች እንኳን የማይረሱት ነው። በአስደሳችነቱ አይደለም። በአሰቃቂነቱ እንጂ!
ታሪኩ በዘራችሁ አይድረስ የሚባለው፣ የኤዲፐስ ታሪክ ነው። የቲብስ ንጉስ በሞተበት ጊዜ ነው አሉ:- ሌዎስ የሚባለው ልጁ ገና ጡት ያልጣለ የአንድ አመት ድክ ድክ ባይ ነበር። እንደ ወጉ ቢሆን ፣ በሞግዚቶች ስር ለአቅመ ንግስና እስኪበቃ እየተሞረደ ባደገ ነበር። ሆኖም ግን ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ፣ቤተ-መንግስቱ ውስጥ አድፍጠው የከረሙ የስልጣን ጮሌዎች፣በአባቱ መሞት ‘ሀ’ብሎ የጀመረውን የብላቴናውን ዕጦት፣ስልጣን በመንጠቅ ‘ለ’ብለው አስቀጠሉት። ወራሽ ባለበት ተረጋግቶ መተኛት የዛፍ ላይ እንቅልፍ የሆነባቸው ጭልፊቶቹም ሁለት አይናቸውን ዘግተው ይተኙ ዘንድ ብላቴናው ሌዎስን ኤሊስ ወደምትባል ሀገር አካልበው ሸኙት።
ሟሙታ የፈረጠችው ፍርቱናውም አፈር ልሳ የተነሳች ይመስል የዛ ሀገር ገዢ የነበረው  ፔሎፕ የተባለው ንጉስ እጁን ዘርግቶ ተቀበለው። አስራ ስምንት አመት እስኪሞላውም ፀጉሩን እያሻሸ፣ያጣውን የቤተሰብ ፍቅር፣ እየለገሰ አሳደገው። ክሪሲፈስ በሚባለው ልጁ ላይ አስተማሪም አድርጎ ፣በአደራ ሾመው።
ሌዎስ ግን ጊዜያት እያለፉ ሲሄዱ የንጉስ ፔሎፕን ውለታ እየረሳ፣በልጁም ላይ ይጎመዥ ጀመር። አደራውን ቀርጥፎ በመብላት አንድ ፍሬውን ክሪሲፈስንም ማባለግ ከጀለ። በሀሳቡም ገፋበት፣ብላቴናውንም ደፈረው። ድርጊቱንም ከፈፀመ በኋላ በፍራቻ ወደ ተወለደበት ሀገር ሲፈረጥጥ፤የተደፈረው ብላቴና ክሪሲፈስም በሀፍረት እራሱን በከብቶች በረት ውስጥ አንጠልጥሎ ተገኘ። እምነቱን የተበላው አባትም ወደ አምላኮቹ እግር ስር ተደፋ።
“አደራዬን በልቶ ፣ዘሬን አቋርጦ፣ማጀቴን ገልብጦ የኮበለለውን ሌዎስ ክፉውን ካላየሁማ የላችሁም” ሲልም አለቀሰ።
ወደ ትውልድ ሀገሩ ቲብስ የተመለሰው ሌዎስም፣ሀገሪቱ መሪዎቿን አስኮብልላ፣በትረ-መንግስቷም አፉን ከፍቶ ጠበቀው። ህዝቡም “ድሮውንም በጮሌ ተነጥቀህ እንጂ፣ቦታውስ ያንተ ነበር” ብሎ አክሊሉን ደፋበት። እንደ ንጉስ ልማድም፣ከጨዋ ቤተሰብ ጃኮስታ የተሰኘች ሚስት አገባ። ያደረገውንም በሆዱ ይዞ በሰላም ይገዛ ጀመር።
ከልጅ በስተቀር ምንም ያልጎደለው ንጉስ ሌዎስም፣የባለቤቱ ልጅ አለመፀነስ ከንክኖት፣ዴልፊ ወደምትገኝ አዋቂ ዘንድ ጎራ አለ። “ወራሽ አልባ” ሆኖ የመቆየቱን ጉዳይም ተናግሮ “መፍትሄውን በርሶ መጀን” አለ። አዋቂዋም “የኋላው በደልህ እርግማን እየተከተለ እያስከፈለህ ነው” ስትልም ኩም አደረገችው። አለመውለድህን አትጥላው። ምክንያቱም  እርግማንህ “ከአብራኩ የሚወጣው ቀጥፎ ይብላው” ነውና ብላ መልካም ያለመውለድ ጊዜን ተመኝታ ሸኘችው። የወጋ ቢረሳም የግሪክ አምላኮች አይረሱም ነውና ተረቱ።
እንደ እፉኝት፣ መውለድ መሞት የሆነበት ሌዎስ፤ ከሚስቱም ሆነ ከሌላ ሴት ጋር መገናኘት እርም አለ። በተቃራኒው ከወንድ ጠያቂዎች ጋር መታየትን ያዘወትር ጀመር። በዚህ ሁኔታ ብዙ ጊዜያቶች ቢያልፉም ፣ከለታት በአንዱ ቀን  ስሜት ከፍራቻ በላይ ሆኖ ሸበበው። የናፈቀውን የሚስቱን ገላም አስታቅፎ አሳደረው። “ሲፈልጉት በፈረስ፣ሲተውት ደጅ ድረስ” ሆነና፣ ሰኔና ሰኞ ዘጠኝ ወሯን ጠብቃ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ይዛ ከተፍ አለች።
የተወለደው ወንድ ልጅም ለሌዎስ አይጨበጥ የእሳት አሎሎ፣አይቆረጠም የብረት ቆሎ ሆኖበት:- አይገለው ነገር የአምላኮቹን አፀፋ ፈራ፣አይተወው ነገር የትንቢቱን ፍፃሜ ሰጋ። ለአንድ እረኛም ህፃኑን ወደ ሜዳው ወስዶ፣እንዳያመልጥም ቋንጃውን ቆርጦ ለአውሬዎች እንዲተወው በድብቅ ከእናቱ ሰርቆ ሰጠው። እረኛውም የተባለውን ለማድረግ ህፃኑን ከአንድ ገደል ሊገፋው ሲልም፣ የልጁ ፍልቅልቅ ሳቅ ልቡን አራደው። ከእራሱም ጋር እየታገለ እያለ፣ወደ ኮሪነስ የሚሄድ መንገደኛም አይቶት ምን እያደረገ እንደሆነ ጠየቀው። እረኛውም የታዘዘውን ትዕዛዝ ከአዛዡ ውጪ፣ በሙሉ ለመንገደኛው አጫወተው። በስተመጨረሻም መንገደኛው፣ ያለ ልጅ የተቀመጡ የኮሪንስ ገዢዎች ባለሟል እንደሆነና ልጁን ቢወስድላቸው ደስተኛ እንደሚሆኑ በማሰብ ከእረኛው ልጁን ተቀብሎ ወሰደው። ወደ ኮሪንስ እንደደረሰም እንደጠበቀው ከንጉሰ ነገስቱ ሞቅ ያለ አቀባበል ጠበቀው። ንጉሰ ነገስቱም ህፃኑን ተቀብለው በጉዲፈቻም ያሳድጉት ገቡ። ስሙንም ኦዲፐስ ብለው አወጡለት:- ስለት ገብቶባት የተነፋፋች ቋንጃውን በማሰብ።
ኦዲፐስም እንደ ልዑል ያሻውን እያማረጠ፣አፈር አይንካህ ተብሎ አደገ። በአንድ አጋጣሚ ግብር ተጥሎ ያገሬው ሰው እያውካካና እያሽካካ በሚበላበት ሰዓትም፣ከመሃከል አንድ አፉ የሚያዳልጠው ሰካራም ተነስቶ፣ኦዲፐስን የንጉሱ ልጅ እንዳልሆነ አረዳው። ልጅ አለመሆኑ ሲሰማ ሰማይ የተደፋበት ኦዲፐስም፣ወደ አባቱ ሮጦ ስለ ጉዳዩ እውነተኛነት ቢጠይቅም፣ከአባቱ ጥርጣሬውን የሚያስወግድ መልስ ባለማግኘቱ፣ግሪካዊያን ሲጨንቃቸው እንደ አምላካቸው ወኪል ቆጥረው ወደ ሚሄዱባት የዴሊፊ አዋቂ ቤት ሄደ። እዚያም ሄዶ ግን ያገኘው ምላሽ የጠየቀውን ሳይሆን ያልጠየቀውን ትንቢት ሆነ። አዋቂዋም፤ “ወደድክም ጠላህም አባትህን ገድለህ፣እናትህን ታገባለህ ስትል” አስተጋባችበት። ኦዲፐስም የሰማውን ማመን ከብዶት እንደተቀዣበረ፣ትንቢቱ እንዳይደርስ በማሰብ፣ እናቴና አባቴ ከሚላቸው የኮሪንስ ንጉሰ ነገስት በተቃራኒ አቅጣጫ ይጋልብ ጀመር።
ያለምንም ልጓም ሰረገላውን ሽምጥ እየጋለበም  ጠባብ ወደሆነ፣ ሁለት ሰረገሎችን በአንድ ጊዜ ማስተላለፍ ወደማይችል ማሳለጫም ደረሰ። ከተቃራኒ አቅጣጫ ከሚመጣ ጎልማሳ ባለሰረገላ ጋርም ንትርክ ውስጥ ገባ። ጎልማሳውም በደም ፍላቱ ቅርብ አዳሪ ሆነና፣ከሰረገላው ላይ ጎራዴውን መዝዞ ወረደ። ነገር ግን ጥንካሬ በወጣቱ ኦዲፐስ ጎን ነበረችና፣ጎልማሳውን እራሱ በመዘዘው ጎራዴ ሆዱን ሽጦ፣ዘርግፎ ገደለው። ከጎልማሳው ጋር የነበረው አገልጋይም ኦዲፐስን ፍራቻ ከመንገዱ ገሸሽ አለ። ኦዲፐስም ሽምጡን ቀጠለ። ቲብስ ወደ ምትባል ከተማም ደረሰ። በዚያም ያገኛቸው የከተማዎቹ ሰዎች የሀዘን ቆብ የደፉ ሆነው አያቸው። ምክንያቱንም ሲጠይቅ ንጉሳቸውን  ስለተነጠቁ እንደሆነ ሰማ። የንግስቲቱም ወንድም ስፊንክስ የሚባለውን ከቤተመንግስቱ አፋፍ ላይ የቆመውን ጥልማሞት አውሬ ለገደለ ወንድ፣ የንጉሱን አክሊል አቀዳጀዋለሁ እንዳለም አከሉለት።
ኤዲፐስም “የምጓጓለት ህይወት እንደሆነ እንደጉም ብን ብሏል፣ሞቴም በከንቱ ከሚሆን ፋይዳ ይኑረው፣ እኔ እሞክረዋለሁ” በማለት ከሀገሪቱ እንደራሴ ቡራኬ ተቀብሎ ወደ አውሬው አመራ። አውሬውም የአንበሳ ፊትና የንስር ክንፍ ያለው ሲሆን፣ለቀረበው ሰው በሙሉ “እንቆቅልሽ” እያለ ጥያቄ በመጠየቅ፣ያልመለሱትን ሲቆረጣጥም የከረመ ነው።
ኦዲፐስንም ሲያየው እንደልማዱ የስላቅ ሳቁን ፈገግ በማለት “እንቆቅልህ” አለው። ኦዲፐስም “ምን አውቅልህ?” ብሎ ተጠጋው። “ጠዋት አራት እግር፣በቀትር ጥንድ እግር ፣ሲመሽ ስሉስ እግር ምንድን ነው?” አለው። በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ፍራቻ አልባ ጨረር የሚለቁት አይኖቹን ትንሽ ካንከራተታቸው በኋላም፣ ኦዲፐስ “ሰው አለ!” አለ የመጣው ይምጣ በማለት።  “ሲወለድ እየዳኸ በአራት እግር፣ሲያድግ ቀጥ ብሎ በሁለት እግር፣በሽምግልናው ዘመን በከዘራ በሦስት አግር የሚሄድ ከሰው ውጪ ምን አለ?” ብሎም ለስፊንክስ አከለለት። መልሱን የሰማው ስፊንክስም ወዲያውኑ እራሱን ከገደል ላይ ወርውሮ ፈጠፈጠ። ለካስ ያልተመለሰ እንቆቅልሽ ነበር አውሬ ያደረገው።
ከአፋፉ በድል የተመለሰው ኦዲፐስም ቃል የተገባችለትን ንግስት ጃኮስታን አግብቶ ነገሰ። አራት ልጆችንም አፈሩ። ከለታት በአንዱ ቀንም ከኮሪንስ መርዶ ነጋሪ መጣ። ኦዲፐስንም የአባቱን ፔሎፕስ ሞት አረዳው። ነገር ግን መርዶ ነጋሪው በአንድ መርዶ ብቻ አልቆመም። ንጉሱ የእርሱ እውነተኛ አባት እንዳልሆነም አከለለት። በልጅነቱ ቋንጃው እንደተቆረጠ፣ ከእረኛ ላይ ወስዶ ለንጉስ ፔሎፕ የሰጣቸው መልዕክተኛም እኔ ስለሆንኩ በመረጃው አትጠራጠር አለው። በቆመበት እንደጨው አምድ የደረቀው ኦዲፐስም፣ትንንሽ የድንዛዜ ቅፅበቶችን ካሳለፈ በኋላ፣ለጋሻ ጃግሬዎቹ “ለዚህ መልዕክተኛ በልጅነቴ ወስዶ የሰጠኝን እረኛ፣ወልዳችሁም ቢሆን አምጡልኝ!” አለ። አሽከሮቹም በእግር በፈረስ ብለው አንድ አዛውንት አመጡለት። አዛውንቱም የኦዲፐስን አይን እያየ ለመልዕክተኛው ቋንጃው የተቆረጠ ህፃን የሰጠው እሱ እንደሆነ መሰከረ። ከማን እንደተቀበለው ሲጠየቅም፤ “ከንጉስ ሌዎስ ለአውሬዎች እራት እንዲሆን እንደተሰጠና የንጉስ ሌዎስ የገዛ ልጁ እንደሆነም፣ “የሞቴን ቀን ይስጠኝም!” ሲል ማለ። ኦዲፐስ የቱንም ያህል ከመወለዱ አስቀድሞ የተነገረበትን ንግርት ለመሸሽ ቢርቅም፣በተቃራኒው ንግርቱን ለመፈፀም እንደታገለ ገባው፦ አባቱንም ገሎ እናቱን እንዳገባም አወቀ።
ይህንን ትዕይንት ከኋላ ሆና ስትሰማ የነበረችው ንግስት ጃኮስታም ምድር ተገለባበጠችባት። ከተቀመጠችበትም ቦታ እሮጣ ወደ እልፍኟ ገባች። የማይደርስ የደረሰበት ኦዲፐስም፣ ንግስቱን ከአፍታ በኋላ ተከተላት። ንግስቱም እራሷን አንጠልጥላ፣አይኗ ተገለባብጦ ደረሰባት። ተንዘረዘረም፣አበደም። በክፋቷ ሰቅዛ የያዘችውንም አለ፣ ላለማየት በሚመስል አኳኋን የጆካስታ ገመድ የተሰካበትን ሹል ብረት አውጥቶ አይኑ ውስጥ ሸቀሸቀው። ከዚያም በኋላ እስከለተሞቱ፣ አለምን በአይኑ ዳግመኛ ላያይም ተሰናበታት። ያችንም የተወለደባትን፣ የነገሰባትንና፣እናቱን ያገባባትንም ከተማ ጥሎ ወጣ። እየተንከራተተም ኖረ።
ይህ ታሪክ ደመነፍሳዊ የሆነን፣በወንድ ልጆች ላይ የሚታይ ማለትም ወደ እናታቸው የመሳብና አባታቸውን እንደተቀናቃኝ የመቁጠር ያልተገራን ባህሪን በመግለፅ ለሲግማን ፍሮይድ “ኦዲፐስ ኮምፕሌክስ” ትወራ መዘወሪያ ሆኗል። ከምንም በላይ ግን ፍሬድሪክ ኒቼ ‘Amor Fati’  “እጣ ፈንታን መቀበል” ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ኦዲፐስስ የቱንም ያህል በመሸሽ ያላመለጠው ነገር ዕጣ-ፋንታውን አይደል? መፍትሄውም ኒቼ እንዳለው ‘love your fate’ ወይም ‘ዕጣ-ፋንታህን ውደደው’ ነበርና! ባንወደውስ ምን ልናመጣ!

Read 713 times