Monday, 01 July 2024 08:50

የዓለማየሁ ገላጋይ ጦርነት!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

በተመሳሳይ ቃና፣ብዙም በማይለያይ የታሪክ ሀዲድ፣ ዳናውን እያሰቀመጠ፣የኖረው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ዘግይቶ ከመወለዱም ባሻገር እየዳኸ ቆይቶ፣ቶሎ ከመሬት ያለመነሳቱን የታሪክ ገጾችን በገለጥን ቁጥር እንረዳለን። ከጥቂት ሥራዎች በቀር ያለማፈንገጥ አንገቱን ደፍቶ፣በተመሳሳይ ዘውግና ሥነ ጽሑፋዊ ፍልስፍና ዕድሜውን መቆርጠሙ ምቾት የሚከለክልና የሚጎረብጥ ነገር አለው።
የጉዟችን ጎዳናዎች ጥርጊያ፣የመከራዎቻችን የሽግግሮቻችን ጤዛነት፣ሥራዎቻችን ጤናማ እንዳልሆኑና ከሥነ ልቡናዊ ማንነታችን ጋር በአንድ ወስካ የተጠመዱ የሚያስመስላቸው ሰበቦችም ብዙ ናቸው። ለዚህ ፍተሻ  ቃላቸው ጸንቶ፣ልባቸው ከቀና የሀገር ልጆች መካከል፣የኑሮና የጥበባችንን መስቃ በመፈተሽ፣ ከሚታመሙት ውስጥ ለረዥም ዓመታት፣ በጓዳ አድፍጦ፣ሩጫው ከረር ሲል ያፈተለከው ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ አንዱ ይመስለኛል።
ዓለማየሁ፣ ለብዙ ዓመታት በጋዜጠኝነት ሪፖርት ሲለቅምና ጋዜጦች ላይ መጣጥፍ ሲያቀርብ ላየው፣ ነፍሱ በጥበብ  እንደ ጧፍ የተለኮሰች አይነት አልነበረም። የምናቡ ግድግዳዎች በሐሳብ ሲቧጠጡ፣ልቡ በሕይወት ዋልሴ ቁልቁል ሰትሸረከት፣በማዕበል ስትናወጥና ጎንበስ-ቀና ስትል ሀገር ምድሩ አላወቀለትም። ይልቅስ እንደ ቄብ ዶሮ ሳያስካካ፣ሁሉን በውስጡ አምቆ፣ በእልፍኙ ተሰውሮ እየጫረ፣ ራሱን ካበቃ በኋላ”አጥቢያ”የተባለች መጽሐፉን ጽፎ ለኀያሲ አብደላ እዝራ ሲያቀብለው፣አብደላ ግር ተሠኝቶ ነበር። እናም፣ ”የራስህን ወርቅ ይዘህ በሰው ጠጠር ትደክማለህ” በማለት እንደወቀሰው፣ከአጥቢያ መጽሐፍ ጀርባ ላይ ከታተመው አስተያየት ተረድተናል።
በርግጥም ዓለማየሁ ያኔ ኅያሲና ጋዜጠኛ እንጂ የፈጠራ ድርሰቶች ጌታ አልነበረም። የበኩር ሥራውን ለገጸ ንባብ ካበቃ በኋላ፣ያ ትንቢታዊ የተባለ መጽሐፉ፣ የአራት ኪሎን መፍረስ በእርጥባን አባት ልብ ውስጥ አስጸንሶ፣እንደጎመራ ሊፈነዳ ሲተናነቅ አሳየን። ከሁሉ በላይ ሀገራዊ በሽታችን የሆነውን ሥነ ልቡናዊ መዘዝ አደባባይ ላይ አሰጣው። ከዚያ በኋላ አሥራ ስድስት የልቦለድና ኢ-ልቦለድ ሥራዎችን ሠርቶ ዘውድ ደፍቶ አሳየን። ከእነዚህ ሁሉ መጻሕፍት አብዛኛዎቹ ከእርከን ወደ እርከን ከፍ እያሉ የመጡ ነበሩ።
ከአጠቃላይ ሥራዎቹ በቅርቡ የሠራቸውና በአንድ የተከተቱ መጣጥፎቹ ጥራዝ የዓለማየሁ ገላጋይ ሌላ መልኮች ሲሆኑ፣ ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ የደከመውን ድካምና ያደረገውን ጥረት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። “ማዕበል ጠሪ ወፍ”በሚል ያሰባሰባቸው መጣጥፎች፣ የተለያዩ ሥነ ጽሑፋዊና ማኅበራዊ ኂሶችንና ሀገራዊ ቁጭቶችን ያካተተበት፣ በ250 ገፆች ጠርዞ፣ በአብዛኛው ከአደራደራቸው ጀምሮ  የዘመንንና ሁነቶች በቅደም ተከተል ለማሳየት የሞከረበት ሥራ ነው። በዚህም መሠረት የአማርኛ ቋንቋ ከግዕዝ ጋር እንደ አባትና ልጅ፣ከዚያም ለአቅመ አዳም ደርሶ ጎጆ እንደወጣ ሰው አድርጎ፣ የምሁራንን ማስረጃ መሠረት በማድረግ ለማቅረብ ሞክሯል።
ለዚህ ጥናቱ በዋናነት የዘመኑን ምሁር ፕሮፌሰር ታምራት አማኑኤልን እየጠቀሰ፣ አማርኛ በሦስቱ ነገሥታት ዘመን በጉልበቱ ድሆ፣ወፌ ቆመች ብሎ እየተንገዳገደ፣ እንደመጣና ራሱን ችሎ እንደቆመ ያሳያል። በዚህም መሠረት ሦስት ቦታ ሲከፍሏቸው እንዲህ ይጠቅሳል፦
ዐፄ ዐምደ ፅዮን
ዐፄ ሱስንዮስ
ዐፄ ቴዎድሮስ
በሌላ በኩል፣ግዕዝ የአንድ ሀገር ቋንቋ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር አዳምን ያናገረበት የዐለማችን ቋንቋ ነው የሚሉትን ሊቅ አለቃ አስረስ የኔ ሰውን አተያይም ያነፃፅራል። ዓለማየሁ ከዚህ የመነሻ ርዕሰ ጉዳይ ባሻገር የሚገርሙና የሚደንቁ ርዕሰ ጉዳዮችን ያነሳል። አንደኛው ገራሚ ነገር የኮከብ ደራሲዎቻችን የትውልድ ዘመን በአንድ የዘመን አንጓ መታጨቅ ነው። ይህን ስናይ ምዕራፉን የከፈቱት ጸሐፌ ተውኔቱና ገጣሚው መንግሥቱ ለማ ሲሆኑ፤ የተወለዱት በ1921 ዓ.ም ነበር። ከእርሳቸው በመቀጠል በመደዳ ሠልፍ ይዘው ወደዚች ምድር የመጡት፣ዳኛቸው ወርቁ፣ስብሀት ገብረእግዚአብሔር፣መንግሥቱ ገዳሙ፣አሰፋ ገብረማርያም፣ሥህለ ሥላሴ ብርሃነማርያም ናቸው።ትውልዳቸውም 1928 ዓ.ም ነው። በርግጥ አምስት ደራስያን በአንድ ዓመት መወለዳቸው እንደ ትዕንግርት የሚታይ ነው። ከዚያም በቀጣዩ ዐመት በ1929 ዓ.ም ጸጋዬ ገብረመድኅን፣በዐሉ ግርማ፣ሰለሞን ዴሬሳ፣ተስፋዬ ገሠሠና ዮሐንስ አድማሱ፤ለጥቆም በ1923 ዓ.ም ታደሠ ሊበን፣በ1925 ዓ.ም አቤ ጉበኛ፣በ1926 ዓ.ም ብርሃኑ ዘርይሁን፣አስፋው ዳምጤ፣ጳውሎስ ኞኞ ተወለዱ።
ይህ የጥበብ ሰዎች መግተልተል ክስተት እንጂ አጋጣሚ አይመስልም።በአንድ ዐሠርት ውስጥ የሀገሪቱን ኮከብ ደራስያን ማግኘት ጉድ የሚያሠኝ ነው። አንዳንዴ ተፈጥሮና ፈጣሪ የዚህ ዐይነት ዐመል ያላቸው ይመስል ተመሳሳይ ነገሮች በሌሎች ሀገራትም ይከሰታሉ። ታላላቅ ሰዎች በዐመታት ቀርቶ በአንድ ቀን እንኳ ይወለዳሉ። ለምሳሌ የዐለማችን ታላቁና ተወዳጁ መሪ አብረሃም ሊንከን፣ በተወለደበት ዕለት የዐለማችን የሥነ ሕይወት ዐለም ያሽከረከረው ቻርልስ ዳርዊን ተወልዶ ነበር። የዚህን ዐይነቱን ገጠመኝ ከዐለም አቀፍ ሁነቶች ጋር ስናስተያየውም፣የእንግሊዝ ሳይንሳዊ ግኝት ጣሪያ የነካው በናፖሊዮን ጦርነትና በአንደኛው የዐለም ጦርነት መካከል መሆኑ፣ የአሜሪካው ዕንቁ ቤንጃሚን ፍራንክሊን በወጣ ዘመን፣ አሜሪካ ታላላቅ መሪዎችንና ብርቅ ሰዎችን ማፍራቷ ሊጠቀስ ይችላል።።
ዓለማየሁ እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸውንና በአንድ የዘመን ሰንሰለት አጽቅ ያሠርናቸውን ደራስያን የሁለተኛው/የመካከለኛው ዘመን ደራስያን እያለ ይጠራቸዋል፤ የአማርኛን ሥነ ጽሑፍ ወደ ዘመናዊነት ፈቅ አድርገውታል ብሎም ያምናል። ለዚህም ሥራቸውን ዋቤ እየጠቀሰ ለማሳየት ይሞክራል። በሥነ ግጥሙ ዐለም መንግሥቱ ለማንና ጸጋዬ ገብረመድኅንን እያስተያየ፣በቅደም ተከተል፣አንዱን የኮሜዲ፣ሌላውን የትራጀዲ ኮከቦች ያደርጋቸዋል። ከዚህ ጋር አያይዞ በመላው ዐለም ተከስቶ የነበረውን “ጥበብ ለጥበብነቱና ጥበብ ለማኅበራዊ ፋይዳው”የሚለውን የጎራ ልዩነት፣ ለሥነ ጽሑፍ ዕድገት እንዴት እንደተጠቀሙበት ይጠቅሳል።
በዚህ ጎራ ሰለሞን ዴሬሳ አፈንግጦ፣ደበበ ሠይፉ፣አቤ ጉበኛና ዮሐንስ አድማሱ ጥበብ ለማኅበራዊ ፋይዳው በሚል ተታኩሰዋል። ዓለማየሁ፣ ዳኛቸው ወርቁም በይዘት እንኳ ባይሆን በቅርጽ አምጿል ባይ ነው። ሰለሞንማ ተደጋጋሚና ተመሳሳይ ነገሮች ባሕል በሚል መታገጊያ ታጥሮ እንዳማረረው ጠቅሷል፤እንዲህ፦”ባሕል እንደሚሉት የአማርኛ ቃል የሰለቸኝ ያማርኛ ቃል የለም”እስከማለት ደርሷል።
ሌላኛው የዓለማየሁ ትኩረትና ቁጭት ሀገራችን ኢትዮጵያ ያሳለፈችው መከራና ሠቆቃ እንዴት የማኅበረሰባችንን ፍልስፍናና አተያይ፣በተለይ የደራሲዎቻችንን መንገድ አልቀየረውም?..የሚል ቃንዛ ነው። የዓለማየሁ ዋልሴ ያስመዘዘው ሥነ ጽሑፋዊ ጦርነት፣ ባብዛኛው ወደዚህ ያዘመመ ነው። የዓለማየሁ ገላጋይ የብዙ ጊዜ ፍልሚያው፣ ለራሱ ሀብት ማግኘት፣ኑሮውን የማመቻቸት ቃቃ አይደለም። ጋራ ላይ ወጥቶ ቢጮህ፣ጥሩምባ ይዞ ቢነፋ፣እግዜርን ቢወቅሰው፣ወደ ሰማይ ቢያፏጭ፣ወይም ሕዝቡን አግድም ቢገላምጥ “ወገኔ ጓዳው አይጉደል፤ረሀብ አይፈትነው” ብሎ ነው።
ይሁን እንጂ አንዳንዶቻችን ይሄን ጩኸት “እንዴት ፈጣሪን ትሟገታለህ?...እንዴት መንበሩን ትዳፈራለህ?”ብለን እንቆጣለን።አንዳንዴም፣ እንደ ጴጥሮስ ሠይፍ እንመዝበታለን፤ጌታ ግን ጴጥሮስ እንዳለው “ሠይፍህን ወደ ሰገባው ክተት!”ይላል። ጦርነቱ የሠይፍ አይደለምና! የአሁኑም  የዓለማየሁ መጽሐፍ ጦርነት ወደ ላይ አይደለም፤ወደጎን “ለምን አንነቃም?..ለምን እንተኛለን?” የሚል ነው።
”በዐለማችን ላይ የተፈጠሩ ነውጦችና ለውጦች፣እንዲሁም ታላላቅ ጦርነቶች በኅብረተሰቡ አኗኗርና ፍልስፍና ላይ ለውጥ ካመጡና የከያንያኑን አመለካከትና የጥበብ ሥራዎቹን ዘውግ ከቀየሩ እኛ ሀገር ያለፍንባቸው የረሀብና የመከራ ዐመታት እንዴት በሥራዎቻችን ለውጥ አላመጡም?” ነው ሙግቱ።
እነዚህ ጥያቄዎቹና ቁጭቶቹ የሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች እኔን በግሌ ማርከውኛል። እውነት ነው፤እኛ ረሀብ መጥቶ ጀርባችን እስኪላጥ ገርፎን ጠዝጥዞን ሲሄድ፣ ተመልሶ መጥቶ ደግሞና ሠልሶ፣ በዚያው ሁኔታ እንዳያገኘን፣ራሳችንንና ሁኔታዎቻችንን የማንለውጠው ለምንድነው?... ደራሲዎቻችንስ ይህ ነገር እንዳይደገም፣የሕመሙን ጥልቀትና ማምለጫ ሽንቁሩን የማያሳዩን ለምንድነው?...ቢያንስ ቀለማቸውን ያልቀየሩት ለምንድነው? የሚል ነውና ጤናማ ጥያቄ፣ትክክለኛ ቁጭትም ነው። ጠላት ድንበራችንን ጥሶ ገብቶ፣ሕዝባችንን በግፍ ጨፍጭፎና አዋርዶ፣ድል የለመደችን ሀገር በሽንፈት አንገት ሲያስደፋ፣እንዴት የደራሲዎቻችን አእምሮ አላመጸም?..እንዴት አልተቆጣም?”የሚል ቁጭት የዓለማየሁ ጽሑፎች ውስጥ ቢደመጥም፤በሌሎቻችን ልብ ያለማስተጋባቱ አጥንት ያሳክካል ብዬ አምናለሁ።
ዓለማየሁ የኛን ሀገር ሲወቅስ ለማንጸሪያነት ወደ ውጭም ዘወር ብሎ የሌላ ሀገር ከያንያንን  ያመጣል፤ እንዲህ እናየዋለን፦በአንዳንድ የለውጥ ዘመን ተወላጅ ደራስያንና ፈላስፎች ሕይወት ላይ በውጭ የተደረጉ ጥናቶች የሚያመላክቱት ይሄንኑ ነው። ከአሜሪካ አብዮት ጋር አያይዘን የጀርሚ ቤንታን ሕይወት ስንፈትሽ፤ ከእንግሊዝ የተሃድሶ ለውጥ ጋር አገናኝተን፣ የጆን ስቱዋርት ሚልን ሥራ ስንዳስስ፤ ከፈረንሳይ አብዮት ጋር አሰናስለን ጆን ሞርሊን ስናገኘው የምንረዳው ይህንኑ ነው። ወደ ሩስያ አብዮት ብቅ ካልንም ዶስተየቭስኪ፣ቶልስቶይ፣ቼኮቭ፣ቱርጌኔቭና ጎርኪን የመሳሰሉ ብርቅዬ ደራስያን እናገኛለን።”ይልና የግለሰቦች ስሜት መነካት እንኳ የሚያመጣውን ለውጥ ያስመለክታል።
እናም የወለፈንዱ ድርሰት ተጠቃሽ አየር ላንዳዊውን ሳሙኤል ቤከትን ይጠቅሳል። ቤከት ከጓደኞቹ ጋር ስለ አንድ ፊልም እየተጨቃጨቁ ሳለ፣በድንገት የመጣው ሰው በጩቤ ወግቶት ይሄዳል። ቤከት ሆስፒታል ገብቶ ከዳነ በኋላ የወጋውን ሰው ለምን እንደወጋው ምክንያቱን ለማወቅ ፍለጋ ይሄድና አግኝቶ ይጠይቀዋል፤ይሄኔ ወጊውም ለምን እንደወጋው ያለማወቁን ይነግረዋል። ከዚህ በኋላ የሳሙኤል ቤከት አእምሮ ባመጣው ጥያቄ፣ ሕይወት መልክ የሌላት ከንቱ ናት ብሎ፣ ወደ አዲሱ የአጻጻፍ ዘውግና ፍልስፍና ሲስፈነጠር ያሳያል። እና ሕይወት ስትገርፈው ዜማውን የማይቀይር ማን ነው?...የቁጭቱ ጥያቄ ነው። ዓለማየሁ ኩሬነት ሰልችቶታል፤ምድራችን ላይ የሚፍለቀለቁ ምንጮች አዳዲስ ቀለሞች ይዘው ሲመጡ ማየት ጎምዥቷል። የተስፋው አድማስ ግን ርቋል...
ከፈረንጆቹ ያየነው ነውጥና ለውጥ የሚሆነው ሰው፣ ስለ ሕይወት ሲጠይቅ፣በገጠመኞቹ ሕመም ሕሊናው ሲመዘመዝ ነው የሚል እሳቦት አለው- ዓለማየሁ። ደሞ እንዲህ ያስባል፤ይፈትላል፤ያባዝታል-እኛ ግን የመጣ ሁሉ ጋልቦን ሲሄድ መልሰን እዚያው ነን። አንለወጥም፤አስተሳሰባችንም እንደ ሐውልት ተገትሮ ቆሟል። እኔም ከዓለማየሁ ጋር እስማማለሁ፤በዘመነ አክሱም፣በዐፄ ካሌብ ዘመን እስከ ደቡብ ዐረቢያ የነበረው ገዢነታችንና ክብራችን ወርዶ፣ የደቡብ ዐረቢያ የንግድ ማዕከላችን የቀይ ባሕሩ የንግድ መስመር የበላይነታችን በፐርሽያኑ መነጠቅና፣ ጠብበን ጎጇችን መከተታችን ቆጭቶን፣ከመሸሽ በቀር መች ጠየቅን?..
በዐሥራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን የመጡትን ሁለት ፈላስፎች፤ ዘርዐ ያዕቆብና ወልደ ሕይወት ጩኸት መች ኮረኮረን?..መች ጆሮ ሰጠነው?..መች አዳመጥናቸው?...በታሪካችን የተነሳው ነውጥስ መች አናወጠን? ወደ ሥነ ጽሑፋችን ስንመጣም አልፎ-አልፎ ጣልቃ ከገቡት ፋንታዚዎችና ስትሪም ኦፍ ኮንሸስነስ በቀር፣ከእውነታዊነት መች ዘወር አልን?...መች ተነቃነቅን ? መች ከአጥር ወጣን?”
ስንት መቶ ዐመታት የዘለቁ የውጭው ዐለም የሥነ ጽሑፍ ዘውጎች፣ እስከ ዛሬ መች ምድራችንን ረገጡ?...በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ለሥልጣኔ የጀመርነውን መንገድ ገትተን፣እንደ ጃፓን ወታደራዊ ገዢዎች በራችንን ጠርቅመን፣ወደ ምናኔ ከገባን በኋላ የዐለምን ጉዞ፣መች በር ከፍተን አየን?..
ዓለማየሁም ስለ ሥነ ጽሑፉ የሚለው ይህንኑ ነው።...በተለመደ የአጻጻፍ ስልትና ዘውግ፣ በአንድ አቅጣጫ በተኮራመተ ፍልስፍና ከደሳሳ ሕልማችን መቼ ወጣን? ዓለማየሁ ከዚህ ቁጭት ባሻገር “አንቱ” የተሰኙትን ደራሲዎቻችንን ቀለም፣ፍልስፍናና የሕይወት መልኮች በር አንኳኩቷል። የሚወደሱትን አወድሶ የሚወቀሱትን ወቅሷል። ዳኛቸው ወርቁን፣ በዐሉ ግርማን፣ጸጋዬ ገብረመድኅንን፣ወዘተ እያነሳ በመተረክ ገጾች ላይ ደክሟል። እነዚህ ሁሉ ከንቱ አይደሉም፤እነዚህ ሁሉ የቁጭትና ለወገን ካለው ቅንዐት የበቀሉ ሥራዎች ለጥበባችንና ለሀገራችን ማኅበራዊና ሥነልቡናዊ ችግሮች ድል የተጠሙ ናቸው።
አንዳንድ ቦታ” እንደ ዛዶካውያን “ዐይነቶቹ ነገሮች”፣ወደ ክህነቱ አገልግሎት መውሰዱና በንጉሥ ዳዊትና በልጁ ሰለሞን ወደነበረው ካህኑ ሳዶቅ ወገኖች እንጂ ወደ ባሕታዊነት ይወስዳል በሚል የተጠቀሰውና መሠል ጉዳዮች ጥያቄ ቢያስነሱም፤አጠቃላይ መጽሐፉ ሲታይ ጠቀሜታው የትየለሌ ነው። ለሚያነብቡት ሰዎች የሚሰጠው ግንዛቤና ለጥናት የሚከፍተው በርም ሠፊ ነው። ይሁን እንጂ በመጽሐፉ ውስጥ ሁሉ የዓለማየሁ ድግስና የኂስ ፍልሚያ፣የሙገሳ ታምቡር ደስ እንደተሠኘን እንድንጨርስ የሚያደርገን ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ ታሪክ፣ ኮርስ ለወሰዱ እንኳ ተጨማሪ ዘለላዎች አሏት።
መጽሐፉ ውስጥ መካተት አልነበረባቸውም፣የሚል ቁጭት የሚፈጥሩ ሁለት መጣጥፎች አሉ። አንደኛው የተለያዩ ግለሰቦችን ስም የሚጠራውና በሁለተኛው እትም  የተቀነሰው ሲሆን፣ ሁለተኛው “ግለ-ታሪክና ወጣ ገባነቱ” በሚል ርዕስ በደበበ ሠይፉ የሕይወት ታሪክ ሥራ ላይ ለተፈጸመ ቸልተኝነት የተሰጠች ምላሽና ተቆርቋሪነት ናት። የተጻፈችበት መንገድ፣ቃናና የሞራል መስመር ለእኔ አልተመቸኝም፤ምክንያቱም የዓለማየሁን ውስጣዊ መልክና ቀለም ይቀይርብኛል። ለነገው ትውልድ የሚያልፍ ሰነድ ላይ የማይገባ እርሾ  ሊቀመጥ አይገባም የሚል ሙግትም አለኝ። ...ጠመንጃ ይዞ ፎቶ መነሳት፣ሽለላና ቀረርቶ ከባዶ ጎተራ ጋር የምናወርሳቸው አንሶ፣ ሥነ ጽሑፋችን ውስጥ እንደ ጴጥሮስ የመዘዝነውን ሰይፍ ካጠቀሰው ደም ጋር ማስቀመጥ የለብንም።...በዚህ ጉዳይ ዓለማየሁ ተሳስቷል፤ሲጠረዝ እያዩ፣አውቀው ዝም ያሉትም ሰዎች አሳስተውታል።
ከአዘጋጁ፡-
 ደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አያሌ መጣጥፎችን አስነብቧል፡፡ በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ትንተና አቅርቧል፡፡ ደረጀ በላይነህ ገጣሚና አርታኢም ነው፡፡ 12 ያህል መጻሕፍትን አሳትሞ  ለአንባቢያን አድርሷል፡፡


Read 533 times