Monday, 01 July 2024 09:02

የመፈከር ሙክርታዎች፤ ‹‹የጊዜ ሠሌዳ››

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

    ‹‹ጣና ልቡን ባርኮ፣ ዓባይ ፍቅሯ ያልፋል፤
ሰው እንዴት ተጉዞም፣ ተኝቶም ይገዝፋል፤›› [ገጽ 56]

ገጣሚነት ትጋትን ይጠይቃል፤ በመጠኑም ቢሆን፣ አንድ ገጣሚ ዘጋቢ መሆን አይጠበቅበትም፤ ባለ ቅኔ ቢሆን ይመረጣል፤ ጋዜጠኛ አንድን ክስተት አስመልክቶ ተጨባጭ የሆነ ዜና ይዘግባል፤ የጋዜጠኛ ተቀዳሚ ዓላማ በዜናው ተጽእኖ መፍጠር ሳይሆን፣ አድማጭ ተመልካችን ተደራሽ ማድረግ ነው፤ ገጣሚ ደግሞ ጥበባዊ በሆነ መልኩ ተርጉሞ ያቀርባል…
…ገጣሚ ስለ አንድ ሁነት፣ ወይም  ሀሳብ የሚነግረን፣ ጋዜጠኛ ከሚነግረን የተለየ መሆን አለበት፤ ጋዜጠኛ ቀጥተኛ፣ ግልጽ፣ ተጨባጭና ‹objective› የሆነን ዜና ለአድማጩና ለተመልካቹ ይሰጣል፤ ገጣሚ ደግሞ ከሥነ-ውበት ጋር እያዛመደ፣ እየተረጎመ፣ እያፍታታ፣ በቅኔ እየለወሰ ይሰናኛል፤ ግጥም እንደ ዜና ተነብቦ የሚታለፍ ሳይሆን ዘለዓለማዊነቱ ዕሙን መሆን ያለበት የኪነ-ጥበብ ሁሉ አውራ ነው።
ገጣሚ መንበረማርያም ኃይሉ፣ በ‹‹የጊዜ ሠሌዳ›› የመጣውን አብዮት ታክካ አታላዝንም፤ አትዘግብም፤ ዜናነትን ወግድ ብላ ከዕውን ያልራቁ ምናባዊ ሀሳቦችን አንጸባርቃለች፤ ዛሬ ላይ ተቸንክሮ ስለ ትላንት ማላዘን፤ ወይም ትምኪህተኝነት አልያም ዳተኝነት የጎበኘው ስንኝ ጥበባዊነት ይጣላዋልና፣ ማላዘንና መኩራራት በመድበሉ አይስተዋሉም።
ሥነ-ግጥም የሀሳብ፣ የቋንቋ፣ የምትና ምጣኔ፣ የሥነ-ውበት፣ የሙዚቃዊነት…ወዘተ. ብቻ ውቅር አይደለም፤ ሥነ-ግጥም ይኼ ነው ተብሎ የተሠፈረ መለኪያ ያለው አይመስለኝም፤ ምናልባት ከተደመጠ ወላ ከተነበበ በኋላ ለዘለዓለም የማይረሳ መሆን ያለበትም ይመስለኛል፤ ነፍስን የማተራመስ አቅም ያለው ቢሆንም መልካም ነው፤ እንደ ዜና ተነብቦ የማይረሳ፤ ከመዘገብ አልፎ ሕይወትና ዓለምን በሥነ-ውበት መፈከር የሚችል መሆን ይገባዋል፡- ‹‹ቤት ያፈራው ፍቅር›› እንዲል በረከት በላይነህ።
ዘለስ ሲል፣ ሥነ-ግጥም በንባብ ወቅት አታካች እንዳይሆን፣ የሀሳብ ተያያዥነትን ዕውን ለማድረግ፣ ፍሰትን ለመጠበቅ…ወዘተ. አያያዥ ቃላትን ይሻል፤ ሆኖም እነዚህ አያያዥ ቃላቶች (በአብዛኛው የዚህ ጊዜ ገጣሚያን ሥራ ላይ የሚስተዋሉ ናቸው፤ ለምሳሌ፡- እና፣ ስለዚህ፣ ዳሩ ግን፣ ውዴ፣ እቴ፣ ሆኖም እና ሌሎችም) እነዚህም፣ የግጥምን ዜማ ይሸራርፋሉ፤ ደንቃራነታቸው ዕሙን ነው፤ ያታክታሉ፤ አንባቢ ስንኞቹን በሚገባ፣ በምጣኔ እንዳይዘፍናቸው ይከላሉ፤ ያልተመጠነ ግጥም ዜማ አልባ ሊሆን ይችላል፤ ‹‹የጊዜ ሠሌዳ›› ከዚህ ጣጣ የፀዳ ነው፤ ሆኖም፣ አንዳንድ የምጣኔ ክፍተቶችን አስተውዬአለሁ።
በዚህ ዘመን፣ በመርቀቅ ሰበብ ቃላት ላይ በመራቀቅ ፍጆታ የሥሜትንና የዕውነታን አንድነት የሚያባክኑ ገጣሚያን ብዙ ናቸው፤ ቃላትን ካለ ጎራቸው እየዶሉ ትርጉም የሚያዛቡ ማለቴ ነው፤ ሌላኛው ጣጣ በአርአያ ገጣሚያን ጥላ ሥር ሆነው የኩረጃ ያህል የተጠጋ ግጥምን ለንባብ ማቅረብ ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ የሥነ-ግጥምንና የሥነ-ውበትን ተራክቦ በአግባቡ ባለመለየት ዕውነታን፣ የዓለምን ስብጥርጥር ገጽታ በአግባቡ መፈከር ያለመቻል ጣጣ ነው፤
መንበረማርያም ከእነዚህ ጣጣዎች የጸዳ መድበል ይዛ መጥታለች። ሥነ-ውበት ላይ ሙጥኝ ብላ ሀሳቧን በጥበባዊ መንገድ ትገልጻለች፤ የትም ብንሄድ ሀሳብ አለ፤ ሀሳብን የምንገልጽበት መንገድ ለእየቅል ነው፤ ለዚህም በመድበሉ ከ[ገጽ 56] ላይ፡-
‹‹…ስለምን ተገኘሁ?
ስለምን ተመኘሁ?
በሞተ ሸንበቆ፣
መኖርን መዘመር፤
ናፍቆትን መዘከር፤
. . . . .ለምን?
ጊዜ ትርጉም አለው፤
ጊዜ ሥልጣን አለው፤
(ጊዜ መልስ ይሰጣል?)
የለም… መልስ ይዞ እየሄደ፣
ጥያቄ ያመጣል፤…››
ስትል ትሰኛለች፡፡ የግጥም ሀሳብ የሚገለጽበት መንገድ ፍዝ፣ አታካችና ዘጋቢ መሆን እንደሌለበት ዕሙን ነው፤ ግጥምን ጥንካሬ ከሚያድሉት መስፈርቶች አንዱ ሀሳብ የሚተረጎምበትና የሚገለጽበት ዘዴ ነው፤ ገጣሚ ሀሳቡን ለመሰደር የሚመርጥበት ስንኝ ጥበባዊ በሆነ መንገድ የተቃኘ መሆን አለበት።
‹‹የጊዜ ሠሌዳ›› የጊዜን ዲያሌክቲክስ ማዕከል ያደረጉ ስንኞች የታጨቁበት መድበል ነው፡፡ በመድበሉ ሂደት፣ ሕይወት፣ አበባ፣ ጣዕም፣ መዓዛ፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ፍቅር፣ ጸዳል… በተለያዩ ዐውዶች ውስጥ ተተርከዋል፤ ሥነ-ውበትና ሥነ-ሕይወት ተዛምዷቸው በዚህ መድበል ተስተውሏል። ከ[ገጽ 10] ላይ እንሆኝ ማሳያ፡-
‹‹አንተ ሆይ መቅድም፤
አንተ ሆይ ጊዜ፤
አትሆንም ወይ፣ የዐደይ ሥር ሚዜ?
አንሆንም ወይ፣ የአበበ መዝሙር፤
የወይን እርሻ፤
አንሆንም ወይ፣
የጥቅምት ውበት፤
የሐዘን መርሻ፤
አንቀስምም ወይ
የዓመት በረከት፤
የእሸት ወተት፤
አንበቃም ወይ፤
ለኸርሞ ጥንስስ፤
ለተስፋ ጥምቀት፤
ለፍለጋ እንጂ፣
ለናፍቆት እንጂ፣
ለትዝታ እንጂ፣
ለግጥም እንጂ፣
. . . . .የምንሰነብት፤
ምን አለን ከሞት
ምን አለን ከሕይወት?!››
በዚህ ግጥም፣ ገጣሚዋ ንግግር የምታደርገው ከጊዜ ጋር ነው፤ ከጊዜ ጋር ትመክራለች፤ ውል የምትፈጽመው ከወቅት ጋር ነው፤ ወቅትን ትጠይቀዋለች፤ ጊዜንና ወቅትን ያማከለ ሁነት እንዲከተልና፣ ከጊዜ ጋር ዕኩል እየተጓዘች፣ መስከረም ሲጠባ ልታብብ፣ አሽታ ልትቃም፣ አብባ ልትቀሰም፣ አፍርታ ልትታጨድ፣ ዘንባ ልታረጥብ… ዘመንን ደጅ ትጠናለች፤ የሚሆነው ሁሉ ጊዜን የሸሸ አይደለምና፣ ከመኖርና ከመሞት በላይ ዋጋ የሰጠቺው ወቅትን ማዕከል ላደረገ ሁነት ነው፤ ሁለቱ ዋልታ ረገጥ ኩነቶች አይገዷትም፤ በእነዚህ መካከል የሚፈጸመው ሁሉ ነው ትኩረቷ፤ የዚህ ሁሉ መፈጸም ደግሞ ጊዜን የዋጀ እንደሆነ ዕሙን ነው።
ከዚህ በማስከተል፣ በ[ገጽ 70] ላይ ትጋትና ነጻነት ተጎራባች እንደሆኑ የምንመለከትበትን አንድ ግጥም  እንቃኝ፡-
‹‹…ፈቅጄ ነበር - መሄድን፤
ለምጄው ነበር - መንገድን፤
ሁሉ ባመነበት፤
በተጠራው ሲድን፤…››
በእነዚህ ስንኞች ትጋት፣ ላመኑበት መገዛት፣ ብርታት ነጻነትን እንደሚያቀዳጅ ተመልክተናል፤ መቁረጥ፣ ወይም መወሰን መቻል ብርታት እንደሆነ መመስከሪያ ስንኝ ነው። በመሆኑም፣ መትጋት ነጻነትንና ምንዳን ሲቸር መረዳት ችለናል።
በመጨረሻ፣ በ[ገጽ 68] ላይ ‹‹ፍቅርን እንካፈል›› ከተሰኘ ግጥም ጥቂቱን ስንኝ ቀንጭበን እንመልከት፡-
‹‹…ለሕይወት ለራሷ፣
ጥቂት ብንቆምላት፤
እንደ ብስል ፍሬ፣
ዝቅ ብለንም ቢሆን፤
ተስፋ ብንይዝላት፤
እንዴት በታደለች!
ወፍ እንኳን በተዐምር፣
ካፏ በወደቀ፣ ዘር ትባረካለች፤
ብስባሽ አፈር ላይ፣
ትንፋሽ ታበቅላለች፤››…
ከላይ በተሰደሩ ስንኞች ገጣሚዋ ልትነግረን የተለመቺውን አሳክታለች፤ ፍቅርን ተካፋይ አካላት ተወክለው ብንመለከትም፣ በሚካፈሉት ፍቅር ልክ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ተፈጥሮ ራሷ ተጠቃሚ፣ የመልካም ገድ ቀማሽ እንደሆነች ተመልክተናል።
ስናጠቃልል፣ ሥነ-ግጥም በኪነ-ጥበብ እንዲጎላና አውራ እንዲሆን ዕሙን ነው፤ ሥነ-ግጥም በብሉይነቱ ዘለዓለማዊነቱ ይጸናል፤ ገጣሚ ደግሞ ዛሬ ሳይገነትረው ነገን ይተልማል። በ‹‹የጊዜ ሠሌዳ›› የግጥም መድበል ውስጥ ዘገባነት ያልጎበኛቸው በርካታ ስንኞች የቅኔአዊነት መከዳ ላይ ተደላድለው እናገኛለን፤ ዘለስ ሲል፣ ገጣሚዋ የውበት ልክፍተኛ ናት…
…በግጥሞቿ ተፈጥራዊ ውበትን፣ ጸዳልን፣ ብርሃንን፣ ፍቅርን፣ ጽጌያትን፣ ውሃን፣ ጨረቃን፣ ፀሐይንና መልካም መዓዛን ከሕይወት ታወዳጃለች፤ ይኼንን ስታደርግ በሌጣ ዘገባ ሳይሆን ዐውዱን ማዕከል በማድረግ በምሰላ አሃድ፣ በዘይቤአዊነት፣ በመፈከርና በማነጻጸር ይትባሃል ነው፡፡ መድበሉ የሥነ-ግጥምንና የሥነ-ሕይወትን ተራክቦ የጠነቀቀ ነው፤ ገጣሚዋ የዚህችን ዓለም ስብጥርጥር ዕውነታ በሥነ-ውበት አስታክካ ትፈክራለች!
በመድበሉ ለሕይወት ትርጉም የማበጀት ከኀሊነት ደምቆ ይታያል። ‹‹የጊዜ ሠሌዳ›› የጊዜን ዲያሌክቲክስ ማዕከል ያደረጉ ስንኞች የታጨቁበት መድበል ነው፤ በመድበሉ ሂደት፣ ሕይወት፣ አበባ፣ ጣዕም፣ መዓዛ፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ፍቅር፣ ጸዳል… በተለየዩ ዐውዶች ውስጥ ተተርከዋል፤ እዚሁ ‹‹የጊዜ ሠሌዳ›› መድበል ውስጥ ነኝ - ብርሃን አልባለሁ፤ ሽቱም ይናኘኛል!    
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።Read 178 times