Monday, 01 July 2024 10:10

ሦስተኛው ጥሩንባ (ምናብ ወለድ ወግ)

Written by  ነቢል አዱኛ
Rate this item
(5 votes)

 ፨ ከተማው ተረብሿል። መላቅጡ ጠፍቷል። ሰው ከቤቱ ግልብጥ ብሎ ወጥቷል። የጓዳ ሃቅ አደባባይ ተሰጥቷል። በትልቅ ሞንታርቦ ዘፈን ተከፍቷል። የሰውን ጫጫታና የዘፈኑን ድምጽ መለየት አይቻልም። ሌሊት ነው። ጨረቃ የለችም። በተለያዩ መብራቶች ጨለማው ድል ተነስቷል። ሰማይ ካልታየ በቀር ያልመሸ ይመስላል። መጠጥ ይከፈታል። ይጠጣል። ይደፋል። ይጨፈራል። መሃል መንገድ ላይ ድሪያው ይደራል። እፍረት የለም። መብላት ነው። መጠጣት። እርቃን መጨፈር። የፈለገ የተመኛትን ይዞ መሃል መንገድ ላይ ለስሪያ ይጣደፋል። መንገድ ላይ የተኙት ያደናቀፈው አንድ ‘ጥሩ’ ሰው፤ ሰውን እንዳያደናቅፉ ዳር ይዘው እንዲዘሙቱ ይመክራል።
    ብሉ ብሉ... ጠጡ ጠጡ
    ይጠቅማችኋል ኋላ ስትቀጡ።
የሚለው ዘፈን ከሞንታርቦው ወጥቶ ጆሮው ላይ ጮኸበት። ከተማዋ ላይ እየኾነ ያለው ነገር ግራ አጋብቶት፣ ፈዝዞ ቆሞ ነበር። ከሩቅ እሳት ይነዳል። ዛፎችን እየቆረጡ እሳት አያይዘው፤ ቤታቸው ሲናድ ደንግጠው ከሚወጡ እንስሳት እያደኑ የሚበሉ ሰዎች አየ። ሳይታደኑ የቀሩቱ እንስሳት መኖሪያቸው በእሳት ሲነድ ወደ ሰዎች ቤት እየገቡ መተኛት ጀምረዋል። ወደ እሳት አንዳጆቹ ሄደ። መንገድ ላይ ‘ደንቃራ’ እንዳያደናቅፈው እየተጠነቀቀ። መጠጥ የያዘ አሳላፊ  ጋ እንዳይጋጭም። “ዛፍ መመንጠር፣ እንስሳት ማባረር የለባቸውም እንጂ መብታቸው ነው። መብላት፣መጠጣት፣ መተኛት ሰዋዊ ባህሪይ ነው።” እያለ ነበር ለራሱ። የዘፈናቸው ግጥም እሱ ያስተማራቸው አይደለ? ያስገረመው... በአንድ ጀንበር እንዴት ከተማዋ ተለወጠች? ብሎ ነው። ጫጫታቸው የሌሊት ትሎችን ሲርሲርታ ያስናፍቃል። ወደ አንዳጆቹ ሲቀርብ ከጫጫታቸው በትንሹ ራቀ። ትንሽ እፎይታ አለው። “እንዴት ናችሁ ሰዎች?” አላቸው ድምጹን ከፍ አድርጎ። የተጠበሰ የአጋዘን ስጋ እየዋጡ ፤
“እንደምን ነህ መምህር” አሉት።
“አንድ ቀን ከከተማዋ ወጣ ብል ምን አድርጋችሁ ጠበቃችሁኝ?” አለ ፊቱ ላይ ፈገግታ እየተንሳፈፈ።
“ምን ይደረግ መምህር? እስከዛሬ የታሰርነው ይብቃን ብለን ራሳችን ለራሳችን የነጻነት አብዮት አነሳን”
“ጥሩ ነው ግን ምነው እንስሳትን ማባረራችሁ? ዛፎችን መንደላችሁ?”
አንገታቸውን አቀረቀሩ።
“እሱን አስተካክሉ”  ብሎ ሌላ ጊዜ ለሌሎች ከተሞች እንደሚያደርገው፣ በስስት ከተማዋን አያትና ወደ ሌላ ከተማ ሊያስተምር ሄደ።
፨ ከተማዋ ከመጠጥ ዓይነት ሌላ ለውጥ የላትም። መሸ ነጋ ያው ነው። ሁሉም ፌሽታ ነው። “የምን ሃሳብ? የምን ጭንቀት?” ነው።
ብሉ ብሉ
ጠጡ ጠጡ
ታልበሉ ታልጠጡ መኖርዎ ምነው?
በጣም አጭር ዕድሜ እምድር ላይ ኖረው
ኋላ ይጠቅምዎታል በፈጠረሁ ጌታ
እሳት ተወርውረው።
 ከዚህች ከተማ የተነሳው ‘የነጻነት አብዮት’፤ በሌሎች ከተሞች ላይም ተስፋፍቶ ሃገሪቷ አንድ ኾነች። ሃገርም ከሃገር እየወሰደ አለም ሙሉ አንድ ኾነ። መምህሩም፤ ከከተማ ከተማ፣ ከሃገር ሃገር እየተዘዋወረ ጫካ እንዳያነዱ፣ እንስሳት እንዳይጎዱ ይመክራል። በሌላው ደስተኛ ነው። ያስተማራቸውን ነው የሆኑት። ያስተማራቸው እንዲህ ነበር። ወደ ተወለደባት ከተማ ሄዶ ህዝቡ አንድ ላይ እንዲሰበሰብ አስነገረ።
“ምንድነው የምትፈልጉት?” አላቸው።
“ተርበናል። ተጠምተናል።” አሉ።
“ምግብ መጠጥ ሞልቷል ግን እኛ ጋ የለም። ለኛ የሚሰጥ የለም። ገንዘብ የለንም። መስረቅ ሃጢአት ነው። እንታገሳለን።”
“ታግሳችሁ በረሃብ ብትሞቱስ?”
“ጀነት አለ። እዚያ እንካሳለን።”
“አሁን ብትሰርቁስ?”
“ጀሃነም አለ። እዚያ እንከሰሳለን።”
ያለውን ሁሉም ተካፍሎ በአደባባይ እንዲበላ ነገረ። ተቀባይነት አልነበረውም - መጀመሪያ ላይ። “ለምን ተሸሽገን እንበላለን? በአደባባይ በጋራ! ሁላችንም የሰው ልጅ ነን!” ይላል አስተምህሮው።
“በቀኖና ታስረን ነጻነታችን መገደብ የለበትም!”. . . . .
፨ መብላት መጠጣቱ፣ መጨፈር መዳራቱ በሰላም ቀጥሎ እያለ፣ አንድ ቀን ጠዋት እንዲህ ኾነ። የጠዋት ጸሃይ ሊሞቁ በምስራቅ አቅጣጫ ሲጠብቁ የነበሩ ጸሃዪቱ ከጀርባቸው ወጣች። በምዕራብ። የገባቸው ገባቸው። እንዲህ ከተከሰተ በኋላ “ፈጣሪዬ ማረኝ! ተለመነኝ!” ትርጉም እንደሌለው። አዋጅ ተነገረ። ህዝቡም ሲራወጥ መምህሩን ፍለጋ፤ መምህሩም እነሱን ለማረጋጋት። ከባድ ድምጽ ያለው ጥሩንባ ተነፋ። ሁሉንም ቀጥ አርጎ ባሉበት የሚገድል ድምጽ። የሰው ዘር ጠፋ። ሁሉም ትቢያ ለበሰ። ቆየ። ብዙ ቆየ። ሁለተኛው ጥሩንባ ተነፋ።  አፈር አራግፈው፣ መቃብር ፈንቅለው የሰው ልጅን የሚያነቃ ድምጽ - ከአደም ጀምሮ። ድንጋጤው እርጉዝ የሚያጨናግፍ፣ ህጻን የሚያሸብት ነው። የሰው ዘር ጠቅላላ በድንጋጤ ቆሞ ሳለ ነዲድ እሳት ተነሳ። ዕርቃን ፍጡር ተሯሯጠ። በመጨረሻ ሁሉን በአንድ የሚሰበስብ ኾነ። በትልቅ ሜዳ። ሚዛን ተተከለ። ፍርድ ቆመ። ቂያማ ደረሰ። ትንሳኤ ፍጡር ኾነ።. . .
                   2                    
፨ ፊቱ የማይታየው፣ ድምጹ የሚሰማው ፈጣሪ እየተቆጣ ነው። “እንዴት ብትደፍሩ ነው! እኔው ፈጥሬያችሁ እኔን ማመጻችሁ!” ጸሃይ ለአናት ስንዝር ቀርባለች። ድንጋጤና ሙቀት ገላን በላብ ያጥባል። የሚናገር የለም። ረጭ። የፈጣሪ ቁጣ ብቻ።  ከሰማይ ወፍ ቢኖር ወላፈኑ ጠልፎ የሚጥል፣ ማቀጣጠያው ድንጋይና የሰው ልጅ የኾነበት፣ ትሉ የማያንቀላፋበት እሳት ወለል ተደርጎ ለሁሉ ታየ። “የሰራችሁትን ታገኛላችሁ! በደላችሁ ወንጀላችሁ በዚህ ይካካሳል!” ህዝቡ መላቀስ ጀመረ። ልጅ ወደ እናቱ፣ ወደ ወንድሙ፣ ወደ ወዳጁ እንዲያድነው መሮጥ ጀመረ። ግን ሁሉም የሚያድነውን ፈላጊ ነው - እንደማይተዋወቅ ኾነ።
“ጸጥታ! ባላችሁበት እርጉ!” ቁጡ ድምጽ።
“መጀመሪያ በስርዓት ስትገዙ ነበር። እኔ ጌታችሁ ነኝ። እናንተ ባሮቼ፤ ስለዚህ መታዘዝ ግዴታችሁ ነው። ያልታዘዘ ይቀጣል! መጥፊያችሁን ያቀረባችሁት ራሳችሁ ናችሁ። አንድ ላይ ማመጽ ጀመራችሁ። .....በቅድሚያ ግን እንዲህ ዓይነት እኔን የምታምጹበት ሃገር እንድትሰሩ፣ እኔን እንድታምጹ ያረጋችሁ ሰው መጠየቅና መቀጣት አለበት” መምህሩ ተጠራ። በላብ ተጠምቆ፣ ሰውነቱን እየጎተተ ያለ ድንጋጤና ፍርሃት ቀረበ። ትልቅ መዝገብ ተሰጠው፤ በግራ እጁ። መዝገቡን ሲገልጠው ያሰባቸው፣ የሰራቸው ‘መጥፎ’ ስራዎች በዝርዝር ከእነ ቀንና ደቂቃቸው ተጽፈዋል።
“አየኸው?”
“አዎ”
“እንዴት ብትደፍር ነው እኔ የፈጠርኳቸው የከለከልኳቸውን እንዲፈጽሙ የምታዘው?”
“ምንድነው እሱ?”
“መጠጥ መጠጣትን ዝሙት መፈጸምን ሌላም ብዙ። እኔ የምታመጽበትን መንገድ እንዴት ትመክራለህ? ወንጀል የሚፈጸምበትን አለም እንዲኖር አርገህ መጥፊያችሁን አፈጠንክ!”
“ወንጀል የሚፈጸምበትን ቦታ የሰራ ጥፋተኛ ነው” ጠየቀ መምህሩ።
“አዎን!”
“..ስለዚህ.. ምድርን የፈጠራትስ ምን ሊባል ነው?”
 ዝምታ ኾነ።
“እኛ በምድር ላይ የምንኖረው ሰባና ሰማንያ አመት ብቻ ነው። ግን እዚህ ትሉ የማያንቀላፋበት እሳት ውስጥ ዘላለም ልታኖረን ታስባለህ። ይሄ በየትኛው ሚዛን ነው ልክ የሚሆነው?  የሰባና ሰማንያና አመት ስራ (እሱንም እኮ ሙሉ እድሜውን የሚያምጽ የለም) እንዴት ከዘላለም እኩል ይኾናል?”
ጠየቀ መምህሩ። ዝምታው ቀጠለ። በላብ የራሱት፣ ዕርቃን የቆሙት የሰው ዘሮች በትንሹ የልብ ልብ እየተሰማቸው መጣ። ቀጠለ መምህሩ “ደግሞ ‘ምትኮቼ ናችሁ’ ብለህ በራስህ ፍላጎት ጭቃ ጠፍጥፈህ ከፈጠርከንና ምድርን ካወረስከን በኋላ ምን ዓይነት አንጀት ቢኖርህ ነው? መልሰህ እንደዚ ዓይነት እሳት ውስጥ የምትከተን? እኛ ሰዎች አንድ ሰው ቢበድለን (ቢበድለን የሚለው ይያዝልኝ) ምን ብንጨክንበት እንዲህ ዓይነት እሳት ውስጥ አንከተውም። እኔ በበኩሌ አልከተውም። ምድር ላይ ሳለን ‘ሌላን አመለካችሁ’ እያሉ እሳት ውስጥ የነበሩትን አልዘነጋሁም። የኛ እሳትና ይሄ እሳት ይለያያል። ቢኾንም ግን አንተን እንዴት ያስችልሃል?”
ከህዝቦች መሃል አንድ ድምጽ ተሰማ፤
“አይወልዴ አባ ግድ የለው!”     
ዝምታ።
ለየሁሉም ሰው መዝገቡ እየታደለው ነው። በግራው። በቀኙ።
“ቢበድለን የሚለው ይያዝልኝ ብዬ ነበር። ማን ነው የበደለ? እኛን አንተ በደልከን እንጂ እኛ አንተን መች በደልንህ ? እኛ እንዳንተ በመዝገብ አስፍረን ባንይዝና ባንሰጥህ ነው እንጂ ያንተ በደል ከውስጣችን መች ይጠፋል? ከነዚህ የሰው ዘር በሙሉ በየተራ ብንጠራ ያንተን በደል የማይናገር አለ?”
“እኔ አለኹ!” አለች አንዲት ባልቴት። በአንድ እጇ መዝገቧን፣ በአንድ እጇ ታዳጊ ልጇን ይዛ ዕርቃኗን ፍርዱ ቦታ ተሰየመች።
“እኔ አንተን ብዬ. . . ላንተ የገባሁትን ቃል ሳላጥፍ በረሃብ ሦስት ልጆቼና አባታቸው አልቀው አንዱ ብቻ ሲቀርልኝ ያበላኛል ብዬ አንተን አምኜ ነበር።” በረሃብ ሆዱ ከጀርባው ተጣብቆ፣ ሁለቱ ጉንጮቹ ተገናኝተው ግን እኛ አንተን እናመልክ ነበር። እሱ የከፈተውን ሳይዘጋው አያድርም እያልን። ግን ረሳኸን። ከሰው ሰርቆ አምጥቶ እኔን አበላና ለራሱም ቢበላ ‘ሌባ!’ ተብሎ ያንተ ቅርቦች ነን በሚሉ አምላኪያን ተወገረ። ‘በዚህ በልጅነቱ ሌብነት ለምዶማ...’ እያሉ። ለራሱ ረሃብ የገደለው ነው እንኳን ዱላ ተጨምሮ! ሞተ! ብቀየምህም ይሁን እሱ ያውቃል ብዬ ብተው፣ አሁን የሱ መዝገብ ላይ የጻፍከው የሰረቀውን ዳቦ ነው። ምን ማለት ነው ይሄ? ዳቦ አውርደህ እኛን እንደማብላት ልጆቼ በረሃብ ሲያልቁ እያየህ ዝም ብለህ ጭራሽ በእሳት እቀጣችኋለሁ ትላለህ? የኔ ልጅ ብቻ አይደለም። ብዙ ህጻናት፣ ብዙ ልጆች ዓይናችን እያየ ነው በረሃብ የተቆሉት። ቅጠል በልተው.. አፈር ልሰው አጥንታቸው ገጦ፣ ዓይናቸው ፈጦ ሲሞቱ እያየህ እንዴት ዝም አልከን? እኔንስ በመዝገቡ ላይ ‘ፈጣሪ የለም’ ብለሻል በሱ ትቀጫለሽ ትለኛለህ? ያልኩበትን ቀን ዘርዝረህ እንደጻፍከው የነበርኩበትን ሁኔታ ለምን አልጻፍከውም?
<እንዲህ የትም ስንቀር.. እያየህ ዝም ካልክማ
እውነት.. እውነት ከመንበርህ የለህማ!> ብያለሁ። ተሳሳትኩ? ብትኖር እያየህ ዝም ትላለህ? ብዬ ማሰቤ ስህተት ነው? ተወው የኛን፣ የኛን ተወው
<የኛስ ይሁን እንዳሻው ለእጥፍ ፈተና ከፈጠርከን
ለፍታችሁ ተፍታችሁ ኑ ካልከን -  
ለቀብር አፈር ከወጠንከን።
ግን - ግን ብላቴናዎቹ ምን በደሉ?
የማንን አደራ በልተው - የማንን አማና አጎደሉ?
እምብርታቸው ያላረረ - አጥንታቸው ያልከረረ
ሰማይ በቀል እንደቋጠረ - እጣቸውን እየመነጠረ
   መንገዳቸውን እያጠረ
እንደ ደራሽ ውሃ አግተልትሎ -
በራብ አኮርማጅ ጠቅልሎ
ከናት እቅፍ በግፍ ነጥቆ
ምሱን ሊቃመስ ተባጥቆ - ሲሰለፍብን ባጭር ታጥቆ
እያየህ ዝም ካልክማ...?
እውነት -- እውነት አንተም ከመንበርህ የለህማ!>
ማለቴ ስህተት ነው? ጡቷ ወተት አጥቶ ልጇም እሷም በረሃብ ሲደፉ.. መንገድ ወጥተን
<በየጥሻው ተወትፈን እንደ ተምች ስንረፈረፍ>
እያየህ ዝም ስትል ምን ማለት ነበረብኝ? ወልደን ስመን ሳንጠግብ በድርቅ በረሃብ ማለቅ!
<ዘርን ሳይተኩ ታክቶ መጥፋት!> ምን ማለት ነው ይሄ? መልስልኝ እንጂ! ምን ይዘጋሃል አሁን ደርሦ?!
 <ምን ይሉታል ይህን ብይን? አንቀጽ ገልጦ ሳያጣቅስ
በዘመድ ወዳጅ ሳያስመክር.. በገንዳ ጎረቤት ሳያስወቅስ
የደም እንባ የሚያስለቅስ...
ምን ይሉታል ይሄንን ፍርድ?
እንዲህ ያለም ጉድ አለንዴ?>
ይሄን ዓይቼ የለህም ማለት ስህተት ነው ወይ? ዓይኔ እያየ አራት ልጆቼን ስቀብር? ምን ዓይነት ህመም እንዳለው፣ ወልደህ ስመህ ዓላየኸው! መች ይገባሃል ይሄ??” አለች ባልቴቷ በእንባ ታጅባ። መምህሩ ቀጠለ
“አየህ ማን በዳይ ማን ተበዳይ እንደኾነ? አንዲት ሴት ብቻ ባንተ የተሰራባት ይሄ ሁሉ ግፍ አለ። ለዚህ መልስ አለህ? ሁሉንም ብንጠራ ብዙ በደል ብዙ እሮሮ አይኾንብህም? ዝም አልን ማለት አልተበደልንም ማለት ነው?”
   ዝምታው ቀጥሏል።
“ሌላው.. በእሳት ለሚቃጠሉት ማዘን የለብንም? ገነት የገባን ስንዝናና፣ እሳት ያሉት ሲቃጠሉ፣ ከንፈራቸውን ማርጠቢያ ጠብታ ቀዝቃዛ ውሃ ሲፈልጉ... ብናውቃቸውም ባናውቃቸውም ማዘን የለብንም? ያንተ ባህሪይ የተባለውን እዝነትን አንተገብረውም?
‘ጎረቤቱ ተርቦ እሱ ጠግቦ ያደረ አማኝ አይደለም’ ተብለን ነው የተማርነው። ጎረቤታችን ጠብታ ውሃ አጥቶ ሲሰቃይ የኛ በወተት መጫወት ከአማኝነት አያወጣም? ወይስ ያ ምድር ላይ ብቻ ነው የሚሰራው? እነሱ ተጠምተው የኛ ጠግቦ ማደር አማኝ ስለማያደርገን፣ሁላችንም አብረን መቀጣት አለብን! አይመስልህም?”
  ዝም። ዝም። ዝም። መልስ ሲጠፋ ጥሩንባ ተነፋ። ሦስተኛው ጥሩንባ። ከዚህ በፊት ያልታዘዘ ጥሩንባ። መልስ ሲጠፋ የታዘዘ። ሁሉም የሰው ልጅ ባለበት ወደቀ።. . .


Read 822 times