Wednesday, 03 July 2024 20:27

ነቢይ መኮንን አለቃዬ ሆኖ አያውቅም!!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሰው ካልሞተ አይመሰገንም የሚሉት ብሂል ትክክል መሆኑን ዛሬ በተጨባጭ አረጋገጥኩኝ፡፡ ለምን እስከዛሬ ስለ ቅርብ ወዳጄ ነቢይ መኮንን የማውቀውን በጎነትና መልካምነት አልመሰከርኩም ብዬ ራሴን ስጠይቅ፣ በተደጋጋሚ ያገኘሁት  ምላሽ፣ ”ንፉግነት” የሚል ሆኖ አገኘሁት፡፡ በዚህም ራሴን ክፉኛ ወቀስኩት፡፡ በጸጸት ተቃጠልኩ፡፡ በራሴም አፍሬ የምገባበት ጠፋኝ፡፡  

የሰው ልጅ ኖሮ ኖሮ ማለፉ እንደማይቀር እያወቅን፣ ለምን ይሆን በህይወት ሳለ በጎነቱን  ተንፍሰን፣ በአደባባይ የማናመሰግነው? (ጥያቄውም ወቀሳውም ለራሴ ነው!) ያንን ያደረገ መቼም የታደለ ነው - የተባረከ!! ቢያንስ እንደኔ በጸጸት ከመሰቃየት ይድናል፡፡ በቁጭት ከመብሰልሰል ይተርፋል፡፡ እንደኔ በራሱ ከማፈር ራሱን ይታደጋል፡፡ የህሊና ሰላም ይቀዳጃል፡፡ በወዳጁ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን ብቻ ያስተናግዳል - አልቅሶም ሃዘኑን በእንባው ይወጣል፡፡ የእኔ ዓይነቱ ግን ሃዘኑና ህመሙ  ሁለት ነው፡፡

ስለ ነቢይ መኮንን በህይወት እያለ ለመናገር ያልደፈርኩትን፣ በዚህ መሪር የሃዘን ስሜት ውስጥ ሆኜ በጥቂቱም ቢሆን ልተንፍሰው - ምናልባት ከጸጸት ፈውስ ቢሆነኝ፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ በቅርበት  የማውቀው የልብ ወዳጄ ነቢይ መኮንን፣ በደግነት የተትረፈረፈ ሰው ነበር፡፡ እኔ ዛሬ ላለሁበት ደረጃ የደረስኩት፣ በአሰፋ ጎሳዬና በነቢይ መኮንን የተትረፈረፈ ደግነት ነው፤ በሁለቱ የአዲስ አድማስ ዕንቁዎች፡፡ እግሬ የአዲስ አድማስ  ግቢን ከረገጠበት ዕለት ጀምሮ፣ ሁለቱም በጓደኝነት ነበር የተቀበሉኝ - በፍቅር፡፡

አዲስ አድማስን ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ ከ15 ዓመታት በላይ ከነቢይ አጠገብ ተለይቼ አላውቅም፡፡ መጀመሪያ ላይ የተቀጠርኩት በከፍተኛ ሪፖርተርነት ቢሆንም፣ ከጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ከነቢይ መኮንን ቢሮ ውጭ የሰራሁበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ አንድ ቢሮ ውስጥ መሥራት ብቻ ግን አይደለም፤ ሦስታችንም ምሣ የምንበላው አንድ ላይ ነበር - የጋዜጣው መሥራችና ባለቤት አሴ፣ ዋና አዘጋጁ ነቢይ መኮንንና ከፍተኛ ሪፖርተሩ እኔ፡፡ ሁለቱም ደግሞ አንድም ቀን አለቆቼ መስለው ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ እንደ ቅርብ ወዳጅ እንጂ እንደ አለቃ ቆጥሬአቸው አላውቅም - ዛሬም ድረስ የሚሰማኝ እንዲሁ ነው፡፡

የእኔና የነቢይ መኮንን ቅርርብ ከቢሮም ይሻገራል - የቤተሰቡም አባል ነበርኩ፡፡ በሳምንት ሁለት ወይም ሦስት ቀን አዳሬ ነቢይ ቤት ነበር - በተለይ የጋዜጣው ሥራ በሚበዛበት ዘወትር ሃሙስ፡፡ ባለቤቱና ልጆቹ ለእኔ ፍቅር ነበሩ፡፡ ለአንድ ሳምንት እንኳን ከጠፋሁ ባለቤቱ ደውላ ትቆጣኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ነቢይና ባለቤቱ ዘመድ ጥየቃ ክፍለ ሃገር ቢሄዱ እኔን አስከትለው ነበር፡፡

ነቢይ መኮንን የሙያ አባቴም ነበር - ኮትኩቶ ለዛሬ የሙያ ማንነቴ ያበቃኝ፡፡ ከእርሱ ሥር ተቀምጬ ስለ ጋዜጣ አሰራር፣ ስለ አርትኦት፣ ስለ አጻጻፍ፣ ስለ ግጥም፣ ስለ ትርጉም ሥራ ወዘተ--- ተምሬአለሁ፡፡ እንዲያም ሆኖ አንድም ቀን ነቢይ አለቃዬ መስሎ ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ በዕድሜና በዕውቀት የትናየት ብንራራቅም፣ ነቢይ ሁሌም ለእኔ  ጓደኛዬ ነበር - የልብ ወዳጄ፡፡

በጠለቁና በረቀቁ  ግጥሞቹ ስሙ የናኘው  ነቢይ መኮንን፤ ከልቡ ሰው ነበር - የሰው መጨረሻ፡፡

በተባ ብዕሩና በውብ ቋንቋው የሚታወቀው ነቢይ መኮንን፤ የደግነት ጥግ ነበር - ደግነት የተትረፈረፈው፡፡

በደርግ ዘመን ለአስር ዓመት በእስር ማቆ ከሞት የተረፈው ነቢይ መኮንን፤ የማይሞቀው የማይበርደው ሰው ነበር - ሃዘኑም ደስታውም የተመጠነ፡፡

ዛሬ እንግዲህ ይህን የአዲስ አድማስ ሌላውን እንቁ አጥተነዋል፡፡

 ፈጣሪ ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑርለት፡፡

ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዱና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ከልቤ እመኛለሁ፡፡

(-ኢዮብ ካሣ-)

Read 1099 times