Thursday, 04 July 2024 16:20

የሁለገቡ ከያኒ ነቢይ መኮንን የህይወት ታሪክ (1946 - 2016)

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ገጣሚ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ ከአባቱ ከአቶ መኮንን ወንድም እና  ከእናቱ ከወይዘሮ በለጤ በድሉ፣ በነሐሴ ወር 1946 ዓ.ም፣ በቀድሞዋ ናዝሬት፣  በአሁኑ አዳማ ከተማ ተወለደ፡፡
 ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመግባቱ አስቀድሞ፣ መምህር ተከስተ ጋር የቄስ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን፤ እዚያም ሳለ ዳዊትን በቃሉ በመሸምደድ የማስታወስ ችሎታውን አዳበረ፡፡  
 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው ናዝሬት በአጼ ገላውዲዮስ ት/ቤት  የተከታተለው ነቢይ መኮንን፤ በትምህርት አቀባበሉም ከጎበዞቹ ተርታ የሚሰለፍ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ለትምህርት ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው  የገንዘብ ሚኒስቴር ባልደረባ የነበሩት አባቱ፤ ጉልህ ሚና ነበራቸው፡፡  ልጃቸው ሁልጊዜም  በትምህርቱ ብርቱ ሆኖ  ምክራቸውን  ይለግሱት  ነበር፡፡ ነቢይም፣ ከክፍሉ አንደኛ በመውጣት አባቱን ከማስደሰት ቸል ብሎ አያውቅም፡፡  ነቢይ አባቱን አቶ መኮንን ወንድምን በሞት ያጣው  የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነበር፡፡
ነቢይ መኮንን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን  እንዳጠናቀቀ፣ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ልኡል በእደ ማርያም ተማሪ ቤት ከገቡ ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ነበር፡፡  በመቀጠልም በ1966 ዓ.ም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲን የተቀላቀለው ነቢይ፤ ኬሚስትሪን በዋናነት (ሜጀር)፣ ሂሳብን ደግሞ  ማይነር በማድረግ አጥንቷል፡፡  
እንደ ዘመነኞቹ  በወቅቱ  የተማሪዎች  ንቅናቄ ውስጥ ተሳትፎ የነበረው ነቢይ መኮንን፤ ከደርግ ወጥመድ አላመለጠም፡፡ በኢህአፓ አባልነቱ ታስሮ ለ10 ዓመታት መከራውን በልቷል፡፡ ነገር ግን ደርግንም ሆነ አገሪቱን ወይም ሌላ ወገን ሲያማርር፣ ሲወቅስ ወይም ሲረግም ተሰምቶ አይታወቅም፡፡  እንደ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታግዬለታለሁ፣ ሞቼለታለሁ ወዘተ እያለም መመጻደቅ አያውቅበትም፡፡  በሚመጻደቁትም ይስቃል፡፡ እሱና ዘመነኞቹ በአብዮቱ ወቅት ያሳለፉትን በጎም ሆነ ክፉ፣ ያሁኑ ትውልድ እንዲማርበት ከመጻፍና ከመናገር ግን  ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ጽንፈኝነትና አክራሪነት እንደማያዋጣ ሲመክር ኖሯል፤ በጽሁፎቹ፡፡    
 ነቢይ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኬሚስትሪ ያጠና  ቢሆንም፣ በገጣሚነት፣ በደራሲነት፣ በተርጓሚነትና በጋዜጠኝነት  በርካታ ሥራዎችን ለአንባቢያን  ያበረከተ ታላቅ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ነበር።
በ1992 ዓ.ም ህትመት የጀመረችውን አዲስ አድማስ ጋዜጣን ከመሰረቱት አንዱ የነበረው አንጋፋው የጥበብ ባለሙያ  ነቢይ መኮንን፤ ለሁለት አስርት ዓመታት ጋዜጣዋን በዋና አዘጋጅነት በመምራት፣ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ስኬታማ አድርጓታል፡፡ የአዲስ አድማስ ዋና አዘጋጅ የነበረው ነቢይ፣ በጋዜጣው ላይ በየሳምንቱ በተረትና ምሳሌ እያዋዛ በሚጽፋቸው ርዕሰ አንቀጾች ታዋቂነትን ያተረፈ ሲሆን፤ ለጋዜጣዋም ተነባቢነትን አቀዳጅቷታል፡፡  
ሁለገቡ ከያኒ ነቢይ መኮንን፣ ከአሰርት ዓመታት በፊት “ባለጉዳይ” የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ ከማብቃቱም በላይ በትወናም ተሳትፎበታል፡፡ የእዚህ ተከታታይ ድራማ ጭብጥ ከመሬት ጋር የተያያዘ የሙስና ጉዳይ ሲሆን፣ ታዋቂዎቹ ተዋናዮች  አበበ ባልቻ፣ ፈቃዱ ተክለማሪያምና ፍቅርተ ጌታሁንን ጨምሮ ሌሎችም ተሳትፈውበት ነበር፡፡
ነቢይ፣ “ናትናኤል ጠቢቡ” እና “ጁሊየስ ቄሳር” የተሰኙ ተውኔቶችንም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል። ”ባለካባ እና ባለዳባ” በተሰኘ ተውኔት ላይ ደግሞ በትወና ተሳትፏል።
“ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ” የሚለው ነቢይ መኮንን፤ “ጥቁር፣ ነጭ፣ ግራጫ ግጥሞች” እና “ስውር ስፌት- (ሁለት ቅጾች)” የግጥም መድበሎችን ለንባብ  አብቅቷል፡፡  
ነቢይ፤ “የኛ ሰው በአሜሪካ” - የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻው፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ሲወጣ ቆይቶ፣ በመጨረሻ  በመጽሐፍ ተዘጋጅቶ ለህትመት የበቃ ሌላኛው ሥራው ነው። ለንባብ የበቃው ሌላው  የነቢይ መጽሐፍ ደግሞ “የመጨረሻው ንግግር” የተሰኘ ሲሆን፤ “ዘ ላስት ሌክቸር” ከሚለው መጽሐፍ የተተረጎመ  ነው።
ነቢይ፤ ዳን ብራውን የጻፈውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ የነበረውን "The Davinci Code" የተሰኘ መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ አስነብቧል፡፡  
ከነቢይ ጥበባዊ ሥራዎች  ሌላው  የሚጠቀሰው  "ማለባበስ ይቅር" ነው፡፡ ኤች አይቪ-ኤይድስ  የሀገር አደጋ በሆነበት ዘመን፣ ነቢይ መኮንን "ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩትን ማግለል በሽታውን ያባብሳል፤ ስለዚህ ፍቅር እንስጣቸው፤ አናግልላቸው"  የሚል መልእክት ያዘለ  ግጥም ገጥሞ  ታዋቂ ወጣት ዘፋኞች አቀንቅነውታል፡፡  "ማለባበስ ይቅር" የተሰኘው የሙዚቃ ሥራ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተደጋጋሚ ይታይ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ከ32 ዓመት በፊት ሜጋ ኪነጥበባት ማእከልን ከመሰረቱት አንዱ የነበረው ነቢይ መኮንን፤ በጊዜው በሜጋ ኪነጥበባት ማእከል አሳታሚነት ትወጣ የነበረችውን  ‹‹ፈርጥ›› የኪነ-ጥበብ መጽሄትንም በዋና አዘጋጅነት በመምራት ይታወቃል፡፡
ነቢይ፣ ከጋዜጠኝነቱና ከጥበብ ሥራው ጋር በተገናኘ የተለያዩ የዓለም አገራትን የመጎብኘት ዕድል የገጠመው ሲሆን፤ ከጎበኛቸው ሀገራት  መካከልም ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ኢራን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ፣  ኬንያና   ሱዳን ይገኙበታል፡፡
ነቢይ ለሀገሩ ኪነጥበብ ማደግ ከወጣትነቱ ጀምሮ ብዘ የለፋ ታላቅ የሀገር ባለውለታ እንደመሆኑ መጠን፣ ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የቅርብ ወዳጆቹ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ፣ ነቢይ በሀገሩ ይከበራል የሚል  የምስጋና መሰናዶ አዘጋጅተውለት ነበር፡፡  
.ከሁሉ ወዳጅና  ተግባቢ የነበረው ነቢይ መኮንን፣ ባለትዳርና  የሦስት ሴት  ልጆች አባት ነበር፡፡ አንጋፋው ገጣሚ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ፣ ረቡዕ ሰኔ 26 ቀን  2016 ዓ.ም  በተወለደ በ69 አመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹና ለአድናቂዎቹ  መጽናናትን እንመኛለን፡፡

Read 1386 times