Saturday, 06 July 2024 20:25

“አገሬ አቃቤ ጥበቧን በሞት ተነጥቃለች”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- ነቢይ ተደራራቢ የጤና እክሎች ነበሩበት
- “ነቢይ መኮንን ከሳቅ የተሰራ ሰው ነው
“ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ” የሚለው ሁለገብ ከያኒ ነቢይ መኮንን፤ የጥበብ መክሊታቸውን አሟጠው ሳይጠቀሙ ህይወታቸውን በሞት ለሚነጠቁ የጥበብ ሰዎች “የዕድሜ ዕቁብ በኖረ” ሲል በግጥም ምኞቱን አስፍሯል።
….”ምነው ለጥበብ ሰው
 ለበሳል ኪነት ሰው
እቁብ በኖረ፣ ወይ የእድሜ ቀይ መስቀል
የክፉ ቀን ደራሽ፣ አንድ ቀን የሚውል
አንድ የጥበብ መዓልት ለሟች የሚቀጥል
ከባካኝ ጊዜያችን፣ ደቂቃና ሰዓት እየቆነጠርን
ለልባም ፀሃፊ የምንለግስበት፣
ዋ! የዕድሜ ዕቁብ ቢኖር!...”
የአንጋፋው ገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን የህልፈት ዜና ድንገተኛ ነበር - አስደንጋጭ። ምንም እንኳን ባደረበት ህመም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ፣ ባለፈው ረቡዕ ህይወቱ ማለፉ ከቤተሰቦቹ የተነገረ ቢሆንም፣ ህመሙም ህልፈቱም ዱብ ዕዳ ነበረ - ለብዙዎች። ነቢይ በአንድ ወቅት ታምሞ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ የጤንነቱን ሁኔታ ይከታተል የነበረ አንድ የህክምና ባለሙያ እንደሚናገረው፤ “ነቢይ ተደራራቢ የጤና እክል ቢገጥመውም ጨዋታ አዋቂነቱን፣ ገጣሚነቱንና አገር ወዳድነቱን አላጎደለበትም።”
ግን አሁን ሳይሆን ያኔ። በቅርቡ በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርቦ ራሱ እንደገለፀው፤ ወደ ህንድ አገር ተጉዞ  የልብ ህክምና ያደረገ፤ ሲሆን በህንዳውያኑ የተራቀቁ የህክምና ቴክኖሎጂ መደመሙንም ተናግሯል። እንዲያም ሆኖ የ70 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ነቢይ መኮንን፤ የልብ ህመም፣ ስኳርና፣ ደም ግፊት እንደነበረበት የሆስፒታል ምንጮች ይናገራሉ።
የትኛው ህመሙ ተባብሶ ለህልፈት እንደዳረገው ግን ለማወቅ አልተቻለም፡፡ የቅርብ ወዳጆች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ያልተጨናነቀ ህይወቱ ለሚወደው ገጣሚና ደራሲ ነብይ መኮንን የመጨረሻዎች የህይወት ምዕራፎቹ ተግዳሮት የበዛባቸው ነበሩ። ህመሙን ለመንከባከብና ራሱን ለመጠበቅ ምቹ ሁኔታ አላገኘም የሚሉት ወዳጆቼ፣ የቅርብ ሰው በአጠገቡ እንዳልነበረም ነው የሚናገሩት፡፡
የአዲስ አድማስ ዋና ጋዜጣ አዘጋጅና የሁለገብ ጥበብ ባለቤት የነበረው ነቢይ መኮንን ህልፈትን ተከትሎ ለዓመታት ያበረከታቸውን የኪነጥበብ ስራዎች የሚያደንቁና እውቅና የሚሰጡ በርካታ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል- በማህበራዊ ሚዲያው። በአንጋፋው ገጣሚ ፀሃፊ ተውኔት፣ ተርጓሚና አርታኢ - ነብይ መኮንን ህልፈት እጅጉን ማዘናቸውን የሚገልፁት የጥበብ ወዳጆች፤ ነቢይንና ሥራዎቹን እየዘረዘሩ አድናቆታቸውንና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት አስርት ዓመታት ተወዳጇን አዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ ከምስረታ አንስቶ በዋና አዘጋጅነት   የመራው ነቢይ መኮንን፤ ርዕሰ አንቀጽን በተረትና ምሳሌ አዋዝቶ መጻፍን ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋውቋል፤ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ለተቀረውም ዓለም ጭምር፡፡ ይህም  የጋዜጣው አንዱ መለያ ቀለም በመሆን የዘለቀ ሲሆን፤ በአንባቢያን ዘንድም ተነባቢነትን አትርፎለታል፡፡
ነቢይ መኮንን ከዋና አዘጋጅነቱ ጎን ለጎን ግጥሞችን ይጽፍ ነበር፡፡ ተወዳጅ ታሪክ ያላቸው መጻህፍትን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም በተከታታይ ያስነብብ ነበር፡፡ ዘ ዳ ቬንቺ ኮድ ፣ ዉመን አት ፖይንት ዚሮ፣ ቱስዴይ ዊዝ ሞሪሰን (ፕሮፌሰሩ በሚል  ርዕስ) በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
የገጣሚና ደራሲ ነቢይ መኮንን ቀብር ሥነ-ስርዓት ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በአዳማ ተፈጽሟል። ከዚያ በፊት ግን ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ፣ በብሔራዊ ቴአትር ዕውቅ አርቲስቶች፣ ወዳጆቹና ቤተሰቦቹ በተገኙበት የነቢይ አስከሬን የሽኝት መርሃ ግብር ተከናውኗል። በመርሃ ግብር ላይ መድረኩን የመራው የማስታወቂያ ባለሙያው አርቲስት ተስፋዬ ማሞ፤ አንጀት በሚበላ የሐዘን፣ የሙዚቃ ቅንብር ታጅቦ እንዲህ ሲል መድረኩን ከፈተው፣
“የደራሲው ብዕር ታጠፈ!”
ከአርቲስት ተስፋዬ በመቀጠል፣ ዕውቁ ተዋናይና ሁለገብ የመድረክ ሰው አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ፤ የነቢይ መኮንንን የሕይወት ታሪክ በንባብ ያቀረበ ሲሆን፤ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች ስለነቢይ የሚያውቁትንና የተሰማቸውን ምስክርነት ሰጥተዋል።
ሌላው በመድረኩ ላይ ምስክርነታቸውን የሰጡት የነቢይ መኮንን የረዥም ዓመታት ወዳጅ ወግ አዋቂው አቶ በሃይሉ ገብረመድህን  ሲሆኑ፤ ሳግ በተናነቀው አንደበታቸው፣ ምንጊዜም ሲገናኙ እርስ በርስ የሚለዋወጧትን ግጥም በማውሳት፣ “ለእኔ ዛሬ ኮረኮንቻማ ቀን ነው” ብለዋል። “ነቢይ ከሳቅ የተሰራ ሰው ነው” ያሉት አቶ በሃይሉ፣ የነቢይን ጨዋታ አዋቂነት በስፋት አንስተዋል። የነቢይ መኮንን ሁለተኛ ልጅ የሆነችው ራኬብ ነቢይ በተመጠነ ንግግሯ ስለአባቷ ቤተሰባዊ ሰብዕና ተናግራለች። በልጅነታቸው ነቢይ የሚጽፋቸውን ጽሁፎች እንደሚያነብላቸው፣ በነጻነት እንዳሳደጋቸው፣ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የተለየ ቅርርብ  እንደነበረው ገልፃለች። “እኔ እንደእናንተ ብዙም አላገኘሁትም፣ በጣም ነው ያስቀናችሁኝ” ስትልም ልብ የሚነካ መልእክት ልቅሶ እየተናነቃት አስተላልፋለች።
በመጨረሻም የስንብት መርሃ ግብሩ የተደመደመው በጭብጨባ ነበር፤ ነቢይ ላለፉት በርካታ ዓመታት ላበረከተው የጥበብ ሥራዎች ዕውቅና ለመስጠት አስከሬኑ እስኪወርድ ድረስ  ጭብጨባው አዳራሽ ያስተጋባ ነበር።
መርሃ ግብሩ አንጋፋና ወጣት ዕድምተኞች የተገኙበት ቢሆንም፣ በቂ እንዳልሆነ የሙዚቃ ተንታኙ ፍሬስብሃት ሰርጸ ይናገራሉ።
“የዛሬው ስንብት ብዙ ትዝብት ያለው ስንብት ነው። ብዙውን ጊዜ ለክዋኔ ጥበባት ሰዎች ሕልፈት የሚኖረው ዓይነት ታዳሚ አይደለም ዛሬ ያየነው። በጥራት ካየኸው ጥርት ያለ ሊሆን ይችላል። ትልልቅ ሰዎችን አይተናል። ግን ነቢይን የሚያውቀው ሰው ይህ ብቻ ነው ብዬ አላምንም። ከፍ ባለ ሁኔታ ሁላችንም ወጥተን አመስግነን ልንሰናበተው ይገባ ‘ነበር’ የሚል ቁጭት አለኝ ብለዋል። ለነቢይ ክብር ያለው ፕሮግራም በተከታታይ በማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም መክሯል።
ለ10 ዓመታት ያህል ከነቢይ ጋር በማዕከላዊ እስር ቤት አብረው የታሰሩት አቶ ግርማ አበራ፣ ከነቢይ ጋር እንዴት እንደተዋወቁ ሲናገሩ፤ “ድርጅት ነው ያስተዋወቀን” ይላሉ። “የቀረውን ዕድሜያችንን እስር ቤት ነው ያሳለፍነው። ነቢይ ከእኔ አንድ ዓመት ቀድሞ ወጣ እንጂ እስከመጨረሻ አብረን ነው የታሰርነው። ከወጣንም በኋላ ቅርርባችን የወንድም ያህል ቀጥሏል - ሲሉ ተናግረዋል።”
ከነቢይ መኮንን ጋር ከ30 በፊት ዓመት እንደተዋወቁ የነገረን  ደግሞ፣ ተዋናይ ኩራባቸው ደነቀ ነው። “ከ30 ዓመት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ ስራዎችን በምንሰራበት ወቅት ‘ጁሊየስ ቄሳር’ን ይዞ ይመጣ ነበር። እኛ ደግሞ፣ ‘የጫጉላ ሽርሽር’ን የምንሰራበት ወቅት ነበር፤ እኔ፣ ጀማነሽ ሰለሞን፣ ተፈሪ ዓለሙ፣ ሙሉዓለም ታደሰ፣ መንበረ ታደሰ...ወዘተ በዚያ ጊዜ እርሱ እዚያ አዘውትሮ ይመጣ ስለነበር የዚያን ጊዜ ነው የተዋወቅነው” ሲል አውግቶናል።
ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም ደግሞ እንዲህ ይላል። “እኔ ነቢይን የማውቀው... በሚሰራቸው ስራዎች ነበር። ከዚያ በኋላ ነው እርሱን ለማወቅ ፍላጎት ያደረብኝ። አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቅዳሜ ቅዳሜ ሳነብ፣ ከአምዶቹ ውስጥ ‘የግጥም ጥግ’ የሚል አምድ ነበር። ይህ አምድ  አሁን ያለነውን ገጣሚያን መንፈስ ከፍ ያደረገና ያነሳሳ ክፍል ነው። የመጀመሪያ ትውውቄ እርሱ ነው። ከዚያ በኋላ በተለያዩ መድረኮችና አጋጣሚዎች የምንገናኝባቸው ነገሮች ይፈጠሩ ነበር።  ወዳጅነታችን እንደዚህ ነው የተጀመረው።” ሲል  ተናግሯል።
የተወዳጁ የኪነት ሰው ነቢይ መኮንን  አስከሬን በብሔራዊ ቴአትር ሽኝት ከተደረገለት በኋላ በቀጥታ ያመራው ወደሚወዳት የትውልድ ቀዬው ናዝሬት/አዳማ ነው - በኑዛዜው መሰረትም የሚወዳቸው ወላጅ እናቱ ባረፉበት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስከሬኑ አርፏል። ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በተፈፀመው የቀብር ሥነ-ስርዓት ላይ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹና የሚወዳቸው አድናቂዎቹ በ70 ዓመቱ ህይወቱ ያለፈው ነቢይ መኮንን ባለትዳርና የሦስት ሴት ልጆች አባት ነበር።
በማህበራዊ ሚዲያ “የአዲስ አድማስ እንቁ ነቢይ መኮንን አለፈ” ሲል አስተያየቱን ያሰፈረው ኤልያስ የተባለ አድናቂ፣ “አገሬ ኢትዮጵያ ዛሬ ቀን ጎድሎባታል…. ወጓን ጠብቆና ሰብኮ የኖረ ዐቃቤ ጥበቧን በሞት ተነጥቃች” ሲል ሃዘኑን ገልጿል።

Read 1214 times