“ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ”
ኢ.ካ
አንጋፋው ገጣሚና ደራሲ፣ ተርጓሚና ጸሃፌ ተውኔት ነቢይ መኮንን የናዝሬት ልጅ ነው - ናዝሬት ተወልዶ ያደገ፡፡ ናዝሬትን ከልቡ ይወዳታል- ከእነ አቧራዋ፡፡ በልጅነቱ ፊደል ቆጥሮ ዳዊት ደግሞባታል፤ ዘመናዊ ትምህርት ቀስሞባታል፡፡ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በናዝሬት የአጼ ገላውዲዮስ ት/ቤት ነው፡፡ ስለዚህም ሁሌም ከአፉ አትጠፋም - ናዝሬት፡፡
ገጣሚ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ ከአባቱ ከአቶ መኮንን ወንድምና ከእናቱ ከወ/ሮ በለጤ በድሉ፣ በነሐሴ ወር 1946 ዓ.ም ነው የተወለደው፡፡ ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመግባቱ በፊት መምህር ተከስተ ዘንድ የቄስ ትምህርቱን ተከታትሏል - እስከ ዳዊት ድረስ፡፡
ነቢይ መኮንን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በስድስት ኪሎ በሚገኘው ልኡል በእደ ማርያም ተማሪ ቤት ነው የገባው - በጉብዝናው ተመርጦ፡፡ በ1966 ዓ.ም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲን የተቀላቀለው ነቢይ፤ ኬሚስትሪ ነበር ያጠናው፡፡ ተማረበት የሙያ ዘርፍ ግን ሰርቶበት አያውቅም፡፡ መላ ህይወቱን በፍቅር የሰጠውና የተጋው ለኪነጥበብ ሥራዎች ነው፡፡
ነቢይንና ሥራዎቹን በጥልቀት የሚያውቁ ብዙዎች እንደሚመሰክሩት፣ ነቢይ መኮንን ሁለገብ ከያኒ ነበር፡፡ ያልሰራበትና አሻራውን ያላኖረበት የጥበብ ዘርፍ የለም፡፡ ከሥነግጥም እስከ ተውኔት፣ ከትርጉም ሥራዎች እስከ የፈጠራ ድርሰቶች ድረስ ተራቆበታል፡፡
የሥነጽሁፍ ረዳት ፕሮፌሰሩ የሻው ተሰማ በቅርቡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ”ሙያና ጥበብ ሲመጋገብ - ከታወቁ ደራስያን ሥራዎች አኳያ“ በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሁፋቸው፣ ነቢይ ዕውቅና ያተረፈው በብዙ ዘርፍ ነው፤ ይላሉ፡፡
“--ነቢይ ዕውቅና ያተረፈው በብዙ ዘርፍ ነው፤ ግሩም ችሎታ ያለው ተርጓሚ ነው። --ነቢይ አንቱ የተባለ ገጣሚም ነው። ግጥሞቹ ልብን ይመስጣሉ። በተለይ በግጥሞቹ የሚያነሳቸው ርእሰ ጉዳዮች ከአዲስ እይታ የሚፈልቁና፣ ሀገራዊ አንድምታ ያላቸው ናቸው። በዚያ ላይ የተነገረለት አርታኢም ነው። በ«አዲስ አድማስ» ጋዜጣ ለረጅም ዓመታት በአዘጋጅነት ሲሠራ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ያስተዋለ ሰው፣ ጠንካራ አርታኢነቱን ለመመስከር ግንባሩን አያጥፍም።” ሲሉ የነቢይን ሁለገብ ከያኒነት አስረግጠው ይገልጻሉ፡፡
ነቢይ የትያትርና ድራማ ጸሃፊም ነበር፡፡ ከአስርት ዓመታት በፊት “ባለጉዳይ” የተሰኘ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ድራማ ለዕይታ አብቅቷል፤ አንጋፋው አርቲስት አበበ ባልቻ፣ ራሱ ነቢይ መኮንንና ሌሎችም አርቲስቶች የተወኑበት፡፡ ጭብጡ ዛሬም ድረስ ተባብሶ የቀጠለው ከመሬት ጋር የተያያዘ የሙስና ጉዳይ ነው፡፡ ድራማው ከ10 ዓመታት በኋላ በድጋሚ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቦ፣ እንደ አዲስ በከፍተኛ አድናቆት ነው የታየለት፡፡ ነቢይ ”ናትናኤል ጠቢቡ“ የተሰኘ ተውኔትም ተርጉሞ ለመድረክ አቅርቧል፡፡ “ጁሊየስ ቄሳር” ሌላው ተርጉሞ ለዕይታ ያበቃው የጥበቡ በረከቱ ነው፡፡
በደርግ ዘመን እንደ እድሜ አቻዎቹ ሁሉ፣ በጸረ-አብዮተኝነት ተጠርጥሮ ወህኒ የተወረወረው ነቢይ መኮንን፤ ከዛሬ ነገ ይሙት ይትረፍ ሳያውቅ፣ Gone With The Wind የተሰኘውን ዳጎስ ያለ ልብወለድ መጽሐፍ በሲጋራ ወረቀት ላይ እየተረጎመ፣ በድብቅ በማስወጣት፣ ከእስር ሲፈታ ነበር፣ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርዕስ ያሳተመው፡፡
ይህን አስገራሚ ታሪክ ሰምታ የተደመመች አንዲት አሜሪካዊት ጋዜጠኛ፣ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ ባህር ተሻግራ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ከነቢይ ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ እኔ ደግሞ አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ወደ ሃገሯ ልትመለስ አንዲት ቀን ሲቀራት አግቼያት ኢንተርቪው በማድረግ፣ ታሪኩን ለአዲስ አድማስ አንባቢያን አድርሻለሁ፡፡
“ነገም ሌላ ቀን ነው” የተሰኘው መጽሐፍ የመጀመሪያ ዕትም በሳንሱር ምክንያት መግቢያውና አንዳንድ ሃሳቦቹ ተቆራርጠው መውጣታቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ በቅርቡ ሦስት መጻሕፍትን በአንድ ላይ ሲያስመርቅ አብሮ የተመረቀው ህትመት ግን በፊት ያልታተመው መግቢያ፣ ታክሎበት በአዲስ መልክ ነበር ለንባብ የበቃው፡፡
በቅርቡ በአንድ ላይ ከተመረቁት ሦስት የነቢይ ሥራዎች አንዱ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከዓመት በላይ በተከታታይ ሲቀርብ የነበረውና ከፍተኛ ተነባቢነትን የተቀዳጀው “የኛ ሰው በአሜሪካ” - የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻ ነው፡፡ ታሪኩ በአሜሪካ በሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን አኗኗር ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ሦስተኛው መጽሐፍ “የመጨረሻው ንግግር” የተሰኘ ሲሆን፤ The Last Lecture ከሚለው በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ መጽሐፍ የተተረጎመ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአዲስ አድማስ ላይ ተቀራራቢ ጭብጥ ያለው መጽሐፍ ነቢይና እኔ እየተረጎምን በተከታታይ አስነብበናል፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ ”ቱስዴይ ዊዝ ሞሪስ” የተሰኘ ሲሆን፤ “ፕሮፌሰሩ” በሚል ርዕስ ነበር ያቀረብነው፡፡
ሁለገቡ ከያኒ ነቢይ መኮንን፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሚያወጣቸውና በመድረክ ላይ በሚያቀርባቸው ጥልቅ ሃሳቦችን ያዘሉ ውብ የሥነግጥም ሥራዎቹ፣ ከፍተኛ አድናቆትንና ዕውቅናን ተቀዳጅቷል፡፡ “ከሁሉም በላይ ገጣሚ ነኝ” የሚለው ነቢይ፤ “ጥቁር፣ ነጭ፣ ግራጫ ግጥሞች” እና “ስውር ስፌት- (ሁለት ቅጾች)” የግጥም መድበሎችን ለአንባቢያን አቅርቧል፡፡ በመጻሕፍት አሰባስቦ ከሰነዳቸው የሥነግጥም ሥራዎቹ ሁለት እጥፍ ያህል የሚሆኑት ግን በየቦታው ተበታትነው ነው የሚገኙት፡፡ አሰባስቦ ለህትመት የማብቃት ሥራ ይጠይቃል፡፡
ነቢይ በደርግ ዘመን በኢህአፓ አባልነቱ ታስሮ ለ10 ዓመታት መከራውን በልቷል፡፡ ነገር ግን ደርግንም ሆነ አገሪቱን ወይም ሌላ ተቀናቃኝን ሲያማርር፣ ሲወቅስ ወይም ሲረግም ማንም ሰምቶት አያውቅም፡፡ እንደ ብዙዎቹ የጦቢያ ፖለቲከኞች፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታግዬለታለሁ፣ ደሜን አፍስሼለታለሁ፣ ሞቼለታለሁ ወዘተ እያለ አይመጻድቅም፡፡ በሚመጻደቁትም ይስቃል፡፡ እሱና ዘመነኞቹ በአብዮቱ ወቅት ያሳለፉትን በጎም ሆነ ክፉ፣ ያሁኑ ትውልድ እንዲማርበት፣ ከመጻፍና ከመናገር ቦዝኖ አያውቅም፡፡ ጽንፈኝነትና አክራሪነት እንደማያዋጣ ሲመክር ኖሯል፤ በጽሁፎቹ፡፡ ቁምነገርን በቀልድ እያዋዛ ማቅረብ ይወዳል - በጽሁፉም በንግግሩም፡፡ መድረክ ላይ ከወጣ ታዳሚን በሳቅ ያፈርሳል - አፍ ያስከፍታል፡፡ አንደበቱም ብዕሩም የተባለት የጥበብ ባለሙያ ነበር፡፡
ነቢይ ባህልና ጥበብ አገርን እንደሚለውጥ ጽኑ እምነት ነበራ፡፡ በዚህም እምነቱ ነው አዲስ አድማስ በተለይ ጥበብና ባህል ላይ አተኩራ እንድትሰራ ያደረገው፡፡ የየሳምንቱን ርዕሰ አንቀጽ በተረትና ምሳሌ በመጻፍ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ተረቶችን ጽፏል - ለጋዜጣው ርዕሰ አንቀጽ፡፡ አያሌ የርዕሰ አንቀጽ አንባቢያንንም አፍርቷል፡፡
የሥነጽሁፍ ረዳት ፕሮፌሰሩ የሻው ተሰማ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ”ሙያና ጥበብ ሲመጋገብ - ከታወቁ ደራስያን ሥራዎች አኳያ“ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፋቸው፤ “በርካታ የነቢይ ተደራስያን ነቢይን የሚያውቁት በተለይ በ«አዲስ አድማስ» ጋዜጣ ላይ በሚጽፋቸው ተረቶቹ ነው። ከዶ/ር እንደለ ጌታ ከበደ ጋር ባደረገው አንድ ውይይት ላይ እንዳስተዋልነው፣ በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ ተረቶችን በጋዜጣው ላይ በርእሰ አንቀጽነት ጽፏል። ይህ ለየት ያለ የርእሰ አንቀጽ ይትበሃል፣ ለጋዜጣው የተለየ የተነባቢነት ሞገስ እንዳጎናጸፈው መናገር ይቻላል።” ብለዋል፡፡
ነቢይ፤ ሃሳብ አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኝ ድልድይ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ለዚህም ነው የተለያዩ ሃሳቦችና አስተያየቶች በአዲስ አድማስ ላይ ያለገደብ በነጻነት የሚስተናገዱት፡፡ እርሱም እንደ ጋዜጣው መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ ሁሉ ሃሳብን አይፈራም፡፡ ለህዝብና ለአገር የሚጠቅም አንዳች ሃሳብ ያላቸው ወገኖች ሁሉ፣ ሃሳባቸውን እንዲገልጹና እንዲጽፉ ሲያበረታታ ነው የኖረው፤ በዋና አዘጋጅነት ዘመኑ ሁሉ፡፡
አዲስ አድማስን ለምን እንደመሰረቱ ባስረዳበት የመጀመሪያ ርዕሰ አንቀጹ ላይ፤”የጋዜጣ ስራ እንጀምር ያልንበት አንዱ ምክንያት የልባችንን ለመናገር ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ሌሎቹ ዘንድ የጎደለ የመሰለንን እኛ ልንሞላ ነው፡፡ ‘ምሉዕ በኩላሄ’ (ፍፁም የተሟላ) ያደርገዋል ባንልም፣ የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለማድረግ ነው፡፡ ሁላችንም ያለንን ካልወረወርን፤ የአንባቢዎቻችን ገደል - አከል የኢንፎርሜሽን ረሃብ፣ ገርበብ ሊል አይችልምና የፕሬስ እድር ውስጥ ገብተን ጠበል እንጠጣ ብለን ነው” ብሏል፤የዛሬ 24 ዓመት ለንባብ በበቃው የመጀመሪያው የጋዜጣው ዕትም፡፡
ከጋዜጣው መሥራቾች አንዱ የነበረው ነቢይ መኮንን፣ ስለ አዲስ አድማስ ዓላማ ሲያስረዳም፤ “የጋዜጣችን አላማ፤ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በባህላዊ ጉዳዮች ዙሪያ፤ መሰረታዊ እውቀትን ሊያስጨብጡ፣ አስተዋይና ሀላፊነት ሊሰማቸው የሚችሉ ዜጎችን ለመፍጠር የሚያግዙና ያሉትንም ለማጠናከር የሚበጁ ዜናዎችን በወግ በወጉ ማቅረብ ነው፡፡” ሲል ገልጾታል፤ በርዕሰ አንቀጽ ፅሁፉ፡፡
ለዛሬ በሁለገቡ ከያኒና የአዲስ አድማስ የቀድሞ ዋና አዘጋጅ ነቢይ መኮንን የጥበብ ህይወት ዙሪያ ያጠናቀርኩትን አጭር የግል ዳሰሳዬን በዚሁ እቋጫለሁ፤ ዳግም እንደምመለስበት ቃል በመግባት፡፡ ራሱ ነቢይ በአንደበቱ እንደተናገረው፣ ከሁሉም በላይ ግጥም ይበልጥበታል፡፡ ነፍሱ ለግጥም ታደላለች፤ ገጣሚ የሚለውን መጠሪያም ይወደዋል፡፡ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የምንለያየው በራሱ ግጥም ይሆናል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ለነቢይ ለቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶችና አድናቂዎች መጽናናትን ከልቤ እመኛለሁ፡፡ የነቢይን ነፍስ ፈጣሪ በአጸደ ገነት ያኑርለት፡፡
ለራስ የተጻፈ ወቀሳ
እንጠራራ እንጂ
እንፋለግ እንጂ
ከያለንበቱ
ሰው የለም አንበል፣ አለ በየቤቱ
ምን ቢበዛ ጫናው፣ አንገት ቢያቀረቅር
ምን አፉ ቢታፈን፣ ዝም ቢልም አገር
ምን መሄጃ እስኪያጣ፣ መንገዱ ቢታጠር
ጎበዝ እንደ ጭስ ነው፤ መተንፈሻ አያጣም
ቀን መርጦ ሰው መርጦ መነሳቱ አይቀርም፡፡
(ነቢይ መኮንን፤ አዲስ አድማስ፤
ግንቦት 9 ቀን 1995 ዓ.ም)
Published in
ነፃ አስተያየት