Saturday, 06 July 2024 20:28

ነቢይን የሚያውቁት ምን አሉ??

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“ነቢይን የሚያውቅ ሁሉ ሳቁን ይጋራል”
‹‹እምቢልታ ማስነፋት ነበር አመላችን
ነጋሪት ማስመታት ነበር አመላችን
ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን››
ብለው ነበር አሉ፣ በአንድ ቀን አዳር፣ ከንግሥትነት ወደ ወይዘሮነት የተቀየሩት እመቤት፡፡
ይህ አባባል ዛሬ ነበር ሊባል ለተገደድነው ለነቢይ ይሁን ለሕያዋን እንደሚሠራ በደንብ ማሰብ ይፈልጋል፡፡ ነቢይ መቶ ወዳጆች ካሉት ከሁሉም ጋር የተለያየ ትዝታ፣ የተለያየ ወግ፣ የተለየ ሣቅ፣ የተለየ ትረካ ያስቀመጠ ሰው ነው፡፡ (እንዲያውም ቢያንስ አንድ ሰው ጋ መቶ የተለያየ ታሪክ አስቀምጧል፡፡) ነቢይን የሚያውቅ ሰው ሁሉ የሚጋራው አንድ ነገር ሣቁን ነው፡፡ ሮንግ ተርን ፊልም ኮሚዲ አድርጎ እንደመተረክ ያለ፣ በሕመም ጭምር ፈገግ ብሎ ማውራት የነቢይ ወዳጆች የጋራ ትዝታ ነው፡፡
ነቢይ በራሡ አባባል ‹‹ቀለሜዋ›› የሳይንስ ተማሪ መኾኑና ኬሚስትሪን ደህና አድርጎ ማጥናቱ ጠቅሞት ይመስላል፣ ፔሬዲክ ቴብሉን ገልብጦ፣ ወደ ጥበብ አምጥቶት ተርጓሚ፣ ደራሲ፣ ጸሐፌ-ተውኔት፣ ተዋናይ፣ ሰዓሊ፣ ተራኪ፣ ገጣሚ፣ ጋዜጠኛ… በሁሉም መስክ ልክ በልጅነቱና በወጣትነቱ ትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪዎቹ እንደሚሠጡት ውጤት 100 ከ 100 በሚያሰጥ ብቃት ተወጥቶታል፡፡ ችግሩ ግን ነቢይ ይህ ሁሉ ማዕረግ ይጠብበዋል፡፡ ነቢይ ራሡ ማዕረግ ነው፡፡
ነቢይ መኮንንን ወደፊት ለሚመጣ ትውልድ ለማስረዳት ቀላሉ መንገድ፣ (ይህም ቢኾን ያንሰዋል) ነቢይ ‹‹ጉግል›› ነው ማለት ነው፡፡ ስለ ቅጠል ሆነ ስለ ሰው አንድ ቃል ብቻ ሲጠራለት ‹‹ኦ እሱኮ አሪፍ ነው፡፡›› ብሎ ይጀምራል፡፡ በቃ ከዚያ ተከትሎ የሚናገራቸው ነገሮች… ራሱ የኮምፒውተሩ ጉግልም የሚያውቃቸው አይመስለኝም፡፡ ደግሞ የሚያወራው መረጃ አይደለም - መረጃማ ሁሉም ሰው ያውቃል፡፡ ነቢይ ግን ራሱ ሰውዬው ቢጠየቅ ስለራሱ የማይናገረውን ሁሉ ያስረዳል፡፡ ነቢይ እንደዚያ ነው፡፡
ነቢይን አግኝቶ ያናገረም ያላናገረም፣ ‹‹ይህን ጉዳይ አንስቼ ሳላወራው…›› ብለው መጸጸት አይቀርላቸውም፡፡ ምክንያቱም ነቢይን አግኝተው ለሚያወሩት ሁሉ ቅርብ ሆኖ የማናገሩን ያህል ዛሬ ሙሉ ቀን ቢያወሩት፣ ቀኑን ሙሉ የሚያወራው ነገር ካለመሰልቸቱም በላይ ያልነገረኝ የቀረ አለ ማለት ነው ያስብላል እንጂ፣ በፍጹም አናግሬዋለሁ ብሎ እፎይ አያስብልም፡፡
ነቢይ መሞቱ እጦት የሚኾነው ለቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ፣ ለሚያውቁት ለሚያውቃቸው አንድ ትልቅ ወዳጅ መንጠቁ እንዳለ ኾኖ፣ እንደ ሰው ግን የሞተው አንድ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ የዚህን ሰው አምሳያዎች ለማግኘት ምናልባትም ዘመናትን መጠበቅ ግድ ይላልና፣ እርሱ ለገብረክርስቶስ ደስታ የተጠቀመውን አገላለጽ ጠቅሰው፣ ወዳጁ በኃይሉ ገብረመድኀን አንተም ያው ነህ እንዳሉት፤
‹‹ነቢይን ዓይነት ሰብል ለማግኘት ሥንት ዘመን ማረስ ያስፈልጋል?››
አንድ ወዳጁ ነቢይን ሲገልጸው ምን አለ?
‹‹ነቢይን ግጥም አንብብልኝ፣ ድርሰት ተርክልኝ ማለት ሳይሆን፣ ጠዋት ሲነሳ ጀምሮ በሄደበት እየተከተለ የሚቀርጽ ካሜራ አሰናድቶ ከአካሄዱ፣ አቀማመጡ ጀምሮ ጫማ ጠራጊዎችን፣ የረዥም ዘመናት ወዳጆቹን፣ ዛሬ ያገኙት አድናቂዎቹን፣ ምግብ የሚበላበት ውኃ የሚጠጣበት ቦታ ከአስተናጋጅ፣ ከጥበቃዎች ጋር ሁሉ ሲያወራ መቅረጽ ነው የሚሻለው፡፡›› ግን እንደዚያስ ቢኾን ነቢይ ያልቅ ይሆን?
ደህና ሁን ናዝራዊው ነቢይ፡፡
ደህና ሁን የአድማሱ ሰው፡፡
ደህና ሁን ነቢይ መኮንን፡፡
ሰው ስለሆንህ አመሠግንሃለሁ፡፡
(ዮሴፍ ዳሪዮስ ሞዲ)
በሰቀቀን የፈራነው፣ ሰንሸሸው የከረምነው
እውነት ደረሰ
የቃል ኃይል፣ የኪነት ጉልበት፣ መቅኒው
ተሰብሮ ፈሰሰ፤
ትውልድን የሚያገናኘው፣ የግጥም የቅኔው
ድልድይ፣
ይኸው ዛሬ ፈረሰ፣
ዛሬን ለቀሪው ትቶ፣ ወደ ትላንት ፈለሰ
እንደ ነፋስ ሲነፍሰን ክርሞ፣ እንደ ውሃ ፈሰሰ፤
የብዙ ተጠየቅ መላሽ፣ የመንፈቅ የዓመቱ
ስንክሳር፤
በወግ ያልተነበበው፣ የየአሳራችን አሳር፤
ከአትሮኑሱ ላይ ወረደ፤
ገድሉን ሰምተን ሳንጨርስ፣ ሰቀቀናችን ላይ
ረፈደ፤
የሁለት ትውልድ መስካሪው፣
መሲህ ነህ ያልነው ነቢይ፣  ላይመጣ ሄደ
ነጎደ፤
ይብላኝልን፣
ያለ ምሥክር ለቀረን።
በሰላም እረፍ ጋሽ ነቢይ !!!!
(ገጣሚ አበባው መላኩ)

Read 830 times