Saturday, 06 July 2024 20:31

የኢትዮጵያ ክብር የሚታደሰው ከተረጂነት ስትላቀቅ ነው - የውጭ ጫናዎችን ስታሸንፍ።

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ተረጂነት እንደ አዙሪት ነው። ከዓመት ዓመት የእርዳታ እጅ ይጠብቃሉ። ጥገኛ ይሆናሉ። የረጂዎች ታዛዥና ተጎታች የመሆን ፈተና ላይ ይወድቃሉ። ክብራቸውን ያጣሉ። እንዲህ ዐይነት ውርደት፣ በጭራሽ ለኢትዮጵያ አይመጥንም። ለየትኛውም አገር ቢሆን፣ የእርዳታ አዙሪት ጥሩ አይደለም። ለኢትዮጵያ ግን በጭራሽ መታሰብ አልነበረበትም።   
ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት። የረዥም ዘመን ታሪክ ባለቤት ናት። በዓለም ታሪክ ሕልውናቸውን አስጠብቀው በነጻነት መዝለቅ የቻሉ አገራት ቢበዛ ከአምስት አይበልጡም። ኢትዮጵያ ከእነዚህ ውስጥ የምትጠቀስ ናት። ለአፍሪካ የነጻነት ፋና ለመሆን የበቃች አገር ናት። በሕዝብ ብዛት ከዓለም 10ኛ ናት። የተረጂነት አዙሪት በፍጹም ለኢትዮጵያ አይመጥንም።
ከተረጂነት ጋር አብሮ የሚመጣ የታዛዥነትና የተጎታችነት ውርደት ለኢትዮጵያ ባህል “አለርጂክ” ነው። ባለፉት ወራት በመላ አገሪቱ በተካሄዱ ውይይቶች ላይ፣ ከሕዝብ የቀረቡ ሐሳቦች ይህን መንፈስ አጉልተው አሳይተዋል ይላሉ - የአዲስ አበባ አስተዳደር የሕዝብ አደረጃጀት ም.ኀላፊ ዘውዱ ከበደ።
ለነገሩ፣ “ውርደት ከኢትዮጵያ ባህል ጋር አይሄድም” የሚል የቁጭት ስሜት በሕዝብ ዘንድ መፈጠሩ አይገርምም።
የሕዳሴ ግድብን ለማስተጓጎልና ለማስቆም ብዙ ዘመቻ ተካሂዶብናል። በኢትዮጵያ ላይ እየተደራረበ የመጣባትን የውጭ ጫና እንዲሁ እንደዘበት የምንረሳው አይደለም። ኢትዮጵያውያንን ምንኛ እንዳስቆጣቸው እናስታውሳለን። እንዴት አናስታውስም? በኛው ዘመን በኛ ትውልድ ላይ የተካሄደ ዘመቻ ነው። የራሳችን ታሪክ፣ የእያንዳንዳችን ትዝታ ነው። ያኔ ክፉኛ አንገብግቦናል። አንገሽግሾናል። ዛሬም ይከነክነናል።
“የሕዳሴ ግድብ ግንባታን አቋርጡ፤ አለበለዚያ እርዳታ እንከለክላለን!” የሚል ማስፈራሪያ ሊዋጥልን ይቅርና መታሰቡ ራሱ ይተናነቀናል።
በተረጂነት ሰበብ የሚመጣ የውጭ ጫና እንዲህ ነው ለካ! አገራዊ ጸጋዎቻችንን እንዳናለማ፣ ሠርተንና ገንብተን እንዳናድግ አስሮ የሚይዘን ከሆነ ዘላለም “ተረጂ” ሆኖከመቅረት ውጭ ምን አማራጭ ይኖረናል? ተረጂነት ተረጂነትን ይወልዳል የሚባለውም ለዚህ ነው። “ተረጂነት ይብቃ” ብለው በጥሰው ሰብረው ካልተላቀቁ፣ እውነትም “አዙሪት ነው” ያስብላል።
በእርዳታ ሰበብ የውጭ ጫናዎችን አሜን ብለን ከተቀበልንማ፣ ከነአካቴው ተስፋችንን ከማጨለም አይመለስም። አገራችን ታዛዥና ተጎታች እንድትሆን ከተገደደች፣ እንዴትስ “አገር አለን” ብለን በሙሉ ልብ እንናገራለን?
የተረጂነት ጣጣ ብዙ ነው። ሁሉንም ነገር ይነካል ይላሉ አቶ ዘውዱ። የሕልውና ፈተና ይሆናል። በኑሮ የመሻሻል ተስፋን ያጨልማል። የኢኮኖሚ እድገትንና የአገር ብልጽግናን አሰናክሎ ያስቀራል። የአገር ሉዓላዊነትን ያሳጣል። የአገርና የሕዝብ ክብርን ያዋርዳል። በተረጂነት ሳቢያ የሚመጡ አደጋዎች ኢኮኖሚን፣ ፖለቲካን፣ ባሕልን ሁሉ የሚያበላሹ ናቸው።
ተረጂነት ያስጠቃል፤ ያስደፍራል፤ ያዋርዳል። ከተረጂነት የመላቀቅ ጉዳይ ትልቅ አገራዊ አጀንዳችን መሆን ያለበትም በእነዚህ ምክንያቶች ነው። ተስፋችን መጨለም የለበትም። ለልጆቻችን ተረጂነትንና የዕዳ ሸክም ማውረስ የለብንም። የአገራችንና የሕዝባችን ክብር መታደስ አለበት። አገራችን ከተረጂነት በመላቀቅ ወደ ብልጽግና መጓዝ አለባት። ደግሞም ትችላለች። እንደምትችልም ከራሳችን ልምድና ከራሳችን የስኬት ጅምሮች መማር እንደማይከብደን አቶ ዘውዱ ይገልጻሉ።
ፈተናዎችን በራሳችን ዐቅም ተቋቁመን መሻገር እንደምንችል በኮቪድ ወረርሽ ወቅት አይተናል። ያኔ የዓለም ኢኮኖሚ እንደተናጋ ሁላችንም እናውቃለን። የብዙ አገራት ኢኮኖሚ አሽቆልቁሏል። በኢትዮጵያ ግን፣ ወረርሽኙን ከመከላከልና ከመቋቋም ጎን ለጎን፣ ኢኮኖሚያችንም እንዲያድግ በጥበብና በትጋት ስለጣርን ተሳክቶልናል።
በኮቪድ ምክንያት የዓለም አየር መንገዶች ከፍተኛ ኪሳራ ላይ ሲወድቁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በርካታ የመፍትሔ አማራጮችን በመጠቀም ውጤታማ ሆኗል። ይህም ብቻ አይደለም። ወረርሽኙን ከመከላከል ባሻገር ለዘለቄታው የሚጠቅም መንገድ የጤና ተቋማትን ዐቅም ለማሳደግ ተችሏል።
ኢትዮጵያ ችግሮችን በራሷ ዐቅም ተቋቁማ ወደ ተሻለ ከፍታ ማደግ አያቅታትም።   
የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በሚመለከት በኢትዮጵያ ላይ የደረሰባት ከባድ የውጭ ጫናም ሁለት ነገሮችን ያስተምረናል ብለው እንደሚያምኑ አቶ ዘውዱ ይገልጻሉ።
በአንድ በኩል፣ በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ የውጭ ጫናዎችን ተቋቁመን፣ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ ተከራክረን የማሸነፍ ዐቅም እንዳለን አሳይተናል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በተረጂነት ሳቢያ የሚመጣ የውጭ ጫና የቱን ያህል አደገኛና የቱን ያህል ቅስም ሰባሪ ሊሆን እንደሚችል በዚሁ አጋጣሚ አይተናል። የሕዳሴ ግድብን ለማስቆም የተካሄደ ዘመቻ፣ የኢትዮጵያን ቅስም ለመስበር የተደረገ ሙከራ ነው ማለት ይቻላል።
ለዚያውምኮ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በብድር ወይም በእርዳታ የሚካሄድ አይደለም። እንደዚያ ቢሆንማ፣ ከመነሻውም እርዳታና ብድሩ አይገኝም። በሆነ ተዓምር እርዳታ ተገኝቶ የግድብ ግንባታ ቢጀመርም፣ የትም አይደርስም ነበር። እርዳታው ተቋርጦ፣ የግድብ ግንባታው ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀር ነበር።
ኢትዮጵያ በራሷ ዐቅም የምትገነባው ስለሆነ ነው፣ “የአገር ምኞት” በተግባር “የአገር እውነት” ወደመሆን እየተሸጋገረ የመጣው።
እንዲያም ሆኖ፣ ከብዙ ፈተና አላመለጠም። በውጭ እርዳታ የሚካሄድ ፕሮጀክት ባይሆንም፣ ከውጭ ጫና አልዳነም። ለምን? ኢትዮጵያ ተረጂ አገር ስለሆነች በውጭ ተጽዕኖ እጇን መጠምዘዝ እንችላለን ብለው ስላሰቡ ነው። “በደካማ ጎኗ እንግባባት” ብለው ነው የተረባረቡባት። “ለግድብ ግንባታ ባይሆንም ለሌላ ለሌላ ነገር እርዳታ ትፈልጋለች። እርዳታ እንቀንሳለን፤ ከፈለግንም እናቋርጣለን” ብለው የማስፈራራት ቀዳዳ አግኝተዋል።
እንዳሰቡት ቢሳካ ኖሮ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለዘመናት ይቅር የማንለው ከባድ የታሪክ ቁስል ይሆንብን ነበር። ትልቅ የታሪክ ስብራት በደረሰብን ነበር። ፊት ለፊት የመጡ ወረራዎች ሳይበግሯት አሸንፋ መልሳለች። ወረራው እጅግ ሲከፋም “አሻፈረኝ” ብላ፣ እጅ ሳትሰጥና በባርነት ሳትንበረከክ ነጻነቷን አስከብራለች። ዛሬ፣ “ያለ ጦርነት እንድትንበረከክ መጠበቃቸው” ቢያንገበግበን አይገርምም። ነገር ግን አንድ እውነት እንድንገነዘብም ያስገድደናል። ተረጂነት ያስደፍራል፤ ያስጠቃል፤ ለውርደት ያጋልጣል።
ታዲያ ምን እስኪመጣብን፣ ምን እስክንሆን ነው የምንጠብቀው? እስከ መቼስ ነው የእርዳታ እጅ የምናየው? ለምንስ ነው ከትውልድ ወደ ትውልድ የምናስተላልፈው?
በእርግጥ “ተረጂነት ውርደትን ያመጣል” ሲባል፣ በአደጋ ጊዜ ያገዙንን ሰዎች ለማጣጣል አይደለም። እንዲያውም በችግር ጊዜ የደረሱልንን ለማመስገን አናመነታንም። ኢትዮጵያ ታመሰግናለች። አቶ ዘውዱ እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከማመስገን ወደ ኋላ አይለም። ክብር የሚያውቅ አገር ውለታ ቢስ አይሆንም። ኢትዮጵያ ደግሞ ክብር ታውቃለች። ታሪኳ ነው። ባለውለታዎቿን ታመሰግናለች።
ነገር ግን “ተረጂ” ሆና ለመቅረት አይደለም። በጭራሽ! አዎ ተከባብሮ መተጋገዝ መተባበር መልካም ነው። ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት የራሷን ድጋፍ እንዳበረከተች አቶ ዘውዱ ይናገራሉ። በቅርቡ የሩዋንዳው መሪ ፖል ካጋሜ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ ያበረከቱትን የምስጋና ሽልማት በምሳሌን እንደሚጠቀስም ገልጸዋል።
በበርካታ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሰማርተዋል። ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የተላበሱና የአፍሪካዊ ወዳጅነትን የሚያስፋፋ አገልግሎት ሰጥተዋል።
አሜሪካ የሽብር ጥቃት በደረሰባት  ጊዜ ኢትዮጵያ አጋርነቷን አሳይታለች። ኢትዮጵያውያን ደቡብ ኮሪያ ድረስ ሄደው መስዋዕት ከፍለዋል። ወደ ኮንጎም ተሰማርተዋል ። በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ በስልጠና ረድታለች። በዓለም መድረክ ዋና አለኝታ ሆናላቸዋለች።
እንዲህ ዐይነት የመደጋገፍ ተግባር መልካም ነው። ከመከባበር ጋርም ይሄዳል።
አንዱ አገር የሁልጊዜ ረጂ፣ ሌላኛው አገር የሁልጊዜ ተረጂ ከሆነ ግን መከባበርን ያጠፋል።
“ተረጂነት? በጊዜ ካልተገታ፣ “ጌታና አሽከር” ለመፍጠር ይጠቀሙበታል። በወዳጅነት ምትክ የበላይነትና የበታችነት ስሜትን ያቀነቅኑበታል።
“ቁጭ ብድግ በሉልኝ” የሚል ይመጣል።
“ማን ነው አጎንብሶ ያልሰገደልኝ? ማን ነው ተንበርክኮ ያልተለማመጠኝ?” ብሎ ማስፈራራት ይጀምራል።
ኢትዮጵያ እንዲህ ዐይነቱን ውርደት እንደማትቀበል በተደጋጋሚ አሳይታለች።
ሁነኛውና አስተማማኙ መፍትሔ ግን፣ ችግሮችን በራሷ ዐቅም ተቋቁማ በመሻገር  የሚገኝ መፍትሔ ነው። ከተረጂነት በመውጣት ነው የውጭ ጫናዎችን ሙሉ ለሙሉ ማምከን የሚቻለው።
እንዲያውም ከረጂነት ውጥታ ወደ ብልጽግና ስትሸጋገር፣ ለወዳጅነት የሚፈልጓት፣ የሚያከብሯትና ከጎኗ የሚቆሙ ይበረክታሉ። በጠላትነት ስሜት ክፉ የሚያስቡባት ደግሞ ሐሳባቸውን ይለውጣሉ። ወይም ለክፉ ያሰቡትን ዋጥ አድርገው ያስቀሩታል። ለጥቃት ሊሰነዘሩ የነበሩ እጆችም ይሰበሰባሉ።
ከተረጂነት የመላቀቅ ሐሳብ ዙሪያ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል እንዲህ ዐይነት መሠረታዊ መግባባትና የጋራ ጽኑ ዓላማ በውይይት እንደተፈጠረና በውይይት እየዳበረ መሄድ እንዳለበት የገለጹት አቶ ዘውዱ፣ ከተረጂነት መላቀቅ ለኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የአገር ክብር ጉዳይ ነው በሚለው የጋራ አቋም ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ።
የውጭ ኃይሎች የሚደፍሩት ሳይሆን የሚያከብሩት አገር፣ የሚያከብሩት ሕዝብ እንሆናለን - ለጠላትነት የሚያስቡት ሳይሆን ለወዳጅነት የሚፈልጉት።
ደካማ ጎን አይተው ጥቃት የሚሰነዝሩበት ሳይሆን፣ “ጠንካራ ነው፤ ለምንም አይበገርም፤ የሚቃጡበትን ያሳፍራል” ብለው ይጠነቀቃሉ። “ኢትዮጵያ የሚያከብራትን ታከብራለች” ብለው የሚተማመኑባት ጠንካራ አገር ትሆናለች። ክብሯም ይታደሳል። በኛ ዘመን የኢትዮጵያን ክብር ማዋረድ የለብንም።
“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ከዕዳ ወደ ምንዳ” እንዲሉ ነው። ከተስፋ ብርሃን ወደ ተጨባጭ ብርሃን መሸጋገር ይቻላል። ይህም ብቻ አይደለም። ካወቅንበትና ከሠራንበት፣ አገራችን ዕምቅ ጸጋ የበዛላት አገር ናት። በአገራችን በየአካባቢያችን የሚገኙ ጸጋዎችን ወደ ብልጽግና ልንቀይራቸው እንችላለን። በአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የምንሆንበት ጊዜም ሩቅ አይሆንም።
ያኔ፣ የተረጂነት ታሪክ የድሮ ትዝታ ይሆናል። በችግር ጊዜ በቀና ልቦና የረዱንን የምናመሰግንበት ትክክለኛው መንገድም፣ ከተረጂነት በመውጣትና ራሳችንን በመቻል ነው። ከራሳችን አልፈን ወደ ብልጽግና ስንጓዝና ሌሎችን የመርዳት ዐቅም ሲኖረንም ነው “ውለታ ከፋይ” የምንሆነው ይላሉ - አቶ ዘውዱ ከበደ።


Read 355 times