Saturday, 06 July 2024 20:31

“እኔስ ሮጬ አመልጣለሁ፤ ታሪኬ ወዴት ያመልጣል?”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

የሚቀጥለው ታሪክ ዛሬ እንደ ተረት ይወራል እንጂ ዱሮ እውነት  ነበር።
በአንድ የሀገራችን አሰቃቂ ዘመን፣ የአንድ ከፍተኛ፣ ሊቀመንበር  ነበር። ክፉ ነው ይሉታል - ልጆቻቸውን ከጉያቸው ነጥቆ ያሰረባቸው እናቶች። ክፉ አረመኔ ነው ይሉታል - ልጆቻቸው በእስር ቤት ተሰቃይተው የተገደሉባቸው አባቶች። ነብሰ-በላ ነው ይሉታል- ጓደኞቻቸው የሞቱባቸው ወጣት ባልንጀሮቹ።
ይህ ሰው ድንገት በከፍተኛው ውስጥ ያልታሰረ ወጣት ካየ፤ ስራውን በሚገባ ሳይሰራ እንደኖረና “አብዮታዊ ግዴታውን እንዳልተወጣ” አድርጎ ይቆጥረዋል ይባላል። ስለዚህም፤ ወጣቱን ያስጠራውና፤
“እስከዛሬ የታባክ ተደብቀህ ከርመህ ነው፣ ገና አሁን ብቅ ያልከው?” ይላል።
ወጣቱ ግራ በመጋባትና በድንጋጤ፤
“ኧረ በጭራሽ ተደብቄ አይደለም ጓድ!” ይላል።
“ጉድጓድ ግባና ጓድ አትበለኝ! በእንዳንተ ያለ ጸረ- አብዮተኛ ‘ጓድ’ አልባልም!”
“ኧረ ጸረ አብዮተኛ አይደለሁም ጓድ!”
“ጓድ አትበለኝ!- ጓድነቴን ታረክስብኛለህ ነው የምለው! ይልቅ ና ቅደም!” ብሎ እስር ቤት አስገባው።
አንድ ቀን ደግሞ ለእስረኞች ንቃት ለመስጠት እንደተለመደው ንግግር ሲያደርግ፤ አብዮት ጥበቃው ከጎኑ ነበር። “ጓድ፤ እነዚህ የምታስተምራቸው እስረኞች እኮ ማታ ይወጣሉ (ይገደላሉ)፤ ምን አለፋህ?” ይለዋል።
ሊቀመንበሩ፤ “ቢሆንም፤ ነቅተው ይሙቱ” አለ፤ ይባል።
ጊዜው አለፈና ይህ ሊቀ መንበር ዩኒቨርሲቲ ገባ- ህግ ሊያጠና። ታዲያ እንደ ሱው ህግ ት/ቤት በዚያው ወቅት የገቡ አንድ ተረበኛ ሽማግሌ አሉ። ከሱ ጋር የአንድ ሀገር ልጆች ናቸው። እኚህ ሽማግሌ ለረዥም ጊዜ ዳኛ ሆነው የሰሩ ናቸው።”
“ለምን ህግ ይማራሉ?” ሲሏቸው፤” “ምናባቴ ላድርግ፤ ‘ያለወረቀት አይሆንም’ የሚባልበት ዘመን መጣ’ኮ! እኛ ‘የልምድ አዋላጅ’ የሚል ስም ተሰጥቶናል!” እያሉ ሰውን ያስቁታል። ታዲያ አንድ ቀን እኚህ ጨዋ አዋቂ ሽማግሌ፣ ያን ከፍተኛ ሊቀመንበር እዚያው ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያገኙትና፤
“ኦ እንዴት ነው ያገሬ ልጅ!” ብለው ሰላምታ ያቀርቡለታል።
“እንደምን ነዎ? በአገር አሉ እንዴ እርስዎ?” ይላል ሊቀመንበሩ።
“በዚያ አንተ ሞቅ ባለህ ዘመን ‘አለሁ’ አልልም ነበር እንጅ፣ መኖርስ አለሁ፤ ከአገሬ ወዴት እሄዳለሁ?” ይሉና ይመልሱለታል።
“እርስዎ ይሄን ተረብ ዛሬም አልተውትም እንዴ?”
“‘ተራቢ ቢሞት ተረብ አይሞትም’ ልበላ፤ በአንተው የትግል ቋንቋ!”
“እንደው አሁን ጊዜው አለፈ እንጂ፣ እርስዎን ነበር እዚያ እስር ቤት አስገብቶ እየገረፉ ማስለፍለፍ?”
“በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ! ምነው ምን አደረኩህ ያገሬ ልጅ! እኔን! የገዛ ወገንህን! በአገር አማን ትጎመዠኝ!?...እሱ ይቅር ይበልህ…”
አሉና ወሬውን ለመቀየር “ለመሆኑ ወደ ግቢ ምን እግር ጣለህ?” ብለው ይጠይቁታል።
“ኦ አልነገርኩዎትም ለካ! እዚህ ዩኒቨርሲቲ ህግ እየተማርኩ‘ኮ ነው። ሁለተኛ አመቴ ነው” አላቸው ሞቅ አድርጎ።
ይሄኔ ሽማግሌው በድንጋጤ አናታቸውን ይዘው፤
“እንዴ!! ፈርደህ ጨርሰህ?!”
***
ፍትህና ርትዕ የጎደለው ስርዓት ውስጥ መኖር ክፉ መርገምት ነው። የአሜሪካ ሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር፤ “የትም ቦታ የሚፈጠር ኢ-ፍትሃዊነት፤ በማንኛውም ቦታ ያለውን ፍትሃዊነት አደጋ ላይ ይጥለዋል” እንዳለው የፍትህ መጓደል እዚህ ድንበሩ፤ እዚህ ክልሉ የሚባል አይደለም። ግፍ በተፈጸመበት ቦታ ሁሉ ስለእውነት የሚጮሁ ድምጾች  ይጮሃሉ-ህያዋን ቢጠፉም ከመቃብር የሚመጡ አሉ ይባላል።
በታሪክ ያየነው ኢ-ፍትሃዊ ሁኔታ እንዳይደገም፣ የአሁን ዘመን ዜጎች ስለ መብትና ስለ ፍትህ መቆም፣ ስለ ሰላም ስንል መንገዶችን ሁሉ ማጽዳት ይገባል። ፍትህን የሚያጎድሉ፣ ዳኝነትን የሚያዛንፉ ሰዎች ድርጊታቸው አይታወቃቸውም። ስለሆነም የተበዳዮች ቁጥር ይበረክትባቸዋል። ያም ሆኖ ራሳቸውን አይጠብቁም። ታሪክ ይጠይቀናል አይሉም። የእነሱ ሚዛን፣ የእነሱ ፍርድ ሁሌ ልክ፣ ሁሌ ፍጹም ይመስላቸዋልና ህሊናቸውን አይቆረቁራቸውም።
ፒዩ ባሮዣ የተባለ ታዋቂ ጸሃፊ፤ “እንደ እኔ ጉዳዩ ውስጥ የሌለ ማንም ተራ ሰው፤ ጅብን፣ ሸረሪትንና ዛፍን በማየት በቀላሉ መኖር እንዳለባቸው ይረዳል። የፍትህ አስተሳሰብ አለኝ የሚል እቡይ ሰው ግን ጅብን ሲገድል፣ ሸረሪትን በእግሩ ሲድጣትና ከዛፍ ጥላ ስር ሲቀመጥ፣ ደግ ስራ የሰራ ይመስለዋል” ሲል ግራሞቱን የጻፈው በተመሳሳይ አንፃር ነው። ሰውም እንደ ሀዲስ አለማየሁ ስንኝ፤ “ዳሩ ዳኛ የለም ልተወው ግዴለም” ይላል እስከ ጊዜው።
የህዝብን ምሬትና ብሶት እህ ብሎ ማስተናገድ፣ የማንኛውም መሪ፣ ሃላፊና ሹም ግዴታ ነው። ህዝብን ባልሆነ ተስፋ መሸንገልም ሆነ መዋሸት ኗሪ ትዝብት ማትረፍ ነው። አንዴ ሊሸነገል ቢችል፣ ሌላ ጊዜ በጄ አይልምና።
ኦሉፍ ፓርም የተባሉ ስዊድናዊ መሪ፤ “ስለ ማህበራዊ ፍትህ የሚጠየቁ ጥያቄዎችን በሃይልና በወታደራዊ ጉልበት ምላሽ ለመስጠት መሞከር ከንቱ ቅዠት ነው። ከቶም ህዝቦች አይተውት የማያውቁትን ነጻነት እከለከልላችኋለሁ በማለት የህዝቦችን እምነት ለማግኘት መሞከር ከንቱ ድካም ነው” ያሉት እንዲህ ያለውን ሁኔታ አይተው ሳይሆን አይቀርም። በየትኛውም የስልጣን እርከን ላይ ብንሆን የሰራነው ክፉ ስራ እንደ ጥላ ይከተለናል። ፍትሃዊ ያልሆነ እርምጃና ጠያቂ የለንም በሚል የጉልበት ስሜት የሚመነጭ መብት-ረገጣ፤ በታሪክ የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል እንዳልሆነ የአያሌ አገራት ታሪክ ይመሰክርልናል።
አሪስቲድ ብሪያንድ የተባሉ የፈረንሳይ መሪ፤
“ጠመንጃችሁን አስቀምጡ። ማሽንገናችሁን እጠፉ። መድፎቻችሁን ፊታቸውን መልሱ። በመቻቻል፣ በመሸማገል፣ በሰላም እመኑ… ሀገር በታሪክ ውስጥ የምታድገው በጦር ሜዳ በጀግንነት በሚዋደቁላት ሰራዊት ብቻ አይደለም። ፊቷን ወደ ፍትህና ወደ መብት መልሳ ስለእነሱ ጠቀሜታ ስትቆም እንጂ” ብለው ነበር።
ሚዛናዊ ያልሆነ የአእምሮ ፍርድ፣ ስሜታዊ የሆነ ኢ-ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ፣ የማይፈጸም ባዶ-ተስፋና ሰበካ፤ ፍትህን ሊያጨልም የሚችል የማንአለብኝ አቅጣጫ… በታሪክ አስወቃሽ እንደሚሆኑ አንድና ሁለት የለውም። በጊዜ መታረም ያለባቸውን ነገሮች፣ በግትርነት አሻፈረኝ የሚል፣ የማታ ማታ እጣፋንታው፣ “እኔስ ሮጬ አመልጣለሁ፤ ታሪኬ ወዴት ያመልጣል?” ያለው ሰው አይነት እንዳይሆን፣ ከወዲሁ ማሰብ የአባት ነው።

Read 1352 times