Saturday, 06 July 2024 20:49

ነቢይ አድማስ ነው!

Written by  -ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

“--ነቢይ ደቡብ አፍሪካ ለሥነ ጽሑፍ ዎርክ ሾፕ ሄዶ፣ በፈርጥ መጽሔት ላይ የጻፈውን የጉዞ ማስታወሻ፣ ከአሥራ .ምማምን ዓመታት በኋላ ዘንድሮ እንኳ ሁለቴ አንብቤዋለሁ። እንደ ግጥም ይጣፍጣል፤ምሰላ አለው፤አቤት የዘይቤዎቹ ቅብጠትና ዳንስ!..የመስመር ቅኝቱስ?የተሸከሙት ተራራ? ..ነቢይ የሚለየው በአንዲት ስንኝ ሙሉ ዐለምን ወርቅ ማሸከሙ ነው። አቤት በአፉ ሲያወራስ?...ማር አይደል እንዴ  ጠብ የሚለው?--”

ገና የሰማይ መስኮት ሲከፈት፣ሰማያት ሳቃቸው በቅጡ ሳይፈካ፣አንድ ሬዲዮ ጋሽ አሰፋን አስታወሰኝ፤የሀገሬን ባንዲራ የሚመስለኝን ሰው። ጋሽ አሰፋን በልቤ መቅረዝ አድርጌ ለኮስኩት፣ፍም ትዝታዬን ቆሰቆስኩት። እወድደዋለሁ፣ደግሞ እፈራዋለሁ።
በዚሁ ሳቢያ ከጋሽ አሰፋ ጋር፣ የነቢይ መኮንንን የትዝታ ጉንጉኖች ተረተርኩና ተከዝኩ። በአጋጣሚ ባለፈው ሳምንት ”ስውር ስፌት 1ን” አንስቼ ሳነብብ፣ ስለ ነቢይ ብዙ-ብዙ ነገር አስታውሼ ነበር። ከበፊቱ የአዲስ አድማስ ደማቅ ትዝታ፣ አድማስ ወዲህ፤
በቅርብ ሃያ ሁለት ቺቺኒያ አካባቢ ተገናኝተን፣ ከወዳጄ ቢኒ ምዕራፍ ጋር ምሳ እየበላን የተጫወትነውን ሁሉ ገጽ በገጽ ገለጥኩት። ነቢይ ተጎድቶ ነበር። ቁመቱ ሁሉ ያጠረ እስኪመስል፣ ትከሻው ተንሸራትቷል። ውስጤ በጣም ባባ፤እንባዬን ዋጥኩት፤ፈራሁ!..ነቢይ እየተንሸራተተ ነው፤የሚታይ ንፋስ አለ።
ድሮም  ነቢይን ሳይ ሆዴ ይባባል፤በሙሉ ጉልበቱ፣በፈገግታው ፀሐይ መሐል እንኳ እሳሳለታለሁ።
ሁሌ፤ “ጌታ ሆይ ዕድሜ ስጠው!” ሳልል አላልፍም።
ነቢይና አዲስ አድማስ የረዥም ዐመታት ወዳጆቼ ናቸው። ብዙ የተማርኩበት፣ ወደ ንባብ የተገፋሁበት ዐለሜ ስለሆነ ልዩ ስሜትና አክብሮት አለኝ። አሰፋ ጎሳዬና ነቢይን ያወቅኋቸው በአንድ የዘመን አንጓ ነው። አዲስ አድማስ ያኔ ገና ድንግል ልጃገረድ፣የሁሉም ዐይን ያረፈባት ሳለች፣ያኔ የጫጉላ ቤት ዜማዎቿ ሲንቆረቆሩ፣በሁሉ ዐይን ብርቅዬ ሆና በቬሎዋ ውስጥ ዐይኖቿን ስታንከባልል፣ከዚያም  አርግዛ ስትወልድ ነቢይ የመጀመሪያ ባሏ፣የጫጉላ ቀኗ ሙሽራ ነበር። አዲስ አድማስ ዛሬ የሀገራችንን ፈርጥ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ሁሉ አምጣ የወለደች ኮከብ ናት። ያኔ ነቢይ  የዘመኑ አባወራ ነበር።
እንደ ልጅ እያግባባ፣አንዳንዱን እሽሩሩ እያለ፣ትከሻ እየመታታ፣ስንሳሳት እያረመ፣ስናጠፋ እየገሰጸ እጃችንን እንድንፈታ፣ መጽሐፍ ማንበብ እንድናዘወትር፣ በቀጥታና በተዘዋዋሪ አግዞናል። ከነቢይ ጋር በዚያ በጥድፊያ ዘመን፣በዚያ የሠርግ ቤት  ድባብ ረዥም ሰዐት ያወራንበት ጊዜ ነበር። ያ ቀን ፈጽሞ አይረሳኝም።
ነቢይን ፈዝዤ እያየሁ ዐለም ላይ ስላሉ ታላላቅ ገጣምያንና ግጥሞቻቸው፣ በሚጣፍጥ አንደበት፣በማይረሳ ዜማ አውርቶልኛል። “ምነው ባላቆመ፣ምነው ባልጨረሰ” እንዳልኩ ሕልም ከመሠለኝ ዐለም ባንኜ ስወጣ፣ ከደመና አበባ ላይ የረገፍኩ ነበር የመሰለኝ።...የያዝኩትን ፍሬ ግን አልጣልኩም።
ያ ትረካው ነቢይን ውስጤ ውስጥ በፍቅር ተከለው። ያኔ ጫፍ ያስያዘኝንና በጉጉት ያስደመጠኝን ሰዎችና ሥራዎቻቸውን ያነበብኩትና ያወቅሁት ከዐመታት በኋላ ነው። ስለ እነ አሚሊ ዲክንሰን፣ስለእነ ዋልት ዊትማን፣ስለ እነ ሚልተን፣ስለእነ የትስ፣ስለእነ  ወርድስ ወርዝ፣ድራይደን ወዘተ-- እያወራ ግጥሞቻቸውን በቃሉ ብሎልኝ ነበር። አቤት፤ እንዴት ያለ የማር ፏፏቴ እንደሆነ!?
ባለፈውም ስንገናኝ ሰውነቱ ቢጎዳም፣ ፈገግታውና ቀልዱ እንደ ድሮው ነው። ከፊት ለፊታችን ሲመጣ አላየነውም ነበር። የክሊፕ ዳይሬክተሩና የሙዚቃ ባለሞያው ቢኒ ምዕራፍ ነው፣ ጎሸም አድርጎ፣ “ጋሼ”ያለኝ። የቱ ጋሼ ሳልል አተኩሬ አየሁት፤ነቢይ ነው። ሊያልፍ ሲል “ነቢይ” ስለው አየና”አንቺ” አለኝ። እንዲህ የሚሉኝ ሦስት ሰዎች ናቸው። ወንድዬ ዐሊ፣ነቢይ መኮንንና አንድ ነጋዴ ጓደኛዬ።
ታዲያ በዚህም ቀለደ፤”በየመንገዱ ጋሼ ጋሼ ስለሚሉኝ፣ እናንተም እንደዚያ መስላችሁኝ ነበር”አለንና ለምሳ ገብተን፣ሠፈሩ ላይ አንዳንድ ሰዎች ፈርምልን እንደሚሉትና እንደሚያከብሩት ሲነግረን እኔ ደስ አለኝ። ቢያንስ ለሥነ ጽሑፋችን ለዋለው ውለታ፣ እንደዚህ ዐይነት የወገን አክብሮት ሲሰጠው ደስ ይለዋል ብዬ አሰብኩ። አካሉ ተጎድቶ፣ውስጡ ቢለመልም!..እና “አለ” አንዳንዶቹ የጥበብ ሰው አንቱ ስለማይባል ‘አንተ’እንበልህ”ሲሉኝ” ችግር የለውም፣ ትንሽ ቆይታችሁ ብቻ ‘አንቺ’እንዳትሉኝ”አልኳቸው፤ አለና አሳቀን። ፈገግታው አሁንም ድረስ  ዐይኖቼ ውስጥ ይንከባለላል።
የነቢይን ግጥሞች በመጽሐፍ ጠርዞ፣ካሳተመ በኋላ፣በተደጋጋሚ አንብቤያቸዋለሁ። በተለይ ስውር ስፌትአንድን አንብቤ፣ይበልጡኑ የፍቅር ግጥሞቹ እንቅልፍ ከልክለውኝ፣ ስጽፍ ማደሬን አስታውሳለሁ። ከዚያም ለደራሲው ወዳጄ እንዳለጌታ ከበደ(ዶ/ር) ሰጥቼው በኢትዮጵያ ደራስያን የሥነ ጽሑፍ መጽሔት ላይ ታትማ ነበር።
ነቢይን የማስታውስበት ሌላ ነገር፣ አንዴ ሳይታተምልኝ በቀረው ጽሑፌ ምክንያት ነው። ያኔ ጋዜጣ ላይ፣ያውም አዲስ አድማስ ላይ ጽሑፍ ሲወጣ የሚሰማን ደስታ ልዩ ነው። የጻፍኩት አንድ ደራሲ የአብረሃም ሊንከንን ሚስት ሜሪ ቶድን ክፋትና አስቸጋሪነት አስመልክቶ የጻፈውን አሉታዊ ነገር ተቃውሜ ነበር። የጽሑፌ ዋና ዐላማ፤ “የሊንከን ሚስት አንተ እንደምትላት አይደለችም” የሚል ነው። የሚገርመው ያኔ ስለ አብረሃም ሊንከን ያነበብኩት አንድ መጽሐፍ ብቻ ነው፤የስቴፈን ሎረንት ይመስለኛል። እና ነቢይ መኮንን ሳያወጣው ቀረና ተበሳጨሁ። ከዐመታት በኋላ ሊንከንን በተለያዩ ጸሐፍት  ዐይን  በጥልቀት ተጽፎ ሳነበው፣ደነገጥኩ። በተለይ ዴል ካርኔጌ  ሚስቱን ብቻ ሳይሆን ጀኔራሎቹን፣ሼርማንና ግራንት ሳይቀር፣ባላንጦቹንና ወዳጆቹን ሁሉ ጽፏል። ታዲያ ያቺ ሜሪ ቶድ፣ ለካ ቀናተኛ፣ሀብት አባካኝ፣ነጭናጫና አስቸጋሪ ነበረች። ጸሐፊው ያለው ሁሉ እውነት ነበር። ነቢይ መኮንን ለካስ ከጉድ ነበር ያወጣኝ። ደግነቱ በሕይወት እያለ ሁሉን ነግሬዋለሁ።
ነቢይ ዛሬን ብቻ ሳይሆን እንደ ስሙ ነገን ያያል። ከነገ ወጥመዶች ያድናል። ነቢይን በበኩሌ አንዴ አንብቤ መተው አልችልም፤ ደግሜ ደጋግሜ አነብበዋለሁ። በፈርጥ መጽሔት ላይ ደቡብ አፍሪካ ለሥነ ጽሑፍ ዎርክ ሾፕ ሄዶ፣ የጻፈውን የጉዞ ማስታወሻ፣ ከአሥራ ዐመታት በኋላ ዘንድሮ እንኳ ሁለቴ አንብቤዋለሁ። እንደ ግጥም ይጣፍጣል፤ምሰላ አለው፤አቤት የዘይቤዎቹ ቅብጠትና ዳንስ!..የመስመር ቅኝቱስ?የተሸከሙት ተራራ? ..ነቢይ የሚለየው በአንዲት ስንኝ ሙሉ ዐለምን ወርቅ ማሸከሙ ነው። አቤት በአፉ ሲያወራስ?...ማር አይደል እንዴ  ጠብ የሚለው?
አንዴ ከነቢይ ጋር የሚያቀያይመንን አንድ ነገር አድርጌ ነበር። አንድ ቀን “የግጥም ደም በእጅህ አይገኝ!”የሚል ጽሑፍ ጽፌ “ነቢይ፣ይህን ጽሑፍ ከፈለግህ አንተ ጋዜጣ ላይ አውጣው፤ያለበለዚያ ሌላ ቦታ እሰጠዋለሁ” አልኩት። ጉዳዩ፣ሰው በሞተ ቁጥር ገጽ ሙሉ ይጻፉ ስለነበሩ ግጥሞች ነበር። ነቢይ ስነግረው በጣም ደነገጠ፤እናም ምክንያቱን ሊነግረኝ ሞከረ።...”ነቢይ፤ እኔ በግልጽ ስላወራሁህ እንጂ ይህ የብዙ ሰዎች ሐሳብ ነው”አልኩት። ዝም ብሎ ጽሑፉን ተቀበለኝና ሳያወጣው ቀረ። ያኔ የሩሕ ጋዜጣ አዘጋጅ አብረሃም ረታ ዓለሙ ነበረና፣ ለእርሱ ሰጥቼው ጋዜጣ ላይ አወጣው።
ከዚያ አዲስ አድማስ አካባቢ ስለሆነው ነገር አንድ ወዳጄ ነገረኝ። ሩሕ ጋዜጣ ላይ በነቢይ ላይ የጻፍኩትን ወቀሳ ያነበበ ሰው ሮጦ ነቢይ ቢሮ ይሄድና፣ “ደረጀ፤ ሩሕ ጋዜጣ ላይ ጻፈብህ”ይለዋል። ነቢይ ተረጋግቶ፤ “ተወው ግድ የለም፤ቀድሞ ነግሮኛል” አለው። ነቢይ መኮንን ትልቅ ነው። ነቢይ መኮንን አድማስ ነው። ነቢይ መኮንን አራት ማዕዘን ግጥም ነው። ነቢይ መኮንን ሀገር ነው።


Read 560 times