Saturday, 06 July 2024 20:53

ወዳለፍነው መንገድ

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(9 votes)

ተወልጄ ያደግኩበትን ቀዬ ለቅቄ እዚህ አሁን እምኖርበት መንደር ከገባሁ ሁለት ዓመት ሞላኝ፡፡ ቀየዬን ለቅቄ የወጣሁት አግብቼ ነው፡፡ ለምን አገባሁ? የኅብረተሰቤን ወግ ለመጠበቅ፡፡ ከእዚህ የዘለለ ምክንያት አለኝ ብል ቃሌ እብለት ይሆናል፡፡
ሄለን አበራን ያገኘኋት እዚሁ አዲሱ መንደሬ በገባሁ በአመቱ ነበር – ከተለያዬን ከረጅም ዘመን በኋላ፡፡ በእዛ ዕለት ከሚስቴ ጋር ገበያ ሄደን እየተመለስን ነበር – እሷ ፊት እኔ ከኋላ፡፡
“አቤ!” ከኋላ ባማረ የሴት ድምጽ ስሜ ተቆላምጦ ተጠራ፡፡ ስዞር ፊቷ በማዲያት የተዥጎረጎረ ጠይም ሴት፡፡ ራሷን የመሰለች ልጅ ይዛለች፡፡ አእምሮዬ የትውስታዉን ማጀት በመበርበር ቢባጅም መልኳን ማስታወስ አልቻለም፡፡  
“እረሳኸኝ? ሄለን ነኝ፡፡” በግርታ ለሰላምታ የዘረጋችልኝን እጇን ጨበጥኩ፡፡
“ሄለን? አልመጣሽልኝም፡፡ ይቅርታ!”  
“ሄለን አበራ፡፡ ሃይስኩል አብረን ተምረናል፡፡” እያፈረች ስትፈግ በፍንጭቷ አወቅኳት፡፡ ክው አልኩ፡፡ ከዘመናት በፊት በፍቅሯ ግዞት አድሬ ብዙ ያየሁባት ሴት ናት፡፡ ትዝታዋ አብሮኝ ኗሪ ነው፡፡   
“ኦ! ሄለን? በጣም ተለወጥሽ፡፡” መልኳን ያስጠፋኝ ጉስቁልናዋ ነበር፡፡ ምን መከራ አገኛት?   
“ማኪ! ሰላም በይው! ልጄ ናት፡፡” የያዝኩትን ከረጢት አዉርጄ ሞሳዋን ሳምኩ፡፡
“እዚህ ነው የምትኖረው?”
“አዎ፡፡ ፊት ለፊት የምታይው ነው ቤቴ፡፡”
“ጎረቤት ነና፡፡ ከጀርባ ነኝ፡፡” ከሴት ጋር ቆሜ ወሬ መያዜን ያየችው ሚስቴ የግቢዋን በር ከፍታ ገባች፡፡ ቀናተኛ ናት ሚስቴ፡፡ ሕይወቴን ገሀነም ያደረገው ምላሷ ነው፡፡
ጊዜ ኃያል ነው ጃል፡፡ የሄለን ውበት ፍፁም ረግፏል፡፡ አጀብ አልኩ፡፡
ሄለንን ተሰናብቼ ቤቴ ስገባ ሚስቴ የጥያቄ ናዳ አከታተለች፡፡
“ማን ናት? የት ነው የምታውቃት?”
“ሄለን ናት፡፡”
“እሷ ናት ሄለን?” ከእሷ ጋር የተያያዘ ታሪኬን ታውቃለች፡፡     
“ስታገኛት ምን ተሰማህ?”
“ደነገጥኩ፡፡”
“ደስ አላለህም?”  
“ምን ማለት ፈልገሽ ነው?”
“ትወዳት አልነበር?”
“ነበር፡፡ ዛሬ ሌላ ጊዜ ነው፡፡” አፈጠጥኩባት፡
“ዘሮቿ ብዙ አንገላተውሃል፡፡ ያሳዝናል፡፡” የምታውቀዉን ያረጀ ታሪክ አነሳች፡፡ ይኸኛዉ የታሪኬ ምዕራፍ ሲወሳ መስማቱ እንደሚረብሸኝ ልቦናዋ ያዉቃል፡፡ እኔን በነገር ጦር ማቁሰሏ ነዉ – በቁስሌ እንጨት መስደዷ፡፡ ይቺ ሚስቴ በጨርቃምነቴ ብቻ በሄለን ወንድሞች ደይኔን እንዳየሁ ታውቃለች፡፡ እና ምን ይጠበስ? ሰው ሲፈጠር ብፁዕ አይደለምን? ሰው ዘሩን መርጦ ይወለዳል? ደግሞስ ማን ነው ዕጣውን ከልሶ የሚጽፍ?
አንዳንዴ በነገር ሸራቢ እኩዮች ሳንወድ በትዝታ ወዳለፍነው መንገድ እንመለሳለን – ፈቅደን መርሳት ወደማንችላቸው ያልሻሩ ቁስሎቻችን፣ ደለሉ ወደሚያመን በደላችን፡፡
* * *          
ሄለንን የተዋወቅኋት አስራ አንደኛ ክፍል ሳለሁ ነው፡፡ በነጻ የትምህርት ዕድል  የገባሁበትን የሞጃዎች ትምህርት ቤት በረገጥኩበት የመጀመሪያው ዕለት ነበር ትውውቃችን፡፡
ትላልቅ ዛፍ የከበበውን የአዲሱ ትምህርት ቤቴን ሰፊ ግቢ በእግሬ አካልላለሁ፡፡ ከአስተዳደር ሕንፃ ጀርባ ራቅ ብሎ ከሚገኝ መናፈሻ ስደርስ አንዲት ልጅ ብቻዋን ዛፍ ስር ተቀምጣለች፡፡ ለምን ብቻዋን? በጎኗ ሳልፍ ኮቴዬን ሰምታ ስትዞር ዓይናችን ተጋጨ፡፡ ጣዖት ትመስላለች፡፡
የቀትሩ ፀሐይ አናት ያነዳል፡፡ አካባቢው ታላቅ ፀጥታ ሰፍኖበታል፡፡ ገኖ የሚሰማ የወፎች ድምፅ እንኳ አልነበረም፡፡    
ከቀይ ዳማዋ ልጅ ጀርባዋ ትልቅ ዛፍ ሥር ነው የተቀመጥኩት፡፡ ከአስተዳደር ሕንፃ የተከፈተው ባለ ዋሽንቱ እረኛ1 ብዙ ሜትሮችን አቋርጦ በጆሮዬ ይፈሳል፡፡ ይህ ሙዚቃ ነፍሴን ወደ ሌላ ዓለም ይወስደዋል – ሌላ ጋላክሲ፡፡ እንዴት ያለ ኪነት ነው? ያለሁበትን ሥፍራ እረሳሁ፣ ልጅቷን ፍፁም እረሳሁ፡፡
ሙዚቃው አልቆ የተከደኑ ዓይኖቼን ስገልጥ ልጅቷ ወዳለሁበት መንገዱን ይዛ መምጣት ጀምራለች፡፡ ስትራመድ ጡቶቿ ያረግዳሉ፡፡ ነጭ ሸሚዟ ያንፀባርቃል፡፡ መጥታ አንዳች ነገር ትለኛለች ብዬ ስጠብቅ ሰበር ሰካ እያለች ገርምማኝ አልፋ ኋላዬ ወዳለ ጫካ ተጓዘች፡፡
እዚህም እዚያም የፈኩት የፀደይ አበቦች ጠረን፣ የሐመልማሉ ማማር እዚያው ዉሎ ማደርን እንዲመኙ ያባብላል፡፡ ልጅ ሳለሁ በሰዎች ስበደል፣ ባይተዋርነት ሲሰማኝ፣ ስደሰት ወደ ጫካ ነበር የምሰደደው፡፡ ብቻዬን የካ ጫካ ውስጥ ስዞር መዋሌ ዓለም ነበር፡፡ እዛ አጋም ስለቅም፣ እንጆሪ ሳረግፍ ውዬ ፀሐይ ስታዘቀዝቅ ሰፈሬ እወርዳለሁ – የዳዊት እና ሲራክን ናፍቆት ተሸክሜ፡፡
ዳዊት እና ሲራክ የልጅነቴ ቀለም ናቸው፡፡ ዛሬ ሁለቱም የት እንዳሉ አላውቅም፡፡ ትዝታቸው ግን ልቤ ውስጥ ኗሪ ነው፡፡ ብሩሑ ልጅነቴ እነሱን አሰልፎ የሚቆም ነው፡፡
በትዝታ ጀልባ ልጅነቴ ባሕር ላይ ስቀዝፍ ቆይቼ ምሳ ልበላ ወደ ተማሪዎች ካፍቴሪያ አመራሁ፡፡                         
* * *
ተማሪዎች ካፍቴሪያ ምሳ በልቼ መማሪያ ክፍሌ 11ኛ ሲ ውስጥ ገብቼ ከተጎለትኩ ጥቂት ቆየሁ፡፡ ቦታዬ 3ኛው ረድፍ መጨረሻ ነው፡፡ 11ኛ ሲ ክፍል ውስጥ የተመደቡ ወንድ ተማሪዎች ቁጥር ጥቂት ነው፤ ሴቶች ይበዛሉ፡፡ ተማሪው እዚህም እዚያም ተቧድኖ ያውካካል – ቤተሰብ ይመስላል፡፡ ባይተዋሩ እኔ ዓይኔን እዚህም እዚያም አንገዋላለሁ – በትዝብት፡፡ ቀይ – ጥቁር፣ ረጅም – ኩሩሩ፣ ባለ ትላልቅ ጡት – ባለ አጎጥጓጤ፣ ፀጉረ ሉጫ – ኪንኪ፣ ዓይነ ዐሎሎ – ዓይነ ልም፣ ፀጉረ ረጅም – ፀጉረ አጭር፣ ቆንጆ – ፉንጋ፣ በስብ የደደረ – ከሲታ፣ ጥርሰ መልካም –ገጣጣ፣ ፍልቅልቅ – ኮስታራ፡፡
የክፍሉ ትዕይንት ሰልችቶኝ ከስልኬ የቦይዝ ቱ ሜንን ዘፈን አዳምጣለሁ፡፡ ከውጭ ትምህርት ቤቱ መናፈሻ ውስጥ ያየኋት ልጅ ገባች፡፡ መካከለኛ ነው ቁመቷ፡፡ በዐይኗ ሙሉ ክፍሉን አማትራ ወዳለሁበት መጣች፡፡
“ይቅርታ፣ ተይዟል ቦታው?”
“ነፃ ነው ተቀመጪ፡፡”
“አመሰግናለሁ፡፡” የቆዳ ቦርሳዋን ከትከሻዋ አውርዳ ተቀመጠች፡፡ ጠረኗ የዝባድ ነው፡፡  
“ሙቀቱ አልተቻለም፣ ኡፍፍፍ፡፡” ሹራቧን አውልቃ አንገቷ ስር ደብተር ማራገብ ጀመረች፡፡  
“ዘንድሮ ከብዷል፡፡”
የሮም ሐውልት የሚመስሉት ጡቶቿ ወደ ምሥራቅ እና ምዕራብ አቅጣጫ ተቀስረዋል፡፡
“እኔ ደግሞ ሙቀት አልችልም፡፡”
“አዲስ ተማሪ ነህ?”
“አዲስ ተማሪ እመስላለሁ?”
“እንጃ፣ አይቼህ አላውቅም፡፡”
“አዲስ ነኝ፡፡”
“አይዞህ እናላምድሃለን፡፡” ፈገግ ብላ፡፡ እንጆሪ የመሰሉ ከንፈሮቿ የልብ ቅርጽ አላቸው፡፡ ሙት ቢስሙ ያስነሳሉ፡፡  
“ተስፋ አደርጋለሁ፡፡”
“ሄለን እባላለሁ፡፡”
“አበበ፡፡”
* * *
እኔ እና ሄለን ልባችን ተፈላልጎ የፍቅርን መዐድ መቋደስ የጀመርነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ፍቅርን ሳላውቅ ያደግኩት ሰው በሄለን ልብ ውስጥ ነገሥኩ – ሕይወቴ ምልዓት አገኘ፡፡ ሕይወትስ ከፍቅር በላይ ምን እፁብ ነገር አለው? ማፍቀርን የሚስተካከል ምን ስጦታ አለ? ከመወደድ በላይ ምን ሽልማት አለ? ሄለን ከበታችነት ደዌ ፈወሰችኝ፡፡ ፍቅር ኃያል ነው – ቅዠቴ የነበረች ልጅ እቅፌ ውስጥ አደረች፡፡ ቅዠቴ ለምን ሆነች? ድህነቴ አንገቴን ሰብሮት – ወኔ ቢስ ሆኘ፡፡ ኅብረተሰቤ ያበጀው የመደብ እርከን ሽቅብ እሷን እንድመኝ አይፈቅድም፡፡
ጥቅምት 2001 ዓ.ም፣ አስራ ሁለተኛ ክፍልን በጀመርን በወሩ፡፡ በሚስጥር የያዝነው ፍቅር ዘመዶቿ ጆሮ ደረሰ፡፡ ለጋ ፍቅራችን ተፈተነ፡፡
ወገኖቿ እኔን ጠሉ፣ በቃል ሰበሩኝ፡፡ የእነሱ ቢብስም ብዙ ጊዜ የክፉዎች ቃል ሰብሮኛል፡፡ ስብራት ግን አይለመድም፣ ሁሌም ህመሙ አዲስ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡-
መኮንን ደፍሮ ልብወለድ ጸሐፊ፣ ገጣሚ እና የሥነ ጽሑፍ ኀያሲ ነው፡፡ የባችለር ድግሪውን በ2009 ዓ.ም፣ የማስተርስ ድግሪዉን ደግሞ በ2015 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና አግኝቷል፡፡ በተማረው የሙያ መስክ በጅማ፣ በመቐለ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሠርቷል፡፡ ጸሐፊው አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጨምሮ በተለያዩ መጽሔቶች ግጥሞቹንና የልብ ወለድ ሥራዎቹን አሳትሟል፡፡      መኮንን በርካታ የኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ሥራዎች ላይ ኂሳዊ መጣጥፎችን ጽፏል፡፡


Read 757 times