Saturday, 06 July 2024 21:00

ዘጋቢው መድበል፤ ‹‹ምልኪ እና ቡና››

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

‹‹…የቃለ-እሣት ነበልባሉ፤
የዘር ንድፉ የፊደሉ፤
ቢሞት እንኳን፣ ሞተ አትበሉ፤››
              (ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን)
የአገሬ ሰው ለግጥም ቅርብ ነው፤ ሥነ-ቃል የሥጋ ዘመዱ ነው፤ ግጥም ‹‹ማንን ትወዳጅ፣ ትቀርባለህ?›› ተብሎ ቢጠየቅ፣ ፍርጥም ብሎ ‹‹ሐበሻን›› የሚል ይመስለኛል፤ ሰዋችን ሽልማትና ርግማኑን በግጥም ይወርዳል፤ እርሻውን የሚያቀናው ሥነ-ቃል እየደረደረ ነው፤ መጀገን ማጀገኑን፣ መርታት መረታቱን፣ ጣመንና ርካታን በስድ ከመግለጽ ይልቅ ግጥማዊ ለዛ ባለው ቋንቋ ይተነፍሳል፤ ሥነ-ቃል እና ግጥም ‹በመወለድ የሚቸሩ ክኅሎቶች እስኪመስል ከሐበሻ የተጎራበቱ ናቸው።
ለዚህም፡-
‹‹አረገዘች አሉ፣ የርብርብ ልጅ፤
እኔን ይደርሰኛል፣ አንድ እግር ካንድ እጅ፤››
ከሚል መጽናኛ ጥበባዊ ሀብቱ እስከ፡-
‹‹እኔ እዘጋዋለሁ፣ ቤቴን እንዳመሉ፤
ሰዎች ከጠየቁ፣ ከፍቶት ሄደ በሉ፤››
የሚል ሆድ የሚያስብስ እንጉርጎሮውን መመልከት ተገቢ ነው፤ በመጀመሪያው ሁሉን እንደማያጣና ተስፋው እንደማይደበይ ይተልማል፤ ዕጣው ከአንዱ እንደሚወድቅ ያትታል፤ በሁለተኛው ደግሞ ታክቶት እየተሰናበተ መሆኑን ይናዘዛል፤ ግጥምን በመድበል አንብቦ የመረዳትና የመተንተን ይትበሃሉ ደካማ አይደለም፤ በእርግጥ በብያኔ ወቅት መናጆነት አይስተዋልም ባይባልም፣ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን የሚያንሸራሽ አንባቢ ያለበት አገር ላይ ነው ያለነው።   
ግጥም የኪነ-ጥበብ ሁሉ አውራ ነው ተብሎ በተሾመ አገር ላይ መኖራችን መዘንጋት የለበትም፤ ግጥም ሰንካላ አይደለም፤ መሄድና መምጣት፣ ሂደት ነው በግጥም ገላ ውስጥ የሚንፀባረቀው፤ በጊዜ እና በወቅት የተገነተረ ሁነት በግጥም እንዲተላለፍ ሕገ-ደንቡ አይፈቅድም፤ ግጥም ዛሬ ላይ አይቸነከርም፤ ነገ ብቻም አይደለም፤ የግጥም ሀሳብ በትናንት፣ በዛሬ እና በነገ መካከል ላይ የሚዘልቅ መሆን አለበት።
ገጣሚ ‹ከእኔ ወዲያ ለአሣር› የሚል ሐኬተኛ መሆን የለበትም፤ መግጥም በፍፁማዊነት ተሞኝቶ ሀሳብ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን፣ በንቃት ሀሳብ መሻት ነው፤ መጠየቅ መቻል ነው የገጣሚነት ልኩ፤ የበርካታ ገጣሚያን ከቅኔ ላይ መከዳ የመንሸራተት ዋንኛ ምክንያት የ‹ገጣሚ ነኝ› ተዐብዮአቸው ነው፤ እንዲያ ያለ ገጣሚ ለጋዜጠኝነት ያደላ ዘጋቢ ዲስኩር በመድበሉ ይዞ ከተፍ ይልና፣ ደክሞ አንባቢን ሊያደክም ይችላል፤ ጥሬ ሀሳቡን በጥሬ ቃል የሚሰድር ገጣሚ፣ አንባቢን ከመመራመር እንዲታቀብ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
በዋናነት ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ግጥም ከዜና የተለየ ጥበብ መሆኑ ነው፤ ገጣሚ ‹‹ይኼንን ለምን አሰብክ?›› ተብሎ በአንባቢ አይብጠለጠልም፤ ነገር ግን ሀሳቡን የገለጸበት መንገድ ሊያስወድሰው፣ ወይ ሊያስተቸው ይችላል፤ የግጥም ሀሳብ እንደ ዜና አይነበብም፤ ፍዝ እና ዘጋቢ ከሆነ ጉድለት አይሞላም፤ ወይም በአዲስ ነገር አንባቢን አይደጉምም። በመሆኑም፣ ገጣሚ ምናባዊ ምልከታውን በሃቲቱ ማካተትና ከኖርነው ይልቅ የምንኖረውን ወይም ያልኖርነውንና የማንኖረውን አክሎ የሰፋ ሀሳብ ይዘን እንድንመራመር ሊያደርግ ይገባል።
እንደ ሌሎች የዕወቀት እና የዕድገት መስኮች ሁሉ፣ ግጥም የዕውቀት ማግኛ መንገድ ነው፤ የመማሪያ እና የመመራመሪያ ሥነ-ዘዴ ነው፤ ግጥም ዓላማ አለው፤ የሰው ልጆችን አዕምሮ ማዳበር እና ንቃተ-ኅሊናቸውን ከፍ ማድረግ ግቡ ነው፤ ጥበባዊ ዋጋው ደግሞ በሰብዕናው የጎለበተን ማኅበረሰብ ማፍራት ነው፤ ግጥምን ከዕሴት አንጻር ብንቃኘው የተውሸለሸለ ጉዳይ ላይ ዕድሜውን አይባጅም፤ ያበቃል፣ ያነቃል፤ የዘመመ ያቀናል።
ወደ ጉዳያችን እንዝለቅ…
…ገጣሚ ኤፍሬም ሥዩም፣ ግጥምን አስመልከቶ የፈካ መጠሪያ ካላቸው ጥቂት ገጣሚያን አንዱ መሆኑ ሐቂቃ ነው፤ ሙዚቃዊ ቃናን የተላበሰ ‹‹ሶሊያና›› የግጥም ሲዲው ተወዳጅ ሥራ ነው፤ ኤፍሬም አብዛኛውን ጊዜ መተረክ ላይ ያተኮሩ እና ሂደትን ያማከሉ ግጥሞችን ያዘወትራል፤ በተራኪ ግጥሞቹ የአንድን ክስተት መነሾ ማዕከል ያደርግና፣ ክስተቱ ወደተደመደመበት ሁነት እየተጓዘ ይተርካል፤ ሂደት ተኮር ግጥሞቹ ደግሞ የክስተቶችን ያለፈ፣ የአሁን እና የወደፊት መልካቸውን በማመላከት የሚደረግ አሰነኛነት ነው፤ በሁለቱም መልኮች ምሥል ይፈጥራል፤ አተራረክ ያቆነጃል፤ በዚህ ምክንያት፣ በርካታ ወጣት ገጣሚያንን አነሳስቷል።
ለዛሬ ‹‹ምልኪ እና ቡና›› የተሰኘውን የገጣሚውን ሥራ እንመልከት፤ ከሁለት መቶ አሥራ ስድስት (216) ገጾች ተውጣጥቶ በ2016 ዓ.ም. ለመነበብ የበቃ መድበል ነው፤ የኢትዮጵያን መልክ የሚከስቱ ግጥሞችን ለማግኘት ቋምጬ ንባቤን ጀመርኩ…
…አልሆነም፤ ስብጥርጥር የኢትዮጵያ መልክ የታጣበት መድበል ነው፤ ገጣሚው ዘገባ የጎበኛቸው ግጥሞችን በዚህ መድበል ሰንዶ ለአንባቢ አቅርቧል፤ በጎዋንና ክፉዋን ኢትዮጵያ ጥበባዊነት በጎደለው መልኩ ይኩላል፤ የኖርነውን ሁሉ በወርድ በቁሙ ይናዘዛል፤ ይኼ ተግባሩ አታካች ሆኖ አግኝቼአለሁ፤ በተራ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ሃቲት በማቅረብ ጊዜያቸውን የሚባጁ ግጥሞች ዕልፍ ናቸው፤ ኤፍሬም ሥዩም በዚህ ልክ ለምን አንባቢን ድካምና መታከት ውስጥ እንደዶለ ሊገባኝ አልቻለም፤ በአጭሩ ገጣሚው ከቅኔ ተጻርሮ የዘገበበት መድበል ነው ‹‹ምልኪ እና ቡና››፤ ‹‹ገጠመ›› ከምንል ‹‹ዘገበ››፣ ወይም ‹‹ዜና አነበበ›› ብንል ያዋጣል።
ግጥምን የምናነብበው ሀሳባችንን ለማዳበር ነው፤ ስለ ቁመታችን፣ ስለ ክብደታችን፣ ስለ ልባሻችን ዓይነት እኛ እናውቃለንና ገጣሚ ባይነግረን ደግ ነው፤ ገጣሚም ሀሳባችንን የምናጦነችበትን ግጥማዊ ጭብጥ እንካችሁ ካላለን ምን አደከመው? ኤፍሬም ሥዩም በዚህ መድበል ከራሱ ጋር ይቃረናል፤ ገጽ 10 ላይ፣
‹‹…የጸጋዎች አባት፣ ውሃቤ ጥበባት፣
እግዚሔር ከጠበቀህ፤
አንተ እድለኛ ነህ፤
በፍቅርና ስሜት፣ በእውነትና በእምነት፤
በደስታና ሃዘን፣ ያለውን ልዩነት፣ ማወቅ
ስላለብህ፤
‹‹ግጥም›› ታነባለህ፤  
ምክንያቱም….
ደስ ብሎት የሚያለቅስ፣ ብዙ ሰው አለና፤
አዝኖም የማይጨንቀው፣ ሰው አይጠፋምና፤
ይህን ለመረዳት፣
ምክንያቱን ትሻለህ፣ ግጥም ታነባለህ፣ ጠያቂ
ነህና፤…››
ይሰኝና፣ ለመጠየቅ፣ ለመመርመር፣ ለጥናት የማይጋብዙ አያሌ ግጥሞችን ለአንባቢ ያቀርባል፤ እንግዲህ፣ ከጅማሬው ግጥም አንባቢያኑ በምን ተያዥነት እንደሚያነብቡ፣ ለግጥም የሚጠራ ልብ ምን ዓይነት እንደሆነ፣ የግጥም መልከ-ብዙ ገጽታን… ወዘተ. ተንትኖ ሲያበቃ፣ ውስጥ ውስጡን ዜና መሰል ያልተብላሉ ግጥሞችን ነው በመድበል ያካተተው፤ ለምርምር የሚገፋፋ ግጥም በማጣቴ ቆጭቶኛል፤ በአመዛኙ ሳይሆን በጠቅላላውም በሚባል ደረጃ ገጣሚው ለመጠየቅ የማያነሳሱ ሀሳቦችን ነው እንካችሁ ያለን።
ሌላ ተጨማሪ ተቃርኖ እንካችሁ፤ ገጽ 68 ላይ ‹‹መ›› በሚል ግጥም እንዲህ ይሰኛል፡-
‹‹ለእንዳንተ ዓይነት ሰው፣
በግጥም መመለስ፣ ግጥምን ያረክሳል፤
ነፍስን ያሳንሳል፤…››
ይላል፤ በዚህ ግጥም ‹‹ግጥም የሰነፎች፣ የሥራ ፈቶች መክሊት ነው›› በመባሉ የተነሳ የመልስ ምት ነው እየሰጠ ያለው፤ መነሾው ላይ፣ ስለ ገጣሚ የተነገረ እኩይ ነገር ገጥሞታል፤ ነገር ግን መልስ ለመስጠት አልገጥምም ይልና፣ ይኼንን ምላሹን በግጥም ያቀርባል፤ ‹‹በግጥም አልመልስም›› እያሉ መግጠም ከራስ ጋር ተቃርኖ ነው።
የገጣሚው ጉልህ ጣጣ ራሱን ልዩ ገጣሚ አድርጎ መሾሙ ይመስለኛል፤ ኤፍሬም ሥዩም በዚህ መድበል ኤፍሬም ሥዩምን ይስማል፤ ያቆለጳጵሳል፤ ራሱን እንደ አውራ ገጣሚ ቆጥሮ ያበቃና፣ ራሱን መልሶ ተምሳሌት አድርጎ ይጠቅሳል፤ አንድ ገጣሚ በዚህ ልክ ሐኬተኛ መሆን የለበትም፤ ልቡናው በማንአኽሎኝነት ተወድሮ ሊታበይ አይገባም፤ ይኼንን ሀሳብ በመረጃ ለመደገፍ አንድ ዋቢ እንጥቀስ፤ ገጽ 19 ላይ ገና ከመጀመሩ፡-
‹‹…ህዝብ የሚባለው፣ የእውቀት ጾመኛ፤››
ይላል፤ ለመሆኑ ህዝብን እየናቁ ለህዝብ የግጥም መድበል እንካችሁ ማለት አይከብድም ይሆን? ገጣሚውስ የዚህ ህዝብ አንድ አካል አይደለምን? መቼም ኤፍሬም ራሱን ቁንጮ አድርጎ ካደላደለ በኋላ የተሰናኛት ናት ይህቺ ስንኝ፤ ደግሞስ ህዝብን ለመዝለፍ ገጣሚ መሆን ይጠበቃል? መረን የነኩ ቃላቶችን በግጥም መድበል ላይ ለማግኘት አልፈቅድም፤ ግጥም ብሉይ ነው።
የህዝብን ሥነ-ልቡና የሚያንኮታኩት ቃል በግጥም መድበል አይካተትም፤ ገጣሚው ይታረም፤ መብረቅ ለመታው አፈር ወይ እበት ምሶ፣ በመቅበር በተጠቂው ሰውነት ውስጥ ያለውን ኤለክትሮድ የሚያመክን ህዝብ ነው ይኼ ህዝብ፤ ከአፈር ይልቅ እበት ውስጥ ይዶላል፤ አንደኛ እበት ለመማስ ቀላል ነው፤ ሁለተኛ እበት ውስጥ መጠነ-ሰፊ ‹‹ሚቴን ጋስ›› ስላለ ኤለክትሮዱን በፍጥነት የማምከን ዕድሉ ሰፊ ነው፤ ይኼንን ተምሮ ሳይሆን በልምድ ያካበተው እውቀት እንደሆነ መዝግቡልኝ፤ ከዚህ በላይ እውቀት ከየት ይምጣ? ይኼንን ዓይነት ወቀሳ ገጸ-ባሕሪውንና ዐውዱን እያማከለ በልብ-ወለድ ቢያቀርብ መልካም ነው እላለሁ። ተጨማሪ ማሳያ እናንሳ፤ ገጽ 213 ላይ ‹‹የአንዲት ቀጭን መስመር የግጥም ስጦታ›› ተብሎ በሰፈረ ግጥም፡-
‹‹…ምንም እንኳ’ን እኔ፣
እንደ ገጣሚዎች፣ ባይሆንልኝ መጻፍ፤
ምንም እንኳን እኔ፣
ልክ እንደ ኤፍሬም፣
ማሳየት ባልችልም፣ ውበት እየኳሉ፣ ቃላትን
ማሳለፍ…››
በማለት ራሱን ከታላቅ ገጣሚያን ስፍራ ይደለድላል፤ በመሆኑም፣ ራሱን የማምለክና የመሳም አባዜ ውስጥ ገብቷል፤ ገጣሚው ራሱን እንደ ምሳሌ ጠቅሶ ቢገኝም መድበሉ ያካተታቸው ግጥሞች ከሥነ-ውበት ጋር ያላቸው ተራክቦ የተውሸለሸለ ሆኖ አግኝቼአለሁ። የሆነው ሆነና፣ ራሱ ገጣሚው በተምሳሌትና በአርአያነት የተጠቀሰበት ግጥም ዕድሜው አልፎ የተንዛዛ፣ የሚያብራራ፣ በድግምግሞሽ የታጀበና አታካች ስልተ-ምት የተስተዋለበት ነው፤ ደህና ግጥም ላይ ራሱን ጠቅሶ ቢሆን አይቆጨኝም ነበር።
ዘለስ ሲል፣ በመድበሉ ከገጽ 216 ላይ፡-
‹‹…ግን… ግን፣
ይህን ስትጽፍላት፤
ይህን ስትልክላት፤
አደራ ተጠንቀቅ፤
ልክ እንደ ጀማሪ፣ ግጥም ጸሐፊዎች….
ትላንትና ምሽት፣
የላኩትን ግጥም፣ የጻፍኩትን ግጥም፤
እንዴት አገኘሽው፣ ብለህ እንዳትጠይቃት፤…››
እያለ ጀማሪና ወጣት ገጣሚያንን ቢያጣጥልም የተሻለ ሥራ ይዞ መቅረብ ያለመቻሉ አስቆጭቶኛል፤ በቀጣይ ሥራዎቹ ላይ እምርታን እመኛለሁ!
ከዚህ በዘለለ፣ መድበሉ በተንዠረገጉ፣ የተንዛዙ፣ ማለቅ ባለባቸው ዕድሜ ውስጥ ያላለቁና ያልተቋጩ፣ ፍሬ ሀሳባቸው የሚያምታታ፣ ርዕስ የሌላቸው፣ ዜማን የሚረብሹ አያሌ አያያዥ ቃላቶች የተሞጀረባቸው፣ ስልተ-ምትታቸው አታካች የሆኑ…ወዘተ. ግጥሞችን ያጨቀ ነው፤ የአንዳንድ ግጥሞች ርዕስ ‹‹አ››፣ ‹‹በ››፣ ‹‹ገ››፣ ‹‹ደ››…ወተዘ. የሚል ውክልና ያለው ሲሆን፣ ለብያኔ አሻሚ ነው፤ ርዕስ አልባ የሆኑ ግጥሞች ርዕስና ሃቲታቸውን እያመሳከሩ ጭብጡን ለማግኘት አዳጋች እንደሚሆኑ ዕሙን ነው። በመሆኑም፣ ገጣሚው ከገጽ 30 ላይ፡-
‹‹…አሁን ከዚህ በላይ፣
የጻፍኩትን ግጥም፤
አምጥተን እዚህ ጋር፣ እንተንትነው ብንል፤
ያኔ…
ፊደላትን ጠርበን፤
ቃላትን አዋቅረን፤
በድካም ያቆምነው፣ የሃሳብ ሕንጻችን፣
መፍረስ ይጀምራል፤…››
ብሏልና (ራስ ላይ ማሟረትም ይመስላል)፣ መድበሉን ‹‹የሃሳብ ሕንጻው ነው›› እንበል፤ ከዚያ አፍርሶ እንዲገነባው እንማጠን፤ መልካም ዕድል!
በመጨረሻ፣ በገጣሚ፣ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን ሕልፈት የተሰማኝን ኀዘን ለመግለጽ እወዳለሁ፤ በእኔና በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ሥም፣ ለመላው ቤተሰቦቹ፣ ለዘመድ ወዳጆቹና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን እመኛለሁ፤ ነፍስ ይማር!   
*  *  *
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር/ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።


Read 381 times