Saturday, 06 July 2024 21:18

አዎን - “ውበት ያሸንፋል!”

Written by  ዙፋን ክፍሌ
Rate this item
(4 votes)

ደራሲ ፦ ሀብታሙ ሃደራ
ዘውግ፦ ስብስብ ግጥም
የመጽሐፍ ርዕስ፡- እንዲህም ያለ የለ!
የሕትመት ዘመን፦ 2016 ዓ.ም
የገጽ ብዛት፦ 126

የገጣሚ ፈረስ ገጣባ መሆን አለበት። የዘመን ጫማው ውስጥ እየተሽሎከሎከች የምትፈትነው ጠጠር ያስፈልገዋል። ትንሽ ጠጠርማ አትጥፋ። ገጣሚ የነሐስ ገምባሌ አይታጠቅም። በባዶው እየተረገጠ፣ የጭቃ እሾህ ያደማው ዘንድ ግድና ቃልኪዳን አለውና። መሶብ ሲከፍት ከተያዘ ልጅ ጋር አብሮ የሚቆነጠጥበት ራቁት ያለው ነው ገጣሚ። ገጣሚ ጨርሶ አይለብስም - ጥቂት ራቁት ያሻዋል። የአዛባንና የአበባን ሽታ እኩል የሚምግበት ሰርን ያስፈልገዋል - አያ ገጣሚ። እነዚህ እንጂ ከሌሉት ቃሉ እንደሆን የሕዋው ነው ? በምናባቱ ገንዘብ ነፍሳችንን ሊገዛት ይሻል? አለዚያማ እሱም አያብብ እኛም አና`ሸት!!
ታዲያሳ? ዛሬሳ?
ዛሬማ ግሩም ጊዜ ነው። ጸደይ ነው ። በተለይ  ለስነጽሁፍ፣ በተለይ ለግጥም። በነጋ በጠባ እያበበ ያድራል፤ ይሄ ድርሰት። ይሄ ግጥም። ያውም በያይነት ነዋ! ያውም ሕብረ ቀለም። የሚያሳሳ ማሳ ነው፤ ማሳው። ቡቃያውን ካረም ይጠብቅልን። ከአዝመራው ክፉ ወፍ ይከልክልልን ብቻ!!
አሁን ስለ አንድ አበባ ነው...፤ ስለ <<እንዲህ ያለም የለ!>> በሉ እናሽትት!
1)  በአፍዓ፤
አፍዓው (ውጭው፣ ደጁ)፤ <<እንዲህ ያለም የለ!>> የሚል ጆሮ/ዓይን ገብ፣ ቀልብ ቀብ የሚያደርግ  ርዕስና ጠይምነት የሚሰለጥንበት፣ “ጠጋ  ብላችሁ እዩኝ” የሚል የሽፋን ቅንብር አለው። ማለፊያ!
2) ግቡ፥ ግቡ -
“ጫማ ብናወልቅ ከለከለችን” ብሏልና፤ አታውልቁ ግቡ።
2.1) ማውጫ ላይ የግጥሞቹ አርዕስት ቢዘረዘርም፣ ስንተኛው ገጽ ላይ እንደሚገኙ አልተመላከተም። ከማውጫ ይልቅ ‘መዘርዝር’ ነው መባል የነበረበት።  የኔ ጌታ፣ ምነው በተወደደ ወረቀት፣ አንድ ገጽ ካባከንክ አይቀር፣ ገጽ በመጠቆም ብታግዘን?
ተቀመጡ፣ የእግር ውሃ ይምጣላችሁ!
2.2) ቀለል ማለት(Simplicity)
ቀለል ማለት የዚህ መድብል ብቻ ሳይሆን፣ የገጣሚውም ባህሪ ይመስለኛል። አለማወሳሰብና ለሕይወት ቀላል ትርጉም መስጠት፤ ‘የሚፈለገው ጥቂት ነበር፤ አንቺ ግን በብዙ ለፋሽ‘ ከመሰኘት ያድናል።
እስራኤላውያን የሚበቃቸውን ጥቂት መና ብቻ በመሰበስብ፣ ቀለል እንዲያደርጉት ተነግሯቸው ባይሰሙ፣ እየተራወጡ የሰበሰቡት በስብሶባቸው ጥለዋል። ማወሳሰብ ለመጣል ነው። ከዛው ከክርስትና አስተምህሮ ሳንወጣ ክርስቶስ ባስተማረው ጸሎት ውስጥ ‘የዕለት እንጀራ’ የምትለዋን ቀለል ያለች ስንኝ ማስታወስ ነው።
ሀብታሙ ይናገር፦
ከዚህ ግዙፍ ሰማይ
(በግድ የምትታይ)
አንዲት ሞሳ ፀሐይ
         ፤
ከዚህ ሰፊ ምድር
ነፍስ የምታሳምር
ሆድ የምታባባ
አንዲት ውብ አበባ
          ፤
(ገጽ 18)
እንድገም:-
ግን እንረጋጋ...
እዚሁ ቁጭ ብለን ፥ እንዳሻን እናውጋ
ምን አሳጣን ሜዳው?
ምን አሳጣን ምድር?
ቀልሎ መኖር አይደል፥ ትልቁ ተዓምር!?
(የፍቅር እግረ አጣጣል፤ ገጽ 23 - 24)
ሀ) ሦስተኛው አማራጭ (3rd alternative)
ከማቅለያ መንገዶቹ አንዱ ሶስተኛው አማራጭ (3rd alternative)ን መጠቆም ነው።
ሶስተኛው አማራጭ ማለት ከምንዋጠርባቸው ሁለት ጽንፎች ሌላ ሦስተኛው መንገድ ነው። ይሄን መንገድ ወርቃማው አማካይ (the golden ratio) ማለትም ይቻላል። ከRumii የተመለሰችውን የትርጉም ስራ እንይ :-
እንደ ቀትር ጥላ፥ እንደ ክረምት ጉም
እያለሁ የለሁም።   (ገጽ 144)
“እያለሁ የለሁም” ማለት የመኖር / ያለመኖር ወርቃማው አማካይ ወይም ሦስተኛው አማራጭ ነው።
ገጽ 76 ላይ የሰፈረው ግጥምም ሦስተኛም ባይሆን፣ ሁለተኛ አማራጭን ያሳያል። በሌሎች ብዙ ግጥሞች የተለመዱ ትርክቶችን በማፍረስ (Deconstruct) ሁለተኛ መንገድ ይጠቁመናል። “አቅልሉት” ይለናል።
ለ) ቅጽበት(Moment)
በአኗኗራችን ውስጥ እቅጭና ተጨባጭ ጊዜና ቦታ (Time and Space) ካለ ፥ ‘አሁንና እዚህ’ (Now and here) ይመስለኛል - ቅጽበት።
ዓመት ሁለት ዓመት ማለት የነዚህ ‘አሁንና እዚህ’ ዎች ጥርቅም ነው።
መድበሉ ማቅለልን (Simplicity)ን እንኩ የሚለን ስለ ቅጽበት በመፈሰር ነው።
ያንዲት ቅጽበት፥ እምጷ
የሰኮንዶች ቅንጣት፥
የትኛው ሁነት ነው፥
እሷን የሚበልጣት?  (ገጽ 88?)
እስቲ የቱ? የቱም! ነው መልሳችን።
ሐ) ውበት
ገጣሚው ሕይወትን የማቅለሉን ነገር፣ ለሕይወት ትርጉምና ምክንያት ናቸው ያልናቸውን ነገሮች እስከ መንጠቅ ያደርሳል።
ከሰው ልጅ ይበልጣል? ዛሬ ነገ ትናንት?
ግድ ነው ለመኖር : ሰበብና ምክንያት?
(ገጽ 21) ይለናል።
ትርጉማችንን ነጥቆን ምን ሊሰጠን ካላችሁ መልሱ - ውበት ነው።
እናሽትት? ይኸዋ :-
ሕይወት እንደ ሕልም፥ ሳይኖራት ፍቺ
ያለ ስሟ ስም፥
ያለ መልኳ መልክ፥ ሰጠናት እንጂ
ምን ትርጉም አላት፥ ከማማር ውጪ?
(ገጽ 115)
እንድገም?
እንደ እውር አሞራ፥ በጭምት ቢያከንፈን
በምናብ አሳፍሮ፥ ድንበር ቢያሳልፈን
ወደድንም ጠላንም፥ ውበት ነው ‘ሚተርፈን።
(ውበት ያሸንፋል፤ ገጽ 120 - 121)
አዎን - “ውበት ያሸንፋል!”
ባጠቃላይ ይሄ መድበል ማለፊያ ከሆነባቸው መልኮች አንዱ ቀለል(simple,not easy)ማለቱና ለወጣኒውና ፍጹሙ አንባቢ በተቀራራቢ ስሜት ሊነበብ የሚችል መሆኑ ነው።
2.3) ጦርነት
ገጣሚው ስለ ጦርነት የተወሰኑ ቦታዎች ላይ (10,53,....) በውብ ቋንቋ አስፍሯል። ከሰሜኑ ጦርነት ገፈት እንደቀመሰ ሰው ጦርን፣ ጦረኛን፣ ጦረኝነትንና ጦር ሜዳን ያያቱን ታቦት ጠርቶ እንዲረግመው ተደብቄ ጠብቄ ነበር። የለም? አለ እንጂ!
....ግን “እንጋባለን” ብለሃል ለግንቦት
ነገርኩህ እንዳትሞት!
(ገጽ 11)
እንዲህ ክሽን! እምቅ ብሎ!
2.4) ትዝታ ናፍቆት
ትዝታና ናፍቆትን አንዳንዱን ገጸ - ባሕርይ ተጣብተዉት አልለቅ ሲሉት ፣ ሌላው ደሞ ስልጣን ሲያገኝባቸው ያሳየናል። ኧረ ‘ጫን’ ይበል ካላችሁም፣ የሕይወትን ትርጉም ከእነዚህ አላ`ቁ ይለናል።
2.4) የገጣሚው ሴቶች
በተጠሩበት(በተወከሉበት) ግጥም ውስጥ ያሉ የገጣሚው ሴቶች በሙሉ የተጋነኑና መሬት ያልያዙ ናቸው። እንጀምር፥
ምግባር ሥራጅ፤ በ<<መንደሪን መንደሪን>> መድብሉ ውስጥ “ሙና” ለተባለች ልዕለ ሰብእ ሴት፡-
<<...
ጥሪ...ጥሪ
በጥርሶቹ እሳት ጫሪ
በሳቁ እቶን ወርዋሪ
ካንቺ በቀር አንድ ጥሪ!
ጥሪ...ቁጠሪ
አንድ።
አንድ።
አንድ።
ብቻ ቀሪ
እመኚኝ ከራስሽ አትሻገሪ..ሙና..>> ይላል።
(መንደሪን መንደሪን ፤ ገጽ 101)
በፍጹም ተመሳሳይ ቅርጽ፣ አያያዝና ዜማ(tone) ሀብታሙ ያለውን በማየት እንጀምር፦
ጥሪ፣ ... አንድ ስም፣ ...
በትንፋሹ፥ ልብ የሚስም
ከሬት ገላ፥ ፅጌሬዳ የሚቀስም
ጥሪ አንድ ስም፣ ....
በአንድ ኩርፊያ
ግዙፍ ፀሐይ የሚያከስም
በፈገግታው፥
ግልገል ዕድሜ የሚያረዝም።
 ዝም።
ዝም።
ዝም።
ተፈጥሮ እንደሁ ፥ ካንቺ በቀር አይታዘዝም።
(ገጽ 87)
እንቀጥል...
አዛኝ አንጀቷ፥ ከማርያም ባይልቅ
በእጇ እየሰጠች፥ በዓይኗ ምትመርቅ፥
ትሑት ናት ጻድቅ!
(ገጽ 30)
ብሎ ከማርያም መለስ ያደረጋትን ሴት ፤
“እግዜር አይስቅም!” ይባላል
ከሳቀ ግን አንቺን ይመስላል።
(ገጽ 94)
በማለት ያገንናታል። ያጎናታል!
ከከንፈርሽ ደጃፍ፥ ብርሃን ወጣ በሰልፍ
ታምር ወጣ በገፍ!
ኧረ ተንገዳገድን ፥ ምኑን እንደገፍ?
(ገጽ 94)

ማድያት የበላት፣ ወሬኛ፣ ፌዘኛ፣ ጨካኝ፣ በ‘ሜካፕ’ ችሮታ የተዋበች የ‘እታች ቤቷ’ ሴት ትቅር፤ መደበኛ ሴት እንዴት ትጠፋለች? ያዲሳባ ጎዳና የቱን ይነግረናል? Surrealist ገጣሚ ነው እንበለው ይሆን? እኔ ለ realism መወገኔ ይሆናል። የሆንኩ ፉንጋ!
አዎን - “ውበት ያሸንፋል!”
--------
2.5) ቋንቋ
ሀ) ስነ - ውበት(Aesthetics)
ውብና ቀላል ቋንቋዎችን ተጠቅሟል። ፈጣን ናቸው ግጥሞቹ።
Robert Frost “A poem is like an ice on a hot stove” ይላል። እንጂ ግጥም እንዳደረ አሹቅ የስሜት መንጋጋችንን ሊያደክም አይገባውም። እንደ ምጣድ ላይ በረዶ እያለቀ ፣ እ`ልቅ እያለ እ`ልቅ ሊያረገን ግዱ ነው።
ለ) ግሩም ማገናዘብ
ገጣሚው በማገናዘብና ርቱዕ ተነጻጻሪ (analogy) በማቅረብ ጎበዝ ነው። እ`ያሉ ያለመኖር እንዴት ነው ያላችሁት እንደሆነ:-
እንደ ቀትር ጥላ ፥ እንደ ክረምት ጉም
እያለሁ የለሁም።   (ገጽ 144) ይላችኋል።
እንቀጥል :-
ቅር ቅር አልሽኝ ፥ ..
ውዱዕ ሳያደርግ ፥ እንደሰገደ
እያመነታ ፥ እንደፈረደ
ሳይሰናበት ፥ ርቆ እንደሄደ ፥..
(ገጽ 49)
ተመልከት ቅር ቅር ማለት ከነዚህ ነገሮች በላይ የታል!?
ሐ) ገ`ደፈ ብንል ጎደፈ አንል!
የቋንቋ ግድፈት ያየሁበት ግጥም የሚከተለው ነው። ሦስተኛው ስንኝ :-
ከዚህ ግዙፍ ሰማይ
(በግድ የምትታይ)
አንዲት ሞሳ ፀሐይ
(ገጽ 18)
 የእንግሊዝኛውን ‘አርቲክሎች’ (a,an and the) ያለማጤን ችግር ነው። አንድ ለሆነና ለታወቀ ነገር -ዩ / -ዋ(the-) የሚል ቅጥያ ነው የምንጠቀመው። ሰማዩ ፣ ፀሐይዋ(the sun) እንላለን እንጂ አንዲት ፀሐይ(a sun) አንልም። ገጽ 39 ላይ ‘ፀሐይዋ’ ብሎ በትክክለኛው ተጠቅሟል።
2.5.1)  የማቅለል ዕዳ
ግጥሞቹ በቀለለ ቋንቋ መቅረባቸው አንዳንዴ ለጉዳት ዳርጓቸዋል።
ሀ) ድግግሞሽ ና መለዘዝ
ከዓይኔ ነው? ወይስ..
......
ስለወደድኩሽ ነው ፥ ወይስ?...
(ገጽ 43)
ከ36 ገጽ ርቀት በኋላ እነዚህን ስንኞች መልሶ ይላቸዋል።
ከዓይኔ ነው? ወይስ....
........
ስለምወድሽ ነው ወይስ ፣ ...
(ገጽ 79)
ለምን? ለምን?
እንዝለቅማ :-
ቁልምጫ ከአፉ ፥ ከሞቀ እቅፉ
ለትንሽ ቀናት ፥ እንዳስለመዳት
                ወዳጇ ከዳት።
ከዚህ የባሰው ትልቁ ክፋት
ልጁ ሲለያት ፥ ልጅቱ እርጉዝ ናት።
(ገጽ 108)
ልጅት ተደፍራለች ፥
ተደፍራ ወልዳለች።
ደግሞም ፥ ልጇም እሳት
ስትገባ ስትወጣ
“አባቴስ” እያለ የሚነዘንዛት...
(ገጽ 65)
 ድግግሞሹ ሁለት የተለያየ ገጽ ላይ ብቻ ሳይሆን በ’ለት ተለት ኑረት ውስጥም ነው።  
            የሕይወት ትርጉሙ ፥
ሰርክ መጠየቅ ነው ፥ በፈላስፎች ዓለም ፤
           በአማኞች ኑሮ ፥
ከሞትም ያስፈራል ፥ ከአንድ ፈጣሪ ውጭ
         ፥ ሌላ እውነት ማለም።
(ገጽ 99)
..በዳይ ተጋዳይ ነው ፥ ራሱን ወቃሽ ነው
ከዓለም የሚፋለም ፥ አሳዛኝ ፍጡር ነው።
ተበዳይ በአንጻሩ ፥ ጻድቅ በመሆኑ
የሚጸጸትበት ፥ ጥፋት ስለሌለው..
(ገጽ 55)
እነዚህ ከላይ ያሉ ስንኞችና መሰሎቻቸው ፉርሽ ናቸው ለኔ። የተለመዱ ናቸው። ይሄ አዘቦት ነው። ድግግሞሽ ነው። ይሄ አልጫ ነው። ይሄ ጨው የለውም።
3) ሽኝት
በዚህ ዓመት የታተሙ ምርጥ የግጥም መድበሎች ብትሉኝ “እንዲህ ያለም የለ!” ቶሎ አፌ ከሚመጡ ጥቂቶች አንዱ ነው። ግሩም ነው። ድንቅ ነው። ማለፊያ ነው።
ይነበብ። ይጠርጠና ይቃም!
ቸር እንሰንብት!!

Read 204 times