Sunday, 14 July 2024 11:47

ስውር ስፌት ነው ምሥጢሩ

Written by  ፍካሬ ሰላም የሻው (መዓዛ ድንግል
Rate this item
(1 Vote)

ተብረከረከ ያ ዝሆን፤ ተንሰፈሰፈ ያ ዝሆን!
ነቢይ መኮንን፣ ምን ሆኖ ይሆን!
ሚስቱ-ልጆቹ፣ ምን ሰምተው ይሆን!
    
አይ የእምዬ ሆድ … አይ የእናት ነገር፤
በተድላ ስትኖር … በላይ በሰማይ … በጻድቃን ሀገር፤
ሲባክን ብታይ … እዚህ በሥጋ፤
ገስግሳ መጣች … ልጇን ፍለጋ።
እያልን እዬዬ … አንብተን ነበር፤
ሰማይ እስኪርድ … ጦቢያ እስኪሸበር፤
የጥበብ ባላው … ዋልታው ቢሰበር።
የሚስቱ አለኝታ … የልጆቹ አጥር … ኬላው ቢሰበር።
ለካ ሌላ ነው ጉዳዩ …. ለካ ሰውር ነው ምሥጢሩ፤
በሉ ምሥጢሩን ዜናውን ይስሙ … ሚስቱን-ልጆቹን … ደራስያን ጥሩ።
ምን ሆኗል ዛሬ ያ አንበሳ፤ ምን ሆኗል ዛሬ ያ አንበሳ!

ምነው ጨጎፈ፣ ምነው ሞገሱ ጎፈሩ ሳሳ!    
ነቢይ መኮንን፤ ዛሬ ከመድረክ የቀረውሳ!

    ለካ ተጎድቷል … እናቱን ናፍቆ፤
    ከግራ ጎኑ … ምሥጢር ደብቆ፤
    ስንቅ ልቋጥር … እንዳትል ሚስቱ፤ ሳመኝና ሒድ … እንዳትል ልጁ፤
    አትሔድም ብሎ … እንዳያስቀረው … ዘመድ-ወዳጁ፤
    ሰዉን አታሎ … እንደልማዱ … እየቀለደ …
    ቅል-ጨርቄን ሳይል … ከእናቱ ሔደ።
     እያልን በአግቦ … ወቅሰንው ነበር፤
    የግጥሙን ሻማ … የጥበቡን ፀሐይ … የጦቢያን ጀንበር።
    ለካ ሌላ ነው ጉዳዩ፣ ስውር ስፌት ነው ምሥጢሩ፤
    በሉ ምሥጢሩን … ዜናውን ይስሙ … ሚስቱን-ልጆቹን … ተዋንያን ጥሩ።
«
ተንሰፈሰፈ ያ አጋዘን፤ ተንሰቀሰቀ ያ አጋዘን!
የነቢይ ሚስት፣ ጠቁራ ቢያገኛት፣ ከል ለብሳ ያዘን!    
መድረኩን ቢያየው፣ ተክዞ ባዘን!
ተንሰቀሰቀ ያ አጋዘን!
«
    ችሎት አለብኝ … ከእናት ክርክር፤
    ናዝሬት ይፍረደኝ …  ጦቢያም ይመስክር፤
    ምንስ የእትብቱ … የእናትነት ክር፤
    ምን ቢደነድን … ምን ቢጠነክር፤
    ልጆቹን ሳይስም … ከቤት ሳይመክር፤
    በቀረ ባህል … ድንገት ከመንገድ፤
    ምን የሚሉት ነው …. ልጅ ጠልፎ መውሰድ!
«
ብለን እናትን … ከሰናት ነበር፤
በእናት ተጠርቶ … በደመና ክንፍ … ተጠልፎ ሲበር።
ለካ ሌላ ነው ጉዳዩ … ለካ ሰውር ነው ምሥጢሩ፤
በሉ ብሥራቱን አብሥሩት ይስማ … ባለቅኔው ጸጋዬን ጥሩ።

     ተንሰቀሰቀ ዱር-ጫካው፤ ተንሰቀሰቀ ዱር ጫካው!
    ቁርስም አልበላ፤ ምሳም ዘገየ፣ ነቢይ መኮንን፣ ዛሬ ምን ነካው!
    መቅረቱ አይደለም-የምር አይደልም፤ ሲያሾፍ ነው ለካ!
    እንደልማዱ-በዚያው፣ በቀልዱ እንድናውካካ።

ምነው ሸዋ!
የምን ቀልድ ነው … የምን ቧልት ነው፤
ይህን ፌዝህን … ለሌላ ንገር … ለሚያሳምነው!
ተጠልፎ ሲሔድ … የተለየን ለት፤
ቤተሰብ ሲጮኽ … የሚሳሳለት
የልጁን እንባ … ማን ያብስለት።
እሱስ እሺ ቢል … አለአኳኋኑ-አለወገኑ፤
መች አማከራት … ለግራ ጎኑ።
ይኼ ነውር ነው … ግፍ የለየለት፤
ልጅ ጠልፎ ወስዶ … ከልጅ መለየት።
ይኼ ወንጀል ነው … ሕግ መተላለፍ፤
ልቡን ሰውሮ … ድንገት የሰው ባል … ከመንገድ መጥለፍ።
ልጆች አሳቆ … እኛን በሐሜት… ኃጢአት ማስለፍለፍ።
«
እያልን … እናቱን ወቅሰናት ነበር፤
መድረኩ እስኪርድ … ጦቢያ እስኪሸበር፤
የግጥሙ ቋሚ … ነቢይ ቢታጣ … ጥበብ ቢሰበር።
ለካ ሌላ ነው ጉዳዩ፣ ስውር ስፌት ነው ምሥጢሩ፤
በሉ ምሥጢሩን … ለዓለም ይለፍፍ … አዲስ አድማስን … ይዘግብ ጥሩ።

ተርገፈገፈ ተራራው፤ በቀን ጨለመች ይቺ ዓለም!
ገዱ ክፉ ነው ምሳሌው፤ መቼም በሰላም፣ በጤና አይደለም!
መድረኩ ሳስቷል … ከመሐላችን … አንድ ሰው የለም።
ደግ እናት-አባት … ልጅ ትዳር ሲይዝ … ጎጆ ሲወጣ፤
ቁርጥ እያበላ … ጠጅ እያጠጣ፤
እስያፎከረ … መድፍ እያንጣጣ፤
ቅርስ ይሸልማል … ላምና በሬ … በቅሎና ፈረስ፤
ይቺኛዋ እናት … ልጅ ለማስለቀስ … ሆድ ለማደፍረስ፤
ልጅ ትጠልፋለች … ትዳር ለማፍረስ።
ደግሞ የአባቱ … አጉል ይሁንታ፤
አይቆጡም ወይ … ልጆች ሲንጫጩ-ትዳር ሲፈታ።
አንዴ ከሔድ … እንዳይመለስ … ጠንቅቀው ሲያውቁ፤
ምን ቢያሳሳቸው ምን ቢናፍቁ፤
ትዳር አፍረሰኽ … ልጆች በትናህ … ከእኛ ና ብለው … የሚጠይቁ።
ደግሞ የእግዜሩ፤
ድብቅ ዓላማው … ዕጹብ ምሥጢሩ፤
ገብርኤል እያለ … ፈጣኑ መላክ፤  
ልጅ እምቢ እንዳይል … እናትን መላክ!

    እያልን እግዜርን … አምተንው ነበር፤
    ድንገት በሞት ክንፍ … ተጭኖ ሲበር።
    ለካ ሌላ ነው ጉዳዩ … ስውር ስፌት ነው ምሥጢሩ፤
    በሉ ምሥጢሩን … ዜናውን ይስሙ … ገጣምያኑን፣ ከበደን፣ አቤን ደበብን ጥሩ።
 
 አሁን በሰማይ … በላይ በራማ፤
እነሆ ብሥራት …. ዜና ተሰማ!
አሸበሸበ ደመናው … አሸበሸበ ጸፍጸፉ፤
ታቅፎት ሲሔድ … ገብርኤል በክንፉ።
እናት ከፊት-ፊት … አባት ከኋላ፤
ማርያም በድባብ … አርሴማ በጥላ፤
ጻድቅ ተክልዬ … ማጥንት ሲያጥኑ … ጸናጽል ይዘው፤
ሽቶ አርከፍክፈው … ወይራ ጎዝጉዘው፤
አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ-ጴጥሮስ፣ ማኅሌት ታዘው፤
ኪሩቤል በግራ- ሱራፌል በቀኝ፤
ሳቁኤል ለብሥራት፣ ማኅሌት ሲቀኝ፤
ሰይፍ ይዞ ሲያጅብ … ቅዱስ ሚካኤል፤
ተፈስሑ አሉ፤ እነ አዛርያ እነ ሚሳኤል።
እንዲህ አጅበው … ነፍሱን ይዘዋት … ገነት ሲገቡ፤
ጻድቃን-ሰማዕታት … አሸበሸቡ።
የነቢይ ነፍስ … ተፍነከነከች … ሐሴት አነባች …
ከአእላፍ ተመርጣ … ሰማይ ቤት ገባች።
በመድኃኔ ዓለም … ሆኖ ሽኝቱ፤
እያማለደች … ድንግል እናቱ፤
መጠርጠሩሳ … እንዴት አያርግ ... ጸሎት-ማጥንቱ!
ለካ እናት አባት … እሱን የጠሩ።
ይህ ነው ጉዳዩ … ሰውር ስፌቱ … ድንቅ ምሥጢሩ።
ጸድቷል ከኃጢአት … ጸድቷል ከስኃ፤
በገፍ መጽውቷል … ጥበብ አምኃ፤
ቄዴር ተጠመቆ … በቅኔ ውኃ፤
የጽድቅ ስንቁን … ይዟል ንስሓ።
 እኔ ኃጥኡ … በለቅሶ ቋያ … በኃዘን ጋየሁ፤
እሱ ግን በላይ … እንደልማዱ … ከእናት-አባቱ … ሲሳሳቅ አየሁ።
በሰማይ ድል ነው … ባራት መዓዘን፤
በሉ በምድርም … ይበቃል ኃዘን።
ምንድነው ኃዘን … ምንድነው እንባ፤
ነቢይ በልልታ … ገነት ሲገባ።
ለእኛም ደግ አይደል … ለእሱም አይበጂ፤
በኃዘን መጠበስ፣ ፍቅር አይደለም፣ ቅናት ነው እንጂ።
ይበቃል ሙሾ፣ ይወልቃል ከሉ፤
ይህን ጥቁር ጨርቅ … ቀዳችሁ ጣሉ።
ውሸት ወይ ሐሰት … ካፌ ቢወጣ፤
ይመስክርብኝ … ከክርስቶስ ጋር … ነቢይ ሲመጣ።
«ደራሲ አይሞትም … ቅኔው አይሞትም» ሲል የተነባው፣ የነቢዩ ቃል-ትንቢቱ ያዘ፤
በእናት መጠራት … ድንቅ ቅኔ ነው-በስውር ስፌት የተሰበዘ።
ነፍስ ይማር!



Read 733 times