Sunday, 14 July 2024 11:48

ነቢይ መኮንን በአሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ዓይን

Written by  ኢ.ካ
Rate this item
(1 Vote)

“ነቢይ ተሰጥኦ ያለው ሰው ነው፡፡ ነቢይ ይጽፋል፤ ይስላል፤ ህዝብ ፊት የመናገር ችሎታ አለው፤ ግጥሞች
ይደርሳል፡፡ ነቢይ ሥራ የሚበዛበት ሰው ይመስለኛል፡፡ ቁምነገረኛም ነው፡፡ ቀልድ መናገር ያውቅበታል፤ ተጫዋች
ነው፡፡ በአንዳንድ ነገሮች ደግሞ ቁጥብ ይመስለኛል፡፡ የራሱ ክልል አለው፡፡ እኔም አንዳንዴ እንደሱ ቁጥብ ነኝ፡፡--”


ኢ.ካ

አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ካሮል ሁዋንግ፣ በአንድ አሜሪካዊ  የጉዞ ማስታወሻ ፀሃፊ በተዘጋጀ መጽሐፍ ላይ አንድ ያስደመማትን መረጃ አነበበች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው በእስር ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እያለ፣ የአሜሪካ ክላሲክ ልብወለድ የሆነውን Gone With the Wind  መጽሐፍ በሲጋራ ቁርጥራጭ ላይ ተርጉሞ ማጠናቀቁን ይገልጻል - የመጽሐፉ መረጃ፡፡ በዚህ ተርጓሚ ጽናትና ብርታት የተደመመችው ጋዜጠኛ ካሮል ሁዋንግ፤ ይህን ሰው በአካል አግኝታ ለማነጋገርና ይበልጥ ስለ እሱ ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አደረባት፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላም እዚያው አሜሪካ ሳለች፣ ተርጓሚውን በስልክ አግኝታ አነጋገረችው፡፡  የማታ ማታም፣ ባህር ማዶ ተሻግራ ወደ ኢትዮጵያ መጣች - የ39 ዓመቷ አሜሪካዊት ጋዜጠኛ (ዛሬ 58 ዓመት ይሆናታል ማለት    ነው፡፡)
በነገራችን ላይ ከተርጓሚ ነቢይ መኮንን ጋር  ቃለመጠይቅ ልታደርግ የመጣችውን አሜሪካዊት ጋዜጠኛ፣ ሥራዋን አጠናቅቃ ወደ አገሯ ልትሳፈር 30 ደቂቃ ያህል ሲቀራት አግኝቼ አንዳንድ ነገሮች አውርቼአት  ነበር፡፡ ለምልልሱም የዛሬ 19 ዓመት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ የታህሳስ 2 ቀን 1997 ዓ.ም ዕትም ላይ ለንባብ በቅቷል፤ “ከአሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ጋር ለአፍታ” በሚል ርዕስ፡፡ አንዳንድ ዝርዝር የቃለምልልሱን ክፍሎች ትተን ወደ አስኳሉ ጉዳይ እንግባ፡፡
ለአሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ፤ “ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት እንዴት አሰብሽ?” አልኳት፡፡
ጋዜጠኛውም መለሰች፤ “ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የወሰንኩት Travelling to Africa የተሰኘውን በአሜሪካዊ የጉዞ ማስታወሻ ጸሃፊ የተጻፈ መጽሐፍ ካነበብኩ በኋላ ነው፡፡ እንግዲህ ከዚያ በፊት ቻይና ሄጃለሁ፤ደቡብ አሜሪካና አውሮፓ ሄጃለሁ፡፡ ህንድና አፍሪካን ግን በደንብ አላውቃቸውም፡፡ በርግጥ ግብጽን አይቻለሁ፡፡ ሌላው ደግሞ በዚህ መጽሐፍ ላይ Gone With the Wind የተባለውን ክላሲክ ልብወለድ፣ ነቢይ መኮንን የተባለ ኢትዮጵያዊ፣ እስር ቤት እያለ መተርጎሙን ስላነበብኩ፣ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ላነጋግረውና ታሪኩን ልጻፈው ብዬ አሰብኩ፡፡”
“የነቢይን ታሪክ ለመጻፍ ያነሳሳሽ ምንድን ነው?” አስኳሉን ጥያቄዬን ወረወርኩኝ፡፡
”ምክንያቱ ምን መሰለህ---አንዳንዴ ህይወት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይከትሃል፤ ባልፈለግኸው መንገድ እንድትጓዝ ያደርጋለህ፡፡ እና ነቢይ በዚያ ሁሉ ከባድና አስቸጋሪ ህይወት ውስጥ እያለ፣ አንድ ውብ ነገር ለማግኘት ችሏል -  Gone With the Wind የተባለውን መጽሐፍ ወደ አማርኛ ተርጉሟል፡፡ ያንንም ደግሞ ከሌሎች ጋር መጋራት ችሏል፡፡ እስቲ ይታይህ፣ እርሱ በእስር ቤት እያለ፣ ምንም ነገር አልነበረውም፡፡ የሚጽፍበት ወረቀት እንኳን የለውም፡፡ መጻፊያ ብዕር አልነበረውም፡፡  በሲጋራ ወረቀቶች ላይ ይጽፍ እንደነበር ነው የነገረኝ፡፡ ይኸው አንተ እንኳን ድምጽ መቅረጫ፣ ማስታወሻ ደብተር ይዘህ ነው ወደኔ የመጣኸው፡፡ እኛ ያሻንን ልብስ ለብሰን፣ ሰዓት እጃችን ላይ አስረን፣ በተቻለ መጠን በአንዳንድ ሥራዎች ለመጠመድ እንሞክራለን፡፡ እዚህ ጋ ግን ምንም የሚሰራበት ነገር የሌለው ሰው አለ፤ በእጁ ላይ ያለው እንግዲህ አንድ መጽሐፍ ብቻ ነው - Gone With the Wind. በዚያች መጽሐፍ ግን ህልሙን እውን አድርጓል፡፡ ይኼ ነው ስሜቴን በጣም  የነካኝ፡፡ ባለችን ትንሽ ነገር እንዴት ብዙ መሥራት እንደምንችል የሚያሳይ ነው፡፡ በጣም አስቸጋሪ በሆነ  ህይወት ውስጥ እያለንም እንኳን ውብና ድንቅ ነገሮችን ማግኘት፣ መሥራት እንደምንችል ያስተምረናል፡፡” ስትል አብራርታ መለሰችልኝ፡፤
“ከዚህ ቀደም ይህን የመሰለ ተመሳሳይ ጉዳይ ገጥሞሽ ወይም አንብበሽ ታውቂያለሽ?” (የነቢይን ዓይነት ማለቴ ነው፡፡) ጋዜጠኛዋ የሰጠችው መልስ ግን አስገርሞኛል፤ የማይነጻጸሩትን ነው ለንጽጽር ያስቀመጠችልኝ፡፡ ለፍርድ እንዲመች የምትለውን እንስማት፡፡
“አዎ እናቴ ለእኔ ጥሩ ምሳሌ ነች፡፡ የዛሬ 40 ዓመት እናትና አባቴ ወደ አሜሪካ ሲመጡ የሚያውቁት ሰው ወይም ዘመድ አልነበራቸውም፡፡ ገንዘብ የላቸውም፡፡ እንግሊዝኛ እንኳን መናገር እንኳን አይችሉም፡፡ ነገር ግን ኑሮዋቸውን ከምንም ተነስተው  መመሥረት  ነበረባቸው፡፡ ችግራቸውን ሁሉ ተወጥተው የተረጋጋ ኑሮ መቀጠል ነበረባቸው፡፡ እናም ተሳክቶላቸዋል፡፡ እናቴ በደንብ አሳድጋኛለች፡፡ ት/ቤት ልካ አስተምራኛለች፡፡ በነቢይ ሁኔታም ካየኸው ---አንድ መጽሐፍ ወይም ሥነጽሁፍ ውብ መስሎ ከታየህ፣ በራሱ ጥበብ እንደማለት ነው፡፡ በርግጥ ሁሉም መጽሐፍ ውብ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ውብ መስሎ ከታየህ ግን በቃ ውብ በመሆኑ ብቻ ላንተ ልዩ ነው፡፡ ሌላው ሰው ያልታየውን ውብ መጽሐፍ ፈልጎ ማግኘት ለእኔ አስደሳች ነገር ነው፡፡”
አሁን በምን ተዓምር ነው የነቢይ በመከራና በሰቆቃ የተሞላ አሰቃቂ የእስር ህይወት፣ ባዶ እጃቸውን በስደት አሜሪካ ከገቡ ጥንዶች ጋር ለንጽጽር የሚቀርበው፡፡ ሞትና ህይወትን፣ ገነትና ሲኦልን እንደማነጻጸር ነው፡፡ ደግሞስ ማንኛውም ስደተኛ አሜሪካ ሲገባ ከባዶ ተነስቶ  አይደለም እንዴ ህይወቱን የሚለውጠው፡፡ ግን ምን ነክቶኝ ነው ንጽጽሯ ላይ ጥያቄ ያላነሳሁባት፡፡ ያኔ የዛሬ 19 ዓመት ማለቴ ነው፡፡
ቀጣዩ ጥያቄዬ፤ ”የነቢይን ታሪክ በምን መልኩ ነው ለህትመት የምታበቂው?” የሚል ነበር፡፡
ካሮል ሁዋንግ ስትመልስም፤ “ስለ ታሪኩ ለአንዳንድ ሰዎች ለመንገር እየሞከርኩ ነው፡፡ ስፖንሰር እንዲያደርጉኝ እጠይቃለሁ፡፡ አሜሪካን ሄጄ ታሪኩን የሚያወጣልኝ መጽሔት ወይም ጋዜጣ አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡”  ነበረች ያለችው፡፡  
ብዙም ሳትንገላታ ታሪኩን የሚያወጣላት ድረገጽ ያገኘች ይመስለኛል፡፡ የነቢይ ታሪክ “Tomorrow is Another Day“ (ነገም ሌላ ቀን ነው) በሚል ዋና ርዕስና “አንድ ኢትዮጵያዊ ተማሪ Gone With the Wind የተሰኘውን አሜሪካዊ  ልብወለድ፣ ወደ አማርኛ በመተርጎም ከአሰቃቂ እስር ተርፏል” በሚል ንዑስ ርዕስ ለንባብ በቅቷል - የዛሬ 18 ዓመት ገደማ፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሰፊ ዘገባ የተሰራለት የነቢይ የእስር ቤት አሰቃቂ ታሪክ The American Scholar በተሰኘ ድረገጽ ላይ ነው የወጣው፤ በፈረንጆቹ ሴፕቴምበር 1 ቀን 2006 ዓ.ም፡፡  ጋዜጠኛዋ ነቢይን ቃለመጠይቅ ባደረገችው በዓመቱ ማለት ነው፡፡
ዋናው የካሮል ሁዋንግ  የዘገባ ትኩረት ነቢይ ምንም ተስፋ በሌለበት እስር ቤት ውስጥ ሳለ፣ Gone With the Wind የተሰኘውን ዳጎስ ያለ ልብወለድ በብልጭልጭ የሲጋራ ወረቀቶች ላይ የመተርጎም ጽናቱና ተስፈኝነቱ ላይ የሚያጠነጥን ቢመስልም፣ ዘገባው ከነቢይ መኮንን ባሻገር፣ ዘመኑን ጭምር የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ዘገባው የወቅቱን የፖለቲካ ቀውስና የአብዮት ምስቅልቅል፣ የሥልጣን መጠላለፍና የእርስ መጠፋፋት ሳይቀር ይዳስሳል፡፡ በተጨማሪም የ82 ዓመቱ የኢትዮጵያ የመጨረሻ ንጉሰ ነገስት (ጃንሆይ) በኩዴታ ከሥልጣን ስለመገርሰሳቸው፣ ጨካኙ የደርግ ወታደራዊ ኃይል፣ ወታደራዊ ባላንጣዎቹን አጥፍቶ ከጨረሰ በኋላ፣ ፊቱን ወደ ሲቪሉ የተቃውሞ ሃይል ማዞሩን፣ ወቅቱ ወጣቶች የገቡበት የማይታወቅ ያህል ያለቁበት ጊዜ እንደነበር ወዘተ---ዘገባው ይጠቁማል፡፡
ንጉሱ ከሥልጣን ሲገረሰሱ ነቢይ መኮንን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲ የኬሚስትሪ ተማሪ ነበር ትለናለች -ሁዋንግ በዘገባዋ፡፡ ነቢይ በወቅቱ  እያቆጠቆጠ የነበረውን የመንግሥቱ ሃይለማርያም አምባገነናዊ አገዛዝ የሚታገለው  የሕቡዕ ንቅናቄ አባል እንደመሆኑ መጠን፣ በደርግ የደህንነት ዓይነቁራኛ ውስጥ ነበር፡፡  ሁለቴም ተይዞ ነበር፡፡ የደህንነት ሃይሎች ነቢይን የያዙት ጊዮን ሆቴል አቅራቢያ ነበር፡፡ በወቅቱ የህቡዕ ንቅናቄ አባላት የምስጢር መገናኛ ሥፍራ ሲያመራ ነበር የደህንነቶችን አራት ነጭ ፔጆ መኪኖች የተመለከተው፡፡ የእርምጃውን አቅጣጫ ከመቀየሩ በፊት ሁለት ሰዎች ወደሱ ቀረቡት፡፡ አንዱ ወደ እርሱ አመራ፡፡ ሌላኛው ከኋላ መጣ፡፡ ነቢይ ወደ ጎዳናው ሊሮጥ ሲሞክር ሌሎች ከበቡት፡፡ ከዚያም እየገፉ ቆሞ የሚጠብቅ መኪና ውስጥ አስገቡት፡፡ ከዚያም ደህንነቶቹ ለአዛዣቸው “ሸንኮራ አገዳው ተቆርጧል” ሲሉ የሬዲዮ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ጽፋለች፤ ጋዜጠኛዋ፡፡
ደህንነቶቹ ነቢይን በቀጥታ ይዘውት የሄዱት ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት ነበር፡፡ እዚያም እንደደረሰ ዓይኑን በጨርቅ ሸፍነውት፣ የተባባሪዎቹን ስምና አድራሻ እንዲጠቁም ጠይቀውት፣ አሻፈረኝ በማለቱ ስቃዩን እንዳበሉት በዝርዝር ትተርካለች፤ አንድም ሳይቀራት፡፡ አፉ ውስጥ ከሱ ቀድሞ በተሰቃየ እስረኛ ትኩስ ደምና ትውከት የተጨማለቀ  ጨርቅ  ጎስጉሰውበት፣ ፖል ላይ ሰውነቱን ገልብጠው በማንጠልጠል የውስጥ እግሩ ደም እስኪያዥ ድረስ ለቀናት በግርፋት እንዳሰቃዩት ተርካለች፡፡
ለአሜሪካዋ ጋዜጠኛ በመቀጠል ያነሳሁላት ደግሞ፤ ”የነቢይን ታሪክ ለመጻፍ ብቻ ከአሜሪካ ድረስ መምጣት ከባድ አይደለም ወይ?“ የሚል በአስተያየት የተጠቀለለ ጥያቄ ነበር፡፡ ጋዜጠኛዋም ከባድነቱን አልካደችም፡፡ ነገር ግን ነቢይ እስር ቤት ሳለ፣ ከወሰደው ሪስክ አንጻር የእኔ ምንም አይደለም ባይ ናት፡፡
“በጣም ከባድ ነው፡፡ እኔን በገንዘብ የሚረዳኝ ማንም ሰው የለም፤ ሁሉንም ነገር እየሰራሁ ያለሁት በግሌ ነው፡፡ ለነገሩ በአውሮፕላን ተሳፍሬ ስመጣ፣ ነቢይ እኔን ለማነጋገር ጊዜ ይኑረው አይኑረው እንኳን  አላውቅም ነበር፡፡ ላገኘው እንደምችል ሳላረጋግጥ  ነው ተሳፍሬ የመጣሁት፡፡ በእርግጥ አሜሪካ እያለሁ በስልክ ላገኘሁ ሞክሬአለሁ፡፡ አዎ ትልቅ ሪስክ መሆኑ ይገባኛል፡፡ ነገር ግን እርሱ የሰራው ሥራ እምነት አሳድሮብኛል፡፡ እርሱ እኮ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አንድ ትልቅ ሥራ የሰራውና ያሸነፈው ትልቅ ሪስክ ወስዶ ነው፡፡ እኔ ደግሞ በጣም ትንሹ ልሰራው የምችለው ነገር ቢኖር፣ የቱንም ያህል ሪስክ ቢኖረው፣ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ የእርሱን ታሪክ መጻፍ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ሥራ ፈትቼ የተቀመጥኩባትን ትንሽ ጊዜ ተጠቅሜ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ነበረብኝ፡፡”
“በቆይታሽ ስለ ኢትዮጵያ ምን አወቅሽ? ምንስ ተገነዘብሽ ?” አልኳት፤ የ39 ዓመቷን ጋዜጠኛ፡፡
“የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ፡፡” በማለት ጀመረች፤“ ምን ያህል እውነት እንደሆነ ባላውቅም፣ ካነበብኩት ነገር እንደተረዳሁት፣ ኢትዮጵያ ከመላው አፍሪካ ረዥም ዕድሜ ያላት አገር ናት፡፡ ለአምስት ዓመት ያህል በኢጣልያ ከመያዟ በቀር ፈጽሞ ቅኝ ያልተገዛች አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መፈጠርያ ናት፤ ሉሲ የተገኘችው እዚህቹ አገር ነው፡፡ የአባይ ወንዝ መነሻም እዚሁ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች አስደናቂ አገር ያደርጋታል፡፡” ብላ አንጀቴን አረሰችልኝ፤ አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ፡፡ ይህን መልሷን ሳነብ ከላይ ያቀረብኳቸውን ወቀሳዎች ሁሉ ይቅርታ አደረግሁላት፡፡ ስለ ኢትዮጵያ መሰረታዊ ነገሮች እኮ ነው የተናገረችው፤ ያውም በአጭር ጊዜያት፡፡
ቀጣዩ ጥያቄዬ ደግሞ፤ “ነቢይን እንዴት ትገልጪዋለሽ?” የሚል ነበር፡፡ በቀናት ዕውቂያና ዕውቀት ብቻ እንዴት ትገልጠዋለች ብዬ ጓጉቼ ነበር፡፡ በምላሽዋ ግን በእጅጉ ነው የተደመምኩት፡፡ እንዲህ አለች ጋዜጠኛዋ ስትመልስ፤
”ነቢይ እንደሚታወቀው በጣም ተሰጥኦ ያለው ሰው ነው፡፡ ነቢይ ይጽፋል፤ ይስላል፤ ህዝብ ፊት የመናገር ችሎታ አለው፤ ግጥሞችና የዘፈን ግጥሞች ይደርሳል፡፡ ነቢይ ሥራ የሚበዛበት ሰው ይመስለኛል፡፡ ቁምነገረኛም ነው፡፡ ቀልድ መናገር ያውቅበታል፤ ተጫዋች ነው፡፡ በአንዳንድ ነገሮች ደግሞ ቁጥብ ይመስለኛል፡፡ የራሱ ክልል አለው፡፡  እኔም አንዳንዴ እንደሱ ሳልሆን አልቀርም፡፡ እንደሱ ተሰጥኦ አለኝ እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ እንደሱ ቁጥብ ነኝ፡፡“
የመጨረሻ ጥያቄዬ በጋዜጠኝነት ሙያ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነበር፡፡ የጋራ ጉዳያችን ነው ማለት ይቻላል፤ ለእኔም ለእርሷም፡፡
“ጋዜጠኝነት በአሜሪካ ምን ይመስላል? ጋዜጠኞች ይታሰራሉ?“ አልኳት፡፡ (በውስጠ ታዋቂነት “እንደኛ አገር” የሚል ድምጸት ያለው ይመስላል)
ካሮል ሁዋንግም የመጨረሻዋን ምላሽ ሰጠችኝ፡፡ እንዲህ በማለት፤
“አሜሪካ ውስጥ እስር ቤት የገባ እስረኛ አላውቅም፡፡ እውነት ያልሆነ ነገር ግን መጻፍ አትችልም፡፡ ፍርድ ቤት ትከሰሳለህ፡፡ የተለያዩ መመዘኛዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ታዋቂ ሰው ወይም ፖለቲከኛ ከሆንክ፣ ጋዜጠኛው ስለ አንተ የፈለገውን መጻፍ አለበት፡፡ አየህ፤ በአሜሪካ ህግ ታዋቂ ሰው (Public figure) ከሆንክ፣ ራስህን በህዝብ ፊት አደረግህ ማለት ነው፡፡ እንደ ተራ ግለሰብ አይደለህም፡፡ በቂ ማስረጃ ካለህ የፈለግኸውን መጻፍ ትችላለህ፡፡ ሌላው ደግሞ የጻፍከው ነገር፣ ለሌላው ሰው ያስፈልጋል? (አስፈላጊ ነው?) ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ለምሳሌ ፕሬዚዳንቱ ድመት ነው ውሻ የሚወዱት? ዓይነት ትናንሽ ጉዳዮች ምንም ዜናዊ ይዘት የላቸውም፡፡ የአሜሪካን ህዝብ የነጻ ፕሬስን አስፈላጊነት በደንብ ያውቀዋል፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ትክክለኛ ውሳኔ እንዲወስን መረጃ ያስፈልገዋል፡፡ መረጃ ከሌለ ያወቀና የነቃ (informed) ህብረተሰብ መፍጠር አትችልም፡፡ በአሜሪካ ጋዜጠኛ መሆን ግን በቀላሉ የሚቻል አይደለም፤ፉክክሩ ሃይለኛ ነው፡፡”
በነገራችን ላይ አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ ካሮል ሁዋንግ፣ ያኔ እንደነገረችኝ፣ ሮይተርስ የዜና ወኪል ውስጥ የፋይናንሽያል ጉዳዮች ዘጋቢ ሆና ለአራት አመት ሰርታለች፡፡ ይህን የዛሬ 19 ዓመት የተደረገ ቃለ ምልልስ በድጋሚ ላስታውሳችሁ የወደድኩት አንድም የነቢይ መኮንን ታሪክ በመሆኑ ነው፡፡ ነቢይንም ለማስታወስ፤ ለመዘከር ጭምር፡፡
ፈጣሪ  ነፍሱን በአጸደ ገነት ያኑርለት፡፡  

Read 1203 times