ከዚህ ቀደም በነበረው እትም በመንግስት የህክምና ተቋማት ስለሚሰጥ የቅድመ ወሊድ የህክምና አገልግሎት ለንባብ ማቅረባችን ይታወሳል። የዚህን ቀጣይ ክፍል በተለይም የወሊድ አገልግሎትን አስመልክቶ ለንባብ እንሆ ብለናል።
በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በ1 ዓመት ውስጥ ለ140 ሚሊዮን እናቶች የማዋለድ አገልግሎት ይሰጣል። እኤአ በ1990 በጤና ባለሙያ አማካኝነት አገልግሎቱን ያገኙት 58 በመቶ ናቸው። እንዲሁም እኤአ በ2019 81 በመቶ የሚሆኑ እናቶች በጤና ባለሙያ አማካኝነት አገልግሎቱን ማግኘት ችለዋል። የዓለም የጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው ሁሉም ሴቶች በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት የህክምና ባለሙያ ድጋፍ ማግኘት አለባቸው። ይህም ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል እና መፍትሄ ለመስጠት ይረዳል። የእናቶች እና የጨቅላ ህፃናትን ሞትን ይቀንሳል። እናም ብዙ ሀገራት የእናቶች እና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ መቶ በመቶ በሚባል ሁኔታ የማዋለድ አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ተቋማት ላይ እየሰሩ ይገኛሉ።
በአ.አ ከተማ ኮ/ቀ ክ/ከ ወረዳ 3 ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት የጤና መኮንን ፍቅሬ አየለ እንደተናገሩት ጤና ጣቢያው በ1 ወር ውስጥ በአማካይ እስከ 350 ለሚሆኑ ነፍሰ ጡር እናቶች ቅድመ ወሊድ የህክምና ክትትል አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ማለትም በ1 ዓመት ውስጥ ከ4ሺ በላይ ነፍሰ ጡር ሴቶች አገልግሎቱን ያገኛሉ። እነዚህ ተጠቃሚዎች በጤና ጣቢያው ለመጀመሪያ ጊዜ ክትትል ማድረግ የጀመሩ ብቻ ናቸው። እንዲሁም በ1 ወር ውስጥ በተቋሙ የሚወልዱ እናቶች ከ150 እስከ 200 መሆናቸውን ባለሙያው ተናግረዋል። በጤና ጣቢያው ክትትል አድርገው ወደ ከፍተኛ የህክምና ተቋም (ሆስፒታል) የሚላኩ እናቶች ቁጥር በ1 ወር ውስጥ በአማካይ 200 ነው።
“ባለፈው ወር ከ700 በላይ ማለትም በቀን እስከ 26 እናቶች የቅድመ ወሊድ እና የወሊድ አገልግሎት አግኝተዋል” ያሉት በአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ክፍል ሀላፊ የሆኑት የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሺመክት ይልማ ናቸው። ከእነዚህ መካከል 520 ሴቶች ቅድመ ወሊድ የህክምና ክትትል ያገኙ እንዲሁም 160 እናቶች ትስስር ካላቸው የህክምና ተቋማት ተልከው(ሪፈር) የወሊድ አገልግሎት የተሰጣቸው ናቸው።
ዶ/ር ሺመክት ይልማ እንደተናገሩት በብዛት ወደ አለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚላኩ ነፍሰ ጡር እናቶች ተጓዳኝ ችግር ወይም ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ (high risk) ናቸው። ስለሆነም በእርግዝና ወቅት አንዲት እናት 8 ጊዜ የህክምና ክትትል ማድረግ እንዳለባት ከተቀመጠው መመሪያ በበለጠ (ቁጥር) ነው ክትትል የሚያደርጉት። በዚህም ሁሉን ያማከል የህክምና አገልግሎት ያገኛሉ። አገልግሎቱን የሚያገኙት ነፍሰ ጡር ሴቶች ጥቅሙን በመገንዘብ የህክምና ክትትሉን እንደሚያደርጉ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሺመክት ይልማ ተናግረዋል።
በአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስር (ትስስር ባላቸው) ጤና ተቋማት ክትትል ሲያደርጉ የነበሩ ወደ ሆስፒታሉ የተላኩ (ሪፈር የተባሉ) እና የወለዱ እናቶችን አነጋግረናል። እናቶቹ በሆስፒታሉ ከወለዱ ከሰአታት በኋላ የህክምና አገልግሎት በሚያገኙበት ወቅት ነው ሀሳባቸውን ያጋሩን። የመጀመሪያዋ ልምዷን ያካፈለችን እናት ተሚማ ትባላለች። በአለርት ሆስፒታል የወለደችው 3ኛ ልጇን ነው። ከዚህ ቀደም 2 ልጆች የወለደችው እንዲሁም የ3ኛ ልጇን የህክምና ክትትል ያደረገችው ቀራኒዮ አከባቢ በሚገኝ ወረዳ 8 ጤና ጣቢያ ነው። እንደ ተሚማ ንግግር ወደ አለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እንድትሄድ የተደረገበት ምክንያት የፅንሱ አቀማመጥ ልክ ባለመሆኑ ነው። “ህክምና መከታተል በጣም ጥሩ ነው። የሚሰጠው አገልግሎት ጥሩ ነው” ብላለች ተሚማ።
“ቡሉ ሆራ አከባቢ ክትትል ሳደርግ ቆይቻለው። ከዛ አየር ጤና አከባቢ ያለ ጤና ጣቢያ ስከታተል ከቆየሁ በኋላ ደም ከፍ ሲል ወደ አለርት ተላኩ” ያለችው ያስሚን ናት። ያስሚን ለህክምና ክትትል በሄደችበት አጋጣሚ (ምጥ ሳይመጣ) ነው እንድትወልድ ወደ አለርት የተላከችው። እንደ ያስሚን ንግግር እርግዝናው ከ9 ወር አልፎ ነበር። እንዲሁም ያጋጠማት የጤና ችግር በማንኛውም እርግዝና ላይ ሊያጋጥም የሚችል መሆኑን ነው ባለሙያዎች የነገሯት። በምጥ ነው ልጇን የወለደችው። ነገር ግን ያስሚን እንደተናገረችው የመጀመሪያ ልጇ እንደመሆኑ በምጥ ለመውለድ ባላት ፍራቻ ምክንያት ቀዶ ጥገና ነበር ምርጫዋ። ለህክምና ባለሙያዎቹ በቀዶ ጥገና እንዲያዋልዷት እና በምጥ ለመውለድ ፍቃደኛ አለመሆኗን ነበር የነገረቻቸው። “በጣም አስቸግሬያቸው ነበር። ዶክተሮቹ ግን አላህ ይስጣቸው በምጥ መውለድ ትችያለሽ ብለው እንድወልድ አድርገውኛል” ብላለች ያስሚን። እንዲሁም በምጥ መውለድ ህመም ቢኖረውም የተሻለ መሆኑን ያስሚን ተናግራለች።
“አንዳንድ ጊዜ ከዚህ ቀደም ያልወለዱ እናቶች ምጥ ይፈራሉ። ምጡን ሳያዩ ነው የሚፈሩት። ስለዚህ በአዕምሯቸው ላይ የተቀረፀ ነገር አለ ማለት ነው” በማለት የጤና መኮንን ፍቅሬ አየለ ተናግረዋል። ነገር ግን በተፈጥሯዊ መንገድ መውለድ የተሻለ መሆኑን እና ቀዶጥገና አስፈላጊ ሲሆን እንደሚሰጥ ተናግረዋል። አክለውም በሙሉ ጤንነት ላይ ያሉ እና በምጥ ለመውለድ የሚያስተጓጉል ችግር የሌለባቸው ሴቶች በምጥ ቢወልዱ የተሻለ ነው ብለዋል።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሺመክት ይልማ “መቼስ ተፈጥሮን የመሰለ ነገር የለም። መለኪያም የለውም” በማለት በምጥ ስለመውለድ ተናግረዋል። ባለሙያው እንደተናገሩት በምጥ መውለድ በቀዶ ጥገና ከመውለድ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጥቅም አለው። ከጥቅሞቹ መካከል የህመም ስሜት፣ የሚፈሰው ደም፣ ተያያዥ የሆኑ የሰውነት ክፍሎች ጉዳት እና በወለደችበት የህክምና ተቋም የሚኖራት ቆይታ አነስተኛ መሆን ይጠቀሳል። እንዲሁም የህመም ስሜት ለመቀነስ የሚሰጥ መድሃኒት የመፈለግ ሁኔታ እና ጡት ለማጥባት ዝግጁ ለመሆን የምትፈልገው ጊዜ አነስተኛ ነው። ማንኛዋም እናት በምጥ መውለድ ትችላለች። በምጥ መውለድ ለማትችል ወይም በተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች (ችግሮች) ምክንያት ነው አንዲት ሴት በቀዶ ጥገና እንድትወልድ የሚፈቀደው። በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት እ.ኤ.አ 1990 በዓለም አቀፍ ደረጃ 7 በመቶ ለሚሆኑ እናቶች በቀዶ ጥገና አማካኝነት የማዋለድ አገልግሎት ተሰቷል። እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2021 21በመቶ የሚሆኑ እናቶች ናቸው በቀዶጥገና አማካኝነት የወለዱት። ለዚህ ቁጥር መጨመር እንደ ምክንያት የተጠቀሰው ፅንሱ ከ1 ልጅ በላይ መሆን፣ የእናቶች ከመጠን ያለፈ ውፍረት እና እድሜ ከገፋ በኋላ መውለድ ነው።
ወላዶች ወይም ነፍሰ ጡር እናቶች ህክምና በሚያስፈልጋቸው ወቅት በመንግስት ተቋማት ባለ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት የህክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚቸገሩበት ወይም የሚጉላሉበት ሁኔታዎች መኖሩ ይነገራል። ስለሆነም በወረዳ 3 ጤና ጣቢያ እንዲሁም በአለርት ሆስፒታል ስላለው ሁኔታ (አሰራር) ለዶ/ር ሺመክት ይልማ እና ለጤና መኮንን ፍቅሬ አየለ ጥያቄ አቅርበናል። በአዲስ አበባ ከተማ ኮ/ቀ ክ/ከ ወረዳ 3 ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት የጤና መኮንን ፍቅሬ አየለ ወደ ወረዳው ለሚመጡ ሴቶች በሙሉ አስፈላጊውን ህክምና እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተመሳሳይ በአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ክፍል ሀላፊ የሆኑት የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሺመክት ይልማ “ምንም ገደብ የለንም” በማለት ምላሽ ሰተዋል። ለአገልግሎቱ ተደራሽነት ጤና ጣቢያዎች አቅራቢያቸው ወደሚገኙ ከፍተኛ የህክምና ተቋማት (ሆስፒታሎች) መመደባቸው አስተዋፅኦ አበርክቷል።
መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ከሚደረጉ 5 የማዋለድ አገልግሎቶች ውስጥ 1 እናት የምትወልደው በግል የህክምና ተቋም ውስጥ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አስቀምጧል። የጤና መኮንን ፍቅሬ አየለ እንደተናገሩት ነፍሰ ጡር ሴቶች ቅድመ ወሊድ የህክምና ክትትል እንዲሁም የማዋለድ አገልግሎት በጤና ጣቢያ (የመንግስት የህክምና ተቋም) በማግኘታቸው የተለያዩ ጥቅሞችን ያገኛሉ።
ለእናት እና ለልጅ ከሚሰጠው የጤና ጥቅሞች በተጨማሪ አገልግሎቱ ያለ ክፍያ መሰጠቱ እናቶችን (ወላጆች) ከወጪ ይታደጋል። ባለሙያው እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም ወደ ጤና ጣቢያ የሚሄዱ እናቶች በኑሮ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነበሩ። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ሰዎች ስለ አገልግሎቱ ግንዛቤ ስላላቸው በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች ወደ መንግስት የህክምና ተቋማት ይሄዳሉ። ባለሙያው ከህክምና ተቋማት ሳቢነት እና ከተገልጋዮች አቀባበል አንፃር የመንግስት ተቋማት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ችግሮቹ ላይ መስራት እንደሚፈልግ ተናግረዋል። አክለውም መንግስት ትኩረት በመስጠት እየሰራበት ነው ብለዋል። በአ.አ ከተማ ኮ/ቀ ክ/ከ ወረዳ 3 ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት የጤና መኮንን ፍቅሬ አየለ እናቶች ወደ ጤና ጣቢያዎች በመሄድ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ በአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ክፍል ሀላፊ የሆኑት የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ሺመክት ይልማ ሆስፒታሉ አስፈላጊውን አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል። “ከዚህ ቀደም አለርት ከቆዳ ጋር በተያያዘ ህክምና ነበር ስሙ የሚነሳው። ነገር ግን ሆስፒታሉ የቅድመ ወሊድ፣ የማዋለድ እና የድህረ ወሊድ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል። ሁሉንም ያማከለ አገልግሎት ነው የሚሰጠው። ስለሆነም በራችን ክፍት ነው” በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።
Sunday, 14 July 2024 12:00
የማዋለድ አገልግሎት በመንግስት የህክምና ተቋማት
Written by ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Published in
ላንተና ላንቺ