Saturday, 19 May 2012 10:18

እኔ “ሎካል ዜጋ” ነኝ!

Written by  ዳዊት
Rate this item
(1 Vote)

“ዳያስፖራዎች በህልማቸው የሚያዩት ሚኒስትር አላቸው”

አውሮፓና አሜሪካ ከአራት አመታት ወዲህ ያጋጠማቸው ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ የፈጠረባቸው መንኮታኮት” ለዘመናት ይዘውት የቆዩትን የአለም የኢኮኖሚና ብልፅግና መዘውር በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ለመጡትና “ብሪክስ” በሚባል ዘመነኛ ምህፃረ ቃል ለሚጠሩት አገራት ለማስረከብ በቁዋፍ ላይ ናቸው፡፡ “ብሪክስ” የሚለው ዘመነኛ የምህፃረ ቃል የሚገልፀው ብራዚልን” ሩሲያን” ህንድንና ቻይናን ነው፡፡ እነዚህ አገራት ደግሞ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገትና ብልፅግና በማስመዝገብ በአለም የኢኮኖሚና የፖለቲካ መድረክ የዋና ተዋናይነቱን ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ ሀገራት ናቸው፡፡ከሀገርም ሀገር አለ እንደሚባለው ሁሉ” ከእነዚህ ሀገራት ውስጥ ቻይናና ህንድ ላለፉት አስርት አመታት ያስመዘገቡት የኢኮኖሚ እድገት” በተለይ ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂው መስክ ያሳዩት እርምጃ ድፍን አለሙን  አጀብ ያሰኘ ነው፡፡

በቅርቡ ጃፓንን አስለቅቃ በአለም ታላቅ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ” የሁለተኝነትን ቦታ የተቆጣጠረችውና በጥቂት አመታት ውስጥም አሜሪካንን በመብለጥ የአለምን ቁጥር አንድ የኢኮኖሚ ሀያልነት ዘውድ እንደምትደፋ የተተነበየላት ቻይና” ለዚህ ደረጃ  እንድትበቃ በዋናነት ያገዛት በሳይንስና ቴክኖሎጂው መስክ ያስመዘገበችው አቻ የለሽ ከፍተኛ እድገት ነው፡፡ ለዚህ ከፍተኛ እድገት ቁልፍ ሚና ከተጫወቱት ዜጐቿ ውስጥ በመላው አለም በተለይ ደግሞ በአሜሪካና አውሮፓ ተበትነው የሚገኙት ምርጥ ልጆቿ ወይንም በእኛ አገር አጠራር “ዳያስፖራዎቿ” ናቸው፡

እንደ ቻይና ሁሉ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገትና ብልፅግና እያስመዘገበች” በእድገት ጐዳና በከፍተኛ ፍጥነት በመገስገስ ላይ የምትገኘው ህንድም በሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ያሳየችው የላቀ ግስጋሴ” የመላውን አለም አድናቆት አትርፎላታል፡፡ እንደ ቻይና ሁሉ ህንድም ላቅ ላለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገቷ” መተኪያ የለሽ ሚና ከተጫወቱት ዜጐቿ ውስጥ በመላው አለም የተበተኑት ዳያስፖራዎቿ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡

እነዚህ የቻይናና የህንድ ዳያስፖራዎች በሚኖሩባቸው ሀገራት (በተለይም ደግሞ በአሜሪካና በአውሮፓ ሀገራት ያሉት) የተለያዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ሀገራቸው እንዲገባ በማድረግ” ከእነዚህ የበለፀጉ ሀገራት ባገኙት እውቀትና ክህሎት በመታገዝ” የተራቀቁና የላቁ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመፍጠር” ሀገራቸው ተጠቃሚ ትሆን ዘንድ ባደረጉት አስተዋፅኦ በየሀገሮቻቸው” ትውልድና ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ድንቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡

የቻይናና የህንድ ዳያስፖራዎች” ሀገራቸው በእድገትና ብልፅግና ወደፊት እንድትገሰግስ ይህንን  ታላቅ ሚና የተጫወቱት” በተሰማሩበት የስራ መስክ ከሚያገኙት ክፍያ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠረውን ወደ ሀገራቸው መላካቸውን ለአፍታም እንኳ ሳያቋርጡ ነው፡፡ የዳያስፖራዎችን የ“ሬሚታንስ” ወይም ወደየአገሮቻቸው የሚልኩትን የገንዘብ መጠን አስመልክቶ ባለፈው የፈረንጆች አመት (2011ዓ.ም) የአለም ባንክ ባወጣው መረጃ መሰረት “ ከዳያስፖራ ዜጐቻቸው ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ቻይናና ህንድ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡

የቻይናና የህንድ ዳያስፖራዎች በዚህ እንቅስቃሴአቸው ውስጥ ቀዳሚውና ዋናው ጉዳያቸው አንድ ነገር ነው - ሀገራቸውና ሀገራቸው ብቻ፡፡ በሌሎች ሀገራት ዳያስፖራዎች ዘንድ እንደሚታየው” የቻይናም ሆነ የህንድ ዳያስፖራዎች በየሀገሮቻቸው የሚካሄደውን የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተመለከተ የተለያየ አቁዋምና  የየግል ተሳትፎም አላቸው፡፡

በየሀገሮቻቸው ያሉትን መንግስታት በተመለከተም እንደየግል አመለካከታቸው በድጋፍና በተቃውሞ ጐራቸውን ለይተው ይቆማሉ፡፡ ይህ የአመለካከትና የአቋም ልዩነት ግን  ከሀገራቸው ቀጥሎ የሚመጣና በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ነው፡፡ ታሪክ በግልፅ እንደሚያሳየው” ለቻይናና ለህንድ ዳያስፖራዎች” የመንግሥትና የፖለቲካ ጉዳይ ጨርሶ ከግምት ውስጥ የማይገባ ነው ባይባልም” ለሀገራቸው እድገትና ብልፅግና የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ የሚያስተጓጉል አለያም የሚያስቀር አቅም ግን የለውም፡፡ ለእነሱ የሀገራቸው ሁኔታ የፖለቲካ አመለካከትና አቋም የማይያዝበት” ከሁሉም ነገር በላይ የላቀ” ይልቁንም በሀገራቸው የእድገትና የብልፅግና የታሪክ ማህደር ውስጥ ለመመዝገብ እሽቅድድም የሚደረግበት የአርበኝነት ትግል ነው፡፡

ለምሳሌ በዋናነት በአሜሪካና በአውሮፓ የሚኖሩ እጅግ በርካታ የቻይና ዳያስፖራዎች” በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሚከተለውን የፖለቲካ መርህና የዜጐች የነፃነትና የሰብአዊ መብት አያያዝ መቃወም ብቻ ሳይሆን አደባባይ በመውጣት በግልፅ ያወግዙታል፡፡ ነገር ግን ይህ ተቃውሞዋቸው” የአውሮፓና የአሜሪካ የተራቀቁ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶችን ወደ ሀገራቸው ለማስገባት ሲሉ በስለላ ወንጀል ላይ ከመሰማራት እንኳ ሊገታቸው አልቻለም፡፡

ለቻይናና ለህንድ ዳያስፖራዎች” የሀገራቸው እድገትና ብልፅግና ጉዳይ” የግል ጥቅምና ምቾት ጥያቄዎች የማይቀርብበት” የዜግነት ድርሻን የመወጣት መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ለቻይናና ለህንድ ዳያስፖራዎች የሀገር ግንባታ ጉዳይ አንዳች አይነት የቅድመ ሁኔታ ዴዚዴራታ የማይተረክበት ሲሆን ከግለኝነት በፀዳ ሙሉ ፈቃደኝነት የሚከወን ታላቅ የአርበኝነት ትግል ነው፡፡

የተለያዩ መንግስታት ከዳያስፖራ ዜጐቻቸው የሚያገኙትንና ሊያገኙት የሚችሉትን ተጨማሪ ጥቅሞች ለማሳደግ ሲሉ እንደሚያደርጉት ሁሉ” የቻይናና የህንድ መንግስታትም መልካምና አዋጭ ነው ያሉትን የተለያዩ የማትጊያ እርምጃዎችን ይወስዳሉ፡፡ አብዛኞቹ የቻይናና የህንድ ዳያስፖራዎች” መንግስታቸው በሚወስዳቸው እንደዚህ ያሉ የማትጊያ እርምጃዎች ተጠቃሚ በመሆናቸው ደስተኛ ቢሆኑም” ከመንግስታቸው ጋር ተቀምጠው የሚደራደሩበት ጉዳይ ግን አይደለም፡፡ ለቻይና የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ እድገት እንደ ፊታውራሪ የሚቆጠረው ትውልደ ቻይና አሜሪካዊው ኢንጂነር ሮበርት ኩያንባኦ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ተጠይቆ ሲመልስ” “መንግሥት ባዘጋጀው የተለያየ የማትጊያ ፕሮግራም ተጠቃሚ በመሆኔ ከቻይናና ከህዝቧ ጋር ያለኝ ግንኙነት እጅግ ቅርብ እንዲሆን ስላደረገልኝ በእጅጉ ደስተኛ ነኝ፡፡ ባለኝ እውቀትና ችሎታ ለቻይና እድገትና ብልፅግና የሚደረገውን ትንሽዬ አስተዋፅኦ የማደርገው” የዜግነት ታሪካዊ ግዴታዬንና ሃላፊነቴን ለመወጣት እንጂ የመንግስትን የማትጊያ ጥቅማ ጥቅም ለማግኘት ብዬ አይደለም፡፡ እንዲህ ከሆነማ ሀገርን የመክዳት ያህል አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ ቻይና አሁን እያስመዘገበችው ባለችው ከፍተኛ እድገት ከመጠን በላይ ደስተኛ ነኝ፡፡ ለእኔ ቻይና ምንጊዜም ቻይና ናት፡፡ እናት ሀገሬ!” ሲል  “ቻይና ዴይሊ” ከተባለ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ አስረድቷል፡፡

ትውልደ ህንድ አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ሳሙኤል ቻንድራካር” ከአራት አመት በፊት ለፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ የሰጡት መግለጫ ከመርዘሙና ይበልጥ ዘርዘር ከማለቱ በቀር ቻይናዊው ኢንጂነር ከተናገረው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ቻንድራካር” ህንድ በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ላደረገችው ከፍተኛ እድገት የላቀ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ የሚነገርለት ከፍተኛ ባለሙያ ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ከፍተኛ ባለሙያዎች  የሚያመሳስላቸው ሌላ ጉዳይ ደግሞ የመንግሥታቸውን የተለያዩ ፖሊሲዎችና አሰራሮች በግልፅ የሚቃወሙ መሆናቸው ነው፡፡ ትውልደ ቻይና አሜሪካዊው ኢንጂነር ሮበርት ኩያንባኦ” የቻይና መንግስትን የቲቤት ፖሊሲ በግልፅ ሲቃወም” ትውልደ ህንዱ አሜሪካዊ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ቻንድራካር ደግሞ የህንድ መንግስት በከፍተኛ ሙስና መዘፈቁንና ሙሰኝነትን ለመዋጋትም የሚያደርገው ትግል አናሳና እዚህ ግባ የማይባል ነው በሚል በግልፅ ተቃውሞውን ያሰማል፡፡

አሁን ወደ ሀገራችን ዳያስፖራዎች እንመለስ፡፡ የእኛ ሀገር ዳያስፖራዎች ወደ ሀገር ውስጥ በሚልኩት የማይናቅ መጠን ያለው ገንዘብና በአንዳንድ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት ለሀገራችን እድገት በሚያደርጉት አስተዋፅኦ ማንም አድናቆቱን ሊነፍጋቸው አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ የእኛን ሀገር ዳያስፖራዎች ከቻይናና ህንድ ዳያስፖራዎች ጋር ሳነፃፅራቸው ቢያንስ በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ይለያዩብኛል፡፡

የእኛዎቹ ዳያስፖራዎች በውጭ ሀገር በመኖራቸውና ገንዘብ ወደ ሀገር ቤት ለወዳጅ ዘመድ በመላካቸው” ያም ገንዘብ ሀገሪቱ አንዳንድ ምርቶቿን ወደውጭ ሀገር በመላክ ከምታገኘው በእጅጉ ስለሚበልጥ” ራሳቸውን ከሌላው የሀገሪቱ ዜጋ የላቁና ልዩ የሆኑ የሀገሪቱ የህብረተሰብ ክፍል አድርገው መቁጠራቸው አንደኛው መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች”“ዲያስፖራ” የተሰኘ አዲስ ብሄረሰብ በሀገራችን ተፈጥሯል እያሉ መሸርደድ ጀምረዋል፡፡

ሁለተኛው መሰረታዊ ጉዳይ ደግሞ ከላይ በጠቀስነው አስተዋፅኦዋቸው የተነሳ ብቻ ከሌላው ዜጋ በተለየ ሁኔታ “መጠቀም” አለብን ብለው መፈጠማቸው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የእኛ ሀገር ዳያስፖራዎች በተለያዩ አስገዳጅ ፖለቲካዊና “ከዚህች ሀገር የማይሻል ምንም ነገር የለም” በሚል ምሬትና ጥላቻ የተነሳ” በውጭ ሀገር በመኖራቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው በሚልኩት ገንዘብ የተነሳ እኛኑ ጥቀሙን ባይ መሆናቸው ነው፡፡

እነዚህ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ማንም በቀላሉ ሊታዘበው የሚችልና እነሱም ቢሆን በተለያየ አጋጣሚ በተደጋጋሚ ያረጋገጡት ጉዳይ በመሆኑ” አሌ ብሎ መሟገት “ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” የሚለውን ሀገርኛ አባባል ሊያስጠቅስ ይችላል፡፡

የሆኖ ሆኖ መንግስት ልክ እንደኛው ሁሉ ከላይ የጠቀስናቸውን ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ጥንቅቅ አድርጐ እያወቀም ቢሆን” እንደ መንግሥት መወጣት ያለበትን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ሲል የተለያዩ የማትጊያ እርምጃዎችን በመውሰድ” ከሌላው ዜጋ በተለየ ሁኔታ ዳያስፖራዎቻችንን የተለያዩ ጥቅሞችና አገልግሎቶች ተጠቃሚና ተገልጋይ እንዲሆኑ ከማድረግ ጨርሶ ወደ ሁዋላ አላለም፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሚሰጣቸውን ጥቅምና አገልግሎቶች ለማዳበር እንዲሁም አሉብን የሚሏቸውን ችግሮች ለመፍታትም” የተለያዩ የውይይትና የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀትና ከፍተኛ ባለስልጣኖቹን በመላክ ያወያያል፡፡ ይህንን ጥረቱን የበለጠ ለማዳበር በማሰብም” ዳያስፖራዎችን ብቻ የሚመለከት አዲስ የዳያስፖራ ፖሊሲ ቀርፆ ህግ አድርጐ ለማውጣት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡

በቅርቡም መንግሥት የዚሁ እንቅስቃሴ አካል የሆነ ውይይት በማዘጋጀት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑትን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣኖቹን በመላክ ከዳያስፖራዎቻችን ጋር ተወያይቷል፡፡ በውይይቱም ወቅት የእኛ ዳያስፖራዎች ያው እንደተለመደው በ“ጥቀሙኝ”ና “አገልግሉኝ” አስተሳሰባቸውና ጠንካራ እምነታቸው የተነሳ” ቀረብን ተጓደለብን ያሉትን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጥያቄዎችን ለመንግስት አዥጐድጉደው በጭንቀት ወጥረውት ከርመዋል፡፡

ዳያስፖራዎቻችን ከመንግሥት ባለስልጣኖች ጋር ያደረጉትን ውይይትና ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ከተከታተልኩ በሁዋላ” በግሌ የተሰማኝ ስሜት ሁለት አይነት ነው፡፡ ቅናትና ቅሬታ፡፡

የቅናት ስሜት የተሰማኝ ለወገኖች ለሀገሬም ሆነ ለመንግስት እያበረከትኩት ያለሁት አገልግሎት ከአብዛኛዎቹ ዳያስፖራዎች የሚበልጥ ሆኖ ሳለ” ውጭ ሀገር ባለመኖሬ ወይም እዚሁ ሀገሬ ውስጥ ኗሪ በመሆኔ የተነሳ ብቻ” የአዲሱ የዳያስፖራ “ብሔረሰብ” አባል መሆን አለመቻሌ ሲሆን የቅሬታ ስሜት የተፈጠረብኝ ደግሞ ከአብዛኛዎቹ ዳያስፖራዎች የሚበልጥ አገልግሎት እየሰጠሁ ቢሆንም ቅሉ” እንኳን አዲስ የማትጊያ ፖሊሲ ሊቀረጽልኝና የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ባሉብኝ ችግሮች ዙሪያ ሊያነጋግሩኝ ቀርቶ” እኔ ራሴ ያስገባሁዋቸው  የማመልከቻ ደብዳቤዎችና አቤቱታዎች እንኳ ምላሽ አላገኙም፡፡

የቅሬታዬና የቅናቴ መነሻም ሆነ መድረሻ ለወገኖቼ” ለሀገሬና ለመንግስት አሁን ከምሰጠው በእጅጉ የላቀ ጥቅምና አገልግሎት ለመስጠት በመፈለግ እንጂ ከሌላው ዜጋ የተለየ ተጨማሪ ጥቅምና አገልግሎት እንዲሰጠኝ ለመጠየቅ በመፈለግ አይደለም፡፡

በኢህአዴግኛ የበለጠ ለማብራራት” ሀገሬን ወገኖቼንና ልማታዊውን መንግስት” በላቀ ግለሰባዊ ተነሳሽነት” አቻየለሽ ህዝባዊ አገልግሎት በማበርከት” የምዕተ አመቱን የልማት ግቦች በማሳካት” የሀገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ በመፈለግ እንጂ ጨርሶ የኪራይ ሰብሳቢነት አባዜ ተጠናውቶኝ አይደለም፡፡

ስለዚህ ይህን መሪና ግንባር ቀደም የሆነ ማሳሰቢያዬን ተቀብላችሁ” ልክ ካላችሁልኝ ሌላው እዳው ገብስ ነውና ወደ ዋናው ጉዳዬ ልሸጋገር፡፡

የእኛ ዳያስፖራዎች” የመንግስት የማትጊያ ጥቅሞች ባለቤት እንዲሆኑ ያስቻላቸውና ለእነሱ ብቻ ተለይቶ የተቀረፀ ፖሊሲ እንዲዘጋጅላቸው ያደረጋቸው አንዱና ዋነኛው ምክንያት” ለወዳጅ ዘመዶቻቸው የሚልኩት ገንዘብ” ለመንግስት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ስለሆነለት ነው፡፡

እኔም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሠራተኛ” እንደ ታላቅ እድለኛ አድርጐ ከሚቆጥራቸው ጥቂት የአለም አቀፍ ድርጅት ተቀጣሪዎች አንዱ በመሆኔ” ከመንግስት መስሪያ ቤት ሠራተኞች ምናልባትም ከአንዳንድ የግል ድርጅት ሠራተኞች የተሻለ ሳይሆን ላቅ ያለ የወር ገቢ እንዲኖረኝ አስችሎኛል፡፡

በወር ከማገኘው ገቢ ውስጥ ዳያስፖራዎችም ሆኑ ሌሎች ወገኖቼ እድሜ ዘመናቸውን ሲያደርጉት እንደኖሩት ወላጆችን” እህት ወንድሞችን” አክስት አጐቶችን ሁሉ አስተዳድራለሁ፡፡ በጐደለ እሞላለሁ፡፡ ታላቅ ወንድም ጥላ ከለላ ነው የሚለው ዘመን የጠገበ አገርኛ አባባል እኔም ትከሻ ላይ እንዳለ ነው፡፡

አብዛኛው ዳያስፖራና ያገር ውስጡ ህዝባችን በሆዱ አምቆ የሚበግንበት የተደጓሚዎቻችን እጅን ረዘም አድርጐ መዘርጋት እንጂ በወሩ የተሰጣቸውን አንድ መቶ ብር” አንድ መቶ አንድ ብር ለማድረግ አለመፈለግ ወይም አለመትጋት በግልጽ ባልናገረውም እኔንም ያበግነኛል፡፡

የአብዛኞቹ ዳያስፖራዎች ወንድም እህቶቻቸው” ወዳጅ ዘመዶቻቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ንዋይ ፈሰስ አድርገው የቢዝነስ ተቋም እንዲከፍቱላቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚወተወቱት ውትወታ እኔም ዘንድ አለ፡፡ “የፈረንጁ ዶላር እየዛቀ ለእህቱ ወይም ላክስትና ላጐቱ ልጅ ሚኒባስ አሊያም ገልባጭ መኪና ቢገዛለት ወይም ደግሞ በመርካቶና በፒያሳ አንድ አምስት መቶ ሺ ብር የምታወጣ” ውላ የምትገባበት ትንሽዬ ቡቲክ ቢከፍትላት ምናለ? ወንድም ለመቼ ነው?” እኔም ቤት ነጋ ጠባ ያለማቋረጥ የማዳምጠው” ጥሩ አቀናባሪ ያልነካውና ጥሩ ድምጻዊ ያላንጐራጐረው ነጠላ ዜማ ነው፡፡

“መጥኖ መውለድ” በሚለው መርህ ሳይሆን የኑሮው ሁኔታ ከእለት እለት በማይታመን ከፍተኛ ፍጥነት እያሻቀበ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ መሄዱን ብቻ በዋናነት ታሳቢ በማድረግ” መጥኜ የወለድኩዋቸውን ሁለት ህፃናት ልጆቼን ሁኔታም ልትዘነጉት አይገባም፡፡ የልጆቹን ትምህርት በተመለከተ የተሻለ እውቀት እንዲያገኙ” እንደ አይ ሲ ኤስና ሳንፎርድ የመሳሰሉትን ት/ቤቶችን ብቋምጣቸውም “ላያዛልቅ ፀሎት ለቅጥፈት” እንዳይሆንብኝ ብዬ ትቻቸዋለሁ፡፡

ከህሊናዬ የፀፀት እብክ ለማምለጥና “የፈረንጅ ዶላር እየዛቀ” የሚለውን የጓደኞቼንም ሆነ የአካባቢዬን ህብረተሰብ ትችትና ሽሙጥ በመፍራት” መካከለኛ ደረጃ አላቸው ከሚባሉት ት/ቤቶች በአንዱ” በአመት በርካታ አስር ሺ ብሮችን መክፈል እኔው ትከሻ ላይ የተጣለ ሃላፊነት ነው፡፡

የእኔን ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች ሁሉ በገንዘብ እንደማስተዳድርና በዙሪያ መለስ እንደምደጉመው ሁሉ” የባለቤቴን ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች ማስተዳደርና መደጐምም የእኔው ሃላፊነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እኔ እያልኩ የምተርክላችሁ የእኔን ግማሽ አካል ከባለቤቴ ግማሽ አካል ጋር አዳብዬ ነው፡፡

ማህበራዊ ኑሮአችን ግድ የሚሉንና ለተለያዩ የሀገር ግንባታ አላማዎች ከመንግስትና ከተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚቀርቡልንን የትብብር ጥሪዎች መመለስም ቀላል ነው ተብሎ የሚታለፍ ሃላፊነት አይደለም፡፡

እያንዳንዳቸውን ዘርዝሮ ለማቅረብ የሚያዳግቱ እጅግ በርካታ ጥቃቅን የኑሮ ወጪዎችም ደረሰኛቸው በአንድ ላይ ሰብሰብ ብሎ ሲመጣ” መርከቧን ለማስጠም የሚገዳደር ማዕበል ይሆናል፡፡ እነዚህንና ሌሎች እዚህ ላይ ያልተጠቀሱ የእለት ተዕለት የህይወት ስንክሳሮችን ሁሉ ደፍኖ” ወደ ቀጣዩ ወር መሻገር የሚችል ትራፊ ገንዘብ አግኝቶ ወደ ቁጠባ ሂሳብ ውስጥ መጨመር መቻል እንደ ታላቅ ስኬት “ማታ ነው ድሌን” የሚያስጨፍር ነው፡፡

በርካታ ዳያስፖራዎች በቀን ለአስራ ስምንት ሰአታት ሠርተው የሚያገኙት ገንዘብ ከራሳቸው ፍጆታና ከወዳጅ ዘመድ እርዳታ ተርፎ” ለነገ እጅ እያጠራቸው የብድር ካርድ ሰለባ እንደሚሆኑት ሁሉ እኔም ተመሳሳይ ዕጣ ወድቆብኛል፡፡ እኔ ጋ ያለው ደግሞ የወሩን የመጀመሪያ ቀን ከቀጣዩ ወር የመጀመርያ ቀን ለማገናኘት የመረረ ትግልና እኔንም ሆነ የቤተሰቤን አባል መጥፎ አጋጣሚ ገጥሞት” ላልተጠበቀና ካቅም በላይ ለሆነ ወጪ እንዳልዳርግ ምህላ መያዝ ነው፡፡

ከዚህ በላይ ባነሳሁዋቸው የተለያዩ ጉዳዮች እኔም ሆንኩ ዳያስፖራዎች እጣችንና ፈተናችን ተመሳሳይ ነው፡፡ የምንለያየው ለመንግስት ከምናስገባው ገቢ ላይ ነው፡፡ ዳያስፖራዎች ካሉበት ሀገር እዚህ አገር ቤት ላሉት ዘመድ ወዳጆቻቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሪ ቀጥታ ገቢ የሚሆነው ለመንግስት ነው፡፡

መንግስት ግን የተላከለትን የውጪ ምንዛሬ ውጦ ጭጭ አይልም፡፡ የውጭ ምንዛሬውን ገንዘብ የብር ልኬታ አስልቶ ለተላከላቸው የዳያስፖራዎች ወዳጅ ዘመዶች ቆጥሮ ያስረክባል፡፡

የእኔ አስተዋጽኦ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ እዚሁ አገር ውስጥ ነዋሪ በመሆኔ” በየወሩ የምከፍለው የገቢ ግብር በቀጥታ ገቢ የሚሆነው ለራሱ ለመንግስት ብቻ ነው፡፡ የጥቂት እድለኛ ሠራተኞች ወይም በወዳጅ ዘመዶቻችን አጠራር “የፈረንጅ ዶላር ዛቂዎች” አባል በመሆኔ” በየወሩ የምከፍለው ግብር 577 ዶላር ያህል ነው፡፡ ከእኛ ሀገር ዳያስፖራዎች ይህን ያህል ዶላር በየወሩ የሚልክ ምን ያህሉ ይሆን?

ከአመታት በፊት ኮንዶሚኒየም ቤት ብመዘገብም የህልም እንጀራ እንደሆነብኝ ቀርቷል፡፡ አሳዛኙ ነገር እኔ እዚህ አገር ቤት ነዋሪ “ሎካል ዜጋ” በመሆኔ” የመንግስት የተለያዩ የዳያስፖራ ማትጊያ እድሎች አይመለከቱኝም፡፡ እየተጠናቀቀ ያለው አዲሱ የዳያስፖራ ፖሊሲም እነሱን እንጂ እኔን አይጨምርም፡፡

በእኔና በዳያስፖራዎች መካከል ሌሎች በርካታ ልዩነቶችም አሉን፡፡ ለምሳሌ ዳያስፖራዎች የኦሞ ድልድይ ባለመሠራቱ የተነሳ በስራቸው ላይ መጓተት ቢፈጠር” የቢሮክራሲውን የተወሳሠበ የስራ መጉዋተት  መቋቋም ቢያቅታቸው ወይም ደግሞ አለአግባብ ተወስዶብናል የሚሉትን የቤተሠቦቻቸውን መሬት ለማስመለስ እንዲረዳቸው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣኖች በራሳቸው ተነሳሽነት ሰብስበው በማነጋገር የመፍትሄ መመሪያ ይሠጡላቸዋል፡፡

እኔ ግን “ሎካል” ነኝ፡፡ እጣዬም እንደሌላው በሚሊዮን እንደሚቆጠረው “ሎካል ሲቲዝን” ነው፡፡ “ሎካሎች” ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ እያልን እንደምንተርተው” ሌላው ቀርቶ እኔው ራሴ ስፍር ቁጥር በሌለው ማመልከቻና የአካል ደጅ ጥናት ላመለከትኩት ችግሬ መፍትሄ የሚሠጠኝ የመንግስት አካል ብርቅዬ ከሆነብኝ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡

ዳያስፖራዎች ግን ችግሮቻቸውን ከመቅፅበት የሚፈታላቸው በህልማቸው የሚያዩት ሚኒስትር አላቸው፡፡ እኔ ዝርዝር ሳንቲሙን ሳይቀር ካላመጣህ “የመብራት ኪራይ ሂሳብ አልቀበልም” ብላ ባባረረችኝ የመብራት ሀይል ካሸር ምክንያት የተቆረጠብኝን የኤሌክትሪክ መብራት” ቅጣቱንም ጭምር ከፍዬ እንኩዋን በወቅቱ እንዲቀጠልልኝ ትዕዛዝ የሚሠጥልኝ አለቃ የማገኘው በስንት ደጅ ጥናት ነው፡፡

ዳያስፖራዎች በተለያዩ ከተሞች በነፃና በሊዝ የከተማ ቦታ ተሠጥቷቸው የመኖሪያ ቤት እንደሰሩና ከቀረጥ ነፃ የቤት መኪና ማስገባት እንደቻሉ ማንም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ለእኔ ለ“ሎካሉ” ይህ የማይደረስበት ሩቅ ህልም ነው፡፡ እንኳን መቶ ሀያና ሀምሳ ካሬ ሜትር ቦታ ላገኝ ቀርቶ መንግስት እኔው በከፈልኩት ታክስ ከሚገነባው ኮንዶሚኒየም እንኩዋን ተጠቃሚ መሆን አልቻልኩም፡፡

እኔ በየወሩ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለመንግስት ለራሱ በባንክ አማካኝነት እልክለታለሁ፡፡ ይህንን ለአንድ ወር እንኳ ባቋርጥበት በቅጣት በትሩ ከመዠለጥ የሚያስጥለኝ የለም፡፡ የእኔን ችግር  ለመስማትና መፍትሔ ለመስጠት የሚተጋ ባለስልጣን ግን የለም፡፡

ምክንያቱም “ሎካል” ነኝ፡፡ እዚሁ አገር ውስጥ ነዋሪ የሆንኩ “ሎካል ዜጋ” ስለሆንኩ እጣዬ የመንግስት የተዛባና ጨርሶ የተሳሳተ ፖሊሲና መመሪያ መሞከሪያ “ጊኒፒግ” እንደሆንኩ መቀጠል ብቻ ነው፡፡ ዳያስፖራዎች እጣ ፈንታቸው የጣፋቸው ለልዩ ጥቅምና አገልግሎት ነው፡፡ እንደ ዜግነቴ ከማንም ያላነሰ ግዴታዬን እየተወጣሁ እጣዬ የጣፈልኝ ግን የመንግስትን ስህተት እዳውን ያለ አበሳዬ እንዳወራርድ ነው፡፡ ምክንያቱም  እኔ “ሎካል ዜጋ” ነኝ፡፡

 

 

Read 2783 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 10:23