Sunday, 14 July 2024 17:14

አረንጓዴ አሻራ - ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያቀፈ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ሲተክሉ ነው ያገኘናቸው - የስሪላንካ አምባሳደር ቴሻንታ ኩማራሲሪ። ፍላጎታቸው ግን ችግኝ ለመትከል ብቻ አይደለም። “አረንጓዴ አሻራ እንዴት እየሄደ ነው? ምን ዐይነት ትምህርትና ልምድ እናገኝበታለን?” በማለት በቅርበት እንደሚከታተሉት ነግረውናል። አረንጓዴ አሻራ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲኖረው አድርጋችኋል፤ በርካታ አገራት ከኢትዮጵያ ልምድ እንደሚቀስሙ አምናለሁ ብለዋል - አምባሳደሩ።
አረንጓዴ አሻራ የሁላችንም ሥራ የሁላችንም አሻራ ነው በሚል የባለቤትነት መንፈስ ያነጋገረን ደግሞ አሸናፊ ወርቁ (አሸበል) ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ ነው የመጣነው፤ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ እየተከልን ነው ብሎናል። ሐሳባቸው ግን ከዚህም በላይ ነው። ዓመቱን ሙሉ የሚንከባከቡትና የሚያለሙት ቦታ እንዲኖር ይፈልጋሉ። እናም፣ ከመንግሥት የምንፈልገው “እዚህ ጋር ትከሉ ብሎ ቦታ እንዲሰጠን ብቻ ነው” ይላል - አሸበል።
አረንጓዴ አሻራ የፖለቲካ ሽታ እንደሌለውና ሊኖረው እንደማይገባ የገለጹልን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለስ ምን ይላሉ? አረንጓዴ አሻራ ከፖለቲካ በላይ እንደሆነ ሲገልጹ፣ ትውልድን የማኖር አገርን የማጽናት ጉዳይ ነው ብለዋል ጠቅላይ ጸሐፊው። አረንጓዴ ዕፅዋት የፈጣሪ ጸጋ ነው፤ ሀብትም ውበትም ነው። ሰዎች ጥበብ ጎድሏቸው አረንጓዴ ጸጋ አጥተዋል። እናም… ይህን ለመመለስና ትውልድን ለማዳን የሃይማኖት ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ ላይ አርአያነታቸውን እንደሚያሳዩ ተናግረዋል - ጠቅላይ ጸሐፊው።
አረንጓዴ አሻራ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያቅፋል። አረንጓዴ አሻራ ምግብም ውበትም ነው። ይሄ፣ የከንቲባ አዳነች አቤቤ አገላለጽ ነው። የከተማችን ነዋሪዎች የፆታ፣ የእድሜ፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው ሀገር በቀል ዛፎችን፣ የውበት ዕፅዋትን፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኞች በጋራ እየተከሉ እንደሆነ ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ታሪክ… ለዓለምም ለአገርም ነው። “አካባቢ ተራቆተ” እየተባለ በዓለም ዙሪያ ለበርካታ ዓመታት ተወርቷል። ዓለማቀፍ ስብሰባዎች በብዛት ተካሂደዋል። እልፍ የስምምነት ሰነዶች ተፈርመዋል። ነገር ግን፣ በጎ ለውጥ ሲያመጡ እንዳልታየ ጠ.ሚ. ዐብይ አህመድ ሲገልጹ፣ “በስብሰባ አይቀየርም፤ በሱፍ ለባሾች አይቀየርም” ብለዋል። ችግኝ የሚተክሉ እጆች ናቸው የችግር መፍትሔ የሚሆኑት። “ይህን ተግባር በመፈጸም ለዓለም ማስተማር ከኢትዮጵያ ይጠበቃል” ብለዋል - ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አረንጓዴ አሻራ፣ እንደ ስሙ ልምላሜ ነው - አብቦ የሚያፈራ። ባለፉት አምስት ዓመታት በቢሊዮን የሚቆጠሩ የፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል። አረንጓዴ አሻራ ፍሬያማ ነው። ግን ለዛሬ ብቻ አይደለም። ለትውልድ ይተርፋል። ለኑሮ ብቻ ሳይሆን ለታሪክም ነው። ከነስሙ “አሻራ” ተብሎ የለ!

 

ለዘመናት የተራቆተውን የአገር ገጽታ የሚቀይር፣ ኢትዮጵያን የሚያለመልም፣ ዘመን ተሻጋሪ ትልቅ የጥበብ ሥራ ስለሆነም፣ “ታሪካዊ” የሚል ማዕረግ አይበዛበትም።
እንደማንኛውም ትልቅ ቁምነገር፣ እንደማንኛውም ታሪካዊ ሥራ፣ አረንጓዴ አሻራ “አቃፊ” ባህርይ አለው።
የአረንጓዴ አሻራ ትርጉም፣ የተራቆተውን አገር የልምላሜ ግርማ ማጎናጸፍ ብቻ አይደለም። አዎ፣ አረንጓዴ አልብሶ ያስውባል። ሲታይ ያምራል። ነገር ግን፣ ጣዕምም ምቾትም ጭምር አለው። እንዴት ቢሉ…
ከውጭ አገር፣ ፍራፍሬ፣ የእንጨት ቁሳቁስና የሥጋ ምግቦችን እንደ ብርቅ ነገር ማስመጣት ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ አስቡት። የመራቆት ዕዳ እዚህ ድረስ ነው። የእንጨት ቁሳቁስ ለኢትዮጵያ ብርቅ መሆን ነበረበት? ፍራፍሬስ? ማርና ወተትስ? ብርቅ መሆን አልነበረበትም።
ኢትዮጵያ የፍራፍሬ አገር መሆን ነበረባት። መሆንም አለባት። ንቦች የሚቀስሙት አበባ፣ ላሞች የሚጥግቡበት ሳርና ሰብል፣ ለእንስሳት ሁሉ ተስማሚ መኖ እንደ ልብ የምታበቅል ለምለም አገር መሆን አለባት። በሙያተኞች ታሪክ የምትጠቀስ ኢትዮጵያን የመሰለች የጥበብ አገር፣ የእንጨት ቁሳቁስን ብርቅ ሊሆንባት፣ ተቸግራ ከውጭ አገራት ልታስመጣ አይገባም ነበር። ይሄ የዝቅታ ታሪክ መቀየር አለበት - በአረንጓዴ አሻራ።
ይህም ብቻ አይደለም። ተራራውና ሸለቆው ዛፎች ሲበቅሉበትና አረንጓዴ ሲለብስ፣ ለም አፈር እየተሸረሸረ ተቦረቦረ የኢትዮጵያ መሬት አይራቆትም። በደለል ብዛት ሐይቆችና ግድቦች ውኃ አይሸሻቸውም።
አረንጓዴ አሻራ፣ አገርን ልምላሜ ከማልበስ ባሻገር፣ የማርና የወተት ጉዳይም ነው። የፍራፍሬና የሥጋ፣ የእንጨት ሙያንና የኤሌክትሪክ ብርሃንን ሁሉ ያቅፋል - አረንጓዴ አሻራ።
“ሀብትም ውበትም ነው” የተባለው አለምክንያት አይደለም። ሲያዩት ያምራል። መዓዛው ይማርካል። ግን ደግሞ የኑሮ ጣዕምም ነው። ሲቀምሱት ሲገምጡት ይጣፍጣል። ሲመገቡት ያጠግባል። “ለምግብነትም ለውበትም” በማለት ይገልጹታል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
በአገር ደረጃ እንደታየው በአዲስ አበባም የተተከሉ ችግኞችም ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። በመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ 41 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።
ዓምና 17.5 ሚሊዮን ችግኞች።
ዘንድሮ ደግሞ 20 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከት የዓመቱ አረንጓዴ አሻራ ባለፈው ቅዳሜ “ሀ” ተብሎ ተጀምሯል።
ገሚሶቹ የአትክልትና የፍራፍሬ ችግኞች ናቸው። ገሚሶቹ አገር በቀል የደን ዛፎች ናቸው። ገሚሶቹ ደግሞ የውበት ዕፅዋት። አረንጓዴ አሻራ ሁሉንም ያቀፈ አገራዊ ፕሮጀክት ነው - የሀብትና የውበት ፕሮጀክት። ለኑሮም ለመንፈስም ነው።
ይህም ብቻ አይደለም። በልዩነቶች የታጠረ አይደለም። ሁሉንም የሚያቅፍ እንጂ።
የእገሌ ፓርቲ ችግኝ… የእከሌ ፓርቲ ችግኝ የሚል ልዩነት የለም። ችግኞች የፖርቲ አርማ ለብሰው አይጸድቁም። የዚህኛውም የዚያኛውም ችግኞች በአረንጓዴ ልምላሜያቸው አገርን ያሳምራሉ። አብበው ያፈራሉ።
በጾታ፣ በብሔር፣ በሃይማኖት ልዩነቶች የተገደበ አይደለም። አንተ፣ እሷ፣ እኔ … ሁላችንም የምንተክላቸው ችግኞች በሙሉ፣ “አረንጓዴ አሻራ” ናቸው።
ያለ ልዩነት ሁሉን የሚያሰባስቡና የሚያቀራርቡ፣ እንደ አረንጓዴ አሻራ የመሳሰሉ “አቃፊ” ቁምነገሮችና ሥራዎች እንዲበዙልን አትመኙም? ካሰብንበትና ከተጋንበት ደግሞ፣ ምኞት ብቻ ሆኖ አይቀርም። አይከብደንም። ከአረንጓዴ አሻራ ጥሩ ልምድ አግኝተንበታልና።
የአረንጓዴ አሻራ የበረከት ምሥጢር ብዙ ነው።
ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በዓለም ዙሪያ “የአካባቢ መራቆጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥና የዓለም ሙቀት”… እየተባለ በብዙ ስብሰባዎች ብዙ ተወርቷል። እልፍ መግለጫዎች ከግራ ቀኝ እየተቀባበሉ ይስተጋባሉ። የተፈረሙ የስምምነት ውሎችና ሰነዶችም ለቁጥር ያስቸግራሉ።
ኢትዮጵያ የዓለማችን አካል፣ ለዚያውም ከትልልቅ አገሮች መካከል አንዷ ናትና፣ ይሄ ሁሉ ኢትዮጵያን ይመለከታል። ጉዳይዋ ነው። ነገር ግን፣ ኢትዮጵያ ራሷን የቻለች ኩሩ ታሪካዊ አገርም ናት። ከአገራት ጋር የምትተባበር፣ ትምህርት የምትለዋወጥ ብትሆንም፣ በየአህጉሩና በየአገሩ የሚስተጋቡ አጀንዳዎችን በደረቁ ሊያጎርሷት ሊግቷት ቢሞክሩ፣ እሺ አትልም። በደመነፍስ “ኮፒ” እያደረገች፣ በጭፍን አትከተልም። ተነጂ አትሆንም።
ፍሬና ገለባውን ለይታ፣ የሚሆነውንና የሚበጃትን ለክታ፣ የራሷን መንገድ እየቀየሰች ትጓዛለች። ለአገርና ለሕዝብ፣ ለኑሮና ለታሪክ ትርጉም ባለው መንገድ እያገናዘበች የራሷን ቁምነገር ልብ ትላለች። የራሷን አጀንዳ ትቀርጻለች።
በርካታ አገራት “የአካባቢ መራቆትን እንከላከላለን” በማለት ኢኮኖሚያቸውን ሲያቃውሱ አይተናል። ኢትዮጵያ ግን፣ ኢኮኖሚን የማሳደግና ኑሮን የማሻሻል ራዕይን ጭምር የሚያቅፍ አረንጓዴ አሻራዋን ለዓለም እያሳየች ነው። እንዲህ ዐይነት “ዐቃፊ” የጥበብ ትጋትም ነው፤ ለሌሎች ጥሩ ትምህርትና ልምድ የሚወጣው።
የባለቤትነት መንፈስ መፍጠርስ?
ቀሲስ ታጋይ እንደሚሉት፣ የሃይማኖት ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ መልካም አርአያነትን የማሳየት ኀላፊነት አለብን ብለው በጋራ ወስነዋል። በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ችግኞችን በብዛት ለመትከልና ለማልማት ቃል ገብተው፣ በተግባር እያሳዩ እንደሆነም ተነግሯል።
የስሪላንካው አምባሳደር በበኩላቸው፣ አረንጓዴ አሻራ በትልልቅ ቁጥሮች ተዘርዝረው የሚቀርቡ ብዙ ስኬቶችን የማስመዝገቡ ያህል፣ በቁጥር የማይገለጹ ስኬቶችንም አስገኝቷል ብለዋል። በአረንጓዴ አሻራ ውስጥ ብዙ ወጣቶችና ታዳጊ ልጆች ሲሳተፉ አይቻለሁ። ይህም የአዲሱን ትውልድ መንፈስ የሚያነሳሳና የሚያነቃቃ ነው ብለዋል - አምባሳደሩ። አረንጓዴ አሻራን በባለቤትነት ይዞ የሚያሳድግ ትውልድ ተፈጥሯል ማለት ነው።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ ባልደረቦቹ ጋር በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ከመትከል ባሻገር፣ በባለቤትነት መንፈስ የሚያለሙት ፓርክ ላይም ችግኞችን እየተከልን እንንከባከባለን ሲል ነግሮናል። በባለቤትነት መንፈስ እየሠሩ ያስመዘገቡት ውጤት ታይቶም እንደሽልማት ሌላ የሚለማ ቦታ በአዲስ አበባ መስተዳደር እንደተፈቀደላቸው አሼበል ይገልጻል። በእርግጥ ቦታውን ገና አልተረከቡም። እናም ከመንግሥት የምትፈልጉት ድጋፍ ምን እንደሆነ ስንጠይቀው፣ “እዚህ ችግኝ ትከሉ ብሎ ቦታ እንዲሰጠን ብቻ ነው የምንፈልገው” በማለት መልሶልናል።
አረንጓዴ አሻራ የዚህን ያህል ነው ኢትዮጵያውያንን በሰፊው ማቀፍ የቻለው። ኢትዮጵያውያንም አረንጓዴ አሻራን የራሳቸው አድርገው አቅፈውታል።

Read 1302 times