Monday, 15 July 2024 19:54

ዕውቁ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ የተዘከረበት መርሃ ግብር ተካሄደ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አብሮ አደግ በፍቅር የመረዳጃ ማሕበር ያዘጋጀው የዕውቁ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ የተዘከረበት መርሃ ግብር ዛሬ በተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል። በዚህ መርሃ ግብር የገነነ ስራዎች እና ሕይወት በዝርዝር መዘከሩ ተነግሯል።

መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የማሕበሩ ሰብሳቢ አቶ ቤዛው ሹምዬ ማሕበሩ ባለፉት አስር ዓመታት ስላደረጋቸው ዕንቅስቃሴ አትተዋል። አክለውም "ያለፉትን በመዘከር፣ የሰሩትን በማክበር ተተኪዎችን እንፍጠር!" በሚል መሪ ቃል ስለተዘጋጀው ይህ መርሃ ግብር በዝርዝር አብራርተዋል።

የገነነ መኩሪያ የሕይወት ታሪክ በንባብ የቀረበ ሲሆን፣ በሕይወት ዘመኑ ያበረከታቸው የተለያዩ ስራዎች በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ ተዘክረዋል። ከገነነ መኩሪያ "ኢሕአፓ እና ስፖርት" መጽሐፍ የተቀነጨበ ስራ ለዕድምተኞች በትረካ ቀርቧል።

በተጨማሪም፣ ለቀድሞ የእግርኳስ ተጨዋቾች ተካ ገለታ፣ ግርማ አበበ፣ እና ጌቱ መልካ፤ ለቀድሞ ቦክሰኛ ደረጀ ደሱ እና ለድምጻውያኑ ጎሳዬ ተስፋዬ እና አብዱ ኪያር፣ ለሁለገቡ የኪነ ጥበብ ሰው ዳዊት አፈወርቅ፣ ለተዋናይ ተሰማ ገለቱ፣ ለኬሮግራፈር ዳንኤል ደሳለኝ፣ ለጋዜጠኛ እንግዱ ወልዴ እና ለሕግ ባለሞያዋ ሰናይት ፍስሐ (ፕ/ር) ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ እና የገነነ መኩሪያ ባለቤት ወይዘሮ አስቴር አየለ ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመርሃ ግብሩ ላይ ታድመዋል።

አብሮ አደግ በፍቅር የመረዳጃ ማሕበር የተመሰረተበትን አስረኛ ዓመት በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ተከብሯል።

Read 1088 times