“ይሄ ጦርነት ምን ያላደረገን አለ ብለህ ነው”
በብዙ መንገድ መለስ ቀለስ ያልኩባት ክልል ትግራይ ናት። ሆኖም ከጦርነቱ በኋላ ሄጄ አላውቅም። ጦርነቱ ሊጀመር አካባቢ የህወሃትና የፌደራሉ ሰዎች ድንበር ለይተው ከመቀሌና አዲስ አበባ የነገር ጦር ሲወራወሩ አንዴ ሄጃለሁ። እንደውም ያኔ የሰላም ሚኒስትሯ (ያሁኗ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል) እንባ ያፈሰሱ ጊዜ... እዛው አዳራሽ ውስጥ ነበርኩ።
ከብዙ ጊዜ በኋላ አለቆቼ ለስራ ሊልኩኝ ሻንጣህን ሸክፍ ሲሉኝ ደስ አለኝ። ግራም ገባኝ። ትግራይ እንዴት ሆና አገኛት ይሆን? “እንደሰሙት አይሆን” ይባል የለ? ስለ ትግራይ ደጋግሜ ጠይቄ ደጋግሜ ሰምቻለሁ። ያገኘኋቸው ነጥቦች ሲገጣጠሙ ወጥ ስእል ሊሰጡኝ አልቻሉም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀሌን በሻሻ አድርገናታል ይላሉ። ከሰላሙ በኋላ ደርሰው የመጡት ትግራዋዮችም፤ መቀሌ ፈርሳለች ይላሉ። እላዩ ላይ ‘መንግሥት አፈራረሰን’ የሚል መብከንከን ይጨምሩበታል። NGO የሚሰሩትም ወዳጆቼ መቀሌን አይተው ሲመጡ ከሶርያ ብሳ የፈራረሰች፣ እንደ ሊብያ የወደመች ያስመስሏታል። አንድ ሁለት መቀሌን ያዩ ወዳጆቼ ደግሞ እንደነበረችው ናት፤ ጉዳቱ ትንሽ ነው ይላሉ።
በየሚዲያው የሚታይና የሚነገረውም ከዚህ የተለየ አልሆን ብሎኝ ነው የከረመው። ብቻ ነጥቦቹ ሲገጣጠሙ ግልፅ ስእል የለኝም። አውሮፕላን ሆድ ውስጥም ሆኜ የማስበው አንድ ነገር ነበር፤ የትግራይ ሰው እንዴት ነው? አውሮፕላኑ ሽረ አውርዶ ሲያራግፈን፣ ትንሽ ጥቁር የለበሱ ትግራዋዮች አብረውን ተሳፍረው እንደነበር አስተዋልኩ። ሀዘን ፊታቸው ላይ አለ። የተወሰኑት ከጦርነቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከውጪ ሀገር የገቡ መሆናቸውን ከንግግራቸውም ከዘያቸውም ተረዳሁ። በርግጠኝነት እርማቸውን ሊያወጡ ነው።
ደግሞ ጥበብ ለብሰው በሽፎን ደምቀው የተንቆጠቆጡም አሉ። (ቆይቶ እንደተረዳሁት፤ በመላ ትግራይ ለሦስት አመት ሰርግ አልነበረም። የቀደመውን ሁሉ ሰብስባ ትግራይ ልጇቿን የምትድርበት ሰሞን ላይ ናት።) ወደ አክሱም የሚወስደኝ መኪና ውጪ እየጠበቀኝ ነው። ሽረን ትንሽ እንዲያሳየኝ ጠየኩትና ጉዞ ቀጠልን። ሽረን አንድ ሁለቴ መጥቼባታለሁ። እኔ ስሄድ ገጥሞኝ ይሁን አይሁን አላውቅም እንጂ ሩጫ የበዛባት ከተማ ናት። ጥድፊያ የሞላባት። እንደውም “በዚህ ከተማ ቆሞ ያለው የሀየሎም ሀውልት ብቻ ነው።” የሚል ትዝብቴን ፅፌ እንደነበር አስታውሳለሁ። ሽረ እንደደመቀች ናት። ልጆቿ ከግራ ወደ ቀኝ አሁንም ይዋከባሉ። አንዱን አንስተው፣ አንዱን ይጥላሉ። ይሮጣሉ።
በዚህ ሰሞን እያነበብኩት የነበረው የያየሰው ሽመልስ ‘የደም እርካብ የሴራ መንበር’ መፅሐፍ ላይ ከአንድ ቀን በፊት በሽረ ስለፈረሱ ሆቴሎችና የግለሰብ ቤቶች እያነበብኩ ነበር። አንዱ ደጀና ሆቴል ነው። እንደ ያየሰው ትረካ፤ ይህ ሆቴል የፈረሰው በባለቤቱና በአንድ ጀነራል የግል ፀብ ምክንያት በመድፍ ተደብድቦ ነው። መፅሐፉ ላይ ያየሰው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መድፈኞች፣ ሆቴሉን ከሀምሳ ሜትር ርቀት ላይ ሆነው ደጋግመው እንደሳቱት ሲያስነብብ ስቄ ነበር። (ያዬ መከላከያውን ለማጣጣል የሄደችበት ርቀት አንዳንድ ቦታ ላይ አስበልቷታል። እንኳን ስለ መድፍ የሚያውቅ መድፈኛ ይቅርና፣ እኔ እንዲህ ተኩስ ቢሉኝ ከሀምሳ ሜትር ላይ አልስተውም እኮ... መሬትን በድንጋይ እንደ መሳት ነው።) ሆቴሉ ግን በመድፍ መመታቱን ከሁለት ሰዎች ሰምቻለሁ። ሆቴሉ አሁንም የተሰባበሩ መስታወቶች አሉት። ቢሆንም በመጠኑ ታድሶ ወደ ስራ ገብቷል። ገባር ሽረ የተባለው ሆቴል ደግሞ ገና እድሳቱ አልቆ ወደ ስራ አልገባም። አፍሪካ ሆቴል ግን ይበልጥ አምሮበታል።
ጉዟችን ቀጥሏል። መኪናውን የሚዘውረው ሰው ስለ ጦርነቱ ጊዜ እያወራኝ ነበር። አስከፊ ጊዜ እንዳሳለፈ ሁለመናው ይናገራል። ያንን ጊዜ እንዲያስታውስ መወትወቴ የስሜት ጭካኔ እንደሆነ ቢገባኝም፣ መስማት ፈልጌያለሁና ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ ቀጠልኩ። የሹፌራችንን ስም አስገዶም ብለን እንያዘው። (እውነተኛ ስሙ ይቅር) ስለ መዝመት አለመዝመቱ ሊነግረኝ አልፈለገም። በጦርነቱ ወቅት አክሱም ነበር። ከሁሉም በላይ የሻቢያን ስም ደጋግሞ ያነሳል። “ሰዎች አይደሉም እነሱ... ማንም እንደነሱ ሊከፋ አይችልም። እንዴት ሰው የሰባ አመት አዛውንት በጥይት ደብድቦ ይገድላል? እንዴት ሰው ጡት ያልጠገበ ህፃን ላይ ይተኩሳል?... ተወኝ ባክህ እነዚህ አውሬ ናቸው!”
ንግግሩ ውስጥ ምሬት አለ። እያወራ ትካዜውንና ሀዘኑን መሪውን መታ እያደረገ ያስተነፍሳል። ፊቱ ላይ ያጠላው የሀዘን ድባብ አልተገፈፈም። ጥልቅ ሀዘን፣ የከፋ ምሬት...
አክሱም ውስጥ በአንድ ጀምበር ተገደሉ ስለተባሉት ሰዎች ሲነግረኝ፣ ከ1200 በላይ ናቸው አለኝ። አስቀድሜ የሰማሁት 800 የሚል ነው፤ 400 ከየት መጣ? ወደ አክሱም እየሄድን ገደላ ገደሉን ሳይቀር ማጤን ጀመርኩ። ከራሴም ጋር እያወጋሁ ነው። መረጃ እየሰበሰብኩ ያለሁት በተዘበራረቀ መልኩ መሆኑ ገባኝ። ቆይ ማወቅ የምፈልገው ምንድነው? ብዬ ራሴን ጠየቅሁ። የጦርነቱ ጊዜ ላይ የነበረው ህይወት፤ ከዘመቱትም ካልዘመቱትም! አሁን ያለውን ሁኔታ? ኢኮኖሚያዊውንም ስነልቦናዊውንም ጉዳይ…
ቀጠልኩ። አሽከርካሪያችን ትካዜ ውስጥ እንደገባ ስለገባኝ ሌላ ጨዋታ አስጀመርኩት። እሱም ጨዋታ አዋቂ ነውና የሀዘኑን ድባብ በሳቅ አባረርነው። ዱራ የምትባል ስፍራ ደረስንና የተጠበሰ በቆሎ እሸት ገዛን። ይጣፍጣል። አካባቢውም ለም ነው። በአካባቢው ዱራ የሚባል ግድብም እንዳለ ሰማን። መኪናውን ሲያቆም ከተሰበሰቡት ህፃናት አስገዶም በቆሎ ገዛ። ለረበሽኩት ስሜቱ ካሳ የበቆሎውን ከፈልኩና ቀጠልን።አክሱም ገብተን ኢትዮጲስ ሆቴል እንዳረፍን፣ በዋናነት ስለሄድኩበት ጉዳይ የሚያወሩኝን ሰዎች አገኘሁ። ስለ ነገ ስራ አጭር ወሬ ብቻ አወራንና በፍጥነት ወደ ጦርነቱ ወሬ ወሰድኳቸው። የእነዚህንም ስም እንቀይረውና ታደሰና ሀጎስ እንበላቸው። (ሀጎስ ከአክሱም ያመጣንን አሽከርካሪ አስገዶምን ተክቶ አብሮን የሚቆይ አዲሱ ወዳጃችን ነው።)
ብዙ አውግተን ለነገም ቀጠሮ ይዘን ስንሰናበት የነገሩኝ ሁሉ ውስጤ ቀርቶ ሀዘን አጥልቶብኝ ነበር። ሰው ስንቱን ይሸከማል? የማይችለው የመከራ አይነት የቱ ነው? ይሄንን እያሰብኩ ወደ ከተማ ወጣን። ፅዮንን ተሳለምን፤ ሀውልቱን አየን። በአክሱም ያልተጎናበሰና እንደነበር ያለው ይህ የአክሱም ሀውልት ብቻ መሆኑን ያወኩት አክሱምን ለቅቄ ከወጣሁ በኋላ ነው። ፅዮን ስር ተንበርክኮ ወደተነሳው ሁሉ እጃቸውን ለምጽዋት የሚዘረጉ ብዙ ናቸው፡፡ አዛውንቶች ይበረክታሉ፡፡ ልጆቻቸውን በጦርነቱ ያጡ ወይንም ቆስለውባቸው የሚጦሩ መሆናቸውን ገምቼ ነበር፡፡ በቀጣዩ ቀን አክሱም ዙርያ ያገኘኋቸው አዛውንቶችም ያንን አረጋገጡልኝ፡፡
የአክሱማውያኑን አሁናዊ ስሜት የሚገልፀው የቅዱስ ያሬድ ሀውልት ይመስለኛል። የዜማ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በአክሱም መታሰቢያ ሀውልት የቆመለት እኔ ከመሄዴ ከቀናት በፊት እንደነበር በዜና አይቻለሁ። የአክሱም ሀውልትን ፈልፍለው ከገቦድራ ተራራ ስር አሁን የቆመበት ስፍራ ድረስ ያመጡ እጆች፤ አሻራቸው ቅዱሱ ሀውልት ላይ የለም። በወግ ፅናፅን መያዝ ያቃተው የግእዝ፣ እዝልና አራራዩ አባት፤ አክሱም ላይ የቆመበት ሁኔታ የወቅቱን ባታች ስሜት ከመግለፅ የዘለለ ፋይዳው ምን ይሆን?
ወደ ሆቴል ከመሄዴ በፊት ስለ ጦርነቱ እያሰብኩ ነበር። ጦርነቱን በጣም በርቀትና ትንሽ ቀረብ ብዬ አይቼዋለሁ። ጥይት ባናቴ አልጮኸም። ጀትና ድሮን አላንዣበበብኝም ነበር። ግን አንድ ሁለት ቀን አልቅሻለሁ። (‘ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅሰው’ የሚለውን የፀጋዬን መፈክር ነገር ትቼ፣ ወዳጄ ፊት አልቅሼ እረጅም ጊዜ ሀፍረት ይሰማኝ ነበር፡፡) በዚህ የማያቸው የማገኛቸው ሁሉ ግን ያ ጦርነት አድቅቋቸዋል። ክልሌን ላድን ብለውም፣ ከአንድ ቤተሰብ አንድ ሰው አዋጡ ተብለውም፣ የፖለቲከኞቹ ፕሮፓጋንዳ አስምጧቸውም፣ ተስፋ ቆርጠውም፣ ስራ አጥ ስለነበሩም... በርሀ የወረዱትም በቤታቸው የነበሩትም እኩል ደቀዋል። ክፍሌ ገብቼ ስቀመጥ አስገዶም ያለኝን እያስታወስኩ ነበር። በቆሎ ልንገዛ ዱራ ጋ ስንቆሞ በቆሎ ይዘው ግዙን ያሉንን ህፃናት እያሳየኝ፤ “እነዚህን የሚያካክሉት ሳይቀሩ እኮ በርሀ ወርደዋል። ጥይት ጮኾባቸዋል። ምናልባትም ተደፍረዋል። አሁን ከዚህ በኋላ ተምረው ሰው ይሆናሉ?”
ከተሰበሰቡት ውስጥ ትልቅ የምትባለው በጣም አጋንኜ ብገምታት 15 ቢሆናት ነው።
ደጋግሜ እንደሰማሁት፣ ወደ በርሃ ውርደው የነበሩ የትግራይ ልጆች ከተመለሱ በኋላ መማር አስጠልቷቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ከተማ ከተማውን ናቸው፤ የቀናቸው ከሃገር ወጥተዋል፤ እየወጡም ነው፡፡ የቀሩት አካላቸው ጎድሎ በቤታቸውና በካምፕ ውስጥ ናቸው፡፡ በከፍተኛ የድብርት ስሜት ውስጥ ሆነው አእምሯቸውን ወሰድ የሚያደርጋቸውም በየቤቱ አሉ፡፡ መተኛትም መቀመጥም አልቻልኩም። ወጣሁ። ቢራ ፍለጋ። ወጥሮ የያዘኝን ስሜት በቀዝቃዛ ሀበሻ ላበርደው።
ታደሰና ሀጎስ በጠዋት ሆቴል ድረስ መጥተው እየጠበቁኝ ነበር። አጭር ሰላምታ ተለዋወጥንና ጉዞ ጀመርን። የዛሬ ውሏችን ገጠር ይወስደናልና አጭር ጉዞ አለን። ጀመርነው፡፡ ‘በቅርቡ ስራ ይጀምራል ተብሏል’ አለኝ ታደሰ፤ የአክሱምን አየር ማረፊያ እያሳየኝ። ‘ለነገ ሳይሉ እኮ ነው ያፈረሱት... አየህ ጦርነት ላይ ነገን አታስብም። ዛሬ መትረፍህን ብቻ ነው የምታስበው።’ ታደሰ ቀጠለ።
የአክሱም አየር ማረፊያን አሻግሬ ተመለከትኩ። በዙሪያው ያሉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ላይ የነበሩ የሶላር ሀይል መሰብሰቢያዎች ተነቅለው መወሰዳቸውን ሰምቼ ነበርና አይኔ ፈለጋቸው። ሁሉም ምሰሶዎች ወድቀው ሶላሮቹ ተወስደዋል። ምናልባት ጥቂት ቀናትን በበርሀ አብርተው ይሆናል። ምናልባትም በዲሽቃና መድፍ፤ በጄትና ድሮንም ነደው ይሆናል። በአየር ማረፊያው ዙሪያ አንዳንድ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች እንደወደቁ ናቸው።
‘ማነው ያፈረሰው?’ አልኳቸው
‘ሁለቱም... በተለይ እነዚህኞቹ’ (እነዚህኞቹ ያለው የትግራይ ሀይሎችን ነው።)
‘ለምን?’
‘አየር ከዚህ እየተነሳ እንዳያጠቃቸው ነዋ!’
ትንሽ እንደተጓዝን አርሶ አደሮች ተሰብስበው አየን። እኛን ነው የሚጠብቁት። የእለቱ ስራዬ ከእነሱ ጋር ነበርና ወደ ስራ ገባሁ። በስራዬ መሀል ስለ ጦርነቱ አወራቸዋለሁ። እንዴት እንደነበሩ እጠይቃለሁ። እመለከታቸዋለሁ። እለቱ የኪዳነ ምህረት እለት ስለሆነ እርሻ እንደማይኖር ሰምቼ ነበር። አንድ ሁለት ሰዎች እያረሱ አየሁ። የትግራይ አርሶ አደሮች እርፍ አያያዝ ከለመድኩት የተለየ ስለሆነ ሁሌ ይገርመኛል። ቀጥ ብሎ እስከ ብብታቸው የሚደርሰውን እርፍ፣ ከታች ወደ ላይ ይዘው ነው የሚያርሱት። ሁለቱም እንደዚህ ነበርና የሚያርሱት ገርሞኝ አየኋቸው። አንዱ ሰዉዬ በጣም ደካማ ሽማግሌ ናቸው። እድሜ እስኪበቃው ደቁሷቸዋል። አንድ ሁለት ዙር ደርሰው ከመጡ በኋላ ለአንድ ገና እየበቀለ ላለ ወጣት እርፉን ይሰጡታል። ትንሽ ይውተረተርና የደከመው ሲመስላቸው ይቀበሉትና ያሳርፉታል። እድሜ ብቻ ሳይሆን ሀዘንም በወግ ደቁሷቸዋል። እየፈራሁ ጠጋ አልኳቸው። የእሳቸው ሀዘን ስላስፈራኝ ልጁን አወራሁት።
“እንዴት ነው እርሻ በወጣትነት?”
አማርኛ አይችልም። ይሄንን ሰላምታ ስንለዋወጥ ተረድቻለሁ። ግን ይሰማኛል። ታደሰ ደግሞ እሱ የሚለውን ይነግረኛል።
“ትምህርት እንደሆነ ትተናል ... ምን እንሰራለን ሌላ!”
ከ16 አመት አይበልጥም። ቢበዛ 9 ወይ 10ኛ ክፍል ቢሆን ነው። እና ለምን አቋረጠ? አባቱን ዞሬ አየኋቸው። አባቱ ጠጋ ብለው አወሩኝ። ያሉኝን አሳጥሬ ልተርከው።
“መከላከያ አካባቢውን ሲይዝ አሁን የሚያርሱትን አካባቢ መጠነኛ ካምፕ አደረገ። ልጆቻቸውን ብቅ እንዳይሉ አደረጉና እሳቸው ብቻ ወጣ ገባ እያሉ፣ ልጆቻቸውን መጠበቅ ሆነ ስራቸው። እንደሰሙት አልሆነም። መከላከያው ምናቸውንም አልነካ። ቦታውን እንጂ እነሱን አልፈለገም። ልጆቻችሁን አውጡ አላላቸውም። ይሄንን አምጡ፤ ይሄንን እረዱ አልተባሉም...ልጆቹም ብቅ ማለት ጀመሩ። ብዙ ሳይቆዩ የትግራይ ሀይሎች ቦታውን መልሰው ተቆጣጠሩ። ተዋጊዎቹ በዚህ መንገድ ሲያልፉ ተርበው ነበር። የሰው እጥረትም ነበረባቸው። ትልቁ ልጃቸውን ተከተለን አሉ። አልከተልም ማለት አይቻልም። ተከተላቸው።
አባት እያለቀሱ ልጃቸውን ሸኙ። ምናልባት ያለቀሱት ታይቷቸው ሳይሆን አይቀርም። አልተመለሰም። እናም ይሄ ልጅ ታላቅ ወንድሙን ተክቶ ነው እርፍ የጨበጠው። በራሴ የስሜት ጭካኔ እያዘንኩ ወደ መኪና ገባሁ። አክሱም አላድርም። ወደ መቀሌ እጓዛለሁና ቶሎ መውጣት አለብኝ።
“እርቦኛል፤ ምግብ ወዳለበት ውሰዱኝ” አልኩ መኪና ውስጥ እንደገባሁ፡፡
ሀጎስ ከመኪናው ኪስ ጣፋጭ ዳቦ አውጥቶ ሰጠኝ። ውሀም አቀበለኝ። ቢርበኝም የትግራይ ጣፋጭ ሽሮ እንጂ ዳቦ መመገብ አልፈለኩም። ስኳር የበዛበት ነገር መመገብም ቀንሻለሁ። አልበላም ብለው ደግሞ ውለታውን መግፋት ሆነብኝ። ክፉ ይሉኝታ አለብኝ።
“ታጥቀህ ነውና እምትዞረው በል” አልኩት
“እረሀብ የመቋቋም አቅሜ ቀንሷል... እና ቶሎ ቶሎ ትንሽ ትንሽ ነው የምበላው”
“ስኳር አለብህ?” (ስኳር ያስርባል ሲባል ስለምሰማ ነው እንጂ፣ ሳይንሱ ምን እንደሚል አላውቅም፡፡)
“ኧረ የለብኝም... ግን ያኔ ሦስት ቀን አራት ቀን ሳልበላ ነበር የምቆየው። ደሞ አይቼው የማላውቀውን እንኳ ታሽጎ የሚመጣ አረቄ በየቀኑ እጠጣ ነበር። እሱ ነው የጎዳኝ። አሁን አሁን እርሀብ አልችልም... ይሄ ጦርነት ምን ያላደረገን አለ ብለህ ነው።”
በዛ ቀውጢ ዘመን ወደ ትግራይ ማካሮኒና ፓስታ ማስገቢያ ቀዳዳ አልነበረም፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች በሰው በሰው እየታገዙ ከአላማጣ ያመጡ ነበር፡፡ ለመግዛት ግን ዋጋው ውድ ነበር፡፡ ስሰማው የገረመኝ ለማካሮኒና ፓስታ የጠፋው መግቢያ ቀዳዳ፣ ለአንድ በፕላስቲክ ጠርሙስ ታሽጎ ለሚቀርብ አረቄ ግን ሰፊ ነበር፡፡ በዚህም ብዙዎች የረሀብ ጊዜን አሳልፈዋል፡፡ በረሃባቸው ላይ ደግሞ ይሄን መጠጥ ይጠጡ ነበር፡፡
ሀጎስ ሁሌም አቆላምጦ ነው የሚጠራኝ። የሚያቆላምጠኝ ከሙሉ ስሜ በኋላ ‘ዬ’ን እየጨመረ ነው። ሲያቆላምጠኝ ገጠር ያሉት ዘመዶቼ እንደሚያቆላምጡኝ ነው። ደስ ይላል። ወዳጅነትን የሚያጠናክር አጠራር አለው።
ያነጋገርኳቸው ሁሉ ከሻቢያ ቀጥለው የሚፈሩት እረሃብን ነው፡፡ በጦርቱ ወቅት ያልተራበ ትግራዋይ ያለ አይመስለኝም፡፡ በተለይ ህፃናት እረሃብ መቋቋም እያቃታቸው ይወድቁ ነበር፡፡ በዚህ መሃል ብዙ አትርፈው እንሽጥ ያሉ ነጋዴዎችም ነበሩ፡፡ አሁን ቂም ሳይያዝባቸው አልቀረም፡፡ ወደ መቀሌ ከመጓዛችን በፊት ጠላ ቤት ውሰዱኝ አልኩ። መጀመሪያ አክሱም የሄድኩት ከ8 አመት በፊት ነበር። ያኔ ጥሩ ጠላ ጠጥቼ ነበርና ሁሌም አክሱም ስሄድ ጠላ ቤት እሄዳለሁ። ዮሀንስ የሚባል ሰው ተቀላቀለንና ሄድን። ዮሃንስ በግሌ የፈረንጅ የምለውን አይነት አለባበስ ነው የለበሰው፡፡ ጠንካራ ሰፊ ጂንስ ሱሪ፣ ወፈር ያለ ሸሚዝ (ሱሪው ውስጥ ጠቅጥቆታል) ጠንካራ ጫማ፡፡ ልብሱ ለቀለም ቅንብሩ ሳይሆን ለጥንካሬው የተመረጠ ይመስላል፡፡ በዚህ ላይ ተለቅ ያለ ቦርሳ አዝሏል፡፡
መንደር ውስጥ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ በረንዳ ላይ ተቀምጠን ጠላ አዘዝን፡፡ ጠላ አዝዘን በባዶ ሆዳችን እንዳንሆን ሴትዮዋ እንጀራ በበርበሬ አቀረቡልን። በደንብ የበላሁ ቢሆንም እንጀራ በበርበሬውን ተያያዝኩት። በርበሬው ያቃጥላል። ሲያቃጥል ያስጠጣል። የይሁዳ አንበሳ ባለበት መጠጫ ተያያዝነው።
ዮሀንስ ከእነ ጥንካሬው ይመስላል። ኩስትር ቁጥር ያለ ፊት ነው ያለው። ንግግሩም ቀጥተኛ ይመስላል። በጦርነቱ ወቅት አንድ ወሎዬ ጓደኛው 21ሺህ ብር ልኮለት ትንሽ ቀን እንደገፋ ነገረኝ። ከዛ ውጪ ግን ደጋግሞ ስለ ረሀብ አስከፊነት አወራኝ። ብዙ የተራቡ ሰዎችን አይቷል። እሱም ጋ እረሀብ ሲመጣ አሰቃቂ ቀን አሳልፎ ነበር። እንዲነግረኝ ስወተውተው የራሱን ታሪክ ተወት አድርጎ የጎረቤቱን ታሪክ ነገረኝ፡፡ ሳሳጥረው እንዲህ ነው፡፡ አጥር ተጋርቶት የሚኖረው ሰው ጥሩ ነጋዴ ነበር፡፡ ሁለት ልጆች አሉት፡፡ ጦርነቱ ሲጀመር ግን ባንክ አካውንቱ ውስጥ ብር እንጂ በጎተራ የተቀመጠ እህል አልነበረውም፡፡ ሆኖም የተወሰነ ቀን ለነፍስ መያዣ የሚሆነውን ያህል ለልጆቹ ማቅረብ አልተቸገረም፡፡ ቀኑ ሲረዝም ግን አካውንቱ ውስጥ ያለው ብር ሊረባው አልቻለም፡፡ ልጆቹ ተራቡ፡፡ እያያቸው ጠወለጉ፡፡ ሱቅ ወዳላቸው ሰዎች ሁሉ ሄዶ ፓስታና ማካሮኒ ስጡኝ፤ ቀን ሲያልፍ እከፍላለሁ አለ፡፡ የሄደባቸው ቀና ምላሽ አልነበራቸውም፡፡
ከቤት የልጆቹ እረሃብ፣ ከውጪ የነጋዴ ፊት እሳት ሆነበት፡፡ አንድ ሰሞን የባንክ አካውንቱን ይዞ እንደ እብድ አደረገው፡፡ መፍትሄ አልሆነውም፡፡ የነጋዴ ልብ ቢራራ ብሎ፣ ልጆቹን ይዞ በአቅራቢያው ወዳለ ሱቅ ሄደ፡፡ ልጆቹ ሱቅ ሲደርሱ ያዩትን ሁሉ እያነሱ ወዳፋቸው ለማድረግ ታገሉ፡፡ ነጋዴው ልቡ እራራና “ቀን ሲያልፍ ትከፍላለህ፤ ለልጆችህ ነፍስ መያዣ ውሰድ” አለው፡፡
የሁለችንም ፊት በሃዘን ጨፍግጎ ነበር፡፡ በጠላው ለማረሳሳት ሞከርኩ፡፡ አልሆነም፡፡ ታደሰ ሌላ የሰቆቃ ታሪክ ጨመረልን፡፡ በነገራችን ላይ ታደሰ የጦርነቱን መደረግ ይቃወም የነበረ ሰው ነው፡፡ ገና ድሮ ህወሃት ሰንበት ጠብቃ ወታደራዊ ትርኢት እያሳየች፣ የልዩ ሃይሌን ክንድ እዩ ስትል፣ ተው ብለን ነበር ይላል፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረም በኋላ ሸሽቶ ወደ ገጠር ሄዶ ነበር፡፡ መከላከያ ስፍራ ሲይዝ ተመለሰ፡፡ “ስንመለስ ደግሞ የኤርትራ ሰራዊት መቀመጫ አሳጣን” ይላል፡፡ “በየቤታችን እየገባ እናንተ እዚህ ከሆናችሁ ደብረጽዮን ምን ይዛ ነው የምትፎክረው” ይሉ እንደነበርም ነገረኝ፡፡ (ይቺን ነገር ከብዙ ሰው ነው የሰማኋት) ወፈር ያለ ሰው ካገኙም፤ “አሁን አንተ በርሃ ብትወርድ ምን ትሆናለህ?” እያሉ ይሳለቁበት ነበር አሉ፡፡ ከፍ ሲል በየቤቱ እየገቡ ፈላጭ ቆራጭ ሲሆኑ ብዙዎች ተማረዋል፡፡
እንደተረዳሁት የህወሃት አመራሮች ተጠራርገው በርሃ ከወረዱ በኋላ፣ በአጭር ጊዜ ተመልሰው ያንሰራሩት ብዙ ሰው በኤርትራ ሰራዊት ተማርሮ ስለነበር ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ትግሉ የህልውና ሆኖ ነበር፡፡ በጦርነቱ ከመከላከያ ወገን የነበሩ ትግራዋዮችም ከህወሃት ጎን ተሰልፈው ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ በዚህ ቆይታዬ ያወኩት ነገር፣ ህወሃት ከመቀሌ ተነቅላ በርሃ ስትወርድ እሰይ ያሉ ትግራዋዮች ነበሩ፡፡ ከመንግስት ጎን ቆመው ህወሃትን ሲሰልሉም ነበር አሉ፡፡) ህዝቡ ተማሮ ባለበት ጊዜ ተከትሏቸው ወደ በርሃ እንዲወርድ ለማድረግም የህወሃትም ፕሮፓጋንዳ የሚናቅ አልነበረም፡፡
መቀሌን ከተቆጣጠሩ በኋላም ወደ ወሎና ሰሜን ሸዋ ላደረጉት ጉዞ ሃይል ሲያሰባስቡ ህጻናትን አስታጥቀው በከተማ ያንቀሳቅሷቸዋል፡፡ ህጻናቱ “ለትግራይ ነፃነት እሰዋለሁ!” አይነት መፈክር ያሰማሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ወጣቶች “ህጻናቱ እንዲህ ሲሆኑ እኔስ” እያሉ ወደ በርሃ ለመውረድ ነፍጥ ያንጠለጥላሉ፡፡
የአክሱም ቆይታችን አበቃና ታደሰና ዮሃንስን ተሰናበትኩ፡፡ ጉዞ ወደ መቀሌ ሆነ፡፡
ሃጎስ መሪውን ጨብጧል፡፡ ጠላ እንቅልፌን ያመጣዋል ስላለ አልጠጣም እሱ፡፡ ደግሞ እርሃቡ አቅሙን በጣም ጎድቶታልና አልኮል አይቋቋምም፡፡ በገፅታው ወደ ስልሳ ገምቼው ነበር፡፡ ስለ እድሜው ስናወራ 47 እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ቢያንስ 10 ቀንሶ እንደነገረኝ እየገመትኩ ነበር ለራሴ፡፡
“ጦርነቱ አደቀቀኝ እንጂ ገና እኮ ነኝ” አለና እየነዳ ሞባይሉን አወጣ፡፡ ሞባይሉን ሲጎረጉር መኪናው ላይ ችግር ቢፈጠር የሚል ስጋት ስለነበረኝ መሪ ለመደገፍ ተሰናዳሁ፡፡ (ይቺ ልምዴ ሁሌ ስታልፍ ታስቀኛለች) ትንሽ ቆይቶ ሞባይሉን ሰጠኝ፡፡ “ጦርነቱ እንደተጀመረ የተነሳሁት ነው” አለኝ፡፡ እስክሪኑ ላይ ያለውን ፎቶ አየሁት፡፡ አብሮኝ ያለው ሰው ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል፡፡ በፎቶውና አብሮኝ ባለው ሰው መሃል ያለው እርቀት ቢያንስ የአስራአምስት አመት ነው የሚመስለው፡፡ ፎቶው ላይ ደንዳና ወዛም ሰው፤ እዚህ የረገፈ ሽማግሌ፡፡ ባይፈቅድልኝም ፎቶዎቹን ገለጥ እያደረኩ አየሁ፡፡ ተሰብስበው ካርታ ሲጫወቱ፣ ዳማ ሲጫወቱ፣ ቤት ቁጭ ብለው፣ እየጠጡ … ፎቶዎች አየሁ፡፡ ከፎቶዎቹ መሃል ሃጎስን እየፈለኩ አየሁት፡፡ ፎቶዎቹ በተቀያየሩ ቁጥር እየጠወለገ መጥቷል፡፡
ሃጎስ ልጁ ዘምቶበት ነበር፡፡ እንዲዘምት ያደረገው የሃጎስ ወንድም፤ የልጁ ደግሞ አጎት ነው፡፡ ከትግራይ ክልል ከወጡ በኋላም አጎትየው እየደወለ “ወደማይሆን ነገር ነው የገባነው፤ ቢያንስ እሱ ይትረፍ!” እያለ ይወተውተው እነደነበርም ነግሮኛል፡፡ ግን ልጁን አግኝቶ ተመለስ ሊለው አልቻለም፡፡ በወቅቱ ይኑር ይሙት አይታወቅም፡፡ አባት መሃል መቀሌ ላይ አይቶት እንኳ የማያውቀውን በፕላስቲክ ጠርሙስ ታሽጎ የቀረበለትን መጠጥ እየጠጣ፣ ጭንቁን ለማራገፍ ይጥራል፡፡ ልጅ ጥይት የሚረግፍበት በርሃ ውስጥ ነው፡፡
አንድ ቀን አባት እንደወትሮው እኩለሊት አካባቢ ወደ ቤቱ ሲገባ አቅሉን አያውቅም፡፡ መጠን አልፎ ጠጥቷል፡፡ “በር ጋ ስደርስ…” አለኝ፡፡ ደስታው አሁን የሆነ እስኪመስል ድረስ ፊቱ ላይ ብልጭ እያለ፤ “… በር ላይ የልጄን ሻንጣ አየሁት፡፡ ተንደርድሬ ቤት ስገባ ልጄ መጥቶ ከቤተሰብ ተቀላቅሏል፡፡ ብዙ አያወራም፡፡” ይላል ሃጎስ፡፡ ሃጎስ ቤቱ ሲገባ ያገኘው ልጅ ትንሽ ወሰድ አድርጎት እንደነበር ያወቀው ቆይቶ ነው፡፡ ልጅ ውጪ ያስቀመጠውን ሻንጣ አባት ሲያስገባ፣ ልጅ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ ግን ይሄ የመነካቱ ምልክት መሆኑ ለአባት አልገባውም፡፡ በወቅቱ ሸሽቶ የመጣን የትግራይ መከላከያ ሃይል መሸሽግ ስለሚያስቀጣ፣ ሃጎስ ልጁን በሌሊት ወደ ሌላ ቤት ወስዶ ሸሸገ፡፡ “ባንዱ ሲመጡ ወደ ሌላ እየወሰድኩ ልጄን አተረፍኩ፡፡ በህይወት ቢተርፍም አሁንም ትንሽ ያመዋል” አለኝ፡፡ ያመዋል ሲል እጁን ወደ ጭንቅላቱ ወስዶ እንደማላላት ነገር እያደረገ ነው፡፡
“ዝም ነው የሚለው፡፡ ያ ቀልድ ካፉ የማይጠፋ ልጅ ምንም አይናገርም፡፡ ሳቅ ይወድ ነበር በፊት… አሁን ሁሌ ሃዘን ላይ ነው፡፡ ግን እንኳን ህይወቱ ተረፈልኝ” ሃጎሰ ይህንን ሲናገር ፊቱ ላይ የነበረው ሃዘን ይጋባል፡፡
“ስንት አመቱ ነው?” ጠየኩት
“አሁን እኮ ነው ገና በነሃሴ 19 ዓመት የሚሆነው፡፡ የዛን ጊዜ አስራ ስድስት አመቱ ነበር…” አለኝ፡፡
ዝም አልኩ፡፡ የምናገረው ነገር ሃዘኑን ከመቀስቀስ የዘለለ ፋይዳ ያለው አልመሰለኝም፡፡ እሱ ግን ቀጠለ፤ “ምንም እኮ አያውቅም ነበር፡፡ ገና መጎርመሱ ነው፡፡ እስፖርት ይሰራ ነበር፡፡ ጡንቻው እንደዚህ ነው (መሪውን እንደጨበጠ ሁለት እጁን እንደማጠንከር ነገር እያደረገ)፤ ሽቶውን ተቀባብቶ ይወጣል በቃ…”
ልጁ ስለ ጦርነቱ ምን እንደሚያስብ አባትን ጠየኩት፡፡ በፍፁም ማውራት እንደማይፈልግ፣ ጉዳዩ ሲነሳበትም እንደሚረበሽ ነገረኝ፡፡ እነሱም ፀሎታቸው ሰምሮ በህይወት ተርፎ የመጣ ልጃቸው እንዳይረበሽ እያሉ አያነሱበትም፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ለህወሃት አመራሮች ከፍተኛ ጥላቻ እንዳደረበት መናገሩን ጠቆመኝ፡፡ ሃጎስ ደጋግሞ አንድ ነገር ይላል፡፡ “ያላወቁ አለቁ” ጦርነቱ ሲጀመር ፍጻሜው እንዲህ እንደሚሆን አውቅ ነበር ባይ ነው፡፡ ህወሃት የፈለገችውን ብትልም፣ መንግስት መንግስት ነው ባይ ነው እሱ፡፡ ደሞ አይወዳቸውም፤ ህውሃቶቹን፡፡ “ያላቅማቸው…” ማለት ያበዛል፡፡
የሃጎስና የልጁ ለህወሃት ያላቸውን ጥላቻ ስሰማ አክሱም ያገኘሁት አንድ አርሶ አደር ትዝ አለኝ፡፡ ለእሱ ሰማዩም ምድሩም ህወሃት ናት፡፡ በጣም ነው የሚወዳቸው፡፡ ዘምቶ በነበረበት ጊዜ የለበሳትን ሬንጀር ሸሚዝ አሁንም እንደለበሳት ናት፡፡ ስለነሱ ሲያወራ ውሎ ቢያድር አይጠግብም፡፡ ለኛ ብለው እንጂ መች ለነሱ ሆነና ይላል ደጋግሞ፡፡ ቆራጥ ናቸው፤ ምሁር ናቸው፤ ጀግኖች ናቸው እያለ ገድላቸውን ያወራኛል፡፡ ማሳ ላይ ቆመን ነበርና የምናወራው፣ የሚለኝን የሰማ ሌላ የመንደሩ ነዋሪ መጥቶ፣ ተቃውሞውን አሰማ፡፡
ይሄኛ ደግሞ ከፍ ያለ ጥላቻ ነው ያለበት፡፡ ለራሳቸው ሲሉ ህዝቡን አስጨረሱት ባይ ነው፡፡ በክርክራቸው ትንሽ እንደቆዩ ከእኔ ሚስጢር ለመደበቅ በሚመስል መልኩ ቋንቋ ቀየሩ፡፡ በመንገዳችን አልፎ እልፎ የድሮን ወይንም የሌላ ከባድ መሳሪያ ሰለባ የሆኑ ትልልቅ ተሽከርካሪዎች እርር እንዳሉ አሉ፡፡ አልፎ አልፎ የተገነጣጠሉ፣ በከፊል የተቃጠሉ ቤቶች ይታያሉ፡፡
መቀሌ ደረስን፡፡ ፀሃይ በርዳ ስለነበር ብዙም ሳናርፍ ዙረት ወጣሁ፡፡ “መቀሌ ከጦርነቱ በኋላ የሆነችው ምንድን ነው?” በዙረቴ ማየት የፈለኩት ነገር ነው፡፡ ሃጎስ ጠዋት እንዲመጣ ነግሬው ወደ ቤቱ ሄዷል፡፡ ብዙም ሳልቆይ ተመልሼ ወደ ሆቴል ገባሁ፡፡ ምግብ ፍለጋ እንደገና ወጣን፡፡ ላንድ ማርክ የተባለ ቤት አገኘንና በረንዳ ላይ ተቀመጥን፡፡ የስራ ባልደረባዬም አለ። አስተናጋጇ አጠገቤ ተቀምጣ፣ እሷ በትግርኛ እኔ በአማርኛ እያወራን ነው። የእሷ አማርኛ መሞከር ተግባቦታችንን አቅልሎታል። ስለ አካባቢው እያወራን ነበር። ድንገት ጩኸት ሰማን። ክው ብላ ደነገጠችና በትግርኛ የሆነ ነገር አለች።
ስትረጋጋ ጠብቄ፤ “ኢትዮጵያዊ አይደለሽ እንዴ? ለምን ፈራሽ አልኳት?”
በትግርኛ መለሰችልኝ፡፡ በትግርኛ ካወራችው ውስጥ ጦርነት የሚለውን ሰምቻለሁ። በእጇ ጭንቅላቷ አካባቢ እንደማላላት ያደረገችውም ገብቶኛል። የገባኝ ምንድን ነው… መብራትን ጦርነቱ አስጨንቋታል። ጦርነቱ ካለቀ ቢቆይም ከውስጧ አልወጣም። ዛሬም ስጋት ላይ ናት። ከላንድ ማርክ ወጣሁና አልጋ ወደያዝኩበት ሆቴል ገባሁ፡፡ መተኛት፣ ማንበብ፣ ፊልም ማየት… ሁሉን ሞክሬ አልተሳካልኝም፡፡ የሰማኋቸው ሁሉ እያቃጨሉብኝ ነው፡፡ የሰቆቃ ድምፅ፣ ባታች ሰው፣ ስጉ ሰው፣ ተጠራጣሪ ሰው፣ ያለፈው ጦርነት ከውስጡ ያላለፈ ትግራዋይ፣ አልፎ አልፎ በየመንገዱ የተቃጠሉ ተሽከርካሪዎች…
ቢራ አማረኝ… ወጣሁ!
ጠዋት ለመጣሁበት ስራ ወደ ውቅሮ መሄድ ነበረብኝና፣ ሃጎስን ከቤቱ እስኪመጣ ጠብቄ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ውቅሮን አንድ ሁለቴ ለስራ ጉዳይ ሄጄባት ነበር፡፡ ስለከተማዋ ያለኝን ትውስታ ስበረብር ምንም ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ ውቅሮን የማስታውሳት የሆነ ጊዜ በአፋር ክልል ክልበቲ ረሱ ዞን ዋና ከተማ አብአላ ላይ፣ ከ52 በላይ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች እንሰራለን ያሉ ባለሃብቶች፣ ከክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ከቀረጥ ነፃ ፈቃድ አፅፈው ብረት እያስገቡ፣ ብረቱን ለሌላ መሸጣቸው ተሰማ፡፡ ያቺ የበሬ ግንባር የምታክል ከተማ ሃምሳ ሁለት ሆቴልና ሞቴል ሊያውም በባለ ኮከብ ደረጃ ምን ሊያደርግላት ፈቃድ ሰጠች? ባለሃብቶቹስ ምን ያህል ሰው ቢንቁ ነው፣ ግልጽ ማጭበርበር የሚፈፅሙት? እያልን ስንብሰለሰል ቆየን፡፡ በዚህ መሃል እኔ ለስራ ወደ አብኣላ ሄድኩ፡፡ በዛን ጊዜ መዘጋጃ ቤት ገብቼ የግንባታ እቅዱን የያዘውን ሰነድ የማየት እድል አገኘሁ፡፡ እነ ስዩም ተሾመ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል እያሉ በፌስቡክ ያዳነቁት፣ ባለሁለት ኮከብ ሆቴሎች ሆነው አገኘኋቸው፡፡ (በርግጥ ለከተማዋ ባለሁለት ኮከብ ሆቴልም በዛን ያህል ቁጥር በጣም ይበዛባታል፡፡) እኔ ሰነዶቹን ስመለከት አብዛኛዎቹ ኢንቨስተሮች ከውቅሮ የሄዱ መሆናቸውን አይቻለሁ፡፡ ውቅሮ ሲባል ትዝ የሚለኝ ይሄ ነበር፡፡
ውቅሮ ስደርስ ሰዎች እየጠበቁኝ ነበር፡፡ ለእለቱ የያዝነውን ስራ አስቀድመን በስልክ አውርተን ስለነበር ስራ ጀመርን፡፡ አብሮኝ አንድ የአካባቢው መካከለኛ አመራር አለ። ክላሽ ይዞ አልዘመተም እንጂ አዲግራት ስትከበብ የወገን ላለው ጦር ምግብና ውሀ አቀብሏል። ላለመዝመቱም የሚሰጠው ምክንያት “ሸክም ላለመሆን” የሚል ነበር። “እዛ ስንት ነገር አለ... ሁላችን ብንሄድስ መሳሪያ እናገኛለን? እንጂ ለትግራይ ህዝብ እንኳን ጦር ሜዳ ሲኦልስ ብንገባለት!” አለኝ፡፡ ደም ግፊት አለበት፡፡ ይሄ በዋናነት ከመዝመት አገደኝ የሚለው ነው፡፡ ለሱም ለልጆቹም የሚያበላቸው አጥቶ ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ባለውለታዬ የሚለውን አንድ ወዳጁን አስቸግሮ መቀሌ ድረስ ሄዶ 25 ኪሎ ስንዴ እንዳገኘና የልጆቹን እረሃብ እንዳስታገሰ ሲነግረኝ እንባ አይኑ ላይ አቅርሮ ነበር፡፡ ስለ ዘማቾችና ስለ ዘማቾች ቤተሰብ በደንብ አወራኝ፡፡ ልጆቻቸው የሞቱባቸው የቆሰሉባቸው ብዙ ናቸው፡፡ አሁንም ድረስ ቢሯቸው እንዳልተሟላ ነገረኝ፡፡
“እንዴት?” ጠየኩት፡፡
“በርሃ ከወረዱት ሰራተኞች መካከል ብዙዎቹ ዛሬም አልተመለሱም እኮ፤ አሁንም ካምፕ ናቸው፡፡ ሰራዊቱ በዙር ሲበተን የመጀመሪያ ዙር ብቻ እኮ ነው የተመለሰው”
ይቺ ነገር ትንሽ አሰጋችኝና እንዲያወራኝ ፈለግሁ፡፡ ፍላጎቴን አወቀ መሰለኝ ወሬ ቋጠረ፡፡
“ጦርነቱ እንደገና የሚነሳ ይመስልሃል?” ጠየኩት
“ተው! ከዚህ በኋላ ትግራይ ላይ ጦርነት ከተነሳ ይሄ የምታየው ቅጠል እንኳ አይተርፍም” አለኝ ወደሆነ ዛፍ እየጠቆመኝ፡፡ የቆምንበት ቦታ ሰፊ የእርሻ ቦታ ነው፡፡
“ድንገት ቢነሳስ?”
“ትግራይ ጦርነት በቃት… ማንስ ይዋጋል ብለህ ነው!”
“ጦሩ መች ሙሉ ለሙሉ ተበተነ!” ቅድም ያለኝን እያስታወስኩት እንደሆነ ገብቶታል፡፡ መልሱ ላይ ተቆጠበብኝ፡፡
“ህዝቡ ጦርነት መሮታል፡፡ አያቶቻችንም እኛም ጦርነት ብቻ ነው ታሪካችን፡፡ እስከ መቼ? ጦርነት በቃን” አለኝ፡፡
“ፖለቲከኞቹ የበቃቸው ይመስልሃል?”
“እንጃ!”
ከውቅሮ ወጣ ብለን ስለነበር ወደ ከተማዋ ተመለስን፡፡ ሀጎስ የሚያቅበዘብዝ እረሃብ ላይ ነበርና ፋታም ሳይሰጠን ምግብ ቤት ገባን፡፡ ያዘዘው እስኪደርስ እንጀራ በበርበሬ አስመጥቶ ተያያዘው፡፡ ትንሽ እንደበላ በቃኝ አለን፡፡ ሲበላ በጣም አልቦት ነበር፡፡ በዋናነት ያዘዝነው ምግብ ሲመጣ አንድ ሁለቴ ጎርሶ በቃኝ አለና ተነሳ፡፡ ወደ መቀሌ ተመለስን፡፡ መቀሌን በደንብ ዞርኳት፡፡ በጣም አልፎ አልፎ ቁስለኞች አሉ፡፡ ከሁሉም ከተሞች ቁስለኞች ተሰብስበው ካምፕ እንደገቡ ሰምቻለሁ፡፡ መቀሌን በምሽት መዞሩ ብዙ አስተማማኝ እንዳልሆነ ተነግሮኛል፡፡ ዘራፊዎች በዝተዋል፡፡ እንደውም አሁን ቀንሶ እንጂ በቀን ሳይቀር ዘረፋ በዝቶ እንደነበር ሰማሁ፡፡ በሌት ሳይቀር የዞርኩባት ከተማ ናት፤ ያኔ በሰላሙ ጊዜ፡፡ እና ከፋኝ፡፡ ከፍቶኝ ተሰበሰብኩ፡፡
እንቅልፍ እንቢ አለኝ፡፡ ካረፍኩበት ሆቴል ፊት ለፊት የሙዚቃ ድምጽ ሲሰማኝ ወጣሁ፡፡ ሞቅ ያለ ሙዚቃ አለ፡፡ ቢራም በላይ በላይ እየተጠጣ ነው፡፡ ተቀላቀልኩ፡፡ ሲነጋ የተለየ ስራ አልነበረኝም፡፡ የመቀሌ ወዳጆቼን እያገኘሁ የተላኩትን እያደረስኩ ቆየሁ፡፡ ወደ አዲስ አበባም ስለምመለስ ቶሎ ወደ አየር ማረፊያ ሄድኩ፡፡ ከኔ ጋር ሲንከራተት ለነበረው ሃጎስ እረፍት ለመስጠትም ነው፡፡
ሰአታችን ደርሶ ወደ አውሮፕላኑ ለመግባት ሰልፍ ሲጀመር ወደ ኋላ ቀረሁ፡፡ ሁሉም ሲገቡ ተነሳሁና ስሄድ ከሁሉም ወደ ኋላ የቀረ አንድ ሰው አየሁ፡፡ ክፉኛ ያነክሳል፡፡ ሃምሳን ያልፋል እድሜው፡፡ ቀስ ብሎ ስለሚሄድ ሁሉም ቀድመውት እኔ ብቻ ነኝ ከኋላው የቀረሁት፡፡ ባለው አቅም ሁሉ ከቀደሙት ለመድረስ እየጣረ እንደሆነ አረማመዱ ያስታውቃል፡፡ በፍፁም ልቀድመው አልፈለኩም፡፡ ጠጋ አልኩና የያዘውን ሻንጣ ተቀበልኩት፡፡ በትግርኛ አወራኝ፡፡ ዝም አልኩት፡፡ እንዳልገባኝ ሲያውቅ በአማርኛ ቀጠለ፡፡ “የቆሰልንላቸው ቅድሚያ እንኳ አልሰጡንም… ለህዝብ የቆሰልነው ወደ ኋላ እንዳስቀረን እንኳ አላወቁም” ጥሩ ለብሷል፡፡ ፊቱ ላይ ግን ብሶት አለ፡፡ ጥልቅ ብሶት፡፡ ወደ አውሮፕላኑ ሆድ አብረን ገባን፡፡
በትግራይ ምድር ከሽረ አክሱም፣ ከአክሱም መቀሌ፣ ከመቀሌ ውቅሮ ተመላልሻለሁ፡፡ አንድ ቦታ የኢትዮጵያ ባንዲራ ተሰቅሎ አላየሁም፡፡ ትግራይ የኢትዮጵያን ባንዲራ እንዳወረደች ናት፡፡ ሰንደቁ ባዶውን ሆኗል፡፡ ምናልባት መቀሌ ላይ አሁን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ያለው፣ እዚህ አውሮፕላን ላይ ብቻ ይመስለኛል፡፡
ወደ አዲስ አበባ ስመለስ እያሰብኩ ነበር፡፡ ይሄ ጦርነት ወሎ፣ አፋር፣ ሰሜን ሸዋ፣ ጎንደር… የፈጠረው ቀውስስ ምን ድረስ ይሆን? ስብራቱንስ ምን ይጠግነዋል? ኢትዮጵያስ መቼ ይሆን ከእርስ በርስ ጦርነት የምትላቀቀው?
Saturday, 20 July 2024 21:05
ትግራይ ከጦርነቱ በኋላ---
Written by በንጉሱ ይበልጣል
Published in
ነፃ አስተያየት